“ስውር የሕብረተሰብ ጤና ጠንቅ”
“ስውር የሕብረተሰብ ጤና ጠንቅ”
በዩናይትድ ስቴትስ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ከሆኑ አዋቂዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ከወሲባዊ ነገሮች ጋር ግንኙነት ያላቸውን አንድ ዓይነት የዌብ ገፆች እንደተመለከቱ በቅርቡ ወሲብን አስመልክቶ የተደረገ አንድ ጥናት አመልክቷል። በአሁኑ ጊዜ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በኢንተርኔት አማካኝነት በውስጣቸው ለሚቀሰቀሰው ወሲባዊ ግፊት እየተሸነፉ ነው። “ይህ በሕብረተሰቡ ዘንድ በመስፋፋት ላይ ያለ ስውር የጤና ጠንቅ ሲሆን ለዚህም በከፊል ምክንያት የሆነው ነገር ራሱን ችግሩን የተገነዘቡት ወይም አሳሳቢነቱን የተረዱት ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑ ነው” በማለት ጥናቱን ያካሄዱት ዶክተር አል ኩፐር የተባሉ የሥነ ልቦና ጠበብት ተናግረዋል።
እንዲህ ላሉት በኢንተርኔት ለሚተላለፉ ወሲባዊ ነገሮች ይበልጥ የተጋለጡት እነማን ናቸው? “እድሜ ልካቸውን የጾታ ስሜታቸውን አምቀው የያዙ ወይም ገድበው የቆዩ” ሆኖም በኢንተርኔት አማካይነት “በድንገት የተትረፈረፉ ወሲባዊ አጋጣሚዎችን ያገኙ ሰዎች ናቸው” በማለት ዶክተር ኩፐር ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ አዘውትረው የወሲብ ገፆችን የሚመለከቱ ሰዎች እንዲህ ያለው ተግባር ምንም ጉዳት የማያስከትል እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ሁኔታው እንደዚያ ነው? አንድ የዕፅ ሱሰኛ ሱስ ለተያዘበት ዕፅ ምርኮኛ እንደሚሆን ሁሉ በኢንተርኔት የሚተላለፉትን የወሲብ ሥዕሎች የመመልከት ልማድ የተጠናወታቸው አብዛኞቹ ሰዎችም የወሲብ ምኞታቸውን ለማርካት “ተጨማሪ” የወሲብ ሥዕሎችን መመልከት ይፈልጋሉ። እንዲያውም ሥራቸውን አልፎ ተርፎም ትዳራቸውን አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ!
ይሁን እንጂ አምላክን ለማስደሰት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በኢንተርኔት የሚተላለፉትን ወሲባዊ ሥዕሎች ከመመልከት እንዲርቅ የሚያደርገው ተጨማሪ ምክንያት አለው። የአምላክ ቃል እንዲህ በማለት ያሳስባል:- “እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፣ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣዖትንም ማምለክ የሆነ መጐምጀት ነው፤ በእነዚህም ጠንቅ የእግዚአብሔር ቊጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል።” (ቆላስይስ 3:5, 6) አንድ ሰው ተገቢ ካልሆነ የጾታ ስሜት ጋር በተያያዘ ‘ብልቶቹን መግደል’ ከፈለገ ለይሖዋ አምላክ ጠንካራ ፍቅር ማዳበር ይኖርበታል። (መዝሙር 97:10) አንድ ሰው ከወሲብ ጋር በተያያዘ የሕብረተሰብ ጤና ጠንቅ በሆነው በዚህ ስውር ዘዴ እንደተያዘ ከተገነዘበ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ለይሖዋ ያለውን ፍቅር ማሳደግ ይኖርበታል። በዚህ ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት አንድ ሰው አምላክን ለማስደሰት ያደረገውን ቁርጥ ውሳኔ በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክትለት ይችላል።