በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?

ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?

ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?

“እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?”—ሚክያስ 6:8

1, 2. አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ተስፋ የሚቆርጡት ለምንድን ነው? ይሁን እንጂ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

 የሰባ አምስት ዓመት አረጋዊ የሆኑት ቪራ የጤና እክል ያለባቸው ታማኝ ክርስቲያን ናቸው። “አንዳንድ ጊዜ” ይላሉ ቪራ፣ “በመስኮት ወደ ውጭ ስመለከት ክርስቲያን ወንድሞቼና እህቶቼ ከቤት ወደ ቤት ሲሰብኩ አያቸዋለሁ። ባለብኝ ሕመም የተነሳ ከእነርሱ ጋር አብሬ ይሖዋን ማገልገል አለመቻሌን ሳስበው እንባ በዓይኖቼ ግጥም ይላል።”

2 አንተስ እንደእኚህ እህት ተሰምቶህ ያውቃል? ይሖዋን የሚወድዱ ሁሉ በስሙ መሄድና የሚፈልግባቸውን ብቃቶች ማሟላት ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ ጤና ያጣን፣ በዕድሜ የገፋን ወይም የቤተሰብ ኃላፊነት ያለብን ብንሆንስ? እንዲህ ያለው ችግር የምንፈልገውን ያህል ይሖዋን እንዳናገለግል ስለሚያግደን የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሊያድርብን ይችላል። እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የምንገኝ ከሆነ ሚክያስ ምዕራፍ 6 እና 7ን መመርመራችን ከፍተኛ ብርታት እንደሚሰጠን አያጠራጥርም። እነዚህ ምዕራፎች ይሖዋ ከእኛ የሚፈልጋቸው ብቃቶች ምክንያታዊና ሊደረስባቸው የሚችሉ መሆናቸውን ያሳያሉ።

ይሖዋ ሕዝቡን የሚይዘው እንዴት ነው?

3. ይሖዋ ዓመፀኞቹን እስራኤላውያን የያዛቸው እንዴት ነበር?

3 በመጀመሪያ ሚክያስ 6:3-5ን በመመርመር ይሖዋ ሕዝቡን እንዴት እንደሚይዝ እንመልከት። በሚክያስ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን ዓመፀኞች እንደነበሩ አስታውስ። ቢሆንም ይሖዋ “ሕዝቤ ሆይ” በማለት በርህራሄ ተናግሯቸዋል። እንዲሁም “ሕዝቤ ሆይ . . . አስብ” ሲል ተማጽኗቸዋል። ጥፋታቸውን እያነሳ ከመውቀስ ይልቅ “ምን አድርጌሃለሁ?” በማለት ልባቸውን ለመንካት ሞክሯል። እንዲያውም ‘መስክሩብኝ’ ብሏቸዋል።

4. አምላክ ርኅራኄ በማሳየት የተወልን ምሳሌ ምን እንድናደርግ ይገፋፋናል?

4 ይሖዋ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል! ዓመፀኛ የነበሩትን የእስራኤልንና የይሁዳን ሕዝብ በርኅራኄ ስሜት “ሕዝቤ ሆይ” ብሎ ከመጥራቱም በላይ አንጀት በሚበሉ ቃላት ተማጽኗቸዋል። እኛም ለጉባኤው አባላት ርኅራኄና ደግነት ልናሳያቸው እንደሚገባ እሙን ነው። አንዳንዶች አስቸጋሪ ጠባይ ሊኖራቸው ወይም በመንፈሳዊ ደካማ ሊሆኑ እንደሚችሉ አይካድም። ሆኖም ይሖዋን የሚወድዱ ከሆነ ልንረዳቸውና በርኅራኄ ልንይዛቸው ይገባል።

5. ሚክያስ 6:6, 7 የትኛውን ነጥብ ያጎላል?

5 ቀጥለን ደግሞ ሚክያስ 6:6, 7ን እንመልከት። ሚክያስ የሚከተሉትን ተከታታይ ጥያቄዎች ያቀርባል:- “ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን? እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጎች ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? ወይስ የበኩር ልጄን ስለ በደሌ፣ የሆዴንም ፍሬ ስለ ነፍሴ ኃጢአት እሰጣለሁን?” ይሖዋን “በሺህ አውራ በጎች ወይም በእልፍ የዘይት ፈሳሾች” ደስ ማሰኘት አይቻልም። ይሁን እንጂ እርሱን ደስ የሚያሰኘው ሌላ ነገር አለ። ይህ ምን ይሆን?

ፍትሕን ማሳየት ይኖርብናል

6. በሚክያስ 6:8 ላይ የተጠቀሱት ሦስት መለኮታዊ ብቃቶች የትኞቹ ናቸው?

6 ሚክያስ 6:8 ይሖዋ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ ይነግረናል። ሚክያስ እንዲህ በማለት ይጠይቃል:- “እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን [“ፍትሕን፣” አ.መ.ት] ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ ከአምላክህም ጋር በትሕትና [“ልክህን አውቀህ፣” NW] ትሄድ ዘንድ አይደለምን?” እነዚህ ሦስት ብቃቶች ከስሜታችን፣ ከአስተሳሰባችንና ከድርጊታችን ጋር የተያያዙ ናቸው። እነዚህን ባሕርያት የማንጸባረቅ ፍላጎት ማዳበር፣ እንዴት እንደምናንጸባርቃቸው ማሰብና ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ይገባናል። እስቲ እነዚህን ብቃቶች አንድ በአንድ እንመርምር።

7, 8. (ሀ) ‘ፍትሕ ማድረግ’ ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) በሚክያስ ዘመን የፍትሕ መጓደል ምን ያህል ተስፋፍቶ ነበር?

7 ‘ፍትሕ ማድረግ’ ሲባል ትክክለኛ የሆነውን ነገር መፈጸም ማለት ነው። የፍትሕ መለኪያችን ደግሞ ይሖዋ ነገሮችን የሚያደርግበት መንገድ ነው። በሚክያስ ዘመን የነበሩት ሰዎች ግን ፍትሕን በማድረግ ፋንታ ግፍ ይፈጽሙ ነበር። እንዴት? ሚክያስ 6:10ን እንመልከት። በዚህ ጥቅስ መጨረሻ ላይ ነጋዴዎቹ “ውሸተኛ መስፈሪያ” ማለትም አሳንሶ የሚለካ የሐሰት መስፈሪያ እንደነበራቸው ተገልጿል። ቁጥር 11 ‘አባይ ሚዛን’ እንደነበራቸው ይናገራል። ቁጥር 12 ደግሞ “ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ተንኰለኛ ነው” ይላል። ስለዚህ በሚክያስ ዘመን በንግዱ ዓለም ሐሰተኛ መስፈሪያዎች፣ አባይ ሚዛኖችና የውሸት ንግግሮች በጣም ተስፋፍተው ነበር።

8 ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች ይፈጸሙ የነበረው በገበያ ቦታዎች ብቻ አልነበረም። ፍርድ ቤቶችም ፍትሕን ያጓድሉ ነበር። ሚክያስ 7:3 “አለቃውና ፈራጁ ጉቦን ይፈልጋሉ” ይላል። ዳኞች በንጹሐን ሰዎች ላይ ፍትሐዊ ያልሆነ ፍርድ ለመፍረድ ጉቦ ይቀበሉ ነበር። “ትልቁም ሰው” ወይም በሌሎች ዘንድ ተደማጭነት ያላቸው ሰዎችም በዚሁ ወንጀል ይተባበሩ ነበር። እንዲያውም ፈራጁ፣ አለቃውና ትልቁ ሰው ‘ክፋትን እንደሚጎነጉኑ’ ወይም የክፋት ድርጊታቸውን እንደሚያስተባብሩ ሚክያስ ተናግሯል።

9. ክፉዎች ይፈጽሙት የነበረው ግፍና በደል በይሁዳና በእስራኤል ሕዝብ ላይ ምን ችግር ፈጥሮ ነበር?

9 ክፉዎቹ መሪዎች ይፈጽሙ የነበረው ግፍና በደል በመላው የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ ላይ ችግር አስከትሎ ነበር። ሚክያስ 7:5 ፍትሕ በመጥፋቱ የተነሳ በባልንጀራሞች፣ በምሥጢር ጓደኛሞችና በትዳር ጓደኛሞች መካከል ሳይቀር መተማመን ጠፍቶ እንደነበር ያመለክታል። ከቁጥር 6 ማየት እንደሚቻለው ትልቅ ማኅበራዊ ቀውስ በመፈጠሩ ምክንያት የቅርብ ዘመዳሞች ሳይቀሩ ማለትም አባትና ወንድ ልጁ እንዲሁም እናትና ሴት ልጅዋ ይናናቁ ነበር።

10. የፍትሕ መጓደል በነገሰበት በዚህ ሥርዓት ውስጥ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ባሕርይ ያሳያሉ?

10 ዛሬስ ሁኔታው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ አይደለም? እንደ ሚክያስ ሁሉ እኛም ፍትህ በተጓደለበት፣ መተማመን በጠፋበት፣ ማኅበራዊና የቤተሰብ ሕይወት አደጋ ላይ በወደቀበት ሥርዓት ውስጥ እንኖራለን። ሆኖም የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን በዚህ ዓለም ውስጥ የሚታየው ፍርደ ገምድልነት ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ሰርጎ እንዲገባ መፍቀድ አይገባንም። ከዚህ ይልቅ በዕለት ተዕለት ኑሯችን ሐቀኝነትንና ጨዋነትን በማሳየት ለእነዚህ ባሕርያት ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ እናሳያለን። አዎን፣ “በነገር ሁሉ በመልካም” መኖር እንፈልጋለን። (ዕብራውያን 13:18) ፍትሕን የምናንጸባርቅ ከሆነ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ወንድማማችነት ከሚያስገኘው ደስታ ተካፋይ እንሆናለን ቢባል አትስማማም?

አሕዛብ ‘የእግዚአብሔርን ድምፅ’ የሚሰሙት እንዴት ነው?

11. ሚክያስ 7:12 ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

11 ሚክያስ የፍትሕ መጓደል ቢስፋፋም ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ፍትሕ እንደሚያገኙ በትንቢት ተናግሯል። ነቢዩ ሕዝቦች ይሖዋን ለማምለክ “ከባሕርም እስከ ባሕር፣ ከተራራም እስከ ተራራ ድረስ” እንደሚሰበሰቡ ተናግሯል። (ሚክያስ 7:12) ይህ ትንቢት የመጨረሻ ፍጻሜውን ባገኘበት በዛሬው ጊዜ አንድ የተለየ ብሔር ሳይሆን ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች አድልዎ ከሌለበት የአምላክ ፍትሕ ተጠቃሚዎች ሆነዋል። (ኢሳይያስ 42:1) ይህ የሆነው እንዴት ነው?

12. በዛሬው ጊዜ ሰዎች ‘የእግዚአብሔርን ድምፅ’ የሚሰሙት እንዴት ነው?

12 የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በሚክያስ 6:9 ላይ የሚገኙትን ቃላት መለስ ብለን እንመልከት። ጥቅሱ “የእግዚአብሔር ድምፅ ከተማይቱን ይጠራታል፤ ስምህን መፍራት ጥበብ ነው” ይላል። አሕዛብ ‘የእግዚአብሔርን ድምፅ’ የሚሰሙት እንዴት ነው? ይህስ የፍትሕን ባሕርይ ከማሳየታችን ጋር ምን ግንኙነት አለው? ሰዎች በዛሬው ጊዜ የአምላክን ድምፅ በቀጥታ መስማት እንደማይችሉ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በዓለም አቀፋዊው የስብከት ሥራችን አማካኝነት ከሁሉም ዘሮችና የኑሮ ደረጃዎች የተውጣጡ ሰዎች የይሖዋን ድምፅ በመስማት ላይ ናቸው። በዚህም መንገድ ድምፁን የሚሰሙ ሁሉ ‘የአምላክን ስም ይፈራሉ፤’ ለስሙም ጥልቅ አክብሮት ያድርባቸዋል። በእርግጥም ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሆነን በማገልገል ፍትሕንና ፍቅርን እናሳያለን። የአምላክን ስም አለምንም አድልዎ ለሰው ሁሉ በማዳረስ ‘ፍትሕን እናንጸባርቃለን።’

ደግነትን መውደድ ይኖርብናል

13. በፍቅር ተነሳስቶ ደግነት በማሳየትና በፍቅር መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

13 ቀጥለን በሚክያስ 6:8 ላይ የተጠቀሰውን ሁለተኛ ብቃት እንመልከት። ይሖዋ ‘ምሕረትንም እንድንወድድ’ ይፈልጋል። በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ምሕረት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በፍቅር ተነሳስቶ ደግነት ማድረግ የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። እንዲህ ዓይነቱ ደግነት በአዘኔታ ተነሳስቶ ለሌሎች አሳቢነት ማሳየትን ያመለክታል። ሆኖም ይህ ባሕርይ ከፍቅር ጋር አንድ ነው ማለት አይደለም። እንዴት? ፍቅር ብዙ ነገሮችን የሚያቅፍ ሰፊ ትርጉም ያለው ቃል ነው። ግዑዛን ነገሮችና ጽንሰ ሐሳቦች እንኳን ሊወደዱ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ‘የወይን ጠጅንና ዘይትን’ እንዲሁም “ጥበብን” ስለሚወድዱ ሰዎች ይናገራል። (ምሳሌ 21:17፤ 29:3) ከላይ የጠቀስነው የደግነት ባሕርይ ግን ሁልጊዜም የሚያተኩረው በሰዎች ላይ በተለይ ደግሞ አምላክን በሚያገለግሉ ሰዎች ላይ ነው። በዚህ ምክንያት ሚክያስ 7:20 ይሖዋ አምላክን ስላገለገለው ስለ አብርሃም ሲናገር “ምሕረትንም [“ደግነትንም፣” NW] ለአብርሃም ታደርጋለህ” በማለት ይናገራል።

14, 15. በፍቅር ተነሳስቶ ደግነት ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው? ለዚህስ ምን ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል?

14 በሚክያስ 7:18 ላይ ነቢዩ ስለ ይሖዋ ሲናገር “ምሕረትን [“ደግነትን፣” NW] ይወድዳል” ይላል። በሚክያስ 6:8 ላይ ደግነት እንድናሳይ ብቻ ሳይሆን ይህን ባሕርይ እንድንወድ ተነግሮናል። ከእነዚህ ጥቅሶች የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? በፈቃደኝነትና ምንም ወሮታ ሳንጠብቅ በፍቅር ተነሳስተን ደግነት ማሳየት የምንችለው በመጀመሪያ ይህን ባሕርይ የማንጸባረቅ ፍላጎት ሲያድርብን ነው። እኛም እንደ ይሖዋ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ደግነት ብናሳይ ደስታ እናገኛለን።

15 እንዲህ ዓይነቱ ደግነት በዛሬው ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች ተለይተው የሚታወቁበት ባሕርይ ሆኗል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በሰኔ 2001 በቴክሳስ፣ ዩ ኤስ ኤ የጣለው ኃይለኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በመቶ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ጨምሮ በሺህ የሚቆጠሩ ቤቶችን አውድሞ ነበር። አሥር ሺህ የሚያክሉ የይሖዋ ምሥክሮች ችግር ላይ የወደቁ ክርስቲያን ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ሲሉ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በፈቃደኝነትና በነጻ ሰጥተዋል። ፈቃደኛ ሠራተኞች ከመንፈቅ ለሚበልጥ ጊዜ ቀን፣ ሌሊት፣ ቅዳሜ እሁድ ሳይሉ አላንዳች ፋታ የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰበሰቡባቸውን 8 የመንግሥት አዳራሾችና ከ700 በላይ ቤቶችን ሠርተው ለክርስቲያን ወንድሞቻቸው አስረክበዋል። በሥራው መካፈል ያልቻሉ ደግሞ የምግብ፣ የቁሳቁስና የገንዘብ አስተዋጽኦ አድርገዋል። እነዚህ በሺህ የሚቆጠሩ ምሥክሮች ወንድሞቻቸውን ለመርዳት የተነሳሱት ለምንድን ነው? ‘ደግነትን ስለወደዱ’ ነው። በመላው ዓለም የሚኖሩ ወንድሞቻችን በፍቅር ተነሳስተው እንዲህ ዓይነት የደግነት ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ ማወቁ ምንኛ ደስ የሚያሰኝ ነው! አዎን፣ ‘ደግነትን መውደድ’ ደስታ የሚያስገኝ እንጂ ሸክም አይደለም።

ከአምላክ ጋር በትሕትና ተመላለስ

16. ከአምላክ ጋር ባለን ግንኙነት አቅማችንን ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

16 በሚክያስ 6:8 ላይ የሚገኘው ሦስተኛው ብቃት “ከአምላክህም ጋር በትሕትና [“ልክህን አውቀህ፣” NW] ትሄድ ዘንድ” የሚለው ነው። ይህ ማለት አቅማችን ውስን መሆኑን ማወቅና በአምላክ መታመን ማለት ነው። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- የአባቷን እጅ ሙጭጭ አድርጋ ይዛ ጎርፍና ውሽንፍር በበዛበት ዝናብ ውስጥ የምትሄድን አንዲት ትንሽ ልጅ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ልጅቱ አቅሟ ደካማ መሆኑን በደንብ ታውቃለች። ቢሆንም በአባቷ ትተማመናለች። እኛም አቅማችን ውስን መሆኑን አውቀን በሰማዩ አባታችን መታመን ይገባናል። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ወደ አምላክ መቅረብ አስፈላጊ የሆነባቸውን ምክንያቶች ምንጊዜም በማስታወስ ነው። ሚክያስ ሦስት ምክንያቶችን ይኸውም ይሖዋ አዳኛችን፣ መሪያችንና ጠባቂያችን መሆኑን ያስታውሰናል።

17. ይሖዋ ለሕዝቦቹ አዳኝ፣ መሪና ጠባቂ የሆነላቸው እንዴት ነው?

17 በሚክያስ 6:4, 5 ላይ አምላክ “ከግብጽ ምድር አውጥቼሃለሁ” ብሏል። አዎን፣ ይሖዋ ለእስራኤላውያን አዳኛቸው ነበር። በተጨማሪም ይሖዋ “በፊትህም ሙሴንና አሮንን ማርያምንም ልኬልህ ነበር” ብሏል። ሙሴንና አሮንን የእስራኤልን ብሔር ለመምራት ሲጠቀምባቸው ማርያም ደግሞ የድል መዝሙር ለመዘመር የእስራኤላውያን ሴቶችን አስተባብራ ነበር። (ዘጸአት 7:1, 2፤ 15:1, 19-21፤ ዘዳግም 34:10) ይሖዋ በአገልጋዮቹ አማካኝነት መመሪያ ሰጥቷቸዋል። በቁጥር 5 ላይ ይሖዋ የእስራኤልን ብሔር ከባላቅና ከበለዓም ጠብቋቸው እንደነበረና በጉዟቸው መገባደጃ ላይ በሞዓብ ምድር ከሚገኘው ከሰጢም ተነስተው በተስፋይቱ ምድር ወዳለው ወደ ጌልገላ ሲጓዙ እንዴት እንደጠበቃቸው አስታውሷቸዋል።

18. አምላክ በዛሬው ጊዜ አዳኝ፣ መሪና ጠባቂ የሆነልን እንዴት ነው?

18 እኛም ከአምላክ ጋር በምንሄድበት ጊዜ ከሰይጣን ዓለም ያድነናል፣ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት ይመራናል እንዲሁም ከተቃዋሚዎቻችን ጥቃት ሲሰነዘርብን በቡድን ደረጃ ይጠብቀናል። ስለዚህ ከጥንቷ ተስፋይቱ ምድር ብልጫ ወዳለው የአምላክ አዲስ የጽድቅ ሥርዓት በሚወስደው አስቸጋሪ ሁኔታዎች በበዙበት ጎዳና ላይ ስንጓዝ የሰማዩ አባታችንን እጅ ሙጭጭ አድርገን የምንይዝበት በቂ ምክንያት አለን።

19. ልክን ማወቅ ያለብንን የአቅም ገደብ ከማወቅ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?

19 ከአምላክ ጋር በምንመላለስበት ጊዜ ልካችንን ማወቃችን ስለ ሁኔታችን ከእውነታው ያልራቀ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። እንዲህ የምንለው ልክን ማወቅ ያለብንን የአቅም ገደብ መገንዘብን ስለሚጨምር ነው። የጤና መታወክ ወይም የዕድሜ መግፋት ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎት በተወሰነ ደረጃ ሊገድብብን ይችላል። በዚህ ሁኔታ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ አምላክ የሚቀበለው ‘በሌለን መጠን ሳይሆን ባለን መጠን’ የምናደርገውን ጥረትና የምናቀርበውን መሥዋዕት እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። (2 ቆሮንቶስ 8:12) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ሁኔታችን በሚፈቅድልን መጠን በሙሉ ነፍሳችን እንድናገለግለው ይጠብቅብናል። (ቆላስይስ 3:23) የቻልነውን ያህል በይሖዋ አገልግሎት በቅንዓት በተካፈልን መጠን ይሖዋ አብዝቶ ይባርከናል።—ምሳሌ 10:22

ይሖዋን ተስፋ ማድረግ በረከት ያስገኛል

20. እንደ ሚክያስ ይሖዋን በተስፋ የመጠበቅ ዝንባሌ እንዲኖረን የሚረዳን ምንን ማወቃችን ነው?

20 የአምላክን በረከት መቅመሳችን የሚክያስ ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን ይገፋፋናል። እርሱ “የመድኃኒቴን አምላክ ተስፋ አደርጋለሁ” ብሎ ነበር። (ሚክያስ 7:7) እነዚህ ቃላት ከአምላክ ጋር ባለን ግንኙነት ልካችንን ከማወቃችን ጋር የሚዛመዱት እንዴት ነው? በተስፋ የምንጠባበቅ ወይም የምንታገስ ከሆነ የይሖዋ ቀን እስካሁን ባለመምጣቱ ተስፋ አንቆርጥም። (ምሳሌ 13:12) ሁላችንም ይህ ክፉ ሥርዓት የሚጠፋበትን ጊዜ እንደምንናፍቅ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ በእያንዳንዷ ሳምንት በሺህ የሚቆጠሩ አዳዲስ ሰዎች አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር እያደረጉ ነው። ይህን ማወቃችን ይሖዋን በተስፋ እንድንጠባበቅ ይገፋፋናል። በእውነት ውስጥ ብዙ ዓመታት የቆየ አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብሏል:- “በስብከቱ ሥራ ያሳለፍኩትን 55 ዓመት ወደኋላ መለስ ብዬ ስመለከት ይሖዋን ተስፋ በማድረጌ የከሰርኩት ምንም ነገር እንደሌለ ይሰማኛል። እንዲያውም ልብ ከሚያቆስሉ በርካታ ሁኔታዎች ልድን ችያለሁ።” አንተም ተመሳሳይ ተሞክሮ ይኖርህ ይሆናል።

21, 22. ሚክያስ 7:14 በዘመናችን ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?

21 አካሄዳችንን ከይሖዋ ጋር ማድረጋችን ብዙ ጥቅሞች እንደሚያስገኝልን አያጠያይቅም። በሚክያስ 7:14 ላይ ሚክያስ የአምላክን ሕዝቦች እረኛቸውን ተማምነው ያለ ስጋት ከሚኖሩ በጎች ጋር አመሳስሏቸዋል። ይህ ትንቢት በስፋት በሚፈጸምበት በአሁኑ ጊዜ የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎችም ሆኑ “ሌሎች በጎች” በእረኛቸው በይሖዋ ተማምነው ያለ ስጋት ይኖራሉ። እያደር ይበልጥ አስጨናቂና አደገኛ እየሆነ ከመጣው ከዚህ ዓለም በመንፈሳዊ ተለይተው “በቀርሜሎስ መካከል ባለው ዱር ብቻቸውን” ይኖራሉ።—ዮሐንስ 10:16፤ ዘዳግም 33:28፤ ኤርምያስ 49:31፤ ገላትያ 6:16

22 በሚክያስ 7:14 ላይ በትንቢት እንደተነገረው የአምላክ ሕዝቦች ብልጽግናም አግኝተዋል። ሚክያስ ስለ አምላክ በጎች ወይም ሕዝቦች ሲናገር “በባሳንና በገለዓድ ይሰማሩ” ብሏል። የባሳንና የገለዓድ በጎች የለመለመ ሣር በልተው ይጠግቡ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም የአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ ብልጽግና አግኝተዋል። ይህም ልካቸውን አውቀው ከአምላክ ጋር የሚመላለሱ ሰዎች የሚያገኙት ሌላው በረከት ነው።—ዘኍልቍ 32:1፤ ዘዳግም 32:14

23. ሚክያስ 7:18, 19ን በመመርመራችን ምን ትምህርት አግኝተናል?

23 ነቢዩ በሚክያስ 7:18, 19 ላይ ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ሰዎችን ይቅር ለማለት ያለውን ፍላጎት ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ቁጥር 18 ይሖዋ “በደልን ይቅር የሚል” እንዲሁም “ዓመፅ የሚያሳልፍ” እንደሆነ ይናገራል። ቁጥር 19 ደግሞ “ኃጢአታችንን በባሕሩ ጥልቅ ይጥለዋል” ይላል። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? በዚህ ረገድ ይሖዋን እመስለዋለሁን? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን። ሌሎች የፈጸሙብንን በደል ይቅር እንላለን? በድለውናል የምንላቸው ሰዎች ከተጸጸቱና ለመካስ ከፈለጉ የይሖዋን አርዓያ በመከተል ሙሉ በሙሉ ይቅር ልንላቸው ይገባል።

24. ከሚክያስ ትንቢት ምን ጥቅሞች አግኝተሃል?

24 የሚክያስን ትንቢት በመመርመራችን ምን ጥቅሞች አግኝተናል? ይሖዋ ወደ እርሱ ለሚቀርቡ ሁሉ እውነተኛ ተስፋ እንደሚሰጣቸው አስታውሶናል። (ሚክያስ 2:1-13) በአምላክ ስም ለዘላለም መሄድ እንድንችል እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት የተቻለንን ሁሉ እንድናደርግ ተበረታተናል። (ሚክያስ 4:1-4) ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን አምላክ የሚፈልግብንን ብቃቶች ማሟላት እንደምንችል ማረጋገጫ አግኝተናል። አዎን፣ የሚክያስ ትንቢት በይሖዋ ስም እንድንሄድ አበረታቶናል።

ለክለሳ ያህል?

በሚክያስ 6:8 መሠረት ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?

• ‘ፍትሕን ለማሳየት’ ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

• ‘ደግነትን እንደምንወድድ’ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

• ከአምላክ ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ‘ልክን ማወቅ’ ምንን ይጨምራል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሚክያስ በአስቸጋሪ ዘመን ውስጥ ይኖር የነበረ ቢሆንም ይሖዋ የሚፈልግበትን ብቃት አሟልቷል። አንተም እነዚህን ብቃቶች ማሟላት አያቅትህም

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሁሉም የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰዎች በመመስከር ፍትሕን ማንጸባረቅ ትችላለህ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለሌሎች በችግራቸው ጊዜ በመድረስ ደግነትን እንደምትወድድ አሳይ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አቅምህ ውስን መሆኑን አትርሳ፤ ቢሆንም የተቻለህን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አትበል