በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የእግዚአብሔርም ቃል ያድግ ነበር’

‘የእግዚአብሔርም ቃል ያድግ ነበር’

‘የእግዚአብሔርም ቃል ያድግ ነበር’

“ነገሩን ወደ ምድር ይሰድዳል፣ ቃሉም እጅግ ፈጥኖ ይሮጣል።”​—⁠መዝሙር 147:​15

1, 2. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ሥራ ምንድን ነው? ይህስ ምን ማድረግን ይጠይቅ ነበር?

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉት እጅግ አስገራሚ ትንቢቶች መካከል አንዱ በሐዋርያት ሥራ 1:​8 ላይ የሚገኘው ነው። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ጥቂት ቀደም ብሎ ታማኝ ተከታዮቹን “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ . . . እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሏቸዋል። ከፊታቸው ትልቅ ሥራ ይጠብቃቸው ነበር!

2 ለእነዚያ እፍኝ የማይሞሉ ደቀ መዛሙርት የአምላክን ቃል በመላው ምድር የማወጁ ሥራ ተፈታታኝ ሆኖ ታይቷቸው መሆን አለበት። ሥራው ምን ነገሮችን ያካትት እንደነበር አስብ። ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች እንዲያውቁ ሌሎች ሰዎችን መርዳት ነበረባቸው። (ማቴዎስ 24:​14) ስለ ኢየሱስ መመሥከር፣ እርሱ ያስተማራቸውን ልብ የሚነኩ ትምህርቶች ለሌሎች ማካፈልና በይሖዋ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ማብራራትን ይጠይቅባቸው ነበር። ከዚህም በላይ ሥራው ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግና ማጥመቅን የሚጨምር ነበር። ይህ ሁሉ በዓለም ዙሪያ መከናወን ነበረበት!​—⁠ማቴዎስ 28:​19, 20

3. ኢየሱስ ለተከታዮቹ ምን በማለት አረጋገጠላቸው? ለተሰጣቸው ሥራ ያሳዩት ምላሽ ምን ነበር?

3 የሆነ ሆኖ ኢየሱስ እርሱ የሰጣቸውን ሥራ በሚያከናውኑበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ አብሯቸው እንደሚሆን ለተከታዮቹ አረጋግጦላቸዋል። በመሆኑም የተሰጣቸው ሥራ የቱንም ያህል ሰፊ ቢሆንና ተቃዋሚዎችም ሥራቸውን ለማስተጓጎል ምንም ያህል ኃይል የታከለበት ጥረት ቢያደርጉ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ኢየሱስ ያዘዛቸውን ሥራ በተሳካ መንገድ ፈጽመዋል። ይህ ማንም ሊክደው የማይችለው የታሪክ ሐቅ ነው።

4. ለሌሎች በመስበኩና በማስተማሩ ተልዕኮ ረገድ የአምላክ ፍቅር የተገለጠው እንዴት ነው?

4 በመላው ዓለም የሚካሄደው የመስበክና የማስተማር ዘመቻ አምላክ እርሱን ለማያውቁ ሰዎች ያለው ፍቅር የሚገለጥበት መንገድ ነው። ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ያስችላቸዋል እንዲሁም የኃጢአት ይቅርታ ያስገኝላቸዋል። (ሥራ 26:​17, 18) የስብከቱና የማስተማሩ ተልእኮ መልእክቱን ይዘው የሚሄዱት ሰዎች ለይሖዋ ያደሩ መሆናቸውንና ለሰዎች ያላቸውን ፍቅር የሚያሳዩበት መንገድ በመሆኑ አምላክ ለእነርሱ ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ነው። (ማቴዎስ 22:​37-39) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያናዊ አገልግሎቱን እንደዚህ ከፍ አድርጎ ይመለከተው ስለነበር “መዝገብ” [“ክቡር ነገር፣” የ1980 ትርጉም ] ብሎ ጠርቶታል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:​7

5. (ሀ) ስለ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አስተማማኝ የታሪክ ዘገባ የምናገኘው ከየት ነው? እድገትንስ በተመለከተ ምን ዓይነት ዘገባ ሰፍሯል? (ለ) የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በዛሬው ጊዜ ላሉት የአምላክ አገልጋዮች ትርጉም ያዘለ የሆነው ለምንድን ነው?

5 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ስላከናወኑት የስብከት እንቅስቃሴ የሚገልጽ አስተማማኝ ታሪክ ደቀ መዝሙሩ ሉቃስ በመንፈስ አነሳሽነት በጻፈው በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል። አስገራሚና ፈጣን እድገት የተመዘገበበት መጽሐፍ ነው። በአምላክ ቃል እውቀት ረገድ የተገኘው ይህ እድገት መዝሙር 147:​15 ላይ የሰፈሩትን ቃላት ያስታውሰናል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ነገሩን ወደ ምድር ይሰድዳል፣ ቃሉም እጅግ ፈጥኖ ይሮጣል።” መንፈስ ቅዱስ ስላገኙት ስለ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የሚገልጸው ዘገባ በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ሰዎች ስሜት የሚቀሰቅስ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ትርጉም ያዘለም ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በበለጠ ስፋት ተመሳሳይ የሆነ የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛሉ። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን የገጠሟቸው ዓይነት ፈተናዎች እኛንም ይገጥሙናል። ይሖዋ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን እንዴት እንደባረካቸውና ኃይል እንደሰጣቸው መመርመራችን እርሱ በሚሰጠው ድጋፍ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።

በደቀ መዛሙርት ቁጥር የተገኘ ጭማሪ

6. በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ እድገትን በተመለከተ ሦስት ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኘው ሐረግ የትኛው ነው? ምን ነገርንስ ያመለክታል?

6 የሐዋርያት ሥራ 1:​8ን ፍጻሜ ማስተዋል የሚቻልበት አንደኛው መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያውም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ብቻ ከጥቂት ልዩነት በስተቀር በተመሳሳይ መንገድ ሦስት ጊዜ ያህል የተጠቀሰውን “የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ [“እያደገ፣” NW ] ሄደ” የሚለውን መግለጫ በመመርመር ነው። (ሥራ 6:​7፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን፤ 12:​24፤ 19:​20) እነዚህ ጥቅሶች ላይ የሚገኘው “የእግዚአብሔር ቃል” የሚለው መግለጫ የሚያመለክተው ምሥራቹን ማለትም ቀስቃሽ የሆነውን መለኮታዊ እውነት ሲሆን ይህ መልእክት ሕያውና በሚቀበሉት ሰዎች ሕይወት ላይ ለውጥ የማምጣት ኃይል ያለው ነው።​—⁠ዕብራውያን 4:​12

7. በሐዋርያት ሥራ 6:​7 ላይ የአምላክ ቃል እድገት የተገለጸው ከምን አንጻር ነው? በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ምን ነገር ተከናውኗል?

7 ስለ አምላክ ቃል እድገት የተገለጸበት የመጀመሪያው ቦታ የሐዋርያት ሥራ 6:​7 ነው። እዚያ ላይ እንዲህ እናነባለን:- “የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፣ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቊጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ።” እዚህ ላይ እድገት ከደቀ መዛሙርት ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ተገልጿል። በ33 እዘአ ተከብሮ በነበረው የጰንጠቆስጤ በዓል በሰገነት ላይ ተሰብስበው በነበሩት 120 በሚያክሉ ደቀ መዛሙርት ላይ የአምላክ መንፈስ ፈስሶ ነበር። ከዚያም ሐዋርያው ጴጥሮስ ቀስቃሽ ንግግር ያቀረበ ሲሆን ያዳምጡት ከነበሩት ሰዎች መካከል 3, 000 የሚያክሉት በዚያኑ ዕለት አማኞች ሆነዋል። በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከ50 ቀን በፊት እንደ ወንጀለኛ ተሰቅሎ በሞተው በኢየሱስ ስም ለመጠመቅ በኢየሩሳሌምም ሆነ በአቅራቢያዋ ወደሚገኝ ኩሬ ወይም ኩሬዎች ሲጎርፉ የተከናወነው ነገር ምን ያህል ትኩረት የሚስብ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያስቸግርም!​—⁠ሥራ 2:​41

8. በ33 እዘአ ከተከበረው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኋላ የደቀ መዛሙርት ቁጥር የጨመረው እንዴት ነው?

8 እርግጥ ይህ የመጀመሪያ ክንውን ብቻ ነበር። የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች የስብከቱን እንቅስቃሴ ለማስቆም ያደረጉት ያልተቋረጠ ጥረት ሁሉ አልሰመረላቸውም። እንዲያውም ይባስ ብሎ “ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ [በደቀ መዛሙርቱ] ላይ ይጨምር ነበር።” (ሥራ 2:​47) ወዲያው “የወንዶችም ቁጥር አምስት ሺህ ያህል ሆነ።” “የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ።” (ሥራ 4:​4፤ 5:​14) ከጊዜ በኋላ ስለሆነውም ነገር እንዲህ እናነባለን:- “በይሁዳም ሁሉና በገሊላ በሰማርያም የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት በሰላም ኖሩ ታነጹም፤ በእግዚአብሔርም ፍርሃትና በመንፈስ ቅዱስ መጽናናት እየሄዱ ይበዙ ነበር።” (ሥራ 9:​31) ከጥቂት ዓመታት በኋላ ምናልባትም በ58 እዘአ ሳይሆን አይቀርም የአማኞች ቁጥር “ብዙ ሺህ” እንደደረሰ እናነባለን። (ሥራ 21:​20 የ1980 ትርጉም ) በዚህ ወቅት ከአሕዛብ የመጡ በርካታ ሰዎችም አማኞች ሆነው ነበር።

9. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን ሁኔታ እንዴት ትገልጸዋለህ?

9 ይህ ባብዛኛው አዳዲስ አማኞች በመጨመራቸው ምክንያት የተገኘ እድገት ነው። ሃይማኖቱ ገና አዲስ ቢሆንም እንቅስቃሴው ከፍተኛ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ዳር ቆመው የሚመለከቱ የቤተ ክርስቲያን አባላት ሳይሆኑ ለይሖዋና ለቃሉ ሙሉ በሙሉ ያደሩ ነበሩ። አንዳንዶቹ እውነትን የሰሙት ከፍተኛ ስደት ይደርስባቸው ከነበሩ ሰዎች ነው። (ሥራ 16:​23, 26-33) ክርስትናን የተቀበሉት የማገናዘብ ችሎታቸውን ተጠቅመው ጥንቃቄ የተሞላበት ምርምር ካደረጉ በኋላ ነው። (ሮሜ 12:​1) የአምላክን መንገዶች ተምረዋል። እውነት በአእምሯቸውና በልባቸው ውስጥ ተተክሏል። (ዕብራውያን 8:​10, 11) ለሚያምኑበት ነገር ለመሞት እንኳ ፈቃደኞች ነበሩ።​—⁠ሥራ 7:​51-60

10. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር? በዛሬው ጊዜ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ምን ነገር አለ?

10 የክርስትናን ትምህርት የተቀበሉ ሁሉ እውነትን ለሌሎች የማካፈል ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገንዝበዋል። ይህም በቁጥር ተጨማሪ እድገት እንዲያደርጉ አስተዋጽዖ አድርጓል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዲህ ብለዋል:- “እምነትን ለሌሎች መናገር በጣም ቀናተኛ ለነበሩ ወይም ወንጌላዊ ሆነው ለተሾሙ ሰዎች ብቻ የተተወ አልነበረም። ወንጌላዊነት የእያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን አባል መብትና ኃላፊነት ነበር። . . . በአጠቃላይ በክርስትና ማኅበረሰብ ውስጥ የታየው ልባዊ ጥረት ለክርስትና እንቅስቃሴ ገና ከጅምሩ ከፍተኛ ኃይል ሆኖታል።” ጨምረውም “ወንጌላዊነት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ደመ ሕይወት ነበር” በማለት ጽፈዋል። ዛሬም ባሉት የእውነተኛ ክርስቲያኖች ዘንድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

በአገልግሎት ክልል ረገድ የተገኘ ጭማሪ

11. በሐዋርያት ሥራ 12:​24 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ምን ዓይነት እድገት ነው? ይህስ እድገት የታየው እንዴት ነው?

11 የአምላክ ቃል እንዳደገ የተገለጸበት ሁለተኛው ቦታ የሐዋርያት ሥራ 12:​24 ነው። ጥቅሱ “የእግዚአብሔር ቃል ግን ያድግና ይበዛ ነበር” ይላል። እዚህ ላይ ያለው ሐረግ በአገልግሎት ክልል ረገድ ከተደረገ ጭማሪ ጋር የተያያዘ ነው። የመንግሥታት ተቃውሞ ቢኖርም ሥራው ማደጉን ቀጥሎ ነበር። መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያ በኢየሩሳሌም ከፈሰሰ በኋላ ቃሉ ወደሌሎች ቦታዎች በፍጥነት ተዛመተ። በኢየሩሳሌም የተነሳው ስደት ደቀ መዛሙርቱ በይሁዳና በሰማርያ ወደሚገኙ ክልሎች እንዲበተኑ ምክንያት ሆኖ ነበር። ውጤቱስ? “የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ።” (ሥራ 8:​1, 4) ፊልጶስ በተሰጠው መመሪያ ለአንድ ሰው የመሠከረ ሲሆን ሰውዬውም ከተጠመቀ በኋላ መልእክቱን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ ሄዷል። (ሥራ 8:​26-28, 38, 39) ወዲያው እውነት በሰሮና ምድር በሚገኙት በልዳ እና በኢዮጴ ተስፋፋ። (ሥራ 9:​35, 42) ከጊዜ በኋላም ሐዋርያው ጳውሎስ በባሕርና በየብስ ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች በመጓዝ በብዙ የሜዲትራኒያን አገሮች ጉባኤዎችን አቋቁሟል። ሐዋርያው ጴጥሮስም ወደ ባቢሎን ተጉዟል። (1 ጴጥሮስ 5:​13) መንፈስ ቅዱስ በጰንጠቆስጤ ዕለት ከፈሰሰ ከ30 ዓመታት በኋላ ጳውሎስ በዚያን ጊዜ ይታወቅ የነበረውን የምድር ክፍል በማመልከት ሳይሆን አይቀርም ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው” በማለት ጽፏል።​—⁠ቆላስይስ 1:​23

12. የአምላክ ቃል በአገልግሎት ክልል ረገድ እድገት ማድረጉን የክርስትና ተቃዋሚዎች አምነው የተቀበሉት እንዴት ነው?

12 የክርስትና ተቃዋሚዎች እንኳን ሳይቀሩ የአምላክ ቃል በሮማ ግዛት መስፋፋቱን አምነው ተቀብለዋል። ለምሳሌ ያህል በሰሜን ግሪክ በምትገኘው በተሰሎንቄ የነበሩ ተቃዋሚዎች “ዓለምን ያወኩ እነዚህ ወደዚህ ደግሞ መጥተዋል” በማለት በጩኸት እንደተናገሩ የሐዋርያት ሥራ 17:​6 ይገልጻል። ከዚህም በላይ በሁለተኛው መቶ ዘመን መግቢያ ላይ ትንሹ ፕሊኒ ክርስትናን በሚመለከት ከቢታኒያ ሆኖ ለሮማው ንጉሠ ነገሥት ለትራጃን ደብዳቤ ጽፎለት ነበር። “ከከተሞችም አልፈው ልክ እንደተላላፊ በሽታ ወደ ጎረቤት መንደሮችና አገሮችም ተዛምተዋል” በማለት በምሬት ተናግሯል።

13. በአገልግሎት ክልል ረገድ የተገኘው እድገት አምላክ ለሰው ዘሮች ያለውን ፍቅር ያንጸባርቃል የምንለው እንዴት ነው?

13 ይህ በአገልግሎት ክልል ረገድ የተደረገ ጭማሪ ይሖዋ ሊዋጅ ለሚችለው የሰው ዘር ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ነው። መንፈስ ቅዱስ አሕዛብ በነበረው በቆርኔሌዎስ ላይ በፈሰሰ ጊዜ ጴጥሮስ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ” በማለት ተናግሯል። (ሥራ 10:​34, 35) አዎን፣ በዚያን ጊዜም ሆነ አሁን ምሥራቹ ለሁሉም ሰው ሊደርሰው የሚገባ መልእክት ነው። እንዲሁም የአምላክ ቃል በአገልግሎት ክልል ረገድ ያደረገው እድገት በሁሉም ሥፍራ የሚኖሩ ሰዎች ለአምላክ ፍቅር ምላሽ እንዲሰጡ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። በዚህ በ21ኛው መቶ ዘመን የአምላክ ቃል በሁሉም የምድር ክፍል ቃል በቃል ተዳርሷል።

ጉልህ እድገት

14. በሐዋርያት ሥራ 19:​20 ላይ የተገለጸው እድገት ምን ዓይነት ነው? የአምላክ ቃል በምን ነገሮች ላይ ድል አድርጓል?

14 የአምላክ ቃል እድገት እንዳደረገ የተገለጸበት ሦስተኛ ቦታ የሐዋርያት ሥራ 19:​20 ሲሆን እዚያም ላይ “የጌታ ቃል በኃይል ያድግና ያሸንፍ ነበር” ይላል። “ያሸንፍ ነበር” ተብሎ የተተረጎመው የመጀመሪያው የግሪክኛ ቃል “ጥንካሬን መጠቀም” የሚል ሐሳብ የሚያስተላልፍ ነው። ከዚህ በፊት ያሉት ቁጥሮች በኤፌሶን ብዙ ሰዎች አማኞች እንደሆኑና አስማተኞች የነበሩ በርካታ ሰዎችም መጻሕፍታቸውን በሰዎች ፊት እንዳቃጠሉ ይናገራሉ። በዚህ መንገድ የአምላክ ቃል በሐሰት እምነቶች ላይ ድል አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ምሥራቹ እንደ ስደት ያሉ ሌሎች እንቅፋቶችንም በአሸናፊነት ተወጥቷል። ምንም ነገር ሊያግደው አልቻለም። በዚህም ረገድ ቢሆን በዘመናችን ከሚገኘው ክርስትና ጋር አስገራሚ ተመሳሳይነት እናያለን።

15. (ሀ) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጸሐፊ ስለ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ምን ብለዋል? (ለ) ደቀ መዛሙርቱ ላገኙት ስኬት የሚያመሰግኑት ማንን ነው?

15 ሐዋርያትና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ሌሎች ክርስቲያኖች የአምላክን ቃል በቅንዓት አውጀዋል። እነርሱን በማስመልከት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጸሐፊ የሚከተለውን ብለዋል:- “ሰዎቹ ስለ ጌታቸው መናገር በሚፈልጉበት ጊዜ ይህን ለማድረግ ምንም አይቸገሩም ነበር። እነዚህ ወንዶችና ሴቶች ከተጠቀሙበት ዘዴ ይልቅ ይበልጥ የሚያስገርመን ለሥራ ያነሳሳቸው ውስጣዊ ግፊት ነው።” ሆኖም የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በአገልግሎት ያገኙት ስኬት በእነርሱ ጥረት ብቻ የተገኘ እንዳልሆነ ተገንዝበው ነበር። የተሰጣቸው መለኮታዊ ተልዕኮ ነበር። ይህንንም ለመፈጸም መለኮታዊ ድጋፍ አግኝተዋል። መንፈሳዊ እድገት እንዲኖር የሚያደርገው አምላክ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ይህንን ሲገልጽ “እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር” ብሏል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 3:​6, 9

መንፈስ ቅዱስ ያከናወናቸው ሥራዎች

16. ደቀ መዛሙርቱ በድፍረት እንዲናገሩ መንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደሰጣቸው የሚያሳየው ምንድን ነው?

16 መንፈስ ቅዱስ በአምላክ ቃል እድገት ረገድ የሚጫወተው ሚና እንዳለ እንዲሁም ደቀ መዛሙርቱ በሚያደርጉት የስብከት እንቅስቃሴ ኃይል እንደሚሰጣቸው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ማረጋገጫ እንደሰጠ አስታውስ። (ሥራ 1:​8) ይህ የተፈጸመው እንዴት ነው? መንፈስ ቅዱስ በጰንጠቆስጤ ዕለት በደቀ መዛሙርቱ ላይ ከፈሰሰ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ አይሁድ ሳንሄድሪን ማለትም ለኢየሱስ ክርስቶስ መገደል ተጠያቂ የሆኑት ዳኞች ወዳሉበት የአገሩ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሩ። ሐዋርያቱ እንዲህ ወዳለው አስፈሪና ግርማ ያለው ጨካኝ ሸንጎ ፊት ሲቀርቡ በፍርሃት ይርዱ ይሆን? በጭራሽ! ጴጥሮስና ዮሐንስ መንፈስ ቅዱስ በሰጣቸው ኃይል በድፍረት በተናገሩ ጊዜ ተቃዋሚዎቻቸው በጣም ከመደነቃቸውም ሌላ “ከኢየሱስም ጋር እንደ ነበሩ አወቁአቸው።” (ሥራ 4:​8, 13) ከዚህም በተጨማሪ መንፈስ ቅዱስ እስጢፋኖስም በሳንሄድሪን ፊት በድፍረት እንዲናገር ኃይል ሰጥቶታል። (ሥራ 6:​12፤ 7:​55, 56) ከዚያ ቀደም ብሎ ደቀ መዛሙርቱ በመንፈስ ቅዱስ አንቀሳቃሽነት በግልጥ ሰብከው ነበር። ሉቃስ እንዲህ በማለት ዘግቧል:- “ከጸለዩም በኋላ ተሰብስበው የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፣ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፣ የእግዚአብሔርንም ቃል በግልጥ ተናገሩ።”​—⁠ሥራ 4:​31

17. መንፈስ ቅዱስ ደቀ መዛሙርቱ አገልግሎታቸውን ሲያከናውኑ በምን ሌሎች መንገዶች አግዟቸዋል?

17 ይሖዋ ትንሣኤ ባገኘው በኢየሱስና በመንፈስ ቅዱሱ ኃይል አማካኝነት የስብከቱን እንቅስቃሴ መርቷል። (ዮሐንስ 14:​28፤ 15:​26) መንፈስ ቅዱስ በቆርኔሌዎስ፣ በዘመዶቹና በቅርብ ወዳጆቹ ላይ በፈሰሰ ጊዜ ጴጥሮስ ያልተገረዙ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለመጠመቅ ብቁ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገንዝቧል። (ሥራ 10:​24, 44-48) ከጊዜ በኋላም መንፈሱ በርናባስንና ሳውልን (ሐዋርያው ጳውሎስን) ለሚስዮናዊ ሥራ በመሾምና ወዴት መሄድ እንዳለባቸውና ወዴት መሄድ እንደሌለባቸው በመጠቆም ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። (ሥራ 13:​2, 4፤ 16:​6, 7) በኢየሩሳሌም ያሉትን ሐዋርያትና ሽማግሌዎች በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ መንፈስ ቅዱስ መርቷቸዋል። (ሥራ 15:​23, 28, 29) በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካች ሆነው የሚሾሙትን በመምረጥ ረገድም አመራር ሰጥቷል።​—⁠ሥራ 20:​28

18. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ፍቅራቸውን የገለጹት እንዴት ነው?

18 ከዚህም በተጨማሪ መንፈስ ቅዱስ እንደ ፍቅር ያሉ አምላካዊ ባሕርያትን እንዲያፈሩ በማድረግ በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥም ተገልጧል። (ገላትያ 5:​22, 23) ደቀ መዛሙርቱ አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን እንዲያካፍሉ የረዳቸው ፍቅር ነው። ለምሳሌ ያህል በ33 እዘአ ከተከበረው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኋላ በኢየሩሳሌም የሚገኙት ደቀ መዛሙርት የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገር ለማሟላት በጋራ የተሰባሰበ ገንዘብ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “በመካከላቸው አንድ ስንኳ ችግረኛ አልነበረምና፤ መሬት ወይም ቤት ያላቸው ሁሉ እየሸጡ የተሸጠውን ዋጋ ያመጡ ነበርና፣ በሐዋርያትም እግር አጠገብ ያኖሩ ነበር፤ ማናቸውም እንደሚፈልግ መጠን ለእያንዳንዱ ያካፍሉት ነበር።” (ሥራ 4:​34, 35) እንዲህ ያለውን ፍቅር ለእምነት ባልደረቦቻቸው ብቻ በማሳየት ሳይወሰኑ ለሌሎችም ምሥራቹን በማካፈልና ደግነት በማድረግ ፍቅር አሳይተዋል። (ሥራ 28:​8, 9) ኢየሱስ ተከታዮቹ በሚያሳዩት የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር ተለይተው እንደሚታወቁ ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:​34, 35) በእርግጥም ቁልፍ ሚና ያለው የፍቅር ባሕርይ ሰዎችን ወደ አምላክ የሚስብ ሲሆን ልክ በዛሬው ጊዜ እንደሚታየው በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ጭማሪ እንዲገኝ አስተዋጽዖ አበርክቷል።​—⁠ማቴዎስ 5:​14, 16

19. (ሀ) የይሖዋ ቃል በመጀመሪያው መቶ ዘመን እድገት ያደረገባቸው ሦስት አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ምን ነገር እንመረምራለን?

19 በአጠቃላይ “መንፈስ ቅዱስ” የሚለው መግለጫ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ 41 ጊዜ ሰፍሮ ይገኛል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የታየው እውነተኛ የክርስትና እድገት ከመንፈስ ቅዱስ ኃይልና አመራር ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው። የደቀ መዛሙርት ቁጥር አድጓል፣ የአምላክ ቃል በስፋት ወደ ተለያዩ ክልሎች ተሰራጭቷል እንዲሁም በዚያን ዘመን በነበሩት ሃይማኖቶችና ፍልስፍናዎች ሁሉ ላይ ድል አድርጓል። ይህ በአንደኛው መቶ ዘመን የታየው እድገት ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያከናውኑት ሥራም እየታየ ነው። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ዛሬ የአምላክ ቃል ያገኘውን ተመሳሳይ የሆነ አስገራሚ እድገት እንመረምራለን።

ታስታውሳለህን?

• የመጀመሪያው መቶ ዘመን ደቀ መዛሙርት በቁጥር ያደጉት እንዴት ነው?

• በአገልግሎት ክልል ረገድ የአምላክ ቃል እድገት ያደረገው እንዴት ነው?

• የአምላክ ቃል በመጀመሪያው መቶ ዘመን ድል ያደረገው እንዴት ነው?

• በአምላክ ቃል እድገት ረገድ መንፈስ ቅዱስ የተጫወተው ሚና ምንድን ነው?

[የጥናት እትም]

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊው በመመሥከር ምሥራቹ ወደ ሌላ የምድር ክፍል እንዲስፋፋ አድርጓል

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መንፈስ ቅዱስ በኢየሩሳሌም የነበሩትን ሐዋርያትና ሽማግሌዎች መርቷቸዋል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከላይ በስተቀኝ:- Reproduction of the City of Jerusalem at the time of the Second Temple - located on the grounds of the Holyland Hotel, Jerusalem