ደስተኛ ከሆነው አምላክ ጋር ደስ ይበላችሁ
ደስተኛ ከሆነው አምላክ ጋር ደስ ይበላችሁ
“በቀረውስ፣ ወንድሞች ሆይ፣ ደኅና [“ደስተኞች፣” NW ] ሁኑ . . . የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።”—2 ቆሮንቶስ 13:11
1, 2. (ሀ) ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ደስታ የሚያጡት ለምንድን ነው? (ለ) ደስታ ምንድን ነው? ማዳበር የምንችለውስ እንዴት ነው?
በዚህ ጨለማ በዋጠው ዓለም ውስጥ ደስ የሚያሰኙ ነገሮችን ማግኘት ለብዙ ሰዎች በጣም አስቸጋሪ ነው። በእነርሱ ወይም በሚወዱት ሰው ላይ አንድ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ በሚደርስበት ጊዜ “ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ቀን ነው” ብሎ እንደተናገረው በጥንት ጊዜ ይኖር እንደነበረው እንደ ኢዮብ ይሰማቸው ይሆናል። (ኢዮብ 14:1) ክርስቲያኖች ‘ይህ አስጨናቂ ዘመን’ ከሚያስከትለው ጭንቀትና ውጥረት ነፃ አይደሉም። በዚህም የተነሳ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች አልፎ አልፎ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ቢሰማቸው ምንም አያስገርምም።—2 ጢሞቴዎስ 3:1
2 ያም ሆኖ ክርስቲያኖች መከራ እየደረሰባቸውም እንኳ ደስተኞች መሆን ይችላሉ። (ሥራ 5:40, 41) ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት እንደሆነ ለመረዳት በመጀመሪያ የደስታን ትርጉም መርምር። ደስታ “ጥሩ ነገርን በማግኘት ወይም አገኛለሁ ብሎ በማሰብ የሚፈጠር ስሜት ነው።” a በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ስላገኘናቸውና ወደፊት በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ስለምናገኛቸው በረከቶች ቆም ብለን ካሰላሰልን ደስተኞች ልንሆን እንችላለን።
3. እያንዳንዱ ሰው ደስተኛ ሊያደርጉት የሚችሉ ቢያንስ የተወሰኑ ምክንያቶች አሉት ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?
3 እያንዳንዱ ሰው አመስጋኝ እንዲሆን የሚያደርጉት ያገኛቸው የተወሰኑ በረከቶች አሉት። አንድ የቤተሰብ ራስ ከሥራው ሊፈናቀል ይችላል። ይህም ጭንቀት ላይ ሊጥለው እንደሚችል የታወቀ ነው። ለቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማቅረብ ይፈልጋል። ያም ሆኖ በአካል ጠንካራና ጤናማ ከሆነ ለዚህ አመስጋኝ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ሥራ ካገኘ ጠንክሮ የመሥራት አቅም አለው። በሌላው በኩል ደግሞ አንዲት ክርስቲያን እህት ከዕለት ወደ ዕለት በሚያመነምን በሽታ ተይዛ ሊሆን ይችላል። ሆኖም፣ አፍቃሪ ወዳጆቿና የቤተሰብ አባሎቿ በሽታዋን በረጋ መንፈስና በጽናት እንድትቋቋም ለሚያደርጉላት ድጋፍ አመስጋኝነቷን ልትገልጽ ትችላለች። እንዲሁም ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ያሉበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ‘ደስተኛ አምላክ’ የሆነውን ይሖዋንና ‘ደስተኛና ብቻውን ገዥ’ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቃቸው ሊደሰቱ ይችላሉ። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW፤ 6:15 NW ) አዎን፣ ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ በጣም ደስተኞች ናቸው። ምንም እንኳ በምድር ላይ ያለው ሁኔታ ይሖዋ በመጀመሪያ አስቦት ከነበረው ፈጽሞ የተለየ ቢሆንም ደስታቸውን ጠብቀው ኖረዋል። እኛም ደስታችንን እንዴት ጠብቀን መኖር እንደምንችል ከእነርሱ ምሳሌ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን።
ፈጽሞ ደስታቸውን አጥተው አያውቁም
4, 5. (ሀ) የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ዓመፅ በፈጸሙ ጊዜ ይሖዋ ምን እርምጃ ወሰደ? (ለ) ይሖዋ የሰው ዘሮችን በሚመለከት አዎንታዊ አመለካከት እንዳለው ያሳየው በምን መንገድ ነው?
4 አዳምና ሔዋን በኤደን ገነት ውስጥ ፍጹም የሆነ ጤናና ፍጹም የሆነ አእምሮ ይዘው ይኖሩ ነበር። የሚሠሩት ፍሬያማ የሆነ ሥራና ለሥራው አመቺ የሆነ አካባቢ ነበራቸው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ዘወትር የመነጋገር መብት ነበራቸው። ወደፊትም ደስተኛ ሆነው እንዲቀጥሉ የአምላክ ዓላማ ነበር። ይሁን እንጂ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ባገኟቸው በእነዚህ ጥሩ ስጦታዎች ሳይረኩ ቀሩ። እንዳይነኩ ከተከለከሉት “መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ” ፍሬ ሰርቀው በሉ። እንዲህ ያለው የዓመፀኝነት ድርጊት ዛሬ በምንኖረው በእኛ ማለትም በዘሮቻቸው ላይ አሳዛኝ መዘዞችን አስከትሏል።—ዘፍጥረት 2:15-17፤ 3:6፤ ሮሜ 5:12
5 ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን ያሳዩት ውለታ ቢስነት ደስታውን እንዲነጥቅበት አልፈቀደም። ከዘሮቻቸው መካከል እርሱን ለማገልገል የሚገፋፉ ቢያንስ ጥቂት ሰዎች እንደሚኖሩ እርግጠኛ ነበር። እንዲያውም በዚህ ረገድ በጣም እርግጠኛ ከመሆኑ የተነሳ ሌላው ቀርቶ አዳምና ሔዋን ገና የመጀመሪያ ልጃቸውን ከመውለዳቸው በፊት ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን ለመዋጀት ዓላማ እንዳለው ተናገረ! (ዘፍጥረት 1:31፤ 3:15) ከዚያ በኋላ በነበሩት ዘመናት አብዛኛው የሰው ዘር የአዳምንና የሔዋንን ፈለግ በመከተሉ ምክንያት እምቢተኝነት በእጅጉ ቢስፋፋም ይሖዋ መላውን ሰብዓዊ ቤተሰብ እርግፍ አድርጎ አልተወም። ከዚያ ይልቅ ‘ልቡን ደስ የሚያሰኙትንና’ ለእርሱ ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው እርሱን ለማስደሰት ከፍተኛ ጥረት በሚያደርጉ ወንዶችና ሴቶች ላይ ትኩረት አድርጓል።—ምሳሌ 27:11፤ ዕብራውያን 6:10
6, 7. ኢየሱስ ደስተኛ ሆኖ እንዲቀጥል የረዳው ምንድን ነው?
6 ስለ ኢየሱስስ ምን ለማለት ይቻላል? ደስተኛ ሆኖ መኖር የቻለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ በሰማይ ይኖር ስለነበር በምድር ላይ የሚኖሩ ወንዶችንና ሴቶችን እንቅስቃሴ አንድ በአንድ የመመልከት አጋጣሚ አግኝቷል። ፍጹም አለመሆናቸው በገሃድ የሚታይ ቢሆንም ኢየሱስ ወድዷቸዋል። (ምሳሌ 8:31) ከጊዜ በኋላ ወደ ምድር መጥቶ በሰዎች ‘መካከል ማደር’ በጀመረ ጊዜም ለሰው ዘር የነበረው አመለካከት አልተለወጠም። (ዮሐንስ 1:14) ፍጹም የሆነው የአምላክ ልጅ ኃጢአተኛ ለሆነው የሰው ልጅ ቤተሰብ እንዲህ አዎንታዊ አመለካከት እንዲይዝ ያስቻለው ምንድን ነው?
7 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኢየሱስ ከራሱም ሆነ ከሰዎች በሚጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ነበር። ዓለምን ለመለወጥ እንዳልመጣ ያውቅ ነበር። (ማቴዎስ 10:32-39) በዚህም የተነሳ አንድ ቅን ሰው ብቻ እንኳ ለመንግሥቱ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጥ ይደሰት ነበር። ደቀ መዛሙርቱ በአንዳንድ ወቅቶች የሚያሳዩት ጠባይና ዝንባሌ ከእነርሱ የማይጠበቅ በሚሆንበት ጊዜ እንኳ በልባቸው የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች እንደሆኑ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። ይህንንም መሠረት በማድረግ ወድዷቸዋል። (ሉቃስ 9:46፤ 22:24, 28-32, 60-62) ኢየሱስ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ ደቀ መዛሙርቱ የወሰዷቸውን በጎ እርምጃዎች ጠቅለል አድርጎ ሲጠቅስ “ቃልህንም ጠብቀዋል” ብሎ እስከመናገር ደርሷል።—ዮሐንስ 17:6
8. ደስተኞች ሆነን በመኖር ረገድ የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ ልንኮርጅ የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ጥቀስ።
8 ሁላችንም ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ረገድ የተዉልንን ምሳሌ በጥንቃቄ ብንመረምር ጥቅም እንደምናገኝ ምንም ጥርጥር የለውም። አንዳንድ ሥራዎች እኛ በጠበቅነው መንገድ ሳይሠሩ በሚቀሩበት ጊዜ ከልክ በላይ ከመጨነቅ በመቆጠብ በተቻለ መጠን ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ልንመስለው እንችላለን? ያለንበትን ሁኔታ በተመለከተ አዎንታዊ አመለካከት በመያዝና ከእኛ ከራሳችንም ሆነ ከሌሎች በምንጠብቃቸው ነገሮች ረገድ ምክንያታዊ በመሆን የኢየሱስን ፈለግ በቅርብ መከተል እንችላለን? ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዳንዶቹ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ቀናተኛ ክርስቲያኖች እንደ ውድ ነገር አድርገው በሚቆጥሩት ማለትም በመስክ አገልግሎት ላይ እንዴት ሊሠራ እንደሚችል እንመልከት።
ለአገልግሎቱ አዎንታዊ አመለካከት ያዙ
9. ኤርምያስ ደስታው እንደገና የተቀጣጠለው እንዴት ነው? የእርሱ ምሳሌ ሊረዳን የሚችለውስ እንዴት ነው?
9 ይሖዋ በአገልግሎቱ ደስተኞች እንድንሆን ይፈልጋል። ደስታችን በምናገኘው ውጤት ላይ ብቻ የተመካ መሆን የለበትም። (ሉቃስ 10:17, 20) ኤርምያስ ፍሬያማ ባልሆነ የአገልግሎት ክልል ለብዙ ዓመታት ሰብኳል። ኤርምያስ በሰዎቹ አሉታዊ ምላሽ ላይ ትኩረት ባደረገ ጊዜ ደስታውን አጣ። (ኤርምያስ 20:8) ይሁን እንጂ መልእክቱ ባለው ማራኪ ገጽታ ላይ ባሰላሰለ ጊዜ ደስታው እንደገና ተመለሰለት። ኤርምያስ እንዲህ በማለት ለይሖዋ ተናግሯል:- “ቃልህ ተገኝቶአል እኔም በልቼዋለሁ፤ አቤቱ፣ የሠራዊት አምላክ ሆይ፣ በስምህ ተጠርቻለሁና ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነኝ።” (ኤርምያስ 15:16) አዎን፣ ኤርምያስ የአምላክን ቃል ለመስበክ ባገኘው መብት ተደስቷል። እኛም ልንደሰት እንችላለን።
10. የአገልግሎት ክልላችን ፍሬያማ ባይሆን እንኳ በአገልግሎቱ የምናገኘውን ደስታ ጠብቀን ማቆየት የምንችለው እንዴት ነው?
10 ምንም እንኳ ብዙዎቹ ሰዎች ምሥራቹን ለመስማት ፈቃደኞች ባይሆኑም በመስክ አገልግሎት ስንካፈል ደስተኞች እንድንሆን የሚያደርጉን በርካታ ምክንያቶች አሉን። ይሖዋ እርሱን ለማገልገል ከልባቸው የሚነሳሱ አንዳንድ ሰዎች እንደሚኖሩ እርግጠኛ እንደነበር አስታውስ። እኛም የይሖዋን ምሳሌ በመኮረጅ በአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ አገዛዝ ላይ የተነሳውን ግድድር ተገንዝበው የመንግሥቱን መልእክት የሚቀበሉ ሰዎች እንደሚኖሩ ያለንን ተስፋ ፈጽሞ ማጥፋት አይኖርብንም። የሰዎች ሁኔታ እንደሚለወጥ ፈጽሞ መርሳት የለብንም። አንድ አሳዛኝ ሁኔታ ወይም አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ የሚጎድላቸው ምንም ነገር እንደሌለ ይሰማቸው የነበሩ ግለሰቦች እንኳ ሳይቀሩ ስለ ሕይወት ትርጉም በቁም ነገር ማሰብ ሊጀምሩ ይችላሉ። ‘በመንፈሳዊ የሚጎድለው ነገር እንዳለ የሚገነዘብ’ እንዲህ ያለ ሰው ቢያጋጥምህ ለመርዳት ዝግጁ ነህ? (ማቴዎስ 5:3) ማን ያውቃል፣ በድጋሚ በአገልግሎት ክልልህ ስትሠራ ምሥራቹን ለማዳመጥ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ታገኝ ይሆናል!
11, 12. በአንዲት አነስተኛ ከተማ ምን ነገር ተከሰተ? ከዚህስ ምን ልንማር እንችላለን?
11 የአገልግሎት ክልላችን ይዘትም ሊለወጥ ይችላል። አንድ ምሳሌ ተመልከት። በአንዲት ትንሽ ከተማ የጠበቀ የቤተሰብ ትስስር ያላቸው ወጣት ባለትዳሮች ከልጆቻቸው ጋር ይኖራሉ። የይሖዋ ምሥክሮች በየቤታቸው እየሄዱ ባነጋገሯቸው ጊዜ ሁሉም “አንፈልግም” የሚል ተመሳሳይ መልስ ሰጡ! አንድ ሰው ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት እንዳለው ቢያሳይ እንኳ ጎረቤቶቹ ቶሎ ብለው ከምሥክሮቹ ጋር ዳግም እንዳይገናኝ በማድረግ ተስፋ ያስቆርጡታል። መቼም በእዚህ አካባቢ መመሥከር ፈታኝ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ሆኖም ምሥክሮቹ ተስፋ አልቆረጡም። መስበካቸውን ቀጠሉ። ምን ውጤት ተገኘ?
12 ከብዙ ጊዜ በኋላ በመንደሯ ይኖሩ የነበሩ ትንንሽ ልጆች አድገው፣ ትዳር መሥርተው በራሳቸው ቤት መኖር ጀመሩ። ኑሯቸው ምንም ዓይነት እውነተኛ ደስታ እንዳላመጣላቸው ሲገነዘቡ ከእነዚህ ልጆች መካከል አንዳንዶቹ እውነትን መፈለግ ጀመሩ። ምሥክሮቹ የሚያውጁትን ምሥራች በተቀበሉ ጊዜ ይፈልጉ የነበሩትን እውነት አገኙ። በዚህ መንገድ በዚህች መንደር የነበረው ትንሽ ጉባኤ እድገት ማድረግ ጀመረ። ተስፋ ቆርጠው መስበካቸውን ያላቆሙት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ምንኛ ደስ እንደሚላቸው ገምቱ! እኛም ክብራማውን የመንግሥቱን መልእክት በጽናት በማካፈል ደስታ የምናገኝ እንሁን!
የእምነት ባልደረቦች ይደግፉሃል
13. ተስፋ የመቁረጥ ስሜት በሚሰማን ጊዜ ወደ ማን ዞር ማለት እንችላለን?
13 ተጽዕኖዎች እየጨመሩ ሲሄዱ ወይም ያልታሰበ አደጋ በሚያጋጥምህ ጊዜ መጽናኛ ለማግኘት ወደ ማን ዞር ልትል ትችላለህ? ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ አገልጋዮች እርዳታ ለማግኘት በመጀመሪያ በጸሎት አማካኝነት ወደ ይሖዋ ዞር የሚሉ ሲሆን ከዚያም የክርስቲያን ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን እርዳታ ይጠይቃሉ። ኢየሱስ ራሱ ምድር በነበረበት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ የሚሰጡትን ድጋፍ ከፍ አድርጎ ይመለከት ነበር። ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት “በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ” በማለት ስለ እነርሱ ተናግሯል። (ሉቃስ 22:28) እነዚህ ደቀ መዛሙርት ፍጹማን አለመሆናቸው እውነት ቢሆንም ያሳዩት የታማኝነት አቋም የአምላክን ልጅ አጽናንቶታል። እኛም የእምነት አጋሮቻችንን በማየት ብርታት ልናገኝ እንችላለን።
14, 15. አንድ ባልና ሚስት ልጃቸው በመሞቱ ምክንያት የደረሰባቸውን ሐዘን እንዲቋቋሙ የረዳቸው ምንድን ነው? ከእነርሱ ተሞክሮ ምን ትማራለህ?
14 ሚሼል እና ዳያን የተባሉ ክርስቲያን ባልና ሚስት ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው የሚሰጡት ድጋፍ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ለመገንዘብ የሚያስችል አጋጣሚ አግኝተዋል። ጤናማና ፍልቅልቅ የነበረው የ20 ዓመት ልጃቸው ዦናታን በተደረገለት የሕክምና ምርመራ በአንጎሉ ውስጥ እብጠት እንዳለ ታወቀ። ሐኪሞች ሕይወቱን ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ዦናታን በጣም እየተዳከመ ሄደና አንድ ምሽት ላይ በሞት አንቀላፋ። ሚሼል እና ዳያን ልባቸው ክፉኛ በሃዘን ተሰበረ። የዚያን ዕለት ምሽት የሚደረገው የአገልግሎት ስብሰባ ሊያልቅ ትንሽ እንደቀረው ተገነዘቡ። ያም ሆኖ መጽናናትን በጣም ይፈልጉ የነበሩት እነዚህ ባልና ሚስት ወደ መንግሥት አዳራሹ እንዲያካሂዳቸው አብሯቸው የነበረውን ሽማግሌ ጠየቁት። ዦናታን እንደሞተ የሚገልጽ ማስታወቂያ ለጉባኤው እየተነገረ ሳለ ደረሱ። ስብሰባው እንዳለቀ ወንድሞችና እህቶች ሐዘን ላይ የወደቁትን ወላጆች ከብበው በማቀፍና የሚያበረታቱ ቃላት በመሰንዘር አጽናኗቸው። ዳያን ሁኔታውን በማስታወስ እንዲህ ትላለች:- “ወደ አዳራሽ ስንደርስ በጣም ተረብሸን ነበር። ይሁን እንጂ ወንድሞች የሰጡን ማበረታቻ በእጅጉ አጽናናን! የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን ሊያስወግዱልን ባይችሉም እንኳ ሐዘኑን መቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ እንድናገኝ ረድተውናል!”—ሮሜ 1:11, 12፤ 1 ቆሮንቶስ 12:21-26
15 ሚሼል እና ዳያን የደረሰባቸው መከራ ወደ ወንድሞቻቸው ይበልጥ እንዲቀርቡ አድርጓቸዋል። እርስ በርሳቸውም ይበልጥ እንዲቀራረቡ አድርጓቸዋል። ሚሼል እንዲህ ይላል:- “ውድ ባለቤቴን ከምንጊዜውም የበለጠ እንድወዳትና እንድንከባከባት አድርጎኛል። ተስፋ የመቁረጥ ስሜት በሚሰማን ጊዜ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነትና ይሖዋ ስላደረገልን እንክብካቤ እርስ በርስ እንነጋገራለን።” ዳያን እንዲህ በማለት ጨምራ ተናግራለች:- “የመንግሥቱ ተስፋ አሁን የበለጠ ትርጉም ያዘለ ሆኖልናል።”
16. የምንፈልገውን ነገር ለወንድሞቻችን ማሳወቃችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
16 አዎን፣ በሕይወታችን ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን “የብርታት ምንጭ” ሊሆኑልንና ደስተኞች እንድንሆን ሊረዱን ይችላሉ። (ቆላስይስ 4:11 NW ) እርግጥ ነው፣ ልባችንን ማንበብ አይችሉም። ስለዚህ የወንድሞቻችን ድጋፍ እንደሚያስፈልገን በሚሰማን ጊዜ ብንነግራቸው ጥሩ ይሆናል። ከዚያም ወንድሞቻችን የሚሰጡንን ማንኛውም ዓይነት ማጽናኛ ከይሖዋ እንደመጣ አድርገን በመመልከት ልባዊ አድናቆታችንን መግለጽ እንችላለን።—ምሳሌ 12:25፤ 17:17
ጉባኤያችሁን ተመልከቱ
17. አንዲት ነጠላ ወላጅ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉባት? እንደ እርሷ ያሉትን የምንመለከታቸውስ እንዴት ነው?
17 የእምነት ባልንጀሮችህን ይበልጥ በቀረብካቸው መጠን እነርሱን የበለጠ እያደነቅሃቸው ትሄዳለህ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር አብረህ በመሆንህ ትደሰታለህ። እስቲ ጉባኤህን ተመልከት። ምን ታያለህ? ልጆችዋን በእውነት መንገድ ለማሳደግ የምትፍጨረጨር ነጠላ ወላጅ ትኖር ይሆን? ግሩም ምሳሌነቷን ልብ ለማለት ሞክረህ ታውቃለህ? ምን ዓይነት ችግሮችን እየታገለች እንዳለች ለማሰብ ሞክር። ጄነን የተባለች አንዲት ነጠላ ወላጅ ከእነዚህ ችግሮች መካከል አንዳንዶቹን እንዲህ በማለት ትጠቅሳቸዋለች:- ብቸኝነት፣ በሥራ ቦታ ያሉ ወንዶች የሚያቀርቡት ተገቢ ያልሆነ ጥያቄ፣ የወር ወጪን ለማብቃቃት የሚደረግ ጥረት። እያንዳንዱ ልጅ የራሱ የሆነ ባሕርይ ስላለው የልጆችን ስሜታዊ ፍላጎቶች ማሟላት ከሁሉ የከፋ ችግር እንደሆነ ትናገራለች። ጄነን ሌላም ዓይነት ችግር ትጠቅሳለች:- “የትዳር ጓደኛችሁን በምታጡበት ጊዜ ወንድ ልጃችሁ የቤቱ አባወራ እንደሆነ አድርጋችሁ ለመመልከት ትፈተኑ ይሆናል። አንዲት ሴት ልጅ ያለችኝ ሲሆን እርሷን የግል ምሥጢረኛዬ አድርጌ በመመልከት የግል ችግሮቼን በመንገር ማስጨነቅ እንደሌለብኝ የምዘነጋበት ጊዜ አለ።” በብዙ ሺህ እንደሚቆጠሩት ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ነጠላ ወላጆች ሁሉ ጄነንም ሙሉ ቀን ተቀጥራ በመሥራት ቤተሰቧን ታስተዳድራለች። በተጨማሪም ልጆቿን መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናለች፣ በአገልግሎት ታሰለጥናቸዋለች እንዲሁም ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች ትወስዳቸዋለች። (ኤፌሶን 6:4) ይሖዋ ይህ ቤተሰብ የጸና አቋሙን ጠብቆ ለመኖር የሚያደርገውን ጥረት ሲመለከት ምን ያህል ይደሰት ይሆን! እንደነዚህ ያሉ ቤተሰቦች በመካከላችን በመኖራቸው የእኛም ልብ ደስ አይለውም? በእርግጥም፣ ደስ ይለዋል።
18, 19. ለጉባኤው አባላት ያለንን አድናቆት እንዴት ማሳደግ እንደምንችል በምሳሌ አስረዳ።
18 አሁንም ጉባኤህን ተመልከት። ከስብሰባ ፈጽሞ ‘የማይለዩ’ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ታማኝ ወንድሞችንና እህቶችን ትመለከት ይሆናል። (ሉቃስ 2:37) አልፎ አልፎ የብቸኝነት ስሜት ይሰማቸው ይሆን? ምንም ጥርጥር የለውም። የሚወዱትን የትዳር ጓደኛ ከአጠገባቸው ማጣታቸው በጣም ይሰማቸዋል! ይሁን እንጂ በይሖዋ አገልግሎት የተጠመዱ ከመሆናቸውም በላይ ለሌሎች ሰዎችም ያስባሉ። ያላቸው አዎንታዊና የተረጋጋ አመለካከት ለጉባኤው ደስታ አስተዋጽኦ ያደርጋል! በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት ያገለገለች አንዲት ክርስቲያን እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “የተለያዩ መከራዎችን አልፈው ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ያሉ በዕድሜ የገፉ ወንድሞችንና እህቶችን ስመለከት ደስታዬ እጥፍ ድርብ ይሆናል!” አዎን፣ በመካከላችን የሚገኙ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች ለወጣቶች ከፍተኛ የብርታት ምንጭ ናቸው።
19 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጉባኤው ጋር መተባበር ስለ ጀመሩ አዳዲስ ሰዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? በስብሰባዎች ላይ እምነታቸውን ሲገልጡ ስንሰማ አንበረታታም? መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ያደረጉትን እድገት አስብ። ይሖዋ እንደሚደሰትባቸው የተረጋገጠ ነው። እኛስ? ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋናችንንና አድናቆታችንን እንገልጽላቸዋለን?
20. እያንዳንዱ የጉባኤ አባል በጉባኤው ውስጥ ወሳኝ የሆነ ሚና ይጫወታል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
20 ያገባህ፣ ነጠላ ወይም ነጠላ ወላጅ ነህ? አባትህን ወይም እናትህን በሞት ያጣህ ልጅ ነህ? ወይም የትዳር ጓደኛህን በሞት ያጣህ ነህ? ከጉባኤው ጋር መተባበር ከጀመርክ ብዙ ዓመት ሆኖሃል? ወይስ አዲስ ነህ? በታማኝነት በመመላለስ የምታሳየው ምሳሌነት ሁላችንንም እንደሚያበረታታ እርግጠኛ ሁን። የመንግሥቱን መዝሙር አብረኸን ስትዘምር፣ ሐሳብ ስትሰጥ ወይም በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል ስታቀርብ ደስታችን እንዲጨምር የበኩልህን አስተዋጽዖ ታበረክታለህ። ከሁሉም በላይ ደግሞ የይሖዋን ልብ ደስ ታሰኛለህ።
21. ምን ነገር ለማድረግ የሚያበቁ በርካታ ምክንያቶች አሉን? ሆኖም ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?
21 አዎን፣ በዚህ በመከራ በተሞላ ጊዜ ብንኖርም እንኳ ደስተኛ የሆነውን አምላካችንን በማምለክ ደስተኞች ልንሆን እንችላለን። “ደኅና [“ደስተኞች፣” NW ] ሁኑ . . . የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል” በማለት ጳውሎስ ለሰጠው ማበረታቻ አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት የሚያበቁን በርካታ ምክንያቶች አሉን። (2 ቆሮንቶስ 13:11) ይሁን እንጂ የተፈጥሮ አደጋ፣ ስደት ወይም ከባድ የኢኮኖሚ ችግር በሚያጋጥመን ጊዜስ? እንዲህ የመሰሉ ሁኔታዎች በሚከሰቱበት ጊዜም ደስተኛ መሆን ይቻላል? የሚቀጥለውን ርዕስ በመመርመር የራስህ መደምደሚያ ላይ ልትደርስ ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 119 ተመልከት።
ልትመልስ ትችላለህ?
• ደስታ ምን ተብሎ ሊገለጽ ይችላል?
• አዎንታዊ የሆነ አስተሳሰብ መያዝ ደስተኞች ሆነን እንድንቀጥል የሚረዳን እንዴት ነው?
• ጉባኤያችን ላለው የአገልግሎት ክልል አዎንታዊ አመለካከት መያዝ እንድንችል ምን ነገር ሊረዳን ይችላል?
• በጉባኤህ ውስጥ ያሉትን ወንድሞችና እህቶች ከፍ አድርገህ እንደምትመለከታቸው የምታሳየው በምን መንገዶች ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ያሉት ሰዎች ሊለወጡ ይችላሉ
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጉባኤህ ውስጥ ያሉት አንዳንድ ክርስቲያኖች የሚቋቋሟቸው ፈታኝ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?