በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንዳንዶች ምን ዓይነት ስም አትርፈው አልፈዋል?

አንዳንዶች ምን ዓይነት ስም አትርፈው አልፈዋል?

አንዳንዶች ምን ዓይነት ስም አትርፈው አልፈዋል?

የዛሬ ሦስት ሺህ ዓመት ገደማ ዳዊት ከእስራኤል ንጉሥ ከሳኦል ሸሽቶ በስደት ይኖር ነበር። በዚህ ጊዜ ዳዊት ምግብና ውኃ እንዲሰጠው በጎችንና ፍየሎችን ያረባ ወደነበረው ናባል ወደሚባል ባለጠጋ ሰው መልእክተኞች ላከ። ዳዊትና አጋሮቹ የናባልን መንጎች ከአደጋ በመጠበቅ ለናባል ብዙ ውለታ ውለውለት ነበር። ሆኖም ናባል መልካም በማድረግ ውለታቸውን ለመመለስ ፈቃደኛ አልነበረም። እንዲያውም የዳዊትን መልእክተኞች ሰድቦ አባረራቸው። በዳዊት ላይ እንዲህ ማድረግ በእሳት የመጫወት ያህል ነበር።—1 ሳሙኤል 25:5, 8, 10, 11, 14

በመካከለኛው ምሥራቅ እንግዶችን ተቀብሎ ማስተናገድ የተለመደ ሲሆን የናባል ድርጊት ግን ይህን ባሕል የሚጻረር ነበር። ታዲያ ናባል ምን ስም አተረፈ? መጽሐፍ ቅዱስ ‘ባለጌና ግብሩም ክፉ እንዲሁም ምናምንቴ ሰው’ እንደነበረ ይናገራል። የስሙም ትርጉም ‘ሰነፍ’ ማለት ሲሆን ጠባዩም እንደ ስሙ ነበር። (1 ሳሙኤል 25:3, 17, 25) እንዲህ ዓይነት ስም ማትረፍ ትፈልጋለህ? ለሰዎች በተለይ ደግሞ ለተቸገሩና ለምስኪኖች ርኅራኄ ከማሳየት ወደኋላ ትላለህ ወይስ ደግ፣ እንግዳ ተቀባይና አሳቢ ነህ?

አቢግያ—አስተዋይ ሴት

ናባል ያሳየው ይህ መጥፎ ጠባይ ችግር ውስጥ ከተተው። ዳዊትና 400 አጋሮቹ ናባልን ለመቅጣት ሰይፋቸውን ታጥቀው ተነሱ። የናባል ሚስት አቢግያ የሆነውን ሁሉ ሰማች። ግጭት መነሳቱ እንደማይቀር ተገንዝባ ነበር። ታዲያ ምን ማድረግ ትችል ይሆን? እጅ መንሻ የሚሆን ብዙ ዓይነት ምግብ በፍጥነት አዘጋጅታ ዳዊትንና ተከታዮቹን ለመገናኘት ወጣች። ዳዊትንም ባገኘችው ጊዜ በከንቱ ደም እንዳያፈስ ተማጸነችው። ዳዊትም ልመናዋን ሲሰማ ቁጣው በረደ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ናባል ሞተ። አቢግያ ጥሩ ባሕርይ ያላት ሴት መሆኗን ስላስተዋለ ዳዊት ሚስት አድርጎ ወሰዳት።—1 ሳሙኤል 25:14-42

አቢግያ ምን ዓይነት ስም አትርፋ ነበር? “አስተዋይ” ወይም እንደ ዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ “ብልህ” ሴት እንደሆነች ተነግሮላታል። መቼና እንዴት እርምጃ መውሰድ እንዳለባት ጠንቅቃ የምታውቅ አስተዋይ ሴት ነበረች። ያንን ማስተዋል የጎደለውን ባሏንና መላውን ቤተሰብ ከጥፋት ለመታደግ እርምጃ ወስዳለች። ከጊዜ በኋላ የሞተች ቢሆንም አስተዋይ ሴት በሚል ያተረፈችው መልካም ስም እስከ አሁን ሕያው ሆኖ ይኖራል።—1 ሳሙኤል 25:3 አ.መ.ት

ጴጥሮስ ምን ስም አትርፎ አልፏል?

እስቲ ወደ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንምጣና ስለ አሥራ ሁለቱ የኢየሱስ ሐዋርያት የሚናገረውን ታሪክ እንመርምር። ቀደም ሲል በገሊላ በዓሣ አጥማጅነት ሥራ ይተዳደር የነበረው ጴጥሮስ ወይም ኬፋ ከሌሎቹ ሐዋርያት ይበልጥ ግልጽና ችኩል እንደነበር ምንም አያጠራጥርም። የተሰማውን ሁሉ ከመናገር ወደኋላ የማይልና አእምሮው ፈጣን ሰው ነበር። ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር እያጠበ ሳለ ጴጥሮስ የእርሱ ተራ በደረሰ ጊዜ ምን ብሎ እንደተናገረ እንመልከት።

ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፣ በኋላ ግን ታስተውለዋለህ” አለው። ጴጥሮስም “የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም” በማለት ወዲያው ቁርጥ ባለ መንገድ እንዴት እንደተናገረ ልብ በል። ታዲያ ኢየሱስ ምን ብሎ መለሰለት?

ኢየሱስም “ካላጠብሁህ፣ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም” ብሎ መለሰለት። ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ፣ እጄንና ራሴን ደግሞ እንጂ እግሬን ብቻ አይደለም” አለው። አሁን ደግሞ ጴጥሮስ ወደ ሌላ ጽንፍ ሄደ! የጴጥሮስን ባሕርይ ማንም ሰው ያውቀዋል። ማስመሰል ወይም ተንኮል በውስጡ የለም።—ዮሐንስ 13:6-9

ጴጥሮስ በአንዳንድ ሰብዓዊ ድክመቶቹም ይታወቃል። ለምሳሌ ያህል እንዲገደል የተፈረደበት የናዝሬቱ ኢየሱስ ተከታይ እንደሆነ ባጋለጡት ሰዎች ፊት ክርስቶስን ሦስት ጊዜ ክዶታል። እንደተሳሳተ ሲገባው ግን ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ። ማዘኑንና መጸጸቱን ከመግለጽ ወደኋላ አላለም። ኢየሱስን እንደካደ የሚናገረውን ይህን ታሪክ ለወንጌል ጸሐፊዎች የነገረው ጴጥሮስ ራሱ ሊሆን እንደሚችል ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። የፈጸመውን ጥፋት ሳይደብቅ ግልጥልጥ አድርጎ መናገሩ ትሑት መሆኑን የሚያሳይ ነው። አንተስ ስህተትህን አለምንም ማንገራገር አምነህ የምትቀበል ትሑት ሰው ነህ?—ማቴዎስ 26:69-75፤ ማርቆስ 14:66-72፤ ሉቃስ 22:54-62፤ ዮሐንስ 18:15-18, 25-27

ጴጥሮስ ክርስቶስን እንዲክድ ያደረጉት ሁኔታዎች ከተፈጠሩ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ መንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ በጰንጠቆስጤ ዕለት ለተሰበሰቡ ብዙ አይሁዳውያን በድፍረት ሰብኳል። ይህም ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ በጴጥሮስ ላይ የነበረውን እምነት እንዳላጣ የሚያሳይ ጥሩ ማስረጃ ነው።—ሥራ 2:14-21

በሌላ ወቅትም ጴጥሮስ አንድ ሌላ ስህተት ፈጽሟል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው አንዳንድ የአይሁድ ወንድሞች ወደ አንጾኪያ ከመምጣታቸው በፊት ጴጥሮስ ከአሕዛብ አማኞች ጋር በነጻነት ይጫወትና ያወራ ነበር። ‘ከተገረዙት ወገን ያሉት’ ከኢየሩሳሌም ሲመጡ ግን ‘ፈርቶ’ ራሱን ከአሕዛብ አማኞች አገለለ። ጳውሎስ የጴጥሮስን ግብዝነት በማውገዝ ገስጾታል።—ገላትያ 2:11-14

ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ተከታዮቹ ኢየሱስን ትተውት ሊሄዱ ሲሉ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል በድፍረት የተናገረው ማን ነው? ይህ ጊዜ ኢየሱስ ስጋውን የመብላትንና ደሙን የመጠጣትን አስፈላጊነት በተመለከተ አንድ አዲስ ነገር የተናገረበት ወቅት ነበር። ኢየሱስ “የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም” ሲል ተናግሮ ነበር። አብዛኞቹ አይሁዳውያን የኢየሱስ ተከታዮች በዚህ ንግግሩ ተሰናክለው “ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል?” አሉ። ከዚያስ ምን ተከሰተ? “ከዚህም የተነሣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም።”—ዮሐንስ 6:50-66

በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ ኢየሱስ ወደ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ዞር ብሎ “እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን?” በማለት አንጀት የሚበላ ጥያቄ አቀረበላቸው። ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም ብሎ መለሰለት።”—ዮሐንስ 6:67-69

ታዲያ ጴጥሮስ ምን ዓይነት ስም አትርፏል? ስለ ጴጥሮስ የሚናገረውን ታሪክ የሚያነብ ማንኛውም ሰው በሐቀኝነቱ፣ በግልጽነቱ፣ በታማኝነቱና ድክመቱን አምኖ በመቀበል ረገድ ባሳየው ትሕትና መነካቱ የማይቀር ነው። በእርግጥም ጴጥሮስ መልካም ስም አትርፏል።

ሰዎች ኢየሱስን የሚያስታውሱት በየትኞቹ ባሕርያቱ ነው?

ኢየሱስ በምድር ላይ ያገለገለው ሦስት ዓመት ተኩል ብቻ ነው። ሆኖም ኢየሱስ የሚታወቀው በየትኞቹ ባሕርያቱ ነው? ኃጢአት ያልነበረበት ፍጹም ሰው ስለሆነ ሰዎችን ይጸየፍ ነበርን? የአምላክ ልጅ በመሆኑ ሰዎችን ይንቅ ነበርን? ተከታዮቹን በማሸማቀቅና በማስፈራራት እንዲታዘዙት ያደርግ ነበርን? ከሌሎች ጋር መሳቅ መጫወት ክብሩን እንደሚነካበት ሆኖ ይሰማው ነበርን? ሥራ ስለሚበዛበት የደከሙትን፣ የታመሙትን ወይም ልጆችን ለማነጋገር ጊዜ እንደሌለው ሆኖ ይሰማው ነበርን? በዚያ ዘመን እንደነበሩት ወንዶች የሌላ ዘር ሰዎችንና ሴቶችን የሚንቅ ነበርን? ስለ እርሱ የሚናገረው ዘገባ ምን ይላል?

ኢየሱስ ለሰዎች ከልብ ያስብ ነበር። ስለ አገልግሎቱ በሚገልጸው ዘገባ ውስጥ ብዙ ጊዜ የአካል ጉዳተኞችንና በሽተኞችን እንደፈወሰ እናነባለን። የተቸገሩትን ለመርዳት ከልብ ይጥር ነበር። “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው” ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ በመናገር ለልጆች ከልብ ያስብ እንደነበር አሳይቷል። ከዚያም ኢየሱስ “አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው።” ልጆችን ችላ ሳትል ታነጋግራቸዋለህ ወይስ በሌሎች ነገሮች ላይ ብቻ በማተኮር መኖራቸውን እንኳን ትዘነጋለህ?—ማርቆስ 10:13–16፤ ማቴዎስ 19:13-15

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አይሁዳውያን በሕጉ ላይ በተጨመሩ ሃይማኖታዊ ደንቦችና መመሪያዎች እጅግ ተመርረው ነበር። ሃይማኖታዊ መሪዎቻቸው እነርሱ በጣታቸው እንኳ ሊነኩት የማይፈልጉትን ከባድ ሸክም በሕዝቡ ጫንቃ ላይ ይጭኑ ነበር። (ማቴዎስ 23:4፤ ሉቃስ 11:46) ኢየሱስ ከእነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ምንኛ የተለየ ነበር! “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ” ሲል ለሕዝቡ ግብዣ አቅርቧል።—ማቴዎስ 11:28-30

ሕዝቡ ከኢየሱስ ጋር ሲሆኑ ደስ ይላቸው ነበር። ደቀ መዛሙርቱን ፈጽሞ ስለማያሸማቅቃቸው የሚሰማቸውን ለመናገር አይፈሩም። እንዲያውም የልባቸውን እንዲያወጡ ጥያቄዎችን ይጠይቃቸው ነበር። (ማርቆስ 8:27-29) የጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲህ ብለው ራሳቸውን መጠየቅ ይኖርባቸዋል:- ‘የእምነት ባልንጀሮቼ ስለ እኔ ምን ይሰማቸዋል? ሌሎች ሽማግሌዎች አስተያየታቸውን በግልጽ ይነግሩኛል ወይስ ይፈሩኛል?’ በቀላሉ የሚቀረቡ፣ የሌሎችን ሐሳብ በጥሞና የሚያዳምጡና ግትር ያልሆኑ ሽማግሌዎች ምንኛ በረከት ናቸው! ሐሳበ ግትር መሆን ግልጽና ጥሩ ውይይት እንዳይኖር እንቅፋት ከመሆን ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም።

ምንም እንኳ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ቢሆንም ሥልጣኑን አለአግባብ አይጠቀምም ነበር። ከዚህ ይልቅ አድማጮቹን አሳማኝ በሆነ መንገድ ያስረዳቸው ነበር። ፈሪሳውያን በጥያቄ ሊያጠምዱት በፈለጉ ጊዜ መልስ የሰጠው በዚህ መንገድ ነበር። “ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ አንዲት ሳንቲም እንዲያሳዩት ካደረገ በኋላ “ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት?” በማለት ጠየቃቸው። እነርሱም “የቄሣር ነው” አሉት። ከዚያም “እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው።” (ማቴዎስ 22:15-21) ለጥያቄያቸው መልስ ለመስጠት ቀላል ሆኖም አሳማኝ ምሳሌ ተጠቅሟል።

ኢየሱስ የሚስቅና የሚጫወት ነበርን? ኢየሱስ ሃብታም ወደ አምላክ መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል በማለት የተናገረውን ዘገባ ሲያነቡ አንዳንዶች ፈገግ ማለታቸው አይቀርም። (ማቴዎስ 19:23, 24) ግመል በመርፌ ቀዳዳ መሹለክ እንደማይችል የታወቀ ነው። በራሱ ዓይን ውስጥ ያለውን ምሰሶ ማየት ተስኖት በወንድሙ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ እንዳየ የሚገልጸው ሐሳብም በግነት መልክ የቀረበ ሌላ ምሳሌ ነው። (ሉቃስ 6:41, 42) በእርግጥም ኢየሱስ ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር ብቻ የቆመ አልነበረም። ተግባቢና ተጫዋች ነበር። የሚስቅና የሚጫወት ሰው ሌሎች የሚሰማቸው ውጥረት ቀለል እንዲልላቸው ሊያደርግ ይችላል።

ኢየሱስ ለሴቶች ይራራ ነበር

ሴቶች ከኢየሱስ ጋር ሲሆኑ ምን ይሰማቸው ነበር? እናቱን ማርያምን ጨምሮ ታማኝ የሆኑ ሴት ተከታዮችም ነበሩት። (ሉቃስ 8:1-3፤ 23:55, 56፤ 24:9, 10) “ኃጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት” በእንባዋ እግሩን እስከ ማጠብና ሽቶ እስከ መቀባት የደረሰችው ሴቶች ሳይፈሩ በነጻነት ይቀርቡት ስለነበረ ነው። (ሉቃስ 7:37, 38) ለብዙ ዓመታት ደም ይፈስሳት የነበረች አንዲት ሴት ከሕመሟ ለመዳን ስትል በሕዝቡ መሃል ተሽሎክሉካ ልብሱን ነካች። ኢየሱስም ያሳየችውን እምነት በማድነቅ ተናግሯል። (ማቴዎስ 9:20-22) በእርግጥም ሴቶች ኢየሱስን ያለ ፍርሃት ይቀርቡት ነበር።

በሌላ ጊዜም ኢየሱስ አንዲትን ሳምራዊት ሴት በአንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ አነጋገራት። እርሷም በጣም ከመደነቋ የተነሳ “አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ?” አለችው። እንዲህ ልትል የቻለችው በጊዜው አይሁዳውያን ሳምራውያንን ስለማያነጋግሩ ነበር። ‘ለዘላለም ሕይወት ስለሚፈልቅ የውኃ ምንጭ’ ድንቅ ትምህርት አስተማራት። እርሱም ቢሆን ያነጋገራት አለምንም መሸማቀቅ ዘና ብሎ ነበር። እርሷን በማነጋገሩ ክብሩ እንደተነካበት ሆኖ አልተሰማውም።—ዮሐንስ 4:7-15

ኢየሱስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን ጨምሮ ብዙ ግሩም ባሕርያት ነበሩት። የአምላክ ፍቅር ሕያው መግለጫ ነበር። ተከታዮቹ መሆን የሚፈልጉ ሁሉ ፈለጉን እንዲከተሉ ምሳሌ ትቶላቸዋል። አንተስ የእርሱን አርዓያ ለመከተል ምን ያህል ትጥራለህ?—1 ቆሮንቶስ 13:4-8፤ 1 ጴጥሮስ 2:21

በዘመናችንስ አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን ስም አትርፈዋል?

በዘመናችንም በሺህ የሚቆጠሩ ታማኝ ክርስቲያኖች ግማሾቹ በዕድሜ ገፍተው ሌሎቹ ደግሞ ገና በወጣትነታቸው መልካም ስም አትርፈው አልፈዋል። አንዳንዶቹ በዕድሜ ገፍታ እንደሞተችው እንደ ክሪስትል በፍቅራቸውና በተጫዋችነታቸው ይታወሳሉ። ሌሎቹ ደግሞ በአርባዎቹ ዕድሜው እንደሞተው እንደ ደርክ በደስተኝነታቸውና በእሺ ባይነታቸው ይታወሳሉ።

ስፔይናዊው ሆሴም መልካም ስም አትርፈው ካለፉት ክርስቲያኖች መካከል አንዱ ነው። በ1960ዎቹ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በዚህ አገር ታግዶ ሳለ ሆሴ ባለትዳርና የሦስት ሴቶች ልጆች አባት ነበር። በባርሴሎና ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ ነበረው። ሆኖም በዚህ ወቅት በደቡባዊ ስፔይን የጎለመሱ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ያስፈልጉ ነበር። ሆሴ ያን የመሰለ ሥራውን ትቶ ከቤተሰቡ ጋር ወደ ማላጋ ሄደ። እዚያም ለብዙ ጊዜ ሥራ በማጣቱ የተነሳ ቤተሰቡ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ገጥሞት ነበር።

ሆኖም ሆሴ በታማኝነት ባከናወነው አገልግሎትና ደጋፊው ከሆነችው ሚስቱ ከካርሜላ ጋር ልጆቹን ጥሩ አድርጎ በማሳደግ ረገድ በምሳሌነት የሚጠቀስ ሰው ነው። በሚኖርበት አካባቢ ትላልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ለማደራጀት ሰው በሚያስፈልግበት ጊዜ ሁሉ ሆሴ ፈቃደኛ ሆኖ ይሠራ ነበር። የሚያሳዝነው ገና በ50ዎቹ ዕድሜው ሳለ በጠና ታምሞ ሞተ። ሆኖም ታማኝና ትጉህ ሽማግሌ እንዲሁም አፍቃሪ ባልና አባት የሚል መልካም ስም አትርፎ አልፏል።

አንተስ፣ ምን ዓይነት ስም አትርፈህ ታልፍ ይሆን? ትናንት ሞተህ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ሰዎች ስለ አንተ ምን ብለው ይናገሩ ነበር? ይህ አሁን በሕይወት ሳለን ስለምናከናውናቸው ነገሮች ቆም ብለን እንድናስብ የሚያደርገን ጥያቄ ነው።

መልካም ስም ለማትረፍ ምን ማድረግ ይኖርብናል? የመንፈስ ፍሬ የሆኑትን እንደ ፍቅር፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ የውሃትና ራስን መግዛት የመሰሉ ባሕርያትን ለማፍራት ሁልጊዜ ጥረት ማድረግ እንችላለን። (ገላትያ 5:22, 23) በእርግጥም “ከመልካም ሽቱ መልካም ስም፣ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል።”—መክብብ 7:1፤ ማቴዎስ 7:12

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አቢግያ አስተዋይ ሴት የሚል ስም አትርፋለች

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙዎች የጴጥሮስ ስም ሲነሳ ችኩልነቱና ሐቀኝነቱ ትዝ ይላቸዋል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ልጆችን ያቀርብ ነበር