በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትክክለኛ አስተሳሰብ በመያዝ የጥበብ እርምጃ ውሰዱ

ትክክለኛ አስተሳሰብ በመያዝ የጥበብ እርምጃ ውሰዱ

ትክክለኛ አስተሳሰብ በመያዝ የጥበብ እርምጃ ውሰዱ

እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም ያሉት ሃይማኖታዊ ጠላቶቹ እንደሚያሠቃዩትና እንደሚገድሉት እየተናገረ ነው። የቅርብ ወዳጁ የሆነው ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህንን መቀበል ከበደው። እንዲያውም ኢየሱስን ገለል አድርጎ ገሠጸው። ጴጥሮስ እንዲህ ያደረገው በቅንነትና በአሳቢነት እንደሆነ አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የጴጥሮስን አስተሳሰብ እንዴት ተመለከተው? ኢየሱስ “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል” ብሏል።—ማቴዎስ 16:21-23

ጴጥሮስ ይህንን ሲሰማ ምንኛ ደንግጦ ይሆን! በዚህ ወቅት ለሚወደው ጌታው ረዳትና ደጋፊ ከመሆን ይልቅ “ዕንቅፋት” ሆኖበታል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ጴጥሮስ ሰዎች ሁሉ ባላቸው ደካማ አስተሳሰብ በመታለሉ ይኸውም ማመን የሚፈልገውን ነገር ብቻ በማመኑ ሊሆን ይችላል።

ከሚገባው በላይ በራሳችሁ አትታመኑ

ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዳንይዝ ዕንቅፋት ሊሆንብን የሚችለው ነገር ከሚገባው በላይ በራስ የመታመን ዝንባሌ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በጥንቷ ቆሮንቶስ የነበሩ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን “እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” በማለት አሳስቧቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 10:12) ጳውሎስ እንዲህ ያለው ለምን ነበር? የሰዎች አስተሳሰብ በቀላሉ ሊዛባና ክርስቲያኖችም እንኳ ሳይቀር አእምሯቸው “ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና [ሊለወጥ]” እንደሚችል ስለተገነዘበ ሳይሆን አይቀርም።—2 ቆሮንቶስ 11:3

ከጳውሎስ በፊት የነበሩት ትውልዶች እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። በወቅቱ ይሖዋ “አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለም” ብሏቸው ነበር። (ኢሳይያስ 55:8) “በዓይናቸው ጥበበኞች” መሆናቸው ጥፋት አስከትሎባቸዋል። (ኢሳይያስ 5:21) እንግዲያው እኛም ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዴት መያዝ እንደምንችል መመርመራችንና ተመሳሳይ የሆነ ጥፋት እንዳይደርስብን መጠንቀቃችን የተገባ ነው።

ከሥጋዊ አስተሳሰብ ራቁ

በቆሮንቶስ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሥጋዊ አስተሳሰብ ተጠናውቷቸው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 3:1-3) ከአምላክ ቃል ይልቅ ለሰብዓዊ ፍልስፍናዎች የበለጠ ትኩረት ሰጥተዋል። በዘመኑ የነበሩት ግሪካውያን ፈላስፎች በጣም ጥበበኞች እንደነበሩ አይካድም። በአምላክ ዓይን ሲታዩ ግን እንደ ሞኝ ተቆጥረዋል። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና። ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን?” (1 ቆሮንቶስ 1:19, 20) እነዚህ ጥበበኞች የሚመሩት በአምላክ መንፈስ ሳይሆን ‘በዓለም መንፈስ’ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 2:12) ፍልስፍናቸውና አስተሳሰባቸው ከይሖዋ ሐሳብ ጋር አይጣጣምም።

የእንደዚህ ዓይነቱ ሥጋዊ አስተሳሰብ ዋነኛ ምንጭ በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን ያሳታት ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። (ዘፍጥረት 3:1-6፤ 2 ቆሮንቶስ 11:3) እኛንስ ሊያስተን ይችላል? አዎን! ሰይጣን የሰዎችን ‘አሳብ ከማሳወሩ’ የተነሳ በአሁኑ ጊዜ ‘ዓለሙን ሁሉ በማሳት’ ላይ እንደሆነ የአምላክ ቃል ይናገራል። (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ራእይ 12:9) የእርሱን አሳብ ማወቃችን በጣም አስፈላጊ ነው!—2 ቆሮንቶስ 2:11

‘ከሰዎች ማታለያ’ ተጠበቁ

ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በሰዎች እንዳንታለልም’ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (ኤፌሶን 4:14) እውነትን የሚናገሩ የሚመስሉ ሆኖም አዛብተው የሚያቀርቡ “ተንኰለኞች ሠራተኞች” አጋጥመውት ነበር። (2 ቆሮንቶስ 11:12-15) እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ዓላማቸውን ዳር ለማድረስ የሚያዋጣቸውን ማስረጃ ብቻ ይጠቅሳሉ፣ የሌሎችን ቀልብ የሚስብ ንግግር ይጠቀማሉ፣ ውሸት የተቀላቀለበት ሐሳብ ያቀርባሉ፣ አሻሚ የሆኑ ነገሮች ይናገራሉ አልፎ ተርፎም ሽምጥጥ አድርገው ይዋሻሉ።

ፕሮፓጋንዳ የሚነዙ ሰዎች የሌሎችን ስም ለማጉደፍ “ኑፋቄ” እንደሚለው ያሉ ቃላትን መጠቀም ያዘወትራሉ። በአውሮፓ ምክር ቤት የፓርላማ ጉባኤ ላይ አዳዲስ ሃይማኖታዊ ቡድኖችን የሚመረምሩ ባለ ሥልጣናት “ይህንን ቃል ከመጠቀም ቢቆጠቡ የተሻለ እንደሆነ” ሐሳብ ቀርቦ ነበር። እንዲህ የተባለው ለምንድን ነው? “መናፍቅነት” የሚለው ቃል ከመጠን በላይ አሉታዊ ሐሳብ ስለሚያስተላልፍ ነው። በተመሳሳይም የግሪክ ጠቢባን ሐዋርያው ጳውሎስን “ለፍላፊ” ወይም ቃል በቃል ሲተረጎም “ጥሬ ለቃቃሚ” በማለት በተሳሳተ መንገድ ወቅሰውታል። እንደዚህ ሲሉ ጥራዝ ነጠቅ እውቀት ይዞ ከንቱ ወሬ ከሚያወራ ሰው እንደማይሻል መናገራቸው ነው። እውነታው ሲታይ ግን ጳውሎስ ‘የሰበከላቸው የኢየሱስንና የትንሣኤውን ወንጌል’ ነበር።—ሥራ 17:18

ፕሮፓጋንዳ የሚነዙ ሰዎች የሚጠቀሙበት ዘዴ ይሰምርላቸዋልን? አዎን። ሰዎች ስለ ሌሎች ዘሮችና ሃይማኖቶች ያላቸውን አመለካከት በማዛባት የጎሳና የሃይማኖት ጥላቻ በመቆስቆስ ረገድ የጎላ ሚና ተጫውተዋል። ብዙዎች እምብዛም ተወዳጅነት የሌላቸውን አናሳ ቡድኖች ኅብረተሰቡ እንዲያገላቸው ለማድረግ በፕሮፓጋንዳ ተጠቅመዋል። አዶልፍ ሂትለር አይሁዶችና ሌሎች አናሳ ቡድኖች “ወራዳ”፣ “እኩይ” እንዲሁም የመንግሥት “ጠላት” እንደሆኑ በመግለጽ በእነዚህ ዘዴዎች በተሳካ ሁኔታ ተጠቅሟል። እንደዚህ ያለው ማታለያ አስተሳሰባችሁን እንዲበክል ፈጽሞ አትፍቀዱ።—ሥራ 28:19-22

ራሳችሁን አትሸንግሉ

ከዚህም ሌላ ራሳችንን በቀላሉ ልንሸነግል እንችላለን። እንዲያውም በጥልቅ የምናምንባቸውን አመለካከቶች መተዉ ወይም ሌላው ቀርቶ ትክክለኛነታቸውን መጠራጠሩ እንኳ በጣም ሊከብደን ይችላል። ለምን? እንደዚህ ዓይነቶቹ አመለካከቶች ስሜታችንን ስለሚማርኩት ነው። በዚህም ምክንያት ከእውነት የራቁና አሳሳች የሆኑ እምነቶቻችንን ትክክል ለማስመሰል ሰበብ አስባብ በመደርደር ራሳችንን እንሸነግል ይሆናል።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች የዚህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። የአምላክን ቃል ቢያውቁም አስተሳሰባቸውን እንዲመራው ግን አልፈቀዱም። ከዚህም የተነሳ ሰንካላ ምክንያት በማቅረብ ‘ራሳቸውን አስተዋል።’ (ያዕቆብ 1:22, 26) እኛም በምናምንባቸው ነገሮች ላይ ጥያቄ ሲነሳ የምንናደድ ከሆነ በዚህ ዓይነቱ ራስን የመሸንገል ወጥመድ ተይዘን ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም ነው። በዚህ ወቅት ከመበሳጨት ይልቅ አመለካከታችን ትክክል እንደሆነ እርግጠኞች ብንሆንም እንኳ አእምሯችንን ክፍት ማድረጋችንና ሌሎች የሚናገሩትን በጥሞና ማዳመጣችን ጥበብ ይሆናል።—ምሳሌ 18:17

‘የአምላክን እውቀት’ ለማግኘት ቆፍሩ

ትክክለኛ አስተሳሰብ ለመያዝ ምን ማድረግ እንችላለን? በዚህ ረገድ ብዙ እርዳታ ያለልን ቢሆንም የራሳችንን ጥረት ለማከልም ፈቃደኛ መሆን ይኖርብናል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ ብሏል:- “ልጄ ሆይ፣ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፣ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፣ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፣ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፣ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።” (ምሳሌ 2:1-5) አዎን፣ አእምሯችንንና ልባችንን በአምላክ ቃል እውነት ለመሙላት በግላችን ጥረት ካደረግን ትክክለኛ ጥበብ፣ ማስተዋልና የማመዛዘን ችሎታ እናገኛለን። እንደዚህ በማድረግ ከብር ወይም ከማንኛውም ውድ ንብረት የበለጠ ዋጋ ያላቸውን ነገሮች ማግኘት እንችላለን።—ምሳሌ 3:13-15

ጥበብና እውቀት ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዲኖረን በመርዳት ረገድ ትልቅ ድርሻ አላቸው። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል:- “ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፣ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፤ ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፣ ማስተዋልም ይጋርድሃል፣ ከክፉ መንገድ አንተን ለማዳን፣ ጠማማ ነገርን ከሚናገሩም ሰዎች፤ እነርሱም በጨለማ መንገድ ይሄዱ ዘንድ የቀናውን ጎዳና የሚተዉ [ናቸው]።”—ምሳሌ 2:10-13

በተለይ ደግሞ የሚያስጨንቅ ወይም ለሕይወታችን አስጊ የሆነ ሁኔታ ሲያጋጥመን የአምላክ ሐሳብ አስተሳሰባችንን እንዲመራልን መፍቀዳችን በጣም አስፈላጊ ነው። እንደ ቁጣና ፍርሃት ያሉት ኃይለኛ ስሜቶች በትክክል ማሰብ እንዳንችል ያደርጉናል። ሰሎሞን “ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል” ብሏል። (መክብብ 7:7) አልፎ ተርፎም ‘በእግዚአብሔር ላይ ልንቆጣ’ እንችላለን። (ምሳሌ 19:3) እንዴት? ለሚደርሱብን ችግሮች አምላክን በማማረርና ከሕግጋቱና ከመሠረታዊ ሥርዓቶቹ ጋር የሚጋጩ ነገሮችን ለመፈጸም ይህንን ሰበብ በማድረግ ነው። ምንጊዜም ቢሆን የተሻለ እውቀት አለን ብለን ከማሰብ ይልቅ ቅዱሳን ጽሑፎችን በመጠቀም እኛን ለመርዳት የሚጥሩ አስተዋይ ሰዎች የሚሰጡንን ምክር በትሕትና እናዳምጥ። አስፈላጊ ከሆነም በጥልቅ የምናምንባቸው ነገሮች የተሳሳቱ እንደሆኑ ስናውቅ አስተሳሰባችንን ለመለወጥ ፈቃደኞች እንሁን።—ምሳሌ 1:1-5፤ 15:22

‘አምላክን ለምኑ’

የምንኖረው ግራ በሚያጋባና አደገኛ በሆነ ዘመን ውስጥ ነው። ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ እንዲኖረንና የጥበብ እርምጃ ለመውሰድ እንድንችል ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጠን አዘውትረን መጸለያችን አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ወይም ፈተናዎችን ለመወጣት የሚያስፈልገን ጥበብ እንደሚጎድለን ከተሰማን “ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን [መለመን]” ይኖርብናል።—ያዕቆብ 1:5-8

ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያን ባልንጀሮቹ ጥበብ እንደሚያስፈልጋቸው ስለተገነዘበ ‘ቅን አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ለማነቃቃት’ ፈልጎ ነበር። “ቅዱሳን ነቢያት የተናገሩትን ቃልና በሐዋርያቶቻችሁ አማካይነት ያገኛችሁትን የጌታችንንና የአዳኛችንን [የኢየሱስ ክርስቶስን] ትእዛዝ እንድታስታውሱ እፈልጋለሁ” ሲል ጽፎላቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:1, 2 የ1980 ትርጉም) እንደዚህ ካደረግንና አስተሳሰባችንን ከይሖዋ ቃል ጋር ካስማማን ትክክለኛ አስተሳሰብ በመያዝ የጥበብ እርምጃ መውሰድ እንችላለን።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች አስተሳሰባቸው በሰብዓዊ ፍልስፍና ሳይሆን በአምላካዊ ጥበብ እንዲመራ አድርገዋል

[ምንጭ]

ፈላስፎች ከግራ ወደ ቀኝ:- ኤፊቆሮስ:- Photograph taken by courtesy of the British Museum; ሲሴሮ:- Reproduced from The Lives of the Twelve Caesars; ፕላቶ:- Roma, Musei Capitolini

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጸሎትና የአምላክን ቃል ማጥናት አስፈላጊ ነገሮች ናቸው