የምትታመነው እውን በሆነ አምላክ ነው?
የምትታመነው እውን በሆነ አምላክ ነው?
ሮበርት ኢ ፒሪ የተባለው አሳሽ ከሰባት ዓመት በፊት ማለትም በ1906 አይቼዋለሁ ያለውን ምድር ለማግኘት አሜሪካን ሙዝየም ኦቭ ናቹራል ሂስትሪ የተባለው ተቋም ያደራጀው አንድ ቡድን በአርክቲክ ክልል አሰሳ ጀመረ።
ፒሪ በሰሜን አሜሪካ ሰሜን ምዕራባዊ ጫፍ ከምትገኘው ኬፕ ኮሊጌት ከርቀት ዓይኑን አቅንቶ ሲመለከት ጫፋቸው በበረዶ የተሸፈኑ ተራሮችን የሚመስል ነገር አየ። ቦታውን ክሮከር ላንድ በማለት የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉለት ሰዎች መካከል በአንደኛው ስም ሰየመው። የቡድኑ አባላት ከፊት ለፊታቸው ኮረብታዎች፣ ሸለቆዎችና አናታቸው በበረዶ የተሸፈነ ተራሮች ሲመለከቱ ምንኛ ተደስተው ይሆን! ሆኖም ብዙም ሳይቆይ እየተመለከቱት ያሉት ነገር በአርክቲክ ምድር ላይ የተፈጠረ የሚያጥበረብር እይታ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ተገነዘቡ። ይህ ከባቢ አየር የፈጠረው ምስል ፒሪን አሞኝቶታል። ያን ሁሉ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጥሪታቸውን ያባከኑት እውን ላልሆነ ነገር ነበር።
በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች እውን ናቸው ብለው ለሚያምኑባቸው አማልክት ያደሩ ከመሆኑም ሌላ ጊዜያቸውን ይሠዉላቸዋል። በኢየሱስ ሐዋርያት ዘመን ሄርሜን እና ድያ የተባሉ አማልክት ይመለኩ ነበር። (ሥራ 14:11, 12) ዛሬም በሺንቶ፣ በሂንዱና በሌሎች የዓለም ሃይማኖቶች ውስጥ የሚመለኩ በሚልዮን የሚቆጠሩ አማልክት አሉ። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ።” (1 ቆሮንቶስ 8:5, 6) ታዲያ እነዚህ ሁሉ እውን የሆኑ አማልክት ሊሆኑ ይችላሉ?
“ማዳን የማይችሉ” አማልክት
ለምሳሌ ምስሎችንና ቅርጾችን በአምልኮ ስለመጠቀም አስብ። በጣዖታት የሚያምኑና በእነርሱ ተጠቅመው የሚጸልዩ ሰዎች ጣዖታት ለመባረክ ወይም ከአደጋ ለመታደግ የሚያስችል ከሰው በላይ የሆነ ኃይል እንዳላቸው አድርገው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ጣዖታት በእርግጥ ሊያድኑ ይችላሉን? እንደዚህ ያሉትን ነገሮች አስመልክቶ መዝሙራዊው እንደሚከተለው ሲል ዘምሯል:- “የአሕዛብ ጣዖታት የብርና የወርቅ፣ የሰው እጅ ሥራ ናቸው። አፍ አላቸው፣ አይናገሩምም፤ ዓይን አላቸው፣ አያዩምም፤ ጆሮ አላቸው፣ አይሰሙምም፤ እስትንፋስም በአፋቸው መዝሙር 135:15-17፤ ኢሳይያስ 45:20
የለም።” በእርግጥም ጣዖታት “ማዳን የማይችሉ” አማልክት ናቸው።—ጣዖታትን የሚሠሩ ሰዎች የእጆቻቸው ሥራ የሆኑት ጣዖታት ሕይወትና ኃይል እንዳላቸው አድርገው እንደሚያስቡ የታወቀ ነው። እንዲሁም በእነዚህ ጣዖታት ይታመናሉ። ነቢዩ ኢሳይያስ “[ጣዖቱን] በጫንቃቸው ላይ አንሥተው ይሸከሙታል በስፍራውም ያደርጉታል፣ በዚያም ይቆማል” በማለት ተናግሯል። አክሎም “ከስፍራውም ፈቀቅ አይልም፤ ሰውም ወደ እርሱ ቢጮኽ አይሰማውም ከመከራውም አያድነውም” ብሏል። (ኢሳይያስ 46:7) አንድ ጣዖት አምላኪዎቹ የቱንም ያህል በእርሱ ቢታመኑ እርሱ እንደሆነ ምንጊዜም በድን ነው። እንደነዚህ ያሉት የተቀረጹ ምስሎችና ቀልጠው የተሠሩ ሐውልቶች ‘ምንም የማይፈይዱ አማልክት’ ናቸው።—ዕንባቆም 2:18 አ.መ.ት
በዛሬው ጊዜም የመዝናኛውን ዓለም ኮከቦች፣ ታዋቂ ስፖርተኞችን፣ የፖለቲካ ሥርዓቶችና አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎችን እንደ ጣዖት ማምለክ ወይም ለእነርሱ ከአምላክ ያልተናነሰ ክብር መስጠት የተለመደ እየሆነ መጥቷል። ከዚህም በላይ ገንዘብ ለብዙዎች አምላክ ነው። በዚያም ሆነ በዚህ እነዚህ ጣዖታት ጨርሶ የማይገባቸው ቦታ ተሰጥቷቸዋል። የሚያምኑባቸው ሰዎች ተስፋ የሚያደርጓቸውን ነገሮች አይፈጽሙም፤ መፈጸምም አይችሉም። ለምሳሌ ያህል ሀብት ለብዙ ችግሮች መፍትሄ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሀብት ያለው ኃይል አታላይ ነው። (ማርቆስ 4:19) አንድ ተመራማሪ “ይሄን ያህል ብዙ ሰዎች ለማግኘት የሚጓጉለትና የችግሮች ሁሉ መፍትሄ እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱት ነገር እጃቸው ሲገባ ውጤቱ ከብስጭት እስከ ከባድ የስሜት ቀውስ ድረስ የከፋ የሚሆነው ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል። አዎን፣ ሀብትን ማሳደድ አንድ ሰው ጥሩ ጤንነትን፣ አርኪ የቤተሰብ ሕይወትን፣ የተቀራረበ ወዳጅነትን ወይም ከፈጣሪ ጋር ውድ ዝምድና መመሥረትን የመሳሰሉ በሕይወት ውስጥ እውነተኛ ዋጋ ያላቸውን ነገሮች መሠዋት ሊጠይቅበት ይችላል። እንደ አምላክ አድርጎ የተመለከተው ገንዘብ ‘ከንቱ ጣዖት’ ከመሆን አያልፍም!—ዮናስ 2:8 አ.መ.ት
“የሚመልስ የለም”
እውን ያልሆነውን እውን ነው ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው። በነቢዩ ኤልያስ ዘመን የነበሩት የበኣል አምላኪዎች ይህንን እውነታ ከደረሰባቸው መከራ ተምረዋል። በኣል ከሰማይ እሳት አውርዶ የቀረበለትን የእንስሳ መሥዋዕት ይበላል ብለው በጥብቅ ያምኑ ነበር። እንዲያውም “ከጥዋትም እስከ ቀትር ድረስ:- በኣል ሆይ፣ ስማን እያሉ የበኣልን ስም” ይጠሩ ነበር። በኣል የሚሰማበት ጆሮ ወይም የሚናገርበት አፍ ይኖረው ይሆን? ታሪኩ ሲቀጥል “ድምፅም አልነበረም” ይላል። በእርግጥም “የሚመልስ አልነበረም።” (1 ነገሥት 18:26, 29) በኣል እውን፣ ሕያው አሊያም ንቁ አልነበረም።
እውን የሆነውን አምላክ ማወቃችንና ማምለካችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ይሁን እንጂ እርሱ ማን ነው? እንዲሁም በእርሱ ማመናችን ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የፒሪ የሥራ ባልደረባ የሆነው ኤግንያ የብስ መኖር አለመኖሩን በርቀት ሲመለከት
ሮበርት ኢ ፒሪ
[ምንጭ]
Egingwah: From the book The North Pole: Its Discovery in 1909 Under the Auspices of the Peary Arctic Club, 1910; Robert E. Peary: NOAA
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙዎች ይህ ዓለም እንደ ጣዖት በሚያመልካቸው ነገሮች ተታልለዋል