የሚስዮናዊነት መንፈስ በመያዛችን በጣም ተባርከናል
የሕይወት ታሪክ
የሚስዮናዊነት መንፈስ በመያዛችን በጣም ተባርከናል
ቶም ኩክ እንደተናገረው
የተኩስ እሩምታው የቀትሩን ጸጥታ በድንገት አደፈረሰው። በአትክልት ቦታችን ባሉት ዛፎች መካከል ጥይት እያፏጨ ሲያልፍ ሰማን። ምን ተፈጥሮ ነው? መፈንቅለ መንግሥት እንደተካሄደና ጄኔራል ኢዲ አሚን በኡጋንዳ ሥልጣን መያዛቸውን ብዙም ሳይቆይ አወቅን። ይህ የሆነው በ1971 ነበር።
እኔና ባለቤቴ አን በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ሰላም ከሰፈነበት ከእንግሊዝ ተነስተን መረጋጋት ወደሌለበት ወደዚህ የአፍሪካ አገር የመጣነው ለምን ነበር? በተፈጥሮዬ ወደ ተለያዩ ቦታዎች መጓዝ የምወድ ብሆንም ወደዚህ የመጣንበት ዋነኛ ምክንያት ግን ወላጆቼ የአምላክን መንግሥት በቅንዓት በመስበክ ረገድ የተዉት ምሳሌ የሚስዮናዊነት መንፈስ ስላሳደረብኝ ነው።
በነሐሴ 1946 በአንድ ሞቃታማ ቀን ወላጆቼ ለመጀመሪያ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኙበትን ወቅት አልረሳውም። በደጃፉ ላይ ቆመው ከሁለቱ እንግዶች ጋር ለረጅም ሰዓት ተነጋገሩ። ፍሬዘር ብራድበሪ እና ሜሚ ሽሪቭ የሚባሉት እነዚህ ሁለት ሰዎች ደጋግመው ወደ ቤታችን ይመጡ የነበረ ሲሆን በቀጣዮቹ ወራት ውስጥ የቤተሰባችን ሕይወት በከፍተኛ ሁኔታ ተለወጠ።
ወላጆቼ የተዉት ድፍረት የተሞላበት ምሳሌ
ወላጆቼ በተለያዩ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ይካፈሉ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ከመጀመራችን ጥቂት ቀደም ብሎ የዊንስተን ቸርችል ፎቶዎች ቤታችን ውስጥ ተለጥፈው ነበር። ከጦርነቱ በኋላ በተደረጉት ብሔራዊ ምርጫዎች ወቅት የወግ አጥባቂው ፓርቲ ኮሚቴ የሚሰበሰበው እኛ ቤት ነበር። ከዚህም በላይ ቤተሰባችን ታዋቂ ከሆኑ የሃይማኖት ሰዎችና በማኅበረሰቡ
ዘንድ ከተከበሩ ሰዎች ጋር ትውውቅ ነበረው። በወቅቱ ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ብሆንም ዘመዶቻችን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ግንኙነት መጀመራችንን ሲሰሙ ምን ያህል እንደደነገጡ አይረሳኝም።አብረናቸው እንሰበሰብ የነበሩ ምሥክሮች አገልግሎቱን በሙሉ ነፍስና በድፍረት ማከናወናቸው ወላጆቼ በስብከቱ ሥራ በትጋት እንዲሳተፉ አነሳስቷቸዋል። ብዙም ሳይቆይ አባቴ የትውልድ መንደራችን በሆነው በስፓንደን ዋና የገበያ ቦታ ድምፅ ማጉያ ተጠቅሞ ንግግር መስጠት ጀመረ። እኔና እህቶቼ ደግሞ ሰዎች ሊያዩን በሚችሉ ቦታዎች ላይ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ይዘን እንቆም ነበር። እርግጥ አብረውኝ የሚማሩ ልጆች በአጠገቤ ሲያልፉ መሬት ተሰንጥቃ ብትውጠኝ እመኝ ነበር።
የወላጆቼ ምሳሌነት ታላቅ እህቴ ዳፍኒ አቅኚ እንድትሆን አነሳሳት። በ1955 ከጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ከተመረቀች በኋላ በጃፓን ሚስዮናዊ ሆና እንድታገለግል ተመደበች። a ታናሽ እህቴ ዞዪ ግን ይሖዋን ማገልገል አቆመች።
በዚህ ጊዜ ለጽሑፎች ሥዕል የማዘጋጀትና ፊደላትንም ሆነ ሥዕሎችን ለህትመት የማዘጋጀት ትምህርቴን አጠናቀቅሁ። በወቅቱ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት አብረውኝ በሚማሩት ልጆች ዘንድ ሞቅ ያለ የመወያያ ርዕስ ሆኖ ነበር። በውትድርና አገልግሎት ለመሳተፍ ሕሊናዬ እንደማይፈቅድልኝ ስነግራቸው የማሾፍ መስሏቸው ነበር። ይህ ርዕስ መነሳቱ ከአንዳንዶቹ ተማሪዎች ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመወያየት ብዙ አጋጣሚ ሰጥቶኛል። የውትድርና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኔ የ12 ወራት እስር ተፈረደብኝ። በኮሌጁ ውስጥ ከነበሩት ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ፍላጎት ያሳዩ ተማሪዎች መካከል አንዷ ከጊዜ በኋላ ባለቤቴ ሆነች። አን እውነትን እንዴት እንደሰማች እስቲ ራሷ ትንገራችሁ።
አን እውነትን የሰማችበት መንገድ
“ቤተሰቦቼ ለሃይማኖት ግዴለሾች የነበሩ ከመሆኑም ሌላ በልጅነቴ አላስጠመቁኝም ነበር። እኔ ግን ስለ ሃይማኖት የማወቅ ጉጉት ስለነበረኝ ጓደኞቼ ወደሚሄዱበት ወደማንኛውም ቤተ ክርስቲያን እሄድ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን የማወቅ ፍላጎት ያደረብኝ ቶምና አንድ ሌላ የይሖዋ ምሥክር ኮሌጅ ውስጥ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ሲወያዩ ከሰማሁ በኋላ ነበር። ቶምና ይህ ምሥክር የውትድርና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ወኅኒ መውረዳቸውን ስሰማ በጣም ደነገጥኩ።
“ቶም እስር ቤት እያለ እንጻጻፍ የነበረ ሲሆን ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለኝ ፍላጎትም እየጨመረ ሄደ። ትምህርቴን ለመቀጠል ወደ ለንደን ከሄድኩ በኋላ ሙሪየል አልብሬኸት ከተባለች ሴት ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማሁ። ሙሪየል በኢስቶኒያ ሚስዮናዊ ሆና ታገለግል የነበረ ሲሆን እርሷና እናቷ በጣም ያበረታቱኝ ነበር። በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲሁም ቪክቶሪያ ባቡር ጣቢያ አካባቢ ቆሜ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ማበርከት ጀመርኩ።
“የምሰበሰበው በደቡባዊ ለንደን በሚገኘው በሳውዝዋርክ ጉባኤ ነበር። የጉባኤው አባላት ከተለያዩ አገሮች የመጡ በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆኑ ወንድሞችንና እህቶችን ያቀፈ ሲሆን አብዛኞቹም ኑሯቸው ዝቅተኛ ነበር። ለጉባኤው እንግዳ የነበርኩ ቢሆንም ልክ እንደ ቤተሰባቸው አድርገው ነበር የሚመለከቱኝ። የጉባኤው አባላት ያሳዩኝ ፍቅር የጀመርኩት ጎዳና በእርግጥ የእውነት መንገድ መሆኑን እንዳምን ስላስቻለኝ በ1960 ተጠመቅሁ።”
ሁኔታችን እንጂ ግባችን አልተቀየረም
በ1960 መገባደጃ ላይ እኔና አን ተጋባን፤ ሁለታችንም ሚስዮናዊ ሆኖ የማገልገል ግብ ነበረን። ሆኖም
ልጅ ልንወልድ መሆኑን ስናውቅ ሁኔታችን ተለወጠ። ሴት ልጃችን ሤራ ከተወለደች በኋላ እኔና አን የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አገር የማገልገል ፍላጎት ነበረን። ወደ ተለያዩ አገሮች የሥራ ማመልከቻ ላክሁ። በመጨረሻ ግንቦት 1966 ከኡጋንዳ ትምህርት ሚኒስቴር ሥራ መጀመር እንደምችል የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰኝ። ይሁን እንጂ በዚህ ወቅት አን ሁለተኛ ልጃችንን ጸንሳ ነበር። አንዳንዶች በጣም ሩቅ ወደሆነ አገር መሄዳችን ጥሩ እንዳልሆነ ተሰማቸው። ስለ ጉዳዩ ዶክተራችንን ስናማክረው “የምትሄዱ ከሆነ ባለቤትህ የሰባት ወር ነፍሰ ጡር ከመሆኗ በፊት መሄድ አለባችሁ” አለን። በመሆኑም ወዲያው ወደ ኡጋንዳ አቀናን። በዚህም ምክንያት ወላጆቻችን ሁለተኛዋ ልጃችን ሬቸል ሁለት ዓመት እስኪሆናት ድርስ አላዩአትም። በአሁኑ ጊዜ እኛም አያት ለመሆን በመብቃታችን ወላጆቻችን ያሳዩትን የራስን ጥቅም የመሰዋት መንፈስ ማድነቅ ችለናል።በ1966 ኡጋንዳ ስንደርስ በአንድ በኩል ብንደሰትም በሌላ በኩል ደግሞ ግር ብሎን ነበር። ከአውሮፕላኑ እንደወረድን ወዲያው ያስገረመን የምናያቸው ነገሮች ቀለም ድምቀት ነበር። የመጀመሪያው ቤታችን የሚገኘው ኢጋንጋ የምትባለው ትንሽ ከተማ አቅራቢያ ነበር። ይህ ቦታ የናይል ወንዝ ከሚነሳበት ከጂንጃ ከተማ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ለእኛ ቅርብ የሚባሉት ምሥክሮች የሚኖሩት በጂንጃ ባለ ገለልተኛ ቡድን ነበር። ቡድኑን የሚረዱት ጊልበርትና ጆን ዎልተርስ እንዲሁም ስቲቭንና ባርባራ ሃርዲ የተባሉ ሚስዮናውያን ነበሩ። ይህን ቡድን በቅርብ ሆነን መርዳት እንድንችል ወደ ጂንጃ ለመቀየር አመለከትኩ። ሬቸል ከተወለደች በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወደ ጂንጃ ተዛወርን። በዚያ ከነበሩት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ታማኝ ወንድሞች ጋር አብረን በማገልገላችንና ቡድኑ አድጎ በኡጋንዳ ውስጥ ሁለተኛው ጉባኤ ለመሆን ሲበቃ በማየታችን ተደስተናል።
በባዕድ አገር በቤተሰብ መልክ ማገልገል
እኔና አን ልጆቻችንን ለማሳደግ በጣም ጥሩ የሆነ ቦታ እንደመረጥን ይሰማናል። ከተለያዩ አገሮች ከመጡ ሚስዮናውያን ጋር የማገልገልና አዲስ የተቋቋመው ጉባኤ እድገት እንዲያደርግ የመርዳት አስደሳች አጋጣሚ አግኝተናል። ብዙውን ጊዜ ቤታችን እየመጡ የሚጠይቁንን ኡጋንዳውያን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ወዳጅነት መቅመሳችን አስደስቶናል። በተለይ ስታንሊና ኢሲናላ ማኩምባ በጣም ያበረታቱን ነበር።
አስገራሚ የሆኑ የተለያዩ አራዊት በዙሪያችን ስለነበሩ ወደ ቤታችን እየመጡ የሚጠይቁን ወንድሞቻችን ብቻ አልነበሩም። መሸት ሲል ጉማሬዎች ከናይል ወንዝ ይወጡና ቤታችን አጠገብ ይመጡ ነገር። አንድ ቀን በአትክልቱ ውስጥ 6 ሜትር ርዝመት ያለው ዘንዶ ማየታችንን በደንብ አስታውሳለሁ። አንዳንድ ጊዜ የዱር እንስሳት ለማየት አንበሶችና ሌሎች የዱር አራዊት በነፃነት ወደሚፈነጩባቸው ፓርኮች እንሄድ ነበር።
ሕፃን ልጃችንን በጋሪ እየገፋን ስናገለግል የአገሬው ሕዝብ እንደ ጉድ ያየን ነበር። ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ
ብዙውን ጊዜ ትንንሽ ልጆች ይከተሉን ነበር። ሰዎች በአክብሮት አትኩረው ከተመለከቱን በኋላ ሕፃን ልጃችንን ይነኳታል። ሕዝቡ ሰው አክባሪ ስለሆነ አገልግሎት ያስደስተን ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ቀላል በመሆኑ ሰው ሁሉ ወደ እውነት የሚመጣ መሰለን። ሆኖም አብዛኞቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካልሆኑ ልማዶች መላቀቅ ከበዳቸው። ይሁን እንጂ ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃ መከተል በመጀመራቸው ጉባኤው በቁጥር እያደገ ሄደ። በ1968 በጂንጃ ያደረግነው የመጀመሪያው የወረዳ ስብሰባ በጉባኤው ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ የያዘ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናናቸውን አንዳንድ ሰዎች ጨምሮ በናይል ወንዝ የተካሄደው የጥምቀት ሥነ ሥርዓት አስደሳች ትዝታ ጥሎብናል። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ሰላማችን ደፈረሰ።እምነታችንና ጥበብ የመጠቀም ችሎታችን ተፈተነ
በ1971 ጄኔራል ኢዲ አሚን በኃይል ሥልጣን ያዙ። የጂንጃ ከተማ ቀውጢ ሆነ፤ በመግቢያው ላይ የጠቀስኩት ሁኔታ ሲከሰት አትክልት ቦታችን ውስጥ ሻይ እየጠጣን ነበር። ከዚያ በኋላ በነበሩት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ የነበሩት ብዛት ያላቸው የእስያ ተወላጆች ተባረሩ። አብዛኞቹ የውጭ አገር ዜጎች አገሪቱን ለቅቀው ለመሄድ ስለመረጡ ትምህርት ቤቶችና የሕክምና ተቋማት ለከባድ ችግር ተዳረጉ። ከዚያም የይሖዋ ምሥክሮች እንደታገዱ የሚገልጽ አስደንጋጭ አዋጅ ወጣ። የትምህርት ክፍሉ ለደህንነታችን በማሰብ ወደ ዋና ከተማው ወደ ካምፓላ እንድንዛወር አደረገ። ይህ ዝውውር በሁለት መንገዶች ጠቃሚ ነበር። ካምፓላ ውስጥ ብዙም ስለማንታወቅ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ የተሻለ ነፃነት ነበረን። ከዚህም በላይ በጉባኤም ሆነ በመስክ አገልግሎት ብዙ የሚሠራ ነገር ነበር።
ሁለት ልጆች የነበሯቸው ብራያንና ሜሪየን ዋላስ የእኛ ዓይነት ሁኔታ ገጥሟቸው የነበረ ሲሆን እነርሱም ኡጋንዳ ውስጥ ለመቆየት ወሰኑ። በዚያ አስቸጋሪ ወቅት በካምፓላ ጉባኤ ከእነርሱ ጋር አብረን ማገልገል በመቻላችን በጣም ደስተኞች ነበርን። እገዳ በተጣለባቸው ሌሎች አገሮች ስለሚያገለግሉ ወንድሞቻችን ያነበብናቸው ተሞክሮዎች በዚህ ወቅት በጣም አበረታቱን። የምንሰበሰበው በትናንሽ ቡድኖች ሲሆን በወር አንድ ጊዜ በኢንቴቤ የመናፈሻ ቦታዎች ለመጫወት የተገናኘን አስመስለን ብዙ ሆነን እንሰበሰብ ነበር። ልጆቻችን በዚህ መልክ መሰብሰባችንን በጣም ወደዱት።
በስብከቱ ሥራ የምንካፈልበትን መንገድ በተመለከተ በጣም ጠንቃቆች ነበርን። ነጮች ወደ ኡጋንዳውያን ቤቶች መሄዳቸው የሌሎችን ትኩረት በቀላሉ ሊስብ ስለሚችል የአገልግሎት ክልላችን ሱቆች፣ አፓርታማዎችና አንዳንድ የትምህርት ተቋማት ነበሩ። በሱቆች ውስጥ ሳገለግል የምጠቀምበት አንዱ ዘዴ እንደ ስኳር ወይም
ሩዝ ያለ የማይገኝ ዕቃ መጠየቅ ነው። ባለ ሱቁ በአገሪቱ ውስጥ ባለው ሁኔታ እንዳዘነ የሚያሳይ ነገር ከተናገረ የመንግሥቱን መልእክት እነግረዋለሁ። ይህ አቀራረብ ውጤታማ ነበር። አልፎ አልፎ፣ ተመላልሶ መጠየቅ የማደርግለት ሰው ብቻ ሳይሆን ገበያ ላይ ብዙም የማይገኝ ዕቃም በትንሹ አገኛለሁ።ይህ በእንዲህ እንዳለ በዙሪያችን ዓመፅ እየተቀሰቀሰ ነበር። የኡጋንዳና የብሪታኒያ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸ በመሄዱ ባለ ሥልጣናቱ ኮንትራቴን ሳያድሱልኝ ቀሩ። በዚህም ምክንያት በኡጋንዳ ለስምንት ዓመታት ከቆየን በኋላ በ1974 እያዘንን ወንድሞቻችንን ተሰናበትናቸው። ያም ሆኖ የሚስዮናዊነት መንፈሳችን አልጠፋም።
ወደ ኒው ጊኒ ተዛወርን
በጥር 1975 በፓፑዋ ኒው ጊኒ ሥራ አገኘሁ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዚህ የፓስፊክ ክፍል ለስምንት ዓመታት አስደሳች የአገልግሎት ጊዜ አሳለፍን። ከወንድሞቻችን ጋርና በአገልግሎት ያሳለፍነው ጊዜ አስደሳችና የሚክስ ነበር።
ቤተሰባችን በፓፑዋ ኒው ጊኒ ያሳለፍነውን ጊዜ የሚያስታውሰው እንካፈልባቸው በነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማዎች ነው። በየዓመቱ ለአውራጃ ስብሰባ ድራማ በማዘጋጀቱ ሥራ እንካፈል የነበረ ሲሆን ይህም በጣም ያስደስተን ነበር። መንፈሳዊ አመለካከት ካላቸው በርካታ ቤተሰቦች ጋር አብረን የምናሳልፈውን ጊዜ እንወደው የነበረ ከመሆኑም በላይ በልጆቻችን ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። ትልቋ ልጃችን ሴራ ልዩ አቅኚ የሆነውን ሬይ ስሚዝን ካገባች በኋላ በኢሪያን ጃያ (የኢንዶኔዥያ ግዛት የሆነችው የአሁኗ ፓፑዋ) ድንበር አጠገብ አብረው በልዩ አቅኚነት ማገልገል ጀመሩ። ቤታቸው በመንደር ውስጥ የሚገኝ የሳር ጎጆ ነበር፤ ሴራ በዚያ ምድብ ያሳለፈችው ጊዜ ግሩም ሥልጠና እንደሰጣት ትናገራለች።
ከሁኔታዎች መለዋወጥ ጋር ራሳችንን ማስማማት
በፓፑዋ ኒው ጊኒ ለስምንት ዓመታት ካገለገልን በኋላ ወላጆቼ የሚንከባከባቸው ሰው ያስፈልጋቸው ጀመር። ወላጆቼ እኛ ወደ እንግሊዝ ከምንመለስ ይልቅ እነርሱ እኛ ጋር መጥተው ለመኖር ስለተስማሙ በ1983 ሁላችንም ወደ አውስትራሊያ ተዛወርን። ወላጆቼ በጃፓን ከነበረችው ከእህቴ ከዳፍኒ ጋርም ለተወሰነ ጊዜ ኖረዋል። እነርሱ ከሞቱ በኋላ እኔና አን የዘወትር አቅኚ ለመሆን ወሰንን፤ ይህም ከበድ ያሉ ተጨማሪ መብቶች እንድናገኝ አስቻለን።
አቅኚ ሆነን ብዙም ሳንቆይ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት እንድናገለግል ተጠየቅን። ከልጅነቴ ጀምሮ የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ጉብኝት ከፍ አድርጌ እመለከተው ነበር። አሁን እኔ ራሴ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆንኩ። ይህ አገልግሎት እስከዚያ ጊዜ ድረስ ከተሰጡን ምድቦች ሁሉ ከባዱ ነበር። ሆኖም በተደጋጋሚ ጊዜያት ቀደም ሲል ባልተመለከትናቸው መንገዶች ይሖዋ ባርኮናል።
በ1990 ወንድም ቴዎዶር ጃራዝ የዞን የበላይ ተመልካች ሆኖ ወደ አውስትራሊያ መጥቶ እያለ በዚህ ዕድሜያችን ወደ ሌላ አገር ሄደን ማገልገል እንችል እንደሆነ ጠየቅነው። እርሱም “ለምን በሰለሞን ደሴቶች አታገለግሉም?” አለን። ስለዚህ በስተመጨረሻ እኔና አን በ50ዎቹ እድሜ እያለን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ሚስዮናዊ ተቆጥረን ወደ ሰለሞን ደሴቶች አቀናን።
‘በደስታ ደሴቶች’ ማገልገል
የሰለሞን ደሴቶች የደስታ ደሴቶችም ይባላሉ። እኛም በዚህ ቦታ ከአሥር ለሚበልጡ ዓመታት ያከናወንነው አገልግሎት አስደሳች ሆኖልናል። በሰለሞን ደሴቶች የአውራጃ
የበላይ ተመልካች ሆኜ ሳገለግል የወንድሞችና የእህቶችን ደግነት ማየት ችለናል። እንግዳ ተቀባይነታቸው በጥልቅ ነክቶናል። ከዚህም በላይ በሰለሞን ደሴቶች የፒጀንን ቋንቋ ሊረዱት ይችላሉ ብዬ ባሰብኩት መንገድ ለመናገር የማደርገውን ጥረት ሁሉም ያደንቁ ነበር፤ ይህ ቋንቋ በዓለም ላይ በጣም ትንሽ ቃላት ካላቸው ቋንቋዎች መካከል አንዱ ነው።ሰለሞን ደሴቶች ከደረስን ብዙም ሳይቆይ ተቃዋሚዎች በገነባነው ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንዳንጠቀም ለማድረግ ሞከሩ። የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን በሆኒያራ የሚገኘው አዲሱ የመሰብሰቢያ አዳራሻችን በከፊል በእነርሱ ቦታ ላይ እንደተሠራ በመግለጽ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ክስ መሰረተ። መንግሥት ክሳቸውን ሰምቶ በእኛ ላይ ስለፈረደብን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ አልን። ለይግባኙ የሚሰጠው መልስ 1,200 ሰዎች የሚይዘው አዲሱ የመሰብሰቢያ አዳራሻችን መፍረስ አለመፍረሱ የሚለይበት ይሆናል።
ጉዳዩ ለአንድ ሳምንት ያህል በፍርድ ቤት ታየ። በእኛ ላይ የቀረበው ክስ ሲነበብ የተቃዋሚው ወገን ጠበቃ በትምክህት ተኩራራብን። ከዚያም ከኒው ዚላንድ የመጣው ጠበቃችን ወንድም ዋረን ካትከርት ጠንካራ የመከራከሪያ ነጥቦች በማቅረብ የተቃዋሚዎቹን ክስ አንድ በአንድ ውድቅ አደረገው። የክሱ ወሬ በሰፊው ተሰራጭቶ ስለነበር አርብ ዕለት ፍርድ ቤቱ በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት ባለ ሥልጣናት እንዲሁም በክርስቲያን ወንድሞቻችን ታጨቀ። የፍርድ ቤቱ ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ በተለጠፈው ፕሮግራም ላይ በስህተት የተጻፈው ነገር ትዝ ይለኛል። ማስታወቂያው ጉዳዩ “በከሳሽ የሰለሞን ደሴቶች መንግሥት እንዲሁም የሚላኔዥያ ቤተ ክርስቲያን እና በተከሳሽ ይሖዋ” መካከል እንደሆነ ይገልጽ ነበር። በክሱ እኛ ረታን።
ይሁን እንጂ በደስተኞቹ ደሴቶች የነበረው አንጻራዊ ሰላም ብዙም አልዘለቀም። እኔና አን በሕይወታችን ለሁለተኛ ጊዜ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት የሚያስከትለው ሁካታና ዓመፅ አጋጠመን። የተቀሰቀሰው የጎሳ ግጭት የእርስ በርስ ጦርነት አስከተለ። ሰኔ 5, 2000 የአገሪቱ መንግሥት ተገለበጠና ዋና ከተማዋ በታጣቂ አብዮተኞች እጅ ወደቀች። ለተወሰኑ ሳምንታት የመንግሥት አዳራሻችን ለተፈናቃዮች ማረፊያ ሆነ። እርስ በርስ የሚጠላሉ ጎሳዎች አባላት ቢሆኑም ክርስቲያን ወንድሞቻችን እንደ አንድ ሰላማዊ ቤተሰብ በአንድ ጣራ ሥር አብረው መኖራቸው ባለ ሥልጣናቱን አስገረማቸው። በእርግጥም ይህ ግሩም ምሥክርነት ነበር!
አብዮተኞቹም ጭምር የይሖዋ ምሥክሮችን የገለልተኝነት አቋም ያከብሩ ነበር። በዚህም ምክንያት ከጦር አዛዦቹ አንዱ ተቃዋሚዎቹ ወገኖች በሚቆጣጠሩት አካባቢ ተነጥለው ለቀሩ ወንድሞቻችን ጽሑፎችና ሌሎች ቁሳቁሶችን የያዘ ከባድ መኪና ለመላክ እንዲፈቅድልን ማድረግ ችለናል። ለወራት ያህል ከእኛ ጋር ተቆራርጠው የነበሩትን ቤተሰቦች ስናገኛቸው ሁላችንም የደስታ እንባ አነባን።
የምናመሰግንበት ብዙ ምክንያት አለን
በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍነውን ጊዜ መለስ ብለን ስናስበው የምናመሰግንበት ብዙ ምክንያት አለ። እንደ ወላጅነታችን መጠን ሁለቱም ሴቶች ልጆቻችን ሬይ እና ጆን ከተባሉት ባሎቻቸው ጋር ሆነው ይሖዋን በታማኝነት ሲያገለግሉ በመመልከታችን ተባርከናል። በሚስዮናዊነት በተመደብንበት ቦታ እውነተኛ ድጋፍ ሆነውልናል።
ላለፉት 12 ዓመታት እኔና አን በሰለሞን ደሴቶች ቅርንጫፍ ቢሮ የማገልገል መብት ያገኘን ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር በእጥፍ አድጎ ከ1,800 በላይ ሲሆን መመልከት ችለናል። በቅርብ ጊዜ በፓተርሰን ኒው ዮርክ ለቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባላት በተዘጋጀው ትምህርት ቤት የመካፈል ተጨማሪ መብት አግኝቻለሁ። በእርግጥም የሚስዮናዊነት መንፈስ በመያዛችን በበረከት የተሞላ የማያስቆጭ ሕይወት መምራት ችለናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በጥር 15, 1977 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “ራሳችንን ከማቅረብ ወደኋላ አላልንም” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1960 በሠርጋችን ዕለት
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኡጋንዳ ስታንሊና ኢሲናላ ማኩምባ ለቤተሰባችን የብርታት ምንጭ ሆነው ነበር
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሤራ ወደ ጎረቤታችን ጎጆ ስትሄድ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሰለሞን ደሴቶች ነዋሪዎችን ለማስተማር በሥዕል እጠቀም ነበር
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሰለሞን ደሴቶች በገለልተኛ ክልል በሚገኝ ጉባኤ ስብሰባ ሲካሄድ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቤተሰባችን በአሁኑ ወቅት