“በምድር እምብርት” የተደረገ ስብሰባ
“በምድር እምብርት” የተደረገ ስብሰባ
“ቴ ፒቶ ኦ ቴ ሄኑዋ” የሚሉ ቃላትን ሰምተህ ታውቃለህ? በኢስተር አይላንድ በሚነገረው ራፓ ኑኢ በተባለው ቋንቋ እነዚህ ቃላት “የምድር እምብርት” የሚል ትርጉም አላቸው። እዚህ ቦታ ላይ የተካሄደውን ስብሰባ ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?
ነዋሪዎቿ ራፓ ኑኢ እያሉ የሚጠሯት ኢስተር አይላንድ የሚያስደንቁ ገጽታዎች ያሏት ለብቻዋ ተነጥላ የምትገኝ ደሴት ናት። ከቺሊ ዋና ከተማ ከሳንቲያጎ 3,790 ኪሎ ሜትር ርቃ በደቡባዊ ፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ትገኛለች። ይህች ደሴት የቺሊ ግዛት የሆነችው መስከረም 9, 1888 ነው።
ሦስት ማዕዘን ቅርጽ ያላት ይህች ደሴት 166 ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ያላት ስትሆን ከጊዜ በኋላ በከሰሙ ሦስት እሳተ ገሞራዎች የተፈጠረች ናት። እንዲያውም እንደ ብዙዎቹ የፓስፊክ ውቅያኖስ ደሴቶች ሁሉ የኢስተር ደሴትም ከባሕር በታች ባሉ ግዙፍ ተራሮች አናት ላይ የምትገኝ ናት። መላዋ ደሴት ተፈጥሯዊ ሐውልት በመባል ትታወቃለች። ደሴቲቱ በይበልጥ የምትታወቀው ሞአይ በመባል በሚታወቁ እጅግ አስደናቂ በሆኑ የድንጋይ ሐውልቶች ነው። a
የኢስተር ደሴት እጅግ ማራኪ ከሆነው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧና ታሪካዊ ቦታዎቿ በተጨማሪ የተለያዩ ጣፋጭ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች የሞሉባት ናት። ከእነዚህም መካከል አናናስ፣ አቮካዶ፣ ፓፓያና ዘጠኝ ዓይነት የሙዝ ዝርያዎች ይገኛሉ። በተጨማሪም ዓሣን ጨምሮ ሌሎች ከባሕር የሚገኙ ምግቦች አሉ።
የደሴቲቱ አየር እጅግ ተስማሚ ሲሆን በየጊዜው የሚጥለው ዝናብና በተደጋጋሚ ጊዜያት የሚታዩት ቀስተ ደመናዎች ጎብኚዎች ንጹሕ አየር እንዲያገኙና ቀልብ በሚስቡ እይታዎች እንዲደሰቱ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በአሁኑ ጊዜ ደሴቲቱ ወደ 3,800 ገደማ የሚሆኑ ነዋሪዎች አሏት። የደሴቲቱ ተወላጆች ከአውሮፓውያን፣ ከቺሊዎችና ከሌሎች አገሮች ከመጡ ሰዎች ጋር ተቀላቅለው ይኖራሉ። ከአውሮፓና እስያ የሚመጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች ደሴቲቱን ስለሚጎበኙ ቱሪዝም ዋነኛ የገቢ ምንጯ ነው።
የመንግሥቱ ዘር ተዘራ
የ1982 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል:- “ለተወሰነ ጊዜ በኢስተር አይላንድ አንዲት አስፋፊ ብቻ ነበረች። [በቺሊ] ቅርንጫፍ ቢሮ የምትገኝ አንዲት ሚስዮናዊት እህት በደብዳቤ አማካኝነት በመንፈሳዊ ትረዳት ነበር። ይህች አስፋፊ ወደ ቺሊ ከተመለሰች በኋላም የመጠበቂያ ግንብ ኮንትራት ያላቸው የደሴቲቱ ነዋሪዎች ነበሩ። የሚያስገርመው ደግሞ በሚያዝያ 1980 አንድ ፍላጎት ያለው ሰው የመታሰቢያው በዓል መቼ እንደሚከበር ለማወቅ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ስልክ ደወለ። ከዚያም በዚያው ዓመት በቫልፐራይዞ ይኖሩ የነበሩ አንድ ባልና ሚስት ወደዚህች ደሴት በመዛወር ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመሩ። በሚያዝያ 1981 በደሴቲቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የመታሰቢያው በዓል የተከበረ ሲሆን በበዓሉ ላይ 13 ሰዎች ተገኝተዋል። ‘ምሥራቹ’ ወደዚህ ገለልተኛ ሥፍራ በመዝለቁ እጅግ ተደስተናል!”
ከጊዜ በኋላ ጥር 30, 1991 ቅርንጫፍ ቢሮው ዳሪዮ እና ዊኒ ፈርናንዴዝ የተባሉ ባልና ሚስት ልዩ አቅኚዎችን ወደ ደሴቲቱ ላከ። ወንድም ፈርናንዴዝ “ከአምስት ሰዓት በረራ በኋላ በጣም አስደናቂ የሆነ ባሕል ወደሚገኝበትና እጅግ ገለልተኛ ወደሆነው የምድር ክፍል ደረስን” ሲል በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ይገልጻል። በደሴቲቱ ላይ በሚኖር አንድ ወንድምና በቅርቡ ከሁለት ልጆቿ ጋር ወደዚያ በመጣች አንዲት እህት እርዳታ ስብሰባዎችን ማድረግና የስብከቱን ሥራ ማካሄድ የሚቻልበት ዝግጅት ተደረገ። ምንም እንኳ የቤተሰብ ተጽዕኖ፣ ሃይማኖታዊ ተቃውሞና በአካባቢው ባሕል የተለመዱ አንዳንድ ለየት ያሉ የአኗኗር ዘይቤዎች ቢኖሩም ይሖዋ ጥረታቸውን ባርኮላቸዋል። ወንድም ዳሪዮ እና እህት ዊኒ በልዩ አቅኚነት ማገልገላቸውን ያቆሙ ቢሆኑም በዚያ የተወለደውን ልጃቸውን እያሳደጉ በደሴቲቱ መኖራቸውን ቀጥለዋል። በአሁኑ ጊዜ በደሴቲቱ 32 አስፋፊዎች ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ የራፓ ኑኢ ተወላጆች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ወደ ደሴቲቱ ተዛውረው መኖር የጀመሩ ወይም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ለማገልገል ሲሉ ወደ ደሴቲቱ የመጡ ናቸው።
የወረዳ ስብሰባ ለማካሄድ የተደረገ ዝግጅት
ደሴቲቱ ከአህጉሩ በጣም ርቃ ስለምትገኝ ጉባኤው በዓመት ሦስት ጊዜ የልዩ ስብሰባ ቀን፣ የወረዳ ስብሰባና የአውራጃ ስብሰባ ፕሮግራሞች የተቀዱባቸው የቪዲዮ ካሴቶች ይላኩለታል። ይሁን እንጂ በ2000 መገባደጃ ላይ በቺሊ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በደሴቲቱ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቅ ስብሰባ እንዲካሄድ ለማድረግ አቀደ። በመጨረሻም ኅዳር 2001 የወረዳ ስብሰባ እንዲደረግ ተወሰነ፤ ከዚያም በቺሊ የተለያዩ ግዛቶች የሚገኙ የተወሰኑ ወንድሞችና እህቶች በዚህ ልዩ ዝግጅት ላይ እንዲገኙ ተጋበዙ። ወደ ደሴቲቱ የሚደረገው የአውሮፕላን በረራ ውስን በመሆኑ ስብሰባው እሁድና ሰኞ እንዲካሄድ ዝግጅት ተደረገ።
በስብሰባው ላይ እንዲገኙ የተጋበዙት 33 ልዑካን በዚያ ገለልተኛ ሥፍራ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የወረዳ ስብሰባ ላይ የመገኘት አጋጣሚ በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል። በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ በአውሮፕላን ለረጅም ሰዓታት ከበረሩ በኋላ በአየር ማረፊያው ይጠብቋቸው የነበሩ ወንድሞች ሲቀበሏቸው የተሰማቸው ደስታ ልዩ ነበር። በደሴቲቱ ልማድ መሠረት ወንድሞች ለልዑካኑ የአበባ ጉንጉን አበረከቱላቸው። ከዚያም ወደሚያርፉበት ቦታ የወሰዷቸው ሲሆን ደሴቲቱን ለአጭር ጊዜ እየተዘዋወሩ ከጎበኙ በኋላ በስብሰባው ፕሮግራም ላይ ክፍል ያላቸው ሁሉ በመንግሥት አዳራሹ ተገኙ።
ያልተጠበቀ ሰው ስብሰባውን ለሕዝብ አስተዋወቀ
ከልዑካኑ መካከል የተወሰኑት ወደ ስብሰባው እየሄዱ ሳለ አንድ ቄስ የእነሱን መምጣት አስመልክቶ በሬዲዮ ሲናገር በመስማታቸው በጣም ተገረሙ። ከደቡብ አሜሪካ የመጡ ጎብኚዎች በየቤቱ እየሄዱ ስለ ዓለም መጨረሻ እንደሚናገሩ ገለጸ። ይህ ቄስ ምዕመናኑ እነዚህን ሰዎች እንዳይሰሟቸው አጥብቆ ያስጠነቀቀ ቢሆንም የሰጠው ማሳሰቢያ ሕዝቡ በርከት ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ደሴቲቱ እንደመጡ እንዲያውቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ይህም ሕዝቡ የእነዚህን ሰዎች ማንነት የማወቅ ጉጉት እንዲቀሰቀስበት አድርጓል። በቀጣዮቹ ቀናት ልዑካኑ ጥበብ በመጠቀም አጽናኝ የሆነውን የምሥራቹን መልእክት ለሕዝቡ አካፈሉ።
ስብሰባው ተጀመረ
የደሴቲቱ ነዋሪ የሆኑት ወንድሞች በስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ጠዋት በመንግሥት አዳራሹ መግቢያ ላይ ቆመው ልዑካኑን “ኢዮራና ኮኢ! ኢዮራና ኮኢ!” “እንኳን ደህና መጣችሁ!” በማለት አቀባበል አደረጉላቸው። አንዳንድ እህቶች የአገር ልብሳቸውን ለብሰውና በአካባቢው ባሕል መሠረት ፀጉራቸውን ውብ በሆኑ አበቦች አስጊጠው ነበር።
የፕሮግራሙን መጀመር የሚያበስር ደስ የሚል ሙዚቃ ከተሰማ በኋላ በመቶ የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች “ጽና፣ አትነቃነቅ!” የሚል ርዕስ ያለውን መዝሙር በአንድነት ዘመሩ። በደሴቲቱ ላይ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ወንድሞችና እህቶች በአንድነት እንዲህ ሲዘምሩ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። የስብሰባው ሊቀ መንበር ራፓ ኑኢ በተባለው የደሴቲቱ ቋንቋ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ሞቅ ያለ አቀባበል ሲያደርግላቸው በዚያ የሚኖሩት ወንድሞች ከደስታ ብዛት እንባቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው ነበር። በምሳ ሰዓት ሦስት አዳዲስ ምሥክሮች ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት አሳዩ። የመጀመሪያው ቀን ስብሰባ ሲጠናቀቅ ፕሮግራሙ ወንድሞች ከይሖዋም ሆነ ከመላው የወንድማማች ማኅበር ጋር ይበልጥ እንደተቀራረቡ ሆኖ እንዲሰማቸው ረድቷቸው ነበር።—1 ጴጥሮስ 5:9
የማለዳ ምሥክርነት
በደሴቲቱ ባሉት አንዳንድ ሁኔታዎች ምክንያት የሁለተኛው ቀን ፕሮግራም ከምሳ በኋላ ተጀመረ። ስለሆነም ልዑካኑ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የጠዋቱን ጊዜ በመስክ አገልግሎት አሳለፉ። በዚህ ጊዜ ምን ተሞክሮዎች አገኙ?
ስምንት ልጆች ያሏቸው አንዲት አረጋዊት ሴት ካቶሊክ ስለሆኑ ምሥክሮቹን ሊያነጋግሯቸው እንደማይችሉ ገለጹላቸው። የቤተሰብ ችግርንና የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነትን ጨምሮ ሁላችንንም ስለሚያሳስቡን ነገሮች ሊያወያዩአቸው እንደመጡ ሲገልጹላቸው ሴትየዋ ለመስማት ፈቃደኛ ሆኑ።
ሁለት ምሥክሮች አንዲትን አረጋዊት ሊያነጋግሯቸው ሲሉ ሴትየዋ ፊት ነሷቸው። “ሂዱና አገራችሁ ያሉትን ርኅራኄ የሌላቸው ሰዎች አስተምሩ” አሏቸው። ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ እያንዳንዱ ሰው መስማት እንዳለበት ከገለጹላቸው በኋላ ወደ ደሴቲቱ የመጡት ሰዎች ከአምላክ ጋር ያላቸው ዝምድና እንዲጠነክር በሚረዳ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት እንደሆነ ነገሯቸው። (ማቴዎስ 24:14) “ወደፊት እንደዚህች ደሴት ውብ በምትሆነው ምድር ላይ በሽታና ሞት ተወግደው ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ቢያገኙ ደስ አይልዎትም” ሲሉ ጠየቋቸው። ምሥክሮቹ በደሴቲቱ ላይ ያሉት በእሳተ ገሞራ የተፈጠሩ ተራሮች ምን ያህል ዘመን እንዳስቆጠሩ እንዲያስቡ ካደረጓቸው በኋላ ሴትየዋ የሰው ዕድሜ ምን ያህል አጭር እንደሆነ ስላስተዋሉ “ዕድሜያችን እንዲህ አጭር የሆነው ለምንድን ነው?” ሲሉ ጥያቄ አቀረቡ። መዝሙር 90:10ን ሲያስነብቧቸው በጣም ተገረሙ።
ምሥክሮቹ ሴትየዋን እያነጋገሩ ሳለ ጎረቤት ያሉ ሰዎች ሲጮኹ ሰሙ። ምሥክሮቹ ሰዎቹ ምን እያሉ እንዳሉ አልገባቸውም ነበር። ሴትየዋ ጎረቤት ያሉት ሰዎች እየተሳደቡና እንዳትመጡብን እያሉ መሆናቸውን ነገሯቸው። ይሁን እንጂ እኚህ ሴት የቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ በመሆናቸው አባትየው ከሞቱ ወዲህ ቤተሰቡን የመምራት ኃላፊነት የወደቀው በእርሳቸው ላይ ነበር። በመሆኑም በመቃወም ላይ የነበሩትን ዘመዶቻቸውን በቋንቋቸው በመገሰጽ ለወንድሞች የተሟገቱላቸው ከመሆኑም በላይ የተበረከተላቸውን ጽሑፍ በደስታ ተቀበሉ። በዚያው ሳምንት ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ሴትየዋ ከወንድማቸው ጋር በመኪና እየሄዱ ሳለ ምሥክሮቹን በማየታቸው ወንድማቸው መኪናውን እንዲያቆም ነገሩት። ወንድምየው ቅር ቢለውም እንኳ እኚህ ሴት የስብከት ሥራቸው የተሳካ እንዲሆን በመመኘት ምሥክሮቹን ተሰናበቷቸው።
ምንም እንኳ መጀመሪያ ላይ አንዳንድ የደሴቲቱ ነዋሪዎች ከቺሊ የመጡትን ወንድሞች ስብከት የመቀበል ፍላጎት ያልነበራቸው ቢመስልም ወንድሞች የራፓ ኑኢ ነዋሪዎች ደግና ሰው ወዳድ መሆናቸውን ሊገነዘቡ ችለዋል። አብዛኞቹ ምሥራቹን ለመስማት ፈቃደኞች ሆነዋል። እንዲያውም በዚያች ደሴት ከተጠመቁት 20 ምሥክሮች መካከል 6ቱ የደሴቲቱ ተወላጆች ናቸው። ከእነዚህም መካከል አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተቀበለው ሚስቱ ሌላ ክፍል ውስጥ ሆና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና በመስማቱ ነው። በአሁኑ ጊዜ ይህ ሰው ተጠምቆ የጉባኤ አገልጋይ ሲሆን ሚስቱም የተጠመቀች የይሖዋ ምሥክር ሆናለች።
ስብሰባው ቀጠለ
የሁለተኛው ቀን ፕሮግራም እኩለ ቀን ላይ ተጀመረ። የደሴቲቱ ነዋሪዎች ከሆኑት 32 ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም ከቺሊ ከመጡት 33 ልዑካን በተጨማሪ ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎችም በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል። “ፍቅርና እምነት ዓለምን የሚያሸንፈው እንዴት ነው?” የተሰኘውን የሕዝብ ንግግር ጨምሮ አጠቃላይ ፕሮግራሙን ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ ሰዎች ተከታትለውታል። እንዲያውም በስብሰባው ላይ የተገኙት ሰዎች የተለያየ ባሕል ባላቸው የይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለውን ፍቅር በዓይናቸው ሊያዩ ችለዋል።—ዮሐንስ 13:35
በወረዳ ስብሰባው ወቅት የወረዳና የአውራጃ የበላይ ተመልካቾች ከአቅኚዎች ጋር ስብሰባ አድርገው ነበር። በደሴቲቱ የሚኖሩት ሦስት የዘወትር አቅኚዎች ከቺሊ ከመጡት የዘወትርና ልዩ አቅኚዎች ጋር የተሰበሰቡ ሲሆን ሁሉም በእጅጉ ተበረታተዋል።
በማግስቱ አስጎብኚ ሆነው የሚሠሩ በደሴቲቱ የሚኖሩ b
አንዳንድ ወንድሞች ከቺሊ ለመጡት እንግዶቻቸው ደሴቲቱን አስጎበኟቸው። የተቀረጹ የድንጋይ ሐውልቶች የሚገኙበትን ካባ፣ ጥንታዊ ውድድሮች ይካሄዱባቸው የነበሩ ቦታዎችንና የመጀመሪያዎቹ የደሴቲቱ ሰፋሪዎች ያረፉበትን አናኬና በመባል የሚታወቀውን ውብ የባሕር ዳርቻ ጎብኝተዋል።ከቺሊ የመጡት ወንድሞች በደሴቲቱ ከሚኖሩት ወንድሞች ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተሰበሰቡት በጉባኤው የመጽሐፍ ጥናት ስብሰባ ላይ ነበር። ከስብሰባው በኋላ የደሴቲቱ ነዋሪዎች የሆኑት ወንድሞች የባሕል ምግብ በማቅረብ እንግዶቻቸው ያልጠበቁትን ዝግጅት አደረጉላቸው። ከዚያም የአገር ልብሳቸውን ለብሰው ደስ የሚል የባሕል ጭፈራ አሳዩአቸው። እንግዶቹም ሆኑ የራፓ ኑኢ ወንድሞችና እህቶች የወረዳ ስብሰባው እንዲካሄድ ዝግጅት በመደረጉ በጣም ተደስተዋል።
ልዑካኑ በሙሉ በዚያች ገለልተኛ በሆነች ደሴት ከሚገኙት ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር ያሳለፉት አስደሳች ሳምንት ልዩ ፍቅር እንዲያድርባቸው አድርጓቸዋል። በመሆኑም ከወንድሞቻቸው መለየት በጣም ከብዷቸው ነበር። እነዚህን ወዳጆቻቸውንም ሆነ በዚያ ያሳለፉትን አበረታች ጊዜ መቼም አይረሱትም። የደሴቲቱ ነዋሪዎች የሆኑት ወንድሞች በአውሮፕላን ማረፊያው ተገኝተው ልዑካኑን ሲሸኟቸው ከዛጎል የሰሯቸውን የአንገት ጌጦች ሸለሟቸው።
ልዑካኑ ወንድሞቻቸውን ሲሰናበቱ “ኢዮራና! ኦው ሄ ሆኪ ማኢ ኤ ራፓ ኑኢ ኤኤ” ሲሉ ቃል ገቡ። ይህም “ደህና ሁኑ! አንድ ቀን ተመልሰን እንመጣለን” ማለት ነው። አዎን፣ ለብቻዋ ተነጥላ በምትገኘውና አስደናቂ ገጽታዎች ባሏት የኢስተር ደሴት የሚገኙ ወዳጆቻቸውንና መንፈሳዊ ቤተሰቦቻቸውን ተመልሰው የሚያዩበትን ጊዜ ይናፍቃሉ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የሰኔ 22, 2000 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ተመልከት።
b በራኖ ራራኩ ተራራ ላይ ጽሑፍ የተቀረጸባቸው በርካታ ድንጋዮች ይገኛሉ። የደሴቲቱ ገዢ ለመሆን ይፈልጉ የነበሩ ሰዎች የሚያደርጉትን ውድድር የሚጀምሩት ከዚህ ቦታ ነበር። ውድድሩ ገደል ወርዶ ከትናንሾቹ ደሴቶች ወደ አንዱ በዋና በመሻገር በዚያ አካባቢ የምትገኝን የአንዲት ወፍ እንቁላል ይዞ መመለስንና እንቁላሉ ሳይሰበር ገደሉን እንደገና መውጣትን ይጠይቅ ነበር።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በኢስተር አይላንድ የተሰጠ ምሥክርነት
ይህ ታሪካዊ ስብሰባ ከመካሄዱ ሁለት ዓመት በፊት አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካችና ሚስቱ ወደዚች ደሴት በመጡበት ጊዜ ብዙ አስደሳች ተሞክሮዎች አጋጥመዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል ወደሚያርፉበት ቦታ የወሰደቻቸው እህት ከ16 ዓመታት በፊት ገና ወጣት ሳለች በደቡባዊ ቺሊ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳስጠኗት አስታውሳ ነገረቻቸው። በዚያ ጊዜ የተዘራው ዘር ከጊዜ በኋላ በራፓ ኑኢ ፍሬ አፈራ።
የወረዳ የበላይ ተመልካቹና ሚስቱ ሌላም አስገራሚ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። የስጦታ ዕቃዎች መሸጫ መደብር ባለቤት ለሆነ አንድ ሰው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁትን የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ መጽሐፍ አበርክተውለት ነበር። ድጋሚ ሊያነጋግሩት ሲሄዱ መጽሐፍ ቅዱሱን ሊያነበው እንዳልቻለ ገለጸላቸው። የሰጡት መጽሐፍ ቅዱስ በስፓንኛ ሳይሆን በፈረንሳይኛ የተዘጋጀ ነበር! ችግሩ ወዲያው ተፈታ፤ በራሱ ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ ያገኘ ሲሆን የደሴቲቱ ነዋሪዎች በሆኑ ወንድሞች እርዳታ መጽሐፍ ቅዱስ ለመረዳት የሚከብድ መጽሐፍ እንዳልሆነ ማስተዋል ቻለ።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ኢስተር አይላንድ
ቺሊ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በወረዳ ስብሰባው ላይ ከተጠመቁት መካከል ሁለቱ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የራኖ ራራኩ ዐቀበት፤ ከላይ የተደረበው ፎቶ:- በደሴቲቱ ላይ የሚገኘው ግዋያባ የተባለው የዱር ፍሬ