በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሃይማኖት ለዓለም ሰላም ያመጣ ይሆን?

ሃይማኖት ለዓለም ሰላም ያመጣ ይሆን?

ሃይማኖት ለዓለም ሰላም ያመጣ ይሆን?

ከነሐሴ 28 እስከ ነሐሴ 31, 2000 ድረስ ከ73 አገሮች የተውጣጡ ከ500 በላይ ልዑካን ወደ ኒው ዮርክ ከተማ ጎርፈዋል። የተሰበሰቡት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሚካሄደው “የሃይማኖታዊና መንፈሳዊ መሪዎች የሺህ ዓመቱ የሰላም ጉባኤ” ነበር። መሪዎቹ ጥምጣም ያደረጉ፣ ብርቱካንማ ካባዎችን ያጠለቁ፣ ከላባ የተሠራ ጎፈር ራሳቸው ላይ ያደረጉ ወይም ጥቁር መደረቢያ የተጎናጸፉና ከተለያዩ እምነቶች የተውጣጡ ናቸው። ከእነዚህም መካከል የባሃይ፣ የቡድሃ፣ የሂንዱ፣ የእስልምና፣ የአይሁድ፣ የሺንቶ፣ የሲክ፣ የታኦ፣ የዞራስተር እምነት እንዲሁም የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ይገኙበታል።

ልዑካኑ የአራቱን ቀን ጉባኤ የመጀመሪያ ሁለት ቀናት ስብሰባ ያካሄዱት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነበር። ስብሰባውን ያዘጋጁትም ሆነ ወጪዎቹን ለመሸፈን የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉት ግን የተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች እንጂ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አልነበረም። ያም ሆነ ይህ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ የሃይማኖት መሪዎቹ ድህነትን፣ የዘር መድሎን፣ አካባቢያዊ ችግሮችን፣ ጦርነትን እንዲሁም ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን በተመለከተ መፍትሔ ለማምጣት በጋራ ተባብረው መሥራታቸው ስላለው ጠቀሜታ ተናግረዋል።

ልዑካኑ “የዓለም ሰላም ቃል ኪዳን” የተሰኘ ሰነድ ፈርመዋል። “በሃይማኖት ስም” ዓመፅና ጦርነት የሚካሄዱባቸው “ጊዜያት እንዳሉ” አምነው ከመቀበላቸውም በላይ የሰነዱ ፈራሚዎች “ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት . . . ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር እንደሚተባበሩ” በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል። ይሁን እንጂ የዚህን ጉዳይ አፈጻጸም በተመለከተ በግልጽ የሰፈረ ስምምነት የለም።

በሁለተኛው ቀን የጉባኤው ዋና ጸሐፊ የሆኑት ባው ጄን የመክፈቻ ንግግራቸውን የቋጩት ከጥቂት ዓመታት በፊት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ስላዩት አንድ ሥዕል በመግለጽ ነበር። በሥዕሉ ላይ የሚታየው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት ሕንጻ የሚበልጥ ቁመት ያለው ሰው ነው። ሰውየው ሕንጻውን ልክ እንደ በር ሲያንኳኳው ይታያል። ከሥዕሉ በታች ያለው መግለጫ ደግሞ “የሰላም መስፍን” ይላል። ከዚያም ሚስተር ጄን እንዲህ በማለት ቀጠሉ:- “[ሥዕሉን] ሳየው በጣም ተነካሁ። ምን ትርጉም እንዳለው ለማወቅ የተለያዩ ሰዎችን ጠይቄ ነበር። ዛሬ መልሱን ያገኘሁት ይመስለኛል። የዓለም መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ መሪዎች የሆናችሁት ሰዎች ዛሬ እዚህ አንድ ላይ መሰባሰባችሁ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በር የሚያንኳኳው የሰላም መስፍን እናንተ መሆናችሁን አረጋግጦልኛል።”

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ግን የተለየ ነው። የሰላሙ መስፍን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ይገልጻል። በምድር ዙሪያ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል። ይሁን እንጂ ይህንን የሚያደርገው በዓለም የፖለቲካ ወይም የሃይማኖት መሪዎች በመጠቀም ሳይሆን በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ነው። ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን በተሳካ መንገድ በአንድነት የሚያስተሳስረውና የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲሆን የሚያደርገው ይህ መንግሥት ማለትም የአምላክ ሰማያዊ መስተዳድር ነው።​—⁠ኢሳይያስ 9:​6 NW ፤ ማቴዎስ 6:​9, 10