በይሖዋ አገልግሎት ያገኛችሁትን ደስታ ጠብቃችሁ ኑሩ
በይሖዋ አገልግሎት ያገኛችሁትን ደስታ ጠብቃችሁ ኑሩ
“ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፣ ደስ ይበላችሁ።”—ፊልጵስዩስ 4:4
1, 2. አንድ ወንድምና ባለቤቱ የነበራቸውን ንብረት ሁሉ ቢያጡም ደስታቸውን ጠብቀው ማቆየት የቻሉት እንዴት ነው?
በሴራሊዮን የሚኖር ጀምስ የተባለ አንድ የ70 ዓመት ክርስቲያን ዕድሜውን በሙሉ ጠንክሮ በመሥራት ገንዘብ ካጠራቀመ በኋላ አራት ክፍል ያለው አንድ መጠነኛ ቤት ሲገዛ የተሰማውን ደስታ ገምት! ይሁን እንጂ ጀምስና ቤተሰቡ በዚህ አዲስ ቤት መኖር ከጀመሩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በዚያች አገር የእርስ በርስ ጦርነት ፈነዳና ቤታቸው እንዳለ ወደመ። ቤታቸውን ቢያጡም እንኳን ደስታቸውን ግን አላጡም። ለምን?
2 ጀምስና ቤተሰቡ አእምሯቸው እንዲያተኩር ያደረጉት በጠፋው ነገር ላይ ሳይሆን ሳይጠፋ በቀረው ነገር ላይ ነበር። ጀምስ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “ሁኔታው በጣም አስፈሪ በነበረበት ጊዜ እንኳን ሳይቀር ስብሰባዎችን እናደርግ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እናነብ፣ አብረን እንጸልይ እንዲሁም ያለችንን አብረን እንቃመስ ነበር። ትኩረታችን ያረፈው ከይሖዋ ጋር በመሠረትነው ውድ ዝምድና ላይ ስለነበር ደስታችንን ጠብቀን መኖር ችለናል።” እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች ባገኙት በረከት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከይሖዋ ጋር በመሠረቱት ውድ ዝምድና ላይ በማሰላሰል ‘ደስተኞች’ ሆነው መቀጠል ችለዋል። (2 ቆሮንቶስ 13:11 NW ) እርግጥ ነው፣ የደረሰባቸውን አስከፊ ሁኔታ መቋቋሙን ቀላል ሆኖ አላገኙትም። ሆኖም በይሖዋ መደሰታቸውን ቀጥለዋል።
3. አንዳንድ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ደስታቸውን ጠብቀው ያቆዩት እንዴት ነው?
3 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ጀምስና ቤተሰቡ ከገጠማቸው ጋር የሚመሳሰል መከራ ደርሶባቸው ነበር። ሆኖም፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች “የገንዘባችሁንም ንጥቂያ በደስታ ተቀበላችሁ” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን) በማለት ጽፎላቸዋል። ከዚያም ጳውሎስ የደስታቸው ምንጭ ምን እንደሆነ ሲናገር “የሚበልጥና ለዘወትር የሚኖር ገንዘብ . . . ራሳችሁ እንዳላችሁ አውቃች[ኋል]” ብሏቸዋል። (ዕብራውያን 10:34) አዎን፣ እነዚያ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ትልቅ ተስፋ ነበራቸው። ማንም ሊነጥቃቸው የማይችል በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ውስጥ የማይጠፋ ‘የሕይወት አክሊል’ ለማግኘት በትምክህት ሊጠባበቁ ይችላሉ። (ራእይ 2:10) ያለን ክርስቲያናዊ ተስፋ ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ መከራ በሚያጋጥመን ጊዜ እንኳ ሳይቀር ደስታችንን ጠብቀን እንድንኖር ሊረዳን ይችላል።
“በተስፋ ደስ ይበላችሁ”
4, 5. (ሀ) ጳውሎስ “በተስፋ ደስ ይበላችሁ” በማለት የሰጠው ምክር ለሮም ክርስቲያኖች በጣም ወቅታዊ የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ክርስቲያን ምን ነገሮች ተስፋውን ሊያደበዝዙበት ይችላሉ?
4 ሐዋርያው ጳውሎስ በዘላለም ሕይወት ‘ተስፋ ደስ እንዲላቸው’ በሮም የሚገኙ የእምነት ባልደረቦቹን አበረታቷቸዋል። (ሮሜ 12:12) ይህ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች ወቅታዊ ምክር ነበር። ጳውሎስ መልእክቱን ከጻፈላቸው አሥር ዓመት እንኳ ሳይሞላ ከባድ ስደት ደረሰባቸው። አንዳንዶቹም በንጉሠ ነገሥት ኔሮ ትእዛዝ ተሠቃይተው እንዲገደሉ ተደርገዋል። አምላክ የሕይወት አክሊል እንደሚሰጣቸው በገባላቸው ተስፋ ላይ የነበራቸው እምነት ይደርስባቸው የነበረውን ሥቃይ እንዲቋቋሙ እንደረዳቸው ምንም ጥርጥር የለውም። በዛሬው ጊዜ ስላለነው ስለ እኛስ ምን ለማለት ይቻላል?
5 ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን እኛም ስደት ይደርስብናል ብለን ልንጠባበቅ እንችላለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ከዚህም በላይ “ጊዜና አጋጣሚ” በሁላችንም ላይ የሚያስከትለው ነገር ሊኖር እንደሚችል እናውቃለን። (መክብብ 9:11 NW ) በድንገተኛ አደጋ የምንወደውን ሰው ልናጣ እንችላለን። የማይድን በሽታ ወላጃችንን ወይም የቅርብ ወዳጃችንን ሊነጥቀን ይችላል። ትኩረታችን ሙሉ በሙሉ በመንግሥቱ ተስፋችን ላይ እንዲያተኩር ካላደረግን እነዚህን የመሰሉ መከራዎች ሲደርሱብን መንፈሳዊነታችን አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። በዚህም ምክንያት እንዲህ እያልን ራሳችንን ብንጠይቅ ጥሩ ይሆናል:- ‘“በተስፋ ደስ” ይለኛል? ጊዜ ወስጄ በዚህ ተስፋ ላይ የማሰላሰል ልማድ አለኝ? መጪው ገነት እውን ሆኖ ይታየኛል? እዚያ ውስጥ እንዳለሁ አድርጌ ራሴን እመለከተዋለሁ? ይህ የነገሮች ሥርዓት ሲደመደም ለመመልከት ያለኝ ጉጉት እውነትን ለመጀመሪያ ጊዜ ስሰማ ከነበረኝ ጋር አንድ ዓይነት ነው?’ በተለይ ይህ የመጨረሻው ጥያቄ በቁም ነገር ልናስብበት የሚገባ ጥያቄ ነው። ለምን? ብዙውን ጊዜ ሰዎች ጥሩ ጤናና የተደላደለ ኑሮ ካለን፣ ጦርነት፣ የምግብ እጥረት ወይም የተፈጥሮ አደጋ እምብዛም በሌለበት አካባቢ የምንኖር ከሆንን ለጊዜውም ቢሆን የአምላክ አዲስ ዓለም በቶሎ የመምጣቱ አስፈላጊነት ያን ያህል ላይታየን ይችላል።
6. (ሀ) ጳውሎስና ሲላስ መከራ በገጠማቸው ጊዜ ትኩረታቸው በምን ነገር ላይ እንዲያርፍ አደረጉ? (ለ) የጳውሎስና የሲላስ ምሳሌ በዛሬው ጊዜ የምንኖረውን እኛን ሊያበረታታን የሚችለው እንዴት ነው?
6 ጳውሎስ የሮም ክርስቲያኖችን “በመከራ ታገሡ” በማለት ተጨማሪ ምክር ሰጥቷቸዋል። (ሮሜ 12:12) ጳውሎስ ለመከራ አዲስ አልነበረም። በአንድ ወቅት ‘ወደ መቄዶንያ ተሻግሮ’ በዚያ የሚኖሩትን ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ እንዲረዳቸው አንድ ሰው ሲጋብዘው በራእይ ተመልክቷል። (ሥራ 16:9) በዚህም የተነሳ ጳውሎስ ከሉቃስ፣ ከሲላስና ከጢሞቴዎስ ጋር ሆኖ ወደ አውሮፓ ተጓዘ። እነዚህ ቀናተኛ ሚስዮናውያን እዚያ ምን ይጠብቃቸው ነበር? መከራ! የመቄዶንያ ከተማ በሆነችው በፊልጵስዩስ ከሰበኩ በኋላ ጳውሎስና ሲላስ በበትር ተደብድበው እስር ቤት ተጣሉ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አንዳንድ የፊልጵስዩስ ነዋሪዎች ለመንግሥቱ መልእክት እንዲያው ግዴለሾች ብቻ ሳይሆኑ ኃይለኛ ተቃዋሚዎች ነበሩ። ቀናተኞቹ ሚስዮናውያን ሁኔታውን እንደጠበቁት ሆኖ አለማግኘታቸው ደስታቸውን እንዲያጡ አድርጓቸዋልን? በጭራሽ። ተደብድበው እስር ቤት ከተጣሉ በኋላ “በመንፈቀ ሌሊት . . . ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር።” (ሥራ 16:25, ፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እርግጥ ነው፣ ጳውሎስና ሲላስ በድብደባው ምክንያት የሚሰማቸው ሕመም ደስታ አላመጣላቸውም። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁለት ሚስዮናውያን ትኩረት ያደረጉት እዚያ ላይ አልነበረም። ትኩረታቸው ሁሉ ያረፈው በይሖዋና በበረከቱ ላይ ነበር። ጳውሎስና ሲላስ የደረሰባቸውን ‘መከራ’ በደስታ ‘በመታገሳቸው’ በፊልጵስዩስና በሌሎች ቦታዎች ለሚኖሩ ወንድሞቻቸው ግሩም ምሳሌ ሆነውላቸዋል። 26
7. በጸሎታችን ውስጥ ምስጋናን ማከል የሚኖርብን ለምንድን ነው?
7 ጳውሎስ “በጸሎት ጽኑ” በማለት ጽፏል። (ሮሜ 12:12) የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች በሚገጥሙህ ጊዜ ትጸልያለህ? ስለምን ነገር ትጸልያለህ? ችግርህን ለይተህ በመጥቀስ ይሖዋ እንዲረዳህ እንደምትለምን የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ላገኘሃቸውም በረከቶች አመስጋኝ መሆንህንም ልትገልጽ ትችላለህ። ችግሮች በሚነሱበት ጊዜ በይሖዋ ጥሩነት ላይ ማሰላሰላችን ‘በተስፋ ደስ እንዲለን’ ይረዳናል። በመከራ የተሞላ ሕይወት ያሳለፈው ዳዊት “አቤቱ አምላኬ፣ ያደረግኸው ተአምራት ብዙ ነው፣ አሳብህንም ምንም የሚመስለው የለም፤ ባወራም ብናገርም ከቍጥር ሁሉ በዛ” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 40:5) እኛም እንደ ዳዊት ከይሖዋ ባገኘናቸው በረከቶች ላይ አዘውትረን የምናሰላስል ከሆነ ምንም ነገር ደስታችንን ሊያሳጣን አይችልም።
አዎንታዊ መንፈስ ይኑራችሁ
8. አንድ ክርስቲያን በስደት ውስጥ እያለ ደስተኛ ሆኖ እንዲቀጥል የሚረዳው ምንድን ነው?
8 ኢየሱስ ተከታዮቹ የተለያዩ መከራዎች ሲደርሱባቸው አዎንታዊ መንፈስ እንዲይዙ አበረታቷቸዋል። እንዲህ አለ:- “ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።” (ማቴዎስ 5:11) እንደነዚህ ያሉ ሁኔታዎች እየደረሱብን እንኳ እንድንደሰት የሚያደርጉን ምን ነገሮች አሉን? ተቃውሞን ለመቋቋም ያለን ችሎታ የይሖዋ መንፈስ በእኛ ላይ እንዳለ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ በዘመኑ የነበሩትን ክርስቲያን ባልደረቦቹን “ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ” ብሏቸዋል። (1 ጴጥሮስ 4:13, 14) ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት እንድንጸናና በዚህም ደስታችንን ጠብቀን እንድንኖር ይረዳናል።
9. አንዳንድ ወንድሞች በእምነታቸው ምክንያት ታስረው እያለ ደስተኞች እንዲሆኑ የረዳቸው ምንድን ነው?
9 በጣም አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በምንገኝበት ጊዜ እንኳ ለደስታ ምክንያት የሚሆን ነገር ልናገኝ እንችላለን። አዶልፍ የተባለ አንድ ክርስቲያን ይህን እውነት ሆኖ አግኝቶታል። አዶልፍ የሚኖረው የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ለበርካታ ዓመታት በታገደበት አገር ነው። እርሱና ጓደኞቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነታቸውን ለመካድ እምቢ በማለታቸው ምክንያት ተይዘው ረዘም ላለ ጊዜ እንዲታሰሩ ተፈረደባቸው። የእስር ቤት ሕይወት በጣም መራራ ቢሆንባቸውም እንደ ጳውሎስና ሲላስ ሁሉ አዶልፍና ጓደኞቹ አምላክን እንዲያመሰግኑ የሚያደርጓቸው ምክንያቶች ነበሯቸው። በእስር ቤት ያሳለፏቸው ጊዜያት እነርሱ እንደተናገሩት እምነታቸው እንዲጠናከርና እንደ ልግስና፣ አዛኝነትና የወንድማማች ፍቅርን የመሰሉ ውድ የሆኑ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንዲያዳብሩ ረድቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ እስረኛ ከቤት የሆነ ነገር ሲመጣለት ይህ ዓይነቱ ዝግጅት ከሁሉ በላቀ ደረጃ ‘የበጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ’ ምንጭ ከሆነው ከይሖዋ እንደመጣ አድርጎ በመመልከት አብረውት ለታሠሩ ጓደኞቹ ያካፍላቸዋል። እንዲህ ያለው ደግነት ለሰጪውም ሆነ ለተቀባዩ ደስታን ያመጣል። መታሰራቸው እምነታቸውን እንዲክዱ ከማድረግ ይልቅ መንፈሳዊነታቸው የበለጠ እንዲጠናከር አድርጓል!—ያዕቆብ 1:17፤ ሥራ 20:35
10, 11. አንዲት እህት ከፍተኛ ምርመራ ከተደረገባት በኋላ ለረዥም ዓመት ለእስር ብትዳረግም ይህን ሁኔታ የተቋቋመችው እንዴት ነው?
10 የመንግሥቱ ሥራ ለረዥም ዓመታት በታገደባት በአንዲት አገር የምትኖረው ኤላም ክርስቲያናዊ ተስፋዋን ለሌሎች በማካፈሏ ምክንያት ተይዛ ታሰረች። ስምንት ወር የፈጀ ከፍተኛ ምርመራ ተካሄደባት። በመጨረሻ ፍርድ ቤት ከቀረበች በኋላ ከእርሷ ሌላ ይሖዋን የሚያመልክ ማንም ሰው በሌለበት እስር ቤት ውስጥ አሥር ዓመት እንድትታሰር ተበየነባት። በዚህ ወቅት ኤላ የ24 ዓመት ወጣት ነበረች።
11 እርግጥ ነው፣ ኤላ ቀሪ የወጣትነት ሕይወቷን በእስር ቤት የማሳለፍ ፍላጎት አልነበራትም። ይሁን እንጂ የገጠማትን ሁኔታ መለወጥ ባትችልም አመለካከቷን መለወጥ እንዳለባት ግን ወሰነች። በዚህም መሠረት እስር ቤቱን ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችል የአገልግሎት ክልሏ እንደሆነ አድርጋ መመልከት ጀመረች። “በስብከቱ ሥራ በጣም ከመጠመዴ የተነሳ ዓመቱ እንዴት እንዳለፈ እንኳ አልታወቀኝም” በማለት ትናገራለች። አምስት ዓመት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ኤላ እንደገና ቃሏን እንድትሰጥ ተደረገ። መርማሪዋ፣ እስር ቤት እምነቷን ሊያስለውጣት እንዳልቻለ በተመለከተ ጊዜ “አልተለወጥሽም፣ ስለዚህ አንፈታሽም” አላት። ኤላ “ተለውጫለሁ!” በማለት ፈርጠም ብላ መለሰች። “እስር ቤት ከገባሁበት ጊዜ ይልቅ አሁን ጠንካራ መንፈስ አለኝ። እምነቴም ከበፊቱ የበለጠ ጠንካራ ነው!” አክላም “ልትፈቱኝ ፈቃደኞች ካልሆናችሁ ይሖዋ የፈቀደው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ እቆያለሁ።” ኤላ አምስት ዓመት ከስድስት ወር በእስር ብታሳልፍም ደስታዋን ግን አላጣችም! በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብትገኝ መርካትን ተምራለች። ከእርሷ ምሳሌ ልትማር የምትችለው ነገር ይኖር ይሆን?—ዕብራውያን 13:5
12. በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያለ አንድ ክርስቲያን የአእምሮ ሰላም እንዲያገኝ ምን ሊረዳው ይችላል?
12 ኤላ እንዲህ ያለውን ተፈታታኝ ሁኔታ መቋቋም የቻለችው ከሰው የተለየ ተሰጥኦ ስላላት እንደሆነ አድርገህ አታስብ። ፍርድ ቤት ቀርባ ፍርዷን ከመስማቷ በፊት ያሳለፈችውን የምርመራ ጊዜ አስመልክታ ስትናገር ኤላ እንዲህ ብላለች:- “በፍርሃት ጥርሶቼ ሲፋጩና ወጥመድ ውስጥ እንደገባች ወፍ በፍርሃት የተሸማቀኩበት ጊዜ ትዝ ይለኛል።” ይሁን እንጂ ኤላ በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት ነበራት። በእርሱ ላይ መታመንን ተምራለች። (ምሳሌ 3:5-7) በዚህም ምክንያት ከበፊቱ ይልቅ አሁን አምላክ እውን ሆኖላታል። እንዲህ ትላለች:- “ቃሌን እንድሰጥ በተጠራሁ ቁጥር ሰላማዊ የሆነ ስሜት ይሰማኛል። . . . ሁኔታው ይበልጥ አስፈሪ እየሆነ በሄደ ቁጥር ሰላሜም የዚያኑ ያህል ጥልቀት እያገኘ ይሄዳል።” የዚህ ሰላም ምንጭ ይሖዋ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።”—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
13. አንድ ዓይነት መከራ በሚገጥመን ጊዜ መቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ እንደምናገኝ ምን ማረጋገጫ አለን?
13 ኤላ መከራ ቢደርስባትም ከእስር ቤት እስከተለቀቀችበት ጊዜ ድረስ ደስታዋን ጠብቃ ኖራለች። ይህንንም ያደረገችው በራሷ ኃይል ሳይሆን ይሖዋ በሰጣት ኃይል ነው። ሐዋርያው ጳውሎስም ተመሳሳይ ኃይል አግኝቶ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። . . . ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።”—2 ቆሮንቶስ 12:9, 10
14. አንድ ክርስቲያን ፈታኝ የሆነ ሁኔታ ሲገጥመው አዎንታዊ አመለካከት ሊይዝ የሚችለው እንዴት እንደሆነና ይህም ምን ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል በምሳሌ አስረዳ።
14 አንተ በግልህ እየተጋፈጥክ ያለኸው ተጽዕኖ እዚህ ላይ ከጠቀስናቸው ተጽዕኖዎች ለየት ያለ ሊሆን ይችላል። የሆነ ሆኖ፣ ተጽዕኖዎች የቱንም ዓይነት መልክ ይኑራቸው በጽናት ለመወጣት ማታገላቸው አይቀርም። ለምሳሌ ያህል፣ አሠሪህ የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ከሆኑት ተቀጣሪዎች ይልቅ በሥራ አንተን ይበልጥ ይጫንህ ይሆናል። ሌላ ሥራ ማግኘት ደግሞ ቀላል ላይሆን ይችላል። ታዲያ ደስታህን ጠብቀህ መቀጠል የምትችለው እንዴት ነው? የእስር ቤት ቆይታቸው ግሩም የሆኑ ባሕርያትን እንዲያዳብሩ የረዳቸውን የአዶልፍና የጓደኞቹን ሁኔታ አስታውስ። አሠሪህ ምንም እንኳ ‘ጠማማ’ ቢሆን እሱን ለማስደሰት ከፍተኛ ጥረት የምታደርግ ከሆነ እንደ ጽናትና ትዕግሥት ያሉትን ክርስቲያናዊ ባሕርያት ታዳብራለህ። (1 ጴጥሮስ 2:18) ከዚህም በላይ በሥራህ መስክ ያለህን ችሎታ ልታዳብርና ከጊዜ በኋላም የተሻለ ሥራ የማግኘት አጋጣሚህን ከፍ ሊያደርግልህ ይችላል። በይሖዋ አገልግሎት ደስታችንን ጠብቀን መቀጠል የምንችልባቸውን ሌሎች መንገዶች እንመልከት።
አኗኗርን ቀላል ማድረግ ደስታ ያስገኛል
15-17. አንድ ባልና ሚስት ምንም እንኳ ከችግራቸው ሙሉ በሙሉ ባይገላገሉም ያለባቸውን ውጥረት በመጠኑም ቢሆን ማቃለል እንዲችሉ ምን ተማሩ?
15 የምትሠራውን የሥራ ዓይነት ወይም የምትሠራበትን ቦታ እንደፈለግኸው መለዋወጥ አትችል ይሆናል። ይሁን እንጂ በተወሰነ መጠን ልትቆጣጠራቸው የምትችላቸው ሌሎች የሕይወትህ ዘርፎች ሊኖሩ ይችላሉ። የሚከተለውን ተሞክሮ ተመልከት።
16 አንድ ክርስቲያን ባልና ሚስት አንድን ሽማግሌ ቤታቸው ጋበዙት። በጭውውታቸው መካከል ወንድምና ባለቤቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኑሯቸው ጭንቀት እየፈጠረባቸው እንደመጣ አዋዩት። ሁለቱም ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ሙጥጥ የሚያደርግ የሙሉ ቀን ሥራ የሚሠሩ ቢሆኑም ሌላ ምንም አማራጭ አልነበራቸውም። በዚህ ሁኔታ እስከ መቼ እንደሚቀጥሉ ግራ ገብቷቸዋል።
17 ምክር እንዲለግሳቸው የጠየቁት ሽማግሌም “ኑሯችሁን ቀላል አድርጉት” ሲል መለሰላቸው። እንዴት? ባልና ሚስቱ ወደ ሥራ ሄዶ ለመመለስ ብቻ በየቀኑ ሦስት ሰዓት ገደማ ያጠፋሉ። እነዚህን ባልና ሚስት በሚገባ የሚያውቃቸው ይህ ሽማግሌ በየቀኑ ወደ ሥራ ለመሄድና ከሥራ ለመመለስ የሚያጠፉትን ጊዜ መቀነስ ይችሉ ዘንድ ወደሚሠሩበት አካባቢ ቀረብ ብለው እንዲኖሩ ሐሳብ አቀረበላቸው። እንዲህ ካደረጉ በጉዞ ይጠፋ የነበረውን ጊዜ አስፈላጊ ለሆኑ ሌሎች ጉዳዮች ወይም እንዲሁ እረፍት ለማድረግ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። የኑሮ ጭንቀቶች በተወሰነ መጠን ደስታህን የሚቀንሱብህ ከሆነ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማድረግ እፎይታ ማግኘት ትችል እንደሆነ ለምን ራስህን አትመረምርም?
18. አንድ ዓይነት ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ጉዳዩን በጥንቃቄ ማጤኑ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
18 ተጽዕኖዎችን መቀነስ የሚቻልበት ሌላው መንገድ ደግሞ አንድ ዓይነት ውሳኔ ከማድረግ በፊት ጉዳዩን በጥንቃቄ ማጤን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ክርስቲያን ቤት ለመሥራት ወሰነ። ከዚህ ቀደም ቤት ሠርቶ የማያውቅ ቢሆንም በጣም የተራቀቀ ዲዛይን መረጠ። ለቤቱ ዲዛይን ከመምረጡ በፊት ‘አካሄዱን ተመልክቶ’ ቢሆን ኖሮ ሳያስፈልግ ችግር ውስጥ ከመግባት መታቀብ ይችል እንደነበር ተገነዘበ። (ምሳሌ 14:15) አንድ ሌላ ወንድም ደግሞ የእምነት ባልደረባው ገንዘብ ሲበደር ዋስ ይሆናል። በስምምነታቸው መሠረት ገንዘቡን የተበደረው ግለሰብ ብድሩን መክፈል ካቃተው ዋስ የሆነው ግለሰብ የመክፈል ግዴታ ይኖርበታል። መጀመሪያ ላይ ምንም ዓይነት ችግር አልነበረም፤ ከጊዜ በኋላ ግን ተበዳሪው ስምምነቱን ሳያከብር ይቀራል። አበዳሪው ሁኔታው ያሳስበውና ዋስ የሆነው ግለሰብ መላውን ብድር እንዲከፍል ይጠይቃል። ይህም በዋሱ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮበታል። ዋስ ለመሆን ከመስማማቱ በፊት ሁኔታዎችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች አጢኖ ቢሆን ኖሮ ከዚህ ሁሉ ራሱን መጠበቅ ይችል አልነበረምን?—ምሳሌ 17:18
19. በሕይወታችን የሚገጥመንን ውጥረት መቀነስ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
19 ድካም በሚሰማን ጊዜ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንንና የመስክ አገልግሎታችንን በማቆምና ከስብሰባዎች በመቅረት የገጠመንን ውጥረት ማቅለል እንደምንችልና ደስታችንን ማደስ እንደምንችል አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። እነዚህ የደስታ ምንጭ የሆነውን የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ የምናገኝባቸው ወሳኝ መንገዶች በመሆናቸው እንዲህ ማድረግ አይኖርብንም። (ገላትያ 5:22) ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች በአብዛኛው የሚያድሱ እንጂ የሚያዝሉ አይደሉም። (ማቴዎስ 11:28-30) ብዙውን ጊዜ በድካም እንድንዝል የሚያደርጉን መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ሳይሆኑ ሰብዓዊ ሥራዎች ወይም መዝናኛዎች ናቸው። በጊዜ የመተኛት ልማድ ማዳበር ኃይላችን እንዲታደስ ሊረዳን ይችላል። ጥቂት ተጨማሪ እረፍት ማድረግ ከፍተኛ ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል። እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ኤን ኤች ኖር ለሚስዮናውያን እንዲህ እያለ የመናገር ልማድ ነበረው:- “ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሲሰማችሁ መጀመሪያ ማድረግ ያለባችሁ ነገር አረፍ ማለት ነው። ሌሊቱን ጥሩ እንቅልፍ ተኝታችሁ ካሳለፋችሁ በኋላ የገጠማችሁ ማንኛውም ችግር በጣም ቀላል ሆኖ ስታገኙት ትገረማላችሁ!”
20. (ሀ) ደስታችንን ጠብቀን መቀጠል የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ጠቅለል አድርገህ ግለጽ። (ለ) ለደስታ ምክንያት የሚሆኑ ምን ነገሮችን ልታስብ ትችላለህ? (በገጽ 17 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)
20 ክርስቲያኖች “ደስተኛውን አምላክ” የማገልገል መብት አግኝተዋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW ) ከላይ እንደተመለከትነው ከባድ ችግር በሚገጥመን ጊዜ እንኳ ሳይቀር ደስታችንን ጠብቀን መቀጠል እንችላለን። የመንግሥቱን ተስፋ ከፊታችን እናስቀምጥ፣ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ አመለካከታችንን እናስተካክል እንዲሁም አኗኗራችንን ቀላል እናድርግ። እንደዚያ ካደረግን ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢገጥመን “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፣ ደስ ይበላችሁ” ለሚሉት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት አዎንታዊ ምላሽ እንሰጣለን።—ፊልጵስዩስ 4:4
የሚከተሉትን ጥያቄዎች በጥንቃቄ አስብባቸው:-
• ክርስቲያኖች ትኩረታቸውን በመንግሥቱ ተስፋ ላይ ማድረግ ያለባቸው ለምንድን ነው?
• በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ደስታችንን ጠብቀን ለመቀጠል ምን ሊረዳን ይችላል?
• አኗኗራችንን ቀላል ለማድረግ መጣር ያለብን ለምንድን ነው?
• አንዳንዶች አኗኗራቸውን ቀላል ያደረጉባቸው አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ደስተኛ እንድንሆን የሚያደርጉን ተጨማሪ ምክንያቶች
ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን እንድንደሰት የሚያደርጉን በርካታ ምክንያቶች አሉን። የሚከተሉትን ተመልከት:-
1. ይሖዋን እናውቃለን።
2. የአምላክን ቃል እውነት ተምረናል።
3. በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ ባለን እምነት መሠረት ኃጢአታችን ይቅር ሊባልንን ይችላል።
4. የአምላክ መንግሥት በመግዛት ላይ ነው፤ አዲሱ ዓለም በቅርቡ እውን ይሆናል!
5. ይሖዋ ወደ መንፈሳዊ ገነት አምጥቶናል።
6. እርስ በርስ ጤናማ የሆነ ክርስቲያናዊ ወዳጅነት አለን።
7. በስብከቱ ሥራ የመካፈል መብት አለን።
8. በሕይወት እንኖራለን እንዲሁም አንዳንድ ነገር ማከናወን እንችላለን።
ለደስታ አስተዋጽዖ የሚያደርጉ ሌሎች ልትጠቅሳቸው የምትችላቸው ምክንያቶች ይኖሩሃል?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስና ሲላስ እስር ቤት እያሉ እንኳ ደስተኞች ነበሩ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ትኩረትህ ያረፈው በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ባሉት ነገሮች ላይ ነው?