የአምላክ ሕዝቦች ደግነትን መውደድ ይኖርባቸዋል
የአምላክ ሕዝቦች ደግነትን መውደድ ይኖርባቸዋል
“እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም [“ደግነትንም፣” NW] ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?”—ሚክያስ 6:8
1, 2. (ሀ) ይሖዋ ከሕዝቦቹ ደግነትን መጠበቁ ሊያስገርመን የማይገባው ለምንድን ነው? (ለ) ደግነትን በሚመለከት ልንመረምራቸው የሚገቡ ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
ይሖዋ ቸር ወይም ደግ አምላክ ነው። (ሮሜ 2:4፤ 11:22) የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት አዳምና ሔዋን የአምላክን ደግነት አድንቀው መሆን አለበት! በዔድን ገነት ሳሉ አምላክ በፍጥረት ሥራዎቹ መደሰት ለሚችሉት የሰው ልጆች ያደረገላቸውን ደግነት በግልጽ በሚያሳዩት ፍጥረታት ተከበው ይኖሩ ነበር። አምላክ ከዚያ በኋላም ቢሆን ለሁሉም ሰዎች ሌላው ቀርቶ ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ደግነት ማሳየቱን ቀጥሏል።
2 ሰዎች በአምላክ አምሳል ስለተፈጠሩ የአምላክን ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ አላቸው። (ዘፍጥረት 1:26) በመሆኑም ይሖዋ ደግነት እንድናሳይ መጠበቁ የሚያስገርም አይደለም። ሚክያስ 6:8 እንደሚናገረው የአምላክ ሕዝቦች ‘ምሕረትን [“ደግነትን፣ NW”] መውደድ’ ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ ደግነት ምንድን ነው? ከሌሎች የአምላክ ባሕርያት ጋር ያለው ዝምድናስ ምንድን ነው? ሰዎች ደግነትን ማንጸባረቅ የሚችሉ ሆነው ሳለ ዓለም ይህን ያህል በጭካኔና ርኅራኄ በማጣት የተሞላው ለምንድን ነው? ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ደግነትን ለማሳየት መጣጣር የሚገባን ለምንድን ነው?
ደግነት ምንድን ነው?
3. ደግነት ሲባል ምን ማለት ነው?
3 ደግነት ለሌሎች ደኅንነት ከልብ አሳቢ በመሆን የሚገለጽ ባሕርይ ነው። ጠቃሚ ተግባራትን በማከናወንና አሳቢነትን የሚያንጸባርቁ ቃላትን በመናገርም ይገለጻል። ደግ መሆን ሲባል ሰውን የሚጎዳ ሳይሆን ጥሩ የሆነውን ማድረግ ማለት ነው። ደግ የሆነ ሰው ተግባቢ፣ ገር፣ አዛኝና ርኅሩኅ ነው። ለሌሎች የልግስናና የአሳቢነት መንፈስ ያሳያል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እንግዲህ የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደ መሆናችሁ ርኅራኄን፣ ቸርነትን [“ደግነትን፣” NW]፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ” በማለት ክርስቲያኖችን አሳስቧል። (ቆላስይስ 3:12) በመሆኑም ደግነት እያንዳንዱ እውነተኛ ክርስቲያን ሊኖረው ከሚገባው ምሳሌያዊ ልብስ መካከል አንዱ ነው።
4. ይሖዋ ለሰው ዘር ደግነት በማሳየት ረገድ ቅድሚያውን የወሰደው እንዴት ነው?
4 ደግነት በማሳየት ረገድ ቅድሚያውን የወሰደው ይሖዋ አምላክ ነው። ጳውሎስ እንደተናገረው አምላክ ‘ዳግም ልደት በሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ያዳነን’ ‘ቸርነቱና [“ደግነቱና፣” NW] ፍቅሩ በተገለጠ ጊዜ’ ነበር። (ቲቶ 3:4, 5) አምላክ፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ከክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ዋጋ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በኢየሱስ ደም ‘አጥቧቸዋል’ ወይም አንጽቷቸዋል። እንዲሁም በመንፈስ የተወለዱ የአምላክ ልጆች እንደመሆናቸው በመንፈስ ቅዱስ ታድሰው “አዲስ ፍጥረት” ሆነዋል። (2 ቆሮንቶስ 5:17) በተጨማሪም አምላክ ‘ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው ላነጹት’ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ደግነትና ፍቅር አሳይቷቸዋል።—ራእይ 7:9, 14 የ1954 ትርጉም፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2
5. በአምላክ መንፈስ የሚመሩ ሁሉ ደግነት ማሳየት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
5 ከዚህም በላይ ደግነት ከአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬዎች መካከል አንዱ ነው። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት [“ደግነት፣” NW]፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም።” (ገላትያ 5:22, 23) ታዲያ በአምላክ መንፈስ የሚመሩ ሁሉ ለሌሎች ደግነት ማሳየት አይኖርባቸውም?
እውነተኛ ደግነት የድክመት ምልክት አይደለም
6. ደግነት ድክመት የሚሆነው መቼ ነው? ለምንስ?
6 አንዳንድ ሰዎች ደግነትን እንደ ድክመት አድርገው ይመለከቱታል። አንድ ሰው መንፈሰ ጠንካራ መሆኑ እንዲታይ ግትር እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ኃይለኛ መሆን ይኖርበታል ብለው ያስባሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ይበልጥ ጥንካሬ የሚጠይቀው እውነተኛ ደግነት ማሳየትና ያለቦታው ደግነት ከማሳየት መቆጠብ ነው። እውነተኛ ደግነት ከአምላክ የመንፈስ ፍሬዎች መካከል አንዱ ስለሆነ ልል ከመሆን ወይም መጥፎ ምግባርን አይቶ በቸልታ ከማለፍ ጋር ምንም ዝምድና የለውም። በሌላ በኩል ተገቢ ያልሆነ ደግነት አንድ ሰው ስህተትን ችላ ብሎ እንዲያልፍ ስለሚያደርገው የድክመት ምልክት ነው።
7. (ሀ) ዔሊ ልል የነበረው እንዴት ነው? (ለ) ሽማግሌዎች ተገቢ ያልሆነ ደግነት እንዳያሳዩ መጠንቀቅ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
7 የእስራኤል ሊቀ ካህን የነበረውን ዔሊን እንደ ምሳሌ እንመልከት። በማደሪያው ድንኳን ካህናት ሆነው ያገለግሉ የነበሩ አፍኒን እና ፊንሐስ የተባሉ ልጆቹን በመገሠጽ ረገድ ልል ነበር። በአምላክ ሕግ መሠረት ከመሥዋዕቱ የሚሰጣቸው ድርሻ አልበቃ ብሏቸው ስቡ በመሠዊያው ላይ ከመቃጠሉ በፊት አገልጋይ ልከው መሥዋዕቱን ከሚያቀርበው ሰው ጥሬ ሥጋ እንዲያመጣላቸው ያደርጉ ነበር። እንዲሁም የዔሊ ልጆች በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር ዝሙት ይፈጽሙ ነበር። ይሁን እንጂ ዔሊ አፍኒንን እና ፊንሐስን ከክህነት ሥራቸው ከማስወገድ ይልቅ ለዘብ ያለ ተግሣጽ ብቻ ሰጣቸው። (1 ሳሙኤል 2:12-29) ‘በዚያ ዘመን የይሖዋ ቃል ብርቅ መሆኑ’ ምንም አያስደንቅም! (1 ሳሙኤል 3:1) ክርስቲያን ሽማግሌዎች የጉባኤውን መንፈሳዊነት አደጋ ላይ ሊጥሉ ለሚችሉ ኃጢአተኞች የማይገባ ደግነት በማሳየት እንዳይሸነፉ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። እውነተኛ ደግነት የአምላክን የሥነ ምግባር የአቋም ደረጃ የሚጻረሩ መጥፎ ቃላትንና ድርጊቶችን ችላ ብሎ አያልፍም።
8. ኢየሱስ እውነተኛ ደግነት ያሳየው እንዴት ነበር?
8 ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የተሳሳተ ደግነት አሳይቶ አያውቅም። እውነተኛ ደግነት በማሳየት ግን ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ለምሳሌ ያህል፣ ‘ሕዝቡ እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ አዝኖላቸዋል።’ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ ኢየሱስ ለመቅረብ አልፎ ተርፎም ትንንሽ ልጆቻቸውን ወደ እርሱ ለማምጣት አይፈሩም ነበር። ‘ሕፃናቱን አቅፎ በባረካቸው ጊዜ’ ምን ያህል ደግነትና ርኅራኄ እንዳሳየ መገንዘብ አያዳግትም። (ማቴዎስ 9:36፤ ማርቆስ 10:13-16) ኢየሱስ ደግ ቢሆንም በሰማይ በሚኖረው አባቱ ዓይን ትክክል ለሆኑ ነገሮች ጥብቅ ነበር። ኢየሱስ ክፉ የሆነውን ነገር ችላ ብሎ አልፎ አያውቅም፤ ግብዝ የሆኑ የሃይማኖት መሪዎችን ለማውገዝ ከአምላክ ያገኘው ድፍረት ነበረው። በማቴዎስ 23:13-26 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ!” በማለት በተደጋጋሚ አውግዟቸዋል።
ደግነትና ሌሎች አምላካዊ ባሕርያት
9. ደግነት ከትዕግሥትና ከበጎነት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?
9 ደግነት የአምላክ መንፈስ ፍሬዎች ከሆኑት እንደ ትዕግሥትና በጎነት ካሉ ሌሎች ባሕርያት ጋር ዝምድና አለው። በእርግጥም ደግ የሆነ ሰው ሌሎችን ታግሦ በማለፍ ይህን ባሕርይ ያንጸባርቃል። ደግነት የጎደላቸውን ሰዎች በትዕግሥት ይይዛቸዋል። ደግነት ከበጎነት ጋር የተያያዘው ብዙውን ጊዜ ለሌሎች ጠቃሚ የሆኑ በጎ ተግባራትን በማከናወን የሚገለጽ በመሆኑ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ደግነት” ተብሎ የተሠራበት የግሪክኛ ቃል በአንዳንድ ቦታዎች ላይ “በጎነት” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። አረማውያን፣ የጥንት ክርስቲያኖች ያሳዩት በነበረው የደግነት ምግባር በእጅጉ ከመደነቃቸው የተነሳ እነዚህን የኢየሱስ ተከታዮች ‘ከደግነት የተፈጠሩ ሰዎች’ ብለው ይጠሯቸው እንደነበር ተርቱሊያን ተናግሯል።
10. ደግነትና ፍቅር የሚዛመዱት እንዴት ነው?
10 ደግነትንና ፍቅርን የሚያዛምዳቸው አንድ ነገር አለ። ኢየሱስ ተከታዮቹን በሚመለከት “እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:35) ጳውሎስ ደግሞ ይህን ፍቅር በሚመለከት “ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር [“ደግ፣” NW] ነው” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 13:4) ደግነትን ከፍቅር ጋር የሚያገናኘው ሌላው ነገር በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ የተጠቀሰው “ፍቅራዊ ደግነት” የሚለው ሃረግ ነው። a ይህ ዓይነቱ ደግነት ከዘላለማዊ ፍቅር የሚመነጭ ነው። “ፍቅራዊ ደግነት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ከፍቅር የበለጠ ስሜትን ያንጸባርቃል። እንዲህ ያለው ደግነት የአንድ ነገር ዓላማ ግቡን እስኪመታ ድረስ ከዚያ ነገር ጋር በፍቅር ይጣበቃል። የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ወይም ጽኑ ፍቅር በተለያዩ መንገዶች ይንጸባረቃል። ለምሳሌ ያህል ሕዝቦቹን ነጻ ለማውጣትና ለመጠበቅ በወሰዳቸው እርምጃዎች ታይቷል።—መዝሙር 6:4፤ 40:11፤ 143:12
11. የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት ምን ዋስትና ይሰጠናል?
11 ይሖዋ “በርኅራኄ [“በፍቅራዊ ደግነት፣” NW]” ሰዎችን ወደ ራሱ ይስባል። (ኤርምያስ 31:3) የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ከችግር የሚታደጋቸው ወይም የሚረዳቸው ሲያስፈልጋቸው ፍቅራዊ ደግነቱ በእርግጥ ታማኝ ስለሆነ እንደማይተዋቸው ያውቃሉ። በመሆኑም “እኔ ግን በጸናች ፍቅርህ [“በፍቅራዊ ደግነትህ፣” NW] እታመናለሁ፤ ልቤም በማዳንህ ደስ ይለዋል” በማለት እንደጸለየው መዝሙራዊ እነርሱም በእምነት መጸለይ ይችላሉ። (መዝሙር 13:5) የአምላክ ፍቅር ጽኑ ወይም ታማኝ ስለሆነ አገልጋዮቹ እንደማይጥላቸው ሙሉ በሙሉ ሊተማመኑበት ይችላሉ። “እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልምና፤ ርስቱንም አይተውም” የሚል ዋስትና ተሰጥቷቸዋል።—መዝሙር 94:14
ዓለም በጭካኔ የተሞላው ለምንድን ነው?
12. የጭቆና አገዛዝ የጀመረው መቼ እና እንዴት ነበር?
12 የዚህ ጥያቄ መልስ በዔድን ገነት ከተፈጸመው ነገር ጋር የተያያዘ ነው። የሰው ልጅ ታሪክ ከጀመረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ራስ ወዳድና ትዕቢተኛ የሆነ መንፈሳዊ ፍጡር የዓለም ገዥ የመሆን እቅድ አወጣ። ይህ እቅዱ ተሳክቶለት ‘የዚህ ዓለም ገዥ’ ለዚያውም ጨቋኝ ገዥ ሆነ። (ዮሐንስ 12:31) የአምላክና የሰው ቀንደኛ ጠላት የሆነው ይህ መንፈሳዊ ፍጡር ከጊዜ በኋላ ሰይጣን ዲያብሎስ ተባለ። (ዮሐንስ 8:44፤ ራእይ 12:9) የይሖዋን የደግነት ዙፋን የሚቀናቀን አገዛዝ ለመመሥረት ያወጣው የራስ ወዳድነት እቅድ ይፋ የሆነው ሔዋን ከተፈጠረች በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነበር። በመሆኑም አዳም ለአምላክ ደግነት ጀርባውን ሰጥቶ ከእርሱ አገዛዝ ነጻ የሚያደርገውን መንገድ በተከተለ ጊዜ የክፋት አገዛዝ ጀመረ። (ዘፍጥረት 3:1-6) አዳምና ሔዋን እንዳሰቡት ራሳቸውን በማስተዳደር ፋንታ ራስ ወዳድና ኩሩ በሆነው በዲያብሎስ ተጽዕኖ ሥር በመውደቅ የእርሱ ተገዥዎች ሆኑ።
13-15. (ሀ) የይሖዋን የጽድቅ አገዛዝ ችላ ማለት ያስከተላቸው አንዳንድ መጥፎ ውጤቶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ዓለም ይህን ያህል በጭካኔ የተሞላው ለምንድን ነው?
13 ይህ ሁኔታ ያስከተላቸውን አንዳንድ መጥፎ ውጤቶች እስቲ እንመልከት። አዳምና ሔዋን ገነት ከነበረው የምድር ክፍል ተባረሩ። ጤንነትን የሚገነቡ አትክልቶችና ፍራፍሬዎች ከተትረፈረፉበት ውብ የአትክልት ሥፍራ ወጥተው ከዔድን ገነት ውጪ ለነበረው የመከራ ኑሮ ተዳረጉ። አምላክ አዳምን እንዲህ አለው፦ “የሚስትህን ቃል ሰምተህ፣ ‘ከእርሱ አትብላ’ ብዬ ያዘዝሁህን ዛፍ በልተሃልና፣ ‘ከአንተ የተነሣ ምድር የተረገመች ትሁን፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ምግብህን ጥረህ ግረህ ከእርሷ ታገኛለህ። ምድርም እሾኽና አሜከላ ታበቅልብሃለች።’” በምድር ላይ የተነገረው እርግማን መሬትን አርሶ ምርት ማግኘትን አስቸጋሪ እንዲሆን የሚያደርግ ነበር። የአዳም ዘሮች ምድር እሾህና አሜከላ እንደምታበቅል የተነገረው እርግማን ውጤት በእጅጉ ተሰምቷቸው ስለነበር የኖኅ አባት ላሜህ ‘እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከልፋታቸውና ከጉልበታቸው የተነሳ ስለሚደርስባቸው ድካም’ ተናግሯል።—ዘፍጥረት 3:17-19፤ 5:29
14 አዳምና ሔዋን በገነት ውስጥ የነበራቸውን የተረጋጋ ሕይወት አጥተው በጭንቀት ለመኖር ተገደዋል። አምላክ ሔዋንን “በምጥ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛለሁ፤ በሥቃይም ትወልጃለሽ፤ ፍላጎትሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፤ እርሱም የበላይሽ ይሆናል” ብሏት ነበር። ከጊዜ በኋላ የአዳምና የሔዋን የመጀመሪያ ልጅ የነበረው ቃየን በጭካኔ ተነሳስቶ የገዛ ወንድሙን አቤልን ገድሎታል።—ዘፍጥረት 3:16፤ 4:8
15 ሐዋርያው ዮሐንስ ‘መላው ዓለም በክፉው ሥር እንደ ሆነ’ ተናግሯል። (1 ዮሐንስ 5:19) በዛሬው ጊዜ ያለው ዓለም ልክ እንደ ገዥው ራስ ወዳድነትንና ኩራትን የመሳሰሉ መጥፎ ባሕርያትን ያንጸባርቃል። ዓለም በክፋትና በጭካኔ የተሞላ መሆኑ ብዙም አያስደንቅም! ይህ ሁኔታ እንዲሁ ይቀጥላል ማለት ግን አይደለም። ይሖዋ በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር በክፋትና በጭካኔ ምትክ ደግነትና ርኅራኄ እንዲሰፍን ያደርጋል።
በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ደግነት ይሰፍናል
16. በክርስቶስ ኢየሱስ የሚመራው የአምላክ አገዛዝ ደግነት የሰፈነበት የሆነው ለምንድን ነው? ይህስ ምን እንድናደርግ ይገፋፋናል?
16 ይሖዋና በእርሱ መንግሥት ላይ የተሾመው ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገዥዎቻቸው ደግነትን እንዲያንጸባርቁ ይጠብቁባቸዋል። (ሚክያስ 6:8 NW) ኢየሱስ ክርስቶስ ከአባቱ በተቀበለው አገዛዝ ሥር ደግነት እንደሚሰፍን በናሙና አሳይቷል። (ዕብራውያን 1:3) ኢየሱስ በሕዝቡ ላይ ከባድ ሸክም የጫኑትን የሐሰት ሃይማኖት መሪዎች ለማጋለጥ ከተናገራቸው ቃላት ይህንን መገንዘብ እንችላለን። እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና።” (ማቴዎስ 11:28-30) አሁን ያሉት ምድራዊ ገዥዎች በሙሉ ሃይማኖታዊ ሆኑም አልሆኑ ማለቂያ የሌላቸውን ደንቦች በመጫንና እምብዛም ጥቅም የማያገኙባቸውን ሥራዎች በማሠራት ሕዝቡን አድክመውታል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከተከታዮቹ የሚጠብቀው ፍላጎታቸውንና ችሎታቸውን ግምት ውስጥ ያስገባ ነገር ነው። በእርግጥም ቀንበሩ እፎይታ የሚያስገኝና ደግነት የሚንጸባረቅበት ነው! ታዲያ ደግነትን በማሳየት ረገድ እርሱን ለመምሰል አንገፋፋም?—ዮሐንስ 13:15
17, 18. ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገዙትም ሆኑ ምድራዊ ወኪሎቹ ደግነትን እንደሚያሳዩ ልንተማመንባቸው የምንችለው ለምንድን ነው?
17 ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የተናገራቸው ግሩም ሐሳቦች የአምላክ መንግሥትና ሰብዓዊ አገዛዝ ምን ያህል ልዩነት እንዳላቸው በማያሻማ ሁኔታ ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ በእነርሱ ዘንድ ክርክር ተነሣ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ ‘የአሕዛብ ነገሥታት ሕዝቦቻቸውን በኀይል ይገዛሉ፤ በእነርሱ ላይ ሥልጣን ያላቸውም በጎ አድራጊዎች ተብለው ይጠራሉ። በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይሁን፤ ይልቁን ከእናንተ ታላቅ የሆነ እንደ ታናሽ፣ ገዥ የሆነም እንደ አገልጋይ ይሁን። ለመሆኑ፣ በማእድ ከተቀመጠና ቆሞ ከሚያስተናግድ ማን ይበልጣል? በማእድ የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ ያለሁት እንደ አንድ አገልጋይ ነው።’”—ሉቃስ 22:24-27
18 ሰብዓዊ ገዥዎች ሕዝቡን ‘በኀይል እየገዙና’ ከተገዥዎቻቸው የበላይ ያደርጋቸው ይመስል ለራሳቸው የማዕረግ ስሞች እያወጡ ታላቅ ለመሆን ይፈልጋሉ። ሆኖም ኢየሱስ እውነተኛ ታላቅነት ሌሎችን በትጋትና በጽናት ከማገልገል እንደሚመጣ ተናግሯል። ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገዙትም ሆኑ ምድራዊ ወኪሎቹ የእርሱን የትሕትናና የደግነት ባሕርይ መኮረጅ ይኖርባቸዋል።
19, 20. (ሀ) ኢየሱስ የይሖዋ ደግነት ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ደግነትን በማንጸባረቅ ረገድ ይሖዋን መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?
19 እስቲ ደግሞ ኢየሱስ በፍቅር የሰጠውን ሌላውን ምክር እንመልከት። የይሖዋ ደግነት ምን ያህል ታላቅ መሆኑን ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፦ “የሚወዷችሁን ብትወዱ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ የሚወዷቸውን ይወዳሉና። መልካም ላደረጉላችሁ መልካም ብታደርጉ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ እንደዚያ ያደርጋሉና። ብድር ይመልሳሉ ለምትሉት ብታበድሩ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ ያበደሩትን ያህል መልሰው ለመቀበል ‘ለኀጢአተኞች’ ያበድራሉ። ነገር ግን ጠላቶቻቸሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ መልሳችሁ ለመቀበል ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፤ በዚህም ወሮታችሁ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ቸር [“ደግ፣” NW] ነውና። አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ እናንተም ርኅሩኆች ሁኑ።”—ሉቃስ 6:32-36
20 አምላካዊ ባሕርይ የሆነው ደግነት ከራስ ወዳድነት የራቀ ነው። በአጸፋው ምንም እንዲደረግለት አይጠብቅም። ይሖዋ በደግነት “ፀሓዩን ለክፉዎችና ለደጎች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኀጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል።” (ማቴዎስ 5:43-45፤ የሐዋርያት ሥራ 14:16, 17) የሰማዩ አባታችንን ምሳሌ በመከተል አመስጋኝ ያልሆኑ ሰዎችን ሊጎዳ የሚችል ነገር ከማድረግ መቆጠብ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ነገር እናደርግላቸዋለን። ደግነትን በማንጸባረቅ በሁሉም ሰብዓዊ ግንኙነቶች ውስጥ ደግነትና ሌሎች የአምላክ ባሕርያት በሚንጸባረቁበት የአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር መኖር እንደምንፈልግ ለይሖዋና ለኢየሱስ እናሳያለን።
ደግነት ማሳየት የሚገባን ለምንድን ነው?
21, 22. ደግነትን ማሳየት የሚገባን ለምንድን ነው?
21 እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን ደግነትን ማሳየታችን በጣም አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማድረጋችን የአምላክ መንፈስ እንዳለን ያሳያል። ከዚህም በላይ እውነተኛ ደግነት ስናሳይ ይሖዋንና ክርስቶስ ኢየሱስን እንመስላለን። በተጨማሪም ደግነት ከአምላክ መንግሥት ዜጎች የሚጠበቅ አንድ ብቃት ነው። እንግዲያው ደግነትን መውደድና እንዴት ማሳየት እንደምንችል መማር ይኖርብናል።
22 በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ደግነትን ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ ተግባራዊ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በዚህ አንቀጽ ውስጥ በሚገኙት ጥቅሶች ላይ “ጽኑ ፍቅር”፣ “ቸርነት” እና “ምሕረት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ውስጥ “ፍቅራዊ ደግነት” ተብሎ በትክክል ተተርጉሟል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ደግነት ምንድን ነው?
• ዓለም በጭካኔና በክፋት የተሞላው ለምንድን ነው?
• በአምላክ አገዛዝ ሥር ደግነት እንደሚሰፍን እንዴት እናውቃለን?
• በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ለመኖር የሚፈልጉ ሰዎች ደግነትን ማሳየታቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያን ሽማግሌዎች መንጋውን በደግነት ለመያዝ ይጥራሉ
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ታማኝ ስለሆነ አገልጋዮቹን በመከራ ጊዜ አይተዋቸውም
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በደግነት ለሰዎች ሁሉ ፀሓይን ያወጣል እንዲሁም ዝናብን ያዘንባል