በፊትና አሁን—ከጨለመ ሕይወት ወደ ብሩህ ተስፋ
“ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ ወደ እናንተም ይቀርባል”
በፊትና አሁን—ከጨለመ ሕይወት ወደ ብሩህ ተስፋ
ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክ ቃል ስላለው ልብን የመንካት ኃይል ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም፣ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፣ . . . የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል።” (ዕብራውያን 4:12) የአምላክ ቃል የሰዎችን ልብ የመንካት ኃይል እንዳለው በመጀመሪያው መቶ ዘመን በተግባር ታይቷል። ክርስትናን የተቀበሉ ሰዎች በወቅቱ የነበረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ተቋቁመው አዲሱን ሰው ለብሰዋል።—ሮሜ 1:28, 29፤ ቆላስይስ 3:8-10
የአምላክ ቃል ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎችን የመለወጥ ኃይል ያለው መሆኑ በዛሬው ጊዜም በግልጽ ይታያል። ለምሳሌ ያህል፣ ለግላጋ ቁመናና ፈርጠም ያለ ሰውነት ያለውን ሪቻርድን ተመልከት። በትንሽ በትልቁ ግልፍ የሚለው ሪቻርድ ብዙ ጊዜ ከሰዎች ጋር ይደባደባል። ሕይወቱ በሙሉ በጠብ የተሞላ ነበር። እንዲያውም የቦክስ ክበብ አባል ሆነና ከብዙ ልምምድ በኋላ በዌስትፋሊያ፣ ጀርመን የከባድ ሚዛን ቦክስ ሻምፒዮን ለመሆን በቃ። ሪቻርድ ከመጠን በላይ ይጠጣ የነበረ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ብጥብጥ ውስጥ ይገባ ነበር። አንድ ወቅት በእንዲህ ዓይነት ብጥብጥ ላይ ሰው በመገደሉ ሪቻርድ በነፍስ ማጥፋት ተወንጅሎ ወኅኒ ቤት ከመግባት ያመለጠው ለጥቂት ነበር።
ትዳሩስ ምን ይመስል ነበር? “እኔና ሄይከ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ከመጀመራችን በፊት የደባል ሕይወት እንኖር ነበር። ሄይከ አብዛኛውን ጊዜዋን ከሴት ጓደኞቿ ጋር ስታሳልፍ እኔ ደግሞ ቦክስ በመለማመድ፣ በውኃ ላይ በመንሸራተትና በጠላቂ ዋናተኛነት ጊዜዬን አሳልፍ ነበር።”
ሪቻርድና ሄይከ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምሩ፣ ሪቻርድ ሕይወቱን በአምላክ ቃል ውስጥ ከሰፈሩት የላቁ የሥነ ምግባር ደረጃዎች ጋር ለማስማማት በአኗኗሩ ላይ ለውጥ ማድረግ ፈጽሞ የማይቻል እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋን ይበልጥ እያወቀው ሲሄድ እርሱን የማስደሰት ከፍተኛ ፍላጎት አደረበት። ዓመፅን የሚወዱ ወይም ለመዝናናት ብለው በዓመፅ ድርጊቶች የሚካፈሉ ሰዎች የአምላክን ሞገስ እንደማያገኙ ተገነዘበ። እንዲሁም ‘ዓመፃን የሚወድዱትን ይሖዋ እንደሚጠላ’ ተማረ።—መዝሙር 11:5
ከዚህም በላይ ሪቻርድም ሆነ ሄይከ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዳለ ሲሰሙ በጣም ተደሰቱ። አብረው በዚያ የመኖር ፍላጎት አደረባቸው። (ኢሳይያስ 65:21-23) “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” የሚለው ግብዣ ሪቻርድን በጥልቅ ነካው። (ያዕቆብ 4:8) “በግፈኛ [“በዓመፀኛ፣” NW ] ሰው አትቅና፣ መንገዱንም ሁሉ አትምረጥ። ጠማማ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ርኩስ ነውና፤ ወዳጅነቱ ግን ከቅኖች ጋር ነው” የሚለውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ምክር መከተል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተገነዘበ።—ምሳሌ 3:31, 32
ሪቻርድ አኗኗሩን የመለወጥ ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖረውም በራሱ ጥረት ብቻ እንዲህ ማድረግ እንደማይችል ተሰማው። አምላክ እንዲረዳው በጸሎት መጠየቅ ያለውን አስፈላጊነት አስተዋለ። በመሆኑም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው” በማለት የሰጣቸውን ምክር ተግባራዊ አደረገ።—ማቴዎስ 26:41
ሪቻርድ አምላክ ለዓመፅና ለቁጣ ያለውን አመለካከት ካወቀ በኋላ ቦክስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ስፖርት መሆኑን ለመቀበል አላንገራገረም። በይሖዋ እርዳታና
ከአስጠኚዎቹ ባገኘው ማበረታቻ የዓመፀኝነት ባሕርይውን እርግፍ አድርጎ ተወ። ቦክሰኛነቱንና በብጥብጥ መካፈሉን ያቆመ ሲሆን የቤተሰብ ሕይወቱን ለማሻሻል ቆርጦ ተነሳ። አሁን በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ በበላይ ተመልካችነት የሚያገለግለው የዋሁ ሪቻርድ እንዲህ ይላል:- “የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማሬ ማንኛውንም ነገር ከማድረጌ በፊት ቆም ብዬ እንዳስብ ረድቶኛል። ባለቤቴንና ልጆቼን የምይዛቸው በፍቅርና በአክብሮት ነው። ይህም በጣም አቀራርቦናል።”ስለ እኛ የተሳሳተ ግንዛቤ ያላቸው አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብን እንደሚከፋፍሉ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ እንደ ሪቻርድ ያሉ ሰዎች ተሞክሮ ይህ አባባል ሐሰት መሆኑን ያረጋግጣል። እንደ እውነቱ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ተስፋ አስቆራጭ ሕይወት ይመሩ የነበሩ ሰዎች የተረጋጋ የቤተሰብ ሕይወትና ብሩህ የወደፊት ተስፋ እንዲኖራቸው ያደርጋል።—ኤርምያስ 29:11
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር ተስፋ በሕይወቴ ላይ ለውጥ እንዳደርግ አነሳስቶኛል”
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያላቸው ኃይል
መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል አለው። ዓመፀኛ የነበሩ ሰዎች የባሕርይ ለውጥ እንዲያደርጉ የረዷቸው አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እስቲ እንመልከት።
“ትዕግሥተኛ ሰው ከኃያል ሰው ይሻላል፣ በመንፈሱም ላይ የሚገዛ ከተማ ከሚወስድ ይበልጣል።” (ምሳሌ 16:32) በቁጣ መገንፈል የድክመት እንጂ የኃያልነት ምልክት አይደለም።
“ሰውን ጠቢብ አእምሮው ከቍጣ ያዘገየዋል።” (ምሳሌ 19:11) አንድ ሰው ለቁጣ ከመቸኮሉ በፊት ስለ አንድ ጉዳይ ጥሩ ማስተዋል ወይም የተሟላ ግንዛቤ ማግኘቱ ግጭት ውስጥ እንዳይገባ ይረዳዋል።
“ከቍጡ ሰው ጋር ባልንጀራ አትሁን፣ . . . መንገዱን እንዳትማር።” (ምሳሌ 22:24, 25) ክርስቲያኖች ግልፍተኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር ወዳጅነት ላለመመሥረት ጥንቃቄ ያደርጋሉ።