በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ አምላኩ የሆነለት ሰው ደስተኛ ነው

ይሖዋ አምላኩ የሆነለት ሰው ደስተኛ ነው

የሕይወት ታሪክ

ይሖዋ አምላኩ የሆነለት ሰው ደስተኛ ነው

ቶም ዲደር እንደተናገረው

የማዘጋጃ ቤቱን አዳራሽ አስቀድመን ተከራይተነው ነበር። በካናዳ ሳስካችዋን ክፍለ ሀገር በሚገኘው በፖርኩፓይን ፕሌይን በሚካሄደው የወረዳ ስብሰባ ላይ 300 ገደማ ተሰብሳቢዎች እንደሚገኙ ጠብቀን ነበር። ረቡዕ ዕለት መጣል የጀመረው በረዶ ዓርብ ላይ በጣም በመባባሱ የተነሳ ምንም ነገር ማየት አይቻልም። ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች ወደ 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ወረደ። ጥቂት ልጆችን ጨምሮ ስብሰባው ላይ 28 ሰዎች ተገኝተው ነበር። የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ የስብሰባውን ዝግጅት በበላይነት ስቆጣጠር ይህ የመጀመሪያዬ መሆኑ ነው። በወቅቱ የ25 ዓመት ወጣት ስሆን ኃላፊነቱም አስጨንቆኝ ነበር። ስብሰባው የተካሄደበትን መንገድ ከመናገሬ በፊት በዚህ ልዩ የአገልግሎት መብት ለመካፈል እንዴት እንደበቃሁ ልንገራችሁ።

በቤተሰባችን ካለነው ስምንት ልጆች መካከል እኔ ሰባተኛው ስሆን ሁላችንም ወንዶች ነበርን። የመጀመሪያው ቢል ሲሆን የእርሱ ተከታዮች ሜትሮ፣ ጆን፣ ፍሬድ፣ ማይክና አሌክስ ናቸው። እኔ የተወለድኩት በ1925 ነው፤ ከእኔ ቀጥሎ የተወለደው ደግሞ ዋሊ ይባላል። የምንኖረው በማኒቶባ ክፍለ ሃገር ኡክሬና ከተማ አቅራቢያ ሲሆን ወላጆቻችን ማይክልና አና ዲደር አነስ ያለ የእርሻ ቦታ ነበራቸው። አባቴ የምድር ባቡር ሠራተኛ ሲሆን በአንድ ጣቢያ ላይ ተመድቦ ይሠራ ነበር። ከከተማ ርቀው በሚገኙ ባቡር ጣቢያዎች ላይ ያሉት የሠራተኛ መኖሪያ ቤቶች ትልቅ ቤተሰብ ለማኖር አመቺ ባለመሆናቸው እኛ በእርሻ ቦታው ቀረን። አብዛኛውን ጊዜ አባባ እቤት ስለማይኖር እኛን የማሳደጉ ኃላፊነት የወደቀው እናታችን ላይ ነበር። አልፎ አልፎ አባባ ጋር ሄዳ አንድ ሳምንት ወይም ከዚያ የሚበልጥ ጊዜ ትቆይ ነበር። በዚህም ምክንያት ምግብ ማብሰል፣ መጋገርና የቤት ውስጥ ሥራዎችን አስተምራናለች። የግሪክ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ስለነበርን እማማ አንዳንድ ጸሎቶችን በአእምሯችን እንድንይዝና በሌሎች የአምልኮ ሥርዓቶች ተሳትፎ እንድናደርግም በልጅነታችን አሠልጥናናለች።

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አገኘሁ

መጽሐፍ ቅዱስን የማወቅ ፍላጎት ያደረብኝ ገና በልጅነቴ ነው። የይሖዋ ምሥክር የሆነ ጎረቤታችን በየጊዜው ቤታችን እየመጣ ስለ አምላክ መንግሥት፣ ስለ አርማጌዶንና በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ ስለሚገኙት በረከቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ያነብብልን ነበር። ምሥክሩ የሚናገረው ነገር እማዬን ፈጽሞ ባይማርካትም ማይክና አሌክስ ግን ትምህርቱን ወደዱት። እንዲያውም ከተማሩት ነገር በመነሳት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በሕሊናቸው ምክንያት የውትድርና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። ከዚህም የተነሳ ማይክ ለአጭር ጊዜ እስራት ሲፈረድበት አሌክስ ደግሞ በኦንታሪዮ ወደሚገኘው የጉልበት ሥራ ካምፕ ተላከ። ከጊዜ በኋላ ፍሬድና ዋሊም እውነትን ተቀበሉ። ይሁን እንጂ ሦስቱ ታላላቅ ወንድሞቼ እውነትን ሳይቀበሉ ቀርተዋል። እማዬ ለበርካታ ዓመታት እውነትን ስትቃወም ብትኖርም ከጊዜ በኋላ ግን ይሖዋን ለማገልገል መወሰኗ ሁላችንንም አስገረመን፤ ከዚያም በ83 ዓመቷ ተጠመቀች። እማዬ የሞተችው በ96 ዓመቷ ነው። አባባም ከመሞቱ በፊት ለእውነት ቀና አመለካከት ይዞ ነበር።

የ17 ዓመት ልጅ ሳለሁ ሥራ ፍለጋና መጽሐፍ ቅዱስ ሊያስጠኑኝ የሚችሉ ሰዎች በቅርብ ለማግኘት ወደ ዊኒፔግ ሄድኩ። በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ የታገደ ቢሆንም ስብሰባዎች በቋሚነት ይደረጉ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ስብሰባ ላይ የተገኘሁት በአንድ የግለሰብ መኖሪያ ቤት ነው። ያደግሁት የግሪክ ካቶሊክ እምነት ተከታይ ሆኜ ስለነበር መጀመሪያ ላይ የሰማሁት ነገር እንግዳ ሆነብኝ። ይሁንና ቀሳውስትና ምዕመናን የሚለው ሥርዓት ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነበት ምክንያትና ቄሶች ለጦርነት ቡራኬ መስጠታቸው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ለምን እንደሆነ ቀስ በቀስ ግልጽ እየሆነልኝ መጣ። (ኢሳይያስ 2:4፤ ማቴዎስ 23:8-10፤ ሮሜ 12:17, 18) የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ርቆ ወደሚገኝ ቦታ ከመሄድ ይልቅ በምድር ላይ በገነት መኖር ይበልጥ አሳማኝና ምክንያታዊ ሆኖ ታየኝ።

ይህ እውነት መሆኑን ስላመንኩ ራሴን ለይሖዋ ወስኜ በ1942 በዊኒፔግ ተጠመቅሁ። በ1943 ካናዳ ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ የተነሳ ሲሆን የስብከቱ ሥራም በስፋት መካሄድ ጀመረ። በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ ያለኝ እምነትም ይበልጥ ሥር እየሰደደ ሄደ። በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የማገልገል፣ በክልሉ ውስጥ የሚካሄዱ የሕዝብ ስብሰባዎችን የማስተባበርና ለየትኛውም ጉባኤ ባልተመደቡ ክልሎች የማገልገል መብት አግኝቻለሁ። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተካሄዱ ትልልቅ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ መገኘቴ ለመንፈሳዊ ዕድገቴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ለይሖዋ የማቀርበውን አገልግሎት ማስፋት

በ1950 አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ፤ በዚያው ዓመት ታኅሣሥ ላይ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ግብዣ ቀረበልኝ። ለዚህ አገልግሎት ያሠለጠነኝ (ቶሮንቶ አቅራቢያ) ቻርሊ ሄፕዎርዝ የተባለ ታማኝና ጥሩ ልምድ ያለው ወንድም በመሆኑ በጣም ተጠቅሜያለሁ። የሥልጠናውን የመጨረሻ ሳምንት ደግሞ ዊኒፔግ ውስጥ የወረዳ የበላይ ተመልካች ከነበረው ከወንድሜ ከአሌክስ ጋር ማሳለፌ አስደስቶኛል።

መግቢያው ላይ እንደገለጽኩት ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀሁት የወረዳ ስብሰባ ፈጽሞ ከአእምሮዬ አይጠፋም። አዲስ እንደመሆኔ መጠን የስብሰባው መሳካት በጣም አሳስቦኝ ነበር። የአውራጃ የበላይ ተመልካቻችን ወንድም ጃክ ኔታን ሁላችንም ተሳትፎ እንዲኖረን ያደረገ ሲሆን ጊዜውን በደስታ እንድናሳልፍም አስችሎናል። በስብሰባው ላይ ለተገኙት አድማጮች የዕለቱን ፕሮግራም በአጭሩ አቀረብንላቸው። ተሞክሮ በመናገር፣ ከቤት ወደ ቤት ማገልገልንና ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግን በመለማመድ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚመራበትን መንገድ በሠርቶ ማሳያ በማቅረብ በየተራ ተሳትፎ አደረግን። መዝሙሮችም ዘመርን። ብዙ ምግብ ስለነበር በየሁለት ሰዓቱ ማለት ይቻላል ብስኩትና ቡና ይቀርብ ነበር። አንዳንዶች አግዳሚ ወንበሮችና መድረኩ ላይ ሲተኙ ሌሎች ደግሞ መሬት ላይ ተኙ። እሁድ ዕለት በረዶ የቀላቀለው ወዠብ ጋብ በማለቱ ሕዝብ ንግግሩ ላይ 96 ሰዎች ሊገኙ ችለዋል። ይህ አጋጣሚ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዴት መወጣት እንደምችል ትምህርት ሰጥቶኛል።

ቀጥሎ የተመደብኩበት ወረዳ እስከ እኩለ ሌሊት ፀሐይ የሚያገኙትን ሰሜናዊውን አልቤርታ፣ ብሪቲሽ ኮሎምቢያን እና ዩኮን ቴሪተሪን ያጠቃልል ነበር። በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ከሚገኘው ከዶውሰን ክሪክ አንስቶ እስከ ዋይትሆርስ፣ ዩኮን ድረስ (1,477 ኪሎ ሜትር ርቀት ይሸፍናል) ወጣ ገባ በሆነው የአላስካ አውራ ጎዳና ላይ በመኪና መጓዝና በጉዞ ላይ ምሥክርነት መስጠት ጽናትና ጥንቃቄ ይጠይቃል። ከበረዶ ናዳውና ከሚያንሸራትተው ቁልቁለት በተጨማሪ ዕይታን የሚጋርደው ንፋስ ቀላቅሎ የሚጥለው በረዶ ጉዞውን በጣም አስቸጋሪ ያደርጉታል።

እውነት እስከ አላስካ ድረስ ዘልቆ መግባቱን ሳውቅ በጣም ተገረምኩ። በአንድ አጋጣሚ እኔና ዎልተር ሉኮዊትስ በአላስካ አውራ ጎዳና ላይ ከዩኮን ቴሪተሪ ድንበር ብዙም ሳይርቅ በብሪቲሽ ኮሎምቢያ የሚገኘው ሎወር ፖስት አቅራቢያ አንዲት ቤት አንኳኳን። በመስኮቱ በኩል የብርሃን ጭላንጭል ስላየን ቤቱ ውስጥ ሰው እንደሚኖር አወቅን። ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ገደማ ይሆናል፤ በሩን ስናንኳኳ ከውስጥ አንድ ሰው ግቡ ስላለን ወደ ቤቱ ገባን። አንድ አረጋዊ ሰው አልጋቸው ላይ ጋደም ብለው መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ሲያነብቡ ስናይ ማመን አቃተን! እንዲያውም መጠበቂያ ግንቡ እኛ ለማበርከት ከያዝነው በኋላ የወጣ እትም ነበር። መጽሔቱ የሚደርሳቸው በአየር መሆኑን ነገሩን። ከጉባኤ ከወጣን ከስምንት ቀናት በላይ ሆኖን ስለነበር አዲስ የወጡት መጽሔቶች ገና አልደረሱንም። ሰውዬው ፍሬድ በርግ እንደሚባሉ ነገሩን። ለበርካታ ዓመታት የመጽሔት ኮንትራት የነበራቸው ቢሆንም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው። ሰውዬው እዚያው እንድናድር አደረጉን። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን የማካፈል አጋጣሚ ያገኘን ከመሆኑም ሌላ በየጊዜው በዚያ አካባቢ የሚያልፉ ሌሎች ምሥክሮች እንዲጠይቋቸው ዝግጅት አደረግን።

ለበርካታ ዓመታት የጎበኘሁት ሦስት ትናንሽ ወረዳዎችን ነበር። እነዚህ ወረዳዎች በስተ ምሥራቅ በኩል ከግራንድ ፕሬይሪ፣ አልቤርታ አንስቶ በስተ ምዕራብ በኩል በአላስካ እስከሚገኘው ኮዲያክ ድረስ ከ3,500 ኪሎ ሜትሮች በላይ ይሸፍናሉ።

እንደ ማንኛውም ቦታ ሁሉ በጣም ርቀው በሚገኙ ቦታዎችም ሳይቀር የይሖዋ የማይገባ ደግነት ለሰዎች ሁሉ የተዘረጋ መሆኑንና የአምላክ መንፈስ ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ ሰዎችን አእምሮና ልብ ሊያነሳሳ እንደሚችል ማየቴ እጅግ አስደስቶኛል። አሁን ዶውሰን ተብላ በምትጠራው በዶውሰን ሲቲ፣ ዩኮን ይኖሩ የነበሩት ሄነሪ ለፓይን ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው ግለሰብ ነበሩ። የሚኖሩት በገለልተኛ አካባቢ ሲሆን ከ60 ለሚበልጡ ዓመታት ወርቅ ከሚወጣበት አካባቢ ወዴትም ሄደው አያውቁም። እኚህ የ84 ዓመት አዛውንት በጉባኤ ስብሰባ ላይ ፈጽሞ ተገኝተው ባያውቁም እንኳ በአንኮሬጅ በሚካሄድ የወረዳ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ሲሉ ከ1,600 ኪሎ ሜትር በላይ እንዲጓዙ የአምላክ መንፈስ አነሳስቷቸዋል። በትምህርቱ የረኩ ከመሆኑም በላይ ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር በነበራቸው ግንኙነት በጣም ተደስተዋል። ሄነሪ ወደ ዶውሰን ሲቲ ከተመለሱ በኋላ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ታማኝነታቸውን ጠብቀው ኖረዋል። ሄነሪን የሚያውቋቸው ብዙ ሰዎች ይህን ያህል ርቀት ለመጓዝ የተነሳሱበትን ምክንያት ለማወቅ ፈለጉ። ይህም በዕድሜ የገፉ ጥቂት ሰዎች እውነትን እንዲቀበሉ መንገድ ከፍቷል። በመሆኑም ሄነሪ በተዘዋዋሪ መንገድ ግሩም ምሥክርነት መስጠት ችለዋል።

ይሖዋ የማይገባ ደግነት አድርጎልኛል

በ1955 በመጠበቂያ ግንብ የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 26ኛ ክፍል እንድሳተፍ መጋበዜ በጣም አስደሰተኝ። በትምህርት ቤቱ ያገኘሁት ሥልጠና እምነቴን ያጠናከረልኝ ሲሆን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድቀርብም ረድቶኛል። ከተመረቅሁ በኋላ ካናዳ ውስጥ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ማገልገሌን እንድቀጥል ተመደብኩ።

ለአንድ ዓመት ያህል በኦንታሪዮ ክፍለ ሃገር አገለገልኩ። ከዚያም ውብ በሆነው በአላስካ እንዳገለግል በድጋሚ ተመደብኩ። በየመንገዱ ዳር ያሉ ዓይን የሚማርኩ፣ የጠሩና አንጸባራቂ ሐይቆች እንዲሁም በመኪና እጓዝባቸው የነበሩት አናታቸው በበረዶ የተሸፈነ እንደ ሰንሰለት የተያያዙ ተራሮች እስከ አሁን ድረስ ከአእምሮዬ አልጠፉም። በበጋ ወቅት ሸለቆውና መስኩ ማራኪ በሆኑ የሜዳ አበቦች አሸብርቆ ሲታይ የሚያምር ምንጣፍ የተነጠፈበት ይመስላል። አየሩም ሆነ ውኃው የጠራ ነው። ድቦች፣ ተኩላዎች፣ የተለያዩ የአጋዘን ዝርያዎችና ሌሎች የዱር እንስሳት ተፈጥሮ በለገሳቸው መኖሪያ ያለ ምንም ስጋት ይፈነጫሉ።

ይሁን እንጂ ተለዋዋጭ ከሆነው የአየር ጠባይ በተጨማሪ ክልሉ ሰፊ መሆኑ በአላስካ ማገልገልን ፈታኝ ያደርገዋል። እኔ የማገለግልበት ወረዳ ከምሥራቅ አንስቶ እስከ ምዕራብ ድረስ 3,200 ኪሎ ሜትሮች ይሸፍናል። በዚያን ጊዜ ለወረዳ የበላይ ተመልካቾች መኪና የሚሰጥበት ዝግጅት አልተጀመረም። በመሆኑም በወረዳው ውስጥ ያሉ ወንድሞች ከአንድ ጉባኤ ወደ ሌላው በፈቃደኝነት ያደርሱኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ግን የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ወይም ደግሞ ቱሪስቶች እንዲያሳፍሩኝ እለምናለሁ።

በአንድ ወቅት በአላስካ በሚገኘው በቶክ ጀንክሽን እና ማይል 1202 ወይም ስኮቲ ክሪክ በሚባለው ቦታ መካከል በሚያልፈው የአላስካ አውራ ጎዳና ላይ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞኛል። በእነዚህ ሁለት ቦታዎች ላይ በሚገኙት የጉምሩክ ኬላዎች መካከል ያለው ርቀት 160 ኪሎ ሜትር ያህላል። በቶክ የሚገኘውን የዩናይትድ ስቴትሱን የጉምሩክ ኬላ ካለፍኩ በኋላ መኪና አግኝቼ ወደ 50 ኪሎ ሜትር ገደማ ሸኙኝ። ከዚያ በኋላ አንድም መኪና ስላልመጣ ለአሥር ሰዓት ያህል ከ40 ኪሎ ሜትር በላይ በእግሬ ተጓዝኩ። ይህ የሆነው የጉምሩክ ኬላውን እንዳለፍኩ ከኬላው ብዙም ሳይርቅ አንድ ትልቅ የበረዶ ድንጋይ አውራ ጎዳናውን ስለዘጋው የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ በመቋረጡ ምክንያት መሆኑን የሰማሁት ከጊዜ በኋላ ነበር። እኩለ ሌሊት ላይ ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች 23 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ወርዶ የነበረ ከመሆኑም በላይ በቅርብ ወደሚገኘው ከተማ ለመድረስ 80 ኪሎ ሜትር ይቀረኝ ነበር። የማድርበት መጠለያ ማግኘቴ አንገብጋቢ ጉዳይ ነበር።

የግዴን እየተራመድኩ ሳለ ከመንገዱ ወጣ ብሎ የተወሰነ ክፍሉ በበረዶ የተሸፈነ የተጣለ መኪና አየሁ። መኪናው ውስጥ ገብቼ ወንበሩ ላይ ብተኛ የሌሊቱን ቅዝቃዜ ማሳለፍ እንደምችል አሰብኩ። በሩ ላይ የተጋገረውን በረዶ ጠርጌ ስከፍተው መኪናው ቀፎው ብቻ የቀረ መሆኑን አየሁ። ደግነቱ ከመንገዱ ብዙም ሳይርቅ አንድ የተተወ ቤት አገኘሁ። እንደ ምንም ብዬ ወደ ውስጥ ከገባሁና እሳት ካያያዝኩ በኋላ ለጥቂት ሰዓታት ተኛሁ። በነጋታው እስከሚቀጥለው ከተማ ድረስ የሚወስደኝ መኪና አገኘሁ። እዚያ ደርሼ ረሃቤን ካስታገስኩ በኋላ የተላላጡትን እጆቼን በፋሻ ጠቀለልኳቸው።

ይሖዋ በአላስካ እድገት እንዲገኝ አድርጓል

በፌይርባንክስ በሚገኘው ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረግሁት ጉብኝት በጣም የሚያበረታታ ነበር። በአገልግሎት ጥሩ ውጤት ያገኘን ሲሆን እሁድ ዕለት የሕዝብ ንግግሩን ለማዳመጥ 50 ያህል ሰዎች ተገኙ። ስብሰባው የተካሄደው ቬርኖን እና ሎሬይን ዴቪስ በሚኖሩበት አነስተኛ የሚስዮናውያን ቤት ውስጥ ሲሆን ወጥ ቤት፣ መኝታ ቤትና መተላለፊያው ላይ ያሉ ሰዎች ንግግሩን ለማዳመጥ ጭንቅላታቸውን ብቅ አድርገው ይታዩ ነበር። ንግግሩን ለማዳመጥ የመጡ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ስንመለከት በፌይርባንክስ የመንግሥት አዳራሽ ቢገኝ የስብከቱ ሥራ እንዲጠናከር እንደሚያደርግ ተገነዘብን። በመሆኑም በይሖዋ እርዳታ፣ በፊት ጭፈራ ቤት የነበረ አንድ ትልቅ ቤት ገዝተን ተስማሚ ወደሆነ ቦታ አዛወርነው። የጉድጓድ ውኃ ቆፍረን አወጣን፣ መታጠቢያ ክፍሎች ሠራን እንዲሁም ለአዳራሹ ማሞቂያ መሣሪያ ገጠምን። በዚህ መንገድ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በፌይርባንክስ ጥሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ማግኘት ተችሏል። ሕንፃው ወጥ ቤት ከተሠራለት በኋላ በ1958 በአዳራሹ 330 ሰዎች የተገኙበት የአውራጃ ስብሰባ ተደረገ።

በ1960 በጋ ላይ በዩናይትድ ስቴትስና በካናዳ ለሚገኙ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች በሙሉ የተዘጋጀውን የማጠናከሪያ ኮርስ ለመውሰድ ኒው ዮርክ ወደሚገኘው ዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት በመኪና ረጅም ርቀት ተጓዝኩ። እዚያ እያለሁ ወንድም ናታን ኖርና ሌሎች ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች በአላስካ ቅርንጫፍ ቢሮ መክፈት የሚቻልበትን ሁኔታ በተመለከተ አነጋገሩኝ። ከጥቂት ወራት በኋላ ከመስከረም 1, 1961 አንስቶ በአላስካ ቅርንጫፍ ቢሮ እንደሚቋቋም ስንሰማ በጣም ተደሰትን። ወንድም አንድሩ ኬ ዋግነር በቅርንጫፍ ቢሮው የሚካሄደውን ሥራ እንዲከታተል ተመደበ። እርሱና ባለቤቱ ቪራ በብሩክሊን ለ20 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን ጉባኤዎችን በመጎብኘቱ ሥራም ልምድ ነበራቸው። በአላስካ ቅርንጫፍ ቢሮ መቋቋሙ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ የሚሸፍነውን ክልል ስለቀነሰለት ጉባኤዎችና ገለልተኛ ቡድኖች ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጥ አስችሎታል።

የ1962 የበጋ ወቅት በአላስካ ለሚገኙ ወንድሞች አስደሳች ጊዜ ነበር። የአላስካ ቅርንጫፍ ቢሮ ለአምላክ አገልግሎት የተወሰነ ከመሆኑም በላይ በጁኖው፣ አላስካ የአውራጃ ስብሰባ ተደረገ። በጁኖው እና በዋይትሆርስ፣ ዩኮን አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች የተገነቡ ሲሆን በገለልተኛ ክልሎችም በርካታ ቡድኖች ተቋቋሙ።

ወደ ካናዳ ተመለስኩ

ለበርካታ ዓመታት በካናዳ ከምትኖረው ከማርጋሪታ ፔትራስ ጋር እጻጻፍ ነበር። ሪታ (ብዙውን ጊዜ የምትጠራበት ስም ነው) የአቅኚነት አገልግሎት የጀመረችው በ1947 ሲሆን በ1955 ከጊልያድ ተመርቃ በምሥራቃዊ ካናዳ በአቅኚነት ታገለግል ነበር። ለጋብቻ ስጠይቃት ፈቃደኝነቷን ገለጸችልኝ። በየካቲት 1963 በዋይትሆርስ ተጋባን። በዚያ ዓመት በልግ ላይ በምዕራባዊ ካናዳ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት እንዳገለግል ተመደብኩ። በዚያም ለቀጣዮቹ 25 ዓመታት በደስታ አገልግለናል።

ጤና እያጣን በመምጣታችን በ1988 በዊኒፔግ ማኒቶባ በልዩ አቅኚነት እንድናገለግል ተመደብን። በዚያ ስናገለግል ለአምስት ዓመታት ያህል አንድ ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንጠብቅ ነበር። አቅማችን በፈቀደው መጠን አሁንም አስደሳች በሆነው ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንካፈላለን። በወረዳ ሥራ ላይ እያለን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እናስጀምርና ሌሎች እንዲያስጠኗቸው እንሰጥ ነበር። አሁን ግን ጥናቶች አስጀምረን ተማሪዎቹ እድገት በማድረግ ራሳቸውን ሲወስኑና ሲጠመቁ የማየት ተጨማሪ ደስታ አግኝተናል። ይህም ይገባናል የማንለው የይሖዋ ደግነት መግለጫ ነው።

ይሖዋን ማገልገል በሕይወት ውስጥ ከሁሉ የተሻለ ምርጫ መሆኑን በእርግጠኝነት አምናለሁ። ይህም ትርጉም ያለውና እርካታ የሚያስገኝ ከመሆኑም በላይ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር በየዕለቱ ያሳድግልናል። እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምንችለው በዚህ መንገድ ነው። ምንም ዓይነት የአገልግሎት ምድብ ቢኖረን ወይም በዓለም ላይ በየትኛውም ቦታ ብንሆን መዝሙራዊው “እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ ምስጉን ነው” ሲል በተናገረው ሐሳብ እንስማማለን።—መዝሙር 144:15

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በወረዳ ሥራ ላይ እያለሁ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዶውሰን ሲቲ ውስጥ ሄነሪ ለፓይንን ለመጠየቅ ሄጄ (በግራ በኩል ያለሁት ነኝ)

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአንኮሬጅ የመጀመሪያው የይሖዋ ምሥክሮች መሰብሰቢያ አዳራሽ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እኔና ሪታ በ1998