የአንባብያን ጥያቄዎች
የአንባብያን ጥያቄዎች
ከራእይ 20:8 በመነሳት በመጨረሻው ፈተና ወቅት ሰይጣን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ያስታል ብለን መደምደም ይኖርብናል?
ራእይ 20:8 በመሲሐዊው መንግሥት የሺህ ዓመት ግዛት ማብቂያ ላይ ሰይጣን በምድር በሚኖሩ ሰዎች ላይ የሚሰነዝረውን የመጨረሻ ጥቃት ይገልጻል። ጥቅሱ ሰይጣንን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “በአራቱም በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ፣ ጎግንና ማጎግን፣ እንዲያስታቸው ለሰልፍም እንዲያስከትታቸው ይወጣል፤ ቊጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ የሚያህል ነው።”
ሳይንስ የቱንም ያህል ቢመጥቅና የተራቀቁ መሣሪያዎች ቢኖሩም ‘የባሕር አሸዋን’ መስፈርም ሆነ መቁጠር አልተቻለም። ስለዚህ የባሕር አሸዋ የሚለው አባባል የሚወክለው ያልታወቀ ወይም ያልተወሰነ ቁጥርን ነው ለማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ መግለጫው የሚያመለክተው ኅልቆ መሳፍርት የሌለውን እንዲያውም ፈጽሞ ሊተመን የማይችል ብዙ ቁጥርን ነው ወይስ በውል የማይታወቅ ሆኖም ጥቂት የማይባል ቁጥርን?
“እንደ ባሕር አሸዋ” የሚለው መግለጫ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያየ መንገድ ተሠርቶበታል። ለምሳሌ ያህል በዘፍጥረት 41:49 ላይ እንዲህ ይላል:- “ዮሴፍም እንደ ባሕር አሸዋ እጅግ ብዙ የሆነ ስንዴን አከማቸ፣ መስፈርን እስኪተው ድረስ፤ ሊሰፈር አልተቻለምና።” እዚህ ላይ ለማጉላት የተፈለገው የእህሉን መጠን ለመስፈር አለመቻሉን ነው። ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ይሖዋም እንዲህ ብሎ ተናግሯል:- “የሰማይን ሠራዊት መቁጠር የባሕርንም አሸዋ መስፈር እንደማይቻል፣ እንዲሁ የባሪያዬን የዳዊትን ዘርና የሚያገለግሉኝን ሌዋውያንን አበዛለሁ።” የሰማይ ከዋክብትና የባሕር አሸዋ ሊቆጠሩ የማይችሉ መሆናቸው የተረጋገጠ እንደሆነ ሁሉ ይሖዋ ለዳዊት የገባውን ቃል እንደሚፈጽም የተረጋገጠ ነው።—ኤርምያስ 33:22
“የባሕር አሸዋ” የሚለው አባባል አብዛኛውን ጊዜ ብዛትን ወይም ከፍተኛ መጠንን ለማመልከት ያገለግላል። በጌልገላ የነበሩት እስራኤላውያን በማክማስ የሰፈረውን “በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ” በጣም ብዙ የሆነውን የፍልስጤም ሠራዊት ሲመለከቱ በእጅጉ ፈርተው ነበር። (1 ሳሙኤል 13:5, 6፤ መሳፍንት 7:12) በሌላ ቦታ ደግሞ “እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው” የሚል እናነባለን። (1 ነገሥት 4:29) በሁለቱም ጥቅሶች ላይ ለማመልከት የተፈለገው ከፍተኛ መጠንን ሆኖም ገደብ ያለውን ነገር ነው።
“በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ” የሚለው መግለጫ ከብዛት ጋር ምንም ግንኙነት በሌለው መልኩ ያልተወሰነ ቁጥርን ብቻ ለማመልከትም ሊያገለግል ይችላል። ይሖዋ ለአብርሃም “በእውነት . . . ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 22:17) ይህንኑ ተስፋ ለአብርሃም የልጅ ልጅ ለያዕቆብ በድጋሚ ሲናገር “እንደ ምድር አሸዋ” የሚል መግለጫ የተጠቀመ ሲሆን ያዕቆብም “እንደ ባሕር አሸዋ” በማለት በሌላ መንገድ ጠቅሶታል። (ዘፍጥረት 28:14፤ 32:12) ከጊዜ በኋላ የአብርሃም “ዘር” ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይጨምር 144, 000 እንደሚያህል የታወቀ ሲሆን ኢየሱስ “ታናሽ መንጋ” በማለት ጠርቶታል።—ሉቃስ 12:32፤ ገላትያ 3:16, 29፤ ራእይ 7:4፤ 14:1, 3
እነዚህ ምሳሌዎች ምን ያስገነዝቡናል? “እንደ ባሕር አሸዋ” የሚለው መግለጫ ሁልጊዜ ኅልቆ መሳፍርት የሌለውን ቁጥር ብቻ እንደማያመለክት ያስገነዝቡናል። ይህ መግለጫ አብዛኛውን ጊዜ በውል የማይታወቅ ሆኖም ጥቂት የማይባል ቁጥርን ያመለክታል። በመሆኑም ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች ላይ የመጨረሻውን ጥቃት በሚሰነዝርበት ወቅት ከእርሱ ጋር የሚተባበሩት ዓመፀኞች ኅልቆ መሳፍርት የሌላቸው ባይሆኑም ጥቂት ግን እንደማይሆኑ መገመት ምክንያታዊ ነው። ትክክለኛ ቁጥራቸውን ግን ለጊዜው ማወቅ አይቻልም።