እውነተኛ እምነት ማዳበር ትችላለህ
እውነተኛ እምነት ማዳበር ትችላለህ
ሣራ ጄን 19 ዓመት ሲሞላት የማሕጸን ካንሰር እንዳለባት አወቀች። ቀዶ ሕክምና ከተደረገላት በኋላ ግን ጤናዋ በመሻሻሉ የወደፊቱ ጊዜ ብሩህ ሆኖ ታያት። እንዲያውም በጣም አዎንታዊ ከመሆኗ የተነሣ 20 ዓመት ሲሞላት ለማግባት በማሰብ ለሠርጓ አንዳንድ ዝግጅቶች ማድረግ ጀመረች። ሆኖም በዚያው ዓመት ካንሰሩ በማገርሸቱ በሕይወት የምትቆየው ለተወሰኑ ሳምንታት ብቻ እንደሆነ ተገነዘበች። ሣራ ጄን 21 ዓመት ሊሞላት ትንሽ ሲቀራት ሰኔ 2000 ሞተች።
ሣራ ጄንን ለመጠየቅ ሆስፒታል የመጡትን እንግዶች በጣም ያስገረማቸው ነገር ቢኖር ሣራ ጄን በአምላክና በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የነበራትን ጽኑ እምነት ጨምሮ የወደፊቱን ጊዜ በትምክህት እንደምትጠባበቅ የሚያሳየው በፊትዋ ላይ የሚነበበው የተረጋጋ ስሜት ነበር። ከፊትዋ አሳዛኝ ነገር ይጠብቃት የነበረ ቢሆንም ትንሣኤ እንደምታገኝና ወዳጆቿን በሙሉ እንደገና እንደምታያቸው እርግጠኛ ነበረች። (ዮሐንስ 5:28, 29) ሣራ “ሁላችሁንም በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ አገኛችኋለሁ” በማለት ተናግራለች።
አንዳንዶች ይህ ዓይነቱ እምነት ከንቱ ቅዠት ነው ብለው ያስባሉ። “ከሞት በኋላ ሕይወት አለ ማለት” አሉ ሉዶቪክ ኬኔዲ “የመጨረሻው መለከት ሲነፋ ለምለም በሆነች ኤደን ውስጥ እምቢልታ እየተነፋላቸው ከእነርሱ በፊት ከሞቱትና ከእነርሱ በኋላ ከሚመጡት ሰዎች ጋር ዓለማቸውን እንደሚቀጩ የሚያስቡ ስጋት ያደረባቸው ሰዎች እምነት እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?” ሆኖም ለዚህ አባባላቸው አንድ ጥያቄ እናነሳለን። ምክንያታዊ የሆነው የትኛው ነው? ኬኔዲ እንዳሉት “ሕይወት ማለት የአሁኑ ብቻ ስለሆነ በዚህ ሕይወት የቻልነውን ሁሉ ማድረግ አለብን” የሚለው ነው ወይስ በአምላክና እርሱ በሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ማመን? ሣራ ጄን ሁለተኛውን መርጣለች። እንዲህ ዓይነቱን እምነት ማዳበር የቻለችው እንዴት ነው?
‘እግዚአብሔርን ፈልግ ... አግኘውም’
በአንድ ሰው ላይ እምነት መጣልና በእርሱ መታመን ከፈለግህ ግለሰቡን ማወቅ እንዲሁም የሚያስብበትንና ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ መገንዘብ ይኖርብሃል። በዚህ ሂደት ውስጥ ልብና አእምሮ የሚጫወቱት ሚና አለ። በአምላክ ላይ እውነተኛ እምነት መገንባትም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። አምላክን ማወቅ፣ ባሕርያቱንና ስብዕናውን መገንዘብ እንዲሁም በተናገራቸውና ባደረጋቸው ነገሮች ረገድ ምን ያህል እምነት ሊጣልበት የሚችል ሆኖ እንደተገኘ ማስተዋል ይኖርብሃል።—መዝሙር 9:10፤ 145:1-21
አንዳንዶች ይህ የማይቻል እንደሆነ ይሰማቸዋል። በእነርሱ አመለካከት አምላክ በጣም ሩቅና ሊደረስበት የማይችል ነው። ለዚያውም ካለ። ተጠራጣሪ ሰው “አምላክ እንደ ሣራ ጄን ላሉት ክርስቲያኖች እውን የሆነውን ያህል ለቀረነውስ የማይገለጥልን ለምንድን ነው?” በማለት ይጠይቃል። ይሁን እንጂ አምላክ በእርግጥ ሩቅና ሊደረስበት የማይችል ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ አቴንስ ለሚገኙት ፈላስፎችና ምሁራን በሰጠው ንግግር ላይ የሚከተለውን ብሎ ነበር:- ‘ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረው አምላክ ሰዎች እርሱን [አምላክን] ለማግኘት የሚያስፈልጋቸውን’ ሁሉ ሰጥቷል። እንዲያውም ጳውሎስ “ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም” በማለት ተናግሯል።—ሥራ 17:24-27
ታዲያ ‘አምላክን ፈልገህ ማግኘት’ የምትችለው እንዴት ነው? አንዳንዶች በዙሪያቸው ያለውን አጽናፈ ዓለም በመመልከት ብቻ አምላክን ማግኘት ችለዋል። ለብዙዎች ይህ በራሱ ፈጣሪ የመኖሩን ሃቅ አረጋግጦላቸዋል። a (መዝሙር 19:1፤ ኢሳይያስ 40:26፤ ሥራ 14:16, 17) እነዚህ ሰዎች የሐዋርያው ጳውሎስን ስሜት ይጋራሉ:- “የማይታየው ባሕርይ [የአምላክ] እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና።”—ሮሜ 1:20፤ መዝሙር 104:24
መጽሐፍ ቅዱስ ያስፈልግሃል
ይሁንና በፈጣሪ ላይ እውነተኛ እምነት ለማዳበር እርሱ ያዘጋጀውን አንድ ሌላም ነገር ማግኘት ይኖርብሃል። ይህ ነገር ምንድን ነው? አምላክ ፈቃዱንና ዓላማውን የገለጸበት በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ሆኖም አንዳንዶች “እንዴ ምን ነካህ፣ መጽሐፍ ቅዱስን እንከተላለን እያሉ ስንት አሳፋሪ ተግባራት የሚፈጽሙ ሰዎችን እያየህ እንዴት በመጽሐፍ ቅዱስ አምናለሁ ትላለህ?” ይሉ ይሆናል። ሕዝበ ክርስትና በግብዝነት፣ በጭካኔና በሥነ ምግባር ብልግና ረገድ አስደንጋጭ ታሪክ እንዳስመዘገበች አሌ አይባልም። ሆኖም የማመዛዘን ችሎታ ያለው ማንኛውም ሰው ሕዝበ ክርስትና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እከተላለሁ ብትልም በተግባር ላይ ግን እንደማታውለው ማስተዋል ይችላል።—ማቴዎስ 15:8
ብዙዎች አምላክን እናመልካለን ቢሉም ‘የዋጃቸውን ጌታ እንኳ እንደሚክዱ’ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንቅቋል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል” በማለት ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 2:1, 2) ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች “ዓመፀኞች” ስለሆኑ በመጥፎ ድርጊቶቻቸው ተለይተው እንደሚታወቁ ገልጿል። (ማቴዎስ 7:15-23) ሕዝበ ክርስትና ያስመዘገበችውን ታሪክ መሠረት አድርጎ የአምላክን ቃል ማቃለል ደብዳቤውን ያመጣልን ሰው ምግባረ ብልሹ ስለሆነ ብቻ ከአንድ የምናምነው ወዳጃችን የተላከልንን ደብዳቤ እንደመወርወር ይቆጠራል።
ያለ አምላክ ቃል እውነተኛ እምነት መገንባት አይቻልም። ይሖዋ ለነገሮች ያለውን አመለካከት የገለጸልን በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ውስጥ ብቻ ነው። አምላክ መከራና ስቃይ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? ሁኔታውን ለማስተካከልስ ምን አድርጓል? የሚሉትን ለመሰሉ ዘወትር የሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ይሰጠናል። (መዝሙር 119:105፤ ሮሜ 15:4) ሣራ ጄን መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል መሆኑን ታምን ነበር። (1 ተሰሎንቄ 2:13፤ 2 ጴጥሮስ 1:19-21) እንዴት? ወላጆቿ ያስተማሯትን ሁሉ አሜን ብላ ስለተቀበለች ሳይሆን ጊዜ ወስዳ መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የተገኘ አስደናቂ መጽሐፍ መሆኑን የሚያረጋግጡትን ማስረጃዎች በሃቀኝነት በመመርመሯ ነው። (ሮሜ 12:2) ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከመሠረታዊ ሥርዓቶቹ ጋር ተስማምተው በሚኖሩ ሰዎች ላይ የሚያሳድረውን ከፍተኛ ተጽእኖ መመልከት ችላለች። መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? b እንደሚሉት ባሉ ጽሑፎች እርዳታ መጽሐፍ ቅዱስ በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን የሚያረጋግጡትን በራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ብዙ ማስረጃዎች በጥንቃቄ መርምራለች።
“እምነት ከመስማት ነው”
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን መያዙ ብሎም በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን ማመኑ ብቻ አይበቃም። ሐዋርያው ጳውሎስ “እምነት ከመስማት ነው” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 10:17) እምነትን የሚገነባው መጽሐፍ ቅዱስ መያዙ ሳይሆን የሚለውን መስማቱ ነው። ቃሉን በማንበብና በማጥናት አምላክ የሚለውን ‘መስማት’ ትችላለህ። ልጆችም ሳይቀሩ እንዲህ ማድረግ ይችላሉ። የጢሞቴዎስ እናትና አያት ጢሞቴዎስን ‘ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቅዱሳን መጻሕፍትን’ እንዳስተማሩት ጳውሎስ ተናግሯል። ታዲያ ይህ ማለት የጢሞቴዎስን አእምሮ ለማጠብ አንድ ዓይነት ሙከራ ተደርጎ ነበር ማለት ነው? የለም! ጢሞቴዎስ አልተሞኘም ወይም አልተታለለም። ከዚህ ይልቅ የሰማውንና ያነበበውን ነገር ‘እንዲያምንበት ተደርጎ’ ነበር።—2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:14, 15 NW
ሣራ ጄንም ያመነችው በተመሳሳይ መንገድ ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት የቤሪያ ሰዎች እርስዋም ‘ቃሉን [ከወላጆችዋና ከሌሎች አስተማሪዎቿ] በሙሉ ፈቃድ ተቀብላለች።’ ልጅ ሳለች ወላጆችዋ የነገሯትን ሁሉ እንዲሁ በጸጋ እንደተቀበለች ምንም ጥርጥር የለውም። እያደገች ስትሄድ ግን እንዲህ አላደረገችም። ‘ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? በማለት መጻሕፍትን በጥንቃቄ ትመረምር’ ነበር።—ሥራ 17:11
እውነተኛ እምነት ማዳበር ትችላለህ
አንተም ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንደገለጸው ዓይነት እውነተኛ እምነት ማዳበር ትችላለህ። ጳውሎስ እንደተናገረው እንዲህ ዓይነቱ እምነት “ተስፋ ያደረግነው ነገር እንደሚፈጸም እርግጠኛ የምንሆንበት፤ የማናየውም ነገር እውን መሆኑን የምንረዳበት ነው።” (ዕብራውያን 11:1 አ.መ.ት፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እንዲህ ዓይነቱ እምነት ካለህ አምላክ ስለ ትንሣኤ የሰጠውን ተስፋ ጨምሮ ሌሎች ተስፋ የምታደርጋቸው ነገሮች በሙሉ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ፍጹም እርግጠኛ ትሆናለህ። እነዚህ ተስፋዎች በምኞት ላይ የተመሠረቱ ሳይሆኑ አስተማማኝ ዋስትና ያላቸው ስለመሆኑ ጽኑ እምነት ይኖርሃል። ይሖዋ የገባውን ቃል ሳይፈጽም ቀርቶ እንደማያውቅ ትገነዘባለህ። (ኢያሱ 21:45፤ 23:14፤ ኢሳይያስ 55:10, 11፤ ዕብራውያን 6:17, 18) ቃል የተገባለት የአምላክ አዲስ ዓለም ልክ የመጣ ያህል እውን ይሆንልሃል። (2 ጴጥሮስ 3:13) በተጨማሪም ይሖዋ አምላክ፣ ኢየሱስ ክርስቶስና የአምላክ መንግሥት እንዲሁ ሐሳብ የወለዳቸው ሳይሆኑ እውን መሆናቸውን በእምነት ዓይንህ ታያለህ።
እውነተኛ እምነት ለማዳበር በራስህ መፍጨርጨር አያስፈልግህም። ይሖዋ ቃሉን በቀላሉ እንድናገኘው ከማድረጉም በተጨማሪ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በአምላክ ላይ እምነት እንዲያዳብሩ ለመርዳት በሙሉ ነፍሱ የሚሠራ ዓለም አቀፍ የክርስቲያን ጉባኤ አቋቁሟል። (ዮሐንስ 17:20፤ ሮሜ 10:14, 15) ይሖዋ በዚህ ዝግጅት በኩል በሚሰጠው እርዳታ በሙሉ ተጠቀም። (ሥራ 8:30, 31) እንዲሁም እምነት የአምላክ መንፈስ ፍሬ እንደመሆኑ መጠን መንፈሱ በአምላክ ላይ እውነተኛ እምነት እንድታዳብር እንዲረዳህ ያለማቋረጥ ጸልይ።—ገላትያ 5:22
በአምላክና በቃሉ ላይ እምነት እንዳለው በሚናገር በማንኛውም ሰው ላይ በሚያሾፉ ተጠራጣሪዎች ምክንያት ተስፋ አትቁረጥ። (1 ቆሮንቶስ 1:18-21፤ 2 ጴጥሮስ 3:3, 4) እርግጥ እውነተኛ እምነት ራሱ እንደነዚህ ያሉትን ፍላጻዎች ለመቋቋም ያደረግኸውን ቁርጥ ውሳኔ በማጠናከር ረገድ የሚጫወተው ሚና የላቀ ነው። (ኤፌሶን 6:16) ሣራ ጄን ይህ እውነት ሆኖ አግኝታዋለች። ሊጠይቋት ወደ ሆስፒታል የሚመጡትን ሰዎች ሁልጊዜ እምነታችሁን አጠንክሩ በማለት ታበረታታቸው ነበር። አዘውትራ “እውነትን የራሳችሁ አድርጉ” በማለት ትናገር ነበር። “የአምላክን ቃል አጥኑ። ከአምላክ ድርጅት ጋር ተባበሩ። ዘወትር ጸልዩ። በይሖዋ አገልግሎት ንቁ ተሳትፎ አድርጉ።”—ያዕቆብ 2:17, 26
ሣራ ጄን በአምላክና በትንሣኤ ላይ የነበራትን እምነት ያስተዋለች አንዲት ነርስ “በእርግጥም በዚህ ነገር ላይ ያለሽ እምነት ጠንካራ ነው” በማለት ተናግራለች። አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆናም ይህን የመሰለ ብሩህ አመለካከት ልትይዝ የቻለችበትን ምክንያት ስትጠየቅ “በይሖዋ ላይ ያለኝ እምነት ነው። እርሱ እውነተኛ ጓደኛዬ ስለሆነ በጣም እወድደዋለሁ” በማለት መልሳለች።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) በሚል ርዕስ በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን መጽሐፍ ተመልከት።
b በይሖዋ ምሥክሮች የታተመ።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጢሞቴዎስ ‘ከልጅነቱ ጀምሮ’ “ቅዱሳን መጻሕፍትን” ከእናቱና ከሴት አያቱ ተምሯል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቤርያ ሰዎች ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ በመመርመራቸው ተመስግነዋል
[ምንጭ]
ከ“ፍጥረት ፎቶ ድራማ ” የተወሰደ፣ 1914
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እምነትን የሚገነባው መጽሐፍ ቅዱስ መያዙ ሳይሆን የሚለውን መስማቱና በትኩረት መከታተሉ ነው
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ሁላችሁንም በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ አገኛችኋለሁ”