“ሃይማኖቷን ልናከብርላት እንደሚገባ አስተምራናለች”
“ሃይማኖቷን ልናከብርላት እንደሚገባ አስተምራናለች”
ጣሊያን ውስጥ ሮቪጎ በተባለ ግዛት የምትኖር አንዲት የይሖዋ ምሥክር ለሕይወቷ አስጊ የሆነ የካንሰር ሕመም እንዳለባት ሐኪሞች ነገሯት። ረዘም ላለ ጊዜ በሆስፒታል ስትረዳ ከቆየች በኋላ ወደ ቤቷ ተመልሳ የካንሰር ሕመምተኞችን የሚንከባከቡ ነርሶች ከሚልክ ተቋም የመጡ ባለሞያዎች ያስታምሟት ጀመር። በሆስፒታል እያለች ያለ ደም ለመታከም እንደምትፈልግ ገልጻ ነበር።
ይህች የ36 ዓመት ሴት ባሳየችው ጠንካራ እምነትና የትብብር መንፈስ ይረዷት የነበሩትን የሕክምና ባለሞያዎች አድናቆት አትርፋለች። ባደረባት የካንሰር ሕመም ምክንያት ከመሞቷ ጥቂት ቀደም ብሎ፣ ያስታምሟት ከነበሩት ነርሶች አንዱ አንጄላ ብሎ ስለጠራት ስለዚች ሕመምተኛ በሕክምና መጽሔት ላይ አንድ ጽሑፍ አውጥቶ ነበር።
“አንጄላ ተጫዋች ስትሆን በሕይወት ለመቀጠል ጠንካራ ፍላጎት አላት። የጤንነቷን ሁኔታና ሕመሟ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ የተገነዘበች ከመሆኑም በላይ እንደ ሌሎቻችን ሁሉ እርሷም መፍትሔ፣ ፈውስ ወይም መድኃኒት ለማግኘት ጥረት ታደርጋለች። . . . እኛም የቀረብናት ቀስ በቀስ ሲሆን ልንረዳት ስንሞክር አልተቃወመችንም። እንዲያውም አንጄላ ግልጽ መሆኗ ነገሮችን አቅልሎልናል። ቀና አመለካከት ካላት ከዚህች ሴት ጋር በምናሳልፈው ጊዜ እርሷ ብቻ ሳትሆን እኛም እንደምንጠቀም ስለምናውቅ አንጄላን መንከባከብ ያስደስተን ነበር። . . . ብዙም ሳይቆይ፣ ሃይማኖቷ እርሷን ለማከም በምናደርገው ጥረት እንቅፋት እንደሚሆንብን ተገነዘብን።” ይህንን ያለው አንጄላ ደም ሊሰጣት እንደሚገባ ስለተሰማው ነበር፤ እርሷ ደግሞ ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ አልነበረችም።—የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29
“የጤና ባለሞያዎች እንደመሆናችን መጠን በውሳኔዋ እንደማንስማማ ብንገልጽላትም ለሕይወት አክብሮት እንዳላት እንድንገነዘብ ረድታናለች። ከዚህም በላይ እርሷም ሆነች ቤተሰቦቿ ለሃይማኖቷ ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡት ማወቅ ችለናል። አንጄላ ተስፋ ቆርጣ ለሕመሟ እጅ አልሰጠችም። መንፈሰ ጠንካራ ከመሆኗም በላይ በሽታዋን እየታገለች በሕይወት መቀጠል ትፈልጋለች። ይህን አቋሟንና እምነቷን አሳውቃናለች። አብዛኞቻችን የሌለን ቆራጥነትና ጽኑ እምነት አላት። . . . የሙያችን ሥነ ምግባር ከእምነቷ ጋር የሚጋጭ ቢሆንም እንኳ ሃይማኖቷን ልናከብርላት እንደሚገባ አስተምራናለች። . . . አንጄላ በጣም ትልቅ ትምህርት እንደሰጠችን ይሰማናል። ሥራችን የተለያየ ሃይማኖት ካላቸው ብዙ ዓይነት ሰዎች ጋር የሚያገናኘን ከመሆኑም በላይ የተለያዩ ሁኔታዎች ስለሚያጋጥሙን ከምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ የተወሰነ ነገር ልንማርና እነርሱንም ልንረዳቸው እንችላለን።”
ከዚያም ጽሑፉ በ1999 የጸደቀውን ለጣሊያን ነርሶች የተዘጋጀ የሥነ ምግባር ደንብ በመጥቀስ እንዲህ ይላል:- “አንድ ነርስ ሕመምተኛ በሚንከባከብበት ጊዜ የግለሰቡን ሃይማኖታዊ፣ ሥነ ምግባራዊና ባሕላዊ እምነት እንዲሁም ዘሩንና ፆታውን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል።” አንዳንድ ጊዜ ዶክተሮችና ነርሶች የሕመምተኛውን እምነት ማክበር ሊያስቸግራቸው ይችል ይሆናል፤ በመሆኑም እምነታችንን ለማክበር ፈቃደኛ ለሆኑት የሕክምና ባለሞያዎች አመስጋኞች ነን።
የይሖዋ ምሥክሮች ጤንነታቸውንና የሚደረግላቸውን ሕክምና በሚመለከት ውሳኔ የሚያደርጉት በሚገባ አስበውበት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ምን እንደሚል በጥንቃቄ የሚመረምሩ ሲሆን ከአንጄላ ሁኔታ መመልከት እንደሚቻለው አክራሪ ጽንፈኞች አይደሉም። (ፊልጵስዩስ 4:5 NW) በዓለም ዙሪያ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሕመምተኞችን ሕሊና ለማክበር ፈቃደኛ የሆኑ የጤና ባለሞያዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።