በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትዕግሥትና ጽናት ያስገኙት አስደሳች ውጤት

ትዕግሥትና ጽናት ያስገኙት አስደሳች ውጤት

የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት

ትዕግሥትና ጽናት ያስገኙት አስደሳች ውጤት

ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው ዘመን ‘የብዙ ሰዎች ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ’ አስቀድሞ ተናግሯል። በመሆኑም ዛሬ በብዙ የዓለም ክፍሎች ሰዎች በአጠቃላይ ለመንግሥቱ ምሥራች ግድየለሾች ናቸው። እንዲያውም አንዳንዶች ለሃይማኖት ከፍተኛ ጥላቻ አላቸው።—ማቴዎስ 24:12, 14

ያም ሆኖ ከቼክ ሪፑብሊክ የተገኘው የሚከተለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው የመንግሥቱ አስፋፊዎች በእምነትና በትዕግሥት ይህንን ፈታኝ ሁኔታ መወጣት ችለዋል።

ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ አንድ ቤት ያንኳኳሉ። በቤቱ ውስጥ ያለችው ሴት ከውስጥ ሆና ታዳምጣቸው የነበረ ቢሆንም በሯን ግን አልከፈተችም። ብዙም ሳይቆይ ሴትዮዋ በሩን በትንሹ ከፈተችና እጅዋን አሾልካ ምሥክሮቹ የሚያበረክቱትን የመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ከወሰደች በኋላ “አመሰግናለሁ” ብላ በሩን ዘጋችው። ምሥክሮቹ ግራ በመጋባት “ተመልሰን መምጣት ይኖርብን ይሆን?” ብለው አሰቡ። አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነችው አንደኛዋ የይሖዋ ምሥክር ተመልሳ ለመሄድ ወሰነች። ሆኖም ሴትዮዋ ያነጋገረቻት ልክ እንደ መጀመሪያው ጊዜ በሯን ሳትከፍት ነበር። ለአንድ ዓመት ያህል በዚህ መንገድ መነጋገራቸውን ቀጠሉ።

አቅኚዋ እህት አቀራረቧን መቀየር እንዳለባት በማሰብ ይሖዋ እንዲረዳት ጸለየች። በሚቀጥለው ጊዜ ለሴትዮዋ መጽሔቶቹን ስትሰጣት “እንደምን ነሽ? እንዴት ነው፣ መጽሔቶቹን ወደድሻቸው?” በማለት በወዳጅነት ልታነጋግራት ሞከረች። መጀመሪያ ላይ ሴትዮዋ ምንም መልስ አልሰጠችም። በዚህ መንገድ ለተወሰነ ጊዜ ያህል እየተመላለሰች ካነጋገረቻት በኋላ ግን ሴትዮዋም አንዳንድ ሐሳቦች መሰንዘር ጀመረች። አንድ ቀን በሩን በደንብ ከፈተችው፤ ሆኖም ውይይታቸው አጭር ነበር።

አቅኚዋ እህት በር ላይ ቆሞ መነጋገሩን ሴትዮዋ ብዙም እንዳልወደደችው ስለተሰማት የምትመጣበትን ዓላማና በነጻ መጽሐፍ ቅዱስ ልታስጠናት እንደምትችል የሚገልጽ ደብዳቤ ልትጽፍላት አሰበች። አቅኚዋ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ያህል በትዕግሥት ጥረት ካደረገች በኋላ በመጨረሻ ሴትዮዋ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። ከጊዜ በኋላ ይህቺ ሴት “መጽሔቶቹን ማምጣት ከጀመርሽበት ጊዜ ጀምሮ በአምላክ አምን ነበር” ብላ ስትነግራት እህት በሁኔታው ብትገረምም ባገኘችው ውጤት ተበረታትታለች።

በእርግጥም፣ በመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በትዕግሥትና በጽናት መካፈል አስደሳች ውጤት ሊያስገኝ ይችላል።—ማቴዎስ 28:19, 20