‘ተሻግረህ እርዳን’
የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
‘ተሻግረህ እርዳን’
በኦስትሪያ፣ በጀርመንና በስዊዘርላንድ የሚኖሩ ጀርመንኛ የሚችሉ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቦሊቪያ እንዲሄዱ በሐምሌ፣ 2000 ጥሪ ቀርቦ ነበር። ይህ ጥሪ የቀረበው ለምንድን ነው? ሳንታ ክሩዝ ከተባለችው የቦሊቪያ ከተማ 300 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀው በሚገኙ ገለልተኛ ክልሎች የሚኖሩ በግብርና የሚተዳደሩ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ስለታየ ነበር። ጀርመንኛ ተናጋሪ የሆኑት እነዚህ ሰዎች ሜኖናይት ተብሎ የሚጠራው ሃይማኖታዊ ቡድን አባላት ናቸው።
አንድ መቶ አርባ የሚያህሉ ወንድሞችና እህቶች ጥሪውን ተቀብለው ወደ ቦሊቪያ ሄዱ። አንዳንዶች ለጥቂት ሳምንታት፣ ሌሎች ደግሞ ለአንድ ዓመትና ከዚያም ለሚበልጥ ጊዜ በዚያ ቆይተዋል። ይህም “ወደ መቄዶንያ ተሻግረህ [እ]ርዳን” የሚለውን ጥሪ ተቀብለው እንደሄዱት በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ሚስዮናውያን ዓይነት መንፈስ እንዳላቸው የሚያሳይ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 16:9, 10
በዚህ ክልል መስበክ ምን ጥረት ይጠይቃል? በዚያ አካባቢ በሚገኝ ጉባኤ የሚያገለግል አንድ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል:- “ሜኖናውያን ከሚኖሩባቸው 43 መንደሮች ወደ አንዱ ለመድረስ በኮረኮንች መንገድ ላይ ለስምንት ሰዓታት ያህል በመኪና መጓዝ ያስፈልጋል። በጣም ርቀው በሚገኙት አካባቢዎች ለሚኖሩት ሰዎች ለመስበክ በአብዛኛው ለአራት ቀናት የምንጓዝ ከመሆኑም በላይ አንዳንድ ጊዜ በድንኳን ውስጥ እናድራለን። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ከዚህ ቀደም ምሥራቹን ሰምተው የማያውቁ በመሆናቸው እንደዚህ ያለ ጥረት መደረጉ አያስቆጭም።”
መጀመሪያ ላይ አብዛኞቹ ሜኖናውያን ምሥራቹን ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም። ሆኖም ወንድሞች ያላሰለሰ ጥረት በማድረጋቸው ሰዎቹ የመልእክቱን ጠቃሚነት መረዳት ችለዋል። ለአብነት ያህል፣ አንድ ገበሬ ለአንድ ዓመት ንቁ! መጽሔት ያነብብ እንደነበረ ከተናገረ በኋላ “በዚህ አካባቢ ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች መልእክታችሁን ባይቀበሉም እኔ ግን የምትሰብኩት ነገር እውነት መሆኑን አምናለሁ” ብሏል። በሌላ መንደር ደግሞ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል:- “አንዳንድ ጎረቤቶቼ ሐሰተኛ ነቢያት እንደሆናችሁ ይናገራሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ የምትናገሩት መልእክት እውነት ነው ይላሉ። ትክክለኛውን ነገር ለማወቅ እኔ ራሴ መመርመር እፈልጋለሁ።”
በአሁኑ ወቅት ቦሊቪያ ውስጥ በጀርመንኛ ቋንቋ የሚካሄድ ጉባኤ ተመሥርቷል፤ ጉባኤው 35 አስፋፊዎች ያሉት ሲሆን 14ቱ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ናቸው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያለው ዘገባ እንደሚያሳየው ሜኖናውያን የነበሩ 14 ሰዎች አስፋፊዎች ሆነዋል፤ ሌሎች 9 ደግሞ አዘውትረው በስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። በቅርቡ የተጠመቁ አንድ አዛውንት እንዲህ ብለዋል:- “ይህ ሥራ የሚከናወነው በይሖዋ አመራር መሆኑን በግልጽ እየተመለከትን ነው። እኛን ለመርዳት ጀርመንኛ ተናጋሪ የሆኑ ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞችና እህቶች ልኮልናል። ለተደረገው ዝግጅት በጣም እናመሰግናለን።” አሥራ ሰባት ዓመት የሆናት የአዛውንቱ ሴት ልጅም የተጠመቀች ሲሆን እንዲህ ብላለች:- “ሊረዱን የመጡት ወጣት ወንድሞችና እህቶች ግለት ወደ ሌሎችም የሚጋባ ነው። አብዛኞቹ በአቅኚነት አገልግሎት ተሰማርተው ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ሌሎችን ለመርዳት ያውላሉ። እኔም እንደ እነርሱ መሆን እፈልጋለሁ።”
በእርግጥም፣ ሌሎችን ለመርዳት ‘የተሻገሩት’ ወንድሞችና እህቶች ታላቅ ደስታና እርካታ አግኝተዋል።