የትዳር ጓደኛ ለመምረጥ የሚረዳ መለኮታዊ መመሪያ
የትዳር ጓደኛ ለመምረጥ የሚረዳ መለኮታዊ መመሪያ
“አስተምርሃለሁ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ ዓይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ።”—መዝሙር 32:8
1. ስኬታማ ትዳር ለመመሥረት ምን ነገሮች አስፈላጊ ናቸው?
አንድ በአየር ላይ ትርዒት የሚያሳይ ስፖርተኛ ከጅዋጅዌው ገመድ ላይ ከተወነጨፈ በኋላ ሰውነቱን በማጠፍ አስገራሚ በሆነ መንገድ በአየር ላይ ይገለባበጣል። ከዚያ እንደገና ይዘረጋና በተቃራኒ አቅጣጫ ባለው የጅዋጅዌ ገመድ ላይ በእግሮቹ ተንጠልጥሎ የሚጠብቀውን ሌላ ስፖርተኛ እጅ ይይዛል። የበረዶ ላይ ትርዒት የሚያሳዩ አንድ ወንድና ሴት በመንሸራተቻው ክልል ውስጥ ያለ አንዳች ችግር ሲንሸራተቱ ይታያሉ። ከዚያ ወንድዬው በድንገት ያነሳትና ወደ ላይ ይወረውራታል። እሷም አየር ላይ እንደ እንዝርት ከሾረች በኋላ ሚዛኗን ጠብቃ በአንድ እግሯ በማረፍ እንደገና አብራው መንሸራተቷን ትቀጥላለች። ሁለቱም ትርዒቶች ቀላል ሊመስሉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በቂ ልምምድ ሳያደርግ፣ የሚተማመንበት ጓደኛ ሳይኖረውና በተለይ ደግሞ ትክክለኛ የሆነ መመሪያ የሚሰጠው ወይም የሚያሠለጥነው ሰው ሳይኖር እንዲህ ያለውን ትርዒት ለማቅረብ የሚደፍር ማን ይኖራል? በተመሳሳይም ጥሩ ትዳር እንዲሁ በአጋጣሚ የሚገኝ ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ ጥሩ ትዳርም ቢሆን በጥሩ ጓደኛ፣ በተቀናጀ ጥረትና በተለይ ደግሞ ጥበብ በተሞላበት ምክር ላይ የተመካ ነው። በእርግጥም ትክክለኛ መመሪያ ማግኘት የግድ አስፈላጊ ነው።
2. (ሀ) ጋብቻን ያቋቋመው ማን ነው? ለምንስ ዓላማ? (ለ) አንድ ትዳር የሚመሠረተው እንዴት ነው?
2 አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት ገና ያላገቡ ከሆኑ የትዳር ጓደኛ ማለትም የሕይወት አጋር ለማግኘት ማሰባቸው የተለመደ ነገር ነው። ይሖዋ አምላክ ትዳርን ካቋቋመበት ጊዜ አንስቶ አንድ ወንድና አንዲት ሴት በጋብቻ መጣመራቸው የተለመደ የሕይወት ክፍል ሆኗል። ይሁን እንጂ የመጀመሪያው ሰው አዳም ሚስት የምትሆነውን ሴት ራሱ አልመረጠም። ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ሚስት የምትሆነውን ሴት ሰጥቶታል። (ዘፍጥረት 2:18-24) ቀስ በቀስ ምድር በሰዎች እንድትሞላ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት መባዛት ነበረባቸው። ከዚያ የመጀመሪያ ጥምረት በኋላ የጋብቻ ዝግጅት አንዳንድ ጊዜ ሁለቱ ተጋቢዎች በሚያደርጉት ስምምነት በአብዛኛው ግን በሙሽሮቹ ወላጆች መከናወን ጀመረ። (ዘፍጥረት 21:21፤ 24:2-4, 58፤ 38:6፤ ኢያሱ 15:16, 17) በወላጆች ምርጫ የሚከናወነው ጋብቻ አሁንም ድረስ በአንዳንድ አካባቢዎችና ባሕሎች የተለመደ ቢሆንም በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የትዳር ጓደኛቸውን የሚመርጡት ራሳቸው ናቸው።
3. የትዳር ጓደኛ መመረጥ ያለበት እንዴት ነው?
3 የትዳር ጓደኛ መመረጥ ያለበት እንዴት ነው? አንዳንዶች በመልክ ማለትም በውጫዊ ውበት ይማረካሉ። ሌሎች ደግሞ በቁሳዊ ጥቅም ላይ በማተኮር ጥሩ አድርጎ የሚንከባከባቸውንና የሚፈልጉትን ሁሉ የሚያሟላላቸውን ሰው ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች በራሳቸው አስደሳችና አርኪ ትዳር መመሥረት ያስችላሉን? ምሳሌ 31:30 “ውበት ሐሰት ነው፣ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች” በማለት ይናገራል። ይህ ጥቅስ የትዳር ጓደኛ በምትመርጥበት ጊዜ በጉዳዩ ውስጥ ይሖዋ እንዲገባበት አድርግ የሚል በጣም አስፈላጊ መልእክትም ያስተላልፋል።
አምላክ የሚሰጠው ፍቅራዊ መመሪያ
4. አምላክ የትዳር ጓደኛን ለመምረጥ የሚያግዝ ምን ዝግጅት አድርጓል?
4 አፍቃሪ ሰማያዊ አባታችን ይሖዋ በማንኛውም ጉዳይ መመሪያ እንዲሆነን በጽሑፍ የሰፈረ ቃሉን ሰጥቶናል። እንዲህ ይላል:- “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።” (ኢሳይያስ 48:17) ስለሆነም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የትዳር ጓደኛን በመምረጥ ረገድ ለዘመናት የተፈተነ መመሪያ የሚገኝ መሆኑ ምንም አያስደንቅም። ይሖዋ ትዳራችን ዘላቂና ደስታ የሰፈነበት እንዲሆን ይፈልጋል። ስለዚህ ይህን መመሪያ እንድናስተውልና በሥራ ላይ እንድናውል ይረዳናል። አፍቃሪ ከሆነው ፈጣሪያችን የምንጠብቀው ነገር ይኸው አይደለም?—መዝሙር 19:8
5. በትዳር ውስጥ ዘላቂ ደስታ እንዲኖር ምን ነገር ወሳኝ ነው?
5 ይሖዋ ጋብቻን የመሠረተው የዕድሜ ልክ ጥምረት እንዲሆን በማሰብ ነው። (ማርቆስ 10:6-12፤ 1 ቆሮንቶስ 7:10, 11) ‘በዝሙት’ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ‘መፋታትን’ እንደሚጠላ የተናገረውም ለዚህ ነው። (ሚልክያስ 2:13-16፤ ማቴዎስ 19:9) ስለዚህ የትዳር ጓደኛን መምረጥ በሕይወታችን ውስጥ ከምናደርጋቸው ከባድ ውሳኔዎች መካከል አንዱ ስለሆነ እንደ ቀላል የሚታይ ነገር አይደለም። በሕይወታችን ውስጥ ወይ ለደስታ አሊያም ለሐዘን አስተዋጽዖ የሚያደርግ የዚህን ያህል ክብደት ያለው ውሳኔ የለም ለማለት ይቻላል። አንድ ሰው ጥሩ ምርጫ ካደረገ አስደሳችና አርኪ ሕይወት ይኖረዋል፤ የተሳሳተ ምርጫ ካደረገ ደግሞ ሕይወቱ መራራ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 21:19፤ 26:21) አምላክ ትዳርን ሲያቋቁም ዓላማው ስምምነትና ትብብር የሰፈነበት ጥምረት እንዲሆን ስለነበር ደስታው ዘላቂ እንዲሆን የትዳር ጓደኛን በጥበብ መምረጥና በማይበጠስ ቃል ኪዳን ተሳስሮ ለመኖር ፈቃደኛ መሆን አስፈላጊ ነው።—ማቴዎስ 19:6
6. በተለይ ወጣት ወንዶችና ሴቶች የትዳር ጓደኛ በሚመርጡበት ጊዜ ጠንቃቃ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው? ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ማድረግ የሚችሉትስ እንዴት ነው?
6 ወጣት ወንዶችና ሴቶች የትዳር ጓደኛ በሚመርጡበት ጊዜ በተለይ በውጫዊ ውበት ተማርከውና በስሜት ተገፋፍተው የተሳሳተ ውሳኔ እንዳያደርጉ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። ሙሉ በሙሉ እንደነዚህ ባሉት ነገሮች ላይ የተመሠረተ ግንኙነት በፍጥነት ሊሸረሸርና ከዚያም አልፎ ወደ ጥላቻ ሊያመራ ይችላል። (2 ሳሙኤል 13:15) በሌላ በኩል ደግሞ የትዳር ጓደኛችንን ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድና ለራሳችን ያለን ግንዛቤም በዚያው መጠን እያደገ ሲሄድ ዘላቂ የሆነ ፍቅር ለመኮትኮት ያስችላል። መጀመሪያ ላይ ልባችን የተመኘው ነገር ሁሉ ለእኛ ከሁሉ የተሻለ ነው ማለት እንዳልሆነ መገንዘብም ያስፈልገናል። (ኤርምያስ 17:9) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መለኮታዊ መመሪያ አስፈላጊ የሆነውም ለዚህ ነው። በሕይወታችን ውስጥ ጥበብ የተሞላባቸውን ውሳኔዎች ማድረግ የምንችልባቸውን መንገዶች እንድናስተውል ይረዳናል። መዝሙራዊው ይሖዋን በመወከል “አስተምርሃለሁ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ ዓይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 32:8፤ ዕብራውያን 4:12) ትዳር ለፍቅርና ለጓደኝነት ያለንን ተፈጥሯዊ ፍላጎታችንን ሊያረካልን ቢችልም ጉልምስናና ማስተዋል የሚጠይቁ ጎኖችም አሉት።
7. አንዳንዶች የትዳር ጓደኛን በመምረጥ ረገድ የሚሰጣቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር የማይቀበሉት ለምንድን ነው? ይህስ ምን ሊያስከትልባቸው ይችላል?
7 የትዳር ጓደኛን በመምረጥ ረገድ የጋብቻ መሥራች የሆነው አምላክ ምን እንደሚል ማዳመጥ የጥበብ እርምጃ ነው። ሆኖም ወላጆች ወይም ክርስቲያን ሽማግሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር በሚሰጡን ጊዜ ምክሩን ለመቀበል አሻፈረኝ እንል ይሆናል። ሙሉ በሙሉ እንዳልተረዱን ሆኖ ይሰማን አሊያም ጠንካራ ስሜታዊ ፍላጎታችን የልባችንን ዝንባሌ እንድንከተል ይገፋፋን ይሆናል። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ከእውነታው ጋር ስንፋጠጥ ለእኛ ጥቅም ብለው የሰጡንን ጥበብ የተሞላበት ምክራቸውን ሳንቀበል በመቅረታችን እንድንቆጭ ሊያደርገን ይችላል። (ምሳሌ 23:19፤ 28:26) ምንም ፍቅር የሌለው ትዳር ልንመሠርት፣ ልጆችን ማሳደግ ሊቸግረን እንዲሁም ከማያምን የትዳር ጓደኛ ጋር ለመኖር ልንገደድ እንችላለን። ከፍተኛ ደስታ ልናገኝበት ይገባ የነበረው ዝግጅት ለሐዘንና ለብስጭት የሚዳርግ ሆኖ ሲገኝ ምንኛ ያሳዝናል!
ለአምላክ ያደሩ መሆን—ወሳኝ የሆነ ባሕርይ
8. ለአምላክ ያደሩ መሆን ትዳር ዘላቂና ደስታ የሰፈነበት እንዲሆን የሚረዳው እንዴት ነው?
8 አንዳቸው በሌላው ፍቅር እንዲማረኩ የሚያደርግ ነገር መኖሩ ትዳርን እንደሚያጠናክር አይካድም። ሆኖም የጋራ መመሪያ መኖሩ ጥምረቱ እንዲጸናና ደስታ የሰፈነበት እንዲሆን ለማድረግ የበለጠ አስፈላጊ ነው። ሁለቱም ተጋቢዎች ለይሖዋ አምላክ ያደሩ መሆናቸው ጥምረቱን ዘላቂ እንዲሆን ከማድረጉም በተጨማሪ ሌላ ምንም ነገር ሊያደርገው ከሚችለው በላይ አንድነት እንዲሰፍን ሊያደርግ ይችላል። (መክብብ 4:12) ክርስቲያን የሆኑ ባልና ሚስት ሕይወታቸውን በእውነተኛው የይሖዋ አምልኮ ዙሪያ እንዲያተኩር ካደረጉ መንፈሳዊ፣ አእምሮአዊና ሥነ ምግባራዊ አንድነት ይኖራቸዋል። የአምላክን ቃል አንድ ላይ ያጠናሉ። አብረው ይጸልያሉ። ይህም ልባቸውን አንድ ያደርግላቸዋል። አንድ ላይ ሆነው ወደ ክርስቲያን ስብሰባዎች ይሄዳሉ እንዲሁም በመስክ አገልግሎት አብረው ይሠማራሉ። ይህ ሁሉ እርስ በርሳቸው ይበልጥ እንዲቀራረቡ የሚያደርግ መንፈሳዊ ትስስር እንዲኖር ይረዳል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የይሖዋን በረከት ያስገኝላቸዋል።
9. አብርሃም ለይስሐቅ ሚስት የምትሆነውን ሴት ለመፈለግ ምን አደረገ? ውጤቱስ ምን ሆነ?
9 ታማኙ ፓትሪያርክ አብርሃም ለአምላክ ያደረ ሰው ስለነበር ለልጁ ለይስሐቅ ሚስት በሚመርጥበት ጊዜ አምላክን ማስደሰት ፈለገ። አብርሃም ለታመነው ሎሌው እንዲህ አለው:- “እኔም አብሬ ከምኖራቸው ከከነዓን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስት እንዳትወስድለት በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ፤ ነገር ግን ወደ አገሬና ወደ ተወላጆቼ ትሄዳለህ፣ ለልጄ ለይስሐቅም ሚስትን ትወስድለታለህ። . . . እርሱ [ይሖዋ] መልአኩን በፊትህ ይሰድዳል፣ ከዚያም ለልጄ ሚስትን ትወስዳለህ።” ርብቃ ጥሩ ሚስት ሆና የተገኘች ሲሆን ይስሐቅም ከልቡ ወድዷታል።—ዘፍጥረት 24:3, 4, 7, 14-21, 67
10. ባሎችም ሆኑ ሚስቶች ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ ተጥሎባቸዋል?
10 ገና ያላገባን ክርስቲያኖች ከሆንን ለአምላክ ያደሩ መሆን ትዳርን በተመለከተ ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆኑትን ብቃቶች እንድናሟላ ይረዳናል። ባሎችና ሚስቶች ሊያሟሏቸው ከሚገቡ በርካታ ግዴታዎች መካከል አንዳንዶቹን ጳውሎስ እንዲህ በማለት አስቀምጧቸዋል:- “ሚስቶች ሆይ፣ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ . . . ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ . . . ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። . . . ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት፣ ሚስቱም ባልዋን ትፍራ [“በጥልቅ ታክብረው፣” NW ]።” (ኤፌሶን 5:22-33) ከዚህ ለማየት እንደምንችለው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት የጳውሎስ ቃላት የፍቅርንና የአክብሮትን አስፈላጊነት ያጎላሉ። ይህን ምክር መፈጸም ማለት ለይሖዋ አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳየት ማለት ነው። ይህም በደስታም ሆነ በመከራ ጊዜ አብሮ ለመኖር ከልብ ቃል ኪዳን መግባትን ይጠይቃል። ለማግባት የሚያስቡ ክርስቲያኖች ሁሉ ይህን ኃላፊነት መሸከም መቻል ይኖርባቸዋል።
ትዳር የምንመሠርትበትን ዕድሜ መወሰን
11. (ሀ) ትዳር የምንመሠርትበትን ጊዜ በማስመልከት በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ምን ምክር ሰፍሮ ይገኛል? (ለ) በ1 ቆሮንቶስ 7:36 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መከተሉ ጥበብ እንደሆነ የትኛው ምሳሌ ያሳያል?
11 ለማግባት ዝግጁ የምንሆነው መቼ እንደሆነ ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ከሰው ወደ ሰው የሚለያይ ስለሆነ ቅዱሳን ጽሑፎች በዚህ ረገድ የዕድሜ ገደብ አያበጁም። ይሁን እንጂ ሚዛናዊ አመለካከታችንን ሊያዛባብን የሚችለው የጾታ ስሜት የሚያይልበት ‘አፍላ የጉርምስና ዕድሜ’ እስኪያልፍ ድረስ መጠበቅ ጥሩ እንደሆነ ይጠቁማሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:36 NW ) ሚሼል “በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ብዙዎቹ ጓደኞቼ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥረው ሲጫወቱ እንዲሁም ሲያገቡ ስመለከት አልፎ አልፎ ይህን ምክር መከተሉ አስቸጋሪ ይሆንብኛል” በማለት ተናግራለች። “ይሁን እንጂ ይህ ምክር ከይሖዋ የመጣ እንደሆነ አውቃለሁ፤ እርሱ ደግሞ የሚነግረን ለእኛ የሚጠቅመንን ብቻ ነው። ለትዳር ብቁ እስከምሆንበት ጊዜ ድረስ ከይሖዋ ጋር በመሠረትኩት ዝምድና ላይ ላተኩር እንዲሁም በአብዛኛው በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የማይገኙትን የተወሰኑ ተሞክሮዎችን ላገኝ ችዬአለሁ። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ትዳር የሚያስከትላቸውን ኃላፊነቶች ለመሸከምም ሆነ በትዳር ውስጥ ሊነሱ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት በተሻለ መንገድ ዝግጁ ልሆን ችያለሁ።”
12. ገና በልጅነት ተቻኩሎ ማግባት ጥበብ ያልሆነው ለምንድን ነው?
12 ገና ልጅ እያሉ ለማግባት የሚቻኮሉ ሁሉ ብዙውን ጊዜ እየበሰሉ በሚሄዱበት ጊዜ ፍላጎታቸውና ምኞታቸው ሲለወጥ ይመለከታሉ። መጀመሪያ ላይ የጓጉለት ነገር ከጊዜ በኋላ ያሰቡትን ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። አንዲት ወጣት ክርስቲያን በ16 ዓመቷ ማግባት አለብኝ ብላ ትወስናለች። አያቷም ሆኑ እናቷ ያገቡት በዚህ ዕድሜ ላይ ነበር። ቀልቧ ያረፈበት ወጣት ሊያገባት እንደማይፈልግ በነገራት ጊዜ ፈቃደኛ የሆነ ሌላ ወንድ አገባች። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ተቻኩላ ባደረገችው ውሳኔ በጣም ተጸጽታለች።
13. ዕድሜያቸው ሳይደርስ የሚያገቡ ወጣቶች ብዙውን ጊዜ የሚጎድላቸው ነገር ምንድን ነው?
13 ለማግባት በምታስቡበት ጊዜ ትዳር የሚጠይቃቸውን ነገሮች ሁሉ በብስለትና በማስተዋል ማጤኑ ጥሩ ይሆናል። ዕድሜያቸው ሳይደርስ የሚያገቡ ወጣቶች የሚመሠርቱት ጋብቻ ሊቋቋሟቸው የማይችሏቸውን ብዙ ችግሮች ሊያስከትል ይችላል። ትዳርና ልጆችን ማሳደግ የሚያስከትሉትን ውጥረት ለመቋቋም የሚያስችል ተሞክሮም ሆነ ብስለት ሊጎድላቸው ይችላል። ትዳር መመሥረት የሚኖርብን ትዳር የሚያስከትለውን ኃላፊነት መሸከም የሚያስችል አካላዊ፣ አእምሮአዊና መንፈሳዊ ብስለት ሲኖረን መሆን አለበት።
14. በትዳር ውስጥ ውጥረት የሚያስከትሉ ሁኔታዎችን ለመፍታት ምን ያስፈልጋል?
14 ጳውሎስ የሚያገቡ “በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 7:28) ተጋቢዎቹ ፈጽሞ የተለያዩ ባሕርያትና የአመለካከት ልዩነቶች ያሏቸው በመሆናቸው ችግሮች ይነሳሉ። በሰብዓዊ አለፍጽምና ምክንያት በጋብቻ ዝግጅት ውስጥ ያሉብንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታዎች ሙሉ በሙሉ መፈጸም አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ቆላስይስ 3:18, 19፤ ቲቶ 2:4, 5፤ 1 ጴጥሮስ 3:1, 2, 7) ውጥረት ውስጥ የሚከቱ ሁኔታዎች በሚነሱበት ጊዜ መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት መፈለግና በዚያ መሠረት ችግሩን መፍታት ጉልምስናና መንፈሳዊ ብስለት ይጠይቃል።
15. ወላጆች ልጆቻቸውን ለትዳር በማዘጋጀት ረገድ ምን ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ? ምሳሌ ስጥ።
15 ወላጆች መለኮታዊ መመሪያ መከተል ያለውን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ በመርዳት ልጆቻቸውን ለትዳር ሊያዘጋጁ ይችላሉ። ልጆች ራሳቸውም ሆኑ ለትዳር ያሰቡት ሰው ጋብቻ የሚያስከትለውን ኃላፊነት ለመሸከም ዝግጁ መሆን አለመሆናቸውን መወሰን ይችሉ ዘንድ ወላጆች በቅዱሳን ጽሑፎችና በክርስቲያናዊ ጽሑፎች ጥሩ አድርገው በመጠቀም ሊረዷቸው ይችላሉ። a የአሥራ ስምንት ዓመቷ ብሎሰም ጉባኤዋ ከሚገኝ ከአንድ ወጣት ጋር ፍቅር ይይዛታል። እርሱ የሙሉ ጊዜ አቅኚ አገልጋይ ሲሆን ሁለቱም ለመጋባት ተስማሙ። ሆኖም ወላጆቿ ገና ለትዳር እንዳልደረሰች ስለተሰማቸው አንድ ዓመት እንድትቆይ ጠየቋት። ብሎሰም እንዲህ በማለት ጻፈች:- “ይህን ጥበብ የተሞላበት ምክር በመስማቴ በጣም አመስጋኝ ነኝ። በዚህ የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የተወሰነ ጉልምስና ያገኘሁ ሲሆን ይህ ወጣት ጥሩ የትዳር ጓደኛ ለመሆን የሚያበቁ ባሕርያት እንደሚጎድሉት መገንዘብ ጀመርኩ። በመጨረሻ ድርጅቱን ጥሎ ሄደ፤ በሕይወቴ ውስጥ ሊገጥመኝ ከሚችል እጅግ አሳዛኝ ከሆነ ሁኔታ ልተርፍ ችያለሁ። ትክክለኛ ምክር የሚለግሱ አስተዋይ የሆኑ ወላጆች ማግኘት ምንኛ መታደል ነው!”
‘በጌታ ብቻ አግቡ’
16. (ሀ) ‘በጌታ ብቻ ይሁን’ የሚለው መመሪያ ክርስቲያኖችን ሊፈትን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ክርስቲያኖች የማያምን ሰው እንዲያገቡ በሚፈተኑበት ጊዜ ምን ነገር ማስታወስ ይኖርባቸዋል?
16 ይሖዋ ለክርስቲያኖች የሰጠው መመሪያ ምንም የማያሻማ ነው። ‘በጌታ ብቻ ይሁን’ ይላል። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ክርስቲያን ወላጆችና ልጆቻቸው በዚህ ረገድ ፈተና ላይ ሊወድቁ ይችላሉ። እንዴት? ወጣቶች ማግባት ይፈልጉ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በጉባኤ ውስጥ ተጓዳኝ የሚሆናቸው ሰው አይኖር ይሆናል። በተወሰነ መጠን እንደዚያ ይመስላል። ምናልባት በአንድ አካባቢ ያሉት የወንዶች ቁጥር ከሴቶቹ ያነሰ ሊሆን ይችላል ወይም ተስማሚ የሚሆናቸው ሰው በዚያ አካባቢ አያገኙ ይሆናል። ራሱን ለይሖዋ ያልወሰነ አንድ ወጣት በአንዲት ክርስቲያን ሴት ላይ ዓይኑን ሊጥል ይችላል። (ወይም በተቃራኒው አንዲት ወጣት ሴት በአንድ ክርስቲያን ወጣት ላይ ዓይኗን ልትጥል ትችላለች።) እንዲሁም ይሖዋ ያወጣቸውን የአቋም ደረጃዎች እንዲያላሉ የሚያደርጉ ተጽእኖዎች ይኖራሉ። እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ አብርሃም የተወውን ምሳሌ ማስታወሱ ጥሩ ይሆናል። አብርሃም ከአምላክ ጋር የነበረውን ጥሩ ዝምድና ጠብቆ እንደቆየ ያሳየበት አንደኛው መንገድ ልጁ ይስሐቅ እውነተኛ የይሖዋ አምላኪ የሆነች ሴት እንዲያገባ በማድረግ ነው። ይስሐቅም ለልጁ ለያዕቆብ ተመሳሳይ ነገር አድርጓል። ይህ ሁኔታ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቆባቸዋል። ይሁን እንጂ አምላክን አስደስተዋል በአጸፋውም የእርሱን በረከት አግኝተዋል።—ዘፍጥረት 28:1-4
17. የማያምን ሰው ማግባት በአብዛኛው ጎጂ የሚሆነው ለምንድን ነው? ‘በጌታ ብቻ እንድናገባ’ የሚያስገድደን ከሁሉ የበለጠው ምክንያት ምንድን ነው?
17 የማያምነው የትዳር ጓደኛ ውሎ አድሮ ክርስቲያን ሊሆን የሚችልባቸው በጣም ጥቂት አጋጣሚዎች ይኖሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከማያምን ሰው ጋር በትዳር መቆራኘት በአብዛኛው ውጤቱ መራራ ነው። በማይመች አካሄድ የተጠመዱት የትዳር ጓደኛሞች አንድ ዓይነት እምነት፣ የአቋም ደረጃ ወይም ግብ አይኖራቸውም። (2 ቆሮንቶስ 6:14) ይህም እርስ በርስ የሐሳብ ልውውጥ እንዳይኖርና በትዳር ውስጥ ደስታ እንዲጠፋ ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ክርስቲያን በሚያንጽ ስብሰባ ላይ ከተገኘች በኋላ እቤት ስትመለስ ከማያምነው የትዳር ጓደኛዋ ጋር መንፈሳዊ ጉዳዮችን አንስታ መወያየት አለመቻሏ በጣም ሊያበሳጫት ይችላል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ‘በጌታ ብቻ ማግባት’ ለይሖዋ ታማኝ የመሆን ጉዳይ ነው። ከአምላክ ቃል ጋር ተስማምተን ስንሄድ ‘በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን ስለምናደርግ’ ልባችን አይፈርድብንም።—1 ዮሐንስ 3:21, 22
18. አንድ ሰው ለማግባት በሚያስብበት ጊዜ ትኩረት መስጠት ያለበት ለየትኞቹ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ነው? ለምንስ?
18 አንድ ሰው ማግባት በሚያስብበት ጊዜ የወደፊቱ የትዳር ጓደኛውን በተመለከተ በዋነኝነት ሊያሳስበው የሚገባው ጉዳይ መልካም ምግባርና መንፈሳዊነት መሆን አለበት። ከውጫዊ ውበት ይበልጥ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ግለሰቡ ክርስቲያናዊ ባሕርይ የተላበሰ፣ ለአምላክ ፍቅር ያለውና በሙሉ ነፍሱ ለእርሱ ያደረ መሆኑ ነው። በመንፈሳዊ ጠንካራ የትዳር ጓደኛ የመሆን ግዴታቸውን የሚገነዘቡና ይህን ግዴታቸውን የሚወጡ ሁሉ መለኮታዊ ሞገስ ያገኛሉ። አንድ ባልና ሚስት ከሁሉ ይበልጥ ትዳራቸውን ጠንካራ የሚያደርግላቸው ለፈጣሪ ያደሩ መሆናቸውና መመሪያዎቹን ሙሉ በሙሉ መቀበላቸው ነው። ይህም ይሖዋ እንዲከበር ያደርጋል፤ እንዲሁም ጋብቻው ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ጥምረት ያለው ጠንካራ በሆነ መንፈሳዊ መሠረት ላይ የተጣለ ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የየካቲት 15, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 4-8ን ተመልከት።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
• ጥሩ የትዳር ጓደኛ ለመምረጥ መለኮታዊ መመሪያ መከተል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• ለአምላክ የማደር ባሕርይ የጋብቻን ጥምረት የሚያጠነክረው እንዴት ነው?
• ወላጆች ልጆቻቸውን ለትዳር ማዘጋጀት የሚችሉት እንዴት ነው?
• ‘በጌታ ብቻ ማግባት’ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የትዳር ጓደኛን በመምረጥ ረገድ የአምላክን ምክር ተግባራዊ ማድረግህ ከፍተኛ ደስታ ሊያስገኝልህ ይችላል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘በጌታ ብቻ ማግባት ’ ብዙ በረከቶች ያስገኛል