እውነተኛ ፍቅርን ማዳበር የሚቻለው እንዴት ነው?
እውነተኛ ፍቅርን ማዳበር የሚቻለው እንዴት ነው?
“ፍቅር ፈዋሽ ነው። ፍቅር ሕይወት ነው።”—በ1871 በጆሴፍ ጆንሰን ከተዘጋጀው ሊቪንግ ቱ ፐርፐዝ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ
አንድ ሰው ፍቅርን ማዳበር የሚችለው እንዴት ነው? የሥነ ልቦና ትምህርት በመማር? የተለያዩ መጻሕፍትን በማንበብ? የፍቅር ፊልሞችን በመመልከት? በጭራሽ። ሰዎች በመጀመሪያ ደረጃ ፍቅርን የሚማሩት ከወላጆቻቸው ነው። በሚዋደድ ቤተሰብ ውስጥ የሚያድጉ ልጆች ወላጆቻቸው ሲመግቧቸውና ከአደጋ ሲጠብቋቸው፣ ሲያነጋግሯቸውና ሲንከባከቧቸው የፍቅርን ምንነት ይማራሉ። በተጨማሪም የቱ ትክክል የትኛው ደግሞ ስህተት እንደሆነ መመሪያ በሚሰጧቸው ጊዜ ፍቅርን ይማራሉ።
እውነተኛ ፍቅር ከውስጥ የሚመነጭ ስሜት ነው። ልጆች ተግሣጽ የሚሰጣቸው ለምን እንደሆነ ለጊዜው ባይገባቸውም እንኳ ወላጆች ይህን ከማድረግ እንደማይቆጠቡ ሁሉ መልካም የሚደረግላቸው ሰዎች ባይገነዘቡትም እውነተኛ ፍቅር ለሌሎች መልካም ከማድረግ ወደኋላ አይልም። ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር በማሳየት ረገድ ፍጹም ምሳሌ የሚሆነን ፈጣሪያችን ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ልጄ ሆይ፣ የጌታን ቅጣት አታቅልል፣ በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም፤ ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና” በማለት ጽፏል።—ዕብራውያን 12:5, 6
እናንት ወላጆች፣ ለቤተሰባችሁ ፍቅር በማሳየት ረገድ የይሖዋን ምሳሌ መኮረጅ የምትችሉት እንዴት ነው? እርስ በርሳችሁ ፍቅር በማሳየት ረገድ ለልጆቻችሁ ምሳሌ መሆናችሁ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
ፍቅርን በማሳየት ምሳሌ መሆን
ባል ከሆንክ ለሚስትህ አክብሮትና አድናቆት እንዳለህ ታሳያለህ? ሚስት ከሆንሽ ባልሽን የምትወጂና የምትደግፊ ነሽ? መጽሐፍ ቅዱስ ባልና ሚስት እርስ በርስ መዋደድና መከባበር እንዳለባቸው ይናገራል። (ኤፌሶን 5:28፤ ቲቶ 2:4) ወላጆች እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ ልጆች ፍቅርን ሊማሩ ይችላሉ። ይህም ፍቅርን ለማስተማር የሚያስችል ግሩም መንገድ ነው።
ወላጆች በመዝናኛ ምርጫቸው፣ በሥነ ምግባር አቋማቸውና በሚያወጧቸው ግቦችና ቅድሚያ በሚሰጧቸው ነገሮች ረገድ ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎችን የሚከተሉ ከሆነ በቤተሰባቸው ውስጥ ፍቅር ይሰፍናል። በመላው ዓለም የሚኖሩ ብዙ ቤተሰቦች መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የመሰሉ መሥፈርቶችን ለማውጣት ትልቅ እገዛ እንደሚያበረክት ተገንዝበዋል። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ” መሆኑንና “ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” እንደሚጠቅም የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ብዙዎች በኢየሱስ የተራራ ስብከት ውስጥ የሚገኙት ምክሮችና የሥነ ምግባር መመሪያዎች አቻ የማይገኝላቸው እንደሆኑ ይስማማሉ።—ማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7
መላው ቤተሰብ የአምላክን መመሪያ ለማግኘት የሚጥርና ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምቶ የሚኖር ሮሜ 2:21፤ ቆላስይስ 3:21
ከሆነ እያንዳንዱ የቤተሰቡ አባል ከጭንቀት ነፃ ሆኖ እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ ልጆችም ለወላጆቻቸው ፍቅርና አክብሮት እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል። በተቃራኒው ደግሞ ቤተሰቡ ቋሚ በሆነ የአቋም ደረጃ የማይመራ ከሆነ ይህ ሁኔታ ልጆች እንዲበሳጩና ዓመፀኞች እንዲሆኑ ሊያደርጋቸው ይችላል።—ያለ አባት ወይም ያለ እናት ልጆችን ስለሚያሳድጉ ወላጆችስ ምን ለማለት ይቻላል? አንደኛው የትዳር ጓደኛ አለመኖሩ ለልጆቻቸው ፍቅርን እንዳያስተምሩ ያግዳቸዋል ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። አባትና እናት አብረው ሆነው ልጆችን ማሳደጋቸው የተሻለ መሆኑ የማያጠያይቅ ቢሆንም ብቻቸውን ሆነው ልጆችን በሚያሳድጉ ወላጆችና በልጆች መካከል ጥሩ ግንኙነት ካለ የአንዱ ወላጅ አለመኖር ብዙም ላያጎድል እንደሚችል አንዳንድ ተሞክሮዎች ያሳያሉ። ያለ አባት ወይም ያለ እናት ልጆች የምታሳድጉ ወላጆች በቤተሰባችሁ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት አድርጉ። አንድ ምሳሌ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም [የወላጅነት ኃላፊነትህንም ጨምሮ] ጎዳናህን ያቀናልሃል” በማለት ይናገራል።—ምሳሌ 3:5, 6፤ ያዕቆብ 1:5
በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ በታማኝነት የሚያገለግሉ ያለ እናት ወይም ያለ አባት ያደጉ በአርዓያነት የሚጠቀሱ ብዙ ወጣቶች አሉ። ይህም ያለ እናት ወይም ያለ አባት ልጆች የሚያሳድጉ ወላጆች ለልጆቻቸው ፍቅርን በማስተማር ረገድ ሊሳካላቸው እንደሚችል የሚያሳይ ማስረጃ ነው።
ፍቅርን ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻው ቀን” “ፍቅር” እንደሚቀዘቅዝ ይናገራል። ይህም በቤተሰብ መካከል ሊኖር የሚገባው ተፈጥሯዊ ፍቅር እንደሚጠፋ የሚጠቁም ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 3) ሆኖም ፍቅር በሌለበት ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ሰዎች እንኳ ከጊዜ በኋላ ፍቅርን ሊያዳብሩ ይችላሉ። እንዴት? ዋነኛው የፍቅር ምንጭ ከሆነውና ከልባቸው ተነሳስተው ወደ እርሱ ለሚቀርቡ ሁሉ ፍቅሩን ከሚያሳየው ከይሖዋ በመማር ነው። (1 ዮሐንስ 4:7, 8) አንድ መዝሙራዊ “አባቴና እናቴ ትተውኛልና፣ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ” በማለት ተናግሯል።—መዝሙር 27:10
ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች ፍቅሩን ይገልጽልናል። በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የሚሰጠን አባታዊ መመሪያ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስና በክርስቲያን ወንድሞች አማካኝነት የምናገኘው ድጋፍ ከፍቅሩ መግለጫዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። (መዝሙር 119:97-105፤ ሉቃስ 11:13፤ ዕብራውያን 10:24, 25) እነዚህ ሦስት ዝግጅቶች ለአምላክና ለሰዎች ያለህን ፍቅር ለማሳደግ እንዴት እንደሚረዱህ እንመልከት።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ አባታዊ መመሪያ
ከአንድ ሰው ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ግለሰቡን ጥሩ አድርጎ ማወቅን ይጠይቃል። ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ማንነቱን በመግለጥ ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይጋብዘናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ብቻ አይበቃም። በውስጡ የሚገኙትን ትምህርቶች በሥራ ላይ በማዋል ለሕይወታችን ጠቃሚ መሆናቸውን በተግባር ማየት ይኖርብናል። (መዝሙር 19:7-10) ኢሳይያስ 48:17 “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ” በማለት ይናገራል። አዎን፣ ፍቅር የሆነው ይሖዋ የሚያስተምረን አላስፈላጊ ሕጎችንና ደንቦችን በማውጣት ነፃነታችንን ለመንፈግ ሳይሆን እኛን ለመጥቀም ነው።
መጽሐፍ ቅዱስን ጥሩ አድርገን ማወቃችን ለሰዎች ያለንን ፍቅር እንድናሳድግም ይረዳናል። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አምላክ ለሰዎች ያለውን አመለካከት እንድናውቅ ፊልጵስዩስ 1:9
ከማስቻሉም በላይ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ምን ማድረግ እንደሚኖርብን መመሪያ ይሰጠናል። ይህን ማወቃችን ለሰዎች ፍቅር እንድናዳብር ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ’ በማለት ተናግሯል።—ፍቅርን በማሳየት ረገድ እውቀት ትክክለኛ አመለካከት እንድናዳብር እንዴት ሊረዳን እንደሚችል ለማየት በሐዋርያት ሥራ 10:34, 35 ላይ የሚገኘውን “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ” እንደሆነ የሚናገረውን መሠረታዊ እውነት እንደ ምሳሌ አድርገን እንመልከት። (ሥራ 10:34, 35) አምላክ ሰዎችን የሚመዝነው በዘራቸው ወይም በብሔራቸው ሳይሆን በጽድቅ ሥራቸውና ለአምላክ ባላቸው ፍርሃት ከሆነ እኛም ለሰዎች ተመሳሳይ አመለካከት ሊኖረን አይገባም?—ሥራ 17:26, 27፤ 1 ዮሐንስ 4:7-11, 20, 21
ፍቅር የአምላክ መንፈስ ፍሬ ነው
ወቅቱን ጠብቆ የሚጥል ዝናብ ጥሩ አዝመራ እንደሚያስገኝ ሁሉ የአምላክ መንፈስም አንድ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የመንፈስ ፍሬ” ተብለው የተገለጹትን ባሕርያት እንዲያፈራ ያደርገዋል። (ገላትያ 5:22, 23) በዚህ ፍሬ ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ የያዘው ፍቅር ነው። (1 ቆሮንቶስ 13:13) ሆኖም የአምላክን መንፈስ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ዋነኛው መንገድ ጸሎት ነው። አምላክን ከለመንነው መንፈሱን እንደሚሰጠን የታወቀ ነው። (ሉቃስ 11:9-13) አምላክ መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጥህ ‘ትለምነዋለህ?’ መንፈሱን እንዲሰጥህ አዘውትረህ የምትጠይቀው ከሆነ ፍቅርን ጨምሮ ውድ የሆነው የመንፈሱ ፍሬ በሕይወትህ ውስጥ ይበልጥ ይንጸባረቃል።
ሆኖም ከአምላክ መንፈስ ጋር የሚቃረን ሌላ ዓይነት መንፈስ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን መንፈስ ‘የዓለም መንፈስ’ በማለት ይጠራዋል። (1 ቆሮንቶስ 2:12፤ ኤፌሶን 2:1, 2) ይህም ሰዎች መጥፎ ነገር እንዲያደርጉ የሚገፋፋ ክፉ መንፈስ ሲሆን ምንጩ ከአምላክ ርቆ የሚገኘው “የዚህ ዓለም ገዥ” ከሆነው ከሰይጣን ዲያብሎስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። (ዮሐንስ 12:31) አቧራና ቆሻሻ እንደሚያቦን ንፋስ ‘የዓለም መንፈስም’ ፍቅርን የሚያበላሹ ጎጂ ምኞቶችን ይቀሰቅሳል እንዲሁም የሥጋን ድክመቶች ያራግባል።—ገላትያ 5:19-21
ሰዎች ለፍቅረ ነዋይ፣ ለራስ ወዳድነት፣ ለዓመፅና ፍቅርን በተመለከተ በዚህ ዓለም ላይ ተስፋፍቶ ለሚገኘው የተዛባና የተሳሳተ አመለካከት ራሳቸውን ሲያጋልጡ ይህን ክፉ መንፈስ ወደ ውስጥ ያስገባሉ። በውስጥህ እውነተኛ ፍቅርን ማዳበር ከፈለግህ የዓለምን መንፈስ በጽኑ መቃወም አለብህ። (ያዕቆብ 4:7) ይህን ለማድረግ ግን በራስህ ጥንካሬ ከመታመን ይልቅ ይሖዋ እንዲረዳህ ጠይቀው። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው የአምላክ ኃይል የሆነው መንፈሱ ያጠነክርሃል እንዲሁም በትግሉ እንድታሸንፍ ይረዳሃል።—መዝሙር 121:2
ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ፍቅርን መማር
ልጆች በቤት ውስጥ ከሚደረግላቸው ፍቅራዊ እንክብካቤ ፍቅርን ማሳየት እንደሚማሩ ሁሉ ወጣትም ሆን አረጋዊ ሁላችንም ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር በመሰብሰብ ፍቅራችንን ማሳደግ እንችላለን። (ዮሐንስ 13:34, 35) የክርስቲያን ጉባኤ አንዱ አብይ ተግባር ሰዎች ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዲነቃቁ’ የሚያስችል አጋጣሚ መፍጠር ነው።—ዕብራውያን 10:24
በተለይ ፍቅር በጠፋበት በዚህ ዓለም ውስጥ ‘ተጨንቀውና ተጥለው’ የሚገኙ ሰዎች እንዲህ ያለውን ፍቅር ሲያገኙ እጅግ ይደሰታሉ። (ማቴዎስ 9:36) ፍቅር ተነፍጎት ያደገ አንድ ሰው የሌሎችን ፍቅር ሲያገኝ በልጅነቱ ፍቅር ማጣቱ ያስከተለበትን ጉዳት እንዲቋቋም ሊረዳው እንደሚችል ተሞክሮዎች ያሳያሉ። ስለዚህ ክርስቲያኖች አብረዋቸው መሰብሰብ ለጀመሩ አዳዲስ ሰዎች ከልብ የመነጨ ፍቅራዊ ስሜት ማሳየታቸው በጣም አስፈላጊ ነው!
“ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም”
መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም” በማለት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 13:8) ይህ ሲባል ምን ማለት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “ፍቅር ይታገሣል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፣ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱንም አይፈልግም፣ አይበሳጭም፣ በደልን አይቈጥርም።” (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5) ይህ ዓይነቱ ፍቅር በምናብ የተፈጠረ ወይም ከንፈር በመምጠጥ ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ይህን ዓይነቱን እውነተኛ ፍቅር የሚያሳዩ ሰዎች፣ ሕይወት በመከራና በችግር የተሞላ እንደሆነ ያውቃሉ፤ ሆኖም እነዚህ ችግሮች ለሰዎች ፍቅር እንዳያሳዩ እንቅፋት እንዲሆኑባቸው አይፈቅዱም። በእርግጥም እንዲህ ያለው ፍቅር ‘ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስር’ ነው።—ቆላስይስ 3:12-14
በኮሪያ የምትኖረውን የአንዲት የ17 ዓመት ክርስቲያን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይሖዋን ማገልገል ስትጀምር ቤተሰቧ ተቃወሟትና ከቤት አስወጧት። በዚህ ተበሳጭታ ቤተሰቧን ከመጥላት ይልቅ የአምላክ ቃልና መንፈሱ አስተሳሰቧን እንዲያስተካክሉላት ጸለየች። ከጊዜ በኋላም ለቤተሰቧ በተደጋጋሚ ደብዳቤ በመጻፍ ከልብ እንደምትወድዳቸው ገለጸችላቸው። በዚህም የተነሳ ሁለት ታላላቅ ወንድሞቿ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩና ተጠመቁ። እናቷና ታናሽ ወንድሟም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። በመጨረሻም በጣም ይቃወማት የነበረው አባቷ አመለካከቱ ተለወጠ። ወጣቷ ምሥክር እንዲህ በማለት ጽፋለች:- “አሁን ሁላችንም ትዳር የመሠረትን ክርስቲያኖች ስንሆን በቤተሰባችን ውስጥ ይሖዋን የሚያመልኩት ሰዎች ቁጥር 23 ደርሷል።” ይህ ሁሉ ፍቅር በማሳየቷ ምክንያት የተገኘ አስደሳች ውጤት ነው!
አንተም እውነተኛ ፍቅር ማዳበርና ሌሎችም እንዲህ እንዲያደርጉ መርዳት ትፈልጋለህ? የምትፈልግ ከሆነ የዚህ ውድ ባሕርይ ምንጭ የሆነው ይሖዋ እንዲረዳህ ጠይቀው። አዎን፣ ቃሉን በትጋት አጥና፣ መንፈስ ቅዱስ እንድታገኝ ጸልይ እንዲሁም ከክርስቲያን ወንድሞችህ ጋር አዘውትረህ ተሰብሰብ። (ኢሳይያስ 11:9፤ ማቴዎስ 5:5) በቅርቡ ክፉ ሰዎች ሁሉ ከምድር ላይ ከጠፉ በኋላ እውነተኛውን ፍቅር የሚያሳዩ ሰዎች ብቻ እንደሚቀሩ ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው! በእርግጥም፣ ደስተኛ ሆኖ ለመኖር ፍቅር የግድ አስፈላጊ ነው።—መዝሙር 37:10, 11፤ 1 ዮሐንስ 3:14
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጸለይና የአምላክን ቃል ማጥናት እውነተኛውን ፍቅር እንድናዳብር ይረዱናል