አሌክሳንደር ስድስተኛ—ሮም ፈጽሞ የማትረሳው ጳጳስ
አሌክሳንደር ስድስተኛ—ሮም ፈጽሞ የማትረሳው ጳጳስ
“አንድ የካቶሊክ እምነት ተከታይ አሌክሳንደር ስድስተኛን የሚያወግዝበት ቃላት ያጥረዋል።” (ጌሺሽቴ ዴር ፓፐሰቴ ዚት ዳም ኡስጋንግ ደስ ምትኤላልተርስ) [የመካከለኛው መቶ ዘመን መጨረሻ የጳጳሳት ታሪክ] “የግል ሕይወቱ የጎደፈ ሲሆን . . . በዚህ የጵጵስና ዘመን ቤተ ክርስቲያኒቷ እንደተዋረደች አምነን መቀበል አለብን። በቦርዣ ቤተሰብ ዘመን የነበሩት ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን ለሚያዋርዱ ድርጊቶች አዲስ ባይሆኑም ቦርዣ እና ቤተሰቡ የፈጸሙት ወንጀል ግን ከማንም ጋር የሚተካከል አይደለም። የፈጸሙት መጥፎ ድርጊት አራት መቶ ዘመናት ያለፉት ቢሆንም ከታሪክ ገጽ ፈጽሞ የሚፋቅ አይደለም።”—ሌግሊዝ ኤ ላ ረኔሳንስ (1449-1517) (ቤተ ክርስቲያንና የሥነ ጥበብ ዘመን)
ስለ ሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚገልጹ ታላላቅ የጽሑፍ ሥራዎች በአንድ ጳጳስና በቤተሰቡ ላይ እንዲህ ያለ ከባድ ትችት የሰነዘሩት ለምንድን ነው? ጳጳሱና ቤተሰቡ ይህን ያህል ውግዘት የደረሰባቸው ምን ስላደረጉ ነው? የጵጵስናን የሥልጣን ዘመን በተለይ ደግሞ በሮድሪጎ ቦርዣ ወይም በአሌክሳንደር ስድስተኛ (የጵጵስና ዘመን 1492-1503) ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን ኢ ቦርዣ—ላርቴ ዴል ፖታሬ የተባለ (ከጥቅምት 2002 እስከ የካቲት 2003) አንድ ኤግዚቢሽን በሮም ውስጥ ተዘጋጅቶ ነበር።
ሥልጣን ላይ መውጣት
ሮድሪጎ ቦርዣ በ1431 በአራጎን ግዛት (በአሁኗ ስፔይን ውስጥ) ሥር በምትገኘው በሃቲቫ ከአንድ ታዋቂ ቤተሰብ ተወለደ። ሮድሪጎ እንዲማር ያደረገው የቫለንሺያ አቡን የነበረው አጎቱ አልፎንሶ ደ ቦርዣ ሲሆን ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለ በቤተ ክህነት ውስጥ ሥልጣን እንዲይዝ አድርጎታል። ሮድሪጎ 18 ዓመት ሲሞላው በወቅቱ ካርዲናል ሆኖ የነበረው አጎቱ አልፎንሶ ወደ ኢጣሊያ የላከው ሲሆን ሮድሪጎም እዚያ ሕግ ተማረ። አልፎንሶ ጳጳስ ከሆነ በኋላ ሮድሪጎን እና ሌላ የወንድሙን ልጅ ካርዲናል አድርጎ ሾማቸው። ፔር ልዊስ ቦርዣ በተለያዩ ከተሞች ላይ ገዥ ሆኖ ተሹሞ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሮድሪጎ የቤተ ክርስቲያን ምክትል ቻንስለር ሆኖ የተሾመ ሲሆን የተለያዩ ጳጳሳት ሲፈራረቁ በዚህ ሥልጣኑ ላይ ቆይቷል። ይህም ከፍተኛ መጠን ያለው ሃብትና ንብረት እንዲያካብት እንዲሁም ብዙ ሥልጣን አግበስብሶ እንዲይዝና እንደ ልዑል ተንደላቅቆ እንዲኖር አስችሎታል።
ሮድሪጎ የተማረ፣ አንደበተ ርቱዕ፣ ሥነ ጥበብን የሚወድና ካሰበው ግብ ከመድረስ ፈጽሞ ወደኋላ የማይል ሰው ነበር። ከተለያዩ ሴቶች ጋር ይማግጥ የነበረ ከመሆኑም በላይ ከአንዲት የረዥም ጊዜ ቁባቱ አራት ልጆችን የወለደ ሲሆን ከሌሎች ሴቶችም የወለዳቸው ልጆች ነበሩት።
ጳጳስ ፒየስ ዳግማዊ “ሥነ ምግባር በጎደለው አኗኗሩ” እና “በተድላ ወዳድነቱ” ክፉኛ ቢያወግዘውም ሮድሪጎ አኗኗሩን ለመቀየር ፈቃደኛ አልሆነም።ጳጳስ ኢኖሰንት ስምንተኛ በ1492 ሲሞት እርሱን የሚተካውን ጳጳስ ለመምረጥ የቤተ ክርስቲያኒቱ ካርዲናሎች ተሰብስበው ነበር። ሮድሪጎ ቦርዣ ከፍተኛ መጠን ያለው ጉቦ በመስጠት እርሱን እንዲመርጡት በማግባባት በዚያን ወቅት በተደረገው ዝግ ስብሰባ ጳጳስ አሌክሳንደር ስድስተኛ ሆኖ ተሾመ። ካርዲናሎቹ እርሱን እንዲመርጡት ማግባባት የቻለው እንዴት ነው? የቤተ ክህነት ሥልጣንን፣ ከተሞችን፣ ገዳማትንና አገረ ስብከቶችን እንደ ጉቦ አድርጎ በመስጠት ነው። አንድ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ የአሌክሳንደር ስድስተኛን ግዛት በተመለከተ “በሮም ቤተ ክርስቲያን ምግባረ ብልሹነትና ሙስና የነገሠበት ዘመን” ብሎ የተናገረው ለምን እንደሆነ ከዚህ ልትረዳ ትችላለህ።
ከፖለቲካ መሪዎች ያልተሻለ
አሌክሳንደር ስድስተኛ በቤተ ክርስቲያን ላይ የነበረውን መንፈሳዊ ሥልጣን በመጠቀም በሰሜንና በላቲን አሜሪካ አካባቢ በተገኙ አዳዲስ ግዛቶች ላይ በተነሳ የይገባኛል ጥያቄ ምክንያት በስፔይን እና በፖርቹጋል መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ውዝግብ ዳኝቷል። በማዕከላዊ ኢጣሊያ በሚገኙት በጳጳሳት በሚተዳደሩ ግዛቶች በሙሉ ፖለቲካዊ ሥልጣንም አግኝቶ ነበር። አገዛዙ ሥነ ጥበብ ባንሰራራበት ዘመን ከነበሩት ሌሎች ገዢዎች የተለየ አልነበረም። አሌክሳንደር ስድስተኛ ከእርሱ በፊትና በኋላ እንደነበሩት ጳጳሳት ጉቦኝነትና ወገናዊነት የተጠናወተው ሰው ከመሆኑም በላይ የተወሰኑ ሰዎችን እንዳስገደለ ይገመታል።
የተለያዩ ተቀናቃኝ ኃይሎች አንዳንድ የኢጣሊያን ግዛቶች በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ ይሻኮቱ በነበረበት በዚያ ሁከት በነገሠበት ዘመን እርሱም እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ፖለቲካዊ ሥልጣኑን ለማጠናከር፣ ልጆቹ ከፍተኛ ሥልጣን እንዲጨብጡና የቦርዣ ቤተሰብ ከሌሎች ልቆ እንዲገኝ ለማድረግ ከውጭ ኃይሎች ጋር በየጊዜው ፖለቲካዊ ሽርክና ይመሠርት ነበር። ሕዋን የተባለው ልጁ የካስቲልን ልጅ በማግባት ስፔይን የሚገኘው የጋንዲያ ግዛት መስፍን ሆነ። ሌላው ልጁ ጆፍራ ደግሞ የኔፕልስን ንጉሥ የልጅ ልጅ አገባ።
ጳጳሱ ከፈረንሳይ ጋር የነበረውን ግንኙነት ለማጠናከር ለአራጎን ልዑል ታጭታ የነበረችውን የ13 ዓመት ልጁን ሉክሬዚያን የሚላን መስፍን ዘመድ ለሆነ ሌላ ሰው ዳራት። ይህ ጋብቻ ከዚህ በኋላ ብዙም ፖለቲካዊ ጥቅም የማያስገኝለት መሆኑን ሲገነዘብ ሰበብ አስባብ በመፍጠር ጋብቻውን አፈረሰና ሉክሬዚያን የተቀናቃኙ ሥርወ መንግሥት አባል ለሆነው ለአራጎኑ አልፎንሶ ዳራት። ይህ በእንዲህ እንዳለ የሥልጣን ጥመኛና ጨካኝ የሆነው የሉክሬዚያ ወንድም ቼዛር ቦርዣ ከፈረንሳዩ ንጉሥ ሉዊ አሥራ ሁለተኛ ጋር ሕብረት ቢፈጥርም እህቱ ከአራጎኑ አልፎንሶ ጋር የፈጸመችው ጋብቻ ችግር ፈጠረበት። ታዲያ ለችግሩ ምን መፍትሔ አገኘ? ምንም የማያውቀው ባሏ አልፎንሶ “በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ላይ ሊገድሉት ሙከራ ባደረጉ ሁለት ሰዎች እንደ ቆሰለ” አንድ ምንጭ ተናግሯል። “ከደረሰበት የመቁሰል አደጋ እያገገመ ሳለ ከቼዛር አገልጋዮች አንዱ አንቆ ገደለው።” ሌላ ፖለቲካዊ ጥምረት መመሥረት የፈለገው ጳጳስ በዚህ ወቅት 21 ዓመት የሆናትን ልጁን ሉክሬዚያን ኃያል ለሆነው ለፌራራ መስፍን ልጅ በመስጠት ለሦስተኛ ጊዜ ዳራት።
የቼዛር የሕይወት ዘመን “በሥነ ምግባር የጎደፈና ደም እንደ ውኃ የፈሰሰበት ታሪክ” እንደሆነ ተገልጿል። አባቱ በ17 ዓመቱ ካርዲናል አድርጎ ቢሾመውም ቼዛር ከቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ይልቅ ለጦርነት የቆመ ከመሆኑም በላይ እንደ ሌሎች ጥቂት ገዢዎች እርሱም የሥልጣን ጥም የተጠናወተውና በሙስና የተጠላለፈ
ነበር። የቤተ ክህነት ሥልጣኑን በራሱ ፈቃድ ከለቀቀ በኋላ የፈረንሳይን ንግሥት በማግባት የቫሌንቲኖስ መስፍን ሆነ። ከዚያም በፈረንሳይ ወታደሮች በመታገዝ ሰሜናዊውን የኢጣሊያ ግዛት በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ ዘመቻ ጀመረ።የፈረንሳይ ጦር ለቼዛር የሚሰጠውን ድጋፍ እንዲቀጥል ለማድረግ ጳጳሱ የፈረንሳዩ ንጉሥ ሉዊ አሥራ ሁለተኛ ሕገ ወጥ የሆነ ፍቺ እንዲፈጽምና የብሪታኒዋን አኒ እንዲያገባ ፈቃድ በመስጠት የእርሷን ግዛት በእርሱ ግዛት ሥር እንዲጠቀልል አደረገው። ጳጳሱ በዚህ ድርጊቱ “ለቤተሰቡ ጊዜያዊ ጥቅም ሲል ቤተ ክርስቲያኒቷን እንዳዋረደና ሕግና ደንብ እንደጣሰ” አንድ ጽሑፍ ገልጿል።
በጵጵስና ልቅ ምግባር ላይ የተሰነዘረ ትችት
የቦርዣ ቤተሰብ በነበረው ልቅ ምግባር ምክንያት ጠላት ከማፍራቱም በላይ ለትችት ተዳርጓል። ጳጳሱ የሚሰነዘርበትን ትችት በአብዛኛው ጆሮ ዳባ ብሎ ቢያልፍም ጂረለሞ ሳቮናሮላን ግን በዝምታ ሊያልፈው አልፈቀደም። ሳቮናሮላ የዶሚኒካን መነኩሴ ሲሆን ኃይለኛ ሰባኪና የፍሎረንስ ግዛት ገዥ ነበር። የጵጵስና ፍርድ ቤቱንም ሆነ ጳጳሱን እንዲሁም የፖለቲካ እንቅስቃሴውን ከማውገዙም በላይ ጳጳሱ ከሥልጣኑ እንዲወርድና በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ ተሃድሶ እንዲካሄድ ጥሪ አቅርቧል። ሳቮናሮላ “የቤተ ክርስቲያን መሪዎች . . . ማታ ማታ ወደ ቁባቶቻችሁ ትሄዳላችሁ፣ ጠዋት ጠዋት ደግሞ ወደ ቁርባን ሥነ ሥርዓት ትመጣላችሁ” በማለት ኃይለኛ ትችት ሰንዝሯል። ቆየት ብሎም “[እነዚህ መሪዎች] የጋለሞታ መልክ ያላቸው ሲሆን ያገኙት ዝና ደግሞ ለቤተ ክርስቲያኗ ውርደት ነው። እውነቴን ነው የምላችሁ እነዚህ ሰዎች በክርስትና አያምኑም።”
ጳጳሱ የካርዲናል ሥልጣን በመስጠት ሳቮናሮላን ዝም ለማሰኘት ቢሞክርም ሥልጣኑን ሳይቀበል ቀርቷል። ለሞት የዳረገው ፀረ ጳጳስ አቋሙም ይሁን ስብከቱ፣ በመጨረሻ ሳቮናሮላ ንስሐ እንዲገባ ለማስገደድ ከሰው እንዲገለል፣ እንዲታሰርና እንዲሠቃይ ከተደረገ በኋላ ተሰቅሎ በእሳት ተቃጥሏል።
አንገብጋቢ ጥያቄዎች
ይህ በታሪክ ውስጥ የተፈጸመ ድርጊት አንገብጋቢ የሆኑ ጥያቄዎች ያስነሳል። ስለ ጳጳሱ ሴራና ምግባር ምን ለማለት ይቻላል? ታሪክ ጸሐፊዎች ምን ይላሉ? የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።
ብዙዎች የአሌክሳንደር ስድስተኛ ድርጊት ከዘመኑ ሁኔታ አንጻር መታየት አለበት የሚል አቋም አላቸው። የጵጵስና ሥልጣኑን በዚህ መንገድ የተጠቀመበት ሰላም ለማስፈን፣ ተቀናቃኝ መንግሥታትን ለመፎካከር፣ የጵጵስና ሥልጣኑን ከሚያስጠብቁለት ኃይሎች ጋር ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከርና ክርስቲያን የሆኑ ነገሥታትን በማስተባበር የቱርክን ጥቃት ለመመከት ነበር።
ስለ ምግባሩስ ምን ለማለት ይቻላል? “በየትኛውም ዘመን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጥፎ ክርስቲያኖችና ቀሳውስት ነበሩ” በማለት አንድ ምሁር ተናግረዋል። “ይህ ክርስቶስ አስቀድሞ የተናገረው በመሆኑ ምንም የሚያስደንቅ አይደለም። ቤተ ክርስቲያኒቱን ስንዴና እንክርዳድ ከተዘራበት እርሻ ወይም በሐዋርያቱ መካከል ይሁዳ እንደነበረ ሁሉ ጥሩና መጥፎ ዓሣ ከሚሰበስብ መረብ ጋር አመሳስሏታል።” a
እኚሁ ምሁር ጨምረው ሲናገሩ:- “አንድ ዕንቁ በምንም ላይ ይቀመጥ በምን ውድነቱ እንደማይቀንስ ሁሉ አንድ ቄስ ኃጢአተኛ መሆኑ . . . የሚያስተምረውን ትምህርት . . . ውድቅ አያደርገውም። . . . በንጹሕ እጅም ተሰጠ በቆሻሻ ወርቅ ምንጊዜም ወርቅ ነው።” አንድ ካቶሊክ ታሪክ ጸሐፊ አሌክሳንደር ስድስተኛን በተመለከተ ማቴዎስ 23:2, 3) ሆኖም እንዲህ ያለው ምክንያት አሳማኝ ነው ብለህ ታስባለህ?
አንድ ቅን የካቶሊክ እምነት ተከታይ ሊኖረው ስለሚገባው አመለካከት ሲናገሩ ኢየሱስ ጻፎችና ፈሪሳውያንን በተመለከተ ‘ያዘዟችሁን ሁሉ አድርጉ እንደ ሥራቸው ግን አታድርጉ’ በማለት ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረውን ምክር መከተል ይኖርበታል በማለት ተከራክረዋል። (ይህ እውነተኛ ክርስትና ነውን?
ኢየሱስ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሁሉ ምን እንደሚጠበቅባቸው ለማወቅ የሚያስችል ቀላል መመሪያ ሰጥቷል:- “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን፣ ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፣ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፣ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም። ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።”—ማቴዎስ 7:16-18, 20
በቀደሙት ዘመናትም ሆነ በአሁኑ ዘመን ያሉት የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስ ለእውነተኛ ክርስትና ከተወውና እውነተኛ ተከታዮቹም ከተከተሉት ክርስትና አንጻር ሲመዘኑ እንዴት ይታያሉ? ይህን ለማወቅ የሃይማኖት መሪዎች ከፖለቲካ ጋር ያላቸውን ግንኙነትና የግል አኗኗራቸውን እንደ ምሳሌ አድርገን እንመልከት።
ኢየሱስ ዓለማዊ መሪ ሆኖ የገዛበት ጊዜ የለም። የተደላደለ ኑሮ ለመምራት ጥረት አላደረገም። ከዚያ ይልቅ ራሱ እንደተናገረው “ራሱን የሚያስጠጋበት” ቤት እንኳ አልነበረውም። መንግሥቱ ‘ከዚህ ዓለም አይደለም።’ ‘እርሱ ከዓለም እንዳይደለ ሁሉ’ ደቀ መዛሙርቱም ‘ከዓለም አይደሉም።’ በዚህም የተነሳ ኢየሱስ በዘመኑ በነበረው የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ እጁን አላስገባም።—ማቴዎስ 8:20፤ ዮሐንስ 6:15፤ 17:16፤ 18:36
ይህ ድርጊታቸው ተራውን ሕዝብ ለችግርና ለሥቃይ የሚዳርግ ቢሆንም እንኳ የሃይማኖት ድርጅቶች ሥልጣንና ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ላለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ እየገቡ ሲፈተፍቱ አልኖሩምን? የእነርሱን እንክብካቤ ሊያገኙ የሚገባቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በድህነት ሲማቅቁ በርካታ ቀሳውስት ግን በቅንጦት ሲኖሩ መመልከት የተለመደ አይደለምን?
የኢየሱስ ግማሽ ወንድም ያዕቆብ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “አመንዝሮች ሆይ፣ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።” (ያዕቆብ 4:4) “የእግዚአብሔር ጠላት” የሚሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አንደኛ ዮሐንስ 5:19 “ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ” ይናገራል።
የአሌክሳንደር ስድስተኛን ምግባር በተመለከተ በቦርዣ ዘመን የነበሩ አንድ ታሪክ ጸሐፊ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “አኗኗሩ ወራዳ ነው። ሃፍረት የለሽና ይሉኝታ ቢስ ከመሆኑም በላይ እምነትም ሆነ ሃይማኖት የሌለው ሰው ነበር። ስግብግብ፣ የሥልጣን ጥመኛ፣ ጨካኝና ልጆቹን የበላይ ለማድረግ የሚሯሯጥ ሰው ነበር።” በቤተ ክህነት ሥልጣን እንዲህ ዓይነት ብልሹ ምግባር የነበረው ቦርዣ ብቻ አይደለም።
እንዲህ ስላለው ምግባር ቅዱሳን ጽሑፎች ምን ይላሉ? “ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን?” በማለት ጳውሎስ ይጠይቃል። “አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ . . . ወይም አመንዝሮች . . . ወይም ገንዘብን የሚመኙ . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።”—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10
የቦርዣን ቤተሰብ በተመለከተ በቅርቡ በሮም የቀረበው ኤግዚቢሽን ዓላማ “እነዚህን ታላላቅ ሰዎች ከታሪክ አኳያ ለመመልከት እንጂ . . . ምንም ጥፋት የለባቸውም ለማለት ወይም ለማውገዝ አይደለም።” እርግጥ ነው ጎብኚዎች የራሳቸው መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። ታዲያ አንተ ምን መደምደሚያ ላይ ደረስክ?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስለ እነዚህ ምሳሌዎች ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት የየካቲት 1, 1995 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 5-6 እንዲሁም የሰኔ 15, 1992 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 17-22 ተመልከት።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሮድሪጎ ቦርዣ፣ ጳጳስ አሌክሳንደር ስድስተኛ
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሮድሪጎ ቦርዣ ሥልጣኑን ለማስፋፋት ልጁን ሉክሬዚያን እንደ መሣሪያ አድርጎ ተጠቅሞባታል
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቼዛር ቦርዣ የሥልጣን ጥመኛና ምግባረ ብልሹ ሰው ነበር
[በገጽ 40 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጂረለሞ ሳቮናሮላ ዝም አልልም በማለቱ ተሰቅሎ በእሳት እንዲቃጠል ተደርጓል