በካፒቴኑ ገበታ ዙሪያ የተደረገ ውይይት
በካፒቴኑ ገበታ ዙሪያ የተደረገ ውይይት
ጥሩ ምግብ ስለሚቀርብ፣ አስደሳች ጭውውት ስለሚኖርና ታዋቂ ሰዎች ስለሚጋበዙ በመርከብ ላይ ከካፒቴኑ ጋር በአንድ ገበታ መመገብ በጣም የሚያስደስት ነው። ሆኖም በአንድ ወቅት የዋይት ስታር የመርከብ ኩባንያ ካፒቴን በነበረው ሮበርት ጂ ስሚዝ ገበታ ዙሪያ አምላክ ስላዘጋጀው መንፈሳዊ ድግስ ውይይት ተነስቶ ነበር።—ኢሳይያስ 25:6
በ1894 ሮበርት በ24 ዓመቱ ኪንክሉን ዳንዲ የተባለችው መርከብ ካፒቴን ሆኖ በዓለም ዙሪያ የመጀመሪያውን ጉዞውን አደረገ። በኋላም ሴድሪክ፣ ሴቪክ እና ሩኒክ በተባሉትና በሌሎች በዋይት ስታር ኩባንያ መርከቦች ላይ ካፒቴን ሆኖ ሠርቷል። a ሮበርት ከእነዚህ መርከቦች የአንዱ ካፒቴን ሆኖ ከኒው ዮርክ ተነስቶ አትላንቲክን አቋርጦ ወደ ሊቨርፑል፣ እንግሊዝ በመጓዝ ላይ ሳለ በገበታው ላይ ቻርልስ ቴዝ ራስልን የመጋበዝ አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። ከራስል ጋር ያደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ልቡን የነካው ሲሆን ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ከራስል ስተዲስ ኢን ዘ ስክሪፕቸርስ የተባለውን መጽሐፍ ተቀበለ።
ወንድም ራስል ከሮበርት ጋር በደብዳቤ መገናኘቱን የቀጠለ ሲሆን በዚህም ምክንያት ሮበርት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመማር የነበረው ፍላጎት እያደገ ሄደ። ሮበርት ያገኘውን አዲስ እውቀት ለሚስቱ አካፈላት። ሁለቱም ቀናተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ለመሆን ብዙም ጊዜ አልፈጀባቸውም። ቆየት ብሎም ሮበርት የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን የማቅረብ አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። ለምሳሌ በብሪዝበን አውስትራሊያ “የገለዓድ የመድኃኒት ቅባት” በሚል ጭብጥ ንግግር ያቀረበ ሲሆን የአምላክ ቃል “በምድር ላሉት ችግሮች ሁሉ ማርከሻ” የሚሆን መልእክት መያዙን አብራርቷል። ሚስቱና ልጆቹ ደግሞ በእንግሊዝ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተሰኘው ተንቀሳቃሽ ፊልም በሚታይበት ወቅት በሸክላ የተቀዳውን የራስል ንግግር በማሰማት የበኩላቸውን ተሳትፎ አድርገዋል።
ሮበርት ያገኘውን የመንግሥቱን እውነት ውርሻ ለልጆቹም አስተላልፏል። በአሁኑ ወቅት 18 የሚያህሉ የቤተሰቡ አባላት ምሥራቹን ለሌሎች በትጋት በማካፈል ከአምስት ትውልዶች በፊት በካፒቴኑ ገበታ ላይ ቀርቦ ለነበረው መንፈሳዊ ምግብ ያላቸውን አድናቆት ያሳያሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች በጽሑፎቻቸውና መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ሥራቸው አማካኝነት ካፒቴን ስሚዝን የማረከውን ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለሰዎች በዓለም ዙሪያ በማስተማር ላይ ናቸው። በካፒቴኑ ገበታ ዙሪያ የተደረገውን ውይይት ያን ያህል አስደሳች ያደረገው ምን እንደሆነ አንተም ማወቅ ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ከእነዚህ መርከቦች ጋር ተመሳሳይ የነበረችው ታይታኒክ የተባለችው መርከብ የመጀመሪያዋን ጉዞ እያደረገች ሳለች በገጠማት አደጋ ምክንያት የሰጠመች ሲሆን በወቅቱ የመርከቧ አዛዥ የነበረው ኢ ጄ ስሚዝ (ከሮበርት ስሚዝ ጋር ምንም ዝምድና የለውም) የተባለ ካፒቴን ነበር።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሮበርት ጂ ስሚዝ
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቻርልስ ቴዝ ራስል