ዋስትና ያላቸው ተስፋዎች
ዋስትና ያላቸው ተስፋዎች
የዓለም ታሪክ ሳይፈጸሙ በቀሩ ተስፋዎች የተሞላ ነው። ብሔራት ብዙውን ጊዜ አንዳቸው ሌላውን ላለመውረር በይፋ ቢፈራረሙም ይህን ስምምነታቸውን ጥሰው ሕዝቦቻቸውን ለአስከፊ ጦርነት ዳርገዋል። ናፖሊዮን በአንድ ወቅት “መንግሥታት ቃላቸውን የሚጠብቁት አንድም በኃይል ሲገደዱ አሊያም ጥቅም የሚያስገኝላቸው ሲሆን ብቻ ነው” ብሎ ነበር።
ሰዎች ስለሚገቡት ቃልስ ምን ለማለት ይቻላል? አንድ ሰው የገባውን ቃል ሳይጠብቅ ሲቀር ምንኛ የሚያሳዝን ነው! በተለይ የምታውቀውና የምታምነው ሰው ከሆነ በጣም መጎዳትህ አይቀርም። እርግጥ ሰዎች የገቡትን ቃል የማይፈጽሙት ከአቅማቸው በላይ ስለሆነ ወይም ፍላጎቱ ስለሌላቸው ነው።
ሰዎች በሚሰጧቸው ተስፋዎችና አምላክ በገባው ቃል መካከል ትልቅ ልዩነት አለ! አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች እምነት የሚጣልባቸውና አስተማማኝ ናቸው። ይሖዋ የሚሰጠው ማንኛውም ተስፋ ዋስትና ያለው ሲሆን ፍጻሜውን እንደሚያገኝ አያጠራጥርም። ኢሳይያስ 55:11 አምላክ የሚናገረው ቃል መሬት ጠብ እንደማይል ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።”
ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ስለሚገኙት የአምላክ ተስፋዎች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ እንተማመናለን። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።” (ራእይ 21:3, 4) አንተም “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በሚለው የኢየሱስ ምክር መሠረት እውቀት የምትቀስም ከሆነ እነዚህን በረከቶች ማግኘት ትችላለህ።—ዮሐንስ 17:3