የእውነትን ቃል በትክክል እንድንጠቀም ምን ሊረዳን ይችላል?
የእውነትን ቃል በትክክል እንድንጠቀም ምን ሊረዳን ይችላል?
የትያትር ሃያሲ የሆኑ የአንድ ጋዜጣ አምድ አዘጋጅ በአንድ ወቅት በተመለከቱት ትያትር ብዙም ሳይደሰቱ ቀሩ። በኋላም ስለተመለከቱት ትያትር አስተያየት ሲሰጡ “የማይረባ ነገር ማየት የምትፈልጉ ከሆነ ይህ ትያትር ፈጽሞ አያምልጣችሁ” ሲሉ ጻፉ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የተውኔቱ አዘጋጆች ሃያሲው ከሰጡት አስተያየት ላይ “ይህ ትያትር ፈጽሞ አያምልጣችሁ!” የሚለውን ብቻ ቀንጭበው በመጥቀስ ማስታወቂያ ሠሩ። ማስታወቂያው የሃያሲውን ቃላት በትክክል ቢጠቅስም ሃያሲው ከሰጡት አስተያየት ውስጥ ቁንጽል ሐሳብ ብቻ የያዘ በመሆኑ ሐሳባቸውን አዛብቶ አቅርቧል።
ይህ ምሳሌ አንድን ዓረፍተ ነገር በትክክል ለመረዳት በዙሪያው ያለው ሐሳብ ጉልህ ሚና እንዳለው ያሳያል። ቃላትን ቆንጽሎ መጥቀስ ትርጉማቸውን ሊያዛባ ይችላል። ሰይጣን ኢየሱስን ለማሳሳት በሞከረበት ጊዜ ጥቅሶችን መጀመሪያ ከተጻፉበት መንፈስ ውጪ ጠቅሷል። (ማቴዎስ 4:1-11) በአንጻሩ ደግሞ በአንድ ዓረፍተ ነገር ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ግምት ውስጥ ማስገባት ትርጉሙን በተሻለ መንገድ እንድንረዳ ያስችለናል። ከዚህም የተነሳ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ስንመረምር ጸሐፊው ለማስተላለፍ የፈለገውን ሐሳብ በተሻለ ሁኔታ መረዳት እንድንችል ምንጊዜም በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ (ኮንቴክስት) መመልከታችን ጠቃሚ ነው።
የአምላክን ቃል በትክክል ተጠቀሙ
አንድ መዝገበ ቃላት በሰጠው ፍቺ መሠረት “ኮንቴክስት” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “በጽሑፍ በሰፈረ ወይም በአንደበት በተነገረ አንድ ቃል ወይም ምንባብ ዙሪያ የሚገኙና በአብዛኛው የቃሉን ወይም የምንባቡን ትርጉም የሚወስኑ ሐሳቦችን” ያመለክታል። ከዚህም በተጨማሪ ቃሉ “ከአንድ ክስተት፣ ሁኔታ፣ ወዘተ ጋር ዝምድና ያላቸውን ነገሮች ወይም ተጨባጭ እውነታዎች” ሊያመለክት ይችላል። ቃሉ ከሁለተኛው ፍቺ አንጻር ሲሠራበት “ሥረ መሠረት” የሚል ትርጉምም ሊሰጠው ይችላል። በተለይ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር [“በትክክል የሚጠቀም፣” NW ] የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፣ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ” ሲል መጻፉ የአንድን ጥቅስ ዙሪያ ገባና ሥረ መሠረት መመርመሩ በጣም አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) የአምላክን ቃል በትክክል መጠቀም እንድንችል በሚገባ መረዳትና ከዚያም ምንም ሳናዛንፍ በሐቀኝነት ለሌሎች ማስረዳት ይኖርብናል። ለመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ ለይሖዋ ያለን አክብሮት እንዲህ እንድናደርግ የሚያነሳሳን ሲሆን በዚህ ረገድ የአንድን ጥቅስ ዙሪያ ገባና ሥረ መሠረት መመርመር ከፍተኛ እገዛ ያበረክትልናል።
የሁለተኛ ጢሞቴዎስ ሥረ መሠረት
በምሳሌ ደረጃ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን ሁለተኛ ጢሞቴዎስን እስቲ እንመርምር። a የመልእክቱን ሥረ መሠረት በተመለከተ ጥያቄዎች በማንሳት ምርምራችንን መጀመር እንችላለን። ሁለተኛ ጢሞቴዎስን የጻፈው ማን ነው? መቼ ተጻፈ? ጸሐፊው ሲጽፍ በምን ዓይነት ሁኔታ ሥር ነበር? ከዚያም መልእክቱ የተሰየመበት “ጢሞቴዎስ” የተባለው ሰው የነበረበት ሁኔታ ምን ይመስላል? መልእክቱ የተጻፈለት በምን ምክንያት ነበር? ብለን መጠየቅ እንችላለን። የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማግኘታችን መልእክቱ የያዘውን ቁም ነገር እንድንረዳ የሚያስችለን ከመሆኑም በላይ በዛሬው ጊዜ ከመጽሐፉ ጥቅም ማግኘት የምንችልበትን መንገድ እንድንገነዘብ ይረዳናል።
የሁለተኛ ጢሞቴዎስ የመክፈቻ ቃላት መልእክቱ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፈለት ደብዳቤ እንደሆነ ያሳያሉ። ሌሎች ጥቅሶች ደግሞ ጳውሎስ ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት በምሥራቹ ምክንያት ታስሮ እንደነበር ይገልጻሉ። ጳውሎስን ብዙዎች ርቀውት የነበረ ከመሆኑም በላይ የሚሞትበት ጊዜ እንደቀረበ ተሰምቶታል። (2 ጢሞቴዎስ 1:15, 16፤ 2:8-10፤ 4:6-8) በመሆኑም መልእክቱን የጻፈው ለሁለተኛ ጊዜ በሮም ታስሮ በነበረበት በ65 እዘአ ገደማ መሆን አለበት። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ኔሮ የሞት ፍርድ እንደበየነበት ይታመናል።
ሁለተኛ ጢሞቴዎስ በተጻፈበት ወቅት የነበረው ሁኔታ ይህን ይመስላል። ሆኖም ጳውሎስ መልእክቱን ለጢሞቴዎስ የጻፈው ስለደረሰበት ችግር ለማሳወቅ አለመሆኑ ሊስተዋል የሚገባው ጉዳይ ነው። ከዚህ ይልቅ ጢሞቴዎስ ወደፊት አስቸጋሪ ጊዜ እንደሚጠብቀው ያስጠነቀቀው ከመሆኑም በላይ ትኩረቱን የሚከፋፍሉ ጉዳዮችን እንዲያስወግድ፣ ‘እየበረታ’ እንዲሄድ እና ከጳውሎስ ያገኘውን ትምህርት ለሌሎች እንዲያስተምር አበረታቶታል። ጢሞቴዎስ ያስተማራቸው ክርስቲያኖችም በበኩላቸው ሌሎችን ለመርዳት በሚገባ የታጠቁ ይሆናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 2:1-7) በአስቸጋሪ ጊዜያት ጭምር ለሌሎች የአሳቢነት መንፈስ የተንጸባረቀበት እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! በዛሬው ጊዜ ለእኛስ ምንኛ ግሩም ምክር ይዞልናል!
ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ‘የተወደደው ልጄ’ ሲል ጠርቶታል። (2 ጢሞቴዎስ 1:2) ይህ ወጣት በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የጳውሎስ ታማኝ አጋር እንደሆነ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። (ሥራ 16:1-5፤ ሮሜ 16:21፤ 1 ቆሮንቶስ 4:17) ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ በጻፈለት ወቅት ጢሞቴዎስ በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ወጣት ነበር ለማለት ይቻላል። (1 ጢሞቴዎስ 4:12) ሆኖም በዚህ ጊዜ ለ14 ዓመታት ያህል ‘ከጳውሎስ ጋር በማገልገል’ ታማኝ መሆኑን አስመስክሯል። (ፊልጵስዩስ 2:19-22) ጢሞቴዎስ በዕድሜ ወጣት ቢሆንም ሌሎች ሽማግሌዎች ‘በቃል ከመጣላት’ ይልቅ እንደ እምነትና ጽናት በመሳሰሉ አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጳውሎስ የመምከር ኃላፊነት ሰጥቶታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:14) ጢሞቴዎስ የጉባኤ የበላይ ተመልካቾችንና አገልጋዮችን የመሾም ሥልጣንም ነበረው። (1 ጢሞቴዎስ 5:22) ይሁን እንጂ በሥልጣኑ በመጠቀም ረገድ በራስ የመተማመን መንፈስ ይጎድለው የነበረ ይመስላል።—2 ጢሞቴዎስ 1:6, 7
ሽማግሌ ሆኖ ያገለግል የነበረው ይህ ወጣት አንዳንድ ከበድ ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል። ለምሳሌ ያህል ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ የተባሉት ግለሰቦች “ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል” የሚል ትምህርት እያስፋፉ ‘የአንዳንዶችን እምነት በመገልበጥ’ የፈጠሩት ችግር ይገኝበታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:17, 18) ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው ከመንፈሳዊ ትንሣኤ በስተቀር ሌላ ዓይነት ትንሣኤ እንደሌለና ይህም ቀደም ሲል ለክርስቲያኖች ተፈጽሞላቸዋል የሚል እምነት ነበራቸው። ምናልባትም ጳውሎስ ክርስቲያኖች በኃጢአታቸው ሙታን እንደነበሩና በአምላክ መንፈስ አማካኝነት ግን ሕያው እንደሆኑ የተናገረውን ሐሳብ በተሳሳተ መንገድ ተረድተው ሳይሆን አይቀርም። (ኤፌሶን 2:1-6) ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱ የከሀዲዎች ተጽዕኖ እያየለ እንደሚሄድ አስጠንቅቋል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ . . . እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፣ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4) ጳውሎስ አስቀድሞ የሰጠው ይህ ማስጠንቀቂያ ጢሞቴዎስ ምክሩን ዛሬ ነገ ሳይል ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት ያሳያል።
በዛሬው ጊዜ መጽሐፉ ያለው ጠቀሜታ
ከላይ ከተጠቀሰው በመነሳት ጳውሎስ ሁለተኛ ጢሞቴዎስን የጻፈው ቢያንስ በሚከተሉት ምክንያቶች የተነሳ መሆኑን እንረዳለን:- (1) የሚሞትበት ጊዜ መቃረቡን ስለተገነዘበ ጢሞቴዎስን ከወዲሁ ለማዘጋጀት ስላሰበ። (2) ጢሞቴዎስ በበላይ ተመልካችነት የሚያስተዳድረውን ጉባኤ ከክህደትና ከሌሎች መጥፎ ተጽዕኖዎች የመጠበቅ ብቃት እንዲኖረው እሱን የመርዳት ፍላጎት ስለነበረው። (3) ጢሞቴዎስ በይሖዋ አገልግሎት ራሱን እንዲያስጠምድና የሐሰት ትምህርቶችን ለመቃወም በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትን የቅዱሳን ጽሑፎች ትክክለኛ እውቀት እንዲጠቀም ለማበረታታት ስለፈለገ።
ሁለተኛ ጢሞቴዎስ ሲጻፍ የነበረውን ሁኔታና የተጻፈበትን ዓላማ መረዳታችን መልእክቱን ይበልጥ ትርጉም ያለው ያደርግልናል። ዛሬም የራሳቸውን ትምህርት የሚያስፋፉና እምነታችንን ለመገልበጥ የሚፈልጉ ሄሜኔዎስንና ፊሊጦስን የመሳሰሉ ከሀዲዎች አልጠፉም። ከዚህም በላይ ጳውሎስ “የሚያስጨንቅ ዘመን” እንደሚመጣ ትንቢት በተናገረለት ጊዜ ውስጥ እንገኛለን። ጳውሎስ “በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” ሲል የሰጠው ማስጠንቀቂያ እውነት መሆኑን ብዙዎች በተሞክሮ አይተውታል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 12) ታዲያ ጸንተን መቆም የምንችለው እንዴት ነው? እንደ ጢሞቴዎስ ሁሉ እኛም ይሖዋን ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉ ክርስቲያኖች የሚሰጡንን ምክር መከተል ይኖርብናል። እንዲሁም የግል ጥናት በማድረግ፣ በመጸለይና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት በይሖዋ ጸጋ ‘እየበረታን’ መሄድ እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ ትክክለኛ እውቀት ባለው ኃይል በመታመን ጳውሎስ ‘የጤናማውን ቃል ምሳሌ ያዝ’ ሲል የሰጠውን ጥብቅ ማሳሰቢያ መከተል እንችላለን።—2 ጢሞቴዎስ 1:13
‘የጤናማው ቃል ምሳሌ’
ጳውሎስ የጠቀሰው “ጤናማ ቃል” ምንድን ነው? ጳውሎስ ይህን አባባል የተጠቀመው የእውነተኛውን ክርስትና መሠረተ ትምህርት ለማመልከት ነው። ለጢሞቴዎስ በጻፈው በመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ ‘ጤናማው ቃል’ በመሠረቱ ‘ከኢየሱስ ክርስቶስ የሆነው’ ትምህርት መሆኑን ገልጿል። (1 ጢሞቴዎስ 6:3) አንድ ሰው የጤናማውን ቃል ምሳሌ የሚከተል ከሆነ ትክክለኛ አስተሳሰብ ይኖረዋል እንዲሁም ለሌሎች ፍቅርና አሳቢነት ያሳያል። የኢየሱስ አገልግሎትና ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከሚገኙት ከሌሎቹ ትምህርቶች ጋር ስምምነት ስላለው “ጤናማ ቃል” የሚለው አባባል በተዘዋዋሪ መንገድ መላውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሊያመለክት ይችላል።
እንደ ማንኛውም ክርስቲያን ሽማግሌ ጢሞቴዎስም ‘በአደራ’ የተሰጠውን የጤናማውን ቃል ምሳሌ እንዲጠብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቶት ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 1:13, 14) ጢሞቴዎስ “ቃሉን ስበክ፣ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፣ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፣ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም” ተብሎ ተነግሮታል። (2 ጢሞቴዎስ 4:2) በጢሞቴዎስ ዘመን የክህደት ትምህርት እየተስፋፋ እንደነበር ስናውቅ ጳውሎስ ጤናማውን ቃል ማስተማር አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን አበክሮ የገለጸበት ምክንያት ግልጽ ይሆንልናል። በተጨማሪም ጢሞቴዎስ እየታገሠና እያስተማረ ‘በመዝለፍ፣ በመገሠጽና በመምከር’ ለመንጋው ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎበት እንደነበረ እንገነዘባለን።
ጢሞቴዎስ ቃሉን መስበክ የነበረበት ለእነማን ነው? በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው ጢሞቴዎስ ሽማግሌ እንደመሆኑ መጠን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ቃሉን መስበክ ነበረበት። ተቃዋሚዎች ጫና ያሳድሩ ስለነበር ጢሞቴዎስ መንፈሳዊ ሚዛኑን መጠበቅ እንዲሁም ሰብዓዊ ፍልስፍናን፣ የግል አመለካከቱን ወይም ከንቱ መላምትን ሳይሆን የአምላክን ቃል በድፍረት ማወጅ ነበረበት። እንዲህ ማድረጉ የተሳሳተ አመለካከት ካላቸው ከአንዳንድ ሰዎች ተቃውሞ ሊያስከትልበት እንደሚችል የታወቀ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 1:6-8፤ 2:1-3, 23-26፤ 3:14, 15) ይሁን እንጂ ጢሞቴዎስ፣ ጳውሎስ የተወውን ምሳሌነትና የሰጠውን ምክር በመከተል ክህደት እንዳያንሰራራ መከላከሉን መቀጠል ይችላል።—ሥራ 20:25-32
2 ጢሞቴዎስ 4:5) ወንጌላዊነት ማለትም አማኝ ላልሆኑ ሰዎች፣ ደኅንነት የሚያስገኘውን ምሥራች መስበክ የክርስቲያናዊ አገልግሎት ዐቢይ ገጽታ ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) የአምላክ ቃል ‘አመቺ ባልሆነ ጊዜም’ በጉባኤ ውስጥ እንደሚሰበክ ሁሉ በአስቸጋሪ ሁኔታዎችም ሥር ከጉባኤ ውጪ ላሉ ሰዎች ቃሉን መስበካችንን እንቀጥላለን።—1 ተሰሎንቄ 1:6
ጳውሎስ ቃሉን ስለ መስበክ የተናገረው ሐሳብ ከጉባኤ ውጪ መስበክንም ይጨምራል? አዎን፣ ይጨምራል። ይህንንም በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ ማየት እንችላለን። ጳውሎስ በመቀጠል “አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፣ መከራን ተቀበል፣ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፣ አገልግሎትህን ፈጽም” ብሏል። (ስብከታችንም ሆነ ትምህርታችን በአጠቃላይ የተመሠረተው በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው በአምላክ ቃል ላይ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሙሉ እምነት አለን። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል” ብሎታል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ይህ ጥቅስ አብዛኛውን ጊዜ የሚጠቀሰው መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል እንደሆነ ለማስረዳት ነው። ይህ ትክክል ቢሆንም ጳውሎስ ይህን የጻፈው በምን ዓላማ ነበር?
ጳውሎስ ይህን የጻፈው በጉባኤ ውስጥ ‘የመገሠጽ፣ ልብን የማቅናት፣ በጽድቅ የመምከር’ ኃላፊነት ላለው ሽማግሌ ነበር። በመሆኑም ጢሞቴዎስ ከሕፃንነቱ ጀምሮ በተማረው በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው ጥበብ ላይ ትምክህት እንዲያሳድር እያስታወሰው ነበር። የጢሞቴዎስ ዓይነት ኃላፊነት ያላቸው ሽማግሌዎች መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙ ክርስቲያኖችን መገሠጽ ይኖርባቸዋል። ይህንንም ሲያደርጉ ምንጊዜም በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀም አለባቸው። ከዚህ በተጨማሪ ቅዱሳን ጽሑፎች በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ በመሆናቸው በቃሉ ላይ ተመሥርቶ የሚሰጥ ተግሣጽ በቀጥታ ከአምላክ እንደመጣ ይቆጠራል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተን ተግሣጽ አልቀበልም የሚል ሰው እምቢተኛ የሚሆነው ከሰው ለመጣለት ሐሳብ ሳይሆን ከራሱ ከይሖዋ ለቀረበለት በመንፈስ አነሳሽነት ለተሰጠው ምክር ነው።
ሁለተኛ ጢሞቴዎስ ምንኛ በአምላካዊ ጥበብ የተሞላ መልእክት ይዟል! እንዲሁም በዙሪያው የሚገኘውን ሐሳብ ግምት ውስጥ አስገብተን በውስጡ የሠፈረውን ምክር ስንመረምር ምንኛ የላቀ ትርጉም ያለው ይሆንልናል! በዚህ ርዕስ አማካኝነት ሁለተኛ ጢሞቴዎስ የያዘውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ግሩም ትምህርት ላይ ላዩን ተመልክተናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብበት ጊዜ የምናነብበውን ጥቅስ በዙሪያው ካለው ሐሳብ አንጻርና ከሥረ መሠረቱ ተነስተን መመርመሩ በጣም ጠቃሚ መሆኑን የሚያሳይ አጥጋቢ ትምህርት ቀስመንበታል። እንዲህ ማድረጋችን ‘የእውነትን ቃል በትክክል እንድንጠቀም’ ያስችለናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 1105-8 ተመልከት።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ ጉባኤዎቹን የመጠበቅ ብቃት እንዲኖረው የመርዳት ፍላጎት ነበረው
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል በያዘው ጥበብ ላይ እንዲታመን ጢሞቴዎስን አስታውሶታል