666—ከፍተኛ ትርጉም ያለው ምስጢራዊ ቁጥር
666—ከፍተኛ ትርጉም ያለው ምስጢራዊ ቁጥር
“የአውሬው ምልክት፣ ይኸውም ስሙ ወይም የስሙ ቁጥር የሌለው ማንም ሰው ለመግዛትም ሆነ ለመሸጥ እንዳይችል ነው። ይህ ጥበብ ይጠይቃል፤ አእምሮ ያለው ማንኛውም ሰው የአውሬውን ቊጥር ያስላው፤ ምክንያቱም ቊጥሩ የሰው ቊጥር ነው። ቊጥሩ ስድስት መቶ ሥልሳ ስድስት ነው።”—ራእይ 13:17, 18
ምስጢራዊ የሆነውን ‘የአውሬውን’ ምልክት ወይም ስም ማለትም 666ን በተመለከተ የተነገረውን ትንቢት ያህል የሰዎችን ትኩረት የሳቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሶች ብዙ አይደሉም። በቴሌቪዥንና በኢንተርኔት እንዲሁም በፊልሞች፣ በመጻሕፍትና በመጽሔቶች ላይ የአውሬውን ስም በተመለከተ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ግምታዊ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል።
አንዳንዶች 666 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን ጸረ ክርስቶስ ያመለክታል የሚል እምነት አላቸው። ሌሎች ደግሞ የአውሬውን አገልጋዮች ለመለየት ተብሎ በንቅሳት ወይም በሌላ ስውር መንገድ የሚጻፍ ሰዎች ሁሉ የግድ ሊኖራቸው የሚገባ ምልክት እንደሆነ ይናገራሉ። 666 የካቶሊክ ሊቀ ጳጳሳት ምልክት እንደሆነ የሚያምኑ ሰዎችም አሉ። ከሊቀ ጳጳሱ ስሞች አንዱ የሆነው ቪካሪየስ ፊሊ ዴ (የአምላክ ልጅ ወኪል) የሚለው መጠሪያ የተጻፈባቸውን ፊደላት በሮማውያን ቁጥሮች በመተካትና በቁጥሮቹ ላይ ጥቂት ማስተካከያዎች በማድረግ 666 ላይ ይደርሳሉ። በላቲን የተጻፈውን የሮማ ንጉሠ ነገሥት የዲዮቅላጢያንን ስም እንዲሁም በዕብራይስጥ የተጻፈውን የኔሮ ቄሳርን ስም በመውሰድ እዚህ ቁጥር ላይ መድረስ እንደሚቻል የሚናገሩ ወገኖችም አሉ። a
ይሁን እንጂ በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንደተብራራው እነዚህ ምናባዊና ግምታዊ ትርጓሜዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አውሬው ምልክት ከሚሰጠው ፍቺ በጣም የራቁ ናቸው። አምላክ ይህንን ሥርዓት በሚያጠፋበት ጊዜ ምልክቱ ባለባቸው ሰዎች ላይ ቁጣውን እንደሚያወርድ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ራእይ 14:9-11፤ 19:20) እንግዲያው የ666ን ትርጉም ማወቃችን ምስጢሩን ከመፍታት የበለጠ ጠቀሜታ አለው። የሚያስደስተው ግን የፍቅር ተምሳሌትና የመንፈሳዊ ብርሃን ምንጭ የሆነው ይሖዋ አምላክ በዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ ረገድ አገልጋዮቹን በጨለማ ውስጥ አልተዋቸውም።—2 ጢሞቴዎስ 3:16፤ 1 ዮሐንስ 1:5፤ 4:8
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በቁጥሮች ላይ የሚደረግ ጥናትን በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት የታኅሣሥ 2002ን ንቁ! ተመልከት።