ወደር የማይገኝለት ደስታ!
የሕይወት ታሪክ
ወደር የማይገኝለት ደስታ!
ሬጅናልድ ዎልዎርክ እንደተናገረው
“በዚህ ዓለም ላይ በሚስዮናዊነት ይሖዋን በማገልገል ካገኘነው ደስታ ጋር የሚተካከል አንዳች ነገር ሊኖር አይችልም!” ይህን እንደነገሩ ጫር ጫር የተደረገ ማስታወሻ ያገኘሁት ባለቤቴ ግንቦት 1994 ከሞተች ከጥቂት ጊዜ በኋላ የግል ማስታወሻዎቿን ሳገላብጥ ነበር።
እነዚህ የአይሪን ቃላት ፔሩ ውስጥ በሚስዮናዊነት ያገለገልንባቸውን 37 አስደሳች ዓመታት አስታወሱኝ። እኔና አይሪን በታኅሣሥ ወር 1942 ከተጋባንበት ጊዜ አንስቶ በክርስቲያናዊ አገልግሎት በእርካታ የተሞላ ሕይወት አሳልፈናል። እንዲያውም ታሪኬን ከአይሪን ጋር እንዴት እንደተጋባን በመተረክ ብጀምር ሳይሻል አይቀርም።
እንግሊዝ ውስጥ በሊቨርፑል ከተማ የተወለደችው አይሪን ያደገችው በይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ውስጥ ነበር። ሁለት እህቶች የነበሯት ሲሆን አባቷ የሞተው በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነው። እናቷ የኋላ ኋላ ዊንተን ፍሬዘር የተባለ ሰው አገባችና ሲድኒ የሚባል ልጅ ወለዱ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ትንሽ ቀደም ብሎ ቤተሰባቸው ወደ ኖርዝ ዌልስ፣ ባንጎር ከተማ የተዛወረ ሲሆን እዚያ እያሉ በ1939 አይሪን ተጠመቀች። ሲድኒ ከአንድ ዓመት ቀደም ብሎ ተጠምቆ ስለነበር ሁለቱም የኤንጅልሲ ደሴትን ጨምሮ ከባንጎር እስከ ካርናርቨን ድረስ ያለውን አካባቢ በሚሸፍነው የዌልስ ሰሜናዊ ጠረፍ በሙሉ ጊዜ ወንጌላዊነት ማገልገል ጀመሩ።
በዚያን ጊዜ እኔ ከሊቨርፑል በስተ ደቡብ ምሥራቅ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ረንከርን ጉባኤ ውስጥ አሁን ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች በሚባለው የኃላፊነት ቦታ አገለግል ነበር። በአንድ የወረዳ ስብሰባ ላይ አይሪን ወደ እኔ መጣችና በረንከርን ከምትኖረው ቪራ የተባለች ባለትዳር እህቷ ጋር ለተወሰነ ጊዜ ለመቆየት ስላሰበች የአገልግሎት ክልል ማግኘት ትችል እንደሆነ ጠየቀችኝ። አብራን በቆየችባቸው ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከአይሪን ጋር በጣም የተግባባን ሲሆን ወደ ባንጎር ከተመለሰች በኋላም እዚያ ድረስ እየሄድኩ እጠይቃት ነበር። አንድ ቅዳሜና እሁድ
በዚያ ሳለሁ እንድንጋባ ጠየቅኋትና እንደምትስማማ ስትነግረኝ ምን ያህል እንደተደሰትኩ ልትገምቱ ትችላላችሁ!እሁድ ዕለት ወደ ቤት ተመለስኩና ለሠርጋችን እቅድ ማውጣት ጀመርኩ። ይሁን እንጂ ማክሰኞ የሚከተለው ቴሌግራም ደረሰኝ። “ይህን ቴሌግራም ስታነብ ስሜትህ ሊጎዳ እንደሚችል ይሰማኛል። በጣም አዝናለሁ። ሠርጋችን ተሰርዟል። ደብዳቤ በቅርቡ ይደርስሃል።” በጣም ደነገጥኩ። ምን ችግር ተፈጥሮ ይሆን?
በማግስቱ ደብዳቤው ደረሰኝ። ከሂልዳ ፓጄት ጋር አቅኚ ሆና ለማገልገል ወደ ዮርክሻየር፣ ሆርስፎርዝ ልትሄድ መሆኑን ነገረችኝ። a ከአንድ ዓመት ቀደም ብሎ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ እንድታገለግል ግብዣ ከቀረበላት በፈቃደኝነት ለመሄድ ተስማምታ እንደነበር ገለጸችልኝ። አክላም “ይህን ለይሖዋ እንደተሳልኩት ስዕለት አድርጌ እመለከተው ነበር። ይህን ቃል የገባሁት አንተን ከማወቄ በፊት ስለሆነ ቃሌን መጠበቅ እንደሚኖርብኝ ይሰማኛል” በማለት ጻፈች። ሁኔታው ቢያሳዝነኝም የገባችውን ቃል ለመፈጸም ያላት ቁርጠኝነት አስደነቀኝ። “ሂጂ፣ እጠብቅሻለሁ” የሚል ቴሌግራም ላክሁላት።
አይሪን ዮርክሻየር ሳለች በሕሊናዋ ምክንያት በወቅቱ የነበረውን ጦርነት ለመደገፍ ፈቃደኛ ስላልሆነች የሦስት ወር እስራት ተፈረደባት። ሆኖም ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ በታኅሣሥ 1942 ተጋባን።
የልጅነት ሕይወቴ
በ1919 እናቴ የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት (እንግሊዝኛ) የተባሉ ጥራዞችን ገዛች። b አባቴ በወቅቱ እንደተናገረው እናቴ ከዚያ በፊት አንድም መጽሐፍ አንብባ የማታውቅ ቢሆንም እነዚህን ጥራዞች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እያመሳከረች ለማንበብ ቁርጥ ውሳኔ አድርጋ ነበር። መጽሐፎቹን በደንብ ከመረመረች በኋላ በ1920 ተጠመቀች።
እናታችን የፈለገችውን ነገር እንድታደርግ አባታችን ነፃነት ይሰጣት ነበር። በመሆኑም እኔን፣ ወንድሜን አሌክን እንዲሁም ግዌን እና አይቪ የተባሉ እህቶቼን በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ኮትኩታ ለማሳደግ የምታደርገውን ጥረት አይቃወምም ነበር። ስታንሊ ሮጀርስና በሊቨርፑል የሚኖሩ ሌሎች ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ረንከርን እየመጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮች ይሰጡን የነበረ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ አዲስ ጉባኤ ተቋቋመ። ቤተሰባችንም ከጉባኤው ጋር በመንፈሳዊ ማደጉን ቀጠለ።
ግዌን የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን የአባልነት ማረጋገጫ ትምህርት ትከታተል የነበረ ቢሆንም ከእናታችን ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስትጀምር አቆመች። የቤተ ክርስቲያኑ ቄስ ለምን እንደቀረች ለመጠየቅ ቤታችን ሲመጣ ፈጽሞ ያልተዘጋጀባቸውን ጥያቄዎች አዥጎደጎድንበት። ግዌን የጌታ ጸሎት ምን ትርጉም እንዳለው ጠየቀችውና ራሷ ታብራራለት ጀመር። በመጨረሻም 1 ቆሮንቶስ 10:21ን ጠቅሳ ከዚህ በኋላ ‘ከሁለት ማዕድ መካፈል’ እንደማትፈልግ ገለጸችለት። ቄሱ ለግዌን እንደሚጸልይላትና በሌላ ጊዜ መጥቶ ጥያቄዎቿን እንደሚመልስላት ተናግሮ ወጥቶ ሄደ። ሆኖም ከዚያ በኋላ ቤታችንን ረግጦ አያውቅም። ግዌን ከተጠመቀች በኋላ ብዙም ሳይቆይ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆነች።
በጉባኤያችን ለትናንሽ ልጆች ይሰጥ የነበረው ትኩረት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው። የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ ሊጎበኘን የመጣ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ንግግር እንዳቀረበልን በደንብ አስታውሳለሁ። ከንግግሩ በኋላ ወደ እኔ መጥቶ አነጋገረኝ። አብርሃም ልጁን ይስሃቅን መስዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ተፈትኖ እንደነበር የሚናገረውን ታሪክ እንዳነበብኩ ነገርኩት። “በል እዚያ መድረኩ ጫፍ ላይ ቁምና ታሪኩን አንድ በአንድ ንገረኝ” አለኝ። መድረኩ ላይ ቆሜ የመጀመሪያውን “የሕዝብ ንግግሬን” ለማቅረብ በመቻሌ ምን ያህል እንደተደሰትኩ መገመት አያዳግታችሁም!
በ1931 በ15 ዓመቴ የተጠመቅሁ ሲሆን እናቴም የሞተችው በዚያው ዓመት ነበር። ከዚያም ትምህርቴን አቋረጥኩና ተለማማጅ የኤሌክትሪክ ሠራተኛ ሆንኩ። በ1936 በሸክላ የተቀዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን ለሕዝብ በማሰማት ምሥራቹ ይሰበክ ነበር። አንዲት አረጋዊት እህት እኔንና ወንድሜን በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ እንድንካፈል አበረታቱን። በዚህም ምክንያት እኔና አሌክ ወደ ሊቨርፑል ሄደን ብስክሌት ገዛንና የሸክላ ማጫወቻችንን የምንይዝበት ተጎታች ጋሪ አሠራንለት። በጋሪው የኋለኛ ክፍል 2 ሜትር ቁመት ባለው ተጣጣፊ ዘንግ ላይ የድምፅ ማጉያ አስገጠምን። መካኒኩ እንደዚህ ያለ ነገር ፈጽሞ ሠርቶ የማያውቅ
ቢሆንም የተዋጣለት ሥራ ነበር። እኛም አረጋዊቷ እህት ለሰጡን ማበረታቻና ላገኘነው የአገልግሎት መብት አመስጋኝ በመሆን ክልላችንን በቅንዓት ሸፈንን።ሁለተኛው የዓለም ጦርነት—የፈተና ወቅት
የጦርነት ዳመና እያንዣበበ ሲመጣ እኔና ስታንሊ ሮጀርስ በመስከረም 11, 1938 በለንደን የሮያል አልበርትስ አዳራሽ “እውነታዎቹን መቀበል” በሚል ርዕስ ሊሰጥ የታቀደውን የሕዝብ ንግግር በማስተዋወቁ ሥራ ተጠምደን ነበር። ከዚያም በቡክሌት የተዘጋጀውን ይህንን ንግግርና በቀጣዩ ዓመት የወጣውን ፋሺዝም ወይስ ነጻነት የተሰኘ ቡክሌት በማሰራጨቱ ሥራ ተካፈልኩ። ሁለቱም ቡክሌቶች በሂትለር የምትመራው ጀርመን የምታራምደውን አምባገነናዊ አገዛዝ የሚያጋልጡ ነበሩ። በዚህ ወቅት በአገልግሎት ንቁ ተሳትፎ አደርግ ስለነበር በረንከርን ውስጥ በብዙዎች ዘንድ የታወቅሁና የተከበርኩ ሆኜ ነበር። በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴ በግንባር ቀደምትነት የማደርገው ተሳትፎ በመጪዎቹ ዓመታት በእጅጉ ጠቅሞኛል።
የምሠራበት መሥሪያ ቤት በከተማይቱ ዳርቻ ላይ ለሚገኝ አንድ አዲስ ፋብሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመቀጠል ተዋውሎ ነበር። ፋብሪካው የጦር መሣሪያ ማምረቻ መሆኑን ስረዳ በዚያ የማልሠራ መሆኔን በግልጽ አሳወቅኋቸው። ቀጣሪዎቼ በውሳኔዬ ደስ ባይሰኙም የቅርብ አለቃዬ ሐሳቤን ደግፎ ስለተከራከረልኝ ሌላ ሥራ ተሰጠኝ። ከጊዜ በኋላ እንደተረዳሁት ይህ ሰው የይሖዋ ምሥክር የሆነች አክስት ነበረችው።
አንድ የሥራ ባልደረባዬ “ሬጅ ለብዙ ዓመታት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች ስትሰብክ ስለነበር እንዲህ ያለ ውሳኔ እንደምትወስን እርግጠኞች ነበርን” ሲል አበረታታኝ። የሆነ ሆኖ አብዛኛዎቹ የሥራ ባልደረቦቼ ችግር ሊፈጥሩብኝ ይሞክሩ ስለነበር ጥንቃቄ ማድረግ አስፈልጎኝ ነበር።
ሕሊናዬ ስለማይፈቅድልኝ በጦርነት ላለመካፈል ያቀረብኩትን ጥያቄ የሊቨርፑል ፍርድ ቤት በሰኔ 1940 ተቀብሎ የኤሌክትሪክ ሠራተኛነቴን እስካላቋረጥኩ ድረስ ከወታደራዊ ግዳጆች ነጻ እንድሆን ፈረደልኝ። ይህም በክርስቲያናዊ አገልግሎቴ እንድቀጥል አስችሎኛል።
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መጀመር
ጦርነቱ ሲጠናቀቅ ሥራዬን ትቼ ከአይሪን ጋር የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ወሰንኩ። በ1946 5 ሜትር ርዝመት ያለው ተጎታች ቤት ሠራሁና በዚያ ውስጥ መኖር ጀመርን። በቀጣዩ ዓመት በግሎክስተርሻየር ወደሚገኝ አልቨስተን የሚባል መንደር ተዛወርን። ከጊዜ በኋላም ሲረንሴስተር በምትባል ጥንታዊ ከተማና በባዝ አገልግለናል። በ1951 ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ በደቡባዊ ዌልስ የሚገኙትን ጉባኤዎች እንድጎበኝ ተጋበዝኩ። ይሁን እንጂ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ ማገልገል ከጀመርኩ ሁለት ዓመት እንኳን ሳይሞላኝ በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ለሚስዮናዊነት እንድንሠለጥን ተጋበዝን።
እኛ የነበርንበት 21ኛው ክፍል የተካሄደው በሰሜናዊ ኒው ዮርክ፣ በሳውዝ ላንሲንግ ሲሆን በ1953 ኒው ዮርክ ውስጥ በተደረገው የአዲሲቱ ዓለም ማኅበረሰብ ስብሰባ ላይ
ተመረቅን። እኔና አይሪን እስከምረቃው ዕለት ድረስ ምድብ ቦታችንን አናውቅም ነበር። ፔሩ እንደተመደብን ስንሰማ በጣም ተደሰትን። ምክንያቱም ሲድኒ ፍሬዘር የተባለው የአይሪን ወንድምና ባለቤቱ ማርጋሬት በጊልያድ ትምህርት ቤት ከ19ኛው ክፍል ከተመረቁ በኋላ ፔሩ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ለአንድ ዓመት ያህል ሲያገለግሉ ቆይተው ነበር።የይለፍ ፈቃድ እስክናገኝ ድረስ በብሩክሊን ቤቴል ውስጥ ለአጭር ጊዜ ከሠራን በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወደ ሊማ ሄድን። በፔሩ ካገለገልንባቸው አሥር ቦታዎች ውስጥ የመጀመሪያው ከሊማ በስተ ምዕራብ የሚገኘው የፔሩ ዋነኛ የወደብ ከተማ ካያኦ ነበር። ምንም እንኳን ስለ ስፓንኛ መሠረታዊ ነገሮችን ተምረን የነበረ ቢሆንም እኔም ሆንኩ አይሪን ቋንቋውን አጥርተን መናገር አንችልም ነበር። ታዲያ የስብከቱን ሥራችንን እንዴት ማከናወን እንችላለን?
በስብከቱ ሥራ ያጋጠሙን ችግሮችና ያገኘናቸው መብቶች
በጊልያድ ሳለን አንዲት እናት ለልጅዋ ቋንቋ እንደማታስተምረው ተነግሮን ነበር። ልጁ ቋንቋውን የሚማረው እናቱ ስታወራ እያዳመጠ ነው። ስለሆነም “እዚያ እንደደረሳችሁ ወዲያው የስብከቱን ሥራችሁን ጀምሩ፤ ቋንቋውን ከሕዝቡ ትማራላችሁ። እነርሱም ይረዷችኋል” የሚል ምክር ተሰጥቶን ነበር። ይህን አዲስ ቋንቋ ለመልመድ ጥረት እያደረግሁ ሳለ እዚያ በደረስን በሁለተኛው ሳምንት ላይ የካያኦ ጉባኤ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ሆኜ ስሾም ምን እንደተሰማኝ መገመት ትችላላችሁ! ሲድኒ ፍሬዘርን ሄጄ አነጋገርኩት። የእርሱም ምክር በጊልያድ ከተነገረን የተለየ አልነበረም። ከጉባኤውና በአገልግሎት ክልሌ ውስጥ ከሚገኙት ሰዎች ጋር እንድቀራረብ መከረኝ። ምክሩን በሥራ ላይ ለማዋል ቆርጬ ተነሳሁ።
አንድ ቅዳሜ ጠዋት እያገለገልኩ ሳለ አንድን አናጺ በሱቁ ውስጥ አነጋገርኩት። “ሥራዬን ማቋረጥ አልችልም። ግን ቁጭ በልና የምትነግረኝን አዳምጣለሁ” አለኝ። ይህን የማደርገው በአንድ ነገር የሚስማማ ከሆነ ብቻ እንደሆነ ነገርኩት። “ቋንቋውን ከተሳሳትኩ ዝም ብለህ አትለፈኝ። ብታርመኝ ምንም ቅር አልሰኝም” አልኩት። ሳቀና በሐሳቤ መስማማቱን ገለጸልኝ። በሳምንት ሁለቴ እየሄድኩ አነጋግረው የነበረ ሲሆን ከዚህ ቀደም እንደተነገረኝ አዲስ ቋንቋ ለመማር ከዚህ የተሻለ ዘዴ እንደሌለ ተገነዘብኩ።
አጋጣሚ ሆኖ በሁለተኛው የአገልግሎት ምድቤ በኢካ ሌላ አናጺ አገኘሁና በካያኦ በነበርኩበት ወቅት ቋንቋዬን ለማሻሻል አንድ አናጺ እንዴት ይረዳኝ እንደነበር ነገርኩት። እሱም እንዲሁ ሊረዳኝ የተስማማ ሲሆን ስፓንኛን አቀላጥፌ ለመናገር ተጨማሪ ሦስት ዓመታት ቢወስድብኝም መሻሻል እንዳደርግ በእጅጉ ረድቶኛል። ይህ አናጺ ሥራ ይበዛበት ነበር። ቢሆንም ጥቅሶችን እያነበብኩና ትርጉማቸውን እያብራራሁለት መጽሐፍ ቅዱስን አስጠናው ነበር። አንድ ቀን ላስጠናው ስሄድ ሌላ ሥራ ፍለጋ ወደ ሊማ መሄዱን አሠሪው ነገረኝ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እኔና አይሪን በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ ሊማ ስንሄድ ይሄን ሰውዬ አገኘነው። በአካባቢው የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን ፈልጎ አግኝቶ ጥናቱን እንደቀጠለና እሱም ሆነ ቤተሰቡ ራሳቸውን ለይሖዋ እንደወሰኑ ስሰማ በጣም ተደሰትኩ።
በአንድ ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ወጣቶች የተጠመቁት ጋብቻቸውን ሕጋዊ ሳያደርጉ መሆኑን አወቅን። ከጉዳዩ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ካወያየናቸው በኋላ የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ለመሆን እንዲችሉ ጋብቻቸውን ሕጋዊ ለማድረግ ወሰኑ። ስለዚህ ማዘጋጃ ቤት ሄደን ጋብቻቸውን ለማስመዝገብ ዝግጅት አደረግን። ይሁን እንጂ አንድ ችግር ተፈጠረ። የነበሯቸው አራት ልጆች ሕጉ በሚጠይቀው መሠረት አልተመዘገቡም። የከተማው ከንቲባ ምን ቅጣት ይወስኑባቸው ይሆን ብለን አሰብን። ከንቲባው እንዲህ አሏቸው:- “ጋብቻችሁን ሕጋዊ እንድታደርጉ ሁኔታውን ያመቻቹላችሁ እነዚህ መልካም ባሕርይ ያላቸው የይሖዋ ምሥክር ወዳጆቻችሁ በመሆናቸው በእያንዳንዱ ልጅ መክፈል የነበረባችሁን ቅጣት ትቼላችኋለሁ። ልጆቹም በነጻ እንዲመዘገቡ ፈቅጄላቸዋለሁ።” የቤተሰቡ የኑሮ ደረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ ቅጣቱን መክፈል ይከብዳቸው ስለነበር ቅጣቱ በመቅረቱ በጣም ተደሰትን።
ከጊዜ በኋላ ብሩክሊን ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ወንድም አልበርት ሽሮደር የጎበኘን ሲሆን ሊማ ውስጥ በሌላ አካባቢ አዲስ የሚስዮናውያን ቤት እንዲከፈት ሐሳብ አቀረበ። ስለዚህ እኔና አይሪን፣ ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡ ፍራንሲስና ኤልዛቤት ጉድ የተባሉ እህትማማቾችና ከካናዳ የመጡ ባልና ሚስት ወደ ሳን ቦርሃ ክፍለ ከተማ ተዛወርን። ሁለት ወይም ሦስት ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ በዚያ ጉባኤ በመቋቋሙ ጥረታችን ተባርኳል።
በ3, 000 ሜትር ከፍታ ላይ በሚገኘው የዋንኪዮ ከተማ ባገለገልንበት ወቅት 80 የሚያህሉ አስፋፊዎች ባሉበት ጉባኤ ውስጥ እንሰበሰብ ነበር። በአገሪቱ ውስጥ ሁለተኛው የመንግሥት አዳራሽ በዚህ አካባቢ ሲገነባ በሥራው ላይ ተሳትፎ አድርጌያለሁ። ለአዳራሹ መሥሪያ ለገዛነው መሬት ሕጋዊ ባለመብት መሆናችንን ለማረጋገጥ ፍርድ ቤት ሦስት ጊዜ ያህል መመላለስ አስፈልጎን ስለነበር የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ውክልና ተሰጥቶኝ ነበር። እንዲህ ዓይነቱ እንቅስቃሴና በእነዚያ ዓመታት ታማኝ ሚስዮናውያን ያከናውኑት የነበረው ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ በዛሬው ጊዜ በፔሩ ለሚታየው ግሩም ጭማሪ ጠንካራ መሠረት ጥሏል። በ1953 በፔሩ የነበረው 283 የሚያህል የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ከ83, 000 በላይ ሆኗል።
መለየት ክፉ ነው
በኖርንባቸው የሚስዮናውያን ቤቶች ሁሉ ከሌሎች ሚስዮናውያን ጋር አስደሳች ቅርርብ የነበረን ሲሆን ብዙውን ጊዜ የቤቱ የበላይ ተመልካች ሆኜ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ። በሳምንቱ ውስጥ ለምናከናውናቸው ነገሮች እቅድ ለማውጣትና የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለመከፋፈል ዘወትር ሰኞ ማለዳ ላይ እንሰበሰብ ነበር። ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባው ለስብከቱ ሥራ እንደሆነ ስለምንገነዘብ ሁላችንም ይህንን ኃላፊነታችንን ለመወጣት የተቀናጀ ጥረት እናደርግ ነበር። በየትኛውም የሚስዮናውያን ቤታችን ውስጥ ከባድ አለመግባባት ተነስቶ የማያውቅ መሆኑ በጣም ያስደስተኛል።
በፔሩ ለመጨረሻ ጊዜ ያገለገልነው በሊማ ከተማ ዳርቻ ላይ በሚገኘው ብሬንያ የተባለ አካባቢ ነበር። በዚያ የሚገኘው 70 የሚያህሉ አስፋፊዎችን ያቀፈው አፍቃሪ ጉባኤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአስፈፊዎቹ ቁጥር 100 ደረሰና በፓሎሚኒያ ሌላ ጉባኤ ተቋቋመ። አይሪን የታመመችው በዚህ ወቅት ነበር። የተናገረችውን ነገር አንዳንዴ ለማስታወስ እንደሚቸግራት አልፎ አልፎም ቤቷ እንኳን እንደሚጠፋባት አስተዋልኩ። ጥሩ የሕክምና እርዳታ የተደረገላት ቢሆንም እያደር ሁኔታዋ እየተባባሰ ሄደ።
በ1990 ወደ እንግሊዝ መመለስ ግድ ሆነብን። እህቴ አይቪ በደግነት ተነሳስታ ከእርስዋ ጋር እንድንኖር ፈቀደችልን። ከአራት ዓመት በኋላ አይሪን በ81 ዓመቷ አረፈች። እኔም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቀጠልኩ ሲሆን በትውልድ ከተማዬ ከሚገኙት ሦስት ጉባኤዎች ውስጥ በአንዱ በሽማግሌነት በማገልገል ላይ እገኛለሁ። አንዳንዴም ወደ ማንችስተር እየሄድኩ በዚያ የሚገኘውን የስፓንኛ ተናጋሪዎች ጉባኤ አበረታታለሁ።
ድሮ ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ በሸክላ ማጫወቻዬ የአምስት ደቂቃ ንግግር አሰማ ከነበረበት ወቅት ጋር በተያያዘ በቅርቡ አንድ አስደሳች ተሞክሮ አጋጠመኝ። በዚያን ጊዜ ንግግር በማሰማበት ወቅት ከእናቷ ጀርባ ቆማ ታዳምጥ የነበረች አንዲት ትንሽ ልጅ በደንብ ትዝ ትለኛለች።
ከጊዜ በኋላ ይህቺ ልጅ ወደ ካናዳ የሄደች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክር ከሆነች በረንከርን ከምትኖር አንዲት ጓደኛዋ ጋር ደብዳቤ ይጻጻፉ ነበር። በቅርቡ በጻፈችላት ደብዳቤ ላይ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች እንዳነጋገሯትና ከብዙ ዓመታት በፊት ከሰማችው በሸክላ የተቀዳ ንግግር ጋር የሚመሳሰል ነገር እንዳወያይዋት ገለጸችላት። እውነትን እንዳገኘች ስለተገነዘበች ራስዋን ለይሖዋ የወሰነች አገልጋይ መሆኗን ገልጻ ከ60 ዓመት በፊት ቤታቸው መጥቶ ላነጋገራቸው ወጣት ምስጋናዋን እንድታደርስላት ጠየቀቻት። በእርግጥም የእውነት ዘር እንዴት ሥር ሊሰድና ሊያድግ እንደሚችል አናውቅም።—መክብብ 11:6
አዎን፣ በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍኳቸውን አስደሳች ዓመታት ሳስታውስ የአመስጋኝነት ስሜት ይሰማኛል። ራሴን ከወሰንኩበት ከ1931 ወዲህ የይሖዋ ሕዝቦች ያደረጉት አንድም ስብሰባ አምልጦኝ አያውቅም። ምንም እንኳን እኔና አይሪን ልጆች ባንወልድም በሰማይ የሚገኘውን አባታችንን ይሖዋን በማገልገል ላይ ያሉ ከ150 የሚበልጡ መንፈሳዊ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በማግኘታችን በጣም ደስተኛ ነኝ። ውዷ ባለቤቴ እንዳለችው ያገኘናቸው ልዩ የአገልግሎት መብቶች ወደር የሌለው ደስታ አስገኝተውልናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የሂልዳ ፓጄት የሕይወት ታሪክ “የወላጆቼን ፈለግ መከተል” በሚል ርዕስ በጥቅምት 1, 1995 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 19-24 ላይ ወጥቷል።
b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እማማ በ1900ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከላይ:- እኔና አይሪን ከተጎታች ቤታችን ፊት ለፊት
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስተግራ:- በ1940 በእንግሊዝ፣ ሊድስ ከተማ፤ ሂልዳ ፓጄት፣ እኔ፣ አይሪንና ጆይሲ ሮውሊይ
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1952 በካርዲፍ፣ ዌልስ፣ የሕዝብ ንግግር ሳስተዋውቅ