“ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?”
“ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?”
ወቅቱ የገና ሰሞን ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች የአንድን ሰው ልደት ለማክበር ይዘጋጃሉ። የማንን ልደት? የአምላክን ልጅ ወይስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በአካባቢው ገንኖ የነበረውን ሃይማኖት ለመለወጥ ቆርጦ የተነሣን ለእምነቱ ያደረ አንድ አይሁዳዊ? የአንድን የድሆች ተሟጋች? በሮማ መንግሥት ላይ ስጋት በመፍጠሩ ምክንያት ሞት የተፈረደበትን ዓመፀኛ ወይስ ራስን ስለማወቅና በሰው ውስጥ ስላለው የጥበብ ዓለም ልዩ ግምት የሚሰጥን ጠቢብ? እንግዲያው ‘ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥ ማን ነበር?’ ብለህ የምትጠይቅበት ምክንያት አለህ።
ኢየሱስ ራሱ ሰዎች ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡትን ምላሽ ለማወቅ ይፈልግ ነበር። በአንድ ወቅት ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” በማለት ጠይቋቸዋል። (ማርቆስ 8:27 አ.መ.ት ) ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መጠየቅ ያስፈለገው ለምንድን ነው? ብዙዎች እርሱን መከተላቸውን አቁመው ነበር። ሌሎች ደግሞ ሊያነግሡት ቢሞክሩም ሐሳባቸውን ሳይቀበለው በመቅረቱ ግራ ተጋብተውና ተበሳጭተው ነበር። በተጨማሪም ጠላቶቹ ሲፈትኑት ማንነቱን የሚያሳውቅ ምልክት ከሰማይ አላሳየም። ሐዋርያቱ ለዚህ ጥያቄ ምን ምላሽ ሰጥተው ይሆን? የአብዛኛውን ሕዝብ አመለካከት በማንጸባረቅ “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎችም ኤልያስ፣ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” በማለት መለሱለት። (ማቴዎስ 16:13, 14) ሆኖም አምላክን የሚሳደብ፣ አጭበርባሪ፣ ሐሰተኛ ነቢይ አልፎ ተርፎም እብድ የሚሉትን በጊዜው በፍልስጤም ይናፈሱ የነበሩትን የሚያንኳስሱ ቅጽል ስሞች ሳይጠቅሱ ቀርተዋል።
የኢየሱስ የተለያዩ ገጽታዎች
ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ይህንኑ ጥያቄ ለማንሳት ቢፈልግ “ምሁራን እኔን ማን ይሉኛል?” በማለት ያስቀምጠው ይሆናል። ዛሬም ቢሆን ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡትን መልሶች የተለያዩና በርካታ ናቸው በሚለው ማጠቃለል ይቻል ይሆናል። የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዴቪድ ትሬሲ “ኢየሱስ የተለያዩ ሰዎች በብዙ የተለያዩ አቅጣጫዎች የሚጋልቡት ፈረስ ሆኖ ቆይቷል” በማለት ተናግረዋል። ባለፉት መቶ ዓመታት የተለያዩ ምሁራን የኢየሱስን ትክክለኛ ማንነት አስመልክቶ ለሚነሳው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ባደረጉት ጥረት ውስብስብ የሆኑ በርካታ ማኀበራዊ፣ ሥነ ጽሑፋዊና ሥነ ስብዓታዊ (anthropological) ዘዴዎችን ተጠቅመዋል። ታዲያ ምሁራኑ እነዚህን ሁሉ ዘዴዎች ተጠቅመው ማንነቱን በተመለከተ የደረሱበት መደምደሚያ ምንድን ነው?
አንዳንድ ምሁራን በታሪክ የሚታወቀው ኢየሱስ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ የሚያሳስብ አይሁዳዊ ነቢይ ነበር በማለት ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የአምላክ ልጅ፣ መሲሕና ቤዛ መሆኑን ከመግለጽ ይቆጠባሉ። ብዙ ምሁራን ኢየሱስ ቀደም ሲል በሰማይ እንደነበረና ትንሣኤ እንዳገኘ በሚናገሩት የወንጌል ዘገባዎች ላይ ጥርጣሬ አላቸው። ለሌሎች ደግሞ፣ ኢየሱስ በምሳሌያዊ አኗኗሩና በትምህርቶቹ አማካኝነት ቀስ በቀስ ክርስትናን የወለዱ በርካታ እምነቶችን ያመነጨ ግለሰብ ከመሆን አያልፍም። ቲዎሎጂ ቱዴይ እንደገለጸው ደግሞ አንዳንዶች ኢየሱስን የሚመለከቱት “ተጠራጣሪ ፈላስፋ፣ በየቦታው የሚንከራተት ጠቢብ ወይም አምላክ ያነጋግረኛል ብሎ የሚያምን ባላገር፣ የአገር ሽማግሌ፣ ከኅብረተሰቡ በማፈንገጥ በራሱ ዓለም የሚኖር ባለቅኔ ወይም ቀድሞውንም ቢሆን በቋፍ ላይ ባሉትና ለማኅበራዊ ዓመፅ በተዘጋጁት ድህነት የደቆሳቸው የፍልስጤም ኋላ ቀር መንደሮች እየተዘዋወረ ያሻውን የሚናገር የጎዳና ላይ አዛኝ ቅቤ አንጓች” እንደሆነ አድርገው ነው።
ሌሎች እንግዳ የሆኑ አመለካከቶችም አሉ። የጥቁር ኢየሱስ ምስል በራፕ ሙዚቃ፣ ለሕዝብ እይታ በሚቀርቡ የሥነ ጥበብ ሥራዎችና በዳንስ ላይ እንኳ ሳይቀር ብቅ በማለት ላይ ነው። a ሌሎች ደግሞ ኢየሱስ ሴት ነበር የሚል አመለካከት አላቸው። በ1993 የበጋ ወቅት ካሊፎርኒያ ውስጥ በተደረገው ኦሬንጅ ካውንቲ የንግድ ትርዒት ላይ የተገኙ ሰዎች “ክርስቲን” የሚል ስያሜ የተሰጣትንና ዕርቃኗን በመስቀል ላይ የተሰቀለች የሴት “ክርስቶስ” ሐውልት ተመልክተዋል። በዚሁ ጊዜ ኒው ዮርክ ውስጥ “ክሪስታ” የተባለችና መስቀል ላይ የተሰቀለች ሴት “ኢየሱስ” ለእይታ ቀርባ ነበር። ሁለቱም ሐውልቶች ከፍተኛ ክርክር አስነስተዋል። እንዲሁም በ1999 መግቢያ ላይ “ብላቴናው ኢየሱስና ኤንጅል የተባለ ውሻው እርስ በእርስ ስላላቸው ፍቅር የሚናገር” መጽሐፍ ገበያ ላይ ውሎ የነበረ ሲሆን ግንኙነታቸው “በመንፈሳዊ የሚያነቃቃና ሁለቱ እርስ በእርስ ካላቸው ፍቅር የተነሣ አንዳቸው ለሌላው ሕይወታቸውን እንኳ ሳይቀር ለመሠዋት ዝግጁ መሆናቸውን የሚያሳይ” እንደሆነ ተደርጎ ተገልጾአል።
የኢየሱስን ትክክለኛ ማንነት ማወቅ አለማወቁ ለውጥ ያመጣል?
ኢየሱስ ማን እንደነበረና ዛሬም ማን እንደሆነ ማወቅ የሚኖርብህ ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ናፖሊዮን እንደተናገረው “ኢየሱስ ክርስቶስ በአካል መገኘት ሳያስፈልገው ተገዢዎቹን ለማዘዝና ለመግዛት” በመቻሉ ነው። ኢየሱስ ከፍተኛ ኃይል ባላቸው ትምህርቶቹና በአኗኗሩ ወደ ሁለት ሺህ ለሚጠጉ ዓመታት ያህል በቢልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስከትሏል። አንድ ጸሐፊ ነጥቡን ጥሩ አድርገው ገልጸውታል:- “በምድር ላይ የተነሡት የጦር ሠራዊቶችና የባሕር ኃይሎች በሙሉ፣ በምድር ላይ የነገሡ ነገሥታትና ለውይይት የተቀመጡ ምክር ቤቶች በሙሉ በአንድ ላይ ቢጠቃለሉ የኢየሱስን ያህል የሰው ልጆችን ሕይወት አልለወጡም።”
ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ማን እንደነበረና ዛሬም ማን እንደሆነ ማወቅ የሚኖርብህ ኢየሱስ በወደፊት ሕይወትህ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ስለሚያሳድር ነው። በአሁኑ ጊዜ በሰማይ የተቋቋመውና በኢየሱስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት ተገዥ የመሆን አጋጣሚ አለህ። በመከራ የተሞላችው ፕላኔታችን በኢየሱስ አመራር ሥር እጅግ አስደናቂ የሆነውን ሕይወታዊ ሀብቷንና ሥነ ምሕዳራዊ ሚዛኗን መልሳ ታገኛለች። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚያረጋግጥልን የኢየሱስ መንግሥት የተራቡትን ይመግባል፣ ድሆችን ይንከባከባል፣ የታመሙትን ይፈውሳል እንዲሁም የሞቱትን ያስነሣል።
እንዲህ ዓይነቱን በጣም አስፈላጊ መንግሥት የሚመራው ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ለማወቅ ሳትጓጓ አትቀርም። የሚቀጥለው ርዕስ የኢየሱስን ትክክለኛ ማንነት ማስተዋል እንድትችል ይረዳሃል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የኢየሱስን አካላዊ ቁመና አስመልክቶ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በሚያዝያ 1999 የንቁ! እትም ላይ የወጣውን “ኢየሱስ ምን ይመስል ነበር?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።