በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ ክርስትና ድል ያደርጋል!

እውነተኛ ክርስትና ድል ያደርጋል!

እውነተኛ ክርስትና ድል ያደርጋል!

“የጌታ ቃል በኃይል ያድግና ያሸንፍ ነበር።”​—⁠ሥራ 19:​20

 በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተነሳሱት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የአምላክን ቃል ሊዳፈን በማይችል ቅንዓት አውጀዋል። አንድ ታሪክ ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል:- “ክርስትና በሮማውያኑ ዓለም በሚያስገርም ፍጥነት ተሰራጭቷል። በ100 [እዘአ] ሜዲትራንያንን በሚያዋስነው በእያንዳንዱ አውራጃ የክርስቲያኖች ማኅበረሰብ ተቋቁሞ ነበር።”

2 ሰይጣን ዲያብሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች ዝም ሊያሰኛቸው አልቻለም። ከዚህ የተነሳ የምሥራቹን ግስጋሴ ለማስተጓጎል ክህደትን እንደ መሣሪያ ተጠቅሞበታል። ኢየሱስ ስለ ስንዴና ስለ እንክርዳድ በተናገረው ምሳሌ ላይ ይህ ሁኔታ እንደሚከሰት አስቀድሞ ተንብዮአል። (ማቴዎስ 13:​24-30, 36-43) ሐዋርያው ጴጥሮስም ሐሰተኛ አስተማሪዎች በጉባኤው ውስጥ እንደሚነሱና የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው እንደሚያስገቡ አስጠንቅቋል። (2 ጴጥሮስ 2:​1-3) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ የይሖዋ ቀን ከመምጣቱ በፊት ክህደት ብቅ እንደሚል በግልጽ አስጠንቅቋል።​—⁠2 ተሰሎንቄ 2:​1-3

3 ሐዋርያት ሞተው ካለቁ በኋላ ምሥራቹ በአረማዊ ትምህርቶችና ፍልስፍናዎች ተዋጠ። በትንቢት እንደተነገረው ሐሰተኛ አስተማሪዎች ንጹሑን የእውነት መልእክት አጣምመውትና በርዘውት ነበር። ቀስ በቀስ እውነተኛው ክርስትና ሕዝበ ክርስትና በመባል በሚታወቅ አስመሳይ ክርስትና ተዋጠ። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ በተራው ሕዝብ እጅ እንዳይገባ የሚከላከል የቀሳውስት ክፍል ተነሳ። ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው የሚጠሩት ሰዎች በቁጥር እየተበራከቱ ቢሄዱም አምልኳቸው ንጹሕ አልነበረም። ሕዝበ ክርስትና በተለያዩ የምድር ክፍሎች በመስፋፋት በምዕራቡ ዓለም ብርቱ ኃያል ለመሆን በቅታለች። ሆኖም የአምላክ መንፈስም ሆነ በረከት አልነበራትም።

4 ይሁን እንጂ ሰይጣን የይሖዋን ዓላማ ለማክሸፍ የጠነሰሰው ሴራ ሁሉ መና ሆኖ ቀርቷል። ክህደቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ዘመን እንኳ ሳይቀር እውነተኛ ክርስትና በአንዳንዶች ዘንድ ሕያው ሆኖ ቀጥሏል። መጽሐፍ ቅዱስን ይገለብጡ የነበሩ ሰዎች ሥራቸውን በትክክል ለማከናወን ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገዋል። ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥልጣን ተሰጥቶናል ብለው የሚናገሩ ሰዎች መልእክቱን አዛብተው ቢያቀርቡም መጽሐፍ ቅዱስ ሳይበረዝ እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቆ ቆይቷል። ባለፉት መቶ ዘመናት እንደ ጄሮም እና ቲንደል ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የአምላክን ቃል በድፍረት ተርጉመው አሰራጭተዋል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም ከእውነተኛውም ባይሆን ከአስመሳዩ ክርስትና ጋር ለመተዋወቅ በቅተዋል።

5 በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ እንደተተነበየው ከጊዜ በኋላ ‘እውነተኛ እውቀት እየበዛ’ መጣ። ይህም የሆነው ‘በፍጻሜው ዘመን’ ማለትም አሁን እኛ በምንኖርበት ዘመን ነው። (ዳንኤል 12:​4) መንፈስ ቅዱስ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ እውነትን የሚወድዱ ሰዎች ስለ እውነተኛው አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ረድቷቸዋል። ለብዙ መቶ ዘመናት የዘለቀ የክህደት ትምህርት ቢኖርም የአምላክ ቃል ድል ማድረጉን ቀጥሏል! ዛሬ ምሥራቹ በሁሉም የምድር ክፍል እየታወጀና ሰዎችን አስደሳች ወደሆነው የአዲስ ዓለም ተስፋ እየመራቸው ነው። (መዝሙር 37:​11) እስቲ የአምላክ ቃል በዚህ ዘመን ያደረገውን እድገት እንመርምር።

የአምላክ ቃል ዛሬ ያደረገው እድገት

6 በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች በመባል የሚታወቁትን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አነስተኛ ቡድን ለሥራ አንቀሳቅሷል። በ1914 መጽሐፍ ቅዱስ ለእነርሱ ሕያው ሆኖላቸው ነበር። የአምላክን ዓላማ በተመለከተ ድንቅ የሆኑ እውነቶችን ተረዱ። ይሖዋ የዘላለም ሕይወት የሚገኝበትን በር ለመክፈት ልጁን ወደ ምድር በመላክ ያሳየው ፍቅር በጥልቅ ነክቷቸዋል። የአምላክን ስምና ባሕርያት ለማወቅ በቅተዋል። ከዚህም በላይ ‘የአሕዛብ ዘመን’ እንዳበቃና ይህም የአምላክ መንግሥት መስተዳደር ለሰው ዘር በረከት የሚያመጣበት ጊዜ መቅረቡን እንደሚያመለክት ተገንዝበዋል። (ሉቃስ 21:​24) ይህ እንዴት ታላቅ ምሥራች ነው! እነዚህ ታላላቅ እውነቶች በየስፍራው ላለ ሰው ሁሉ መዳረስ ነበረባቸው። የሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል!

7 ይሖዋ እነዚያን እፍኝ የማይሞሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ባርኳቸዋል። ዛሬ እውነተኛውን ክርስትና የተበቀሉት ሰዎች ቁጥር ከስድስት ሚልዮን በልጧል። የአምላክ ቃል ወደተለያዩ የምድር ክፍሎች የተሰራጨ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች በ235 አገሮች ይገኛሉ። ከዚህም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሃይማኖታዊም ሆኑ ሌሎች እንቅፋቶችን በድል አድራጊነት ተወጥቷል። ይህ በዓለም ዙሪያ እየተካሄደ ያለው የስብከት እንቅስቃሴ ኢየሱስ በመንግሥቱ ሥልጣን ላይ መገኘቱን የሚያረጋግጥ የማይታበል ማስረጃ ነው።​—⁠ማቴዎስ 24:​3, 14

8 ታሪክ ጸሐፊዎች ክርስትና በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስላደረገው አስገራሚ እድገት እንደጻፉ ሁሉ ዛሬም በርካታ ምሁራን የይሖዋ ሕዝቦች በዚህ ዘመን ስላገኙት እድገት ዘግበዋል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ሁለት ምሁራን በአንድነት እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ባለፉት 75 ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች እጅግ አስገራሚ በሆነ ፍጥነት እድገት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን . . . ይህ እድገት ዓለም አቀፋዊ ባሕርይ ያለው ነው።” አንድ የምሥራቅ አፍሪካ ጋዜጣ “በዓለም በከፍተኛ ፍጥነት እያደገና ከፍተኛ አክብሮት እያተረፈ ያለ እንዲሁም በምድር ዙሪያ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር ሙሉ በሙሉ ተስማምቶ በመኖር የሚታወቅ ሃይማኖት” በማለት ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ተናግሯል። እንዲሁም በአውሮፓ የሚታተም አንድ ወግ አጥባቂ የካቶሊክ ጋዜጣ “የይሖዋ ምሥክሮች ስላደረጉት አስገራሚ እድገት” ጽፏል። ለዚህ እድገት አስተዋጽዖ ያደረገው ምንድን ነው?

መንፈስ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ የሚያከናውነው ሥራ

9 በዛሬው ጊዜ የአምላክ ቃል ድል እንዲያደርግ ካስቻሉት ምክንያቶች መካከል በአንደኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የይሖዋ መንፈስ ሲሆን ልክ እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ ዛሬም መንፈሱ በስፋት እየሠራ ነው። ኢየሱስ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 6:​44) እነዚህ ቃላት አምላክ ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ልባቸው እንዲነካ በማድረግ ወደ እርሱ እንደሚስባቸው ያመለክታል። የእርሱ ምሥክሮች በሚያከናውኑት የስብከት እንቅስቃሴ አማካኝነት ‘በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠውን ዕቃ’ ማለትም በምድር ላይ የሚገኙትን ቅንና በግ መሰል ሰዎች ወደ እርሱ አምልኮ እየሰበሰበ ነው።​—⁠ሐጌ 2:​6, 7

10 መንፈስ ቅዱስ የአምላክ ሕዝቦች የአምላክን ቃል እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንዲያደርሱ ኃይል መስጠት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዓይነት ሰዎች ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡም ይገፋፋቸዋል። በእርግጥም የአምላክን ቃል የተቀበሉት ሰዎች “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም” የተውጣጡ ናቸው። (ራእይ 5:​9፤ 7:​9, 10) በመካከላቸው ሃብታምም ደሃም የተማሩም ያልተማሩም ሰዎች ይገኙበታል። አንዳንዶቹ ቃሉን የተቀበሉት ጦርነትና ከባድ ስደት ባለበት ወቅት ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ሰላምና ብልጽግና በሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው ነው። በሁሉም ዓይነት መስተዳድርና ባሕል ሥር የሚገኙ ሰዎች፣ ከማጎሪያ ካምፕ አንስቶ በቤተ መንግሥት እስካሉ ሰዎች ድረስ የተለያዩ ወንዶችና ሴቶች ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል።

11 የአምላክ ሕዝቦች እንዲህ ዓይነት የተለያየ ሁኔታ ያላቸው ቢሆኑም እርስ በርሳቸው ስምም ሆነው በአንድነት ይኖራሉ። (መዝሙር 133:​1-3) ይህም መንፈስ ቅዱስ አምላክን በሚያገለግሉ ሰዎች ሕይወት ውስጥ እየሠራ እንዳለ የሚያሳይ ሌላ ማረጋገጫ ነው። የአምላክ መንፈስ በጎ ተጽዕኖ የማሳደር ኃይል ያለው በመሆኑ አገልጋዮቹ ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ደግነትንና ሌሎች ማራኪ ባሕርያትን እንዲያፈሩ ያደርጋል። (ገላትያ 5:​22, 23) ነቢዩ ሚልክያስ ከረጅም ጊዜ በፊት የተናገራቸው ቃላት ዛሬ ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ በግልጽ እያየን ነው። “ተመልሳችሁም በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል፣ ለእግዚአብሔር በሚገዛውና በማይገዛው መካከል ትለያላችሁ።”​—⁠ሚልክያስ 3:​18

የአምላክ ቃል ቀናተኛ በሆኑ ሠራተኞች አማካኝነት ድል ያደርጋል

12 በዛሬ ጊዜ የሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦች ምንም ተሳትፎ የሌላቸው ቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች አይደሉም። በወንጌላዊነቱ ሥራ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ። እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የአምላክን ፈቃድ ለማድረግና የይሖዋን መንግሥት ተስፋዎች ለሌሎች ለማሳወቅ ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀርባሉ። ከአምላክ ጋር አብረው የሚሠሩ እንደመሆናቸው መጠን ከአምላክ ቅዱስ መንፈስ ጋር በሚስማማ መንገድ ይሖዋን የሚያገለግሉ ሰዎችን ይሰበስባሉ። ይህንን በማድረግ እነርሱም ይሖዋ ለማያምኑ የሰው ዘሮች የሚያሳየውን ምሕረትና ፍቅር ያንጸባርቃሉ። ግዴለሽነት፣ ፌዝና ስደት ቢደርስባቸውም እንኳ ይህን ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። ኢየሱስ ሰዎች ለምሥራቹ ለሚሰጡት የተለያየ ዓይነት ምላሽ ደቀ መዛሙርቱን አዘጋጅቷቸዋል። እንዲህ አለ:- “ባርያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ።”​—⁠ዮሐንስ 15:​20

13 በዛሬው ጊዜ በሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮችና በመጀመሪያው መቶ ዘመን እውነተኛውን ክርስትና ይዘው በነበሩት ሰዎች መካከል ባለው ተመሳሳይነት መገረማችን አይቀርም። በይሖዋ ምሥክሮችና በዛሬዋ ሕዝበ ክርስትና መካከል ያለው ልዩነትም ከዚያ ባልተለየ መልኩ የሚያስደንቅ ነው። አንድ ምሁር የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ለወንጌላዊነቱ ያሳዩ ስለነበረው ቅንዓት ከጻፉ በኋላ እንዲህ በማለት የተሰማቸውን ምሬት ገልጸዋል:- “በአሁኑ ጊዜ ባለው የቤተ ክርስቲያኑ አሠራር ላይ ለውጥ ተካሂዶ የወንጌላዊነት ሥራ እንደገና የእያንዳንዱ የተጠመቀ ክርስቲያን ኃላፊነት እንዲሆን እስካልተደረገና የማያምኑት ሰዎች በሚያስንቅ አኗኗር እስካልታገዘ ድረስ ወደፊት እድገት እናገኛለን ብሎ ማሰብ ዘበት ነው።” ሕዝበ ክርስትና ልትደርስባቸው ያልቻለቻቸው ነገሮች በይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ በሰፊው ይታያሉ! የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው እምነት ሕያው፣ እውነተኛና በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ሊያዳምጣቸው ፈቃደኛ ለሆነ ሁሉ ይህንን እውነት የማካፈል ግዴታ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 2:​3, 4

14 ኢየሱስ አገልገሎቱን በቁም ነገር ይመለከት ስለነበረ በዋነኛነት ያሳስበው የነበረውም ይኸው አገልግሎቱ ነበር። ለጲላጦስ “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ” በማለት ነግሮታል። (ዮሐንስ 18:​37) የአምላክ ሕዝቦችም ይህንኑ የኢየሱስ ስሜት ያንጸባርቃሉ። በልባቸው ውስጥ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የተቻላቸውን ያህል ለብዙ ሰዎች ለማካፈል የሚያስችል ዘዴ ለመጠቀም ይጥራሉ። ከእነዚህ ዘዴዎች መካከል አንዳንዶቹ በሚያስገርም መንገድ ብልሃት የተንጸባረቀባቸው ነበሩ።

15 በደቡብ አሜሪካ በምትገኝ አንዲት አገር የሚኖሩ ምሥክሮች እውነትን ለሰዎች ለማድረስ የአማዞን ገባር በሆነ ወንዝ በኩል ይሄዱ ነበር። ይሁን እንጂ በ1995 የእርስ በርስ ጦርነት ተነስቶ በነበረበት ጊዜ በወንዙ መተላለፍ ተከለከለ። ምሥክሮቹ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን ማግኘታቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ ቆርጠው ስለነበር መልእክቱን በወንዙ እያንሳፈፉ ለመላክ ወሰኑ። ደብዳቤዎች ከጻፉ በኋላ ከመጠበቂያ ግንብ እና ከንቁ! መጽሔቶች ጋር አድርገው በባዶ ፕላስቲክ ጠርሙሶች ውስጥ ከተቷቸው። ከዚያም ጠርሙሶቹን ወደ ወንዙ ወረወሯቸው። ወንዙ እንደገና ሰላማውያን ለሆኑ ሰዎች ዝውውር ክፍት እስከሆነበት ጊዜ ድረስ ይህ ሁኔታ ለአራት ዓመት ተኩል ቀጥሏል። በወንዙ ዳርና ዳር የሚኖሩ ሰዎች ጽሑፎቹን በማግኘታቸው ምሥክሮቹን አመስግነዋቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስን ታጠና የነበረች አንዲት ሴት እቅፍ አድርጋቸው እያለቀሰች እንዲህ አለች:- “እንደገና አገኛችኋለሁ ብዬ ፈጽሞ አላሰብኩም ነበር። ጽሑፎች የያዙ ጠርሙሶች ማግኘት ስጀምር ግን እንዳልረሳችሁኝ ወዲያው ገባኝ!” በወንዙ ዳርቻ የሚኖሩ ሌሎች ሰዎችም መጽሔቶቹን ደጋግመው እንዳነበቡ ተናግረዋል። በርካታ መንደሮች ወንዙ አንሳፍፎ ያመጣቸው ነገሮች ለጊዜው የሚጠራቀሙባቸው ልክ እንደ “ፖስታ ቤት” የሚያገለግሉ ቦታዎች ነበሯቸው። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ከውኃው መነሻ “ፖስታ” መጥቶላቸው እንደሆነና እንዳልሆነ የሚያረጋግጡት ወደነዚህ ቦታዎች በመሄድ ነበር።

16 የምሥራቹ ስብከት የይሖዋና የኃያላን መላእክቱ አመራርና ድጋፍ ያለው ሥራ ነው። (ራእይ 14:​6) ራሳችንን ካቀረብን አንዳንድ ጊዜ ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የሚያስችሉ ያልተጠበቁ አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። በኬንያ ናይሮቢ በመስክ አገልግሎት ተሰማርተው የነበሩ ሁለት ክርስቲያን ሴቶች የተሰጣቸውን ቤቶች ሸፍነው እንደጨረሱ አንዲት ወጣት ሴት በድንገት ወደ እነርሱ ቀረበችና “ከእናንተ ሰዎች አንዱን እንዲያገናኘኝ ስጸልይ ነበር” በማለት በደስታ ነገረቻቸው። ምሥክሮቹ እቤቷ እንዲገቡና ውይይት እንዲያደርጉ አጥብቃ ለመነቻቸው። በዚያው ቀን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላት። ሴትየዋ እንዲህ ባለ ጥድፊያ ሁለቱን ክርስቲያኖች ለማግኘት የፈለገችው ለምንድን ነው? ከሁለት ሳምንት አካባቢ በፊት ልጅዋ ሞቶባት ነበር። ስለዚህ አንድ ልጅ “እናፈቅራቸው የነበሩ ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?” የሚል ትራክት ይዞ በተመለከተች ጊዜ ትራክቱን በጣም ስለፈለገችው እንዲሰጣት ጠየቀችው። እርሱ ግን ሊሰጣት ፈቃደኛ አልሆነም። ከዚያ ይልቅ ትራክቱን የሰጡትን ምሥክሮች ጠቆማት። ሴትየዋ ወዲያው በመንፈሳዊ ጥሩ እድገት ማድረግ በመጀመሯ ልጅዋን በማጣቷ ምክንያት የተሰማትን ሐዘን በተሻለ መንገድ መቋቋም ችላለች።

የአምላክ ፍቅር ሊያሸንፍ ይገባል

17 የአምላክ ቃል በምድር ዙሪያ ያደረገው እድገት ከክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጋር በቅርብ የተያያዘ ነው። እንደ ቤዛው ሁሉ የስብከቱ ሥራም ይሖዋ በየትኛውም ቦታ ለሚኖሩ ሰዎች ያለው ፍቅር መግለጫ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።”​—⁠ዮሐንስ 3:​16

18 ይሖዋ የቤዛውን ዝግጅት በማድረግ ስላሳየው ፍቅር አስብ። አምላክ ሕልቆ መሳፍርት ለሌለው ዘመን ‘በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ ከነበረውና’ ከተወደደው አንድያ ልጁ ጋር የተቀራረበ ዝምድና ነበረው። (ራእይ 3:​14) ኢየሱስ አባቱን በጥልቅ ይወድደዋል። ይሖዋም ልጁን የሚወድደው “ዓለም ሳይፈጠር” ጀምሮ ነው። (ዮሐንስ 14:​31፤ 17:​24) ይሖዋ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ማግኘት ይችሉ ዘንድ ይህ ውድ ልጁ እንዲሞት ፈቅዷል። ለሰው ዘሮች የተደረገ እንዴት ያለ ታላቅ የፍቅር መግለጫ ነው!

19 ዮሐንስ 3:​17 “ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፣ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና” በማለት ይናገራል። በመሆኑም ይሖዋ ልጁን የላከው ለፍርድ ወይም ለኩነኔ ሳይሆን ሰዎችን ለማዳን የተደረገ ፍቅራዊ ተልእኮ ነው። ይህም “[ይሖዋ] ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ” ይፈልጋል ከሚሉት ከጴጥሮስ ቃላት ጋር ይስማማል።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:​9

20 ይሖዋ መዳን የሚገኝበትን ሕጋዊ መሠረት ለመጣል የከፈለው መሥዋዕትነት ከፍተኛ በመሆኑ የተቻለውን ያህል በርካታ ሰዎች ከዚህ ዝግጅት እንዲጠቀሙ ይፈልጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና። እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?”​—⁠ሮሜ 10:​13, 14

21 በዚህ ምድር አቀፍ የስብከትና የማስተማር ሥራ መካፈል ምንኛ ታላቅ መብት ነው! ይህ ቀላል ሥራ ባይሆንም ሕዝቦቹ በታማኝነት በእውነት ሲመላለሱና ምሥራቹን ለሌሎች ሰዎች ሲያካፍሉ ሲመለከት ይሖዋ ምንኛ ይደሰት ይሆን! ስለዚህ ያለህበት ሁኔታ ምንም ዓይነት ይሁን ምን የአምላክ መንፈስና በልብህ ውስጥ ያለው ፍቅር በዚህ ሥራ እንድትካፈል የሚገፋፋህ ይሁን። እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ሲከናወን የምናየው ነገር ይሖዋ ክብራማ የሆነው ‘ጽድቅ የሚኖርባት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር’ እንደሚያመጣ የገባውን ቃል በቅርቡ እንደሚፈጽም የሚያሳምን ማረጋገጫ ነው።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:​13

ታስታውሳለህን?

• ክህደት የምሥራቹን ስብከት ዝም ሊያሰኝ ያልቻለው ለምንድን ነው?

• የአምላክ ቃል በጊዜያችን ድል ያደረገው እንዴት ነው?

• የአምላክ መንፈስ በዛሬው ጊዜ የሚሠራው በምን መንገዶች ነው?

• ቤዛው ከምሥራቹ ስብከት ጋር የተያያዘው እንዴት ነው?

[የጥናት እትም]

1. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስትና ያደረገውን እድገት ግለጽ።

2. ሰይጣን የምሥራቹን ግስጋሴ ለመግታት ሙከራ ያደረገው እንዴት ነው? ይህስ በትንቢት የተነገረው እንዴት ነው?

3. ሐዋርያት ሞተው ካለቁ በኋላ ምን ነገር ተከሰተ?

4. ሰይጣን የአምላክን ዓላማ ለማክሸፍ ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ የቀረው ለምንድን ነው?

5. ነቢዩ ዳንኤል ‘እውነተኛ እውቀትን’ በሚመለከት ምን ትንቢት ተናግሯል?

6. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በ1914 የተረዷቸው እውነቶች ምንድን ናቸው?

7. የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በዘመናችን ድል ያደረገው እንዴት ነው?

8. የይሖዋ ምሥክሮች ስላደረጉት እድገት አንዳንዶች ምን ብለው ተናግረዋል?

9. (ሀ) የአምላክ ቃል በዛሬው ጊዜ ድል እንዲያደርግ ያበቃው ዋነኛው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ሰዎችን ወደ እርሱ የሚስበው እንዴት ነው?

10. ለአምላክ ቃል ምላሽ የሰጡት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?

11. መንፈስ ቅዱስ በአምላክ ሕዝቦች ሕይወት ውስጥ እየሠራ ያለው እንዴት ነው? ምንስ ልዩነት ግልጽ ሆኖ ይታያል?

12. የይሖዋ ምሥክሮች ለወንጌላዊነቱ ሥራ ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው? ለሚያከናውኑት የስብከት እንቅስቃሴ ምን ዓይነት ምላሽ እናገኛለን ብለው ይጠብቃሉ?

13. በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሌሉ በይሖዋ ምሥክሮች መካከል በሰፊው የሚታዩት ነገሮች ምንድን ናቸው?

14. ኢየሱስ ለአገልግሎቱ ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው? በዛሬው ጊዜ ያሉ ደቀ መዛሙርቱስ ምን ዓይነት አስተሳሰብ ያንጸባርቃሉ?

15. አንዳንዶች ምሥራቹን በመስበክ ረገድ ብልሃት የተጠቀሙት እንዴት ነው?

16. ራሳችንን ማቅረባችን አንዳንድ ጊዜ ደቀ መዛሙርት ለማድረጉ ሥራ መንገድ የሚከፍተው እንዴት ነው?

17-19. ይሖዋ በቤዛው በኩል ለሰው ዘር ያሳየው ፍቅር ምንድን ነው?

20. መዳን ከምሥራቹ ስብከት ጋር የሚያያዘው በምን መንገድ ነው?

21. በስብከቱ ሥራ እንድንካፈል አጋጣሚ በማግኘታችን ምን ሊሰማን ይገባል?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ግራፍ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

በ20ኛው መቶ ዘመን በመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር ረገድ የተገኘ እድገት

አማካይ አስፋፊዎች (በሚልዮን)

6.0

5.5

5.0

4.5

4.0

3.5

3.0

2.5

2.0

1.5

1.0

0.5

1900 1910 1920 1930 1940 1950 1960 1970 1980 1990 2000

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጄሮም

ቲንደል

ጉተንበርግ

ሁስ

[ምንጭ]

ጉተንበርግና ሁስ:- From the book The Story of Liberty, 1878

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በ1920ዎቹ ምሥራቹን ሲያውጁ

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ ነው

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የስብከቱም ሥራ የአምላክ ፍቅር ጉልህ መግለጫ ነው