የአንባብያን ጥያቄዎች
የአንባብያን ጥያቄዎች
በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ለሚገኙት መዝሙራት የተሰጡት ቁጥሮች በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ልዩነት የሚታይባቸው ለምንድን ነው?
በምዕራፎችና በቁጥሮች ተከፋፍሎ የታተመው የመጀመሪያው የተሟላ መጽሐፍ ቅዱስ በ1553 በሮበርት ኤትዬን የተዘጋጀው የፈረንሳይኛ ትርጉም ነው። ይሁን እንጂ የመዝሙር መጽሐፍ በበርካታ ሰዎች የተቀናበሩ የተለያዩ መዝሙራት ስብስብ ስለሆነ የተከፋፈለው ከዚያ ብዙ ዓመታት ቀደም ብሎ ይመስላል።
ይሖዋ ሕዝቡ እርሱን ለማምለክ በአንድነት በሚሰበሰቡበት ወቅት የሚዘምሯቸውን መዝሙሮች አሰባስቦ እንዲያቀናብር በመጀመሪያ ለዳዊት መመሪያ የሰጠው ይመስላል። (1 ዜና መዋዕል 15:16-24) ከጊዜ በኋላ ደግሞ መላውን የመዝሙር መጽሐፍ አሁን ባለው መልኩ ያቀናበረው ካህንና “ፈጣን ጸሐፊ” የነበረው ዕዝራ እንደሆነ ይታመናል። (ዕዝራ 7:6) ስለዚህ የመዝሙር መጽሐፍ መጀመሪያም ቢሆን በተለያዩ መዝሙሮች የተከፋፈለ ነበር።
ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት በአንጾኪያ (ጲስድያ) በሚገኝ ምኩራብ ውስጥ በሰጠው ንግግር ላይ ከመዝሙር መጽሐፍ በመጥቀስ “በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ:- አንተ ልጄ ነህ፣ እኔ ዛሬ ወለድሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ” በማለት ተናግሮ ነበር። (ሥራ 13:33) በዛሬው ጊዜ በሚገኙ መጽሐፍ ቅዱሶች ላይም እነዚህ ቃላት በሁለተኛው መዝሙር ቁጥር 7 ላይ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የመዝሙር መጽሐፍን በቁጥር የከፋፈሉበት መንገድ ልዩነት አለው። ይህ የሆነበት ምክንያት አንዳንዶቹ ትርጉሞች የተዘጋጁት በዕብራይስጥ ከተጻፈው የማሶሬቲክ ቅጂ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ከዕብራይስጥ ተተርጉሞ ከተዘጋጀው የግሪክኛው የሴፕቱጀንት ትርጉም በመሆኑ ነው። ለምሳሌ ያህል በርካታ የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱሶች የተተረጎሙበት የላቲኑ ቩልጌት የመዝሙር መጽሐፍን በቁጥር የከፋፈለበት መንገድ ከሴፕቱጀንት ትርጉም ጋር ተመሳሳይ ሲሆን በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም እና በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ያለው ግን ከዕብራይስጡ ቅጂ የተወሰደ ነው።
ልዩነቶቹ በተጨባጭ ምንድን ናቸው? የዕብራይስጡ ቅጂ 150 የሚያህሉ መዝሙሮች አሉት። የሴፕቱጀንት ትርጉም ግን መዝሙር 9 እና 10ን እንዲሁም መዝሙር 114 እና 115ን በአንድ ላይ ያጣምራቸዋል። ከዚህም በላይ መዝሙር 116ን እና 147ን እያንዳንዳቸውን ሁለት ቦታ ይከፍላቸዋል። አጠቃላይ የመዝሙሮቹ ቁጥር ተመሳሳይ ቢሆንም የሴፕቱጀንት ትርጉም ከ10ኛው መዝሙር እስከ 146ኛው ድረስ ላሉት መዝሙራት የሚሰጠው ቁጥር በዕብራይስጡ ቅጂ ላይ ካለው በአንድ ያንሳል። በዚህም ምክንያት የመዝሙር መጽሐፍን ከላቲኑ ቩልጌት (የተተረጎመው ከሴፕቱጀንት ነው) ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ የከፋፈለው ዱዌይ ቨርሽን በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀውን መዝሙር 23ን 22ኛ አድርጎታል።
በተጨማሪም ለአንዳንድ መዝሙራት ስንኞች የተሰጡት ቁጥሮች በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ልዩነት ይታይባቸዋል። ለምን? ምክንያቱም አንዳንድ ትርጉሞች ‘የአይሁዳውያንን ልማድ በመከተል በመዝሙሩ መግቢያ ላይ ያለውን መግለጫ እንደ መጀመሪያ ቁጥር’ አድርገው ሲወስዱት ሌሎች ግን እንዲህ ስለማያደርጉ ነው በማለት በማክሊንቶክ እና ስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ ይናገራል። እንዲያውም የመግቢያው ሐሳብ ረዘም ያለ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ በሁለት ቁጥሮች ስለሚከፈል የመዝሙሩ ስንኞች ቁጥርም እንዲሁ ይጨምራል።