በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን ቃል የማጥናት ልማድ ይኑርህ

የአምላክን ቃል የማጥናት ልማድ ይኑርህ

የአምላክን ቃል የማጥናት ልማድ ይኑርህ

“ሥራህን ሁሉ አሰላስላለሁ፤ ድንቅ ሥራህን ሁሉ አውጠነጥናለሁ።”​መዝሙር 77:​12 አ.መ.ት 

1, 2. (ሀ) ለማሰላሰል ጊዜ መመደብ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) “ማሰላሰል” ሲባል ምን ማለት ነው?

 የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን ከአምላክ ጋር ላለን ዝምድናና እርሱን ለማገልገል ለተነሳሳንበት የልብ ዝንባሌ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይኖርብናል። ይሁን እንጂ ዛሬ የአብዛኞቹ ሰዎች ሕይወት ውክቢያ የበዛበት በመሆኑ የሚያሰላስሉበት ጊዜ የላቸውም። በፍቅረ ነዋይ እንዲሁም ተድላን በማሳደድ ተጠምደዋል። እኛ እንደዚህ ካለው ፋይዳ ቢስ ተግባር መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው? እንደ መብልና መኝታ ላሉት አስፈላጊ ነገሮች በየዕለቱ ጊዜ እንደምንመድብ ሁሉ በይሖዋ ሥራዎች ላይ የምናሰላስልበትም ጊዜ ሊኖረን ይገባል።​—⁠ዘዳግም 8:​3፤ ማቴዎስ 4:​4

2 ቆም ብለህ የማሰላሰል ልማድ  አለህ? ማሰላሰል ሲባል ምን ማለት ነው? ማሰላሰል ስለ አንድ ነገር በተመስጦ ረዘም ላለ ጊዜ ማሰብ፣ ማውጣት ማውረድ ማለት ነው። ከዚህ የምንማረው ነገር ምንድን ነው?

3. መንፈሳዊ እድገት ማድረጋችን የተመካው ምን በማድረጋችን ላይ ነው?

3 ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ ለአገልግሎት አጋሩ ለጢሞቴዎስ የጻፈለትን መልእክት ያስታውሰን ይሆናል:- “እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ። . . . ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፣ ይህንም አዘውትር።” አዎን፣ ጢሞቴዎስ እድገትና መሻሻል ማድረግ ይጠበቅበት ነበር። የጳውሎስም አነጋገር እድገት ማድረግና ማሰላሰል የማይነጣጠሉ ነገሮች መሆናቸውን የሚገልጽ ነው። ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። መንፈሳዊ እድገት በማድረግ የሚገኘውን እርካታ ማጣጣም የምንፈልግ ከሆነ በአምላክ ቃል ላይ ‘ማሰላሰልና መመሰጥ’ ይኖርብናል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​13-15

4. በአምላክ ቃል ላይ አዘውትረህ ለማሰላሰል የሚረዱህን የትኞቹን ዝግጅቶች ልትጠቀም ትችላለህ?

4 ለማሰላሰል ይበልጥ አመቺ የሚሆንልህን ጊዜ የሚወስነው የአንተና የቤተሰብህ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ነው። ብዙዎች ማለዳ ተነስተው ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር የተባለውን ቡክሌት በማንበብ በአንድ ጥቅስ ላይ ያሰላስላሉ። እንዲያውም በዓለም ዙሪያ በሚገኙት የቤቴል ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ 20, 000 የሚያክሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሁልጊዜ ጠዋት ለ15 ደቂቃ በዕለቱ ጥቅስ ላይ ይወያያሉ። በየጠዋቱ በጥቅሱ ላይ ሐሳብ የሚሰጡት ጥቂት ቢሆኑም የቀሩት በሚነገረውና በሚነበበው ነገር ላይ ያሰላስላሉ። ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ ወደ ሥራ ሲሄዱ በአምላክ ቃል ላይ የሚያሰላስሉበት አጋጣሚ ያገኛሉ። በአንዳንድ ቋንቋዎች በቴፕ ክር ተዘጋጅተው የሚገኙትን የመጽሐፍ ቅዱስ፣ የመጠበቂያ ግንብ እንዲሁም የንቁ! መጽሔት ቅጂዎች እያዳመጡ ይሄዳሉ። ብዙ የቤት እመቤቶችም የቤት ውስጥ ሥራዎቻቸውን እያከናወኑ እነዚህን የቴፕ ክሮች ያዳምጣሉ። በዚህ መንገድ “የእግዚአብሔርን ሥራ አስታውሳለሁ፤ የጥንት ታምራትህን በእርግጥ አስታውሳለሁ፤ ሥራህን ሁሉ አሰላስላለሁ፤ ድንቅ ሥራህን ሁሉ አውጠነጥናለሁ” ሲል የተናገረውን የመዝሙራዊውን የአሳፍን ምሳሌ ይኮርጃሉ።​—⁠መዝሙር 77:​11, 12 አ.መ.ት 

ትክክለኛውን አመለካከት መያዝ ጥሩ ውጤት ይኖረዋል

5. የግል ጥናት ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

5 ቴሌቪዥን፣ ቪዲዮና ኮምፒውተር በሰፊው ጥቅም ላይ በዋሉበት በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች እምብዛም አያነብቡም። በይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ መሆን ይኖርበታል። በመሠረቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ከይሖዋ ጋር ላለን ዝምድና ዋና የደም ሥር ነው። ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ኢያሱ ሙሴን ተክቶ የእስራኤልን ብሔር እንዲመራ ተመረጠ። ኢያሱ የይሖዋን በረከት ለማግኘት የአምላክን ቃል በግሉ ማንበብ ነበረበት። (ኢያሱ 1:​8፤ መዝሙር 1:​1, 2) ዛሬም ቢሆን እንዲሁ ማድረግ ይጠበቅብናል። ይሁን እንጂ አንዳንዶች በትምህርታቸው ብዙም ስላልገፉ ማንበብ ሊቸግራቸው ወይም አሰልቺ ሥራ ሊሆንባቸው ይችላል። ታዲያ የአምላክን ቃል የማንበብና የማጥናት ፍላጎት እንዲያድርብን ሊረዳን የሚችለው ምንድን ነው? በምሳሌ 2:​1-6 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የንጉሥ ሰሎሞን ቃላት መልሱን ይሰጡናል። እባክህ መጽሐፍ ቅዱስህን አውጣና ይህንን ጥቅስ አንብብ። ከዚያም በእነዚህ ቁጥሮች ላይ እንወያያለን።

6. የአምላክን እውቀት ማግኘትን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

6 በጥቅሱ መክፈቻ ላይ የሚከተለውን ማሳሰቢያ እናገኛለን:- “ልጄ ሆይ፣ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፣ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ።” (ምሳሌ 2:​1, 2) ከእነዚህ ቁጥሮች የምንማረው ነገር ምንድን ነው? በግለሰብ ደረጃ ሁላችንም የአምላክን ቃል የማጥናት ኃላፊነት እንዳለብን እንገነዘባለን። “ቃሌን ብትቀበል” የሚለውን ቅድመ ሁኔታ ልብ በል። አብዛኛው ሰው የአምላክን ቃል ቸል ስለሚል ይህ ማሳሰቢያ መሰጠቱ በጣም አስፈላጊ ነው። የአምላክን ቃል በማጥናት ደስታ ማግኘት ከፈለግን የይሖዋን ቃል መቀበልና ከእጃችን እንዲያመልጥ እንደማንፈልገው ውድ ሃብት አድርገን በጥንቃቄ መያዝ ይገባናል። የአምላክን ቃል ችላ ማለት ወይም መጠራጠር እስክንጀምር ድረስ በዕለታዊ ጉዳዮቻችን ከልክ በላይ እንድንጠመድ ወይም ሐሳባችን እንዲከፋፈል መፍቀድ አይኖርብንም።​—⁠ሮሜ 3:​3, 4

7. በተቻለ መጠን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና በጥሞና መከታተል የሚኖርብን ለምንድን ነው?

7 በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የአምላክ ቃል ሲብራራ በጥሞና ‘እናዳምጣለን?’ (ኤፌሶን 4:​20, 21) ማስተዋል ለማግኘት ‘ልባችንን እናዘነብላለን?’ ተናጋሪው ብዙም ተሞክሮ የሌለውም ቢሆን እንኳ የሚናገረው የአምላክን ቃል እስከሆነ ድረስ በትኩረት ልንከታተለው ይገባል። እርግጥ የይሖዋን ጥበብ ለማዳመጥ በተቻለ መጠን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይኖርብናል። (ምሳሌ 18:​1) በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም ተደርጎ የነበረው ስብሰባ ያመለጣቸው ሰዎች ካሉ ምን ያህል እንደሚቆጩ ገምት! ስብሰባዎቻችን እንደዚያ ተዓምራዊ ነገር የሚከናወንባቸው ባይሆኑም ዋና መማሪያ መጽሐፋችን የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠናባቸው ቦታዎች ናቸው። በመሆኑም በጥሞና የምናዳምጥና መጽሐፍ ቅዱሳችንን ይዘን የምንከታተል ከሆነ ከእያንዳንዱ ስብሰባ ከፍተኛ ጥቅም እናገኛለን።​—⁠ሥራ 2:​1-4፤ ዕብራውያን 10:​24, 25

8, 9. (ሀ) የግል ጥናት ምን እንድናደርግ ይጠይቅብናል? (ለ) ወርቅ ያለውን ዋጋ የአምላክን እውቀት ከማግኘት ጋር እንዴት ታወዳድረዋለህ?

8 ጠቢቡ ንጉሥ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፣ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፣ . . .” (ምሳሌ 2:​3) ይህ ጥቅስ የሚመክረን ምን ዓይነት ዝንባሌ ወይም መንፈስ እንዲኖረን ነው? የይሖዋን ቃል የመረዳት ልባዊ ፍላጎት እንዲያድርብን እንደሆነ ግልጽ ነው! ማስተዋል ለማግኘትና የይሖዋን ፈቃድ ለመረዳት ብለን እንድናጠና የሚያበረታታ ነው። ይህ ደግሞ ጥረት የሚጠይቅ ሲሆን ቀጥሎ ሰሎሞን የተናገራቸውን ቃላትና የተጠቀመበትን ምሳሌ እንድናስብ ያደርገናል።​—⁠ኤፌሶን 5:​15-17

9 ሰሎሞን በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “እርስዋንም [እውቀትን] እንደ ብር ብትፈላልጋት፣ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ . . .” (ምሳሌ 2:​4) ይህን ስናነብብ ላለፉት ብዙ መቶ ዓመታት ሰዎች የደከሙባቸው እንደ ወርቅና ብር ያሉት የከበሩ ማዕድናት የሚባሉ ነገሮች ትዝ ይሉናል። ሰዎች ለወርቅ ሲሉ እርስ በርስ ተገዳድለዋል። ሌሎች ደግሞ ወርቅ ለማግኘት ሕይወታቸውን በሙሉ ሲማስኑ ኖረዋል። ይሁንና ወርቅ በእርግጥ ዋጋው ምን ያህል ነው? እልም ያለ በረሃ ውስጥ በውሃ ጥም ልትሞት ብትደርስ የትኛውን ማግኘት ትመርጣለህ? አንድ ጥፍጥፍ ወርቅ ወይስ አንድ ብርጭቆ ውኃ? ለወርቅ የሚሰጠው ዋጋ ሰዎች ራሳቸው የተመኑትና በየጊዜው የሚቀያየር ነው። a ያም ሆኖ ሰዎች ወርቅ ለማግኘት በቅንዓት ሲጋደሉ ኖረዋል። ታዲያ እኛ ስለ አምላክና ስለ ፈቃዱ ጥበብ፣ ማስተዋልና እውቀትን ለማግኘት ምንኛ አብልጠን በቅንዓት መጋደል ይኖርብናል! ይሁንና እንዲህ በማድረጋችን የምናገኘው በረከት ምንድን ነው?​—⁠መዝሙር 19:​7-10፤ ምሳሌ 3:​13-18

10. የአምላክን ቃል ብናጠና ምን እናገኛለን?

10 ሰሎሞን እንዲህ በማለት ንግግሩን ይቀጥላል:- “የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።” (ምሳሌ 2:​5) ኃጢአተኛ የሆንነው ሰዎች የአጽናፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ገዥ የይሖዋን እውቀት ማግኘት መቻላችን እንዴት የሚያስገርም ነው! (መዝሙር 73:​28፤ ሥራ 4:​24) ፈላስፎችና በዓለም ውስጥ ጠቢባን ተደርገው የሚታዩ ሰዎች ላለፉት ብዙ መቶ ዘመናት የሕይወትንና የአጽናፈ ዓለሙን ምሥጢር ለማወቅ ብዙ ደክመዋል። ሆኖም ‘የአምላክን እውቀት’ ማግኘት አልቻሉም። ለምን? ይህ እውቀት በአምላክ ቃል ውስጥ ተቀምጦ ብዙ ሺህ ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም ስለናቁትና አቅልለው ስለተመለከቱት ሳይቀበሉትና ሳያስተውሉት ቀርተዋል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 1:18-21

11. የግል ጥናት በማድረግ የሚገኙት አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

11 ሰሎሞን የአምላክን ቃል የምናጠናበትን ተጨማሪ ምክንያት ሲጠቅስ “እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ” ብሏል። (ምሳሌ 2:​6) አንድ ሰው ከልቡ ጥረት ካደረገ ይሖዋ ጥበብን፣ እውቀትንና ማስተዋልን በልግስና ይሰጠዋል። የአምላክን ቃል በግል ማጥናት ጥረት፣ ራስን መገሰጽና መሥዋዕት መክፈልን የሚጠይቅ ቢሆንም እንደ ውድ ነገር እንድንመለከተው የሚያደርጉ በቂ ምክንያቶች አሉን። ሌላው ቢቀር መጽሐፍ ቅዱስን በቀላሉ ማግኘት ስለምንችል ጥንት እንደነበሩት አንዳንድ ሰዎች የራሳችንን ቅጂ በእጃችን መገልበጥ አያስፈልገንም!​—⁠ዘዳግም 17:​18, 19

ለይሖዋ እንደሚገባ መመላለስ

12. የአምላክን እውቀት ለማግኘት ስንጥር ዓላማችን ምን መሆን ይኖርበታል?

12 የግል ጥናት የምናደርግበት ምክንያት ምን መሆን ይኖርበታል? ከሌሎች የተሻልን ሆነን ለመታየት ነው? ወይስ በእውቀት ልቀን ለመገኘት? አሊያም የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቅ ለመሆን ነው? አይደለም። ግባችን በአነጋገራችንም ሆነ በድርጊታችን ክርስትናን ማንጸባረቅና ሰዎችን ለመርዳት ዝግጁ በመሆን እንደ ክርስቶስ ለሌሎች የእረፍት ምንጭ ሆነን መገኘት ነው። (ማቴዎስ 11​:28-30) ሐዋርያው ጳውሎስ “እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል” ሲል አስጠንቅቋል። (1 ቆሮንቶስ 8:​1) እንግዲያው ሙሴ እንደሚከተለው በማለት ለይሖዋ ሲናገር ያሳየውን ዓይነት የትህትና መንፈስ ልናንጸባርቅ ይገባል:- “አሁንም በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፣ አውቅህ ዘንድ በፊትህም ሞገስን አገኝ ዘንድ መንገድህን እባክህ አሳየኝ።” (ዘጸአት 33:​13) አዎን፣ እውቀት ለማግኘት የምንጥረው አምላክን ለማስደሰት እንጂ ሰዎችን ለማስደመም መሆን የለበትም። ለአምላክ እንደሚገባ የምንመላለስ ትሑት አገልጋዮቹ መሆን እንፈልጋለን። እዚህ ግብ ላይ ልንደርስ የምንችለው እንዴት ነው?

13. አንድ ሰው ለአምላክ እንደሚገባ የሚመላለስ አገልጋይ ለመሆን ምን ያስፈልገዋል?

13 ጳውሎስ አምላክን እንዴት ደስ ማሰኘት እንደሚቻል ጢሞቴዎስን ሲመክረው “የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር [“በትክክል የሚጠቀም፣” NW ] የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፣ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ” ብሎታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:​15) ‘በትክክል መጠቀም’ የሚለው መግለጫ ‘በትክክል መከርከም’ ወይም ‘አስተካክሎ መቁረጥ’ የሚል መልእክት ያለው የሁለት ግሪክኛ ግሶች ጥምረት ነው። (ኪንግደም ኢንተርሊኒየር ) አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት ይህ መግለጫ አንድን ዓይነት ቅድ በማሰብ ጨርቁን አስተካክሎ የሚቆርጥን ልብስ ሰፊ ወይም ፈር ተከትሎ የሚያርስን ገበሬ ሁኔታ ያመለክታል። ያም ሆነ ይህ ውጤቱ ትክክለኛና ቀና መሆን ይኖርበታል። በመሆኑም ጢሞቴዎስ ለአምላክ እንደሚገባ የሚመላለስና የእርሱ ሞገስ ያለው አገልጋይ እንዲሆን ትምህርቱንም ሆነ አኗኗሩን ከእውነት ቃል ጋር ለማጣጣም ‘መትጋት’ ነበረበት።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​16

14. የግል ጥናታችን አነጋገራችንንና ድርጊታችንን ሊነካው የሚገባው እንዴት ነው?

14 ጳውሎስ በቆላስይስ ለነበሩት ክርስቲያኖች “በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጋችሁ . . . በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙት ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ” በማለት ሲመክራቸው ይህንኑ ጉዳይ መጥቀሱ ነበር። (ቆላስይስ 1:​10-12) በዚህ ጥቅስ ላይ ጳውሎስ ለይሖዋ እንደሚገባ መመላለስን ‘በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ ከማፍራት’ እንዲሁም ‘በአምላክ ትክክለኛ እውቀት ከማደግ’ ጋር አያይዞ ገልጾታል። በሌላ አባባል በይሖዋ ዘንድ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነገር እውቀት ለመሰብሰብ ያለን ከፍ ያለ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የምናደርገውና የምንናገረው ከአምላክ ቃል ጋር የሚጣጣም መሆኑ ጭምር ነው። (ሮሜ 2:​21, 22) ስለዚህ አምላክን ደስ ማሰኘት ከፈለግን የግል ጥናታችን በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን ላይ ለውጥ ማምጣት ይኖርበታል።

15. አእምሯችንንና ሐሳባችንን መጠበቅና መቆጣጠር የምንችለው እንዴት ነው?

15 ሰይጣን አእምሯችንን በመማረክ መንፈሳዊነታችንን ለማጥፋት ቆርጦ ተነስቷል። (ሮሜ 7:​14-25) በመሆኑም ለይሖዋ እንደሚገባ መመላለስ እንድንችል አእምሯችንንና ሐሳባችንን መጠበቅና መቆጣጠር ይኖርብናል። መሣሪያችን ‘አእምሮን ሁሉ በመማረክ ለክርስቶስ እንዲታዘዝ’ የማድረግ ኃይል ያለው ‘የአምላክ እውቀት ነው።’ ይህ ደግሞ ራስ ወዳድነትንና የሥጋ ምኞቶችን ከአእምሯችን አውጥተን ለመጣል በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያስገነዝብ ተጨማሪ ምክንያት ነው።​—⁠2 ቆሮንቶስ 10:​5

እውቀት ለማግኘት የሚረዱ ጽሑፎች

16. ከይሖዋ በመማር ራሳችንን መጥቀም የምንችለው እንዴት ነው?

16 ከይሖዋ መማር ለመንፈሳዊም ሆነ ለሰብዓዊ ሕይወታችን ይጠቅመናል። ከሕይወታችን ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ሃይማኖታዊ ትምህርት አይደለም። ከዚህ የተነሳ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።” (ኢሳይያስ 48:​17) ይሖዋ በሚጠቅመን መንገድ እንድንመላለስ የሚያደርገው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ በመንፈሱ አነሳሽነት የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ አለን። መጽሐፍ ቅዱስ አዘውትረን የምንጠቀምበት ዋነኛ መማሪያ መጽሐፋችን ነው። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ መጽሐፍ ቅዱሳችንን ገልጠን መከታተላችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው። ይህን ማድረጋችን ምን ጥቅም እንዳለው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 ላይ ተጠቅሶ ከሚገኘው የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ታሪክ ማስተዋል እንችላለን።

17. ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ያጋጠመው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? ከእርሱስ ምን እንማራለን?

17 ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ወደ ይሁዲነት የተለወጠ ከመሆኑም በላይ በአምላክ ላይ እምነት የነበረውና ቅዱሳን ጽሑፎችንም የሚያነብብ ሰው ነበር። በአንድ ወቅት የኢሳይያስን መጽሐፍ እያነበበ በሰረገላው ሲጓዝ ፊልጶስ አጠገቡ እየሮጠ “በእውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” ሲል ጠየቀው። የጃንደረባው ምላሽ ምን ነበር? “የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው።” ፊልጶስም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ጃንደረባው የኢሳይያስን ትንቢት እንዲያስተውል ረዳው። (ሥራ 8:27-35) ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን? መጽሐፍ ቅዱስን በግል ማንበባችን ብቻ በቂ አይደለም። ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት ታማኝና ልባም ባሪያን እየተጠቀመ ቃሉን በትክክል እንድናስተውል ይረዳናል። ይህንን የሚያደርገው እንዴት ነው?​—⁠ማቴዎስ 24:​45-47፤ ሉቃስ 12:​42

18. ታማኝና ልባም ባሪያ የሚረዳን እንዴት ነው?

18 ኢየሱስ ባሪያውን “ታማኝና ልባም” ብሎ ቢጠራውም አይሳሳትም የሚል ዋስትና አልሰጠም። ይህ የታመኑ ቅቡዓን ወንድሞች ቡድን ፍጽምና የሌላቸውን ክርስቲያኖች ያቀፈ ነው። ከልባቸው በቅንነት የሚያገለግሉ ቢሆንም በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ወንዶች ሁሉ እነርሱም ስህተት ሊሠሩ ይችላሉ። (ሥራ 10:​9-15፤ ገላትያ 2:​8, 11-14) ይሁን እንጂ ሥራቸውን የሚያከናውኑት በቀና ልቦና ነው። ይሖዋም በአምላክ ቃልና በተስፋዎቹ ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክሩ ጽሑፎችን እንዲያዘጋጁልን መሣሪያ አድርጎ ይጠቀምባቸዋል። የባሪያው ክፍል ያዘጋጀልን ለግል ጥናት የሚጠቅም ዋነኛው ጽሑፍ የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ነው። በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በ42 ቋንቋዎች የሚገኝ ሲሆን በርካታ በሆኑ እትሞች 114 ሚልዮን ቅጂዎች ታትመዋል። በግል ጥናታችን ጥሩ አድርገን ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​14-17

19. ለግል ጥናት የሚረዱን የባለ ማጣቀሻው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ክፍሎች የትኞቹ ናቸው?

19 ለምሳሌ ያህል ባለ ማጣቀሻው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም እንዴት ሊረዳን እንደሚችል እንመልከት። የማገናዘቢያ ጥቅሶችን የያዘ አምድ፣ የግርጌ ማስታወሻዎች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላትን በቅደም ተከተላቸው የሚዘረዝር መጠነኛ ኮንኮርዳንስ፣ በግርጌ ማስታወሻው ላይ የተሠራባቸው ቃላት ማውጫ እንዲሁም ካርታዎችንና ሰንጠረዦችን ጨምሮ 43 ርዕሰ ጉዳዮችን በሰፊው የሚዳስስ ተጨማሪ ክፍል አለው። “መግቢያው” ይህን ልዩ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለማዘጋጀት እንደ ዋቢ ስላገለገሉት ብዙ ምንጮች ማብራሪያ ይሰጣል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አንተ በምትችለው ቋንቋ የሚገኝ ከሆነ በተቻለ መጠን ከእነዚህ የመጽሐፉ ክፍሎች ጋር ተዋውቀህ በሚገባ ተጠቀምባቸው። በዚህም ሆነ በዚያ የጥናታችን መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ደግሞ መለኮታዊውን ስም ጎላ አድርጎ የሚገልጽና የአምላክን መንግሥት አበክሮ የሚያስተዋውቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው።​—⁠መዝሙር 149:​1–9፤ ዳንኤል 2:​44፤ ማቴዎስ 6:​9, 10

20. የግል ጥናትን በተመለከተ መልስ ማግኘት ያለባቸው ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?

20 አሁን ደግሞ እንደሚከተሉት ያሉትን ጥያቄዎች ልናነሳ እንችላለን:- ‘መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ምን ተጨማሪ እገዛ ያስፈልገናል? ለግል ጥናት ጊዜ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ከጥናታችን የበለጠ ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ እንችላለን? ጥናታችን በሌሎች ላይ ምን ውጤት ሊያመጣ ይገባዋል?’ በሚቀጥለው ርዕስ የክርስቲያናዊ እድገታችን ወሳኝ ዘርፎች በሆኑት በእነዚህ ነጥቦች ላይ እንወያያለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ከ1979 ወዲህ የወርቅ ዋጋ በእጅጉ የዋዠቀ ሲሆን በ1980 ውስጥ 850 የአሜሪካን ዶላር የነበረው 31 ግራም ወርቅ በ1999 ወደ 252.80 የአሜሪካ ዶላር አሽቆልቁሏል።

ታስታውሳለህን?

• “ማሰላሰል” ሲባል ምን ማለት ነው?

• የአምላክን ቃል ስለ ማጥናት ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው?

• የግል ጥናት የምናደርገው በምን ዓላማ መሆን ይኖርበታል?

• የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት ለማግኘት የሚረዱን ጽሑፎች የትኞቹ ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቤቴል ቤተሰብ አባላት ጠዋት ጠዋት በዕለቱ ጥቅስ ላይ መወያየቱን በመንፈሳዊ የሚያበረታታ ሆኖ አግኝተውታል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጉዞ ላይ ስንሆን በቴፕ ክር የተቀዳውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ በማዳመጥ ጊዜያችንን በአግባቡ መጠቀም እንችላለን

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰዎች ወርቅ ለማግኘት ብዙ ሲደክሙ ኖረዋል። እኛስ የአምላክን ቃል ለማጥናት ምን ያህል እንጥራለን?

[ምንጭ]

Courtesy of California State Parks, 2002

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ዘላለም ሕይወት ሊመራ የሚችል ውድ ሀብት ነው