ከኢየሱስ ቤተሰቦች ምን እንማራለን?
ከኢየሱስ ቤተሰቦች ምን እንማራለን?
ኢየሱስ እስከተጠመቀበት ጊዜ ድረስ ለ30 ዓመታት የኖረው ከቤተሰቦቹ ጋር ነበር። ስለ ቤተሰቦቹ ምን ያህል ታውቃለህ? የወንጌል ዘገባዎች ስለ እነርሱ ምን ይላሉ? ስለ ኢየሱስ ቤተሰቦች በመመርመር ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? ከእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ጥቅም እንደምታገኝ አያጠራጥርም።
ኢየሱስ የተወለደው በሀብታም ቤተሰብ ውስጥ ነው? አሳዳጊ አባቱ ዮሴፍ የሚተዳደረው በአናጢነት ነበር። አናጢነት ደግሞ ለጣውላ የሚሆን ዛፍ መቁረጥን ጨምሮ ከባድ የጉልበት ሥራ መሥራትን ይጠይቃል። ኢየሱስ ከተወለደ ከ40 ቀን በኋላ ወላጆቹ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው በሕጉ መሠረት መሥዋዕት አቅርበው ነበር። ታዲያ ያቀረቡት መሥዋዕት ሕጉ እንደሚያዘው አንድ ጠቦትና ዋኖስ ወይም የርግብ ጫጩት ነበር? አልነበረም። እነዚህን ሁሉ መሥዋዕቶች ለማቅረብ የሚበቃ ገንዘብ እንዳልነበራቸው ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ቢሆንም ድሆችም መሥዋዕት ማቅረብ የሚችሉበት ዝግጅት በሕጉ ውስጥ ተካትቶ ነበር። በዚህ መሠረት ዮሴፍና ማርያም “ሁለት ዋሊያ [ዋኖስ] ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች” ለመሥዋዕት አቅርበዋል። አነስተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሥዋዕት ማቅረባቸው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ቤተሰብ እንደነበሩ ያሳያል።—ሉቃስ 2:22-24፤ ዘሌዋውያን 12:6, 8
ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ወደፊት የመላው የሰው ዘር ገዥ የሚሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው መሠረታዊ ማቴዎስ 13:55፤ ማርቆስ 6:3) ኢየሱስ ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ በሰማይ በኖረበት ወቅት “ሀብታም” የነበረ ቢሆንም ለእኛ ሲል “ድሀ ሆነ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ራሱን ዝቅ አድርጎ ሰው ሆኖ በመወለድ ተራ በሆኑ ሰዎች መካከል አደገ። (2 ቆሮንቶስ 8:9፤ ፊልጵስዩስ 2:5-9፤ ዕብራውያን 2:9) ኢየሱስ በሀብታም ቤተሰብ ውስጥ አለመወለዱ ሰዎች በቀላሉ እንዲቀርቡት ሳያስችላቸው አልቀረም። ሰዎች ወደ እርሱ የሚቀርቡት ትልቅ ቦታ ወይም ክብር ስላለው ሳይሆን በትምህርቶቹ፣ በግሩም ባሕርያቱና በሚፈጽማቸው ተአምራት ተስበው ነው። (ማቴዎስ 7:28, 29፤ 9:19-33፤ 11:28, 29) ኢየሱስ ተራ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ እንዲወለድ በማድረግ ይሖዋ አምላክ ጥበቡን አሳይቷል።
ፍላጎቶችን ለማሟላት ደፋ ቀና በሚል ድሃ ቤተሰብ ውስጥ ነበር። ኢየሱስ ካደገ በኋላ እርሱም እንደ አሳዳጊ አባቱ አናጢ ሆኗል። (እስቲ አሁን ደግሞ የኢየሱስን ቤተሰብ አባላት እናንሳና ከእነርሱ ምን ልንማር እንደምንችል እንመልከት።
ጻድቅ ሰው የነበረው ዮሴፍ
ዮሴፍ እጮኛው ማርያም ገና “ሳይገናኙ” መጸነሷን ሲያውቅ ለእርሷ በነበረው ፍቅርና የሥነ ምግባር ብልግና ፈጽማ ሊሆን ይችላል በሚለው ጥርጣሬ ልቡ ተከፍሎ መሆን አለበት። የተከሰተው ሁኔታ ወደፊት ሕጋዊ ባሏ በመሆን መብቱ ላይ እንቅፋት የሚፈጥር ይመስል ነበር። በዚያ ዘመን አንዲት የታጨች ሴት የምትታየው የሰውዬው ሚስት እንደሆነች ተደርጋ ነበር። ዮሴፍ በጉዳዩ ላይ ብዙ ካወጣና ካወረደ በኋላ ማርያም አመንዝራ ተብላ በድንጋይ እንዳትወገር በማሰብ በምስጢር ሊፈታት ወሰነ።—ማቴዎስ 1:18፤ ዘዳግም 22:23, 24
ከዚያም አንድ መልአክ በሕልም ተገለጠለትና እንዲህ አለው:- “ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።” ዮሴፍ ወዲያውኑ ማርያምን ወደ ቤቱ በመውሰድ ይህን መለኮታዊ መመሪያ ተግባራዊ አደረገ።—ማቴዎስ 1:20-24
ጻድቅና ታማኝ የሆነው ይህ ሰው በዚህ ድርጊቱ ይሖዋ “እነሆ፣ ድንግል ትፀንሳለች፣ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፣ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” በማለት በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት ባስነገረው ትንቢት አፈጻጸም ረገድ የራሱን ሚና ተጫውቷል። (ኢሳይያስ 7:14) ዮሴፍ ማርያም የምትወልደው የበኩር ልጅ የአብራኩ ክፋይ እንዳልሆነ ቢያውቅም መንፈሳዊ ሰው ስለነበር የመሲሑ አሳዳጊ አባት ለመሆን ያገኘውን መብት በአድናቆት ተመልክቶታል።
ዮሴፍ ማርያም ልጅዋን እስክትወልድ ድረስ ከእርሷ ጋር ግንኙነት ከማድረግ ተቆጥቧል። (ማቴዎስ 1:25) ይህ ለአዲስ ተጋቢዎች በጣም ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ቢሆንም ዮሴፍና ማርያም የልጁን አባት ማንነት በሚመለከት ምንም ዓይነት ውዝግብ እንዳይነሳ የፈለጉ ይመስላል። ራስን በመግዛት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትተውልናል። ዮሴፍ ተፈጥሯዊ ፍላጎቱን ሳይሆን መንፈሳዊ ነገሮችን ያስቀድም ነበር።
ዮሴፍ የልጁን አስተዳደግ በተመለከተ አራት ጊዜ ከመላእክት መመሪያ ተቀብሏል። ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ ልጁን የት ማሳደግ እንዳለበት የሚገልጹ ነበሩ። ልጁ በሕይወት እንዲቆይ ከተፈለገ ዮሴፍ መመሪያዎቹን ዛሬ ነገ ሳይል ተግባራዊ ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነበር። በሁሉም አጋጣሚዎች ዮሴፍ ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ልጁን ይዞ መጀመሪያ ወደ ግብጽ የሄደ ሲሆን በኋላም ወደ እስራኤል ተመልሷል። ይህ እርምጃ ሄሮድስ ሕፃናትን ባስጨፈጨፈበት ወቅት ኢየሱስ በሕይወት እንዲተርፍ አስችሏል። እንዲሁም የዮሴፍ ታዛዥነት መሲሑን በሚመለከት የተነገሩት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ አድርጓል።—ማቴዎስ 2:13-23
ዮሴፍ ኢየሱስ ራሱን እንዲችል የእጅ ሙያ አሰልጥኖታል። ኢየሱስ “የጸራቢ ልጅ” ብቻ ሳይሆን “ጸራቢው” የተባለው በዚህ ምክንያት ነበር። (ማቴዎስ 13:55፤ ማርቆስ 6:3) ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ “በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ” መሆኑን ጽፏል። ይህ ደግሞ ቤተሰብን ለመደጎም ጠንክሮ መሥራትንም ይጨምራል።—ዕብራውያን 4:15
በመጨረሻም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ዮሴፍ ለመጨረሻ ጊዜ በተጠቀሰበት አጋጣሚ ለእውነተኛ አምልኮ ያደረ ሰው እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ እናገኛለን። ዘገባው ዮሴፍ የማለፍን በዓል ለማክበር ቤተሰቡን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሄደ ይናገራል። በዚህ በዓል ላይ እንዲገኙ የሚጠበቅባቸው ወንዶች ብቻ ቢሆኑም ዮሴፍ ‘በየዓመቱ’ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም የመሄድ ልማድ ነበረው። ከናዝሬት ወደ ኢየሩሳሌም ለመድረስ 100 ኪሎ ሜትር ገደማ መጓዝ ስለነበረባቸው ትልቅ መሥዋዕትነት መክፈል ይጠይቅበት ነበር። በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ በተጠቀሰው በዚህ አጋጣሚ ግን ኢየሱስ ከቤተሰቦቹ ተነጥሎ በኢየሩሳሌም ቀረ። በኋላም በቤተ መቅደስ የሕጉን አስተማሪዎች ሲያዳምጣቸውና ጥያቄ ሲጠይቃቸው አገኙት። ኢየሱስ ገና የ12 ዓመት ልጅ ቢሆንም የአምላክ ቃል እውቀትና ጥልቅ ጥበብ እንደነበረው አሳይቷል። ከዚህ ታሪክ ወላጆቹ መንፈሳዊ ዝንባሌ ያለው ልጅ እንዲሆን በጥሩ ሁኔታ እያስተማሩ እንዳሳደጉት መመልከት እንችላለን። (ሉቃስ 2:41-50) ዮሴፍ ከዚህ በኋላ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ዳግመኛ ስላልተጠቀሰ ብዙም ሳይቆይ እንደሞተ ይገመታል።
አዎን፣ ዮሴፍ ቤተሰቡን በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ ጥሩ አድርጎ የሚንከባከብ ጻድቅ ሰው ነበር። አንተስ እንደ ዮሴፍ አምላክ በዛሬው ጊዜ ለእኛ ያለውን ፈቃድ ተገንዝበህ በሕይወትህ ውስጥ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ትሰጣለህ? (1 ጢሞቴዎስ 2:4, 5) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውን የአምላክ መመሪያ በፈቃደኝነት በመከተል እንደ ዮሴፍ የታዛዥነት መንፈስ ታሳያለህ? ልጆችህ ከሌሎች ጋር የሚያንጹ መንፈሳዊ ውይይቶችን ማድረግ እንዲችሉ ታሰለጥናቸዋለህ?
ማርያም—ራስ ወዳድነት የሌለባት የአምላክ አገልጋይ
የኢየሱስ እናት ማርያም ግሩም ምሳሌ የምትሆን የአምላክ አገልጋይ ነበረች። መልአኩ ገብርኤል ልጅ እንደምትወልድ ሲነግራት በጣም ተደንቃ ነበር። ‘ወንድ ስለማታውቅ’ ድንግል ነበረች። የምትጸንሰው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እንደሆነ ስታውቅ “እነሆኝ የጌታ ባሪያ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” በማለት መልእክቱን በትሕትና ተቀብላለች። (ሉቃስ 1:30-38) ላገኘችው መንፈሳዊ መብት ከፍተኛ አድናቆት ስለነበራት ውሳኔዋ ሊያስከትልባት የሚችለውን ማንኛውንም ችግር ለመቀበል ፈቃደኛ ነበረች።
እርግጥ ነው፣ ይህን ተልእኮ መቀበሏ የሴትነት ሕይወቷን ሙሉ በሙሉ የሚቀይር ነበር። ማርያም የመንጻቷን ወራት ፈጽማ ወደ ኢየሩሳሌም ስትሄድ አንድ ፈሪሃ አምላክ ያለው ስምዖን የተባለ አረጋዊ “በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል” ብሏት ነበር። (ሉቃስ 2:25-35) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ስምዖን እንዲህ ሲል ኢየሱስ በብዙዎች ሲወገዝና በመጨረሻም በመከራ እንጨት ላይ ሲሰቀል ስታይ የሚሰማትን ስሜት ማመልከቱ ነበር።
ሉቃስ 2:19, 51) ልክ እንደ ዮሴፍ እሷም መንፈሳዊ ሴት ስለነበረች የትንቢቶችን ፍጻሜ ለሚያሳዩ ክስተቶችና ነገሮች ትልቅ ቦታ ትሰጥ ነበር። መልአኩ ገብርኤል “እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፣ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም” በማለት የተናገረው ሐሳብ በአእምሮዋ ተቀርጾ መሆን አለበት። (ሉቃስ 1:32, 33) አዎን፣ የመሲሑ እናት እንድትሆን ያገኘችውን መብት በቁም ነገር ትመለከተው ነበር።
ማርያም ኢየሱስ እያደገ ሲሄድ በሕይወቱ ውስጥ የሚያጋጥሙትን ነገሮች ሁሉ በአእምሮዋ ይዛ “በልብዋ ትጠብቀው ነበር።” (ማርያም መንፈሳዊ ሴት እንደነበረች በግልጽ የታየበት ሌላው አጋጣሚ ደግሞ እንደ እርሷ በተአምር የጸነሰችውን ዘመዷን ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ በሄደችበት ጊዜ ነበር። ማርያም ኤልሳቤጥን እንዳየቻት ይሖዋን ያወደሰች ሲሆን ለአምላክ ቃል ያላትን ፍቅር አሳይታለች። በ1 ሳሙኤል ምዕራፍ 2 ላይ የሚገኘውን የሐናን ጸሎት በተዘዋዋሪ ከመጥቀሷም በላይ ከሌሎች የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የተወሰዱ ሐሳቦችንም ጨምራ ተናግራለች። እንዲህ ያለው የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀቷ ትጉህና ፈሪሃ አምላክ ያላት እናት የመሆን ብቃት እንዳላት ያሳያል። ልጅዋን በመንፈሳዊ ተንከባክቦ በማሳደግ ረገድ ከዮሴፍ ጋር ተባብራ ትሠራለች።—ዘፍጥረት 30:13፤ 1 ሳሙኤል 2:1-10፤ ሚልክያስ 3:12፤ ሉቃስ 1:46-55
ማርያም ልጅዋ መሲሕ መሆኑን አጥብቃ ታምን የነበረ ሲሆን ይህ እምነቷ ኢየሱስ ከሞተም በኋላ አልጠፋም። ከትንሣኤው በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከሐዋርያት ጋር ለጸሎት ከተሰበሰቡት ታማኝ ደቀ መዛሙርት መካከል ነበረች። (የሐዋርያት ሥራ 1:13, 14) የምትወደው ልጅዋ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሲሞት ማየቱ መሪር ሐዘን ቢያስከትልባትም ታማኝነቷን ጠብቃለች።
ስለ ማርያም ካገኘኸው ትምህርት ምን ጥቅም አግኝተሃል? መሥዋዕትነት የሚጠይቅብህ ቢሆንም አምላክን ለማገልገል ያገኘኸውን መብት ለመቀበል ፈቃደኛ ነህ? በዛሬው ጊዜ ይህ መብት ትልቅ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ ይሰማሃል? ኢየሱስ የተናገራቸውን ትንቢቶች በዚህ ዘመን ከሚፈጸመው ሁኔታ ጋር እያወዳደርክ ‘በልብህ ታስበዋለህ?’ (ማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25፤ ማርቆስ ምዕራፍ 13፤ ሉቃስ ምዕራፍ 21) የአምላክን ቃል በሚገባ በማወቅና በንግግርህ ውስጥ አዘውትረህ በመጥቀስ የማርያምን ምሳሌ ትኮርጃለህ? የኢየሱስ ተከታይ መሆንህ የቱንም ያህል ስሜታዊ ሥቃይ ሊያስከትልብህ ቢችልም በኢየሱስ ላይ ያለህን እምነት እስከ መጨረሻው ትጠብቃለህ?
ከጊዜ በኋላ የተለወጡት የኢየሱስ ወንድሞች
ኢየሱስ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ወንድሞቹ መሲሕ መሆኑን ያመኑበት አይመስልም። በሞተበት ወቅት ማርቆስ 3:21) ኢየሱስ የማያምኑ የቤተሰብ አባላት ስለነበሩት በዛሬው ጊዜ የማያምኑ የቤተሰብ አባሎች ያሏቸው ክርስቲያኖች ዘመዶቻቸው በእምነታቸው ምክንያት ሲያፌዙባቸው የሚሰማቸውን ስሜት ኢየሱስ እንደሚረዳላቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።
በቦታው አለመገኘታቸውና ኢየሱስ እናቱን ለሐዋርያው ዮሐንስ በአደራ ለመስጠት መገደዱ ይህን የሚያሳይ ነው። የኢየሱስ ዘመዶች ለእርሱ አክብሮት እንዳልነበራቸው አሳይተዋል፤ እንዲያውም በአንድ ወቅት ‘አብዷል’ እስከማለት ደርሰው ነበር። (ኢየሱስ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ ግን ወንድሞቹ በእርሱ ማመን የጀመሩ ይመስላል። በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የጰንጠቆስጤ በዓል ከመከበሩ በፊት በኢየሩሳሌም ከሐዋርያት ጋር ተሰብስበው ለጸሎት ይተጉ ከነበሩት ደቀ መዛሙርት መካከል ነበሩ። (የሐዋርያት ሥራ 1:14) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የወንድማቸው ትንሣኤ ማግኘት የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያደርጉና የእርሱ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ሳይገፋፋቸው አልቀረም። እኛም የማያምኑ ዘመዶቻችን ሊለወጡ አይችሉም ብለን ፈጽሞ ተስፋ መቁረጥ አይኖርብንም።
ኢየሱስ በግል የተገለጠለት ግማሽ ወንድሙ ያዕቆብም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንደነበረው በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተገልጿል። ያዕቆብ የእምነት አጋሮቹ እምነታቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ የሚያበረታታ ደብዳቤ በመንፈስ አነሳሽነት ጽፏል። (የሐዋርያት ሥራ 15:6-29፤ 1 ቆሮንቶስ 15:7፤ ገላትያ 1:18, 19፤ 2:9፤ ያዕቆብ 1:1) ሌላው ወንድሙ ይሁዳም የእምነት ባልንጀሮቹ ለእምነታቸው በብርቱ እንዲጋደሉ በመንፈስ አነሳሽነት ደብዳቤ ጽፎላቸዋል። (ይሁዳ 1) ያዕቆብም ሆነ ይሁዳ በደብዳቤያቸው ላይ ከኢየሱስ ጋር የነበራቸውን የሥጋ ዝምድና በመጥቀስ ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸውን ለማስደነቅ አለመሞከራቸው ልብ ሊባል የሚገባው ነው። ለእኛ ግሩም የትሕትና ምሳሌ ይሆኑናል።
ታዲያ ከኢየሱስ ቤተሰቦች ምን ትምህርት አግኝተናል? የኢየሱስ ቤተሰቦች ለአምላክ ያደሩ መሆናቸውን ካሳዩባቸው መንገዶች ውስጥ የሚከተሉትን በመኮረጅ ጥቅም ልናገኝ እንደምንችል አያጠራጥርም። (1) ለአምላክ ፈቃድ በታማኝነት መገዛትና ይህ የሚያስከትለውን ማንኛውንም ፈተና ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን። (2) አንዳንድ መሥዋዕትነቶች የሚጠይቅብን ቢሆንም ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠት። (3) ልጆችን በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት ማሰልጠን። (4) የማያምኑ የቤተሰብ አባሎቻችን ሊለወጡ አይችሉም ብለን ተስፋ አለመቁረጥ። (5) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ካላቸው ግለሰቦች ጋር ባለን ማንኛውም ዓይነት ዝምድና አለመኩራራት። አዎን፣ ስለ ኢየሱስ ቤተሰቦች በቂ ግንዛቤ ማግኘታችን ወደ እርሱ እንድንቀርብ የሚያደርገን ከመሆኑም በላይ ኢየሱስን እየተንከባከበ የሚያሳድግ ተራ የሆነ ቤተሰብ በመምረጡ ይሖዋን እንድናደንቀው ይገፋፋናል።
[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዮሴፍ ማርያምን ሚስቱ አድርጎ በመውሰዱ መሲሑን አስመልክቶ በተነገሩት ትንቢቶች አፈጻጸም ረገድ የራሱን ሚና ተጫውቷል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዮሴፍና ማርያም ልጆቻቸውን በመንፈሳዊ ያሰለጠኗቸው ከመሆኑም በላይ የሥራንም ጠቀሜታ አስተምረዋቸዋል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢየሱስ ወንድሞች መንፈሳዊ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ቢያድጉም ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የተቀበሉት እርሱ ከሞተ በኋላ ነበር
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢየሱስ ወንድሞች የነበሩት ያዕቆብና ይሁዳ ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸውን አበረታተዋል