“አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም”
“አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም”
“አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም።”—2 ጢሞቴዎስ 4:5 ባይንግተን
1, 2. ሁሉም ክርስቲያኖች ወንጌላውያን ቢሆኑም እንኳ ሽማግሌዎች ምን ይጠበቅባቸዋል?
የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪ ነህ? ከሆንክ ይህን ውድ መብት ስለሰጠህ ይሖዋን ልታመሰግነው ይገባሃል። የጉባኤ ሽማግሌ ነህ? ይህም ከይሖዋ የተገኘ ሌላ መብት ነው። ይሁን እንጂ አንድን ሰው ለአገልግሎት ወይም ለበላይ ተመልካችነት ብቁ የሚያደርገው የትምህርት ደረጃው ወይም የመናገር ችሎታው እንዳልሆነ መዘንጋት አይኖርብንም። ለአገልግሎት ብቁ የሚያደርገን ይሖዋ ነው። በተጨማሪም በመካከላችን የሚገኙ አንዳንድ ወንዶች የበላይ ተመልካች ሆነው የማገልገል መብት የሚያገኙት ከዚህ ኃላፊነት ጋር የተያያዙ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን በማሟላታቸው ነው።—2 ቆሮንቶስ 3:5, 6፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:1-7
2 ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖች በሙሉ የወንጌላዊነትን ሥራ የሚያከናውኑ ቢሆንም በተለይ ግን ሽማግሌዎች በአገልግሎት ጥሩ ምሳሌ መሆን አለባቸው። “በመስበክና በማስተማር የሚተጉ” ሽማግሌዎች የሚያከናውኑትን ሥራ ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ እንዲሁም የእምነት አጋሮቻቸው ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት የታወቀ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 5:17፤ ኤፌሶን 5:23፤ ዕብራውያን 6:10-12) አንድ ሽማግሌ ምንጊዜም የሚሰጠው ትምህርት አድማጮቹን በመንፈሳዊ የሚገነባ መሆን አለበት። ይህን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ የበላይ ተመልካች ለነበረው ለጢሞቴዎስ እንዲህ ብሎታል፦ “ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ። እውነትን ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ። አንተ ግን በሁኔታዎች ሁሉ የረጋህ ሁን፤ መከራን ታገሥ፤ የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን፤ አገልግሎትህን ፈጽም።”—2 ጢሞቴዎስ 4:3-5
3. የሐሰት ትምህርቶች የጉባኤውን መንፈሳዊነት አደጋ ላይ እንዳይጥሉ ምን መደረግ ይኖርበታል?
3 አንድ የበላይ ተመልካች የሐሰት ትምህርቶች የጉባኤውን መንፈሳዊነት አደጋ ላይ እንዳይጥሉ “በሁሉ ረገድ ንቁ ሁን፣ . . . አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም” ሲል ጳውሎስ የሰጠውን ምክር ሊሠራበት ይገባል። (2 ጢሞቴዎስ 4:5 ባይንግተን) አዎን፣ አንድ ሽማግሌ ‘አገልግሎቱን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም’ ይኖርበታል። ምንም ሳያጓድል በጥንቃቄ ማከናወን አለበት። አገልግሎቱን በተሟላ ሁኔታ የሚፈጽም አንድ ሽማግሌ የትኛውንም ነገር ችላ ሳይል ያሉበትን ኃላፊነቶች በሙሉ በሚገባ ይወጣል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ጥቃቅን በሆኑ ጉዳዮች እንኳ ሳይቀር ታማኝ ነው።—ሉቃስ 12:48፤ 16:10
4. አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም ምን ሊረዳን ይችላል?
4 አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም ጊዜን በአግባቡ መጠቀም እንጂ የግድ ሰፊ ጊዜ ማግኘት ላያስፈልገን ይችላል። ሁሉም ክርስቲያኖች አገልግሎታቸውን ለመፈጸም በሁሉም ረገድ ሚዛናዊ መሆን ይኖርባቸዋል። አንድ ሽማግሌ በመስክ አገልግሎት የበለጠ ጊዜ እንዲያሳልፍ በሚገባ የተደራጀ መሆን እንዲሁም የትኛውን ሥራ ለማንና እንዴት መስጠት እንዳለበት ማወቅ ያስፈልገዋል። (ዕብራውያን 13:17) ነህምያ የኢየሩሳሌምን ግንቦች መልሶ በመገንባቱ ሥራ እንደተካፈለ ሁሉ አንድ ትጉ ሽማግሌም የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ የታወቀ ነው። (ነህምያ 5:16) በተጨማሪም ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች በመንግሥቱ የስብከት ሥራ አዘውትረው መካፈል አለባቸው።—1 ቆሮንቶስ 9:16-18
5. አገልግሎታችንን እንዴት ልንመለከተው ይገባል?
5 በሰማይ ስለተቋቋመው መንግሥት የማወጅ አስደሳች ተልእኮ ተሰጥቶናል! መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ምሥራቹን በመላው ዓለም በመስበኩ ሥራ የመካፈል መብታችንን ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። (ማቴዎስ 24:14) ፍጽምና የጎደለን ብንሆንም እንኳ “ይህ እጅግ ታላቅ ኀይል ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ አለመሆኑን ለማሳየት፣ ይህ የከበረ ነገር [አገልግሎታችን] በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን” የሚሉት የጳውሎስ ቃላት ትልቅ ማበረታቻ ይሆኑናል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) አዎን፣ ተቀባይነት ያለው አገልግሎት ማቅረብ እንችላለን፤ ይህን ማድረግ የምንችለው ግን አምላክ በሚሰጠን ብርታትና ጥበብ ብቻ ነው።—1 ቆሮንቶስ 1:26-31
የአምላክን ክብር ማንጸባረቅ
6. ሥጋዊ እስራኤል እና መንፈሳዊ እስራኤል የተነጻጸሩት እንዴት ነው?
6 ጳውሎስ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን አስመልክቶ ሲናገር አምላክ “የአዲሱ ኪዳን አገልጋዮች እንድንሆን ብቁዎች አደረገን” ብሏል። ሐዋርያው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ከመንፈሳዊ እስራኤል ጋር የተደረገውን አዲስ ቃል ኪዳን በሙሴ በኩል ከሥጋዊ እስራኤል ጋር ከተደረገው አሮጌ የሕግ ቃል ኪዳን ጋር አነጻጽሮታል። አክሎም ሙሴ አሥሩ ትእዛዛት የተጻፉባቸውን ጽላቶች ይዞ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ፊቱ በጣም ከማንጸባረቁ የተነሳ እስራኤላውያን ትኩር ብለው ሊመለከቱት እንዳልቻሉ ገልጿል። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ‘ልቡናቸው በመደንዘዙና’ በመሸፈኑ የከፋ ነገር ደርሶባቸዋል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው በሙሉ ልቡ ወደ ይሖዋ ሲመለስ መሸፈኛው ይወገዳል። ጳውሎስ በመቀጠል በአዲሱ ቃል ኪዳን ለታቀፉት ሰዎች የተሰጠውን አገልግሎት አስመልክቶ ሲናገር ‘ሁላችን ባልተሸፈነ ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እናንጸባርቃለን’ ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 3:6-8, 14-18፤ ዘፀአት 34:29-35) በዛሬው ጊዜ ያሉት የኢየሱስ ‘ሌሎች በጎችም’ የይሖዋን ክብር የማንጸባረቅ መብት አግኝተዋል።— ዮሐንስ 10:16
7. ሰዎች የአምላክን ክብር ሊያንጸባርቁ የሚችሉት እንዴት ነው?
7 አምላክን አይቶ በሕይወት ሊኖር የሚችል ሰው ስለሌለ ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች የአምላክን ክብር ሊያንጸባርቁ የሚችሉት እንዴት ነው? (ዘፀአት 33:20) ይሖዋ ካለው ክብር የተላበሰ ስብዕና በተጨማሪ በመንግሥቱ አማካኝነት ሉዓላዊነቱን የማረጋገጥ ክብራማ ዓላማም እንዳለው መገንዘብ ይኖርብናል። በ33 በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ የወረደባቸው ደቀ መዛሙርት የሰበኩት ‘የአምላክ ታላቅ ሥራ’ ከመንግሥቱ እውነት ጋር ዝምድና አለው። (የሐዋርያት ሥራ 2:11) መንፈሱ በሚሰጣቸው አመራር እየታገዙ በአደራ የተሰጣቸውን አገልግሎት በተሟላ ሁኔታ መፈጸም ይችላሉ።—የሐዋርያት ሥራ 1:8
8. ጳውሎስ አገልግሎቱን በተመለከተ ምን ቆራጥ አቋም ወስዷል?
8 ጳውሎስ አገልግሎቱን በተሟላ ሁኔታ ከመፈጸም ምንም ነገር እንዲያግደው አልፈቀደም። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ይህ አገልግሎት ስላለን ተስፋ አንቈርጥም። ነገር ግን ስውርና አሳፋሪ ነገሮችን ትተናል፤ አናታልልም፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ከሐሰት ጋር አንቀላቅልም፤ ይልቁንም እውነትን በግልጽ እየተናገርን በሰው ሁሉ ኅሊና ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረን ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት እናቀርባለን።” (2 ቆሮንቶስ 4:1, 2) ጳውሎስ በገለጸው “አገልግሎት” አማካኝነት እውነት የተገለጠ ከመሆኑም በላይ መንፈሳዊው ብርሃን በስፋት ፈንጥቋል።
9, 10. የይሖዋን ክብር ማንጸባረቅ የሚቻለው እንዴት ነው?
9 ጳውሎስ መንፈሳዊውን ብርሃን ጨምሮ የብርሃናት ሁሉ ምንጭ ስለሆነው አካል ሲናገር “በክርስቶስ ፊት እግዚአብሔር የክብሩን ዕውቀት ብርሃን ይሰጠን ዘንድ፣ ‘በጨለማ ብርሃን ይብራ’ ያለው እግዚአብሔር ብርሃኑን በልባችን አብርቶአል” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 4:6፤ ዘፍጥረት 1:2-5) የአምላክ አገልጋዮች የመሆን ታላቅ መብት የተሰጠን በመሆኑ ልክ እንደ መስተዋት የይሖዋን ክብር ማንጸባረቅ እንድንችል ንጽሕናችንን እንጠብቅ።
10 በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ያሉ ሰዎች የይሖዋን ክብርም ሆነ በታላቁ ሙሴ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሚታየውን የክብሩን ነጸብራቅ ማየት አይችሉም። እኛ ግን የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ከቅዱሳን ጽሑፎች ያገኘነውን አስደናቂ ብርሃን ለሌሎች እናንጸባርቃለን። በአሁኑ ጊዜ በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ያሉት ሰዎች ከጥፋት እንዲድኑ ከተፈለገ አምላክ የሚሰጠውን ብርሃን ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። በመሆኑም ለይሖዋ ክብር ለማምጣት በጨለማ ብርሃን እንድናበራ የተሰጠንን መለኮታዊ ትዕዛዝ በታላቅ ደስታና በቅንዓት እንፈጽማለን።
መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት ብርሃን ማብራት
11. ኢየሱስ ብርሃን ማብራትን አስመልክቶ ምን ብሏል? በአገልግሎታችን ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድስ ምንድን ነው?
11 ኢየሱስ ተከታዮቹን “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትደበቅ አትችልም፤ ሰዎችም መብራት አብርተው ከዕንቅብ ሥር አያስቀምጡትም፤ በቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ እንዲያበራ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል እንጂ። እንደዚሁም ሰዎች ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 5:14-16) ሰዎች መልካም ምግባራችንን ሲያዩ አምላክን ለማክበር ሊገፋፉ ይችላሉ። (1 ጴጥሮስ 2:12) የወንጌላዊነት ሥራችን የተለያዩ ገጽታዎች ብርሃናችንን ለማብራት የሚያስችሉ በርካታ አጋጣሚዎችን ይከፍቱልናል። አንዱ ዓላማችን ሰዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን መንፈሳዊ ብርሃን ማንጸባረቅ ነው። ይህ ደግሞ አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም በጣም ወሳኝ የሆነ መንገድ ነው። እውነትን የሚፈልጉ ሰዎችን ልብ በሚነካ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናት እንድንችል ምን ነገሮች ሊረዱን ይችላሉ?
12. ጸሎት መጽሐፍ ቅዱስን ውጤታማ በሆነ መንገድ በማስጠናት ረገድ ምን አስተዋጽኦ አለው?
12 ይህን ጉዳይ በተመለከተ ወደ ይሖዋ መጸለያችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ልባዊ ፍላጎት እንዳለን ያመለክታል። በተጨማሪም ሌሎች አምላክን እንዲያውቁ መርዳት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንደተገነዘብን ያሳያል። (ሕዝቅኤል 33:7-9) ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚሰማና በአገልግሎት የምናደርገውን ከፍተኛ ጥረት እንደሚባርክ ምንም ጥርጥር የለውም። (1 ዮሐንስ 5:14, 15) ይሁን እንጂ ወደ ይሖዋ የምንጸልየው መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናው ሰው ለማግኘት ብቻ አይደለም። ጥናት ካስጀመርንም በኋላ ተማሪውን በቀጥታ ስለሚመለከቱ ጉዳዮች መጸለያችንና ማሰላሰላችን እያንዳንዱን የጥናት ክፍለ ጊዜ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመምራት ያስችለናል።—ሮሜ 12:12
13. መጽሐፍ ቅዱስን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስጠናት ምን ሊረዳን ይችላል?
13 መጽሐፍ ቅዱስን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስጠናት ከእያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ በፊት ጥሩ ዝግጅት ማድረግ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ብቃት እንደሚጎድለን የሚሰማን ከሆነ የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ በየሳምንቱ የሚጠናውን ትምህርት እንዴት እንደሚመራ ልብ ብለን መመልከታችን ሊጠቅመን ይችላል። አልፎ አልፎም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት ረገድ ውጤታማ ከሆኑ ሌሎች የመንግሥቱ አስፋፊዎች ጋር አንድ ላይ በማስጠናት ተሞክሮ መቅሰም እንችላለን። ከሁሉም በላይ ግን የኢየሱስ ክርስቶስን ዝንባሌና የማስተማር ዘዴ ልንኮርጅ ይገባል።
14. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችንን ልብ መንካት የምንችለው እንዴት ነው?
14 ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ መፈጸምና ሰዎችን ስለ አምላክ ማስተማር በጣም ያስደስተው ነበር። (መዝሙር 40:8) የዋህና አሳቢ የነበረ ከመሆኑም በላይ በሚያስተምርበት ጊዜ የአድማጮቹን ልብ መንካት ችሏል። (ማቴዎስ 11:28-30) እንግዲያው እኛም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችንን ልብ ለመንካት እንጣር። ይህን ለማድረግ ደግሞ ምንጊዜም ከማስጠናታችን በፊት የተማሪውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ጥሩ ዝግጅት ማድረግ አለብን። ለምሳሌ ያህል ተማሪው ቀደም ሲል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ምንም ትውውቅ የሌለው ወይም ጭራሽ በመጽሐፍ ቅዱስ የማያምን ከነበረ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት መሆኑን አምኖ እንዲቀበል መርዳት ሊያስፈልገን ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ብዙ ጥቅሶችን አውጥተን ማንበብና ማብራራት እንደሚያስፈልገን የታወቀ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ምሳሌዎችን እንዲያስተውሉ እርዳቸው
15, 16. (ሀ) አንድ ተማሪ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ ምሳሌ እንግዳ በሚሆንበት ጊዜ ልንረዳው የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችን በሚያጠናው ጽሑፍ ላይ የተጠቀሰን አንድ ምሳሌ መረዳት ቢከብደው ምን ልናደርግ እንችላለን?
15 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሰ አንድ ምሳሌ እንግዳ ሊሆንበት ይችላል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ መብራትን በመቅረዝ ላይ ስለማስቀመጥ የተናገረው ምን ለማለት ፈልጎ እንደሆነ ግልጽ ላይሆንለት ይችላል። (ማርቆስ 4:21, 22) ኢየሱስ በጥንት ዘመን ስለነበረ ኩራዝ መናገሩ ነበር። እንዲህ ያለው መብራት ለዚህ ዓላማ ተብሎ በተዘጋጀ ማስቀመጫ ላይ ተቀምጦ ለቤቱ ብርሃን እንዲሰጥ ይደረግ ነበር። ኢየሱስ የተጠቀመበትን ምሳሌ ግልጽ ለማድረግ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል እንደተባለው መጽሐፍ ባሉ ጽሑፎች ላይ “መብራት” እና “መቅረዝ” በሚሉት ርዕሶች ምርምር ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል። a አስቀድሞ በሚገባ በመዘጋጀት ተማሪው ሊገባውና ሊረካበት የሚችል ማብራሪያ መስጠቱ ጥሩ ውጤት ያስገኛል።
16 መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት የተዘጋጀ አንድ ጽሑፍ የሚጠቅሰው ምሳሌ ለአንዳንድ ተማሪዎች ሊከብድ ይችላል። ስለሆነም የምሳሌውን ሐሳብ ልታስረዳው ወይም ሌላ ምሳሌ ተጠቅመህ ነጥቡን ልታብራራለት ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል አንድ ጽሑፍ ትዳር ስኬታማ እንዲሆን አቻ የትዳር ጓደኛ ማግኘትና የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚጠይቅ ይገልጽ ይሆናል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ደግሞ አንድ የጅምናስቲክ ስፖርተኛ ትርዒት በሚያሳይበት ጊዜ ከጅዋጅዌው ገመድ ላይ ከተወነጨፈ በኋላ ወደ ታች ሲመለስ የሚይዘው ሌላ ስፖርተኛ እንደሚያስፈልግ ይጠቅስ ይሆናል። ይሁን እንጂ ተማሪው ይህን ምሳሌ የማያውቀውና ለመረዳት የሚከብደው ከሆነ ከጭነት መኪና ላይ ዕቃ የሚያወርዱ ሠራተኞች ዕቃውን እንዴት እየተቀባበሉ እንደሚያወርዱና እንደሚተጋገዙ በመግለጽ ነጥቡን ማስረዳት ይቻላል።
17. ምሳሌዎችን በተመለከተ ከኢየሱስ ምን ትምህርት መቅሰም እንችላለን?
17 አማራጭ የሆነ ሌላ ምሳሌ ለመጠቀም አስቀድሞ ጥሩ ዝግጅት ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል። ሆኖም እንዲህ ማድረጋችን ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው ያለንን አሳቢነት ያሳያል። ኢየሱስ ከበድ ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችን ግልጽ ለማድረግ ቀላል የሆኑ ምሳሌዎችን ይጠቀም ነበር። የተራራው ስብከት ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሲሆን የኢየሱስ ትምህርት በአድማጮቹ ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደረ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። (ማቴዎስ 5:1 እስከ 7:29) ኢየሱስ ለሌሎች በእጅጉ ያስብ ስለነበር የሚናገረውን ነገር በትዕግሥት ያስረዳቸውና ያብራራላቸው ነበር።— ማቴዎስ 16:5-12
18. በጽሑፎቻችን ውስጥ ምዕራፋቸውና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱትን ጥቅሶች በተመለከተ ምን ማድረጋችን ጠቃሚ ነው?
18 ለሌሎች ያለን አሳቢነት ‘ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀስን’ እንድናስረዳቸው ይገፋፋናል። (የሐዋርያት ሥራ 17:2, 3) ይህም መጸለይና ምርምር ማድረግ እንዲሁም ‘ታማኙ መጋቢ’ ባዘጋጃቸው ጽሑፎች በሚገባ መጠቀምን ይጠይቃል። (ሉቃስ 12:42-44) ለምሳሌ ያህል ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለው መጽሐፍ ብዙ ጥቅሶችን ይዟል። b ሆኖም ይህ መጽሐፍ መጠኑ አነስተኛ ስለሆነ አንዳንዶቹን ጥቅሶች በአንቀጾቹ ውስጥ በቀጥታ ተጠቅሰው አናገኝም። ስለዚህ በጥናቱ ወቅት ምዕራፋቸውና ቁጥራቸው ብቻ ከተጠቀሱት ጥቅሶች መካከል ቢያንስ የተወሰኑትን አውጥቶ ማንበብና ማብራራት ያስፈልጋል። ትምህርቱ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፤ የአምላክ ቃል ደግሞ ከፍተኛ ኃይል አለው። (ዕብራውያን 4:12) ስለሆነም በአንቀጾቹ ውስጥ ያሉትን ጥቅሶች በመጠቀም ተማሪው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲያተኩር አድርግ። ተማሪው ስለ አንድ ርዕሰ ጉዳይ ወይም ድርጊት መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንዲያስተውል እርዳው። አምላክን መታዘዙ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝለት እንዲገነዘብ ለመርዳት የተቻለህን ጥረት አድርግ።—ኢሳይያስ 48:17, 18
ሐሳቡን እንዲገልጽ የሚያነሳሱ ጥያቄዎችን ጠይቅ
19, 20. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምንመራበት ጊዜ ተማሪው ሐሳቡን እንዲገልጽ የሚጋብዙ ጥያቄዎችን መጠየቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ርዕሰ ጉዳይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚጠይቅ ከሆነ ምን ማድረግ ይቻላል?
19 ኢየሱስ የታሰበባቸው ጥያቄዎች በመጠየቅ ሰዎች ቆም ብለው እንዲያስቡና እንዲመራመሩ ያደርግ ነበር። (ማቴዎስ 17:24-27) ተማሪው ሐሳቡን እንዲገልጽ የሚጋብዙ የማያሸማቅቁ ጥያቄዎችን የምንጠይቅ ከሆነ የሚሰጠው መልስ አንድን ጉዳይ በተመለከተ ምን አመለካከት እንዳለው እንድናውቅ ይረዳናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ አንዳንድ አመለካከቶች ካሉትም ይህን እንድናስተውል ሊረዳን ይችላል። ለምሳሌ ያህል በሥላሴ ያምን ይሆናል። እውቀት የተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ላይ “ሥላሴ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደማይገኝ ይገልጻል። በተጨማሪም ይሖዋና ኢየሱስ አንድ አካል አለመሆናቸውንና መንፈስ ቅዱስ የአምላክ ኃይል እንጂ ራሱን የቻለ አካል እንዳልሆነ የሚያሳዩ ጥቅሶችን ይጠቅሳል። እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ማንበቡና ማብራራቱ ብቻ በቂ ሆኖ ሊገኝ ይችላል። ይሁን እንጂ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት ቢያስፈልግስ? በሚቀጥለው ፕሮግራማችን ጥናታችንን ከጨረስን በኋላ በሥላሴ ማመን ይገባሃልን? እንደተባለው ብሮሹር ያለ ሌላ ጽሑፍ በመጠቀም ሰፋ ያለ ውይይት ማድረግ እንችላለን። ከዚያ በኋላ እውቀት በተባለው መጽሐፍ ማስጠናታችንን መቀጠል እንችላለን።
20 ተማሪው በአንድ ጉዳይ ላይ ያለውን አመለካከት እንዲገልጽ የሚጋብዝ አንድ ጥያቄ ስታቀርብለት ያልጠበቅኸው ዓይነት መልስ ቢሰጥህስ? ማጨስን የሚመለከት ወይም ሌላ ከበድ ያለ ጉዳይ ከተነሳ ጉዳዩን በሌላ ጊዜ በሰፊው እንደምትወያዩበት ገልጻችሁ ለጊዜው ጥናታችሁን መቀጠል ትችላላችሁ። ተማሪው ሲጋራ የሚያጨስ መሆኑን ማወቃችን መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ ሊረዳው በሚችል ጽሑፍ ላይ ምርምር እንድናደርግ ያስችለናል። የተማሪውን ልብ ለመንካት በምንጥርበት ጊዜ ይሖዋ በመንፈሳዊ እንዲያድግ እንዲረዳው ልንጸልይ እንችላለን።
21. እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ከራሱ ሁኔታ ጋር በሚስማማ መንገድ የምናስጠናው ከሆነ ምን ውጤት ሊገኝ ይችላል?
21 ጥሩ ዝግጅት የምናደርግና ይሖዋ እንዲረዳን በጸሎት የምንጠይቅ ከሆነ እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ከራሱ ሁኔታ ጋር በሚስማማ መልኩ ልናስጠናው እንደምንችል የተረጋገጠ ነው። እያደር ተማሪው ለአምላክ የጠለቀ ፍቅር እንዲያድርበት ልንረዳው እንችላለን። ለይሖዋ ድርጅት አክብሮትና አድናቆት እንዲያሳይ ልንረዳውም እንችላለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ‘እግዚአብሔር በመካከላችን እንዳለ’ ሲገነዘቡ ማየት በእጅጉ የሚያስደስት ነው! (1 ቆሮንቶስ 14:24, 25) እንግዲያው ሰዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናትና የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ።
በአድናቆት ልንመለከተው የሚገባ ሀብት
22, 23. አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም እንድንችል ምን ያስፈልገናል?
22 አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም እንድንችል አምላክ በሚሰጠን ኃይል መታመን አለብን። ጳውሎስ አገልግሎትን አስመልክቶ ለቅቡዓን ወንድሞቹ ሲጽፍ “ይህ እጅግ ታላቅ ኀይል ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ አለመሆኑን ለማሳየት፣ ይህ የከበረ ነገር በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን” ብሏል።—2 ቆሮንቶስ 4:7
23 ከቅቡዓን መካከልም ሆንን ‘ከሌሎች በጎች’ ሁላችንም በቀላሉ እንደሚሰበር የሸክላ ዕቃ ነን። (ዮሐንስ 10:16) ይሁንና ምንም ዓይነት ጫና ቢደርስብን ይሖዋ ሥራችንን ማከናወን እንድንችል አስፈላጊውን ኃይል ይሰጠናል። (ዮሐንስ 16:13፤ ፊልጵስዩስ 4:13) እንግዲያው ሙሉ በሙሉ በይሖዋ እንታመን፣ ውድ የሆነውን የአገልግሎት መብታችንን እናድንቅ እንዲሁም አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ እንፈጽም።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ሽማግሌዎች አገልግሎታቸውን በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
• ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት ረገድ ይበልጥ ውጤታማ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
• አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ አንድን ምሳሌ መረዳት ቢከብደው ወይም በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ቢያስፈልገው ምን ታደርጋለህ?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያን ሽማግሌዎች በጉባኤ የሚያስተምሩ ከመሆኑም በላይ የእምነት ባልደረቦቻቸውን በአገልግሎት ያሰለጥናሉ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ውጤታማ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ብርሃናችንን የምናበራበት አንዱ መንገድ ነው