በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኡጋሪት—የበኣል አምልኮ የገነነባት ጥንታዊት ከተማ

ኡጋሪት—የበኣል አምልኮ የገነነባት ጥንታዊት ከተማ

ኡጋሪት​—የበኣል አምልኮ የገነነባት ጥንታዊት ከተማ

በ1928 አንድ ሶርያዊ ገበሬ ማሳውን እያረሰ እያለ ማረሻው ከአንድ ድንጋይ ጋር ተጋጨ። ድንጋዩን ሲያነሳው ከሥሩ በነበረው መቃብር ውስጥ ጥንታዊ የሸክላ ዕቃዎች አገኘ። ገበሬው ይህ ግኝቱ ያን ያህል ጠቃሚ ነው ብሎ አላሰበም ይሆናል። ይህን ያልታሰበ ግኝት የሰማ በክሎድ ሻፌር የሚመራ አንድ የፈረንሳይ የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች ቡድን በቀጣዩ ዓመት ወደ አካባቢው ተጓዘ።

ብዙም ሳይቆይ ተመራማሪዎቹ በአካፋቸው ከሚዝቁት አፈር ሥር ያለችውን የፈራረሰች ከተማ ማንነት የሚጠቁም የተቀረጸ ጽሑፍ አገኙ። ከተማዋ ኡጋሪት ስትሆን “በመካከለኛው ምሥራቅ ከነበሩት ትላልቅ ጥንታዊ ከተሞች ውስጥ አንዷ ነበረች።” እንዲያውም ባሪ ሆበርማን የተባሉ ጸሐፊ “የትኛውም የአርኪኦሎጂ ግኝት ሌላው ቀርቶ የሙት ባሕር ጥቅልሎች እንኳን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ባለን ግንዛቤ ላይ የኡጋሪትን ያህል የጎላ ተጽዕኖ አላሳደረም” ብለዋል።—ዚ አትላንቲክ መንዝሊ

የንግድ መሥመሮችን የምታገናኝ ከተማ

በዛሬው ጊዜ የሶርያ ሰሜናዊ ክፍል በሆነው የሜዲትራንያን የባሕር ዳርቻ በሚገኝ ራስ ሻምራ በተባለ ጉብታ ውስጥ ተቀብራ ያለችው ኡጋሪት ከ3,000 ዓመታት በፊት ከተለያዩ የዓለም ክፍል የመጡ ሰዎች የሚኖሩባት የበለጸገች ከተማ ነበረች። የከተማይቱ ግዛት ከሰሜን ወደ ደቡብ ከቃስየስ ተራራ አንስቶ እስከ ቴል ሱቃስ ድረስ ያለውን 60 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ደግሞ ከሜዲትራንያን ባሕር እስከ ኦሮንተስ ሸለቆ ድረስ ያለውን ከ30 እስከ 50 የሚደርስ ኪሎ ሜትር ይሸፍናል።

ከወይና ደጋ የሚመደበው የኡጋሪት የአየር ሁኔታ ለእንስሳት እርባታ ምቹ ነበር። አካባቢው በጥራጥሬ እህሎች፣ በወይራ ዘይት፣ በወይን እንዲሁም በሜሶጶጣሚያና በግብፅ በእጅጉ በሚፈለገው የእንጨት ምርት የታወቀ ነበር። በተጨማሪም ከተማዋ የተቆረቆረችው የንግድ መሥመሮች በሚገናኙበት ቦታ ላይ ስለነበር ጥንታዊ ከሚባሉት ታላላቅ የወደብ ከተሞች አንዷ ለመሆን በቅታለች። ከኤጂያን ደሴቶች፣ ከአናቶሊያ፣ ከባቢሎን፣ ከግብፅና ከሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚመጡ ነጋዴዎች በኡጋሪት የብረት ማዕድናትን፣ የእርሻ ውጤቶችንና የከተማይቱ ምርት የሆኑ በርካታ ሸቀጣ ሸቀጦችን ይገበያዩ ነበር።

ኡጋሪት የበለጸገች ከተማ ብትሆንም ከቅኝ ግዛት ተላቅቃ አታውቅም። ከተማይቱ በ14ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በኬጢያውያን አገዛዝ ሥር እስከወደቀችበት ጊዜ ድረስ የግብፅ ሰሜናዊ ከተማ ነበረች። ኡጋሪት ለኬጢያውያኑ ግብር የመገበርና ወታደሮች መልምላ የማቅረብ ግዴታ ተጥሎባት ነበር። ለወረራ የተነሱት “የባሕር ሰዎች” a በአናቶሊያ (ማዕከላዊ ቱርክ) እና በሰሜናዊ ሶርያ ላይ ጥቃት በሰነዘሩ ጊዜ ኬጢያውያን የኡጋሪትን ወታደሮችና የጦር መርከቦች ለጦርነቱ ወስደው ነበር። በዚህም ምክንያት ኡጋሪት ራስዋን የምትከላከልበት ምንም ኃይል ስላልነበራት በ1200 ከዘአበ ሙሉ በሙሉ ጠፋች።

የጥንት ታሪክ ቆፍሮ ማውጣት

የኡጋሪት ከተማ ፍርስራሽ የሚገኘው ወደ 20 ሜትር የሚጠጋ ከፍታና 25 ሄክታር ስፋት ባለው ትልቅ ጉብታ ውስጥ ነው። ከዚህ ውስጥ እስከ አሁን ቁፋሮ የተካሄደበት አንድ ስድስተኛ ያህሉ ብቻ ነው። የከርሰ ምድር ተመራማሪዎቹ ከፍርስራሹ ውስጥ 10,000 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውና ወደ መቶ የሚጠጉ ክፍሎች እንዲሁም አደባባዮች ያሉት አንድ ትልቅ ቤተ መንግሥት አግኝተዋል። ቤተ መንግሥቱ የቧንቧ ውኃ፣ መጸዳጃ ቤቶችና የፍሳሽ ማስወገጃ አሉት። በውስጡ የነበሩት ዕቃዎች በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በዝሆን ጥርስ የተለበጡ ነበሩ። በረቀቀ ሁኔታ ከዝሆን ጥርስ የተቀረጹ የቤት ዕቃዎችም ተገኝተዋል። ቤተ መንግሥቱን ለማስዋብ ሲባል ዙሪያውን በግንብ የታጠረ የአትክልት ቦታና ሰው ሠራሽ ኩሬ ተሠርቶለት ነበር።

በከተማይቱ ውስጥ እንዲሁም በዙሪያዋ ባለው ሜዳ ላይ ለበኣል እና ለዳጋን b የተሠሩ ቤተ መቅደሶች በብዛት ይታያሉ። እስከ 20 ሜትር የሚደርስ ቁመት ያላቸው እነዚህ የቤተ መቅደስ ሕንጻዎች ጣዖቱ ወደሚቀመጥበት ውስጠኛ ክፍል የሚያደርስ ጠባብ መተላለፊያ አላቸው። ንጉሡ በተለያዩ ክብረ በዓላት ላይ ወደሚቀመጥበት ከፍ ያለ ሥፍራ የሚያደርስ ደረጃም አለ። በማታ ወይም ማዕበል በሚነሳባቸው ወቅቶች መርከቦች በሰላም ወደ ወደቡ እንዲደርሱ ለመርዳት በቤተ መቅደሶቹ አናት ላይ መብራት ይበራ ነበር። የማዕበል አምላክ በሆነው በበኣል ሃዳድ ቤተ መቅደስ ውስጥ 17 የድንጋይ መልሕቆች የተገኙ ሲሆን መርከበኞች በኣል ሃዳድ ጉዟቸውን ስላቃናላቸው በስዕለት ያገቧቸው ስጦታዎች እንደሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።

ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው የተቀረጹ ጽሑፎች

በኡጋሪት ፍርስራሾች ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የሸክላ ጽላቶች ተገኝተዋል። ኢኮኖሚያዊ፣ ሕግ ነክ፣ ዲፕሎማሲያዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱት እነዚህ ጽሑፎች አምስት የተለያዩ የፊደላት ዓይነቶችን በሚጠቀሙ ስምንት ቋንቋዎች የተቀረጹ ናቸው። ሻፌር የሚመሩት ቡድን ከዚህ በፊት በማይታወቅ ቋንቋ የተቀረጸ ጽሑፍም አግኝቷል። ኡጋሪት ተብሎ የተሰየመው ይህ ቋንቋ 30 የሚያህሉ የሽብልቅ ቅርጽ ያላቸው ፊደላት ያሉት ሲሆን እነዚህም እስከዛሬ ከተገኙት ጥንታዊ የሚባሉ ፊደላት መሃል የሚመደቡ ናቸው።

የኡጋሪት ጽሑፎች የዕለት ተዕለት ጉዳዮችን ከመዳሰሳቸውም ባሻገር በዘመኑ ስለነበረው ሃይማኖታዊ አስተሳሰብና ልማድ አዲስ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ናቸው። የኡጋሪት ሃይማኖት አጎራባች የሆኑት ከነዓናውያን ከሚከተሉት አምልኮ ጋር ከፍተኛ ተመሳሳይነት ነበረው። ሮናልድ ደ ቮ እንዳሉት እነዚህ ጽሑፎች “እስራኤላውያን ከነዓንን ድል አድርገው ከመያዛቸው በፊት የነበረውን የሥልጣኔ ደረጃ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው።”

በኡጋሪት የነበረው ሃይማኖት

በራስ ሻምራ ጽሑፎች ላይ ከ200 የሚበልጡ ተባዕትና እንስት አማልክት ተጠቅሰዋል። ኤል የእነዚህ አማልክት የበላይ ሲሆን የአማልክትና የሰዎች አባት ተብሎ ተጠርቷል። የማዕበል አምላክ የነበረው በኣል ሃዳድ ደግሞ “ዳመና ጋላቢ” እና “የምድር ጌታ” እንደሆነ ተደርጎ ይታመናል። ኤል ከሰዎች ርቆ በሚኖርና ጠቢብ በሆነ ነጭ ጢም ያለው አረጋዊ ተመስሏል። በሌላ በኩል በኣል አማልክትንና የሰው ልጆችን የመግዛት ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ብርቱ አምላክ ነው።

በቁፋሮው የተገኙት ጽሑፎች ዘመን መለወጫንና የመከር በዓልን በመሳሰሉ ሃይማኖታዊ በዓላት ላይ የሚደገሙ ሳይሆኑ አይቀሩም። ይሁን እንጂ ትክክለኛ ትርጉማቸው አይታወቅም። በኤልና በበኣል መካከል ስለነበረው የሥልጣን ሽኩቻ የሚናገር አንድ ግጥም በኣል የኤል ተወዳጅ ልጅ የሆነውን ያም የተባለ የባሕር አምላክ እንዳሸነፈው ይገልጻል። ይህ ድል የኡጋሪት መርከበኞች በጉዟቸው ላይ በኣል እንደሚጠብቃቸው እንዲተማመኑ ሳያደርጋቸው አልቀረም። በኣል ሞት ከተባለው አምላክ ጋር ባደረገው ፍልሚያ ይሸነፍና ወደ ጥልቁ ይወርዳል። በዚህም ምክንያት ድርቅ በመከሰቱ የሰዎች እንቅስቃሴ ይገታል። የበኣል ሚስትና እህት የሆነችው አናት የተባለች የፍቅርና የጦርነት አምላክ ሞትን ትገድለውና ለበኣል ሕይወት ትሰጠዋለች። በኣል የኤል ሚስት የሆነችውን የአቲራትን (አሺራ) ልጆች ጠራርጎ ያጠፋና ዙፋኑን መልሶ ይቆጣጠራል። ሆኖም ሞት ከሰባት ዓመት በኋላ ተመልሶ ይመጣል።

አንዳንዶች ይህ ግጥም የሕይወት ምንጭ የሆነው ዝናብ በበጋው ሐሩራማ ሙቀት ተሸንፎ የሚሄድበትና በመከር ወቅት ተመልሶ የሚመጣበትን ዓመታዊ የወቅቶች መፈራረቅ የሚያሳይ ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ በየሰባት ዓመቱ ረሃብና ድርቅ ይመጣል ከሚለው ፍራቻ ጋር ያያይዙታል። የግጥሙ ትርጉም ምንም ይሁን ምን የበኣል የበላይነት ለሰዎች ስኬታማነት አስፈላጊ እንደሆነ ተደርጎ ይታመን ነበር። ፒተር ክሬት የተባሉ አንድ ምሑር እንዲህ ብለዋል:- “የበኣል አምልኮ ዋነኛ ዓላማ የእርሱን የበላይነት ማስጠበቅ ነበር። እንደ አምላኪዎቹ እምነት ከሆነ ለሰዎች ሕልውና በጣም አስፈላጊ የሆኑት ሰብሎችና እንስሳት ሊኖሩ የሚችሉት በኣል የበላይ እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው።”

ከጣዖት አምልኮ የሚጠብቅ ግድግዳ

በቁፋሮው የተገኙት ጽሑፎች የኡጋሪት ሃይማኖት ልቅነት የሚንጸባረቅበት እንደነበር በግልጽ ያሳያሉ። ዚ ኢለስትሬትድ ባይብል ዲክሽነሪ እንዲህ ይላል:- “ጽሑፎቹ በጦርነት፣ በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ በሚፈጸመው ዝሙትና የጾታ ፍላጎትን መሠረት ባደረገ ፍቅር ላይ ያተኮሩ መሆናቸው ለእነዚህ አማልክት የሚቀርበው አምልኮ አስነዋሪ ብሎም ወራዳ እንደነበርና ይህም ያስከተለውን ማኅበራዊ ዝቅጠት ያሳያሉ።” ደ ቮ “እነዚህን ግጥሞች ያነበበ ሰው የያህዌህ እውነተኛ አምላኪዎችና ታላላቆቹ ነቢያት ለእንዲህ ዓይነቱ አምልኮ የነበራቸውን ጥላቻ በግልጽ ይገነዘባል” ብለዋል። አምላክ ለጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ የሰጠው ሕግ ከእንዲህ ዓይነቱ የሐሰት አምልኮ የሚጠብቅ ግድግዳ ነበር።

ጥንቆላ፣ ኮከብ ቆጠራና አስማት በኡጋሪት በሰፊው የሚዘወተሩ ድርጊቶች ነበሩ። መልካም ወይም መጥፎ ገዶችን ያሳያሉ የሚባሉ ምልክቶችን ለማግኘት የሰማይ አካላትን ብቻ ሳይሆን አካለ ጎደሎ የሆኑ ሽሎችንና የታረዱ እንስሳትን የውስጥ አካላት ይመለከቱ ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ዣኩሊን ጋሼ እንዲህ ይላሉ:- “አምላካቸው መሥዋዕት ሆኖ ከቀረበለት እንስሳ ጋር እንደሚጣመርና መንፈሱ ከእንስሳው መንፈስ ጋር እንደሚዋሃድ ያምኑ ነበር። ስለዚህ በእንስሳው የውስጥ አካላት ላይ ያሉትን ምልክቶች በማየት አማልክቱ ስለ ወደፊቱ ጊዜና አንድ ጉዳይ ሲያጋጥም ምን መደረግ እንዳለበት ለሚቀርብላቸው ጥያቄ የሚሰጡትን መልስ ማወቅ ይቻላል።” (ለ ፔዪ ዱጋሪ ኦቱር ደ 1200 አቮ ዤ. ክ.) በአንጻሩ ግን እስራኤላውያን እንዲህ ካሉ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ተነግሯቸው ነበር።—ዘዳግም 18:9-14

የሙሴ ሕግ ከእንስሳት ጋር የሚደረግ ግንኙነትን በግልጽ ይከለክላል። (ዘሌዋውያን 18:23) የኡጋሪት ነዋሪዎች ለእንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እንዴት ያለ አመለካከት ነበራቸው? በቁፋሮ የተገኙት ጽሑፎች በኣል ከጊደር ጋር ግንኙነት እንዳደረገ ይገልጻል። የከርሰ ምድር ተመራማሪው ሳይረስ ጎርዶን “በኣል እንዲህ ለማድረግ ሲፈልግ ወይፈን ይሆናል ቢባል እንኳ የእርሱን ድርጊት አስመስለው ይፈጽሙ የነበሩት ካህናት እንደ እርሱ መሆን ይችላሉ ማለት ግን የማይመስል ነው” ብለዋል።

እስራኤላውያን “ስለ ሞተውም ሥጋችሁን አትንጩ” የሚል ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 19:28) ይሁን እንጂ በኣል በሞተ ጊዜ ኤል “ገላውን በካራና በምላጭ ቆራርጧል፤ እንዲሁም ጉንጩንና አገጩን ተልትሏል።” የበኣል አምላኪዎች በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ገላቸውን መተልተላቸው የተለመደ ነበር።—1 ነገሥት 18:28

ከነዓናውያን በመራባት አምልኮታዊ ሥርዓት ላይ የፍየል ግልገልን በወተት ይቀቅሉ እንደነበር አንድ የኡጋሪት ግጥም ይጠቁማል። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን በሙሴ ሕግ ላይ “ጠቦት ፍየልን በእናቱ ወተት አትቀቅል” ተብለው ታዘው ነበር።—ዘጸአት 23:19 አ.መ.ት

የኡጋሪት ጽሑፎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሲነጻጸሩ

የኡጋሪት ጽሑፎች በመጀመሪያ የተተረጎሙት መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት የዕብራይስጥ ቋንቋ በመታገዝ ነበር። ፒተር ክሬግ እንዲህ ብለዋል:- “በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ትርጉማቸው ግልጽ ያልሆነ አንዳንዴም ጨርሶ የማይታወቅ በርካታ ቃላት ነበሩ። ከ20ኛው መቶ ዘመን በፊት የነበሩት ተርጓሚዎች የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ትርጉማቸውን ለመገመት ሞክረው ነበር። ሆኖም በኡጋሪት ጽሑፎች ውስጥ ተመሳሳይ ቃላት በመገኘታቸው የእነዚህን ቃላት ፍቺ ማወቅ ተችሏል።”

ለምሳሌ ያህል በኢሳይያስ 3:18 ላይ የሚገኝ አንድ ቃል “መርበብ” ተብሎ ይተረጎም ነበር። ተመሳሳዩ የኡጋሪት ቃል ፀሐይንና የፀሐይን እንስት አምላክ ያመለክታል። ስለዚህ በኢሳይያስ ትንቢት ላይ የተጠቀሱት የኢየሩሳሌም ቆነጃጅት ለከነዓናውያን አማልክት ክብር ሲሉ ‘ጨረቃ ከሚመስለው ጌጥ’ በተጨማሪ የፀሐይ ቅርጽ ባለበት ድሪ ያጌጡ ነበር።

በማሶራውያን የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂ ላይ “ክፋት በልቡ ሳለ ፍቅርን የሚናገር ከንፈር በብር ዝገት” በተለበጠ የሸክላ ዕቃ ተመስሏል። (ምሳሌ 26:23) ተመሳሳዩ የኡጋሪት ቃል ይህ ጥቅስ “የሚያብረቀርቅ ነገር እንደተቀባ የሸክላ ዕቃ ስባሪ” ተብሎ ሊተረጎም እንደሚችል ይጠቁማል። የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ይህን ምሳሌ “ክፋትን በልቡ ቋጥሮ ለስላሳ ቃል የሚናገር ከንፈር ብር ቅብ እንደሆነ የሚያብረቀርቅ የሸክላ ዕቃ ስባሪ ነው” በማለት በትክክል ተርጉሞታል።

የኡጋሪት ጽሑፎች ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ነበሩ?

የራስ ሻምራ ጽሑፎችን የመረመሩ አንዳንድ ምሑራን የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከኡጋሪት ጽሑፎች ላይ የተወሰዱ እንደሆኑ ይናገራሉ። የፈረንሳይ ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑት አንድሬ ካኮ “ለእስራኤላውያን ሃይማኖት መሠረት የሆነው የከነዓናውያን ባሕል” ነው ብለዋል።

በሮም በሚገኘው የጳጳሳት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተቋም አባል የሆኑት ሚቸል ዳሁድ መዝሙር 29ን በሚመለከት እንዲህ ብለዋል:- “ይህ መዝሙር ጥንት ከነዓናውያን የማዕበል አምላክ የሆነውን በኣልን ለማወደስ ይጠቀሙበት ከነበረው መዝሙር ተቀድቶ ለያህዌህ እንዲስማማ ተደርጎ የተቀናበረ ነው። . . . የመዝሙሩ እያንዳንዱ ቃል ማለት ይቻላል ጥንታዊ በሆኑ የከነዓናውያን ጽሑፎች ውስጥ ይገኛል።” ይህ አባባል ትክክል ነውን? በፍጹም!

ለዘብተኛ የሆኑ ምሑራን በመጽሐፍ ቅዱስና በኡጋሪት ጽሑፎች መካከል ያሉት መመሳሰሎች እንደተጋነኑ ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ኡጋሪትን ከፍ ከፍ የማድረግ አዝማሚያ ነው በማለት ነቅፈውታል። ጋሪ ብራንትሌይ የተባሉ የሃይማኖት ምሑር “ከመዝሙር 29 ጋር ሙሉ በሙሉ የሚመሳሰል አንድም የኡጋሪት ጽሑፍ የለም። መዝሙር 29 (ወይም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል) ከአረማዊ ታሪክ የተወሰደ ነው የሚለው አመለካከት ምንም የተጨበጠ ማስረጃ የለውም” ብለዋል።

በምሳሌያዊ አባባሎች፣ በግጥሞችና በአጻጻፍ ዘይቤዎች ተመሳሳይነት መኖሩ መጽሐፍ ቅዱስ ከኡጋሪት ጽሑፎች የተወሰደ ነው ለማለት ያስደፍራል? በፍጹም! እንዲያውም እንዲህ ያለው ተመሳሳይነት የሚጠበቅ ነው። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን እንዲህ ይላል:- “ለአጻጻፍና ለይዘት መመሳሰል ምክንያት የሆነው ባሕል ነው፤ በኡጋሪትና በእስራኤል መካከል ያለው የመልክዓ ምድርና የዕድሜ ልዩነት ጥቂት የማይባል ቢሆንም ሁለቱም የጋራ የሆነ ሥነ ጥበባዊና ሃይማኖታዊ ቃላት ይጠቀሙ እንደነበር መዘንጋት አይኖርብንም።” በመሆኑም ጋሪ ብራንትሌይ “የአገላለጽ ተመሳሳይነት ስላለ ብቻ አረማዊ እምነቶች ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሆነዋል ማለቱ ተገቢ አይደለም” በማለት ደምድመዋል።

በመጨረሻም በራስ ሻምራ ጽሑፎችና በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል አንድ ዓይነት ተመሳሳይነት ቢኖር እንኳን የአጻጻፍ እንጂ የሃይማኖታዊ እምነት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባዋል። የከርሰ ምድር ተመራማሪው ሳይረስ ጎርዶን “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የላቀ የሥነ ምግባር ደረጃ በኡጋሪት ጽሑፎች ውስጥ ፈጽሞ አይገኝም” ብለዋል። በእርግጥም በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ከሚያመሳስላቸው ነገር በእጅጉ ይበልጣል።

በኡጋሪት ላይ የሚደረገው ጥናት ወደፊትም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን ስለነበረው ባሕላዊ፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ሁኔታ እንዲሁም በጥቅሉ ስለ እስራኤል ብሔር ያላቸውን ግንዛቤ እንደሚያሰፋላቸው ምንም ጥርጥር የለውም። በራስ ሻምራ ጽሑፎች ላይ የሚደረገው ቀጣይነት ያለው ጥናት ስለ ጥንታዊው የዕብራይስጥ ቋንቋ ተጨማሪ የእውቀት ብርሃን ይፈነጥቅ ይሆናል። ከሁሉም በላይ ግን የኡጋሪት አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች ወራዳ በነበረው የበኣል አምልኮና በይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መካከል ያለውን ልዩነት በጉልህ ያሳያሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a “የባሕር ሰዎች” የተባሉት ከሜዲትራንያን ደሴቶችና ከጠረፍ አገሮች የተነሱ ባሕረተኞች ነበሩ። ከእነዚህ መካከል ፍልስጥኤማውያን ሳይኖሩበት አይቀርም።—አሞጽ 9:7

b ምንም እንኳን በጉዳዩ ላይ የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም አንዳንዶች ቤተ መቅደሱ የዳጋን ሳይሆን የኤል ነው ይላሉ። በኢየሩሳሌም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት ፈረንሳዊው ምሁር ሮናልድ ደ ቮ በመሳፍንት 16:23 እና በ1 ሳሙኤል 5:1-5 ላይ ዳጎን ተብሎ የተጠራው ዳጋን የኤል መጠሪያ ስም ነው የሚል ሐሳብ አላቸው። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን “ዳጋን እና ኤል አንድ ዓይነት ዝምድና” ሳይኖራቸው እንደማይቀር ይናገራል። በራስ ሻምራ ጽሑፎች ላይ በኣል የዳጋን ልጅ ተብሎ ተጠርቷል። ቢሆንም “ልጅ” የሚለው ቃል ምን እንደሚያመለክት ግልጽ አይደለም።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የኡጋሪት አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች ያለንን ግንዛቤ አስፍተውልናል

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የኬጢያውያን ግዛት በ14ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ

የሜዲትራንያን ባሕር

ኤፍራጥስ

የቃስየስ ተራራ (ጄቤል ኤል-አግራ)

ኡጋሪት (ራስ ሻምራ)

ቴል ሱቃስ

ኦሮንተስ

ሶርያ

ግብፅ

[ምንጭ]

የበኣል ሐውልት እና በእንስሳ ጭንቅላት ቅርፅ የተሠራ መጠጫ:- Musée du Louvre, Paris; ቤተ መንግሥቱን የሚያሳይ ሥዕል:- © D. Héron-Hugé pour “Le Monde de la Bible”

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቤተ መንግሥቱ መግቢያ ፍርስራሽ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ የኡጋሪት ሃይማኖታዊ ግጥም በዘጸአት 23:19 (አ.መ.ት) ላይ የሚገኘው ትእዛዝ የተሰጠበትን ምክንያት እንድንረዳ ያስችለናል

[ምንጭ]

Musée du Louvre, Paris

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለበኣል የቆመ ሐውልት

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንስሳ ሲታደን የሚያሳይ የወርቅ ሳህን

የመራባት እንስት አምላክን የሚያሳይ ከዝሆን ጥርስ የተሠራ መኳኳያ ማስቀመጫ ክዳን

[ምንጭ]

ሥዕሎቹ በሙሉ የተወሰዱት:- Musée du Louvre, Paris