በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ማዳን የይሖዋ ነው’

‘ማዳን የይሖዋ ነው’

‘ማዳን የይሖዋ ነው’

ብሔራዊ ቀውስ በሚያጋጥምበትና ዓለም አቀፍ ውጥረት በሚነግሥበት ጊዜ ሕዝቦች መንግሥታቸው ሰላምና ደህንነት ለማስፈን እርምጃ እንዲወስድ ይጠብቃሉ። መንግሥታት በበኩላቸው የሕዝቡን ሙሉ ድጋፍ ለማግኘት የተለያዩ ፕሮግራሞችን ይነድፋሉ። በእነዚህ ፕሮግራሞች አማካኝነት ብሔራዊ ስሜት እየተቀጣጠለ ሲሄድ ብሔራዊ ስሜት የሚገለጽባቸው ሥነ ሥርዓቶች የዚያኑ ያህል ከፍተኛ ትኩረት እየተሰጣቸው ይሄዳሉ።

በአንድ አገር ላይ ድንገተኛ የሆነ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ሕዝቡ በጋለ ብሔራዊ ስሜት በመነሳሳት አንድነቱን የማጠናከርና እርስ በርስ የመተባበር መንፈስ ብሎም ለወገኑ የመቆርቆር ዝንባሌ ያድርበታል። ይሁን እንጂ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ማጋዚን በተባለ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንዳስቀመጠው “ብሔራዊ ስሜት እንደማንኛውም ስሜት ሁሉ በጣም አደገኛ ነው። ገደብ ካልተበጀለት አስከፊ ወደሆነና ወዳልተፈለገ ሁኔታ ሊያመራ ይችላል።” ብሔራዊ ስሜት የሚገለጽባቸው ሰላማዊ የሆኑ መንገዶች ቀስ በቀስ የአንዳንድ ዜጎችን የጋራ መብትና ሃይማኖታዊ ነጻነት እስከ መጋፋት የሚደርሱ እርምጃዎችን ወደ መውሰድ ሊያመራ ይችላል። በተለይ ደግሞ እውነተኛ ክርስቲያኖች እምነታቸውን እንዲያላሉ ጫና ይገጥማቸው ይሆናል። ክርስቲያኖች በሚኖሩበት አካባቢ እንዲህ ያለ መንፈስ በሚነግሥበት ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ማስተዋል የታከለበት እርምጃ እንዲወስዱና ፍንክች ሳይሉ ከአምላክ ጎን እንዲቆሙ የሚያስችሏቸው አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው?

“አትስገድላቸው”

ለባንዲራ ሰላምታ መስጠት የብሔራዊ ስሜት መግለጫ እንደሆነ ተደርጎ የሚታይበት ጊዜ አለ። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ባንዲራዎች ከዋክብትን የመሳሰሉ የሰማይ አካላትና በምድር ላይ ያሉ የሌሎች ነገሮች ምስል ይኖራቸዋል። አምላክ ለሕዝቦቹ በሰጠው ትእዛዝ ላይ እንደነዚህ ላሉ ምስሎች መስገድን በተመለከተ ያለውን አመለካከት ገልጿል:- “በላይ በሰማይ ካለው፣ በታችም በምድር ካለው፣ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፣ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውምም፤ . . . እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና።”​—⁠ዘጸአት 20:​4-6

ለአንድ አገር ባንዲራ ሰላምታ መስጠት ወይም በባንዲራ ፊት መንበርከክ ይሖዋ አምላክ እርሱን ብቻ እንድናመልክ ከሰጠው ትእዛዝ ጋር ይጋጫልን? በጥንት ዘመን የኖሩት እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ወቅት በሦስት በሦስት ነገድ የተከፈለው ሕዝብ በሚሰፍርበት ቦታ “ምልክት” ወይም ዓርማ ነበራቸው። (ዘኍልቍ 2:1, 2) የማክሊንቶክ እና ስትሮንግስ ሳይክሎፒዲያ እነዚህን ዓርማዎች ለማመልከት የገቡትን የዕብራይስጥ ቃላት አስመልክቶ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቷል:- “ ‘ዓርማ’ የሚለው ቃል ባንዲራን የሚያመለክት እንደሆነ አድርገን ልናስብ ብንችልም የዕብራይስጡ ቃላት ባንዲራን ለማመልከት አልተሠራባቸውም።” ከዚህም በላይ እስራኤላውያን የተጠቀሙባቸውን ምልክቶች እንደ ቅዱስ ነገር አልተመለከቷቸውም ወይም ምልክቶቹን በሚጠቀሙበት ጊዜ የተለየ ሥነ ሥርዓት አከናውነው አያውቁም። ሕዝቡ በየት በኩል መስፈር እንዳለበት ለመጠቆም ብቻ የሚያገለግሉ ምልክቶች ነበሩ።

በማደሪያው ድንኳንም ሆነ በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ውስጥ የኪሩቤል ምስል የተሠራበት ምክንያት በሰማይ የሚገኙት ኪሩቦችን ለመግለጽ ነበር። (ዘጸአት 25:​18፤ 26:​1, 31, 33፤ 1 ነገሥት 6:​23, 28, 29፤ ዕብራውያን 9:​23, 24) እነዚህ የኪሩቤል ምስሎች ሕዝቡ ሊያያቸው በማይችል ሥፍራ መቀመጣቸውና መላእክት የማይመለኩ መሆናቸው ምስሎቹ የተለየ አክብሮት ሊሰጣቸው እንደማይገባ የሚያሳይ ነው።​—⁠ቆላስይስ 2:​18፤ ራእይ 19:​10፤ 22:​8, 9

እስራኤላውያን በምድረ በዳ በቆዩባቸው ዓመታት ነቢዩ ሙሴ ሠርቶት የነበረውን የነሐስ እባብም እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። ይህ የእባብ ምስል ምልክት ሆኖ ከማገልገሉም በላይ ትንቢታዊ መልእክትም ነበረው። (ዘኍልቍ 21:4-9፤ ዮሐንስ 3:14, 15) ከፍ ያለ ክብር አይሰጠውም ወይም ለአምልኮ አያገለግልም ነበር። ይሁን እንጂ ሙሴ ከሞተ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ እስራኤላውያን ለምስሉ ዕጣን ከማጠናቸውም በላይ ምስሉን ማምለክ ጀመሩ። ከዚህ የተነሳ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ የነሐሱን እባብ ሰባበረው።​—⁠2 ነገሥት 18:​1-4

ብሔራዊ ባንዲራዎች በምልክትነት ከማገልገል ያለፈ ሌላ ምንም ትርጉም የላቸውምን? ምልክት ሆነው የሚያገለግሉት ለምን ነገር ነው? ደራሲው ጄ ፖል ዊልያምስ “የብሔረተኝነት ዋነኛው የእምነት መግለጫና ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው የአምልኮ ዕቃ ባንዲራ ነው” ብለዋል። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና “ባንዲራ እንደ መስቀል ሁሉ ቅዱስ ነው” ይላል። ባንዲራ የአንድ አገር መለያ ምልክት ነው። ስለሆነም ለባንዲራ መስገድ ወይም ሰላምታ መስጠት ለአንድ አገር የሚቀርብ የአምልኮ ሥርዓት ነው። እንዲህ ያለው ድርጊት የመዳን ምንጭ የአገሪቱ መንግሥት ነው ማለት ሲሆን ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጣዖት አምልኮ ከሚያስተምረው ትምህርት ጋር ይጋጫል።

ቅዱሳን ጽሑፎች ‘ማዳን የይሖዋ ነው’ በማለት በግልጽ ይናገራሉ። (መዝሙር 3:​8) ማዳን ከሰብዓዊ ድርጅቶች ወይም እነርሱን ከሚወክሉ ዓርማዎች ጋር መያያዝ አይኖርበትም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ወዳጆቼ ሆይ፣ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ” ሲል የእምነት ባልንጀሮቹን አስጠንቅቋቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 10:​14) የጥንት ክርስቲያኖች ለብሔራት በሚቀርቡ የአምልኮ ድርጊቶች ተካፍለው አያውቁም። ዳንኤል ፒ ማኒክስ ዞስ አባውት ቱ ዳይ በተባለው መጽሐፍ ላይ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “ክርስቲያኖች [ለሮማ] ንጉሠ ነገሥት ውቃቤ መሥዋዕት ለማቅረብ . . . ፈጽሞ ፈቃደኞች አልነበሩም። ይህም ዛሬ ለባንዲራ ሰላምታ ለመስጠት ፈቃደኛ ካለመሆን ጋር የሚመሳሰል ነው።” ዛሬም እውነተኛ ክርስቲያኖች አቋማቸው ይኸው ነው። ማምለክ ያለባቸው ይሖዋን ብቻ በመሆኑ ለማንኛውም አገር ባንዲራ ሰላምታ ከመስጠት ይቆጠባሉ። በዚህ መንገድ ለመንግሥታትና ለመሪዎቻቸው መስጠት የሚገባቸውን አክብሮት ሳይነፍጉ አምላክን ያስቀድማሉ። እርግጥ ነው፣ ‘በበላይ ላሉት የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች መገዛት’ እንዳለባቸው ያውቃሉ። (ሮሜ 13:​1-7) ይሁን እንጂ ቅዱሳን ጽሑፎች ብሔራዊ መዝሙርን የመሳሰሉ የአገር ፍቅር መዝሙሮችን ስለ መዘመር ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው?

ብሔራዊ መዝሙር ምንድን ነው?

ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና እንዲህ ይላል:- “ብሔራዊ መዝሙር የሀገር ፍቅር ስሜት መግለጫ ሲሆን እንዲህ ያሉ መዝሙሮች ብዙውን ጊዜ አምላክ ሕዝቡን ወይም የአገሪቱን መሪዎች እንዲመራቸው እና እንዲጠብቃቸው የሚቀርቡ ልመናዎች ናቸው።” ብሔራዊ መዝሙር ስለ አንድ አገር የሚቀርብ ዝማሬ ወይም ጸሎት ነው ሊባል ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ መዝሙሩ ሲዘመር አገሪቱ እንድትበለጽግና ለዘላለም እንድትኖር ልመና ይቀርባል። ታዲያ እውነተኛ ክርስቲያኖች የጸሎት ይዘት ባለው እንዲህ ያለ ሥነ ሥርዓት ላይ መካፈል ይኖርባቸዋልን?

ነቢዩ ኤርምያስ ይኖር የነበረው አምላክን እናገለግላለን በሚል ሕዝብ መካከል ነው። ሆኖም ይሖዋ “አልሰማህምና ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ ስለ እነርሱም ልመናና ጸሎት አታድርግ፤ አትማልድላቸው” የሚል ትእዛዝ ሰጥቶት ነበር። (ኤርምያስ 7:16፤ 11:14፤ 14:11) ኤርምያስ ይህ ትእዛዝ የተሰጠው ለምን ነበር? ሕዝቡ በስርቆት፣ በነፍስ ግድያ፣ በምንዝር፣ በሐሰት መሐላና በጣዖት አምልኮ ተዘፍቆ ስለነበረ ነው።​—⁠ኤርምያስ 7:​9

ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ ስለ እነዚህ እለምናለሁ፤ ስለ ዓለም አልለምንም ስለ ሰጠኸኝ እንጂ” ብሎ በተናገረ ጊዜ ምሳሌ ትቶልናል። (ዮሐንስ 17:9) ቅዱሳን ጽሑፎች “ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ” እና ‘አላፊ’ እንደሆነ ይናገራሉ። (1 ዮሐንስ 2:​17፤ 5:​19) ታዲያ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲህ ላለው ሥርዓት ብልጽግናና ዘላለማዊነት ለመጸለይ እንዴት ሕሊናቸው ሊፈቅድላቸው ይችላል?

እርግጥ ነው፣ ሁሉም ብሔራዊ መዝሙሮች ለአምላክ የሚቀርቡ ልመናዎች ናቸው ማለት አይደለም። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “ብሔራዊ መዝሙሮች የሚያስተላልፉት ሐሳብ እንደ ሁኔታው ይለያያል። አንዳንዶቹ አምላክ የገዥውን መደብ እንዲባርክ የሚቀርቡ ጸሎቶች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ አገሪቱ ድል ስለተቀዳጀችባቸው ወሳኝ ጦርነቶች ወይም ሕዝባዊ ዓመፅ የሚያወሱ . . . የሀገር ፍቅር መግለጫዎችን የያዙ ናቸው።” ሆኖም አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች አንዲት አገር በጦርነትና በአብዮታዊ ንቅናቄ ባገኘችው ውጤት ሊደሰቱ ይችላሉ? ኢሳይያስ እውነተኛ አምላኪዎችን በሚመለከት “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ” የሚል ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 2:4) ሐዋርያው ጳውሎስ “በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፣ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና” ሲል ጽፏል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 10:​3, 4

ብሔራዊ መዝሙሮች ብዙውን ጊዜ በአገር የመኩራራት ወይም የበላይነት ስሜት ያስተላልፋሉ። እንዲህ ያለው አመለካከት ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የለውም። ሐዋርያው ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ ባደረገው ንግግር ላይ “[ይሖዋ አምላክ] በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ” ብሏል። (ሥራ 17:26) ሐዋርያው ጴጥሮስ ደግሞ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ” ሲል ተናግሯል።​—⁠ሥራ 10:34, 35

ብዙ ሰዎች ባገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት መሠረት ለባንዲራ ሰላምታ ላለመስጠትና ብሔራዊ ስሜት የሚንጸባረቅባቸውን መዝሙሮች ላለመዘመር የራሳቸውን ውሳኔ አድርገዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ባሉ ድርጊቶች እንዲካፈሉ በሚያስገድዱ ሁኔታዎች ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል?

አክብሮት በተሞላበት መንገድ አቋምን መግለጽ

የጥንቷ ባቢሎን ንጉሥ የነበረው ናቡከደነፆር የግዛት አንድነቱን ለማጠናከር ባደረገው ጥረት በዱራ ሜዳ ላይ ከወርቅ የተሠራ አንድ ግዙፍ ምስል አቆመ። ለዚሁ ምስል የምረቃ ሥነ ሥርዓት አዘጋጅቶ መኳንንቱን፣ ሹማምንቶቹን፣ አገረ ገዥዎቹን፣ አማካሪዎቹንና ሌሎች ትላልቅ ባለሥልጣኖችን ጋበዘ። የሙዚቃ ድምፅ በሚሰማበት ጊዜ በዚያ የተሰበሰቡ ሁሉ በምስሉ ፊት እንዲሰግዱና ምስሉን እንዲያመልኩ ትእዛዝ አስተላለፈ። ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የሚባሉ ወጣት ዕብራውያንም በቦታው እንዲገኙ ይጠበቅባቸው ነበር። እንዲህ ባለው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደማይካፈሉ ያሳዩት እንዴት ነበር? ሙዚቃው ሲጀምርና በዚያ የተሰበሰቡት ሰዎች በሙሉ በምስሉ ፊት ሲሰግዱ ሦስቱ ዕብራውያን ከቆሙበት ንቅንቅ ሳይሉ ቀሩ።​—⁠ዳንኤል 3:​1-12

በዛሬው ጊዜ በአብዛኛው ለባንዲራ ሰላምታ የሚሰጠው እጅን ወደ ፊት በመዘርጋት ወይም በደረት ወይም በግንባር ላይ በማድረግ ነው። አንዳንድ ጊዜ የተለየ የአቋቋም ሁኔታ ያስፈልግ ይሆናል። በአንዳንድ አገሮች ትምህርት ቤት ውስጥ ልጆች ተንበርክከው ባንዲራውን እንዲስሙ ይታዘዛሉ። ሌሎች ለባንዲራ ሰላምታ በሚሰጡበት ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች ዝም ብለው በመቆም ሁኔታውን በአክብሮት ይከታተላሉ።

ይሁን እንጂ ለባንዲራ ሰላምታ በመስጠት ሥነ ሥርዓቱ መቆም ብቻውን በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተካፈልን የሚያስቆጥር ቢሆንስ? ለምሳሌ ያህል፣ ሁሉንም ተማሪዎች የሚወክል አንድ ተማሪ ይመረጥና ተማሪዎቹ ክፍል ውስጥ በተጠንቀቅ ቆመው እያለ እርሱ በትምህርት ቤቱ ባንዲራ ፊት ለፊት ለባንዲራው ሰላምታ እንዲሰጥ ይደረግ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ክፍል ውስጥ መቆም ለባንዲራ ሰላምታ ለመስጠት ተማሪዎችን ወክሎ የወጣው ተማሪ በግለሰብ ደረጃ እንዲወክለው እንደተስማማ ሊቆጠር ይችላል። ዝም ብሎ መቆሙም ብቻ እንኳን በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተካፈልን ሊያሳይ ይችላል። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ አክብሮታቸውን ከመግለጽ ያለፈ ነገር ማድረግ የማይፈልጉ ተማሪዎች ቁጭ እንዳሉ መቆየት ይችላሉ። ይሁንና ሥነ ሥርዓቱ ከመጀመሩም በፊት ተማሪዎቹ ቆመው ቢሆንስ? በዚህ ጊዜ እንደቆምን ብንቆይ በሥነ ሥርዓቱ እንደተካፈልን አይቆጠርም።

አንድ ሰው ለባንዲራ ሰላምታ እንዲሰጥ ባይጠየቅም ሌሎች ሰላምታ እንዲሰጡ ለማድረግ በሰልፍ መካከል፣ በክፍል ውስጥ ወይም በሌላ በማንኛውም ቦታ ባንዲራ እንዲይዝ ብቻ ቢጠየቅስ? አንድ ሰው እንዲህ ማድረጉ ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚያዙት ‘ከጣዖት መሸሹ’ ሳይሆን የሥነ ሥርዓቱ ዋነኛ ተዋናይ የሆነ ያህል ነው። በብሔራዊ ስሜት መግለጫ ሰልፎች ላይ መካፈልም ከዚህ ተነጥሎ አይታይም። እንዲህ ባለው ሰልፍ ላይ መካፈል የሰልፉን ዓላማ መደገፍ ማለት ስለሚሆን እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሕሊናቸው የተነሳ ከመካፈል ይርቃሉ።

ብሔራዊ መዝሙር በሚዘመርበት ወቅት ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው መዝሙሩ የሚያስተላልፈውን መልእክት እንደሚደግፍ ለማሳየት መቆሙ በራሱ በቂ ነው። እንዲህ ባለው ጊዜ ክርስቲያኖች ከተቀመጡበት አይነሱም። ይሁን እንጂ ብሔራዊው መዝሙር ከመጀመሩ በፊት ቆመው ከነበረ ተሳታፊ አለመሆናቸውን ለማሳየት መቀመጥ አያስፈልጋቸውም። ለብሔራዊ መዝሙሩ በፈቃደኝነት ከመነሳት ጋር አንድ አይደለም። በሌላ በኩል በቦታው ያሉት ሰዎች ከመቀመጫቸው ተነስተው እንዲዘምሩ የሚጠበቅባቸው በሚሆንበት ጊዜ ሳንዘምር አክብሮት ለማሳየት ያህል ብቻ መቆማችን መዝሙሩ በሚያስተላልፈው መልእክት እንደተስማማን ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም።

“በጎ ሕሊና ይኑራችሁ”

መዝሙራዊው የሰው እጅ ሥራ የሆኑት የአምልኮ ምስሎች እርባና እንደሌላቸው ከገለጸ በኋላ “የሚሠሩአቸውም የሚያምኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 115:4-8) በግልጽ እንደምንመለከተው ብሔራዊ ባንዲራዎችን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት የአምልኮ ዕቃዎችን በሚያመርት ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ መሥራት በይሖዋ አምላኪዎች ዘንድ ተቀባይነት የለውም። (1 ዮሐንስ 5:​21) ክርስቲያኖች ከይሖዋ በስተቀር ባንዲራንም ሆነ ባንዲራው የሚወክለውን ነገር እንደማያመልኩ በአክብሮት መግለጻቸው አስፈላጊ የሚሆንባቸው ሌሎች የሥራ ዓይነቶችም ይኖሩ ይሆናል።

ለምሳሌ ያህል አንድ አሠሪ አንድን ሠራተኛ በመሥሪያ ቤቱ ግቢ ውስጥ የሚገኘውን ባንዲራ እንዲሰቅል ወይም እንዲያወርድ ያዝዘው ይሆናል። አንድ ሰው የታዘዘውን ማድረግ አለማድረጉ ለሁኔታው ባለው አመለካከት ላይ የተመካ ነው። ባንዲራ መስቀል ወይም ማውረድ የአንድ ልዩ ሥነ ሥርዓት ክፍል ከሆነ ማለትም ሰዎች በተጠንቀቅ ቆመው የሚከታተሉ ወይም ለባንዲራው ሰላምታ የሚሰጡ ከሆነ ይህ ድርጊት በሥነ ሥርዓቱ እንደመካፈል ተደርጎ ይቆጠራል።

በሌላ በኩል ባንዲራውን ከመስቀል ወይም ከማውረድ ጋር ተያይዞ የሚደረግ ምንም ዓይነት ሥነ ሥርዓት ከሌለ ባንዲራ መስቀሉ ወይም ማውረዱ ሕንጻውን ለአገልግሎት ማዘጋጀትን፣ በር መቆለፍና መክፈትን እንዲሁም መስኮት መዝጋትና መክፈትን የመሳሰሉ ሥራዎችን ከማከናወን ተለይቶ አይታይም። እንዲህ ባለው ሁኔታ ባንዲራው አንድን አገር ከሚወክል አርማ ተለይቶ አይታይም። በመሆኑም በዕለቱ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች መካከል እንደ አንዱ በመቁጠር ባንዲራ መስቀሉ ወይም ማውረዱ ለአንድ ሰው ሕሊና የተተወ የግል ውሳኔ ነው። (ገላትያ 6:​5) አንድ ወንድም ሕሊናው ስለማይፈቅድለት ባንዲራውን የሚሰቅልና የሚያወርድ ሌላ ሰው እንዲመድብ አለቃውን ይጠይቅ ይሆናል። ሌላ ክርስቲያን ደግሞ ባንዲራውን ከመስቀልና ከማውረድ ጋር ተያይዞ የሚፈጸም ሥነ ሥርዓት እስከሌለ ድረስ የታዘዘውን ለማድረግ ሕሊናው ይፈቅድለት ይሆናል። ውሳኔያቸው ምንም ይሁን ምን እውነተኛ አምላኪዎች በአምላክ ፊት “በጎ ሕሊና” ሊኖራቸው ይገባል።​—⁠1 ጴጥሮስ 3:​16

መጽሐፍ ቅዱስ የአንድ አገር ባንዲራ ተሰቅሎ በሚታይባቸው የእሳት አደጋ መከላከያ፣ ማዘጋጃ ቤትና ትምህርት ቤቶች በመሳሰሉ ተቋማት ውስጥ መሥራትን ወይም መገኘትን አይከለክልም። በተጨማሪም የፖስታ ቴምብሮች፣ የመኪና ሰሌዳ ቁጥሮች ወይም መንግሥት የሚያዘጋጃቸው ሌሎች ዕቃዎች የባንዲራ ምልክት ይኖርባቸው ይሆናል። ግለሰቦች እነዚህን ነገሮች መጠቀማቸው ተገቢ ባልሆነ ድርጊት እንደመካፈል ሊቆጠርባቸው አይችልም። ዋነኛው ቁም ነገር ባንዲራው ወይም የባንዲራው ምስል መኖሩ ሳይሆን አንድ ሰው ለባንዲራው ያለው አመለካከት ነው።

መስኮቶች፣ በሮች፣ መኪናዎች፣ ጠረጴዛዎች ወይም ሌሎች ነገሮች ላይ ባንዲራ ተቀምጦ ወይም ተሰቅሎ ማየት የተለመደ ጉዳይ ነው። በተጨማሪም ባንዲራ የተለጠፈባቸው ልብሶች ገበያ ላይ ይገኛሉ። በአንዳንድ አገሮች እንዲህ ያሉ ልብሶችን መልበስ በሕግ የተከለከለ ነው። እንዲህ ያሉ ልብሶችን መልበስ በሕግ የተከለከለ ባይሆንም እንኳን እንዲህ ማድረጉ ግለሰቡ ዓለምን በተመለከተ ስላለው አቋም ምን ይጠቁማል? ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹን በሚመለከት “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:16) እንዲህ ያለው ድርጊት በእምነት ባልንጀሮች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያስከትል መታወቅ ይኖርበታል። በዚህ ምክንያት አንዳንዶች ሕሊናቸው ይጎዳ ይሆን? በእምነት ጸንተው ለመቆም ያደረጉትን ቁርጥ ውሳኔ ያዳክምባቸው ይሆን? ጳውሎስ “ለወንድም እንቅፋትን ወይም ማሰናከያን ማንም እንዳያኖርበት ይህን ቊረጡ” ሲል ለክርስቲያኖች ምክር ሰጥቷል።​—⁠ሮሜ 14:13

“ለሰው ሁሉ ገር” መሆን

በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ውስጥ የዓለም ሁኔታዎች ይበልጥ እየተበላሹ ሲሄዱ የሀገር ፍቅር ስሜትም የዚያኑ ያህል እየተቀጣጠለ ይሄዳል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) አምላክን የሚወዱ ሰዎች ማዳን የይሖዋ ብቻ እንደሆነ ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርባቸውም። አምልኮ የሚገባው እርሱ ብቻ ነው። የኢየሱስ ሐዋርያት ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚጋጭ ድርጊት እንዲፈጽሙ በተጠየቁ ጊዜ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።​—⁠ሥራ 5:29

ሐዋርያው ጳውሎስ “የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር . . . ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም” ሲል ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 2:​24) ስለሆነም ክርስቲያኖች ለባንዲራ ሰላምታ መስጠትንና ብሔራዊ መዝሙር መዘመርን በሚመለከት በመጽሐፍ ቅዱስ በሰለጠነ ሕሊናቸው ተጠቅመው የራሳቸውን ውሳኔ በሚያደርጉበት ጊዜ ሰላማውያን፣ ሰው አክባሪዎችና ገሮች ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሦስቱ ዕብራውያን አምላክን ማስደሰት እንደሚፈልጉ በቆራጥነት ሆኖም በአክብሮት ገልጸዋል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ክርስቲያን የሀገር ፍቅር ስሜት የሚያንጸባርቁ ሥነ ሥርዓቶች በሚካሄዱበት ወቅት ምን ማድረግ ይኖርበታል?