በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ፍቅራችን ይበልጥ ጠነከረ’

‘ፍቅራችን ይበልጥ ጠነከረ’

‘ፍቅራችን ይበልጥ ጠነከረ’

ዓርብ መጋቢት 31, 2000 በሆካይዶ ጃፓን የሚገኘው ለ23 ዓመታት ዋልጌ ገሞራ የነበረው ኡሱ ተራራ ፈነዳ። በሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ከአደጋው ቀጠና ለመሸሽ ተገደዱ። ብዙዎቹ ቤታቸውንና መተዳደሪያቸውን ቢያጡም ምንም ሕይወት አልጠፋም። አካባቢውን ጥለው ለመሸሽ ከተገደዱት ሰዎች መካከል 46 የይሖዋ ምሥክሮች የነበሩ ቢሆንም እነዚህ ምሥክሮች ችግሩን ብቻቸውን እንዲወጡት አልተተዉም።

በአካባቢው በሚያገለግል አንድ ተጓዥ ክርስቲያን አገልጋይ አማካኝነት በዚያው እሳተ ገሞራው በፈነዳበት ዕለት እርዳታ ለማሰባሰብ አንዳንድ ዝግጅቶች ተደረጉ። ብዙም ሳይቆይ ከአጎራባች ጉባኤዎች የተላኩ የእርዳታ ቁሳቁሶች ደረሱ። በጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተቆጣጣሪነት የእርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ በአስቸኳይ የተቋቋመ ሲሆን የመዋጮ ገንዘብ በመላው ጃፓን ከሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች መጉረፍ ጀመረ። መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቀጥሉ ለማድረግ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ይበልጥ ወደተጎዱት ጉባኤዎች የተላኩ ሲሆን የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ስሜታዊና መንፈሳዊ ድጋፍ ለመስጠት አካባቢውን በተደጋጋሚ ጎብኝቷል።

በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ጉዳቱ በደረሰበት አካባቢ የሚኖሩ ምሥክሮች ከአደጋ ነፃ በሆነው አካባቢ ባሉ የግል ቤቶች ውስጥ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻቸውን ማከናወን ቀጥለዋል። አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ የተሰጠው ትእዛዝ ተነሥቶ ወንድሞች ወደ ስፍራው ሲመለሱ ያገኙት ያዘመመ፣ የተሰነጣጠቀና የተጎዳ የመንግሥት አዳራሽ ነበር። ከመንግሥት አዳራሹ ብዙም ሳይርቅ ከሚገኘው አዲስ ከተፈጠረው የእሳተ ገሞራ ቆሬ አሁንም ጥቁር ጭስ እየተትጎለጎለ ይወጣ ነበር። ምሥክሮቹ ‘በዚህ ቦታ መሰብሰብ መቀጠሉ ተገቢ ነው? የመንግሥት አዳራሹ ሊጠገን ይችል ይሆን?’ ሲሉ አሰቡ።

አዲስ የመንግሥት አዳራሽ በአቅራቢያው በሚገኝ ከአደጋ ነፃ በሆነ ቦታ ላይ ለመገንባት ተወሰነ። የአካባቢ የሕንፃ ግንባታ ኮሚቴ አስፈላጊውን እገዛ የሰጠ ሲሆን በአገሪቱ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ያዋጡት ገንዘብ ለዚህ ግንባታ ውሏል። መሬት በፍጥነት ተገዛና በመቶዎች በሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች ትብብር በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ተጠናቀቀ። እሁድ ሐምሌ 23, 2000 በዚህ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስብሰባ ሲደረግ 75 የሚያክሉ ሰዎች ተገኙ። ከተሰብሳቢዎቹ መካከል አብዛኞቹ የደስታ እምባ አልቅሰዋል። በዚያው ዓመት በጥቅምት ወር የመንግሥት አዳራሹ ሲወሰን ከጉባኤው ሽማግሌዎች አንዱ እንዲህ ለማለት ተገፋፍቷል:- “በእሳተ ገሞራ ፍንዳታው ምክንያት ችግርና መከራ ደርሶብን ነበር። ቢሆንም የዚህ አዳራሽ መገንባት ሐዘናችንን ወደ ደስታ ለውጦታል። ለይሖዋና ለውድ ክርስቲያን ወንድሞቻችን ያለን ፍቅር ይበልጥ ጠንክሯል።”

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

የኡሱ ተራራ ሲፈነዳ:- AP Photo/Koji Sasahara