ኮሪያ ውስጥ ለየት ባለ ቋንቋ ማገልገል
ኮሪያ ውስጥ ለየት ባለ ቋንቋ ማገልገል
በ1997 የበጋ ወቅት በይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተገኙት ሰዎች ከፍተኛ ጉጉት የሚነበብባቸው ቢሆንም ድምፃቸው አይሰማም ነበር። መስማት ለተሳናቸውና የመስማት ችግር ላለባቸው ሰዎች የተዘጋጀው ይህ የአውራጃ ስብሰባ በኮሪያ በዓይነቱ የመጀመሪያው ሲሆን ከፍተኛው የተሰብሳቢዎች ቁጥር 1, 174 ነበር። ንግግሮችን፣ ቃለ ምልልሶችንና ድራማውን ጨምሮ አጠቃላይ ፕሮግራሙ የቀረበው በኮሪያ የምልክት ቋንቋ ሲሆን ይህም በአዳራሹ ውስጥ በሚገኝ ትልቅ ስክሪን ላይ በፊልም ይታይ ነበር። ይህ ስብሰባ የበርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች የረጅም ዓመት ድካም ውጤት ነው።
ምድር ገነት በምትሆንበት ጊዜ ‘የደንቆሮች ጆሮ ይከፈታል።’ (ኢሳይያስ 35:5) በዚያ ገነት ውስጥ ለመኖር መስማት የተሳናቸውን ጨምሮ እያንዳንዱ ሰው አምላክ በአሁኑ ጊዜ ለሕዝቦቹ ወዳዘጋጀው የበለጸገ መንፈሳዊ ሁኔታ ይኸውም ወደ መንፈሳዊው ገነት መግባት ይኖርበታል። ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው በመጠመቅ የይሖዋ ምሥክሮች መሆንና የእርሱን መመሪያ መከተል ይኖርባቸዋል።—ሚክያስ 4:1-4
አነስተኛ ጅምር
በ1960ዎቹ ዓመታት የኮሪያ ዋና ከተማ በሆነችው ሴኡል ውስጥ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች በተወሰነ መጠን ይሰበክ የነበረ ቢሆንም እነዚህ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኙት በ1970ዎቹ ነበር። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ፣ በፍጥነት መጻፍ የሚችል አንድ ክርስቲያን የንግግሮቹን ዋና ዋና ነጥቦችና የተጠቀሱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በጥቁር ሰሌዳ ላይ ይጽፍላቸው ነበር።
በ1971 በታይጀን ከተማ የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር መስማት ለተሳነው ልጁና ተመሳሳይ ችግር ላለባቸው ጓደኞቹ ስለ አምላክ መንግሥት ማስተማር ጀመረ። በዚህ ቡድን ውስጥ የነበሩ በርካታ ቀናተኛ ግለሰቦች በአሁኑ ጊዜ በምልክት ቋንቋ በሚካሄዱ ጉባኤዎች ውስጥ የጀርባ አጥንት ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።—ዘካርያስ 4:10
ወጣቶች በፈቃደኝነት ራሳቸውን አቅርበዋል
መስማት የተሳናቸው ሰዎች ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ አውቀው ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ መመላለስ እንዲችሉ ለመርዳት ፈቃደኛ የሆኑ ሌሎች ዮሐንስ 17:3) እንዲህ ዓይነቱን እርዳታ ለመስጠት በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች የምልክት ቋንቋ የተማሩ ሲሆን እንዲህ በማድረጋቸውም የተትረፈረፈ በረከት አግኝተዋል።
ሰዎች ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ነበረባቸው። (ፓርክ ኢንሰን የተባለ አንድ የ15 ዓመት ወጣት የምልክት ቋንቋ የመማር ግብ አወጣ። ለዚህም እንዲረዳው 20 የሚያህሉ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ተቀጥረው በሚሠሩበት ፋብሪካ ውስጥ በተለማማጅነት መሥራት ጀመረ። ቋንቋቸውንና አስተሳሰባቸውን ለማወቅ ሲል ለስምንት ወራት ያህል ከእነርሱ ጋር ሠራ። በቀጣዩ ዓመት ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት ያላቸው መስማት የተሳናቸው ሰዎች ባሉበት ቡድን ውስጥ የዘወትር አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። ቡድኑ በፍጥነት ያደገ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ እሁድ እለት በሚደረገው ስብሰባ ላይ ከ35 በላይ ሰዎች መገኘት ጀመሩ።—መዝሙር 110:3 አ.መ.ት
ከዚያም፣ የምልክት ቋንቋ ቡድኑ ሴኡል ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሱን ችሎ የጉባኤ ስብሰባዎች ማድረግ ጀመረ። ወንድም ፓርክ ኢንሰን ቁጥሩ እያደገ በመጣው በዚህ ቡድን ውስጥ በልዩ አቅኚነት ያገለገለ ሲሆን በዚህ ወቅት በምልክት ቋንቋ በደንብ መግባባት ችሎ ነበር። መስማት የተሳናቸው 28 ሰዎችን ያስጠናባቸው ወራት ነበሩ። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ እድገት አድርገው በመጠመቅ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።
እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረጋቸው ምክንያት ጥቅምት 1976 በሴኡል የመጀመሪያው የምልክት ቋንቋ ጉባኤ ተቋቋመ። ጉባኤው 40 አስፋፊዎችና 2 የዘወትር አቅኚዎች ነበሩት። የዚህ ጉባኤ መቋቋም በሌሎች የኮሪያ ከተሞችም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እንዲደረግ ምክንያት ሆኗል። እውነትን የተጠሙና የሚያወያያቸው ሰው የሚፈልጉ በርካታ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ነበሩ።
መስማት ከተሳናቸው ጋር መሥራት
መስማት የተሳናቸውን ሰዎች እንዴት ማግኘት ይቻላል ብለህ ታስብ ይሆናል። አብዛኞቹ የሚገኙት በሌሎች ጥቆማ ነው። በአካባቢው የሚገኙ የሩዝ ነጋዴዎችን ቀርቦ በማነጋገር መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ስምና አድራሻ ማግኘት ይቻላል። አንዳንድ የመንግሥት ቢሮዎችም መረጃ በመስጠት ረገድ ተባባሪዎች ናቸው። መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ለመስበክ የተደረገው ጥረት በጣም ውጤታማ በመሆኑ ከጊዜ በኋላ በምልክት ቋንቋ የሚካሄዱ አራት ጉባኤዎች ሊቋቋሙ ችለዋል። በርካታ ክርስቲያን ወጣቶች የምልክት ቋንቋ እንዲማሩ ማበረታቻ ተሰጥቷቸው ነበር።
የምልክት ቋንቋ የተማሩ ልዩ አቅኚዎች በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ተመድበው በእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ ማገልገል ጀመሩ። በቅርቡ ደግሞ ከአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የተመረቁ ተማሪዎች በምልክት ቋንቋ ጉባኤዎች ውስጥ እንዲያገለግሉ በመመደባቸው እነዚህን ጉባኤዎች በመንፈሳዊ ሁኔታ አጠናክረዋቸዋል።
በዚህ ክልል ማገልገል አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መቋቋም ይጠይቃል። መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ባሕል ለማወቅ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ሐሳባቸውን በሚገልጹበት ጊዜም ሆነ በድርጊታቸው በጣም ግልጽ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ይህ ሌሎችን የሚያስገርማቸው ከመሆኑም በላይ አለመግባባት እንዲፈጠርም ሊያደርግ ይችላል። ከዚህም በላይ የይሖዋ ምሥክሮች መስማት የተሳናቸውን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስጠኑ የምልክት ቋንቋ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ መርዳትና ለንባብና ለጥናት የራሳቸውን ፕሮግራም እንዲያወጡ ማበረታታት ያስፈልጋቸዋል።
መስማት የተሳናቸው ሰዎች በዕለታዊ እንቅስቃሴዎቻቸው በሌሎች ላይ የማይደርሱ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ብዙውን ጊዜ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ በሕክምና መስጫ ተቋማት እንዲሁም በገበያ ሥፍራዎች ከሰዎች ጋር መግባባት ይቸግራቸዋል። በአቅራቢያው ባሉ ጉባኤዎች የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ፍቅራዊ እርዳታ ስለሚያደርጉላቸው መስማት የተሳናቸው ሰዎች በክርስቲያን ዮሐንስ 13:34, 35
ጉባኤ ውስጥ ካለው እውነተኛ ወንድማማችነት ተጠቃሚ ሆነዋል።—መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ጥሩ ውጤቶች ያስገኛል
በኮሪያ ደቡባዊ ጠረፍ ዋነኛ የወደብ ከተማ በሆነችው በፑሳን አንድ የይሖዋ ምሥክር መስማት ከተሳናቸው ሁለት ሰዎች ጋር በአጋጣሚ ተገናኘ። ሰዎቹም በቁራጭ ወረቀት ላይ “በገነት መኖር እንፈልጋለን። ስለ ዘላለም ሕይወት የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማወቅ እንፈልጋለን” ብለው ጻፉለት። ወንድም አድራሻቸውን ከወሰደ በኋላ ለሌላ ጊዜ ቀጠሮ ያዙ። ተመልሶ ሲሄድ መስማት የተሳናቸው በርካታ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት ቤቱን ሞልተው ጠበቁት። ይህ አጋጣሚ የምልክት ቋንቋ እንዲማር አነሳሳው። ብዙም ሳይቆይ በምልክት ቋንቋ የሚመራ ጉባኤ በፑሳን ተቋቋመ።
በዚያ ጉባኤ ውስጥ የሚገኝ አንድ ወንድም ሁለት ሰዎች በምልክት ቋንቋ ሲነጋገሩ ተመለከተና ቀርቦ አነጋገራቸው። ከሃይማኖታዊ ስብሰባ እየተመለሱ መሆኑን ሲያውቅ በዚያው ዕለት ከሰዓት በኋላ በስምንት ሰዓት በመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ እንዲገኙ ጋበዛቸው። ሰዎቹም በስብሰባው ላይ የተገኙ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላቸው። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሁለቱ ሰዎች መስማት ከተሳናቸው 20 ወዳጆቻቸው ጋር ሆነው በአውራጃ ስብሳባ ላይ ተገኙ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል በአሁኑ ወቅት ብዙዎቹ ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው ተጠምቀዋል። ሁለቱ በምልክት ቋንቋ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌዎች ሆነው የሚያገለግሉ ሲሆን አንደኛው ደግሞ የጉባኤ አገልጋይ ነው።
ጥረታቸው ተክሷል
መስማት የተሳናቸው አንዳንድ ሰዎች የምልክት ቋንቋ ጉባኤ ከሚገኝበት አካባቢ ርቀው ስለሚኖሩ እነርሱን በመንፈሳዊ መመገብ አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ጥረትና ቆራጥነት ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል አንድ የ31 ዓመት ሰው የሚተዳደረው በአንዲት ደሴት ላይ ዓሣ በማጥመድ ነው። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝቶ የነበረው ታናሽ ወንድሙ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ነገረው። ይህ መስማት የተሳነው ዓሣ አጥማጅ መንፈሳዊ ረሃቡን ለማርካት በጀልባ 16 ኪሎ ሜትር ተጉዞ በኮሪያ ደቡባዊ ጠረፍ ወደምትገኘው የቶንግየንግ ከተማ ይሄዳል። ይህንን የሚያደርገው በሞሶን ከተማ በሚገኘው የምልክት ቋንቋ ጉባኤ ውስጥ ከሚያገለግለው ልዩ አቅኚ ጋር ለመገናኘት ነው። በየሳምንቱ ሰኞ ሰኞ ልዩ አቅኚው መስማት የተሳነውን ይህን ዓሣ አጥማጅ ለማስጠናት ሲል ብቻ 65 ኪሎ ሜትር ይጓዛል።
መስማት የተሳነው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እሁድ ዕለት በሞሶን ከተማ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ለመገኘት በጀልባ 16 ኪሎ ሜትር ከተጓዘ በኋላ ቀሪውን 65 ኪሎ ሜትር ደግሞ በአውቶቡስ መጓዝ ነበረበት። ጥረቱ ውጤት አስገኝቶለታል። በጥቂት ወራት ውስጥ የምልክት ቋንቋ ችሎታውን ማሻሻል፣ ተጨማሪ የኮሪያ ፊደላት መማርና ከሁሉ በላይ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ዝምድና መመስረት የሚቻልበትን ብቸኛውን መንገድ ማወቅ ችሏል። በስብሰባዎች ላይ መገኘትና አዘውትሮ መመስከር አስፈላጊ መሆኑን ስለተገነዘበ በምልክት ቋንቋ የሚካሄድ ጉባኤ ወደሚገኝበት አካባቢ ተዛወረ። እንዲህ ዓይነት እርምጃ መውሰዱ ቀላል ነበርን? አልነበረም። በወር እስከ 3, 800 የአሜሪካ ዶላር የተጣራ ገቢ የሚያስገኝለትን ዓሣ የማጥመድ ሥራውን መተው የነበረበት ቢሆንም የወሰደው ቆራጥ እርምጃ መልሶ ክሶታል። በእውነት ውስጥ እድገት አድርጎ የተጠመቀ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ በደስታ ይሖዋን በማገልገል ላይ ይገኛል።
መስማት ለተሳናቸው ሰዎች መተርጎም
አብዛኛውን ጊዜ የመንግሥቱ ምሥራች የሚተላለፈው በቃል ነው። ይሁን እንጂ የአምላክን ቃል በትክክል ለማስተላለፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከዚህ በተሻለ መልኩ መቅረብ አለበት። በዚህም ምክንያት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ልምድ ያላቸው ሽማግሌዎች መጻሕፍትንና ደብዳቤዎችን ይጽፉ ነበር። (ሥራ 15:22-31፤ ኤፌሶን 3:4፤ ቆላስይስ 1:2፤ 4:16) በዘመናችን በመጻሕፍትና በሌሎች ክርስቲያናዊ ጽሑፎች አማካኝነት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ይቀርባል። እነዚህ ጽሑፎች የተለያዩ የምልክት ቋንቋዎችን ጨምሮ በመቶዎች ወደሚቆጠሩ ቋንቋዎች ይተረጎማሉ። ጽሑፎችን በኮሪያ የምልክት ቋንቋ ለመተርጎም ቅርንጫፍ ቢሮው የምልክት ቋንቋ የትርጉም ክፍል አቋቁሟል። የቪዲዮ ክፍል በምልክት ቋንቋ የቪዲዮ ፊልሞችን ያዘጋጃል። በመላው ኮሪያ በሚገኙ ጉባኤዎች ያሉ መስማት የተሳናቸው የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎችና ፍላጎት ያላቸው ሰዎች መንፈሳዊ ምግብ የሚቀርብላቸው በዚህ ዝግጅት አማካኝነት ነው።
ምንም እንኳን ብዙዎች በምልክት ቋንቋ ጥሩ ችሎታ በማዳበራቸው የቪዲዮ ክሮችን በማዘጋጀቱ ሥራ እርዳታ ቢያበረክቱም አብዛኛውን ጊዜ ግን ከሁሉ የተሻሉት ተርጓሚዎች መስማት የተሳናቸው ወላጆች ያሏቸው ልጆች ናቸው። እነዚህ ልጆች የምልክት ቋንቋን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ተምረውታል። በምልክት ቋንቋ ጥሩ አድርገው ሐሳባቸውን መግለጽ የሚችሉ ከመሆኑም በላይ በአካላዊ እንቅስቃሴያቸውና በፊታቸው ገጽታ መልእክቱ ሕያው እንዲሆንና አጽንኦት እንዲኖረው ያደርጋሉ፤ ይህም የሰዎችን አእምሮና ልብ ለመንካት ያስችላል።
ቀደም ሲል እንደተገለጸው በአሁኑ ወቅት ኮሪያ ውስጥ የአውራጃና የወረዳ ስብሰባዎች በምልክት ቋንቋ በቋሚነት ይደረጋሉ። ይህ ብዙ ሥራ፣ ወጪና ጥረት ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ተሰብሳቢዎቹ ለዝግጅቱ አድናቆት አላቸው። ስብሰባው ካለቀም በኋላ እንኳን ብዙዎቹ ወደኋላ ቀርተው ከወንድሞቻቸው ጋር መጫወትና በስብሰባው ላይ ስለቀረበው መንፈሳዊ ምግብ መወያየት ያስደስታቸዋል። በዚህ ለየት ያለ ቋንቋ ማገልገል የራሱ የሆኑ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩትም በምላሹ የሚገኘው መንፈሳዊ በረከት ቢደከምለትም የሚያስቆጭ እንዳልሆነ ያሳያል።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኮሪያ ውስጥ በምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ የቪዲዮ ፊልሞች:- “አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?፣” “መንፈሳዊ ውርሻችንን ማድነቅ፣” “ለጊዜያችን የሚሆኑ የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች” እንዲሁም “የይሖዋን ሥልጣን አክብሩ”
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከታች:- በኮሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ በምልክት ቋንቋ የቪዲዮ ፊልም ሲቀረጽ፤ በስተቀኝ የመጀመሪያው:- ቲኦክራሲያዊ ቃላትን የሚወክሉ ምልክቶች ሲዘጋጁ፤ ቀጥሎ:- የምልክት ቋንቋ ትርጉም ክፍል፤ በስተቀኝ ከታች:- የምልክት ቋንቋ ፊልም የሚሠራው ሰው የሚናገረውን ሐሳብ እንዳይረሳው ሌላ ሰው ይረዳዋል