በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጠባቡን መንገድ ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ

ጠባቡን መንገድ ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ

ጠባቡን መንገድ ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ

ከ550 ዓመታት ገደማ በፊት በአሁኗ ቼክ ሪፑብሊክ ግዛት ውስጥ ካሉት ፕራግ፣ ኬልቺሴ፣ ቪሌሞቭ፣ ክላቶቪይ በሚባሉትና በሌሎች ከተሞች የሚኖሩ ክርስቲያን እንደሆኑ የሚናገሩ ሰዎችን ያቀፉ አናሳ ቡድኖች ቤቶቻቸውን ለቅቀው ጉዞ ጀመሩ። እነዚህ ቡድኖች በሰሜን ምሥራቅ ቦሔሚያ በሚገኝ ሸለቆ ውስጥ ኩንቫልት በተባለ መንደር አቅራቢያ ሠፈሩ። በዚያም ጎጆ ቀልሰው መሬቱን እያረሱና መጽሐፍ ቅዱሳቸውን እያነበቡ መኖር ጀመሩ። ራሳቸውንም የወንድማማች ኅብረት ወይም በላቲንኛ ዩኒታስ ፍራትረም ብለው ሰየሙ።

ሠፋሪዎቹ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ነበሩ። ጭሰኞች፣ መኳንንት፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ሀብታሞችና ድሆች፣ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም መበለቶችና ወላጅ የሌላቸው ልጆች ይገኙበት የነበረ ሲሆን ሁሉም አንድ የጋራ ፍላጎት ነበራቸው። ይህን ፍላጎታቸውን በሚመለከት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ወደ አምላክ በጸሎት ቀርበን በሁሉም ነገሮች ረገድ ያለውን ታላቅ ፈቃድ እንዲገልጽልን ተማጸንነው። በመንገዶቹ የመጓዝ ፍላጎት አድሮብን ነበር።” አዎን፣ ከጊዜ በኋላ የቼክ ወንድሞች ተብሎ የተሰየመው ይህ የወንድማማች ኅብረት ‘ወደ ሕይወት የሚወስደውን ቀጭን መንገድ’ ለማግኘት ፍለጋ አድርጓል። (ማቴዎስ 7:13, 14) ይህ ፍለጋቸው የትኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ገልጦላቸዋል? እምነታቸው በወቅቱ ተቀባይነት አግኝቶ ከነበረው አመለካከት የሚለየው እንዴት ነው? ከእነርሱስ ምን ልንማር እንችላለን?

በዓመጽ አልተካፈሉም፣ አቋማቸውንም አላላሉም

የወንድማማች ኅብረት ለተባለው ለዚህ ቡድን መመሥረት አስተዋጽኦ ያደረጉት በ15ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ የተነሱት በርካታ ሃይማኖታዊ ንቅናቄዎች ናቸው። ከእነዚህ መካከል ከ12ኛው

ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበረው የዋልደንሳውያን ንቅናቄ ይገኝበታል። መጀመሪያ ላይ ዋልደንሳውያን በመካከለኛው አውሮፓ የመንግሥት ሃይማኖት ከነበረው የሮማ ካቶሊክ እምነት ራሳቸውን አግልለው ነበር። ቆየት ብሎ ግን አንዳንድ የካቶሊክ ትምህርቶችን ማስተማር ጀመሩ። ለኅብረቱ መመሥረት አስተዋጽኦ ያደረጉት ሌሎች ክፍሎች ደግሞ የያን ሁስ ተከታዮች የነበሩት ሁሳውያን ናቸው። ከቼክ ሕዝብ መካከል አብዛኞቹ የዚህ ሃይማኖት ተከታዮች ቢሆኑም አንድነት ግን አልነበራቸውም። አንዱ ወገን ማኅበራዊ ጉዳዮችን እያነሳ ሲቃወም ሌላው ደግሞ ሃይማኖትን የፖለቲካ ዓላማዎች ማስፈጸሚያ አድርጎ ይጠቀምበት ነበር። በተጨማሪም የኪልያውያን ቡድኖች እንዲሁም የአገር ውስጥና የውጭ አገር የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን በወንድማማች ኅብረቱ ላይ ያሳደሩት ተጽዕኖ ነበር።

የቼክ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑርና የተሃድሶ አራማጅ የነበረው ፒተር ኬልቺድዝኪ (ከ1390 ገደማ–1460 ገደማ) የዋልደንሳውያንንና የሁሳውያንን ትምህርቶች ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ሁሳውያን ተሃድሶውን ለማምጣት ዓመጽን በመጠቀማቸው ዋልደንሳውያን ደግሞ አቋማቸውን አላልተው ወደ ካቶሊክ ትምህርቶች በመመለሳቸው ምክንያት ይቃወማቸው ነበር። ጦርነት ከክርስትና ትምህርቶች ጋር ስለሚጋጭ ያወግዘው ነበር። አንድ ክርስቲያን ምንም ዓይነት መሥዋዕትነት ቢጠይቅበት ‘በክርስቶስ ሕግ’ መገዛት ይኖርበታል የሚል አመለካከት ነበረው። (ገላትያ 6:2፤ ማቴዎስ 22:37-39) በ1440 ኬልቺድዝኪ ሃይማኖታዊ ትምህርቶቹን ኔት ኦቭ ዘ ፌዝ በተባለ መጽሐፍ ላይ አሰፈራቸው።

በምሑሩ ኬልቺድዝኪ ዘመን በፕራግ ይኖር የነበረ ግሬገሪ የተባለ አንድ ወጣት በኬልቺድዝኪ ትምህርቶች ስለተማረከ የሁሳውያንን ንቅናቄ ለቅቆ ወጣ። በ1458 ግሬገሪ ሁሳውያን የነበሩ ጥቂት ሰዎች በቼክ የነበራቸውን መኖሪያ ለቅቀው ከእርሱ ጋር ወደ ኩንቫልት መንደር እንዲሄዱ አሳመናቸው። በዚያም አዲስ ሃይማኖታዊ ኅብረተሰብ የመሠረቱ ሲሆን ከጊዜ በኋላም ከቼክና ከጀርመን የመጡ ዋልደንሳውያን ከእነርሱ ጋር ተቀላቀሉ።

የታሪክ መዛግብት

የአባላቱ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው ይህ ቡድን ከ1464 እስከ 1467 ድረስ በኩንቫልት አካባቢ በርካታ ጉባኤዎችን በማድረግ አዲሱን ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ መልክ ለማስያዝ የተለያዩ የአቋም መግለጫዎች አውጥቷል። የአቋም መግለጫዎቹ በሙሉ በአሁኑ ጊዜ አክታ ዩኒታቲስ ፍራትረም (የወንድማማች ኅብረት ሥራዎች) በሚል ርዕስ በሚታወቁት ተከታታይ መጻሕፍት ውስጥ አንድ በአንድ የተመዘገቡ ሲሆን እነዚህ መጻሕፍት አሁን ድረስ ይገኛሉ። እነዚህ መጻሕፍት የወንድማማች ኅብረቱ በጊዜው ምን ብሎ ያምን እንደነበር ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ የታሪክ መዛግብት ናቸው። መጻሕፍቱ ደብዳቤዎችን፣ የንግግር ግልባጮችን አልፎ ተርፎም በሐሳብ ልዩነቶች ላይ የተደረጉ ክርክሮችን በዝርዝር ይዘዋል።

መጻሕፍቱ የወንድማማች ኅብረቱን እምነቶች በሚመለከት እንዲህ ይላሉ:- “[መጽሐፍ ቅዱስን] ብቻ በማንበብ፣ ጌታችንና ቅዱሳን ሐዋርያት የተዉልንን ምሳሌ በመከተል፣ በማሰላሰል፣ ትሕትናና ትዕግሥት በማሳየት፣ ጠላቶቻችንን በመውደድ፣ ለእነርሱ መልካም በመመኘትና በማድረግ እንዲሁም ለእነርሱ በመጸለይ ኅብረታችንን ለማጠናከር ቆርጠናል።” በተጨማሪም ጽሑፎቹ እነዚህ ወንድሞች መጀመሪያ ላይ በስብከቱ ሥራ ይካፈሉ እንደነበር ያሳያሉ። ሁለት ሁለት ሆነው እየተጓዙ ይሰብኩ የነበረ ሲሆን ሴቶቹ ደግሞ በአካባቢው የተዋጣላቸው ሚስዮናውያን ሆነው ነበር። የኅብረቱ አባላት ማንኛውንም የፖለቲካ ሥልጣን አይቀበሉም፣ ቃለ መሃላ አይፈጽሙም፣ በወታደራዊ እንቅስቃሴዎች አይካፈሉም እንዲሁም የጦር መሣሪያ አይታጠቁም።

አንድነቱ መቀጠል አልቻለም

ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በኋላ ግን የወንድማማች ኅብረቱ አንድነቱን ጠብቆ መኖር አልቻለም። እምነቶቻቸውን እንዴት መተግበር እንዳለባቸው አለመግባባት የተፈጠረ ሲሆን ይህም ወደ መከፋፈል አመራ። በ1494 ኅብረቱ ብዙኃኑ እና አናሳው ተብሎ ለሁለት ተከፈለ። የብዙኃኑ ቡድን መጀመሪያ ያምንባቸው የነበሩትን እምነቶች ቀስ በቀስ እያላላ ሲሄድ አናሳው ቡድን ግን ከፖለቲካና ከዓለም መለየትን በሚመለከት አቋማቸውን ማላላት እንደሌለባቸው ይሰብክ ነበር።​—⁠“የብዙኃኑ ቡድን ከምን ደረሰ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ለምሳሌ ያህል አንድ የአናሳው ቡድን አባል እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በሁለት መንገድ የሚሄዱ ሰዎች ለአምላክ የሚታዘዙትና የሚገዙት አልፎ አልፎና ጥቃቅን በሆኑ ጉዳዮች ብቻ ስለሆነና ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ግን የራሳቸውን መንገድ ስለሚከተሉ አምላክን እያገለገሉ መጽናታቸው አስተማማኝ አይደለም። . . . ጽኑ አቋምና ንጹሕ ሕሊና ይዘው ዕለት ዕለት መስቀላቸውን ተሸክመው ጌታ ክርስቶስን በጠበበው መንገድ ከሚከተሉት መካከል ለመቆጠር እንፈልጋለን።”

የአናሳው ቡድን አባላት መንፈስ ቅዱስ የአምላክ ኃይል ወይም የእርሱ “ጣት” እንደሆነ ያምኑ ነበር። የኢየሱስን ቤዛ በሚመለከት ደግሞ ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ ኃጢአተኛው አዳም ያጣውን ለማካካስ ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ እንደከፈለ ያምናሉ። ለኢየሱስ እናት ለማርያም ከልክ ያለፈ ክብር አይሰጡም ነበር። ሁሉም አማኞች ካህናት ናቸው የሚለውን የቀድሞ እምነት የሚከተሉ ሲሆን ጋብቻን ግን አይከለክሉም። የጉባኤው አባላት በሙሉ በስብከቱ ሥራ እንዲካፈሉ የሚያበረታቱ ሲሆን ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችን ያስወግዳሉ። ከወታደራዊና ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ፍጹም ገለልተኞች ነበሩ። (“አናሳው ቡድን ምን ብሎ ያምን ነበር?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) የአናሳው ቡድን አባላት በመጽሐፎቻቸው ላይ ያሰፈሯቸውን የአቋም መግለጫዎች በጥብቅ ስለሚከተሉ ራሳቸውን የመጀመሪያው የወንድማማች ኅብረት እውነተኛ ተከታይ እንደሆኑ አድርገው ይቆጥሩ ነበር።

በድፍረት በመናገራቸው ለስደት ተዳርገዋል

የአናሳው ቡድን አባላት የብዙኃኑን ቡድን ጨምሮ ሌሎች ሃይማኖቶችን በድፍረት ይነቅፉ ነበር። እነርሱን አስመልክተው እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “የራሳቸው እምነት የሌላቸው ሕፃናት እንዲጠመቁ ታስተምራላችሁ። በዚህም ማስተዋል በጎደላቸው ሰዎች ገፋፊነት የሕፃናትን ጥምቀት ያስተማረውን ዳየኒሺየስ የተባለ ጳጳስ ልማድ ትከተላላችሁ። . . . ሉተርን፣ ሜላንቸቶንን፣ ቡሴሩስን፣ ኮርቪንን፣ ዪሌሽን፣ ቡሊነርን . . . እንዲሁም የብዙኃኑን ቡድን ጨምሮ ሁሉም አስተማሪዎችና የሃይማኖት ምሑራን ማለት ይቻላል ቀስ በቀስ ተስበው ተመሳሳይ አመለካከት ይዘዋል።”

ከዚህ አኳያ የአናሳው ቡድን አባላት የስደት ዒላማ መሆናቸው ምንም አያስደንቅም። በ1524 ያን ካሌኔስ የተባለው አንደኛው የቡድኑ መሪ የተገረፈ ከመሆኑም በላይ በእሳት ተለብልቧል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሦስት የአናሳው ቡድን አባላት በእንጨት ላይ ተሰቅለው ተቃጥለዋል። አናሳው ቡድን የመጨረሻው መሪያቸው ከሞተ በኋላ ማለትም በ1550 ገደማ ደብዛው የጠፋ ይመስላል።

ሆኖም የአናሳው ቡድን አማኞች በመካከለኛው መቶ ዘመን በአውሮፓ በነበረው ሃይማኖታዊ አመለካከት ላይ አሻራቸውን ትተው አልፈዋል። እርግጥ ነው፣ በጊዜው የነበረው ትክክለኛ ‘እውቀት’ የተትረፈረፈ ስላልነበር አናሳው ቡድን ለረጅም ዘመናት የቆየውን መንፈሳዊ ጨለማ ለመግፈፍ አልቻለም። (ዳንኤል 12:4) የሆነ ሆኖ የቡድኑ አባላት ተቃውሞ እያለም በጠባቡ መንገድ ለመጓዝ የነበራቸው ጠንካራ ፍላጎት በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ሊኮርጁት የሚገባ ነው።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ከ1500 እስከ 1510 ድረስ ባሉት ዓመታት በቦሔሚያ [በቼክ] ቋንቋ ከታተሙት 60 መጻሕፍት መካከል 50ዎቹ የተዘጋጁት በወንድማማች ኅብረቱ አባላት ነው

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የብዙኃኑ ቡድን ከምን ደረሰ?

የብዙኃኑ ቡድን መጨረሻው ምን ሆነ? አናሳው ቡድን ከታሪክ ገጾች ደብዛው ከጠፋ በኋላ የብዙኃኑ ቡድን የወንድማማች ኅብረት የሚለውን የቀድሞ ስሙን ይዞ እንቅስቃሴውን ቀጠለ። ውሎ አድሮ ቡድኑ መጀመሪያ በነበሩት እምነቶች ላይ ማስተካከያዎችን አድርጓል። በ16ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ የወንድማማች ኅብረቱ የሉተራን እምነት ተከታዮች ከነበሩት የቼክ ዩትራክዌስቶች ጋር አንድነት ፈጠረ። a ይሁን እንጂ የኅብረቱ አባላት መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች ሃይማኖታዊ መጻሕፍትን በመተርጎሙና በማዘጋጀቱ ሥራ በንቃት መካፈላቸውን ቀጥለዋል። የሚያስገርመው መጀመሪያ አካባቢ ባሳተሟቸው ጽሑፎች የመጀመሪያ ገጽ ላይ ቴትራግራማተን በመባል የሚታወቁት የአምላክን የግል ስም የሚወክሉ አራት የዕብራይስጥ ፊደላት ይወጡ ነበር።

በ1620 የቼክ መንግሥት በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተጽዕኖ ሥር ወድቆ ነበር። በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ የብዙኃኑ ቡድን አባላት አገሪቱን ለቅቀው የተሰደዱ ሲሆን በባዕድ አገሮች እንቅስቃሴያቸውን ቀጥለዋል። ከጊዜ በኋላም ቡድኑ የሞራቪያ ቤተ ክርስቲያን (ሞራቪያ የቼክ ግዛት አካል ናት) ተብሎ መጠራት የጀመረ ሲሆን አሁን ድረስ እንቅስቃሴ ያደርጋል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ዩትራክዌስት የሚለው ቃል “ከሁለቱም” የሚል ትርጉም ካለው ዩትራክዌ ከሚለው የላቲን ቃል የመጣ ነው። በቅዱስ ቁርባን ሥርዓት ወቅት ወይኑን ለምእመናኑ ከማያቀርቡት የሮማ ካቶሊክ ቀሳውስት በተቃራኒ ዩትራክዌስቶች (ከሁሳውያን የተገነጠሉ ቡድኖች) ወይኑንም ቂጣውንም ለምእመናኑ ያቀርባሉ።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አናሳው ቡድን ምን ብሎ ያምን ነበር?

ከ15ኛው እስከ 16ኛው መቶ ዘመን የወንድማማች ኅብረት ሥራዎች በሚል ርዕስ ከተጻፉት መጻሕፍት የተወሰዱት የሚከተሉት ሐሳቦች አናሳው ቡድን ምን ብሎ ያምን እንደነበር ያሳያሉ። በአናሳው ቡድን መሪዎች የተጻፉት እነዚህ ሐሳቦች በዋነኝነት ያነጣጠሩት በብዙኃኑ ቡድን ላይ ነበር።

ሥላሴ:- “መጽሐፍ ቅዱስን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ብታነቡ ብዙ ሰዎች እንደሚያስቡት አምላክ ሥላሴዎች በሚባሉ የየራሳቸው ስም ባላቸው ሦስት አካላት የተከፋፈለ እንደሆነ የሚያሳይ ሐሳብ አታገኙም።”

መንፈስ ቅዱስ:- “መንፈስ ቅዱስ የአምላክ ጣት እንዲሁም አብ በክርስቶስ ቸርነት አማካኝነት ለአማኞች የሚሰጠው የአምላክ ስጦታ፣ አጽናኝ ወይም የአምላክ ኃይል ነው። መንፈስ ቅዱስ እንደ አምላክ ወይም እንደ አንድ አካል ተደርጎ መጠራት እንዳለበት የሚያሳይ ሐሳብ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አናገኝም፤ የሐዋርያት ትምህርቶችም ቢሆኑ ይህን አያሳዩም።”

ክህነት:- “እናንተን “ካህን” ብለው መጥራታቸው ትክክል አይደለም፤ ቆባችሁን ብታወልቁና ዘይታችሁን ባትይዙ ከተራው ሰው በምንም አትበልጡም። ቅዱስ ጴጥሮስ እንደሚከተለው በማለት ሁሉም ክርስቲያኖች ካህናት እንዲሆኑ ግብዣ አቅርቧል:- እናንተ ደግሞ መንፈሳዊ መሥዋዕት ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት ሁኑ። (1 ጴጥሮስ 2)”

ጥምቀት:- “ጌታ ክርስቶስ ሐዋርያቱን እንዲህ ብሏቸው ነበር:- ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ለሚያምኑት ስበኩ። (ማርቆስ ምዕራፍ 16) የሚድኑት ሲያምኑና ሲጠመቁ ብቻ ነው። እናንተ ግን እምነት የሌላቸው ትናንሽ ሕፃናት እንዲጠመቁ ታስተምራላችሁ።”

ገለልተኝነት:- “የቀድሞ ወንድሞቻችሁ ይጸየፉትና እንደ ርኩስ አድርገው ይመለከቱት የነበረውን ወታደር መሆንንና መግደልን ወይም የጦር መሣሪያ ታጥቆ በመንገዶች ላይ መዘዋወርን እንደ መልካም ነገር ቆጥራችሁታል። . . . ስለዚህ እናንተም ሆናችሁ ሌሎች አስተማሪዎች ስለሚከተለው ትንቢታዊ ቃል በቂ ግንዛቤ እንደሌላችሁ ይሰማናል:- በዚያም የቀስትን ኃይል፣ ጋሻን ሰይፍን ሰልፍንም ሰበረ። (መዝሙር 75 [በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ መዝሙር 76]) እንዲሁም:- በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጐዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን የጌታችን ምድር በመለኮታዊ እውቀት ትሞላለች፣ ወዘተ ይላል። (ኢሳይያስ ምዕራፍ 11)”

ስብከት:- “መጀመሪያ ላይ ሴቶች ወደ ንስሐ ያመጧቸው ሰዎች ቁጥር ጳጳሱም ሆነ ሁሉም ቀሳውስት ወደ ንስሐ ካመጧቸው ሰዎች እንደሚበልጥ እናውቃለን። አሁን ግን ቀሳውስቱ በራሳቸውና ቤተ ክርስቲያን በምትሰጣቸው መኖሪያ ቤት ውስጥ ተንደላቅቀው ይኖራሉ። ይህ ትልቅ ስህተት ነው! ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ።”

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ጀርመን

ፖላንድ

ቼክ ሪፑብሊክ

ቦሔሚያ

የኤልበ ወንዝ

ፕራግ

የቨልታቫ ወንዝ

ክላቶቪይ

ኬልቺሴ

ኩንቫልት

ቪሌሞቭ

ሞራቪያ

የዳንዩብ ወንዝ

[በገጽ 10, 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስተግራ:- ፒተር ኬልቺድዝኪ፤ ከታች:- “ኔት ኦቭ ዘ ፌዝ” ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ ገጽ

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፕራጉ ግሬገሪ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]

ስዕሎቹ በሙሉ:- S laskavým svolením knihovny Národního muzea v Praze, C̆esko