ሄኖክ ፈሪሃ አምላክ በሌለው ዓለም ውስጥ አካሄዱን ከአምላክ ጋር አድርጓል
ሄኖክ ፈሪሃ አምላክ በሌለው ዓለም ውስጥ አካሄዱን ከአምላክ ጋር አድርጓል
ዲያብሎስ ሰዎችን ሁሉ ከአምላክ ማራቅ እችላለሁ ብሎ ይከራከራል። ይህ ግድድሩ የሰመረለት የመሰለባቸው ወቅቶች ነበሩ። አቤል ከሞተ በኋላ ለአምስት መቶ ዓመታት ለማለት ይቻላል አንድም ሰው የታመነ የይሖዋ አገልጋይ ሆኖ አልተመላለሰም። ከዚህ ይልቅ ኃጢአትና ክፋት ነግሦ ነበር።
ሄኖክ ወደ መድረክ ብቅ ያለው መንፈሳዊነት ባዘቀጠበት በዚህ ወቅት ላይ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠር ሄኖክ በ3404 ከዘአበ እንደተወለደ ይጠቁማል። ሄኖክ በወቅቱ ከነበረው ትውልድ በተለየ መልኩ የአምላክን ሞገስ አግኝቶ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያኖች በእምነት ምሳሌ አድርጎ ከጠቀሳቸው የይሖዋ አገልጋዮች መካከል ሄኖክ ይገኝበታል። ለመሆኑ ሄኖክ ማን ነበር? ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መጋፈጥ ነበረበት? እንዴትስ ተቋቋማቸው? ያሳየው የአቋም ጽናት ለእኛ ምን ትርጉም አለው?
ሄኖስ በኖረበት ዘመን ይኸውም ከሄኖክ ዘመን አራት መቶ ዓመታት ገደማ በፊት አንስቶ “በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW ] ስም መጠራት ተጀመረ።” (ዘፍጥረት 4:26) ከሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ አንስቶ አምላክን በስሙ መጥራት የተለመደ ነበር። ስለሆነም ሄኖስ በሕይወት ሳለ ከእምነትና ከንጹሕ አምልኮ በመነሳት የይሖዋን ስም መጥራት እንዳልተጀመረ ግልጽ ነው። አንዳንድ የዕብራይስጥ ቋንቋ ምሁራን ዘፍጥረት 4:26 የአምላክን ስም “በሚያረክስ መንገድ መጠራት ተጀመረ” ወይም የአምላክን ስም “ማርከስ በዚያን ጊዜ ተጀመረ” ተብሎ መነበብ ይገባዋል ይላሉ። ሰዎች የይሖዋን ስም ለራሳቸው መጠሪያነት ተጠቅመውበት አሊያም ለአምልኮ ወደ አምላክ ያቀርቡናል ብለው ለሚያስቧቸው ሌሎች ሰዎች ይህን ስም አውጥተው ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ስሙን ለጣዖት ሰጥተው ይሆናል።
‘ሄኖክ አካሄዱን ከእውነተኛው አምላክ ጋር አደርጓል’
ሄኖክ አምላካዊ አክብሮት በሌላቸው ሰዎች መካከል ቢኖርም ‘አካሄዱን ከእውነተኛው አምላክ ከይሖዋ ጋር’ አድርጓል። አያት ቅድመ አያቶቹ የነበሩት ሴት፣ ሄኖስ፣ ቃይናን፣ መላልኤልና ያሬድ አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር አደረጉ አልተባለላቸውም። ቢያንስ ቢያንስ በአኗኗር መንገዱ ከእነርሱ እንደተለየው እንደ ሄኖክ አላደረጉም።—ዘፍጥረት 5:3-27
ሄኖክ አካሄዱን ከይሖዋ ጋር አድርጓል መባሉ ከመለኮታዊ ፈቃድ ጋር ተስማምቶ በመኖሩ ምክንያት ከአምላክ ጋር መቀራረቡን እንዲሁም ወዳጅነት መፍጠሩን የሚያሳይ ነው። ይሖዋ የሄኖክን ለአምላክ የማደር ባሕርይ ተቀብሎታል። እንዲያውም የግሪክ ሴፕቱጀንት ትርጉም ሐዋርያው ጳውሎስ ከገለጸው ሐሳብ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ‘ሄኖክ አምላክን አስደስቶታል’ ይላል።—ዘፍጥረት 5:22፤ ዕብራውያን 11:5
ሄኖክ ከይሖዋ ጋር ለነበረው መልካም ግንኙነት መሠረት የሆነው እምነቱ ነው። የአምላክ “ሴት” በምታስገኘው “ዘር” ላይ እምነት ኖሮት መሆን አለበት። ሄኖክ አዳም ላይ ደርሶበት ከነበረ አምላክ በኤደን ገነት ከመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ጋር ስለነበረው ግንኙነት አንዳንድ መረጃዎችን አግኝቶ ሊሆን ይችላል። ሄኖክ ስለ አምላክ ያገኘው ይህ እውቀት አምላኩን ‘ከልብ እንዲፈልግ’ አድርጎታል።—ዘፍጥረት 3:15፤ ዕብራውያን 11:6, 13
በሄኖክም ሆነ በእኛ ላይ እንደታየው ከይሖዋ ጋር መልካም ግንኙነት ለመመሥረት ስለ አምላክ እውቀት መሰብሰብ ብቻ አይበቃም። ከአንድ ሰው ጋር ያለንን ወዳጅነት ከፍ አድርገን የምንመለከተው ከሆነ አስተሳሰባችንና ድርጊታችን በእሱ አመለካከት አይቀረጽምን? ወዳጅነቱን ሊያበላሽ የሚችል ነገር ከመናገርና ከማድረግ እንቆጠባለን።
እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ አንዳንድ ለውጦችን ለማድረግ ስናስብ ለውጡ ከሌላው ወገን ጋር ያለንን ወዳጅነት በምን መልኩ እንደሚነካብን ግምት ውስጥ ማስገባታችን ይቀራል?በተመሳሳይም ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ያለን ፍላጎት በምናደርገው ነገር ላይ ተጽእኖ ያሳድራል። በመጀመሪያ ደረጃ እሱ ስለሚወደውና ስለሚጠላው ነገር ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ያስፈልጋል። ከዚያም በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን እሱን ለማስደሰት ጥረት በማድረግ ባገኘነው እውቀት መመራት ያስፈልገናል።
አዎን፣ አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር ለማድረግ እሱን ማስደሰት ይኖርብናል። ሄኖክ ለብዙ መቶ ዓመታት ያደረገው ይህንኑ ነው። እንዲያውም ሄኖክ “አካሄዱን” ከአምላክ ጋር እንዳደረገ የሚገልጸው የዕብራይስጥ ግሥ ተደጋጋሚና ቀጣይነት ያለው ድርጊት መከናወኑን ያመለክታል። “አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር” አድርጎ የነበረው ሌላው ሰው ኖኅ ነው።—ዘፍጥረት 6:9
ሄኖክ ሚስት አግብቶ “ወንዶችም ሴቶችም” የወለደ አባወራ ነበር። ከወንዶች ልጆቹ መካከል አንዱ ማቱሳላ ነው። (ዘፍጥረት 5:21, 22) ሄኖክ ቤተሰቡን በሚገባ ለማስተዳደር የሚችለውን ሁሉ እንዳደረገ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ፈሪሃ አምላክ በሌላቸው ሰዎች መካከል ይኖር ስለነበር አምላክን ማገልገል እንዲህ ቀላል አልሆነለትም። ከዚያ ትውልድ መካከል በይሖዋ ላይ እምነት የነበረው የኖኅ አባት ላሜሕ ብቻ ሳይሆን አይቀርም። (ዘፍጥረት 5:28, 29) ቢሆንም ሄኖክ እውነተኛውን አምልኮ በድፍረት ተከትሏል።
ሄኖክ ለአምላክ ታማኝ ሆኖ እንዲቀጥል የረዳው ምን ነበር? የይሖዋን ስም ከሚያረክሱ ወይም አምላክን ለሚያመልክ ሰው ለጓደኝነት ከማይመረጡ ሰዎች ጋር ወዳጅነት እንዳልመሠረተ ጥርጥር የለውም። ሄኖክ በጸሎት የይሖዋን እርዳታ መጠየቁ ፈጣሪውን ሊያሳዝን ከሚችል ነገር ለመራቅ ባደረገው ቁርጥ ውሳኔ እንዲገፋበት አጠንክሮት መሆን አለበት።
አምላካዊ አክብሮት ስለሌላቸው ሰዎች የተነገረ ትንቢት
አምላካዊ አክብሮት በሌላቸው ሰዎች መካከል ስንኖር ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎችን መጠበቅ በጣም አስቸጋሪ ይሆንብናል። ሆኖም ሄኖክ በክፉዎች ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ ጠንካራ የፍርድ መልእክት ተናግሯል። በአምላክ ይሁዳ 14, 15
መንፈስ ተመርቶ “እነሆ፣ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ፣ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል” በማለት ትንቢት ተናግሯል።—ይህ መልእክት ጠማማ አካሄድ ይከተሉ በነበሩ የማያምኑ ሰዎች ላይ ምን ለውጥ ያስከትል ይሆን? እነዚህ ከባድ ቃላት ሄኖክ እንዲጠላ ምናልባትም ማፌዣና ማላገጫ እንዲሆን እንዲሁም እንዲዛትበት አድርገውታል ብሎ ማሰቡ ከእውነታው መራቅ አይሆንም። አንዳንዶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጸጥ ሊያሰኙት ሳይፈልጉ አልቀረም። ይሁን እንጂ ሄኖክ ይህ ሁኔታ አላርበደበደውም። ጻድቁ አቤል ምን እንደደረሰበት ያውቅ የነበረ ሲሆን እሱም የመጣው ቢመጣ አምላክን ከማገልገል ዝንፍ ላለማለት ቆርጦ ነበር።
“እግዚአብሔር ወስዶታል”
ሄኖክ ‘በአምላክ ከመወሰዱ’ በፊት ለሕይወቱ በሚያሰጋ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንደነበረ ግልጽ ነው። (ዘፍጥረት 5:24) ይሖዋ ታማኝ የሆነው የእሱ ነቢይ በጨካኝ ጠላቶች እጅ እንዲሠቃይ አልፈቀደም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው “ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ።” (ዕብራውያን 11:5) ብዙ ሰዎች ሄኖክ አምላክ ወደ ሰማይ ወስዶት እዚያ ይኖራል እንጂ አልሞተም ይላሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በግልጽ “ከሰማይም ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፣ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” ሲል ተናግሯል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ለሚሄዱት ሁሉ “ቀዳሚ” ነበር።—ዮሐንስ 3:13፤ ዕብራውያን 6:19, 20
ታዲያ ሄኖክ የት ደረሰ? ‘ሞትን እንዳያይ ተወሰደ’ የሚለው አባባል አምላክ ሄኖክ በተመስጦ ትንቢታዊ ራእይ እንዲመለከት አድርጎት በዚያው በሞት እንዲያንቀላፋ አድርጎታል ማለት ሊሆን ይችላል። እንደዚያ ባለ ሁኔታ ውስጥ ሄኖክ የሞትን ጣር አልቀመሰም። ከዚያም ይሖዋ በሙሴ ላይ እንዳደረገው ሁሉ የሄኖክን አስከሬን ስለ ሰወረው ይመስላል “አልተገኘም።”—ዘዳግም 34:5, 6
ሄኖክ 365 ዓመት ብቻ የኖረ ሲሆን እንደ አብዛኛዎቹ አያት ቅድመ አያቶቹ ረጅም ዘመን አልኖረም። ሆኖም ይሖዋን ለሚያፈቅሩ ሰዎች ዋናው ቁም ነገር እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ እሱን በታማኝነት ማገልገላቸው ነው። ሄኖክ “ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና” ይህን እንዳደረገ እናውቃለን። ይሖዋ ይህን ለሄኖክ እንዴት አድርጎ እንደመሰከረለት ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ አይናገሩም። የሆነ ሆኖ ሄኖክ ከመሞቱ በፊት የአምላክን ሞገስ እንዳገኘ ማረጋገጫ ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን ይሖዋ በትንሣኤ እንደሚያስበው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
የሄኖክን እምነት ምሰሉ
አምላካዊ አክብሮት የነበራቸው ሰዎች ያሳዩትን እምነት መምሰል እንችላለን። (ዕብራውያን 13:7) ሄኖክ የመጀመሪያው ታማኝ የአምላክ ነቢይ በመሆን ያገለገለው በእምነቱ ነበር። ሄኖክ የኖረበት ዓለም እንደ እኛው ሁሉ ዓመፀኛ፣ ስሙን የሚያረክስና ፈሪሃ አምላክ የሌለው ነበር። ሆኖም ሄኖክ በዚያን ጊዜ የነበረውን ዓለም አካሄድ አልተከተለም። እውነተኛ እምነት የነበረውና ለአምላክ ያደሩ በመሆን ረገድ ምሳሌ ነበር። አዎን፣ ይሖዋ ከባድ የፍርድ መልእክት እንዲያውጅ የሰጠው ቢሆንም ይህን ተልእኮውን እንዲወጣ ብርታት ሰጥቶታል። ሄኖክ ተልእኮውን በድፍረት የተወጣ ሲሆን ጠላቶቹ እንዳያጠፉት አምላክ ጥበቃ አድርጎለታል።
ሄኖክ እንደነበረው ያለ እምነት ለማዳበር ጥረት ካደረግን ይሖዋ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት መልእክቱን እንድናውጅ ብርታት ይሰጠናል። የሚያጋጥመንን ተቃውሞ በድፍረት እንድንጋፈጥ ይረዳናል፤ እንዲሁም ለአምላክ ያደርን መሆናችን ፈሪሃ አምላክ ከሌላቸው ሰዎች የተለየን እንድንሆን ያደርገናል። እምነት አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር እንድናደርግና ልቡን ደስ የሚያሰኝ ጠባይ እንድናሳይም ያስችለናል። (ምሳሌ 27:11) ጻድቁ ሄኖክ እምነቱ አምላካዊ ፍርሃት ባልነበረው ዓለም ውስጥ አካሄዱን ከአምላክ ጋር አድርጎ እንዲሳካለት እንደረዳው ሁሉ እኛም ሊሳካልን ይችላል።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መጽሐፍ ቅዱስ ከመጽሐፈ ሔኖክ ይጠቅሳልን?
መጽሐፈ ሄኖክ የአዋልድ መጽሐፍ ነው። ሄኖክ ጽፎታል የሚባለው ሐሰት ነው። በሁለተኛው ወይም በአንደኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አካባቢ እንደተጻፈ የሚገመተው ይህ መጽሐፍ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ በአጭሩ የተገለጸውን የሄኖክ ታሪክ መሠረት ያደረገ የተጋነነ የአይሁድ አፈ ታሪክ ነው። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል የሚያፈቅሩ ሰዎች ይህን ማወቃቸው ብቻ መጽሐፉን እንዳይቀበሉት ያደርጋቸዋል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሄኖክ “እነሆ፣ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ፣ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል” በማለት የተናገራቸውን ትንቢታዊ ቃላት የያዘው የይሁዳ መጽሐፍ ብቻ ነው። (ይሁዳ 14, 15) ብዙ ምሁራን ሄኖክ በዘመኑ ስለነበረው አምላካዊ ፍርሃት የሌለው ትውልድ የተነገረው ይህ ትንቢት በቀጥታ የተጠቀሰው ከመጽሐፈ ሄኖክ ላይ ነው ብለው ይከራከራሉ። ይሁዳ ተአማኒነት የሌለውን የአዋልድ መጽሐፍ እንደ ምንጭነት ይጠቀምበታል ማለት ይቻላል?
ይሁዳ ሄኖክ የተናገረውን ትንቢት እንዴት እንዳወቀ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አልተገለጸም። በሰፊው ተቀባይነት ያገኘና ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የታመነ ታሪክ እንደ ምንጭ ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል። በፈርኦን ፊት ሙሴን የተቃወሙትን ጠንቋዮች ኢያኔስንና ኢያንበሬስን ጳውሎስ በስም ሲጠቅስ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር ማድረጉ እንደነበረ ግልጽ ነው። የመጽሐፈ ሄኖክ ጸሐፊ እንደዚህ ያለ ጥንታዊ ምንጭ አግኝቷል ከተባለ ይሁዳ ማግኘት አይችልም የምንልበት ምን ምክንያት አለን? a—ዘጸአት 7:11, 22፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:8
ሄኖክ አምላካዊ አክብሮት የሌላቸውን ሰዎች አስመልክቶ የተናገረውን መልእክት ይሁዳ ከየት እንዳገኘው ማወቁ እምብዛም አስፈላጊ አይደለም። ይሁዳ መልእክቱን በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት መጻፉ አስተማማኝነቱን ያረጋግጣል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ትክክለኛ ያልሆነውን ነገር እንዳይጽፍ ጠብቆታል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስም እንዲሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሌላ ቦታ ላይ የማይገኝ ሐሳብ ጠቅሷል። ይህ ሐሳብ ሙሴ በግብፅ አገር ስላገኘው ትምህርት፣ ከግብፅ ሲሸሽ ዕድሜው 40 ዓመት እንደነበረ፣ በምድያም 40 ዓመት እንደቆየና የሙሴን ሕግ በማስተላለፍ ረገድ መልአክ የተጫወተውን ሚና የሚገልጽ ነው።—ሥራ 7:22, 23, 30, 38
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሄኖክ የይሖዋን መልእክት በድፍረት አውጆአል