የአንባብያን ጥያቄዎች
የአንባብያን ጥያቄዎች
በኤርምያስ 7:16 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው አምላክ የሰጠው መመሪያ ክርስቲያኖች ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከክርስቲያን ጉባኤ ለተወገደ ኃጢያተኛ መጸለይ እንደሌለባቸው ይጠቁማልን?
ይሖዋ በከሃዲዋ ይሁዳ ላይ ፍርዱን ከተናገረ በኋላ ለኤርምያስ እንዲህ ብሎት ነበር:- “እንግዲህም አልሰማህምና ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ ስለ እነርሱም ልመናና ጸሎት አታድርግ፤ አትማልድላቸው።”—ኤርምያስ 7:16
ይሖዋ ኤርምያስን ለእስራኤላውያን እንዳይጸልይ የከለከለው ለምን ነበር? ሕጉን ሆን ብለው በመተላለፋቸው ምክንያት እንደሆነ ግልጽ ነው። ያለምንም እፍረት በግላጭ ‘ይሰርቁ፣ ይገድሉ፣ ያመነዝሩ፣ በሐሰት ይምሉና ለበኣል ያጥኑ እንዲሁም እንግዶች አማልክትን ይከተሉ’ ነበር። በዚህም ምክንያት ይሖዋ እነዚህን እምነተ ቢስ አይሁዳውያን “የኤፍሬምንም ዘር ሁሉ፣ ወንድሞቻችሁን ሁሉ እንደ ጣልሁ፣ እንዲሁ ከፊቴ እጥላችኋለሁ” ብሏቸዋል። ስለዚህ ኤርምያስም ሆነ ሌላ ማንም ሰው ይሖዋ ፍርዱን እንዲለውጥ መጸለዩ ተገቢ አይሆንም።—ኤርምያስ 7:9, 15
ከዚህ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ሐዋርያው ዮሐንስ ለአምላክ መቅረብ ስላለበት ትክክለኛ ጸሎት ጽፏል። በመጀመሪያ ለክርስቲያኖች “እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል” የሚል ማረጋገጫ ሰጣቸው። (1 ዮሐንስ 5:14) ከዚያም ስለሌሎች መጸለይን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ አለ:- “ማንም ወንድሙን ሞት የማይገባውን ኃጢአት ሲያደርግ ቢያየው ይለምን፣ ሞትም የማይገባውን ኃጢአት ላደረጉት ሕይወት ይሰጥለታል። ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ፤ ስለዚያ እንዲጠይቅ አልልም።” (1 ዮሐንስ 5:16) ኢየሱስም ‘የማይሰረይ’ ኃጢአት እንዳለ ተናግሯል፤ ይህም በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሰራ ኃጢአት ነው።—ማቴዎስ 12:31, 32
ይህ ታዲያ ንስሐ ሳይገቡ በኃጢአት ድርጊታቸው በመቀጠላቸው ከክርስቲያን ጉባኤ የሚወገዱ ሁሉ “ሞት የሚገባው” 2 ነገሥት 21:1-9፤ 2 ዜና መዋዕል 33:1-11
ኃጢአት እንደፈጸሙና ሊጸለይላቸው እንደማይገባ ያሳያልን? ሙሉ በሙሉ እንደዚያ ብሎ መደምደም አይቻልም። ምክንያቱም እንዲህ ካሉት ኃጢአቶች መካከል አንዳንዶቹ ሞት የሚገባቸው አይደሉም። እንዲያውም ሞት የሚገባው ኃጢአት ነው ወይም አይደለም ብሎ መናገር አስቸጋሪ ነው። የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ምናሴ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ይሆነናል። ለሐሰት አማልክት መሠዊያ ሠርቷል፣ የገዛ ወንድ ልጆቹን መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል፣ በመናፍስታዊ ድርጊት ተካፍሏል እንዲሁም የተቀረጸ ምስል በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ አቁሟል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ምናሴ እና ሕዝቡ “እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ” እንደሠሩ ይናገራል። ለእነዚህ ሁሉ ድርጊቶቹ ይሖዋ ምናሴን የቀጣው በሰንሰለት ታስሮ ወደ ባቢሎን በግዞት እንዲሄድ በማድረግ ነው።—ምናሴ የሠራቸው ኃጢአቶች ከባድ ቢሆኑም ሞት የሚገባቸው ዓይነት ነበሩን? እንዳልነበሩ ግልጽ ነው። ምክንያቱም ታሪኩ ሲቀጥል እንዲህ ይላል:- “በተጨነቀም ጊዜ አምላኩን እግዚአብሔርን ፈለገ፣ በአባቶቹም አምላክ ፊት ሰውነቱን እጅግ አዋረደ። ወደ እርሱም ጸለየ፤ እርሱም ተለመነው፣ ጸሎቱንም ሰማው፣ ወደ መንግሥቱም ወደ ኢየሩሳሌም መለሰው፤ ምናሴም እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ አወቀ።”—2 ዜና መዋዕል 33:12, 13
ስለዚህ አንድ ሰው ከጉባኤ ስለተወገደ ብቻ ሞት የሚገባው ኃጢአት ፈጽሟል ብለን ለመደምደም መቸኮል የለብንም። የግለሰቡ እውነተኛ የልብ ሁኔታ እስኪታይ ድረስ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። እንዲያውም አንድ ሰው እንዲወገድ የሚደረግበት አንዱ ዓላማ ወደ አእምሮው ተመልሶ ንስሐ እንዲገባና ኃጢአቱን እርግፍ አድርጎ እንዲተው ለማድረግ እንደሆነ ብዙ ጊዜ ይገለጻል።
ግለሰቡ በጉባኤው ውስጥ እስከሌለ ድረስ የሚያደርጋቸውን የልብም ሆነ የአመለካከት ለውጦች በቅድሚያ ሊያዩ የሚችሉት ለእርሱ ቀረቤታ ያላቸው ማለትም እንደ የትዳር ጓደኛ ወይም የቤተሰብ አባል ያሉት ናቸው። እንደዚህ ዓይነት ለውጥ ማድረጉን የተመለከቱ በደለኛው ሞት የሚገባው ኃጢአት እንዳልፈጸመ ሊደመድሙ ይችላሉ። ይህም በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው የአምላክ ቃል ብርታት እንዲያገኝና ይሖዋም እንደፈቃዱ አንድ ነገር እንዲያደርግለት እንዲጸልዩ ሊገፋፋቸው ይችላል።—መዝሙር 44:21፤ መክብብ 12:14
አንዳንዶች ኃጢአተኛው ንስሐ መግባቱን የሚያሳምን በቂ ማስረጃ መመልከት የሚችሉበት አጋጣሚ ቢኖራቸውም በአጠቃላይ ስለ ጉባኤው ግን እንደዚህ ለማለት አይቻልም። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስለተወገደ ሰው ሲጸለይ ሲሰሙ ሌሎች ግራ ሊጋቡ፣ ሊረበሹ ይባስ ብሎም ሊሰናከሉ ይችላሉ። ስለዚህ ለኃጢአተኛው መጸለይ እንዳለባቸው የሚሰማቸው ይህን በግል ማድረግ ያለባቸው ሲሆን ከዚህ በተረፈ ግን ጉዳዩን በጉባኤው ውስጥ ኃላፊነት ለተሰጣቸው ሽማግሌዎች መተው ይኖርባቸዋል።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምናሴ በይሖዋ ፊት ራሱን ባዋረደ ጊዜ ለፈጸማቸው ከባድ ኃጢአቶች ይቅርታ ተደርጎለታል
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Reproduced from Illustrierte Pracht - Bibel/Heilige Schrift des Alten und Neuen Testaments, nach der deutschen Uebersetzung D. Martin Luther’s