እውነተኛ ክርስትና እየተስፋፋ ነው
እውነተኛ ክርስትና እየተስፋፋ ነው
ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን የጀመረው በአንደኛው ክፍለ ዘመን ነበር። እርሱ የሰበከው መልእክት የሚያበረታታ፣ የእውቀት ብርሃን የሚፈነጥቅና ለተግባር የሚያነሳሳ ስለነበር ብዙ ሰዎች ሲያስተምር ከሰሙ በኋላ በትምህርቱ ተገርመዋል።—ማቴዎስ 7:28, 29
ኢየሱስ በወቅቱ በነበረው ጨቋኝ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት ውስጥ እጁን እንዲያስገባ የቀረበለትን ጥያቄ ያልተቀበለ ቢሆንም ለተራው ሕዝብ ግን የሚቀረብ ነበር። (ማቴዎስ 11:25-30) ክፉ መንፈሳዊ ፍጡራን በምድር ላይ ስለሚያሳድሩት በካይ ተጽዕኖ በግልጽ የተናገረ ከመሆኑም በላይ አምላክ በእነርሱ ላይ ሥልጣን እንደሰጠው አሳይቷል። (ማቴዎስ 4:2-11, 24፤ ዮሐንስ 14:30) ኢየሱስ በሰዎች ላይ ሥቃይና መከራ የሚደርሰው በኃጢአት ምክንያት እንደሆነ በዘዴ ያሳወቀ ሲሆን ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት እንደሆነ አስተምሯል። (ማርቆስ 2:1-12፤ ሉቃስ 11:2, 17-23) ከአምላክ ጋር የግል ዝምድና ለመመሥረት ለሚፈልጉ ሁሉ ስሙን በማሳወቅ ለረጅም ዘመናት ተሰውሮ የነበረው የአባቱ እውነተኛ ማንነት በግልጽ እንዲታወቅ አድርጓል።—ዮሐንስ 17:6, 26
በመሆኑም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከሃይማኖታዊና ከፖለቲካዊ ቡድኖች ከባድ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም እርሱ ይሰብክ የነበረውን ኃይለኛ መልእክት በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሰራጨት መቻላቸው ምንም አያስደንቅም። ከ30 በማይበልጡ ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ፣ በእስያና በአውሮፓ ጠንካራ የክርስቲያን ጉባኤዎች ሊመሠረቱ ችለዋል። (ቆላስይስ 1:23) ኢየሱስ ያስተማረው ግልጽ እውነት በመላው የሮማ ግዛት ለሚገኙ ትሑትና ልበ ቅን ለሆኑ ሰዎች መንፈሳዊ ብርሃን ፈንጥቋል።—ኤፌሶን 1:17, 18
ይሁን እንጂ የተለያየ ባሕል፣ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ ቋንቋና ሃይማኖት የነበራቸው እነዚህ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ሐዋርያው ጳውሎስ የገለጸውን እውነተኛ አንድነት ያለው ‘አንድ እምነት’ ሊመሠርቱ የቻሉት እንዴት ነው? (ኤፌሶን 4:5) በመካከላቸው መለያየት ሳይኖር “አንድ ሐሳብ” ሊኖራቸው የቻለውስ እንዴት ነው? (1 ቆሮንቶስ 1:10) በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን ነን በሚሉ ሰዎች መካከል ከፍተኛ መከፋፈል ያለ መሆኑን ስንመለከት ኢየሱስ በዚህ ረገድ ያስተማረውን መመርመራችን ተገቢ ነው።
የክርስቲያናዊ አንድነት መሠረት
ኢየሱስ በጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት በቀረበበት ወቅት ለክርስቲያናዊ አንድነት መሠረቱ ምን እንደሆነ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ መናገርህ ትክክል ነው፤ የተወለድሁት፤ ወደዚህም ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ይሰማኛል።” (ዮሐንስ 18:37) ስለሆነም እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የኢየሱስን ትምህርቶችና በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን መቀበላቸው ጠንካራ አንድነት እንዲመሠርቱ ያስችላቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 4:6፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
ዮሐንስ 16:12, 13) ስለሆነም የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት አምላክ ደረጃ በደረጃ የገለጠውን እውነት እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። እንዲሁም ይኸው መንፈስ ፍቅርን፣ ደስታንና ሰላምን የመሳሰሉ በመካከላቸው አንድነት እንዲሰፍን የሚያደርጉ ባሕርያትን እንዲያፈሩ ያስችላቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 15:28፤ ገላትያ 5:22, 23
እርግጥ ነው፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዳንድ ጊዜ ጥያቄዎችን ሊያነሱ ወይም በመካከላቸው አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን ለመፍታት ምን ሊረዳቸው ይችላል? ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ ከራሱ አይናገርም፤ የሚሰማውን ብቻ ይናገራል፤ እንዲሁም ወደ ፊት ስለሚሆነው ይነግራችኋል።” (ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ መካከል መለያየት ወይም መከፋፈል እንዲኖር አልፈቀደም፤ እንዲሁም መለኮታዊውን እውነት ከሚያገኟቸው ሰዎች ባሕል ወይም ሃይማኖት ጋር እያጣጣሙ እንዲሰብኩ ሥልጣን አልሰጣቸውም። ከዚህ ይልቅ ከእነርሱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ እንደሚከተለው ሲል ከልብ ጸልዮአል፦ “የእነርሱን ትምህርት ተቀብለው በእኔ ለሚያምኑ ጭምር እንጂ ለእነዚህ ብቻ አልጸልይም፤ ይህም፣ አባት ሆይ፤ አንተ በእኔ፣ እኔም በአንተ እንዳለሁ ሁሉም አንድ እንዲሆኑ፤ እንዲሁም አንተ እኔን እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፣ እነርሱም በእኛ እንዲሆኑ ነው።” (ዮሐንስ 17:20, 21) እንግዲያው በመንፈስም ሆነ በእውነት የሚፈጠረው አንድነት ጥንትም ሆነ ዛሬ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ተለይተው የሚታወቁበት ምልክት ነው። (ዮሐንስ 4:23, 24) ሆኖም በጊዜያችን ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚታየው አንድነት ሳይሆን መከፋፈል ነው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?
አብያተ ክርስቲያናት እየተከፋፈሉ ያሉት ለምንድን ነው?
ግልጹን ለመናገር ክርስቲያን ነን በሚሉ ሰዎች መካከል በሃይማኖታዊ እምነቶችም ሆነ ልማዶች ሰፊ ልዩነት የተፈጠረው የኢየሱስን ትምህርቶች ባለመከተላቸው ነው። አንድ የጋዜጣ ዓምድ አዘጋጅ “በጥንት ጊዜ እንደታየው ሁሉ የዛሬዎቹ አዳዲስ ክርስቲያኖችም መጽሐፍ ቅዱስን ከእነርሱ ፍላጎት ጋር የሚስማማ ሆኖ ሲያገኙት ብቻ የመቀበልና ከሃይማኖታዊ ወጋቸው ጋር የሚጋጨውን የመተው ዝንባሌ ይታይባቸዋል” በማለት ተናግረዋል። ኢየሱስና ሐዋርያቱ ይሆናል ብለው አስቀድመው የተነበዩት ይህንኑ ነበር።
ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ እርሱ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግል ለነበረው ለጢሞቴዎስ በመንፈስ ተነሳስቶ እንዲህ ሲል ጽፎለት ነበር፦ “ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ። እውነትን ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ።” ጳውሎስ ሁሉም ክርስቲያኖች ይስታሉ ማለቱ ነበር? አልነበረም። ቀጥሎ እንዲህ ብሏል፦ “አንተ ግን በሁኔታዎች ሁሉ የረጋህ ሁን፤ መከራን ታገሥ፤ የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን፤ አገልግሎትህን ፈጽም።” (2 ጢሞቴዎስ 4:3-5፤ ሉቃስ 21:8፤ የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30፤ 2 ጴጥሮስ 2:1-3) ጢሞቴዎስም ሆነ ሌሎች ታማኝ ክርስቲያኖች በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን ይህን ምክር ተከትለዋል።
እውነተኛ ክርስቲያኖች አሁንም አንድነት አላቸው
እንደ ጢሞቴዎስ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ሰብዓዊ ፍልስፍናዎችን ባለመቀበልና ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ያላቸውን ትምህርቶች ብቻ በመከተል አስተሳሰባቸውን ይጠብቃሉ። (ቆላስይስ 2:8፤ 1 ዮሐንስ 4:1) የይሖዋ ምሥክሮች የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች የተዉትን ምሳሌ በመከተል ኢየሱስ ይሰብክ የነበረውን መልእክት ይኸውም ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች ከ230 በሚበልጡ አገሮች ለሚያገኟቸው ሰዎች ሁሉ በመስበክ ‘አገልግሎታቸውን ይፈጽማሉ።’ የትም ይኑሩ የት አንድ ሆነው የኢየሱስን አርዓያ በመከተል እውነተኛውን ክርስትና የሚያራምዱባቸውን አራት መንገዶች እንመልከት።
ትምህርቶቻቸው የተመሠረቱት በአምላክ ቃል ላይ ነው። (ዮሐንስ 17:17) በቤልጅየም የሚኖሩ አንድ የደብር አለቃ የይሖዋ ምሥክሮችን በሚመለከት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ከእነርሱ የምንማረው ነገር የአምላክን ቃል ለመታዘዝ ፈቃደኛ መሆናቸውንና ስለ እርሱም ለመመሥከር የሚያሳዩትን ድፍረት ነው።”
ሉቃስ 8:1) በኮሎምቢያ ባራንኩላ ከተማ አንድ የይሖዋ ምሥክር የአንድ ፖለቲካዊ ንቅናቄ ደጋፊ የነበረውን አንቶኒዮን አነጋገረው። ወንድም የአንቶኒዮን የፖለቲካ ንቅናቄም ሆነ ሌላኛውን የፖለቲካ ጎራ የሚደግፍ ሐሳብ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ አንቶንዮና እህቶቹ መጽሐፍ ቅዱስን በነጻ እንዲያጠኑ ጥያቄ አቀረበላቸው። ብዙም ሳይቆይ አንቶኒዮ በኮሎምቢያም ሆነ በሌላው ዓለም ለሚኖሩ ድሃ ሕዝቦች እውነተኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ተገነዘበ።
ለዓለም አቀፍ ችግሮች መፍትሔው የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ያምናሉ። (ለአምላክ ስም አክብሮት አላቸው። (ማቴዎስ 6:9) በአውስትራሊያ ቀናዒ የካቶሊክ እምነት ተከታይ የነበረችው ማሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነጋገሯት የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የአምላክን ስም እንዲያሳዩአት ያቀረቡላትን ጥያቄ ተቀበለች። የአምላክን ስም ስትመለከት ምን ተሰማት? እንዲህ ብላለች፦ “የአምላክን ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ስመለከት አለቀስኩ። የአምላክን የግል ስም ሳውቅና በስሙ ልጠራው እንደምችል ስገነዘብ በጣም ተደሰትኩ።” ማሪያ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷን ቀጥላ በሕይወቷ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ይሖዋ ባሕርያት ያወቀች ሲሆን ከእርሱ ጋር ዘላቂ ወዳጅነት መመሥረት ችላለች።
ፍቅር አንድ አድርጓቸዋል። (ዮሐንስ 13:34, 35) ካናዳ ውስጥ በሚታተም ዘ ሌዲስሚዝ ሸሜነስ ክሮኒክል በተባለ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ርዕሰ አንቀጽ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቷል፦ “የራሳችሁ እምነት ኖራችሁም አልኖራችሁ በካሴዲ 2,300 ካሬ ሜትር የሚያህል ስፋት ያለው ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለመገንባት ከሳምንት ለሚበልጡ ጊዜያት ቀን ከሌት ሲሠሩ የነበሩትን የይሖዋ ምሥክሮች ልታደንቋቸው ይገባል። . . . የራስን ክብር ሳይፈልጉ፣ በደስታና ያለ አንዳች ጭቅጭቅ እንዲህ ያለ ሥራ መሥራት የእውነተኛ ክርስትና መለያ ምልክት ነው።”
እስከ አሁን እንደተመለከትነው በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉት ሃይማኖታዊ ምሑራን፣ ሚስዮናውያንና ምዕመናን ከፊታቸው ከተደቀነባቸው አደጋ ጋር ሲታገሉ እውነተኛ ክርስትና ግን በመላው ዓለም እየተስፋፋ ነው። በእርግጥም እውነተኛ ክርስቲያኖች የአምላክን ቃል እንዲሰብኩና እንዲያስተምሩ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣት ላይ ናቸው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) በጊዜያችን እየተፈጸሙ ባሉት ነገሮች ‘ከሚያዝኑና ከሚተክዙ’ እንዲሁም በሕዝበ ክርስትና ውስጥ በሚታየው መከፋፈል ከሚረበሹ ሰዎች መካከል ከሆንህ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ከሚያመልኩት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር በአንድ ክርስቲያናዊ አምልኮ ጥላ ሥር እንድትሰበሰብ እንጋብዝሃለን።—ሕዝቅኤል 9:4፤ ኢሳይያስ 2:2-4