የወጣትነት ሕይወትህን የተሳካ አድርገው
የወጣትነት ሕይወትህን የተሳካ አድርገው
በአንድ አውሮፓ አገር ለሚኖሩ ሰዎች ከውበት፣ ከሃብትና ከወጣትነት የትኛውን እንደሚመርጡ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። በአንደኛ ደረጃ የመረጡት ወጣትነትን ነው። አዎን፣ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች አሥራዎቹን ዕድሜና በ20ዎቹ መግቢያ ላይ ያሉትን ዓመታት ልዩ ጊዜ እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል። እንዲሁም ሁሉም ሰው ወጣቶች ከልጅነት ወደ አዋቂነት የሚያሸጋግራቸው ይህ ጊዜ የተሳካ እንዲሆንላቸው ይመኛል። ግን እንዴት?
በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ይኖር ይሆን? መልሱ አዎን የሚል ነው። የአምላክ ቃል ምናልባትም በየትኛውም የዕድሜ ክልል ከሚገኙት ሰዎች በበለጠ ለወጣቶች ጠቃሚ ሊሆን የሚችልባቸውን ሁለት መስኮች እንመርምር።
ከሌሎች ጋር ተስማምቶ መኖር
ዩጀንት 2000 ጀርመን በሚኖሩ ከ5,000 በሚበልጡ ወጣቶች አስተሳሰብ፣ እሴትና ጠባይ ላይ የተደረገውን ሰፊ ጥናት ያካተተ ሪፖርት ነው። ጥናቱ እንደሚያሳየው ወጣቶች ሙዚቃ በማዳመጥ፣ ስፖርት በመሥራት ወይም ዝም ብሎ በመዞር ትርፍ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ሁልጊዜ ለማለት ይቻላል ከሌሎች ጋር በመሆን ነው። በየትኛውም የዕድሜ ክልል ከሚገኙት ሰዎች በበለጠ ከእኩዮቻቸው ጋር መሆንን የሚመርጡት ወጣቶች ሳይሆኑ አይቀርም። በእርግጥም የወጣትነትን ሕይወት የተሳካ ማድረግ የሚቻልበት አንዱ ቁልፍ ከሌሎች ጋር ተስማምቶ መኖር ነው።
ሆኖም ከሌሎች ጋር ተስማምቶ መኖር ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። እንዲያውም ብዙ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ከማኅበራዊ ኑሮ ጋር በተያያዘ በአብዛኛው ችግር እንደሚገጥማቸው ሳይሸሽጉ ይናገራሉ። በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። የአምላክ ቃል ከሌሎች ጋር ሚዛናዊ ግንኙነት በመመሥረት ረገድ ለወጣቶች የሚያገለግሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ከማኅበራዊ ኑሮ ጋር በተያያዘ በጣም አስፈላጊ የሆነው አንዱ መሠረታዊ ሥርዓት ወርቃማው ሕግ በመባል የሚታወቀው “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” የሚለው ነው። ሌሎችን በደግነትና በአክብሮት ስትይዛቸው እንዲሁም ሰብዓዊ ክብራቸውን ስትጠብቅላቸው እነርሱም በአጸፋው ልክ እንደዚያው ለማድረግ ይገፋፋሉ። ደግነት ግጭትና ውጥረትን ያስቀራል። ለሌሎች አሳቢነት በማሳየት የምትታወቅ ከሆነ በሰዎች ዘንድ ጥሩ ግምትና ተቀባይነት ማግኘትህ አይቀርም። በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘትህ አያስደስትህም?—ማቴዎስ 7:12
መጽሐፍ ቅዱስ “ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ [“ራስህ፣” NW ] ውደድ” በማለት ይመክርሃል። ራስህን መውደድ አለብህ ሲባል ራስህን መንከባከብና ሳይበዛም ሳያንስም ለራስህ ሚዛናዊ የሆነ አክብሮት ሊኖርህ ይገባል ማለት ነው። ይህ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ለራስህ ጥሩ ግምት ከሌለህ ሌሎችን ከመጠን በላይ የምትነቅፍ ልትሆን ትችላለህ። ይህ ደግሞ ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳትመሠርት ማቴዎስ 22:39
እንቅፋት ሊሆንብህ ይችላል። ሆኖም ለራስ ሚዛናዊ የሆነ አክብሮት ማሳደር ጠንካራ ወዳጅነት ለመገንባት የሚያስችል መሠረት ነው።—ወዳጅነት አንድ ጊዜ ከተመሠረተ በኋላ ሁለቱም ወገኖች በሚያደርጉት ጥረት መጠናከር ይኖርበታል። ‘ከመቀበል ይልቅ መስጠት ደስታ’ ስለሚያስገኝ ወዳጅነትህን ለማጠንከር ስትል ጊዜ ማጥፋትህ ሊያስደስትህ ይገባል። መስጠት የሚቻልበት አንደኛው መንገድ ደግሞ ይቅር ባይ መሆን ነው። ይህም ሌሎች የሚሠሯቸውን ጥቃቅን ስህተቶች ማለፍና ከሌሎች ፍጽምና አለመጠበቅን ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስ “ገርነታችሁ [“ምክንያታዊነታችሁ፣” NW ] ለሰው ሁሉ ይታወቅ” በማለት ይናገራል። “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።” ወዳጅህ ድክመት እንዳለብህ ቢነግርህስ? ምን ምላሽ ትሰጣለህ? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን የሚከተለውን ተግባራዊ ምክር ተመልከት:- “የወዳጅ ማቁሰል የታመነ” ስለሆነ “በነፍስህ ለቁጣ ችኩል አትሁን።” ወዳጆችህ በአስተሳሰብህ፣ በአነጋገርህና በባሕርይህ ላይ ተጽእኖ ማሳደራቸው እውነት አይደለም? ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” በማለት ያስጠነቅቃል። በሌላ በኩል ደግሞ “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል።”—ሥራ 20:35፤ ፊልጵስዩስ 4:5፤ ሮሜ 12:17, 18፤ ምሳሌ 13:20፤ 27:6፤ መክብብ 7:9፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33
ማርኮ ቀጥሎ የተናገራቸው ቃላት የብዙ ወጣት ወንዶችና ሴቶችን ስሜት የሚገልጽ ነው:- “ከሌሎች ጋር ተስማምቶ በመኖር ረገድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚሰጡት እርዳታ ከፍተኛ ነው። አንዳንድ የማውቃቸው ሰዎች የሚኖሩት ለራሳቸው ብቻ ሲሆን የሚያስቡትም ስለ ራሳቸው ጥቅም ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከራሳችን ይልቅ ለሌሎች እንድናስብ ያስተምረናል። ይህ ከሰዎች ጋር አብሮ ለመኖር የሚያስችል ከሁሉ የተሻለ ዘዴ እንደሆነ ይሰማኛል።”
እንደ ማርኮ ያሉ ሌሎች ወጣቶችም ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኙት ትምህርት ለአሁኑ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ጊዜ ይጠቅማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ለወጣቱ ትውልድ ጠቃሚ ሊሆን የሚችልበት ሌላኛው መንገድ ደግሞ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ የያዘው ሐሳብ ነው።
ስለ ወደፊቱ ጊዜ መጨነቅ
በብዙ ወጣቶች አእምሮ ውስጥ የሚጉላሉ ጥያቄዎች አሉ። ምናልባትም በየትኛውም የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ሰዎች ይበልጥ ወጣቶች በዙሪያቸው ምን ነገር እየተከናወነ እንዳለና ለምን እንደተከናወነ ማወቅ ይፈልጋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ከማንኛውም ሌላ መጽሐፍ ይበልጥ ለዓለም ሁኔታዎች መንስዔው ምን እንደሆነና ወደፊት ምን እንደሚመጣ ይገልጻል። ወጣቱ ትውልድ ማወቅ የሚፈልገው ደግሞ ይህንን ነው። ታዲያ ይህ እንደሆነ እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
ወጣቶች የሚኖሩት ለአሁኑ ጊዜ ብቻ ነው የሚለው አስተሳሰብ በሰፊው ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም እንኳ አንዳንድ ጥናቶች ከዚህ ትንሽ ለየት ያለ ሐሳብ ያቀርባሉ። እነዚህ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ወጣቶች ብዙውን ጊዜ በዙሪያቸው ምን ነገር እየተከናወነ እንዳለ በትኩረት ከተከታተሉ በኋላ ሕይወት ወደፊት ምን መልክ ሊኖረው እንደሚችል የራሳቸው መደምደሚያ ላይ ይደርሳሉ። ከ4 ወጣት ወንዶችና ሴቶች መካከል ሦስቱ “አዘውትረው” ስለወደፊቱ ጊዜ የሚያስቡ መሆናቸው ለዚህ ማስረጃ ነው። በጥቅሉ ሲታይ ወጣቶች ብሩህ አመለካከት ያላቸው ቢሆንም እንኳ አብዛኞቹ ወጣቶች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሲያስቡ ስጋት ያድርባቸዋል።
ወጣቶች ስጋት ያደረባቸው ለምንድን ነው? በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ወጣቶች የወንጀል፣ የዓመፅና የአደገኛ ዕፅ ሰለባ ሆነዋል። ከፍተኛ ውድድር ባለበት በዚህ ኅብረተሰብ ውስጥ አስተማማኝ ሥራ ማግኘታቸው ያሳስባቸዋል። በትምህርት
ቤት ጥሩ ውጤት እንዲያመጡ ወይም በሥራ ቦታ የተሳካላቸው እንዲሆኑ ጫና እንደሚደረግባቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። አንዲት የ17 ዓመት ወጣት እንደሚከተለው በማለት ምሬቷን ገልጻለች:- “የምንኖረው ጨካኝና የግል ጥቅሙን በሚያሳድድ ኀብረተሰብ ውስጥ ነው። እያንዳንዱ ሰው ያሻውን ለማድረግ ይጥራል። ማድረግ የምትችሉትን ሁሉ በተግባር ማሳየት አለባችሁ። ይህ ደግሞ ያበሳጨኛል።” ሌላ የ22 ዓመት ወጣት ደግሞ እንዲህ ብሏል:- “የተሳካላቸው ሰዎች ተደላድለው መኖር ይችላሉ። በተለያዩ ምክንያቶች ኑሯቸውን ለማቅናት ያልታደሉት ደግሞ ባሉበት ይዳክራሉ።” ሕይወት እንዲህ ውድድር የበዛበት የሆነው ለምንድን ነው? በዚህ መልኩስ ይቀጥል ይሆን?ምክንያታዊና ከእውነታው ያልራቀ ማብራሪያ
ወጣቶች የሚኖሩበትን ኅብረተሰብ ሲመለከቱ በስጋት ወይም በጭንቀት መዋጣቸው አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መስማማታቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ የሚገኘው “ጨካኝና የግል ጥቅሙን የሚያሳድድ” ኅብረተሰብ ጊዜያችንን ለይቶ የሚያሳውቅ ምልክት እንደሆነ ያሳያል። ሐዋርያው ጳውሎስ ጊዜያችንን በማስመልከት ጢሞቴዎስ ለተባለ አንድ ወጣት በጻፈው ደብዳቤ ላይ “በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን” ይሆናል በማለት ገልጿል። የሚያስጨንቅ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ጳውሎስ አክሎ እንደጠቀሰው “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-3
ትዕቢተኞች . . . የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው . . . ጨካኞች” ስለሚሆኑ ነው። ይህ በዛሬው ጊዜ የሚገኘው አብዛኛው የሰው ዘር የሚያሳየውን ባሕርይ በትክክል የሚገልጽ አይደለምን?—ይህ የሚያስጨንቅ ዘመን “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ማለትም በጠቅላላው የሰው ዘር ኅብረተሰብ ላይ ታላላቅ ለውጦች ከመካሄዳቸው በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እነዚህ ለውጦች ወጣት ሽማግሌ ሳይሉ ሁሉንም ሰው የሚነኩ ናቸው። ለውጦቹ ምን ዓይነት ናቸው? በቅርቡ አንድ ሰማያዊ መስተዳድር የሰው ልጆችን አገዛዝ በመቆጣጠር ተገዢዎቹ ‘ብዙ ሰላም’ እንዲኖራቸው ያደርጋል። “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።” ጭንቀትና ስጋት የተረሱ ነገሮች ይሆናሉ።—መዝሙር 37:11, 29
ስለወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ መረጃ የሚሰጠው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። አንድ ወጣት በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት የሚፈጸሙትን ክንውኖች ሲያውቅ ቅድመ ዝግጅት ሊያደርግ፣ የደህንነት ስሜት ሊሰማውና ሕይወቱን በትክክለኛው መንገድ ሊመራ ይችላል። ይህ ስሜት ደግሞ ውጥረትንና ጭንቀትን ይቀንሳል። ወጣቱ ትውልድ በዋነኛነት የሚያስፈልገው ነገር የሚኖርበትን ኅብረተሰብ መገንዘብና የወደፊቱ ጊዜ ምን እንደያዘ ማወቅ ሲሆን እንዲህ ያለው የወጣቱ ትውልድ ፍላጎት ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዚህ መንገድ ተገልጾ ይገኛል።
በወጣትነት ስኬታማ መሆን
የአንድ ወጣት ስኬታማነት የሚለካው በምንድን ነው? ከፍተኛ ትምህርት፣ ቁሳዊ ሃብት ወይስ ብዙ ወዳጆች? ብዙ ሰዎች እንደዚያ ብለው ያስቡ ይሆናል። በአሥራዎቹና በ20ዎቹ መግቢያ ላይ ያሉት ዓመታት አንድን ግለሰብ ለኋለኞቹ ዓመታት ሊያዘጋጁት ይገባል። በሌላ አባባል አንድ ሰው የወጣትነት ሕይወቱ የተሳካለት መሆኑ በኋለኞቹ ዓመታት የሚኖረውን ሕይወት የሚያመላክት ሊሆን ይችላል።
እስካሁን እንዳየነው አንድ ወጣት የወጣትነት ሕይወቱን የተሳካ ማድረግ እንዲችል መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳው ይችላል። ብዙ ወጣቶች በራሳቸው ሕይወት ይህ እውነት ሆኖ አግኝተውታል። የአምላክን ቃል በየዕለቱ የሚያነብቡ ሲሆን ያነበቡትንም በተግባር ላይ ያውሉታል። (አንድ ወጣት የይሖዋ አገልጋይ የሰጠው ምክር የሚለውን በገጽ 6 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬ ያሉት ወጣቶች ‘ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ’ እንዲሆኑ ሊረዳቸው ስለሚችል በእርግጥም ለወጣቶች የሚሆን መጽሐፍ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የወጣትነትን ሕይወት የተሳካ ማድረግ የሚቻልበት አንዱ ቁልፍ ከሌሎች ጋር ተስማምቶ መኖር ነው
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ምናልባትም በየትኛውም የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ሰዎች ይልቅ ወጣቶች በዙሪያቸው ምን ነገር እየተከናወነ እንዳለና ለምን እንደተከናወነ ማወቅ ይፈልጋሉ
[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንድ ወጣት የይሖዋ አገልጋይ የሰጠው ምክር
አሌክሳንደር የ19 ዓመት ልጅ ነው። ያደገው በይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን እምነቱን በሙሉ ልቡ በተግባር መግለጹ ያስደስተዋል። ሆኖም ሁኔታው ሁልጊዜ እንዲህ አልነበረም። አሌክሳንደር እንዲህ ሲል ይገልጻል:-
“ብታምኑም ባታምኑም ያልተጠመቅሁ አስፋፊ ሆኜ ከሰባት ለሚበልጡ ዓመታት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተሰብስቤአለሁ። በእነዚህ ጊዜአት ሁሉ አምልኮቴን አከናውን የነበረው እንዲያው በዘልማድ ነው። በወቅቱ ራሴን በሃቀኝነት ለመመርመር የሚያስችል ድፍረት የነበረኝ አይመስለኝም።”
በኋላ ግን የአሌክሳንደር አመለካከት ተለወጠ። እንዲህ በማለት ይቀጥላል:-
“ወላጆቼና በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ጓደኞቼ ይሖዋን በሚገባ ማወቅ እችል ዘንድ በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳነብብ አጥብቀው ይመክሩኝ ነበር። በመጨረሻ መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ወሰንኩ። ስለዚህ በቴሌቪዥን የማጠፋውን ጊዜ ቀነስኩና በየዕለቱ ጠዋት ጠዋት እየተነሳሁ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብን ልማድ አደረግሁት። በመጨረሻ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን መረዳት ጀመርኩ። በግለሰብ ደረጃ እንዴት ሊጠቅመኝ እንደሚችል ተገነዘብኩ። ከሁሉ በላይ ግን ይሖዋ እርሱን እንዳውቀው እንደሚፈልግ ተረዳሁ። ይህንን ከተገነዘብኩና ተገቢውን እርምጃ ከወሰድኩ በኋላ ከይሖዋ ጋር ያለኝ ዝምድና እያደገ የመጣ ሲሆን ከጉባኤው አባላት ጋር ያለኝ ወዳጅነትም ተሻሽሏል። መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወቴ ላይ ያስከተለው ለውጥ ምንኛ አስደናቂ ነው! እያንዳንዱ ወጣት የይሖዋ አገልጋይ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ እንዲያነብብ አበረታታለሁ።”
በዓለም ዙሪያ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የሚሰበሰቡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች አሉ። አንተስ ከእነርሱ አንዱ ነህ? መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር በማንበብ ጥቅም ማግኘት ትፈልጋለህ? ለምን የአሌክሳንደርን ምሳሌ አትከተልም? እምብዛም አስፈላጊ ባልሆኑ ነገሮች የምታጠፋውን ጊዜ በመቀነስ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴህ ክፍል አድርገው። እንዲህ ካደረግህ በእርግጥ ትጠቀማለህ።