የጌታ እራት ለአንተ ትልቅ ትርጉም አለው
የጌታ እራት ለአንተ ትልቅ ትርጉም አለው
የጌታ እራት በእርግጥ ለአንተ የጎላ ትርጉም አለውን? የሚያስገኝልህ ዘላቂ ጥቅምስ ይኖር ይሆን? መልሱን ለማግኘት በቅድሚያ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ለዚህ ልዩ በዓል የነበረውን አመለካከት እንመርምር።
በ33 እዘአ ኒሳን 14 ምሽት ላይ ኢየሱስ ዓመታዊውን የማለፍ በዓል ለማክበር ኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ቤት ውስጥ ከ12 ሐዋርያቱ ጋር ተሰበሰበ። ለማለፍ በዓል የተዘጋጀውን ምግብ ከተመገቡ በኋላ ከሃዲው ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ክፍሉን ለቅቆ ወጣ። (ዮሐንስ 13:21, 26-30) በዚህ ወቅት ኢየሱስ ከተቀሩት 11 ሐዋርያቱ ጋር “የጌታ እራት” በዓልን አቋቋመ። (1 ቆሮንቶስ 11:20) ኢየሱስ ተከታዮቹን “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሎ ስላዘዛቸው በዓሉ የመታሰቢያው በዓል ተብሎም ይጠራል። ይህ ክርስቲያኖች እንዲያከብሩት የታዘዙት ብቸኛው በዓል ነው።—1 ቆሮንቶስ 11:24
አንድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት መታሰቢያ የሚለውን ቃል “አንድን የተፈጸመ ድርጊት ወይም የሞተ ሰውን ለማስታወስ የሚደረግ ወይም የሚዘጋጅ ወይም የሚቀመጥ፣ . . . ማንኛውም ነገር” በማለት ይፈታዋል። በብዙ ቦታዎች ሰዎች አንድን ሰው ወይም አንድን ልዩ ክስተት ለማስታወስ ሃውልት ያቆማሉ ወይም አንድ ቀን ይወስናሉ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ በዚያ ጉልህ ሥፍራ በሚሰጠው ቀን የተፈጸሙትን ጥልቅ ትርጉም ያላቸው ክንውኖች እንዲያስታውሱ የሚረዳቸው የመታሰቢያ እራት አዘጋጀ። ከዚያ በኋላ የሚመጡት ትውልዶች በዓሉን በሚያከብሩበት ጊዜ ኢየሱስ በዚያን ዕለት ምሽት ያከናወናቸው ነገሮች በተለይ ደግሞ በበዓሉ ላይ የተጠቀመባቸው ምሳሌዎች ምን ትርጉም እንዳላቸው እንዲያስታውሱ ይረዳቸዋል። ኢየሱስ የተጠቀመባቸው ምሳሌዎች ምንድን ናቸው? ትርጉማቸውስ ምንድን ነው? በ33 እዘአ ምሽት ስለተከናወነው ሁኔታ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንመልከት።
ቅዱስ ምሳሌዎች
“ቂጣውንም አንሥቶ አመሰገነ ቆርሶም ሰጣቸውና:- ይህ ስለ እናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ።”—ሉቃስ 22:19
ኢየሱስ ቂጣውን አንስቶ “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው” ብሎ ሲናገር እርሾ ያልገባበት ቂጣ ‘ስለ ዓለም ሕይወት የሚሰጠውን’ ኃጢአት የሌለበትን ሰብዓዊ አካሉን እንደሚያመለክት መግለጹ ነበር። (ዮሐንስ 6:51) የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ይህንን ጥቅስ “ይህ ሥጋዬ ነው [በግሪክኛ ኤስቲን]” ብለው ቢተረጉሙትም በቴየር የተዘጋጀው ግሪክ-ኢንግሊሽ ሌክሲከን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት ይህ ግስ በአብዛኛው “ማመልከት” የሚል ትርጉም እንዳለው ይገልጻል። ቃሉ አንድን ነገር ለማመልከት የቆመ ምሳሌያዊ መግለጫ የሚል ትርጉም አለው።—ማቴዎስ 26:26 አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከማጥኛ ጽሑፍ ጋር የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት
በተመሳሳይም ወይኑ ምሳሌያዊ ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው።”—ሉቃስ 22:20
በማቴዎስ ዘገባ መሠረት ኢየሱስ ጽዋውን አንስቶ “ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 26:28) ኢየሱስ በጽዋው ውስጥ ያለውን ወይን በምሳሌያዊ ሁኔታ ደሙን ለማመልከት ተጠቅሞበታል። የፈሰሰው ደሙ ከእርሱ ጋር በሰማይ ነገሥታትና ካህናት ሆነው የሚገዙት በመንፈስ የተቀቡት ደቀ መዛሙርት ‘በአዲስ ቃል ኪዳን’ ውስጥ እንዲታቀፉ መሠረት ጥሏል።—ኤርምያስ 31:31-33፤ ዮሐንስ 14:2, 3፤ 2 ቆሮንቶስ 5:5፤ ራእይ 1:4-6፤ 5:9, 10፤ 20:4, 6
ከዚህም በላይ በጽዋው ውስጥ ያለው ወይን የፈሰሰው የኢየሱስ ደም “ለኃጢአት ይቅርታ” እንደሚያስገኝ ለማስታወስ የሚያገለግል ሲሆን ይህም ከወይኑ የሚካፈሉት ሰዎች ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ተባባሪ ወራሾች እንዲሆኑ መንገድ ጠርጎላቸዋል። በመሆኑም በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይኑ የሚካፈሉት ሰማያዊ ጥሪ ያላቸው የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ናቸው።—ሉቃስ 12:32፤ ኤፌሶን 1:13, 14፤ ዕብራውያን 9:22፤ 1 ጴጥሮስ 1:3, 4
በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የማይካተቱት ሌሎቹ የኢየሱስ ተከታዮችስ ተስፋቸው ምንድን ነው? እነዚህ የጌታ “ሌሎች በጎች” ተስፋቸው ከክርስቶስ ጋር በሰማይ መግዛት ሳይሆን ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ነው። (ዮሐንስ 10:16፤ ሉቃስ 23:43፤ ራእይ 21:3, 4) ‘አምላክን ሌሊትና ቀን በመቅደሱ የሚያመልኩትና’ “እጅግ ብዙ ሰዎች” የተባሉት እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች በጌታ እራት በዓል ላይ ተገኝተው በዓሉ ሲከበር የመመልከት መብት በማግኘታቸው ደስተኞች ናቸው። በቃላቸውና በድርጊታቸው “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው” ብለው የሚናገሩ ያህል ነው።—ራእይ 7:9, 10, 14, 15
በዓሉ በዓመት ስንት ጊዜ መከበር ይኖርበታል?
“ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት።”—ሉቃስ 22:19
የክርስቶስን ሞት ለማስታወስ የመታሰቢያው በዓል በዓመት ስንት ጊዜ መከበር አለበት? ኢየሱስ በግልጽ የተናገረው ነገር የለም። ሆኖም ኢየሱስ የጌታ እራትን ያቋቋመው እስራኤላውያን በዓመት አንድ ጊዜ የማለፍ በዓልን በሚያከብሩበት በኒሳን 14 ቀን በመሆኑ የመታሰቢያው በዓልም በየዓመቱ እንዲከበር እንደፈለገ ግልጽ ነው። ልዩነቱ እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነጻ የወጡበትን ቀን በየዓመቱ ያከብሩ የነበረ ሲሆን ክርስቲያኖች ግን ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነጻ የወጡበትን ቀን በየዓመቱ ያከብራሉ።—ዘጸአት 12:11, 17፤ ሮሜ 5:20, 21
ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠውን አንድ ክንውን ለማሰብ በዓመት አንድ ጊዜ የመታሰቢያ በዓል ማክበር አዲስ ነገር አይደለም። ለምሳሌ ያህል አንድ ባልና ሚስት የጋብቻቸውን ቀን የሚያከብሩት በዓመት አንድ ጊዜ ነው፤ በተመሳሳይም አንድ አገር በታሪክ ውስጥ የተፈጸመን አንድ ክስተት ለማስታወስ በዓል የሚያደርገው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አብዛኛውን ጊዜ የመታሰቢያ በዓል የሚደረገው ድርጊቱ በተከናወነበት ዕለት ይኸውም በዓመት አንድ ጊዜ ነው። ክርስቶስ ከሞተ በኋላ በነበሩት በርካታ ዘመናት ኩዋርቶዴሲማንስ ማለትም “የአሥራ አራተኛ ቀን አክባሪዎች” ተብለው የሚጠሩ ክርስቲያኖች ነበሩ። ይህን ስያሜ ያገኙት የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ በየዓመቱ ኒሳን 14 ዕለት ያከብሩ ስለነበር ነው።
ቀለል ያለ ሆኖም ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ በዓል
ሐዋርያው ጳውሎስ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የጌታ እራትን ማክበራቸው ‘ሞቱን መናገራቸውን እንዲቀጥሉ’ እንደሚረዳቸው ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 11:26) በዚህም ምክንያት ይህ የመታሰቢያ በዓል የኢየሱስ ሞት በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ውስጥ በተጫወተው ከፍተኛ ሚና ላይ ያተኮረ ይሆናል።
ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ሞት ድረስ ባሳየው የታማኝነት አቋም ይሖዋ አምላክ ጥበበኛና አፍቃሪ ፈጣሪ እንዲሁም ጻድቅ ሉዓላዊ ገዢ መሆኑን አረጋግጧል። ኢየሱስ የሰው ልጆች በጣም ከባድ መከራ ቢደርስባቸውም እንኳን ለአምላክ ታማኝ ሆነው መኖር እንደሚችሉ ከአዳም በተለየ መንገድ በማረጋገጥ ሰይጣን ያስነሳውን ክስ ውድቅ አድርጎታል።—ኢዮብ 2:4, 5
የጌታ እራት ኢየሱስ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ያሳየንን ፍቅር እንድናደንቅም ይገፋፋናል። ኢየሱስ ከባድ ፈተናዎች ቢደርሱበትም እስከ መጨረሻው አባቱን ታዝዟል። በመሆኑም ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት የአዳም ኃጢአት ያስከተለውን ከፍተኛ ኪሣራ አካክሷል። ኢየሱስ ራሱ እንደተናገረው ወደ ምድር የመጣው ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ’ ነው። (ማቴዎስ 20:28) በዚህም ምክንያት በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ ኃጢአታቸው ይቅር ሊባልላቸውና ይሖዋ ለሰው ልጆች ከነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ጋር በሚስማማ መልኩ የዘላለም ሕይወት ሊያገኙ ይችላሉ።—ሮሜ 5:6, 8, 12, 18, 19፤ 6:23፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6 a
ይህ ሁሉ ይሖዋ የሰውን ዘር ለማዳን ሲል ያሳየውን ወሰን የሌለው ጥሩነቱንና ይገባናል የማንለውን ደግነቱን የሚያሳይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፣ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።”—1 ዮሐንስ 4:9, 10
በእርግጥም የመታሰቢያው በዓል ምንኛ ታላቅ በዓል ነው! በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር ለማክበር የሚያመችና ቀለል ያለ ሆኖም የበዓሉን ትርጉም በማይረሳ መንገድ ለማስታወስ የሚረዳ ነው።
ለአንተ የሚኖረው ትርጉም
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ለእሱም ሆነ ለአባቱ ለይሖዋ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ጠይቆባቸዋል። ኢየሱስ ሮሜ 5:12፤ ዕብራውያን 7:26) ለዘላለም መኖር ይችል ነበር። ያለ ፈቃዱ፣ በኃይልም እንኳን ቢሆን ሕይወቱን ሊነጥቀው የሚችል አልነበረም። ኢየሱስ “ሕይወቴን በራሴ ፈቃድ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 10:18 አ.መ.ት
ፍጹም ሰው ስለነበር እንደኛ ሞትን አልወረሰም። (ያም ሆኖ ግን ኢየሱስ “እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፣ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፣ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ” ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን በራሱ ፈቃድ መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል። (ዕብራውያን 2:14, 15) ክርስቶስ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ፍቅር ያሳየበት ሌላው መንገድ የሞተበት ሁኔታ ነው። ምን ዓይነት ሥቃይ እንደሚደርስበትና እንዴት እንደሚሞት አሳምሮ ያውቅ ነበር።—ማቴዎስ 17:22፤ 20:17-19
የመታሰቢያው በዓል ሰማያዊው አባታችን ይሖዋ ያሳየንን ከሁሉ የላቀ ፍቅርም ያስታውሰናል። “ርኅሩኅና መሓሪ” የሆነው ይሖዋ በጌተሰማኒ የአትክልት ቦታ ልጁ ከእንባ ጋር ያቀረበውን ‘ብርቱ ጩኸት’ ሲሰማ፣ ከዚያም ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ሲገረፍ፣ ሲሰቀልና ተሠቃይቶ ሲገደል ሲመለከት ምንኛ አዝኖ ይሆን። (ያዕቆብ 5:11 አ.መ.ት፤ ዕብራውያን 5:7፤ ዮሐንስ 3:16፤ 1 ዮሐንስ 4:7, 8) ይህ ሁኔታ ከተፈጸመ በርካታ መቶ ዘመናት ያለፉ ቢሆንም ስለሁኔታው ማሰቡ ብቻ እንኳን ብዙዎችን በጣም ይረብሻቸዋል።
ይሖዋ አምላክ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኛ ለሆንነው ለእኛ የከፈሉት መሥዋዕት ምንኛ ታላቅ ነው! (ሮሜ 3:23) የወረስነው የኃጢአተኝነት ዝንባሌና አለፍጽምና የሚያስከትሉብንን መራራ ሐቅ በየዕለቱ እንጋፈጣለን። ይሁን እንጂ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ካሳደርን አምላክ ይቅር እንዲለን ልንጠይቀው እንችላለን። (1 ዮሐንስ 2:1, 2) የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ከአምላክ ጋር በነጻነት እንድንነጋገርና ንጹህ ሕሊና እንድናገኝ ያስችለናል። (ዕብራውያን 4:14-16፤ 9:13, 14) ከዚህም በላይ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋም አለን። (ዮሐንስ 17:3፤ ራእይ 21:3, 4) እነዚህንና ሌሎች ብዙ በረከቶችን ማግኘት የቻልነው ኢየሱስ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ በማሳየቱ ነው።
ለጌታ እራት አድናቆት ማሳየት
የጌታ እራት “ከሁሉ የላቀው ይገባናል የማንለው የአምላክ ደግነት” ድንቅ መግለጫ መሆኑ ምንም አያጠራጥርም። ይሖዋ አምላክ ቤዛዊ መሥዋዕት ለማቅረብ ያደረገው ዝግጅት ‘በቃላት ሊገለጽ የማይቻል ነጻ ስጦታ’ ሲሆን ኢየሱስ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ያሳየው ፍቅር ለዚህ ዝግጅት መሳካት አስተዋጽኦ አድርጓል። (2 ቆሮንቶስ 9:14, 15 NW ) አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያሳየን ይህ ጥሩነት በውስጥህ ጥልቅ የሆነ የአመስጋኝነትና የአድናቆት ስሜት እንዲሰማህ አያደርግህም?
እንዲህ ያለ ስሜት እንደሚፈጥርብህ አያጠራጥርም። እንግዲያው የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ በዓል ለማክበር በሚሰበሰቡበት ጊዜ አብረሃቸው እንድትገኝ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልሃለን። በዚህ ዓመት የመታሰቢያው በዓል የሚከበረው ረቡዕ፣ ሚያዝያ 16 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ይሆናል። በአካባቢህ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ይህ በጣም አስፈላጊ በዓል የሚከበርበትን ሰዓትና ቦታ በደስታ ይነግሩሃል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ቤዛውን በተመለከተ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።
[በገጽ 5, 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
“ይህ ሥጋዬ ነው” ወይስ “ይህ ማለት ሥጋዬ ነው”?
ኢየሱስ “እኔ የበጎች በር ነኝ” ወይም “እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ” ብሎ ሲናገር ቃል በቃል በር ወይም የወይን ግንድ ነው ብለን አናስብም። (ዮሐንስ 10:7፤ 15:1) በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስ “ይህ ጽዋ . . . አዲስ ኪዳን ነው” ሲል ጽዋው ራሱ ቃል በቃል አዲስ ኪዳን እንደሆነ አድርገን አናስብም። ልክ እንደዚያው ሁሉ ኢየሱስ ቂጣው ሥጋው ‘እንደሆነ’ ሲናገር ቂጣው ሥጋውን እንደሚያመለክት መናገሩ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም በቻርልስ ቢ ዊሊያምስ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሱን “ይህ ሥጋዬን ያመለክታል” በማለት ተርጉሞታል።—ሉቃስ 22:19, 20
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ያልቦካው ቂጣና ወይን ጠጁ ኃጢአት የሌለበትን የኢየሱስን ሥጋና የፈሰሰውን ደሙን የሚያመለክቱ ተስማሚ ምሳሌዎች ናቸው
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመታሰቢያው በዓል ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳዩንን ታላቅ ፍቅር ያስታውሰናል