‘የይሖዋ ሕግ’ የጸና ነው
‘የይሖዋ ሕግ’ የጸና ነው
“የእግዚአብሔርን ሕግ ዐውጃለሁ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ፤ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ . . . ለምነኝ፤ መንግሥታትን ርስት አድርጌ . . . እሰጥሃለሁ።’”—መዝሙር 2:7, 8
1. በአምላክና በብሔራት ዓላማ መካከል ምን ልዩነት አለ?
ይሖዋ አምላክ ከሰው ልጆችና ከምድር ጋር በተያያዘ ዓላማ አለው። ብሔራትም የራሳቸው ዓላማ አላቸው። ይሁንና እነዚህ ዓላማዎች ፍጹም የተለያዩ ናቸው! ይህ መሆኑ የሚጠበቅ ነው፤ ምክንያቱም አምላክ “ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ፣ መንገዴ ከመንገዳችሁ፣ ሐሳቤም ከሐሳባችሁ እንዲሁ ከፍ ያለ ነው” በማለት ተናግሯል። አምላክ ቀጥሎ የተናገረው ነገር ዓላማው በእርግጥ እንደሚፈጸም ያሳያል፦ “ዝናምና በረዶ ከሰማይ ወርዶ፣ ምድርን በማራስ፣ እንድታበቅልና እንድታፈራ ለዘሪው ዘር፣ ለበላተኛም እንጀራ እንድትሰጥ ሳያደርግ፣ ወደ ላይ እንደማይመለስ ሁሉ፣ ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤ የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል።”—ኢሳይያስ 55:9-11
2, 3. በሁለተኛው መዝሙር ላይ ምን ነገር በግልጽ ተቀምጧል? ሆኖም ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?
2 አምላክ እርሱ ከሾመው መሲሐዊ ንጉሥ ጋር በተያያዘ ያለው ዓላማ እንደሚፈጸም በሁለተኛው መዝሙር ውስጥ በግልጽ ተቀምጧል። መዝሙሩን ያቀናበረው የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ዳዊት ብሔራት የሚያሴሩበት ጊዜ እንደሚመጣ በአምላክ መንፈስ ተነሳስቶ ትንቢት ተናግሯል። ገዥዎቻቸው ይሖዋ አምላክንና መሲሑን ይቃወማሉ። ይሁን እንጂ መዝሙራዊው እንደሚከተለውም ሲል ዘምሯል፦ “የእግዚአብሔርን ሕግ ዐውጃለሁ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ፤ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ . . . ለምነኝ፤ መንግሥታትን ርስት አድርጌ፣ የምድርንም ዳርቻ ግዛት እንዲሆንህ እሰጥሃለሁ።’”—መዝሙር 2:7, 8
3 ‘የይሖዋ ሕግ’ ለብሔራት ምን ትርጉም አለው? የሰውን ዘር በአጠቃላይ የሚነካውስ እንዴት ነው? የይሖዋ ሕግ በብሔራት ላይ የሚኖረው ውጤት ሁለተኛውን መዝሙር ለሚያነቡ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ምን ትርጉም ይኖረዋል?
ብሔራት ያሴራሉ
4. የመዝሙር 2:1, 2ን ዋና ዋና ነጥቦች ተናገር።
4 መዝሙራዊው ሕዝቦችና ገዥዎቻቸው የሚወስዱትን እርምጃ በሚመለከት ያቀናበረውን መዝሙር የከፈተው እንደሚከተለው በማለት ነበር፦ “ሕዝቦች ለምን ያሤራሉ? ሰዎችስ ለምን ከንቱ ነገር ያውጠነጥናሉ? የምድር ነገሥታት ተነሡ፤ ገዦችም በእግዚአብሔርና በመሢሑ ላይ፣ ሊመክሩ ተሰበሰቡ።”—መዝሙር 2:1, 2 a
5, 6. ሰዎች ‘ያውጠነጠኑት ከንቱ ነገር’ ምንድን ነው?
5 በዛሬው ጊዜ ያሉ ብሔራት ‘የሚያውጠነጥኑት ከንቱ ነገር’ ምንድን ነው? ብሔራት አምላክ የቀባውን ማለትም መሢሑን ወይም ክርስቶስን ከመቀበል ይልቅ ሥልጣናቸውን የሚያራዝሙበትን መንገድ ‘ያውጠነጥናሉ’ ወይም ያሰላስላሉ። በሁለተኛው መዝሙር ላይ የሚገኙት እነዚህ ቃላት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የአይሁድና የሮማ ገዥዎች ኅብረት ፈጥረው አምላክ ለማንገሥ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን በገደሉበት ጊዜም ፍጻሜአቸውን አግኝተዋል። ይሁን እንጂ በዋነኝነት መፈጸም የጀመሩት ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ በተሾመበት በ1914 ነው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ በምድር ላይ ያለ አንድም የፖለቲካ መንግሥት አምላክ ለሾመው ንጉሥ እውቅና አልሰጠም።
6 መዝሙራዊው ‘ሰዎች ለምን ከንቱ ነገር ያውጠነጥናሉ?’ ብሎ ሲጠይቅ ምን ማለቱ ነበር? ከንቱ የተባለው ዓላማቸው ሲሆን ይህ ዓላማቸው እርባና ቢስና ጠፊ ነው። ለምድር ሰላምና አንድነት ማምጣት አይችሉም። ያም ሆኖ ግን ሰዎች ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ መለኮታዊውን አገዛዝ የሚጻረር እርምጃ ከመውሰድ አይመለሱም። እንዲያውም ልዑሉንና እርሱ የቀባውን ገዥ አምርረው ለመቃወም ተባብረው ይነሳሉ። እንዴት ያለ ሞኝነት ነው!
ድል አድራጊው ንጉሥ
7. የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት መዝሙር 2:1, 2 በኢየሱስ ላይ እንደተፈጸመ በጸሎታቸው ላይ የገለጹት እንዴት ነው?
7 የኢየሱስ ተከታዮች መዝሙር 2:1, 2 በእርሱ ላይ እንደተፈጸመ ተናግረዋል። በእምነታቸው ምክንያት ስደት በደረሰባቸው ጊዜ እንዲህ በማለት ጸልየው ነበር፦ “ልዑል ጌታ ሆይ አንተ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥረሃል፤ በመንፈስ ቅዱስም አማካይነት በአገልጋይህ በአባታችን በዳዊት አፍ እንዲህ ብለህ ተናግረሃል፤ ‘አሕዛብ ለምን በቁጣ ተነሣሡ? ሕዝቡስ ለምን በከንቱ አሤሩ? የምድር ነገሥታት ተሰለፉ፤ ገዦችም በአንድነት ተሰበሰቡ፤ በጌታ ላይ፣ በተቀባውም ላይ ተከማቹ።’ በእርግጥም ሄሮድስና ጳንጥዮስ ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በዚህች ከተማ አንተ በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ለማሤር ተሰበሰቡ።” (የሐዋርያት ሥራ 4:24-27፤ ሉቃስ 23:1-12) b አዎን፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን አምላክ በቀባው አገልጋዩ በኢየሱስ ላይ ሴራ ተጠንስሶ ነበር። ይሁን እንጂ፣ ይህ መዝሙር ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ሌላ ፍጻሜ ይኖረዋል።
8. መዝሙር 2:3 በዚህ ዘመን ባሉ ብሔራትም ላይ የሚሠራው እንዴት ነው?
8 የጥንቷ እስራኤል፣ ዳዊትን በመሳሰሉ ሰብዓዊ ነገሥታት ትተዳደር በነበረበት ወቅት አረማውያን ብሔራትና ገዥዎቻቸው በአምላክና እርሱ በቀባው ንጉሥ ላይ ተነስተው ነበር። በዘመናችንስ? በዚህ ዘመን ያሉ ብሔራት ይሖዋና መሢሑ የሚፈልጉባቸውን ለማሟላት ፈቃደኛ ስላልሆኑ “ሰንሰለታቸውን እንበጥስ፣ የእግር ብረታቸውንም አውልቀን እንጣል” እንዳሉ ተደርጎ ተገልጿል። (መዝሙር 2:3) ገዥዎችና ሕዝቦች አምላክና እርሱ የሾመው ቅቡዕ የሚጥሉትን ማንኛውንም ማእቀብ ይቃወማሉ። እርግጥ ነው፣ ሰንሰለታቸውን ለመበጠስና የእግር ብረታቸውን ለመጣል ምንም ዓይነት ጥረት ቢያደርጉ አይሳካላቸውም።
ይሖዋ ይሳለቅባቸዋል
9, 10. ይሖዋ በብሔራት ላይ የሚሳለቅባቸው ለምንድን ነው?
9 ይሖዋ ገዥዎች የራሳቸውን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሚያደርጉት ማንኛውም ጥረት አያሳስበውም። ሁለተኛው መዝሙር በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “በሰማይ ዙፋን ላይ የተቀመጠው ይሥቃል፤ ጌታም [ይሖዋም] ይሣለቅባቸዋል።” (መዝሙር 2:4) አምላክ እነዚህን ገዥዎች ከቁብ ሳይቆጥራቸው ዓላማውን ከግብ ለማድረስ እርምጃ ይወስዳል። በመዳፈራቸው የሚስቅባቸው ከመሆኑም በላይ ይሳለቅባቸዋል። እናደርጋለን ስለሚሉት ነገር ጉራቸውን መንዛት ይችላሉ። የይሖዋ መሳለቂያ ከመሆን ግን አያመልጡም። ተቃውሟቸው የትም ስለማያደርሳቸው ይስቅባቸዋል።
10 ዳዊት በአንድ ሌላ መዝሙር ላይ በጠላትነት ተነስተውበት ስለነበሩ ሰዎችና ብሔራት እንዲህ ሲል ዘምሯል፦ “የሰራዊት አምላክ የሆንህ፣ አንተ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝቦችን ሁሉ ለመቅጣት ተነሥ፤ በተንኰላቸው በደል የሚፈጽሙትንም ሁሉ አትማራቸው። እንደ ውሻ እያላዘኑ፣ በምሽት ተመልሰው ይመጣሉ፤ በከተማዪቱም ዙሪያ ይራወጣሉ። ከአፋቸው የሚወጣውን ተመልከት፤ ሰይፍ በከንፈራቸው ላይ አለ፤ ‘ማን ሊሰማን ይችላል?’ ይላሉና። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ትሥቅባቸዋለህ፤ ሕዝቦችን ሁሉ በንቀት ታያቸዋለህ።” (መዝሙር 59:5-8) ይሖዋ ብሔራት እርሱን ለመቃወም በሚነዙት ጉራና በሚፈጠርባቸው ግራ መጋባት ይስቃል።
11. ብሔራት የአምላክን ዓላማ ለማክሸፍ ሲፍጨረጨሩ ምን ይደርስባቸዋል?
11 መዝሙር 2 የያዘው ሐሳብ አምላክ ለምንም ነገር እንደማይበገር ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። ምንጊዜም ፈቃዱን እንደሚፈጽምና ታማኝ አገልጋዮቹን ፈጽሞ እንደማይጥል ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን። (መዝሙር 94:14) ታዲያ ብሔራት የይሖዋን ዓላማ ለማክሸፍ የሚያደርጉት ጥረት ምን ያስከትልባቸዋል? በመዝሙሩ ላይ እንደተገለጸው አምላክ እንደ ነጎድጓድ በሚያስገመግም ድምፅ “በቍጣው ይናገራቸዋል።” ከዚህም በላይ በመብረቅ የተመቱ ያህል “በመዓቱም ያስደነግጣቸዋል።”—መዝሙር 2:5
አምላክ የሾመው ንጉሥ
12. መዝሙር 2:6 ስለ ምን ይናገራል?
12 ይሖዋ ቀጥሎ በመዝሙራዊው አማካኝነት “እኔ ግን በተቀደሰው ተራራዬ፣ በጽዮን ላይ የራሴን ንጉሥ ሾምሁ” በማለት ያወጀው መልእክት ብሔራትን ሳያስቆጣቸው አይቀርም። (መዝሙር 2:6) የጽዮን ተራራ ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ የተሾመበት ኢየሩሳሌም ውስጥ የሚገኝ ኮረብታ ነበር። ይሁን እንጂ መሢሐዊው ንጉሥ የሚቀመጠው በዚያች ከተማ ወይም በምድር ላይ በሌላ ቦታ በሚገኝ ዙፋን ላይ አይደለም። እንዲያውም ይሖዋ ኢየሱስ ክርስቶስን በሰማያዊው የጽዮን ተራራ ላይ መሢሐዊ ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል።—ራእይ 14:1
13. ይሖዋ ከልጁ ጋር ምን ቃል ኪዳን አድርጓል?
13 አሁን ደግሞ መሢሐዊው ንጉሥ እንደሚከተለው በማለት ይናገራል፦ “የእግዚአብሔርን ሕግ [ይሖዋ ከልጁ ጋር ቀደም ሲል የገባውን የመንግሥት ቃል ኪዳን] ዐውጃለሁ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ፤ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ።’” (መዝሙር 2:7) ክርስቶስ ሐዋርያቱን “እናንተም ሳትለዩኝ በመከራዬ ጊዜ በአጠገቤ የቆማችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም ደግሞ በመንግሥቴ እሾማችኋለሁ” ባላቸው ጊዜ ይህን የመንግሥት ቃል ኪዳን ማመልከቱ ነበር።—ሉቃስ 22:28, 29
14. ኢየሱስ ንጉሥ የመሆን የማያጠያይቅ መብት አለው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
14 በመዝሙር 2:7 ላይ በትንቢት እንደተነገረው ይሖዋ፣ ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ እንዲሁም ከሞት አስነስቶ መንፈሳዊ ሕይወት ሲሰጠው ልጁ መሆኑን መስክሯል። (ማርቆስ 1:9-11፤ ሮሜ 1:4፤ ዕብራውያን 1:5፤ 5:5) አዎን፣ በሰማይ በተቋቋመው መንግሥት ላይ ንጉሥ ሆኖ የተሾመው የአምላክ አንድያ ልጅ ነው። (ዮሐንስ 3:16) ኢየሱስ የንጉሥ ዳዊት ዘር እንደመሆኑ መጠን ንጉሥ የመሆን መብት እንዳለው የታወቀ ነው። (2 ሳሙኤል 7:4-17፤ ማቴዎስ 1:6, 16) መዝሙሩ እንደሚናገረው አምላክ ልጁን “ለምነኝ፤ መንግሥታትን ርስት አድርጌ፣ የምድርንም ዳርቻ ግዛት እንዲሆንህ እሰጥሃለሁ” ብሎታል።—መዝሙር 2:8
15. ኢየሱስ መንግሥታት በርስትነት እንዲሰጡት የሚጠይቀው ለምንድን ነው?
15 ንጉሡ ይኸውም የአምላክ ልጅ ከይሖዋ ቀጥሎ ያለውን ሥልጣን ይዟል። ኢየሱስ ተፈትኖ ለይሖዋ ታማኝና እምነት የሚጣልበት መሆኑን አስመስክሯል። ከዚህም በላይ የአምላክ የበኩር ልጅ እንደመሆኑ ውርስ ይገባዋል። በእርግጥም፣ ኢየሱስ ክርስቶስ “የማይታየው አምላክ አምሳል ነው፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው።” (ቆላስይስ 1:15) እርሱ እስከጠየቀ ድረስ አምላክ ‘መንግሥታትን ርስት፣ የምድርን ዳርቻ ግዛት አድርጎ ይሰጠዋል።’ ኢየሱስ ‘በሰው ልጆች ደስ የሚሰኝ’ ስለሆነና በሰማይ የሚኖረው አባቱ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለውን ፈቃድ ለማስፈጸም ልባዊ ፍላጎት ስላለው ይህን ጥያቄ ማቅረቡ አይቀርም።—ምሳሌ 8:30, 31
ይሖዋ በብሔራት ላይ ያሳለፈው ብይን
16, 17. በመዝሙር 2:9 መሠረት የብሔራት ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው?
16 ሁለተኛው መዝሙር ኢየሱስ ክርስቶስ በማይታይ ሁኔታ በመግዛት ላይ ባለበት በዚህ ጊዜ ፍጻሜውን በማግኘት ላይ እንደመሆኑ የብሔራት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን? ንጉሡ በቅርቡ “አንተም በብረት በትር ትቀጠቅጣቸዋለህ፤ እንደ ሸክላ ዕቃ ታደቃቸዋለህ” የሚለውን የአምላክን ፍርድ ያስፈጽማል።—መዝሙር 2:9
17 በጥንት ዘመን ነገሥታት ይይዙት የነበረው በትር ንጉሣዊ ሥልጣንን የሚያሳይ ምልክት ነበር። አንዳንድ በትሮች ልክ በመዝሙሩ ላይ እንደተገለጸው ከብረት የተሠሩ ነበሩ። እዚህ ላይ የገባው ምሳሌያዊ አነጋገር ንጉሥ ሆኖ የተሾመው ክርስቶስ ብሔራትን በቀላሉ እንደሚያጠፋቸው ያሳያል። በብረት በትር የሚሰነዘር አንድ ደህና ምት ሸክላ ሠሪ ያበጀውን የሸክላ ዕቃ አመድ ያደርገዋል።
18, 19. የምድር ነገሥታት የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?
18 ገዥዎች በሙሉ እንዲህ ያለው ጥፋት ፈጽሞ አይቀርላቸውም ማለት ነው? በፍጹም። መዝሙራዊው እንዲህ በማለት ይማጸናቸዋል፦ “እናንት ነገሥታት ልብ በሉ፤ እናንት የምድር ገዦችም፣ ተጠንቀቁ።” (መዝሙር 2:10) ነገሥታት ልብ እንዲሉና እንዲጠነቀቁ ጥሪ ቀርቦላቸዋል። የአምላክ መንግሥት ለመላው የሰው ዘር ከሚያመጣው በረከት አንጻር ሲታይ ዕቅዳቸው እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ መገንዘብ ይኖርባቸዋል።
19 የምድር ነገሥታት የአምላክን ሞገስ ማግኘት ከፈለጉ አካሄዳቸውን መለወጥ ይኖርባቸዋል። “እግዚአብሔርን በፍርሀት አገልግሉት፤ ለእርሱ መራድም ደስ ያሰኛችሁ” የሚል ምክር ተሰጥቷቸዋል። (መዝሙር 2:11) እንደዚያ ቢያደርጉ ውጤቱ ምን ይሆናል? ሴራ ከመጎንጎን ወይም በሽብር ከመዋጥ ይልቅ መሢሐዊው ንጉሥ ወደፊት በሚያመጣላቸው ነገር ደስ መሰኘት ይችላሉ። የምድር ገዥዎች በአገዛዛቸው ውስጥ የሚታየውን ኩራትና ዕብሪት ማስወገድ ያስፈልጋቸዋል። ከዚህም በላይ ባስቸኳይ ለውጥ ማድረግ፣ አቻ የማይገኝለትን የይሖዋን ሉዓላዊነት መገንዘብ እንዲሁም አምላክም ሆነ እርሱ የሾመው መሢሐዊ ንጉሥ ያላቸውን የላቀ ኃይል መቀበል ይኖርባቸዋል።
“ልጁን ሳሙት”
20, 21. ‘ልጁን መሳም’ ሲባል ምን ማለት ነው?
20 አሁን ደግሞ መዝሙር 2 ለብሔራት ገዥዎች የምሕረት ጥሪ ያቀርብላቸዋል። ለተቃውሞ ከሚተባበሩ ይልቅ የሚከተለውን እንዲያደርጉ ምክር ተሰጥቷቸዋል፦ “[ይሖዋ አምላክ] እንዳይቈጣና በመንገድ እንዳትጠፉ፣ ዝቅ ብላችሁ ልጁን ሳሙት፤ ቁጣው ፈጥኖ ይነዳልና።” (መዝሙር 2:12ሀ) ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ አንድ ሕግ ከደነገገ ሕጉ መከበር ይኖርበታል። አምላክ ልጁን በዙፋን ላይ ሲያስቀምጥ የምድር ገዥዎች ‘ከንቱ ነገር ማውጠንጠናቸውን’ ማቆም ይገባቸው ነበር። ወዲያውኑ ለንጉሡ እውቅና መስጠትና ሙሉ በሙሉ እርሱን መታዘዝ ነበረባቸው።
21 ገዥዎች ‘ልጁን መሳም’ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው? ይህ መዝሙር በተቀናበረበት ወቅት መሳም የወዳጅነት መግለጫ የነበረ ከመሆኑም በላይ አንድ ሰው እንግዶች ቤቱ ሲመጡ በመሳም ደስታውን ይገልጽ ነበር። በተጨማሪም መሳም የታማኝነት መግለጫ ሆኖ ያገለግል ነበር። (1 ሳሙኤል 10:1) በሁለተኛው መዝሙር ውስጥ በሚገኘው በዚህ ጥቅስ ላይ አምላክ ልጁ የተቀባ ንጉሥ መሆኑን እንዲቀበሉ ወይም እንዲስሙት ብሔራትን አዝዟል።
22. የዓለም ገዥዎች የትኛውን ማስጠንቀቂያ መቀበል አለባቸው?
22 አምላክ የሾመውን ንጉሥ ሥልጣን የማይቀበሉ ሰዎች ይሖዋን የተሳደቡ ያህል ነው። የይሖዋ አምላክን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት እንዲሁም የሰው ልጆችን ከሁሉ በተሻለ ሁኔታ የሚያስተዳድር ንጉሥ ለመሾም ያለውን ሥልጣንና ችሎታ መቀበል አይፈልጉም። የዓለም ገዥዎች የራሳቸውን ዕቅድ ለማስፈጸም ሲሯሯጡ የአምላክ ቁጣ ድንገት ይነድባቸዋል። ‘ቁጣው ፈጥኖ የሚነድ’ ከመሆኑም በላይ ማንም ሊቋቋመው አይችልም። ገዥዎች ይህን ማስጠንቀቂያ በአመስጋኝነት ስሜት መቀበልና ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል። እንዲህ ማድረጋቸው ሕይወት ያስገኝላቸዋል።
23. ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ምን ለማድረግ ጊዜው አላለፈባቸውም?
23 ይህ አስደናቂ መዝሙር “እርሱን [ይሖዋን] መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ የተባረኩ ናቸው” በማለት ይደመድማል። (መዝሙር 2:12ለ) ግለሰቦች ሕይወታቸውን ለማዳን ጊዜው አላለፈባቸውም። የብሔራትን እቅድ ለማስፈጸም ከላይ ታች የሚሉ ገዥዎችም በግለሰብ ደረጃ እርምጃ መውሰድ ይችላሉ። በንጉሣዊ አገዛዙ አማካኝነት መጠጊያ ወደሚሆነው ወደ ይሖዋ መሸሽ ይችላሉ። ሆኖም መሢሐዊው መንግሥት ተቃዋሚ ብሔራትን ከማጥፋቱ በፊት እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል።
24. በዚህ በመከራ በተሞላ ዓለም እንኳ እርካታ ያለው ሕይወት መኖር የምንችለው እንዴት ነው?
24 መጽሐፍ ቅዱስን ተግተን የምናጠናና ምክሩን በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ መከራ በሞላበት በዚህ ዓለም ውስጥ እንኳ አርኪ ሕይወት መኖር እንችላለን። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ደስታ የሰፈነበት የቤተሰብ ግንኙነት የሚያስገኝልን ከመሆኑም በላይ ይህን ዓለም ቀስፈው ከያዙት በርካታ አስጊ ነገሮች ነጻ እንወጣለን። የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተላችን በእርግጥ ፈጣሪ እንደሚደሰትብን እንዲሰማን ያደርጋል። ከአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ሌላ ማንም ቢሆን “ለአሁኑም ሆነ ለሚመጣው ሕይወት” ዋስትና ሊሰጠን አይችልም። የመንግሥቱን አገዛዝ ባለመቀበል ትክክል የሆነውን የሚቃወሙትን ከምድረ ገጽ በማጥፋት ይህንን ይፈጽማል።—1 ጢሞቴዎስ 4:8
25. ‘የይሖዋ ሕግ’ መፈጸሙ ስለማይቀር በዘመናችን ምን እንደሚከሰት ልንጠብቅ እንችላለን?
25 ‘የይሖዋ ሕግ’ ጽኑ ነው። አምላክ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ ለመላው የሰው ዘር የሚበጀውን የሚያውቅ ሲሆን በውድ ልጁ በሚተዳደረው ንጉሣዊ መንግሥት ሥር ለታዛዥ ሰዎች ሰላም፣ እርካታና ዘላቂ ደኅንነት ለመስጠት ያለውን ዓላማ ከግብ ያደርሳል። ነቢዩ ዳንኤል ጊዜያችንን በሚመለከት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስ . . . መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” (ዳንኤል 2:44) እንግዲያው ከምንጊዜውም ይበልጥ ‘ልጁን ለመሳምና’ ሉዓላዊውን ጌታ ይሖዋን ለማገልገል ጊዜው አሁን ነው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በመጀመሪያ ‘መሢሕ’ (የተቀባ) የተባለው ንጉሥ ዳዊት ሲሆን “የምድር ነገሥታት” ደግሞ ሠራዊቶቻቸውን በእርሱ ላይ ያዘመቱ የፍልስጥኤም ገዥዎች ነበሩ።
b በሁለተኛው መዝሙር ላይ የተጠቀሰው፣ አምላክ የሾመው ቅቡዕ ወይም መሢሕ ኢየሱስ መሆኑን የሚያሳዩ ሌሎች የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችም አሉ። መዝሙር 2:7ን ከሐዋርያት ሥራ 13:32, 33፣ ከዕብራውያን 1:5 እና 5:5 ጋር በማወዳደር ይህን በግልጽ ለማየት ይቻላል። በተጨማሪም መዝሙር 2:9ን እና ራእይ 2:27ን ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ሰዎች ‘ያውጠነጠኑት ከንቱ ነገር’ ምንድን ነው?
• ይሖዋ በብሔራት ላይ የሚሳለቅባቸው ለምንድን ነው?
• አምላክ በብሔራት ላይ ያወጀው ሕግ ምንድን ነው?
• “ልጁን ሳሙት” ሲባል ምን ማለት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳዊት ስለ ድል አድራጊው መሢሐዊ ንጉሥ ዘምሯል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ገዥዎችና የእስራኤል ሕዝብ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ አሲረዋል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቶስ በሰማያዊው የጽዮን ተራራ ላይ ንጉሥ ሆኖ ተሹሟል