የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
“በራሱ ሕይወት” አለው ሲባል ምን ማለት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ “በራሱ ሕይወት” እንዳለው የሚናገር ከመሆኑም በላይ የእርሱ ተከታዮችም ‘በራሳቸው ሕይወት’ እንደሚኖራቸው ይናገራል። (ዮሐንስ 5:26፤ 6:53) ይሁን እንጂ የእነዚህ ሁለት ጥቅሶች ትርጉም ይለያያል።
ኢየሱስ “አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና” በማለት ተናግሯል። ይህን ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ከመናገሩ በፊት “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፣ . . . ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 5:24-26) እዚህ ላይ ኢየሱስ አባቱ ልዩ ኃይል ማለትም ሰዎች በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው አቋም እንዲኖራቸው የማድረግ ችሎታ እንደሰጠው መናገሩ ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ በሞት ያንቀላፉትን ማስነሳትና ሕይወት መስጠት ይችላል። ኢየሱስ “በራሱ ሕይወት” አለው ሲባል እነዚህን ነገሮች የማድረግ ኃይል ተሰጥቶታል ማለት ነው። በሌላ አባባል ኢየሱስም እንደ አብ ‘በራሱ ሕይወት የመስጠት’ ችሎታ አለው ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ስለ እርሱ ተከታዮችስ ምን ለማለት ይቻላል?
ኢየሱስ ከላይ ያለውን ከተናገረ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ እንዲህ አለ:- “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፣ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።” (ዮሐንስ 6:53, 54) እዚህ ላይ ኢየሱስ “በራሳችሁ ሕይወት” ይኖራችኋል ሲል “የዘላለም ሕይወት” ስለማግኘት መናገሩ ነበር። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “በራሳችሁ ሕይወት” ከሚለው ጋር የሚመሳሰል የሰዋሰው አቀማመጥ ያላቸው ሌሎች ሐረጎችም ይገኛሉ። “በነፍሳችሁ [“በራሳችሁ”፣ NW] ጨው ይኑርባችሁ”፣ “ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ” የሚሉትን ሁለት ምሳሌዎች መጥቀስ ይቻላል። (ማርቆስ 9:50፤ ሮሜ 1:27) እነዚህ ሐረጎች ለሌሎች ጨው የመስጠት ወይም ብድራት የመክፈል ችሎታን አያመለክቱም። ከዚህ ይልቅ ውስጣዊ ሙሉነትን ማለትም አንድን ነገር በተሟላ ሁኔታ ማግኘትን ያመለክታሉ። ስለሆነም በዮሐንስ 6:53 ላይ ‘በራሳቸው ሕይወት’ እንደሚኖራቸው የሚናገረው አባባል በአጭሩ የተሟላ ወይም ዘላለማዊ ሕይወት ማግኘትን ያመለክታል።
ኢየሱስ ተከታዮቹ በራሳቸው ሕይወት እንዳላቸው በተናገረበት ወቅት ስለ ሥጋውና ደሙ ጠቅሷል። ከጊዜ በኋላ የጌታን እራት ባቋቋመበት ምሽት ስለ ሥጋውና ደሙ የተናገረ ሲሆን በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የሚታቀፉት ተከታዮቹ እርሾ ካልገባበት ቂጣና ከወይኑ እንዲካፈሉ አድርጓል። ታዲያ እንዲህ ሲባል የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት ከይሖዋ አምላክ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የገቡት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው? በፍጹም። ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ያቋቋመው በዮሐንስ 6:53, 54 ላይ ያለውን ሐሳብ ከተናገረ ከአንድ ዓመት በኋላ ነበር። ኢየሱስ በዮሐንስ 6:53, 54 ላይ የተናገራቸውን ቃላት የሰሙ ሰዎች የክርስቶስን ሥጋና ደም የሚወክሉት ቂጣና ወይን ስለሚቀርቡበት ዓመታዊ በዓል ምንም አያውቁም ነበር።
ኢየሱስ በዮሐንስ ምዕራፍ 6 ላይ እንዲህ በማለት ሥጋውን ከመና ጋር አወዳድሮ ነበር:- “አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤ ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው። ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል።” የኢየሱስ ሥጋና ደም ከመና ብልጫ ነበረው። እንዴት? የኢየሱስ ሥጋ “ስለ ዓለም ሕይወት” የተሰጠ ስለነበር የዘላለም ሕይወት ያስገኛል። a በመሆኑም በዮሐንስ 6:53 ላይ “በራሳቸው ሕይወት” እንደሚኖራቸው የሚናገረው ሐሳብ በሰማይም ሆነ በምድር የዘላለም ሕይወት የሚያገኙትን በሙሉ ያመለክታል።—ዮሐንስ 6:48-51
የክርስቶስ ተከታዮች በራሳቸው ሕይወት የሚኖራቸው ወይም የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት መቼ ነው? የመንግሥቱ ወራሾች እንዲሆኑ የተቀቡት ክርስቲያኖች በሰማይ ለመኖር የማይሞት መንፈሳዊ አካል ይዘው ከሞት ሲነሱ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:52, 53፤ 1 ዮሐንስ 3:2) የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ደግሞ በሺህ ዓመት ግዛት ማብቂያ ላይ ዘላለማዊ ሕይወት ያገኛሉ። በዚያን ጊዜ ተፈትነው ታማኝ መሆናቸው ስለሚረጋገጥ ጻድቃን ተብለው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ።—ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 20:5, 7-10
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እስራኤላውያንም ሆኑ አብረዋቸው የነበሩት “ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” በምድረ በዳ ሳሉ በሕይወት ለመቆየት መና አስፈልጓቸው ነበር። (ዘጸአት 12:37, 38፤ 16:13-18) በተመሳሳይ የተቀቡም ሆኑ ያልተቀቡ ክርስቲያኖች በሙሉ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት መሥዋዕት ሆኖ የቀረበው የኢየሱስ ሥጋና ደም ባለው የመቤዠት ኃይል በማመን ከዚህ ሰማያዊ መና መጠቀም ይኖርባቸዋል።—የየካቲት 1, 1988 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 30-1 ተመልከት።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ ‘በራሳቸው ሕይወት’ ሊኖራቸው ይችላል