የአብርሃም ዓይነት እምነት ይኑራችሁ!
የአብርሃም ዓይነት እምነት ይኑራችሁ!
“ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ።”—ገላትያ 3:7
1. አብራም በከነዓን የገጠመውን አዲስ ፈተና የተወጣው እንዴት ነው?
አብራም ይሖዋን በመታዘዝ በዑር የነበረውን ምቾት ያለው ኑሮ ትቶ ወጥቷል። በቀጣዮቹ ዓመታት የደረሱበት መከራዎች በግብፅ ለገጠመው የእምነት ፈተና እንደ መቅድም ብቻ ነበሩ። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ “በምድርም ራብ ሆነ” በማለት ይገልጽልናል። ይህ ሁኔታ አብራምን በቀላሉ እንዲመረር ሊያደርገው ይችል ነበር! ሆኖም አብራም የቤተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ተግባራዊ እርምጃ ወስዷል። “አብራምም በዚያ በእንግድነት ይቀመጥ ዘንድ ወደ ግብፅ ወረደ፣ በምድር ራብ ጸንቶ ነበርና።” ሰፊ የነበረው የአብራም ቤተሰብ ከግብፃውያን እይታ ሊያመልጥ አይችልም። ይሖዋ የገባውን ቃል በመጠበቅ አብራምን ከጉዳት ይጠብቀው ይሆን?—ዘፍጥረት 12:10፤ ዘጸአት 16:2, 3
2, 3. (ሀ) አብራም የሚስቱን ትክክለኛ ማንነት የደበቀው ለምንድን ነው? (ለ) አብራም የገጠመውን ችግር ለመወጣት ሚስቱን ያነጋገራት በምን መልኩ ነበር?
2 ዘፍጥረት 12:11-13 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “ወደ ግብፅም ለመግባት በቀረበ ጊዜ ሚስቱን ሦራን እንዲህ አላት:- አንቺ መልከ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ እነሆ እኔ አውቃለሁ የግብፅ ሰዎች ያዩሽ እንደ ሆነ:- ሚስቱ ናት ይላሉ እኔንም ይገድሉኛል፣ አንቺንም በሕይወት ይተዉሻል። እንግዲህ በአንቺ ምክንያት መልካም ይሆንልኝ ዘንድ፣ ስለ አንቺም ነፍሴ ትድን ዘንድ:- [“እባክሽ፣” NW ] እኅቱ ነኝ በዪ።” ሦራ ዕድሜዋ ከ65 ዓመት ይበልጥ የነበረ ቢሆንም በጣም ውብ ነበረች። ይህም የአብራምን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነበር። a (ዘፍጥረት 12:4, 5፤ 17:17) ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ በአብራም ዘር በኩል የምድር አሕዛብ ራሳቸውን እንደሚባርኩ ተናግሮ ስለነበር ከዓላማው ጋር የተያያዙት ጉዳዮች ሁሉ አደጋ ላይ ወድቀው ነበር። (ዘፍጥረት 12:2, 3, 7) አብራም አሁንም ገና ልጅ ያልወለደ በመሆኑ የግድ በሕይወት መቆየት ነበረበት።
3 አብራም ቀደም ሲል በተስማሙት መሠረት እህቱ ነኝ ብላ በመናገር ዘዴ እንዲጠቀሙ ለሚስቱ ነገራት። ምንም እንኳ አብራም የፓትሪያርክ ሥልጣን የነበረው ቢሆንም ሥልጣኑን አላግባብ እንዳልተጠቀመበት ልብ በል። ከዚያ ይልቅ እንድትተባበረውና እንድትረዳው ጠይቋታል። (ዘፍጥረት 12:11-13፤ 20:13) በዚህ መንገድ አብራም ባሎች የራስነት ሥልጣናቸውን በፍቅር እንዲጠቀሙበት ግሩም ምሳሌ የተወላቸው ሲሆን ሦራም ያሳየችው የተገዥነት ባሕርይ ዛሬ ላሉ ሚስቶች ምሳሌ ይሆናል።—ኤፌሶን 5:23-28፤ ቆላስይስ 4:6
4. በዛሬ ጊዜ ያሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የወንድሞቻቸው ሕይወት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ምን ሊያደርጉ ይገባል?
4 በእርግጥም ደግሞ ሦራ የአብራም ግማሽ እህት ስለነበረች እህቱ እንደሆነች መናገር ትችል ነበር። (ዘፍጥረት 20:12) ከዚህም በላይ አብራም ለማይመለከታቸው ሰዎች ምሥጢሩን የመግለጥ ግዴታ አልነበረበትም። (ማቴዎስ 7:6) በዘመናችን ያሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች መጽሐፍ ቅዱስ ሃቀኛ ስለመሆን የሚሰጠውን ትእዛዝ ይከተላሉ። (ዕብራውያን 13:18) ለምሳሌ ያህል በፍርድ ቤት ቃለ መሐላ ሲገቡ ፈጽሞ አይዋሹም። ይሁን እንጂ እንደ ስደት ወይም የእርስ በርስ ጦርነት ተከስቶ የወንድሞቻቸው አካላዊ ወይም መንፈሳዊ ሕልውና አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ኢየሱስ “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ” በማለት የሰጠውን ምክር ይከተላሉ።—ማቴዎስ ፤ 10:16የኅዳር 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 18 አንቀጽ 19ን ተመልከት።
5. ሦራ የአብራምን ጥያቄ እሺ ብላ የታዘዘችው ለምንድን ነው?
5 አብራም ላቀረበው ጥያቄ ሦራ ምን ምላሽ ሰጠች? ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደ እርሷ ያሉትን ሴቶች “በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉ” በማለት ገልጿቸዋል። ሦራ አከራካሪ ስለነበረው መንፈሳዊ ጥያቄ በቂ እውቀት ነበራት። ከዚህም በላይ ለባሏ ፍቅርና አክብሮት ነበራት። በዚህም መንገድ ሦራ ‘ለባሏ ለመገዛትና’ የጋብቻዋን ሁኔታ በምሥጢር ለመያዝ መርጣለች። (1 ጴጥሮስ 3:5) እንዲህ ማድረጓ ለአደጋ እንዳጋለጣት የታወቀ ነው። “አብራምም ወደ ግብፅ በገባ ጊዜ የግብፅ ሰዎች ሴቲቱን እጅግ ውብ እንደ ሆነች አዩ፤ የፈርዖንም አለቆች አዩአት፣ በፈርዖንም ፊት አመሰገኑአት፤ ሴቲቱንም ወደ ፈርዖን ቤት ወሰዱአት።”—ዘፍጥረት 12:14, 15
የይሖዋ ማዳን
6, 7. አብራምና ሦራ ምን አስጨናቂ ሁኔታ ገጠማቸው? ይሖዋ ሦራን ያዳናት እንዴት ነው?
6 ይህ ሁኔታ አብራምንና ሦራን ምንኛ ሐዘን ላይ ጥሏቸው ይሆን! ሦራ በፆታ ልትነወር ነው። ከዚህም በላይ ፈርዖን ሦራ ትዳር ያላት መሆኗን ባለማወቁ ለአብራም ከፍተኛ ስጦታ ሰጠው። በዚህም ምክንያት አብራም “በጎችም በሬዎችም አህዮችም ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችም ግመሎችም” ሊኖሩት ችሏል። b (ዘፍጥረት 12:16) አብራም እነዚህን ስጦታዎች ምንኛ ተጸይፏቸው ይሆን! ሁኔታው ምንም ተስፋ የሌለው ቢመስልም ይሖዋ አብራምን አልተወውም።
7 “እግዚአብሔርም በአብራም ሚስት በሦራ ምክንያት ፈርዖንንና የቤቱን ሰዎች በታላቅ መቅሠፍት መታ።” (ዘፍጥረት 12:17) በአንድ ባልታወቀ መንገድ ይህን “መቅሠፍት” ያመጣው ማን እንደሆነ ፈርዖን እንዲያውቅ ተደረገ። ወዲያውም እንዲህ በማለት ምላሽ ሰጠ:- “ፈርዖንም አብራምን ጠርቶ አለው:- ይህ ያደረግህብኝ ምንድር ነው? እርስዋ ሚስትህ እንደ ሆነች ለምን አልገለጥህልኝም? ለምንስ:- እኅቴ ናት አልህ? እኔ ሚስት ላደርጋት ወስጄአት ነበር። አሁንም ሚስትህ እነኋት ይዘሃት ሂድ። ፈርዖንም ሰዎቹን ስለ እርሱ አዘዘ፣ እርሱንም ሚስቱንም ከብቱንም ሁሉ ሸኙአቸው።”—ዘፍጥረት 12:18-20፤ መዝሙር 105:14, 15
8. ይሖዋ በዛሬ ጊዜ የሚኖሩ ክርስቲያኖችን የሚጠብቃቸው እንዴት ነው?
8 በዛሬ ጊዜ ይሖዋ ሞት፣ ወንጀል፣ ረሃብ ወይም የተፈጥሮ አደጋ ከሚያስከትሏቸው መቅሰፍቶች እንደሚጠብቀን ቃል አልገባልንም። ይሖዋ መንፈሳዊነታችንን አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ነገሮች እኛን ለመጠበቅ ቃል ገብቶልናል። (መዝሙር 91:1-4) ይህንንም የሚያደርግበት ዋነኛው መንገድ በቃሉና ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት በጊዜው በሚሰጠው ማስጠንቀቂያ በኩል ነው። (ማቴዎስ 24:45) አሳዳጆች እንደሚገድሉን ቢዝቱብንስ? አምላክ ግለሰቦች እንዲሞቱ ሊፈቅድ ቢችልም መላው ሕዝቡ እንዲጠፉ ግን ፈጽሞ አይፈቅድም። (መዝሙር 116:15) አንዳንድ ታማኝ አገልጋዮች ቢሞቱ እንኳ ትንሣኤ እንደሚያገኙ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።—ዮሐንስ 5:28, 29
ሰላምን ለመጠበቅ የተከፈለ መሥዋዕትነት
9. አብራም በከነዓን በአንድ ቋሚ ቦታ ኑሮውን እንዳልመሠረተ የሚጠቁመው ምንድን ነው?
9 በከነዓን ደርሶ የነበረው ረሃብ ሲያበቃ “አብራምም ከግብፅ ወጣ፤ እርሱና ሚስቱ ለእርሱ የነበረውም ሁሉ ሎጥም ከእርሱ ጋር ወደ አዜብ [ከተራራማው ይሁዳ በስተ ደቡብ ወደሚገኘው ከፊል በረሃማ ቦታ] ወጡ። አብራምም በከብት በብርና በወርቅ እጅግ በለጠገ።” (ዘፍጥረት 13:1, 2) በዚህም የተነሳ የአካባቢው ነዋሪዎች ኃያልና ባለ ሥልጣን እንዲሁም ታላቅ አለቃ እንደሆነ አድርገው ተመልክተውታል። (ዘፍጥረት 23:6) አብራም ኑሮውን በዚያ የመመሥረትና በከነዓናውያን የፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ የመካፈል ፍላጎት አልነበረውም። ከዚያ ይልቅ “ከአዜብ ባደረገው በጉዞውም ወደ ቤቴል በኩል ሄደ፤ ያም ስፍራ አስቀድሞ በቤቴልና በጋይ መካከል ድንኳን ተክሎበት የነበረው ነው።” እንደ ቀድሞው ሁሉ አብራም በሄደበት ቦታ ሁሉ የይሖዋን አምልኮ አስቀድሟል።—ዘፍጥረት 13:3, 4
10. በአብራምና በሎጥ እረኞች መካከል ምን ችግር ተፈጠረ? ችግሩ በፍጥነት እልባት ማግኘት የነበረበት ለምንድን ነው?
10 “ከአብራም ጋር የሄደው ሎጥ ደግሞ የላምና የበግ መንጋ ድንኳንም ነበረው። በአንድነትም ይቀመጡ ዘንድ ምድር አልበቃቸውም የነበራቸው እጅግ ነበረና በአንድነት ሊቀመጡ አልቻሉም። የአብራምንና የሎጥን መንጎች በሚጠብቁት መካከልም ጠብ ሆነ በዚያም ዘመን ከነዓናውያንና ፌርዛውያን በዚያች ምድር ተቀምጠው ነበር።” (ዘፍጥረት 13:5-7) ምድሪቱ የአብራምንና የሎጥን መንጎች ለመመገብ የሚያስችል በቂ ውኃና ግጦሽ አልነበራትም። በዚህም የተነሳ በእረኞቹ መካከል ጠብና ጭቅጭቅ ተፈጠረ። በእውነተኛ የአምላክ አምላኪዎች መካከል እንዲህ ያለው ጥል ሊፈጠር አይገባም። የተፈጠረው ጭቅጭቅ እልባት ካላገኘ እየከረረ ሊሄድ ይችላል። ታዲያ አብራም ጉዳዩን እንዴት ይወጣው ይሆን? ሎጥን አባቱ ከሞተበት በኋላ እንደ ልጁ አድርጎ ያሳደገው እርሱ ነው። አብራም በዕድሜ ታላቅ እንደመሆኑ መጠን የተሻለውን የመውሰድ መብት አልነበረውም?
11, 12. አብራም ለሎጥ ምን ደግነት የተሞላበት ግብዣ አቀረበለት? ሎጥ ያደረገው ምርጫ ጥበብ የጎደለው የነበረው እንዴት ነው?
11 ሆኖም “አብራምም ሎጥን አለው:- እኛ ወንድማማች ነንና በእኔና በአንተ በእረኞቼና በእረኞችህ መካከል ጠብ እንዳይሆን እለምንሃለሁ። ምድር ሁሉ በፊትህ አይደለችምን? ከእኔ ትለይ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ አንተ ግራውን ብትወስድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተም ቀኙን ብትወስድ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ።” ከቤቴል አቅራቢያ “በጳለስጢና ካሉት አካባቢውን ለመቃኘት ከሚያስችሉ ከፍታዎች የተሻለ ነው” የተባለለት ቦታ አለ። ምናልባት ከዚህ ሳይሆን አይቀርም “ሎጥም ዓይኑን አነሣ፣ በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውንም አገር ሁሉ ውኃ የሞላበት መሆኑን አየ፤ እግዚአብሔር ሰዶምንና ገሞራን ከማጥፋቱ አስቀድሞ እስከ ዞዓር ድረስ እንደ እግዚአብሔር ገነት በግብፅ ምድር አምሳል ነበረ።”—ዘፍጥረት 13:8-10
12 መጽሐፍ ቅዱስ ሎጥ “ጻድቅ” እንደሆነ የሚናገር ቢሆንም እንኳ በዚህ ጉዳይ የአብራምን አስተያየት ለማወቅም ሆነ የአረጋዊውን ሰው ምክር ለማግኘት የፈለገ አይመስልም። (2 ጴጥሮስ 2:7) “ሎጥም በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውን አገር ሁሉ መረጠ ሎጥም ወደ ምሥራቅ ተጓዘ፤ አንዱም ከሌላው እርስ በርሳቸው ተለያዩ። አብራም በከነዓን ምድር ተቀመጠ ሎጥም በአገሩ ሜዳ ባሉት ከተሞች ተቀመጠ፣ እስከ ሰዶምም ድረስ ድንኳኑን አዘዋወረ።” (ዘፍጥረት 13:11, 12) ሰዶም የበለጸገችና በርካታ ቁሳዊ ጥቅም የሚገኝባት ከተማ ነበረች። (ሕዝቅኤል 16:49, 50) በሥጋዊ ዓይን ሲታይ ሎጥ ጥበብ ያለው ምርጫ ያደረገ ሊመስል ቢችልም በመንፈሳዊ ዓይን ሲታይ ግን ጥበብ የጎደለው ነበር። ለምን? ምክንያቱም “የሰዶም ሰዎች . . . ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጢአተኞች ነበሩ” በማለት ዘፍጥረት 13:13 ይናገራል። ሎጥ እዚያ ሄዶ ለመኖር ያደረገው ምርጫ ውሎ አድሮ በቤተሰቡ ላይ ከባድ ሐዘን የሚያስከትል ነበር።
13. ገንዘብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ውዝግብ ውስጥ ለገቡ ክርስቲያኖች የአብራም ምሳሌ ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት ነው?
13 አብራም ከጊዜ በኋላ ዘሮቹ መላውን ምድር እንደሚወርሱ ይሖዋ በገባለት ቃል ላይ እምነት ያሳደረ ቢሆንም እንኳ በአንዲት ቁራሽ መሬት ለመጨቃጨቅ አልፈለገም። ከዚያ ይልቅ ከጊዜ በኋላ በ1 ቆሮንቶስ 10:24 ላይ “እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ” ከሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በሚስማማ መንገድ ተመላልሷል። ገንዘብን በተመለከተ ከእምነት ባልንጀራቸው ጋር መግባባት ላልቻሉ ይህ ጥሩ ማሳሰቢያ ነው። አንዳንዶች ማቴዎስ 18:15-17 ላይ የሚገኘውን ምክር ከመከተል ይልቅ ወንድሞቻቸውን ፍርድ ቤት ከስሰዋቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:1, 7) በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ ከማምጣት ወይም የክርስቲያን ጉባኤን ሰላም ከማወክ ይልቅ ገንዘባችንን ብናጣ የተሻለ እንደሚሆን ከአብራም ምሳሌ እንማራለን።—ያዕቆብ 3:18
14. አብራም ደግነት በማሳየቱ የተባረከው እንዴት ነው?
14 አብራም የለጋስነት መንፈስ ማሳየቱ በረከት አስገኝቶለታል። አምላክ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ዘርህንም እንደ ምድር አሸዋ አደርጋለሁ የምድርን አሸዋን ይቈጥር ዘንድ የሚችል ሰው ቢኖር ዘርህ ደግሞ ይቈጠራል።” ልጅ ላልነበረው አብራም ይህ እንዴት ያለ የሚያበረታታ ራእይ ነው! ከዚያም አምላክ “ተነሣ በምድር በርዝመትዋም በስፋትዋም ሂድ እርስዋን ለአንተ እሰጣለሁና” በማለት አዝዞታል። (ዘፍጥረት 13:16, 17) አብራም ምቾት ባለው ከተማ ውስጥ እንዲኖር አልተፈቀደለትም። ከከነዓናውያን ተለይቶ መኖር ነበረበት። በተመሳሳይም በዛሬ ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ከዓለም ርቀው መኖር ይገባቸዋል። ከሌሎች የበለጡ እንደሆኑ አድርገው ስለ ራሳቸው አያስቡም። ሆኖም ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ ድርጊቶች እንዲካፈሉ ሊያባብላቸው ከሚችል ከማንኛውም ሰው ይርቃሉ።—1 ጴጥሮስ 4:3, 4
15. (ሀ) አብራም ያደረገው ጉዞ ምን ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል? (ለ) አብራም በዛሬ ጊዜ ለሚኖሩ ክርስቲያን ቤተሰቦች ምን ምሳሌ ትቷል?
15 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ ሰው መሬት ከመውረሱ በፊት አካባቢውን ተዘዋውሮ ይመለከት ነበር። አብርሃም በምድሪቱ መዘዋወሩ አንድ ቀን ዘሮቹ ይህንን ምድር እንደሚወርሱ ሁልጊዜ እንዲያስታውስ ረድቶት ሊሆን ይችላል። “አብራምም” በታዛዥነት “ድንኳኑን ነቀለ [“በድንኳን መኖሩን ቀጠለ፣” NW ] መጥቶም በኬብሮን ባለው በመምሬ የአድባር ዛፍ ተቀመጠ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ።” (ዘፍጥረት 13:18) አሁንም አብራም ለአምልኮቱ ቅድሚያ እንደሚሰጥ አሳይቷል። የቤተሰብ ጥናት፣ በቤተሰብ አንድ ላይ መጸለይና በስብሰባ ላይ መገኘት በቤተሰባችሁ ሕይወት ውስጥ አንደኛውን ቦታ የያዙ ልማዶች ናቸው?
ጠላቶች የሰነዘሩት ጥቃት
16. (ሀ) ዘፍጥረት 14:1 ላይ ያሉት ቃላት ከገድ ጋር የተያያዘ መልእክት ያላቸው ለምንድን ነው? (ለ) አራቱ የምሥራቅ ነገሥታት የወረራ ጥቃት የሰነዘሩበት ምክንያት ምንድን ነው?
16 “በሰናዖር ንጉሥ በአምራፌል፣ በእላሳር ንጉሥ በአርዮክ፣ በኤላም c ንጉሥ በኮሎዶጎምር፣ በአሕዛብ ንጉሥ በቲድዓል ዘመን . . . ሰልፍ አደረጉ።” በመጀመሪያው የዕብራይስጥ ቋንቋ (“. . . ዘመን እንዲህ ሆነ”) የሚሉት ቃላት ከገድ ጋር የተያያዘ መልእክት ያለው ሲሆን “በበረከት ስለሚጠናቀቅ የመከራ ዘመን” የሚጠቁም ነው። (ዘፍጥረት 14:1, 2፣ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) እነዚህ አራት የምሥራቅ ነገሥታትና ሠራዊቶቻቸው በከነዓን ላይ አውዳሚ ወረራ በፈጸሙ ጊዜ መከራው ጀመረ። ዓላማቸው ምን ነበር? ዓመፀኞቹን አምስት ከተሞች ማለትም ሰዶምን፣ ገሞራን፣ አዳማን፣ ዞዓርን እና ቤላን ለማንበርከክ ነበር። ተቃዋሚዎቻቸውን ሁሉ ጠራርገው በማጥፋት ሁሉም “በሲዲም ሸለቆ ተሰብስበው ተባበሩ፤ ይኸውም የጨው ባሕር ነው።” ሎጥና ቤተሰቡ የሚኖሩት በዚህ አካባቢ ነበር።—ዘፍጥረት 14:3-7
17. ሎጥ ተማርኮ መወሰዱ የአብራምን እምነት ፈተና ላይ የጣለው እንዴት ነው?
17 የከነዓናውያን ነገሥታት የወራሪዎቹን ጥቃት ለመመከት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም አሳዛኝ ሽንፈት ገጥሟቸዋል። “የሰዶምንና የገሞራን ከብት ሁሉ መብላቸውንም ሁሉ ወስደው ሄዱ። በሰዶም ይኖር የነበረውን የአብራምን የወንድም ልጅ ሎጥን ደግሞ ከብቱንም ወስደው ሄዱ።” ይህን ከፍተኛ ጥፋት በሚመለከት ለአብራም ወሬ ደረሰው። “አንድ የሸሸ ሰውም መጣ፣ ለዕብራዊው ለአብራምም ነገረው፤ እርሱም የኤስኮል ወንድምና የአውናን ወንድም በሆነ በአሞራዊ መምሬ የአድባር ዛፍ ይኖር ነበር፤ እነዚያም ከአብራም ጋር ቃል ኪዳን ገብተው ነበር። አብራምም ወንድሙ እንደ ተማረከ [ሰማ።]” (ዘፍጥረት 14:8-14) ምንኛ እምነትን የሚፈትን ነገር ነው! አብራም የወንድሙ ልጅ የተሻለውን ምድር በመውሰዱ ምክንያት በልቡ ውስጥ ጥላቻ አሳድሮ ይሆን? እነዚህ ወራሪዎች የመጡት ከትውልድ አገሩ ከሰናዖር እንደሆነም አስታውስ። በእነርሱ ላይ መዝመት ማለት ወደ ትውልድ አገሩ ዳግመኛ ለመሄድ ያለውን አጋጣሚ ሁሉ መዝጋት ማለት ነው። ደግሞስ የተባበረው የከነዓናውያን ኃይል ሊመክተው ያልቻለውን ጦር አብራም ምን ሊያደርገው ይችላል?
18, 19. (ሀ) አብራም ሎጥን ያዳነው እንዴት ነው? (ለ) ለዚህ ድል የሚመሰገነው ማን ነው?
18 አሁንም አብራም በይሖዋ ላይ የማይናወጥ እምነት እንዳለው አሳይቷል። “በቤቱ የተወለዱትን ሦስት መቶ አሥራ ስምንት ብላቴኖቹን አሰለፈ፣ ፍለጋቸውንም ተከትሎ እስከ ዳን ድረስ ሄደ። ብላቴኖቹንም ከፍሎ በሌሊት እርሱ ከባሪያዎቹ ጋር ወረደባቸው፣ መታቸውም፣ በደማስቆ ግራ እስካለችውም እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው። ከብቱንም ሁሉ አስመለሰ፣ ደግሞም ወንድሙን ሎጥንና ከብቶቹን ሴቶችንና ሕዝቡን ደግሞ መለሰ።” (ዘፍጥረት 14:14-16) አብራም በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት በማሳደር ከእርሱ እጅግ የሚበልጠውን ሠራዊት ድል አድርጎ ሎጥንና ቤተሰቡን አዳነ። በዚህ ወቅት አብራም የሳሌም ንጉሥና ካህን ከሆነው ከመልከ ጼዴቅ ጋር ተገናኘ። “የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ፤ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ። ባረከውም:- አብራም ሰማይንና ምድርን ለሚገዛ ለልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ነው፤ ጠላቶችህን በእጅህ የጣለልህ ልዑል እግዚአብሔርም የተባረከ ነው አለውም። አብራምም ከሁሉ አሥራትን ሰጠው።”—ዘፍጥረት 14:18-20
19 አዎን፣ ድሉ የይሖዋ ነበር። አብራም በእምነቱ ምክንያት አሁንም እንደገና የይሖዋን ማዳን ለማየት በቅቷል። በዛሬ ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች ቃል በቃል በጦርነት ባይካፈሉም በርካታ ፈተናዎችና ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። እነዚህን ችግሮች በመቋቋም ረገድ የአብራም ምሳሌ እንዴት እንደሚረዳን በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ እንመለከታለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (የይሖዋ ምሥክሮች ያሳተሙት የእንግሊዝኛ መጽሐፍ) እንደሚናገረው “የምታምር ሴት ካገኙ ባሏን ገድለው እርሷን ይዘው እንዲመጡ የታጠቁ ወንዶችን ስለላከ አንድ ፈርዖን የሚናገር ጥንታዊ ፓፒረስ አለ።” ስለዚህ የአብራም ፍርሃት የተጋነነ አልነበረም።
b አብራም ከጊዜ በኋላ ቁባቱ የሆነችውን አጋርን ያገኛት በዚህ ወቅት ከተሰጡት አገልጋዮች መካከል ሳይሆን አይቀርም።—ዘፍጥረት 16:1
c በአንድ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ኤላም በሰናዖር ምድር ላይ ምንም ዓይነት ኃይል ኖሯት እንደማያውቅና ኮሎዶጎምር ጥቃት እንደሰነዘረ የሚናገረው ዘገባም ፈጠራ እንደሆነ ተናግረው ነበር። የአርኪኦሎጂያዊ ማስረጃ የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ እንደሚደግፍ ለማየት መጠበቂያ ግንብ 13-110 ገጽ 4-7ን ተመልከት።
አስተውለሃልን?
• በከነዓን የደረሰው ረሃብ የአብራምን እምነት ፈተና ላይ የጣለው እንዴት ነው?
• አብራምና ሦራ በዛሬው ጊዜ ላሉት ባልና ሚስቶች ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት እንዴት ነው?
• አብራም በእርሱና በሎጥ አገልጋዮች መካከል የተነሳውን አለመግባባት ለመፍታት ከወሰደው እርምጃ ምን ትምህርት እናገኛለን?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎ]
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብራም መብቱን ለማስጠበቅ ከመሞከር ይልቅ የሎጥን ጥቅም አስቀድሟል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብራም የወንድሙን ልጅ ሎጥን ለማዳን በይሖዋ ላይ እንደሚታመን አሳይቷል