ወላጆች የሌላቸውን ልጆች እና መበለቶችን በመከራቸው መጠየቅ
ወላጆች የሌላቸውን ልጆች እና መበለቶችን በመከራቸው መጠየቅ
የምንኖረው ፍቅር በጠፋበት ዓለም ውስጥ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “በመጨረሻው ቀን” የሚኖሩ ሰዎችን በማስመልከት ሲናገር “የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ . . . ፍቅር የሌላቸው” ይሆናሉ በማለት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-3) እነዚህ ቃላት ምንኛ ትክክል ናቸው!
የርኅራኄ ስሜት ከብዙዎች ልብ ውስጥ እንዲጠፋ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ በጊዜያችን ያለው የሥነ ምግባር ሁኔታ ነው። ሰዎች ለሌሎች ደህንነት በአንዳንድ ወቅትም ለራሳቸው ቤተሰብ አባላት እንኳ ሳይቀር የሚሰጡት ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መጥቷል።
ይህ ሁኔታ በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ላይ በወደቁ በርካታ ሰዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል። ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋና ሰዎች መጠለያ ለማግኘት ከቦታ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የመበለቶችና ወላጆች የሌላቸው ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ እንዲሄድ አድርገዋል። (መክብብ 3:19) ከተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት የወጣ አንድ ዘገባ “በጦርነት ሳቢያ ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ [ሕፃናት] ያለ ወላጅ ቀርተዋል አሊያም ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተዋል” ሲል ገልጿል። በተጨማሪም ኑሮን ለማሸነፍና ለብቻቸው ሆነው ልጆቻቸውን ለማሳደግ ደፋ ቀና የሚሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነጠላ የሆኑ፣ ባሎቻቸው ጥለዋቸው የሄዱ ወይም የተፈቱ እናቶችን ታውቅ ይሆናል። አንዳንድ አገሮች ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ የገጠማቸው መሆኑና በዚህም የተነሳ አብዛኞቹ ዜጎቻቸው በከፍተኛ የድህነት ማጥ ውስጥ የሚኖሩ መሆናቸው ሁኔታውን ይበልጥ ያባብሰዋል።
ከዚህ አንጻር በመከራ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የሚሆን ተስፋ ይኖር ይሆን? መበለቶችና ወላጆች የሌላቸው ልጆች የሚደርስባቸው መከራ ሊቃለል የሚችለው እንዴት ነው? ይህ ችግር የሚወገድበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የተሰጠ ፍቅራዊ እንክብካቤ
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን መበለቶችና ወላጆች የሌላቸው ልጆች በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማሟላት ለአምላክ የሚቀርብ አምልኮ ክፍል ሆኖ ቆይቷል። እስራኤላውያን የእርሻቸውን ሰብል ወይም ፍራፍሬ በሚሰበስቡበት ጊዜ ማሳው ላይ የቀረውን ቃርሚያ መሰብሰብ አልነበረባቸውም። ቃርሚያውን “ለመጻተኛና ለድሀ አደግ ለመበለትም” መተው ነበረባቸው። ዘዳግም 24:19-21) የሙሴ ሕግ “መበለቲቱንና ድሀ አደጎቹን አታስጨንቁአቸው” ሲል በግልጽ ይናገራል። (ዘጸአት 22:22, 23) ባልየውና አባትየው ወይም ሁለቱም ወላጆች በሚሞቱበት ጊዜ በሕይወት የቀሩት የቤተሰቡ አባላት ብቻቸውን ሊቀሩና ችግር ላይ ሊወድቁ ስለሚችሉ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መበለቶችና ወላጆች የሌላቸው ልጆች ድሀ እንደሆኑ ተደርገው መጠቀሳቸው የተገባ ነው። ፓትሪያርኩ ኢዮብ “የሚጮኸውን ችግረኛ፣ ድሀ አደጉንና ረጂ የሌለውን አድኜ ነበርሁ” በማለት ተናግሯል።—ኢዮብ 29:12
(በክርስቲያን ጉባኤ የቀድሞዎቹ ዘመናት ወላጆቻቸውን ወይም ባላቸውን በሞት በማጣታቸው ምክንያት መከራ ለሚደርስባቸውና በእርግጥ ችግረኛ ለሆኑ ሰዎች እርዳታ መስጠት የእውነተኛው አምልኮ ልዩ ገጽታ ነበር። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንደዚህ ላሉ ሰዎች ደህንነት ልባዊ አሳቢነት በመያዝ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፣ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።”—ያዕቆብ 1:27
ያዕቆብ ወላጆች የሌላቸውን ልጆችና መበለቶችን ጠቅሶ ከመናገሩም በተጨማሪ ድሀ ለሆኑና ከፍተኛ ችግር ላለባቸው ሌሎች ሰዎችም ጥልቅ አሳቢነት አሳይቷል። (ያዕቆብ 2:5, 6, 15, 16) ሐዋርያው ጳውሎስም ተመሳሳይ የአሳቢነት ስሜት አሳይቷል። እሱና በርናባስ ለስብከት በተላኩ ጊዜ ከተሰጣቸው መመሪያ መካከል ‘ድሆችን ማሰብ’ ይገኝበታል። ጳውሎስ “ይህንም ደግሞ ላደርግ ተጋሁ” ሲል በንጹሕ ሕሊና ሊናገር ችሏል። (ገላትያ 2:9, 10) የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ስለነበረው እንቅስቃሴ የቀረበው ዘገባ እንዲህ ይላል:- “በመካከላቸው አንድ ስንኳ ችግረኛ አልነበረም . . . ማናቸውም እንደሚፈልግ መጠን ለእያንዳንዱ ያካፍሉት ነበር።” (ሥራ 4:34, 35) አዎን፣ በጥንቷ እስራኤል ወላጆች የሌላቸውን ልጆች፣ መበለቶችንና ችግረኞችን ለመርዳት የተደረገው ዝግጅት ወደ ክርስቲያን ጉባኤም ተሸጋግሯል።
እርግጥ ነው፣ የሚሰጠው እርዳታ የተወሰነና ከጉባኤው አቅም ጋር የሚመጣጠን ነበር። ገንዘብ እንዲባክን አይደረግም፤ እርዳታ የተሰጣቸውም በእርግጥ ችግረኞች ነበሩ። ማንኛውም ክርስቲያን ከዚህ ዝግጅት ተገቢ ያልሆነ ጥቅም እንዲያገኝ አይፈቀድለትም። እንዲሁም በጉባኤው ላይ አላስፈላጊ ሸክም አይጨመርም ነበር። ጳውሎስ በ1 ጢሞቴዎስ 5:3-16 ላይ ባሰፈረው መመሪያ ውስጥ ይህ በግልጽ ተቀምጧል። በጥቅሱ መሠረት በችግር ላይ የወደቁት ግለሰቦች ዘመዶች አቅም ካላቸውና መርዳት ከቻሉ ይህን ኃላፊነት ይወስዱ ነበር። ችግረኛ መበለቶች እርዳታ ለማግኘት ብቁ ለመሆን አንዳንድ መሥፈርቶችን ማሟላት ነበረባቸው። ይህ ሁሉ ይሖዋ በችግር ላይ ያሉትን ለመንከባከብ የሚጠቀምበትን ጥበብ የተሞላ ዝግጅት ያሳያል። ይሁን እንጂ ማንኛውም ሰው በዚህ የደግነት ዝግጅት አላግባብ እንዳይጠቀም ሚዛናዊ መሆን እንደሚያስፈልግም ያሳያል።—2 ተሰሎንቄ 3:10-12
በዛሬው ጊዜ ወላጆች የሌላቸውን ልጆችና መበለቶችን መንከባከብ
መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች አሳቢነት ማሳየትንና እርዳታ መስጠትን በተመለከተ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ጥንት የአምላክ አገልጋዮች ይከተሏቸው የነበሩትን መሠረታዊ ሥርዓቶች አሁንም ተግባራዊ ያደርጋሉ። ይህ ኢየሱስ እንደተናገረው የወንድማማች መዋደድን ለይቶ የሚያሳውቅ ገጽታ ነው:- “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐንስ 13:35) አንዳንዶች ችግር ከደረሰባቸው ወይም የተፈጥሮ አደጋ ወይም የጦርነት ወይም የእርስ በርስ ብጥብጥ ሰለባ ከሆኑ የተቀረው ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር መንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ እርዳታ መስጠት የሚቻልባቸውን መንገዶች በንቃት ይከታተላል። በዚህ ረገድ እየተደረገ ያለውን ነገር የሚያሳዩ በጊዜያችን የተፈጸሙ አንዳንድ ተሞክሮዎችን እስቲ እንመልከት።
ፔድሮ እናቱ የሞተችው ገና የአንድ ዓመት ተኩል ልጅ እያለ ሲሆን ስለ እናቱ እምብዛም የሚያስታውሰው ነገር የለም። ፔድሮ የአምስት ዓመት ልጅ ሳለ አባቱም ሞተ። በመሆኑም ፔድሮ ከወንድሞቹ ጋር ብቻውን ቀረ። የይሖዋ ምሥክሮች ቀደም ሲል አባትየውን ያነጋግሩ ነበር፤ በመሆኑም ፔድሮ እና ታላቅ ወንድሞቹ በሙሉ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይደረግላቸው ጀመር።
ፔድሮ እንዲህ ይላል:- “በቀጣዩ ሳምንት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርን። ከወንድሞች ጋር እየተቀራረብን ስንሄድ ለእኛ ያላቸውን ፍቅር መገንዘብ ጀመርን። ወንድሞችና እህቶች ልክ እንደ ወላጅ ሆነው ፍቅርና አሳቢነት ስላሳዩኝ ጉባኤው ጥሩ መጠለያ ሆኖልኝ ነበር።” ፔድሮ ከክርስቲያን ሽማግሌዎች አንዱ ወደ ቤቱ ይጋብዘው እንደነበር ያስታውሳል። ፔድሮ እዚያ ሄዶ ከቤተሰቡ ጋር ይጫወትና ይዝናና ነበር። በ11 ዓመቱ ለሌሎች ስለ እምነቱ መስበክ የጀመረውና በ15 ዓመቱ የተጠመቀው ፔድሮ “እነዚያ ፈጽሞ የማልረሳቸው ጊዜያት ናቸው” ብሏል። በተመሳሳይ ታላቅ ወንድሞቹም በጉባኤው አባላት እርዳታ በመንፈሳዊ ከፍተኛ እድገት አድርገዋል።
የዳቪድ ተሞክሮም አለ። ወላጆቻቸው ሲለያዩ ከመንትዬ እህቱ ጋር ብቻቸውን ቀሩ። አያቶቻቸውና አክስታቸው ወስደው አሳደጓቸው። “ነፍስ አውቀን ያለፈውን ነገር ሁሉ መገንዘብ ስንጀምር በስጋትና በከፍተኛ የሐዘን ስሜት ተዋጥን። አለኝታ የሚሆነን ሰው ያስፈልገን ነበር። አክስቴ የይሖዋ ምሥክር ሆነች፤ በዚህም ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተማርን። ወንድሞች ፍቅርና ወዳጅነት አሳዩን። በጣም ይወድዱን የነበረ ከመሆኑም በላይ የተለያዩ ግቦችን እንድናወጣና ይሖዋን ማገልገላችንን እንድንቀጥል አበረታተውናል። አሥር ዓመት ገደማ ሲሆነኝ አንድ የጉባኤ አገልጋይ በመስክ አገልግሎት አብሬው እንዳገለግል እየመጣ ይወስደኝ ነበር። ሌላ ወንድም ደግሞ አውራጃ ስብሰባዎች ላይ ስገኝ ወጪዎቼን ይሸፍንልኝ ነበር። እንዲያውም አንድ ወንድም በሚያደርግልኝ እርዳታ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ መዋጮ እስከ ማድረግ ደርሼ ነበር።”
ዳቪድ 17 ዓመት ሲሞላው የተጠመቀ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ሜክሲኮ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ማገልገል ጀመረ። አሁንም አመስጋኝነቱን እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “እውቀትና ጠቃሚ ምክር እንዳገኝ የረዱኝ በርካታ ሽማግሌዎች አሉ። በዚህ መንገድ የሚሰማኝን ያለመረጋጋትና የብቸኝነት ስሜት ማሸነፍ ችያለሁ።”
እርዳታ የሚያስፈልጋቸው በርካታ መበለቶች ባሉበት ሜክሲኮ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው አቤል እንዲህ ይላል:- “መበለቶቹ የሚያስፈልጋቸው በጣም አንገብጋቢ የሆነው እርዳታ ስሜታዊ ድጋፍ እንደሆነ አምናለሁ። አንዳንድ ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት ያድርባቸዋል፤ ብቸኝነትም ይሰማቸዋል። በመሆኑም ችግራቸውን ማዳመጥና ድጋፍ መስጠት በጣም አስፈላጊ ነው። እኛ [የጉባኤው ሽማግሌዎች] አዘውትረን እንጎበኛቸዋለን። ጊዜ ወስዶ ለችግሮቻቸው ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ነው። ይህም በመንፈሳዊ ሁኔታ መጽናናት እንዲያገኙ ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታል።” ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ቁሳዊ እርዳታ ማድረግም አስፈላጊ ነው። ከጥቂት ጊዜ በፊት አቤል እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በአሁኑ ጊዜ መበለት ለሆነች አንዲት እህት ቤት እየሠራን ነው። በተወሰኑ ቅዳሜዎችና በሳምንቱ መሃል ደግሞ አንዳንድ ከሰዓት በኋላዎች በመገናኘት ቤቷን ሠርተንላታል።”
አንድ ሌላ የጉባኤ ሽማግሌ ወላጆች ለሌላቸው ልጆችና ለመበለቶች እርዳታ በመስጠት ረገድ የራሱን ተሞክሮ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ወላጆች የሌላቸው ልጆች ከመበለቶች በበለጠ በከፍተኛ ሁኔታ ክርስቲያናዊ ፍቅር ማግኘት ያሻቸዋል የሚል እምነት አለኝ። አባትና እናት ካሏቸው ልጆችና ወጣቶች ይልቅ እነርሱ ይበልጥ እንደተጣሉ ሆኖ እንደሚሰማቸው አስተውያለሁ። ወንድማዊ ፍቅር እንዳለን ደጋግመን ልንገልጽላቸው ያስፈልገናል። ከስብሰባዎች በኋላ ፈልገን አግኝተናቸው ስለ ደህንነታቸው ብንጠይቃቸው ጥሩ ነው። ገና ልጅ እያለ ወላጆቹን በሞት አጥቶ የነበረ አንድ ባለትዳር ወንድም አለ። ስብሰባ ላይ ስንገናኝ ሞቅ ያለ ሰላምታ እሰጠው ነበር። እሱም ሲያየኝ መጥቶ ያቅፈኛል። ይህም የእውነተኛ ወንድማማችነትን ፍቅር ማሰሪያ ያጠናክራል።”
ይሖዋ ‘ችግረኛውን ያድናል’
መበለቶችና ወላጆች የሌላቸው ልጆች ያሉበትን ሁኔታ ስኬታማ በሆነ መንገድ ለመወጣት በይሖዋ ላይ መታመን ወሳኝ ነገር ነው። እሱን በተመለከተ እንዲህ ተብሏል:- “እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፤ ድሀ አደጎችንና ባልቴቶችን ይቀበላል።” (መዝሙር 146:9) እንደነዚህ ያሉት ችግሮች ሥር ነቀል መፍትሔ የሚያገኙት በኢየሱስ ክርስቶስ በሚመራው የአምላክ መንግሥት አማካኝነት ብቻ ነው። መዝሙራዊው የመሲሑን አገዛዝ በትንቢታዊ ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል።”—መዝሙር 72:12, 13
የአሁኑ የነገሮች ሥርዓት መጨረሻ ይበልጥ እየተቃረበ ሲመጣ ክርስቲያኖች ባጠቃላይ የሚጋፈጧቸው ጫናዎች መጨመራቸው የማይቀር ነው። (ማቴዎስ 24:9-13) በየቀኑ ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላው ይበልጥ አሳቢነት ማሳየታቸውና ‘እርስ በርሳቸው አጥብቀው መዋደዳቸው’ አስፈላጊ ነው። (1 ጴጥሮስ 4:7-10) ክርስቲያን ወንዶች በተለይ ደግሞ ሽማግሌዎች ወላጆች ለሌላቸው ልጆች አሳቢነትና ርኅራኄ ማሳየት ይገባቸዋል። እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ያሉ የጎለመሱ ሴቶች ለመበለቶች ከፍተኛ ድጋፍ ሊሰጡና የመጽናኛ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። (ቲቶ 2:3-5) እንዲያውም እያንዳንዱ ክርስቲያን በመከራ ሥር ለሚገኙ አሳቢነት በማሳየት ድጋፍ ሊሰጥ ይችላል።
እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘ወንድማቸው የሚያስፈልገውን ነገር አጥቶ እያዩ ርኅራኄ ከማሳየት’ ወደኋላ አይሉም። “ልጆቼ ሆይ፣ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ” የሚለውን የሐዋርያው ዮሐንስን ምክር ለመከተል ንቁ ናቸው። (1 ዮሐንስ 3:17, 18) ስለዚህ ‘ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው እንጠይቅ።’—ያዕቆብ 1:27
“በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ።”—1 ዮሐንስ 3:18
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነተኛ ክርስቲያኖች ወላጆች የሌላቸውን ልጆችና መበለቶችን በቁሳዊ፣ በመንፈሳዊ እና በስሜት ይረዳሉ