“የሃይማኖታዊ መቻቻል ቀን”
“የሃይማኖታዊ መቻቻል ቀን”
በፖላንድ የሚገኝ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆነች አንዲት ሴት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ባደረገችው ውይይት በመነሳሳት በትምህርት ቤትዋ “የሃይማኖታዊ መቻቻል ቀን” በሚል ርዕስ አንድ ፕሮግራም አዘጋጀች። በዚህ ዕለት ከተማሪዎቹ መካከል ፈቃደኛ የሆኑ ስለ እምነቶቻቸውና ልማዶቻቸው ለቀሩት ተማሪዎች አጠር ያለ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሐሳብ አቀረበች። ከተማሪዎቹ መካከል አንዳንዶቹ ካቶሊኮች፣ የቡድሃ እምነት ተከታዮችና የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ሦስት የይሖዋ ምሥክር ወጣቶች ወዲያው ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቀረቡ።
ፕሮግራሙ በሚካሄድበት ዕለት የመጀመሪያዋ ተናጋሪ የ15 ዓመቷ ማልቪና ነበረች። ከተናገረችው መካከል የሚከተለው ይገኝበታል:- “ብዙዎቻችሁ እዚህ ትምህርት ቤት ከመግባታችንም በፊት ታውቁን ነበር። ምክንያቱም በየቤታችሁ መጥተናል። ለምን ሁልጊዜ እንደዚያ እንደምናደርግ ይገርማችሁ ይሆናል። የክርስትና እምነት መስራች የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ስለምንከተል ነው። ክርስቶስ ሰዎች በሚገኙበት ስፍራ ሁሉ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ሰብኳል። ሐዋርያቱና ሌሎች የጥንት ክርስቲያኖችም እንደዚሁ አድርገዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በብዙ ቦታዎች አስቸጋሪ የእምነት ፈተናዎችን በጽናት ይቋቋማሉ። እኛ ግን በትምህርት ቤታችን ሰላም በማግኘታችን ደስተኞች ነን። ለዚህ ሁላችሁንም ልናመሰግናችሁ እንወዳለን!”
ማልቪና ንግግርዋን ስትደመድም እንዲህ አለች:- “ወደ ቤታችሁ የምንመጣበት ሌላው ምክንያት ስለምናስብላችሁ ነው። የሰው ዘር በቅርቡ ዓለምን የሚያናውጡ ክስተቶች ሲፈጸሙ እንደሚመለከት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ስለዚህ በሚቀጥለው ጊዜ ቤታችሁ ስንመጣ እባካችሁ ጊዜ ወስዳችሁ አዳምጡን። በምድር ላይ በገነት ለዘላለም አብረን መኖር እንዴት እንደምንችል ልንነግራችሁ እንፈልጋለን።”
ቀጣዩ ተናጋሪ ማቴዩሽ የተባለ የ15 ዓመት ወጣት ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ባለፉት ብዙ ዓመታት ምሥራቹን ለማሰራጨት በተለያዩ ዘዴዎች እንደተጠቀሙ ተናገረ። ለምሳሌ ያህል ድምፅ አልባ ፊልሞች በሚታዩበት በ1914 ምሥክሮቹ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተሰኘውን ተንቀሳቃሽ ምስልና ከድምፅ ጋር የተቀናጀ የስላይድ ፊልም ያሳዩ ነበር።
ማቴዩሽ የመንግሥቱን መልእክት በማሰራጨት ረገድ ራዲዮ የተጫወተውን ሚና እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች ስላዘጋጁት በብዙ ቋንቋዎች የኤሌክትሮኒክስ ኅትመት ሥራ ለማከናወን ስለሚያስችለው (MEPS) የኮምፒውተር ፕሮግራም አብራራ። በተጨማሪም ያለ ደም ሕክምና መስጠት ስለሚቻልባቸው መንገዶች ለሕክምና ባለሙያዎች መረጃ በመስጠት ረገድ የይሐዋ ምሥክሮች ያበረከቱትን እርዳታ ገለጸ። “በአሁኑ ወቅት፣ ታዋቂ የሆኑ የፖላንድ ዶክተሮች አቋማችንን የሚያደንቁ ከመሆኑም በላይ በየዓመቱ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑም ሕሙማን ያለ ደም ቀዶ ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን በአጽዕኖት ይናገራሉ” ብሏል።
ማቴዩሽ ንግግሩን የደመደመው ስለ መንግሥት አዳራሾች ግንባታ በመናገር ነበር:- “የመንግሥት አዳራሻችንን ለማየት ትፈልጋላችሁ? የመግቢያ ዋጋ አይከፈልም፤ ምፅዋትም አይሰበሰብም።” በሶስኖዊክ ስላለው የአውራጃ ስብሰባ ማዕከል ደግሞ እንዲህ ብሏል:- “ይህን ትልቅና ምቹ የመሰብሰቢያ ሕንፃ ልታዩት ይገባል። ለምን አብረን አንሄድም? እንዲያውም አንድ ሐሳብ አለን። ጓደኛችን ካታርዜና ያሰብነውን ትነግራችኋለች።”
ቀጥሎ የ15 ዓመቷ ካታርዜና በጋለ ስሜት እንዲህ አለች:- “በሶስኖዌክ የስብሰባ ማዕከል ወደሚደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ብትመጡ ደስ ይለናል። ወጣቶችን የሚመለከቱ ርዕሶች ይብራራሉ።” ካታርዜና የክርስቲያኖች ዋነኛ በዓል ስለሆነው ስለ ክርስቶስ ሞት መታሰቢያም ተናግራ ነበር። “ባለፈው ዓመት በዚያ በዓል ላይ በዓለም ዙሪያ 14 ሚልዮን ሰዎች ተገኝተዋል። እናንተስ በሚቀጥለው ስብሰባ ላይ አብራችሁን ለምን አትገኙም?” ስትል አድማጮቿን አበረታትታለች።
ንግግራቸውን አቅርበው ሲጨርሱ ማልቪና፣ ማቴዩሽና ካታርዜና የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የተባለውን መጽሐፍ እና የይሖዋ ምሥክሮችን እምነትና እንቅስቃሴ የሚዳስሱ ሁለት የቪዲዮ ክሮችን ለአስተማሪዎቻቸው አበረከቱ። a አስተማሪዎቹም በታሪክ ክፍለ ጊዜ እንደሚጠቀሙባቸው ቃል በመግባት በአድናቆት ተቀብለዋል።
በፕሮግራሙ መደምደሚያ ላይ የ12 ዓመቷ ማርቲና “ይሖዋ እናመሰግንሃለን” የሚለውን መዝሙር በፕሮግራሙ ላይ ለተገኙት ሁሉ ዘምራላቸዋለች። እነዚህ ወጣት ምሥክሮች ‘በአምላካቸው በመድፈር’ ድንቅ ምሥክርነት ሰጥተዋል። (1 ተሰሎንቄ 2:2) በሁሉም ቦታ ለሚኖሩ ወጣት ምሥክሮች እንዴት ግሩም ምሳሌ ናቸው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማልቪና ንግግሯን በትምህርት ቤት ከማቅረቧ ከጥቂት ቀናት በፊት ስትዘጋጅ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ካታርዜና ለንግግሯ የሚሆኑ ጥቅሶች ስትመርጥ