በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ለትሑታን ክብሩን ይገልጣል

ይሖዋ ለትሑታን ክብሩን ይገልጣል

ይሖዋ ለትሑታን ክብሩን ይገልጣል

“ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት፣ ሀብትን፣ ክብርንና ሕይወትን ያስገኛል።”—ምሳሌ 22:4

1, 2. (ሀ) የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እስጢፋኖስ ‘በእምነትና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ’ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) እስጢፋኖስ ትሑት እንደነበር እንዴት ማወቅ ይቻላል?

 እስጢፋኖስ ‘እምነትና መንፈስ ቅዱስ’ እንዲሁም ‘ጸጋና ኀይል የሞላበት’ ሰው ነበር። ከቀድሞዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ እንደመሆኑ መጠን በሕዝቡ መካከል ድንቅ ነገሮችንና ተአምራዊ ምልክቶችን የማድረግ ችሎታ ነበረው። በአንድ ወቅት የተወሰኑ ሰዎች ተቃውሞ አስነስተው ተከራክረውት ነበር፤ “ይሁን እንጂ ይናገርበት የነበረውን ጥበብና መንፈስ መቋቋም አልቻሉም።” (የሐዋርያት ሥራ 6:5, 8-10) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው እስጢፋኖስ ትጉ የአምላክ ቃል ተማሪ የነበረ ሲሆን በአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ፊት ለቃሉ አሳማኝ በሆነ መንገድ ተሟግቷል። የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 7 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው በሰፊው የሰጠው ምሥክርነት የአምላክ ዓላማ ደረጃ በደረጃ ሲፈጸም በትኩረት ይከታተል እንደነበር ያሳያል።

2 እስጢፋኖስ፣ ከነበራቸው ሥልጣንና እውቀት የተነሳ ከተራው ሕዝብ እንደሚበልጡ ከሚሰማቸው የሃይማኖት መሪዎች በተቃራኒ ትሑት ነበር። (ማቴዎስ 23:2-7፤ ዮሐንስ 7:49) የቅዱሳን ጽሑፎች ጥልቅ እውቀት የነበረው ቢሆንም ሐዋርያት “በጸሎትና በቃሉ አገልግሎት” መትጋት እንዲችሉ “የማእዱን አገልግሎት ለማስተናገድ” ሲመደብ ሥራውን በደስታ ተቀብሏል። እስጢፋኖስ በወንድሞች ዘንድ መልካም ስም ያተረፈ በመሆኑ በየዕለቱ ምግብ የማከፋፈሉን ሥራ እንዲያካሂዱ ከተመረጡት ሰባት የተመሰከረላቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነበር፤ ሥራውንም በትሕትና ተቀብሏል።—የሐዋርያት ሥራ 6:1-6

3. እስጢፋኖስ የአምላክ ታላቅ ደግነት ልዩ መግለጫ የሆነ ምን ነገር ተመልክቷል?

3 እስጢፋኖስ ትሑት መሆኑ እንዲሁም መንፈሳዊነቱና የአቋም ጽናቱ ከይሖዋ እይታ የተሰወረ አልነበረም። በሳንሄድሪን ለተሰበሰቡት በጥላቻ ዓይን ለሚያዩት የአይሁድ መሪዎች ምሥክርነት በሰጠበት ወቅት “ፊቱ የመልአክ ፊት መስሎ ታያቸው።” (የሐዋርያት ሥራ 6:15) የፊቱ ገጽታ የመልአክ ዓይነት የነበረ ሲሆን የክብር አምላክ ከሆነው ከይሖዋ ያገኘው መረጋጋት ይታይበትም ነበር። እስጢፋኖስ ለሳንሄድሪን አባላት ድፍረት የተሞላበት ምሥክርነት ከሰጠ በኋላ የአምላክን ታላቅ ደግነት አስደናቂ በሆነ መንገድ ተመለከተ። “በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኩር ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔርን ክብር፣ እንዲሁም ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየ።” (የሐዋርያት ሥራ 7:55) ይህን አስደናቂ ራእይ ማየቱ ኢየሱስ የአምላክ ልጅና መሲሕ ስለመሆኑ ያለውን እምነት ይበልጥ አጠናክሮለታል። ከዚህም የተነሳ፣ ትሑት የሆነው እስጢፋኖስ ብርታት ያገኘ ሲሆን የይሖዋ ሞገስ እንዳልተለየውም እርግጠኛ እንዲሆን አስችሎታል።

4. ይሖዋ ክብሩን የሚገልጠው ለእነማን ነው?

4 እስጢፋኖስ እንዲመለከት የተደረገው ራእይ እንደሚያሳየው ይሖዋ ክብሩንና ዓላማውን የሚገልጠው ትሑት ለሆኑና ከእርሱ ጋር ያላቸውን ዝምድና በአድናቆት ለሚመለከቱ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ግለሰቦች ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት፣ ሀብትን፣ ክብርንና ሕይወትን ያስገኛል” ይላል። (ምሳሌ 22:4) በመሆኑም ልባዊ ትሕትና ምን ማለት እንደሆነ፣ ይህን እጅግ ጠቃሚ ባሕርይ እንዴት ማዳበር እንደምንችል እንዲሁም በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ትሕትና ማንጸባረቃችን እንዴት እንደሚጠቅመን መገንዘባችን በጣም አስፈላጊ ነው።

አምላካዊ ባሕርይ የሆነው ትሕትና

5, 6. (ሀ) ትሕትና ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) ይሖዋ ትሕትና ያሳየው እንዴት ነው? (ሐ) ይሖዋ ያሳየው ትሕትና ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

5 በአጽናፈ ዓለም ውስጥ በሥልጣኑና በክብሩ አቻ የሌለው ይሖዋ አምላክ በትሕትና ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌ መሆኑ አንዳንዶችን ያስገርማቸው ይሆናል። ንጉሥ ዳዊት ይሖዋን “የድል ጋሻ ሰጥተኸኛል፤ ቀኝ እጅህም ደግፋ ይዛኛለች፤ ዝቅ ብለህም ከፍ አደረግኸኝ” ብሎታል። (መዝሙር 18:35) ዳዊት የይሖዋን ትሕትና ለመግለጽ ‘ዝቅ ማለት’ የሚል ትርጉም ያለውን የዕብራይስጡን መነሻ ቃል ተጠቅሟል። ይህ ቃል “ትሕትና” ከሚለው ቃል በተጨማሪ “ታዛዥ፣” “ቅን” እና “ራስን ማዋረድ” ለሚሉት ቃላትም መነሻ ሆኖ ያገለግላል። ስለዚህ ይሖዋ ፍጽምና ከሚጎድለው ከዳዊት ጋር ለመቀራረብ ራሱን ዝቅ ሲያደርግና የእርሱ ወኪል እንዲሆን ሲያነግሠው ትሕትና አሳይቷል። ለመዝሙር 18 የተሰጠው መግለጫ እንደሚያሳየው ይሖዋ “ከሳዖልና ከጠላቶቹ ሁሉ እጅ” በመታደግ ዳዊትን ጠብቆታል እንዲሁም ረድቶታል። ከዚህም የተነሳ ዳዊት ንጉሥ በመሆኑ የሚያገኘው ማንኛውም ታላቅነት ወይም ክብር ይሖዋ በትሕትና እርሱን ለመርዳት በሚወስደው እርምጃ ላይ የተመካ መሆኑን ተረድቷል። ዳዊት ይህን መገንዘቡ የትሕትና ባሕሪውን እንዳያጣ አስችሎታል።

6 የእኛስ ሁኔታ እንዴት ነው? ይሖዋ እውነትን እንድናውቅ አድርጎናል፤ ምናልባትም በድርጅቱ አማካኝነት አንዳንድ ልዩ የአገልግሎት መብቶች ሰጥቶን ወይም ፈቃዱን እንድንፈጽም እየተጠቀመብን ይሆናል። ይህን አጋጣሚ በማግኘታችን ምን ሊሰማን ይገባል? በትሕትና መመላለስ አይገባንም? ራሳችንን ከፍ ከፍ በማድረግ ለጥፋት ከመዳረግ ይልቅ ይሖዋ ላሳየን ትሕትና አመስጋኝ መሆን አይገባንም?—ምሳሌ 16:18፤ 29:23

7, 8. (ሀ) ይሖዋ ከምናሴ ጋር በነበረው ግንኙነት ትሑት መሆኑ የታየው እንዴት ነው? (ለ) ትሕትና በማሳየት ረገድ ይሖዋ እና ምናሴ ምሳሌ የተዉልን በምን መንገድ ነው?

7 ይሖዋ ፍጽምና ከሚጎድላቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት በመመሥረት ታላቅ ትሕትና ከማሳየቱም በላይ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉትን ከፍ በማድረግ ወይም በማክበር ምሕረቱን ለመዘርጋት ፈቃደኛ መሆኑንም አሳይቷል። (መዝሙር 113:4-7) ለምሳሌ ያህል የይሁዳ ንጉሥ የነበረውን የምናሴን ሁኔታ ተመልከት። በንግሥና ዘመኑ ሐሰት አምልኮ እንዲስፋፋ በማድረግ ሥልጣኑን አላግባብ ተጠቀመበት፤ እንዲሁም “ለቁጣ ያነሣሣው ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ።” (2 ዜና መዋዕል 33:6) በመጨረሻ ይሖዋ የአሦር ንጉሥ ከዙፋኑ እንዲያወርደው በማድረግ ምናሴን ቀጣው። ምናሴ ታስሮ በነበረበት ወቅት “የአምላኩን የእግዚአብሔርን በጎነት ፈለገ፤ . . . ራሱን እጅግ አዋረደ።” ከዚህም የተነሳ ይሖዋ በኢየሩሳሌም ንግሥናውን መልሶ ሰጠው፣ ምናሴም “እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን ዐወቀ።” (2 ዜና መዋዕል 33:11-13) አዎን፣ ይሖዋ ምናሴ ባሳየው ትሕትና ስለተደሰተ ኃጢአቱን የተወለት ከመሆኑም በላይ ንግሥናውን መልሶ በመስጠት እርሱም በተራው ትሕትና አሳይቶታል።

8 ይሖዋ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆኑና ምናሴ ያሳየው የንስሐ ዝንባሌ በትሕትና ረገድ ለእኛ ትልቅ ትምህርት ይዟል። ሰዎች ሲያስቀይሙን የምናሳየው ጠባይና ኃጢአት ስንሠራ የምናሳየው ዝንባሌ ይሖዋ ለእኛ በሚሰጠው ምላሽ ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። ሌሎች ሲበድሉን በደስታ ይቅር የምንል ከሆነና ጥፋታችንን በትሕትና አምነን የምንቀበል ከሆነ ይሖዋ ይቅር እንዲለን መጠየቅ እንችላለን።—ማቴዎስ 5:23, 24፤ 6:12

ትሑታን የአምላክን ክብር ያያሉ

9. ትሕትና የደካማነት ምልክት ነው? አብራራ።

9 ይሁን እንጂ ትሕትናም ሆነ ሌሎች ተቀራራቢ ባሕርያት የድክመት ወይም ጥፋትን ቸል ብሎ የማለፍ ምልክት እንደሆኑ ተደርገው መታየት የለባቸውም። ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚያሳዩት ይሖዋ ትሑት ቢሆንም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የጽድቅ ቁጣ ይቆጣል፤ ታላቅ ኃይሉንም ይገልጣል። ይሖዋ ትሑት በመሆኑ ራሳቸውን ዝቅ ለሚያደርጉ ሰዎች ሞገስ ያሳያቸዋል ወይም ልዩ ትኩረት ይሰጣቸዋል፤ ከትዕቢተኞች ግን ይርቃል። (መዝሙር 138:6) ይሖዋ ትሑት ለሆኑ አገልጋዮቹ ልዩ ትኩረት የሰጣቸው እንዴት ነው?

10. በ1 ቆሮንቶስ 2:6-10 ላይ በተገለጸው መሠረት ይሖዋ ለትሑታን ምን ይገልጥላቸዋል?

10 ይሖዋ በወሰነው ጊዜና በመረጠው የሐሳብ መገናኛ መስመር በኩል የዓላማውን አፈጻጸም ዝርዝር ጉዳዮች ለትሑት አገልጋዮቹ ገልጦላቸዋል። በሰብዓዊ ጥበብ ወይም አስተሳሰብ ለሚታመኑ አሊያም ይህን የሙጥኝ ብለው ለሚከተሉ ሰዎች እነዚህን አስደናቂ ነገሮች አይገልጥላቸውም። (1 ቆሮንቶስ 2:6-10) ሆኖም ትሑት ሰዎች የይሖዋን ዓላማ በትክክል በመረዳታቸው ለይሖዋ ታላቅ ክብር ያላቸው አድናቆት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ስለጨመረ እርሱን ለማክበር ይነሳሳሉ።

11. በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንዳንዶች ትሕትና እንደሚጎድላቸው የታየው እንዴት ነው? ይህስ ምን ጉዳት አስከተለባቸው?

11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ ክርስቲያን ነን የሚሉ አንዳንድ ሰዎችን ጨምሮ ብዙዎች ትሕትና እንደሚጎድላቸው ያሳዩ ከመሆኑም ሌላ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ አምላክ ዓላማ የገለጠላቸው ነገር መሰናከያ ሆኖባቸዋል። ጳውሎስ “የአሕዛብ ሐዋርያ” ለመሆን የበቃው በዜግነቱ፣ በእውቀቱ፣ በዕድሜው ወይም ለረጅም ዘመን ያስመዘገበው መልካም ሥራ በመኖሩ አይደለም። (ሮሜ 11:13) አብዛኛውን ጊዜ፣ ሥጋዊ አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች ይሖዋ አገልጋዮቹ አድርጎ የሚጠቀምባቸውን ሰዎች የሚመርጠው እነዚህን ጉዳዮች አይቶ እንደሆነ ይሰማቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 1:26-29፤ 3:1፤ ቆላስይስ 2:18) ይሁን እንጂ ይሖዋ ጳውሎስን የመረጠው ከፍቅራዊ ደግነቱና ከጽድቅ ዓላማው የተነሳ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:8-10) ጳውሎስ “ታላላቅ ሐዋርያት” ብሎ የጠራቸውም ሆኑ ይቃወሙት የነበሩ ሰዎች ሥልጣኑንና ከቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ያቀረበላቸውን ማስረጃ ለመቀበል ፈቃደኞች አልሆኑም። ትሑት አለመሆናቸው ይሖዋ ዓላማውን የሚፈጽምበትን አስደናቂ መንገድ መረዳትና ማስተዋል እንዳይችሉ አግዷቸዋል። ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም የሚጠቀምባቸውን ሰዎች በንቀት ዓይን ከመመልከት ወይም በእነርሱ ላይ በችኮላ ከመፍረድ እንቆጠብ።—2 ቆሮንቶስ 11:4-6

12. ይሖዋ ትሑት የሆኑ ሰዎችን እንደሚባርክ የሙሴ ታሪክ የሚያሳየው እንዴት ነው?

12 በሌላ በኩል ደግሞ ትሑት ሰዎች የአምላክን ክብር የማየት አጋጣሚ እንደተሰጣቸው የሚገልጹ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች አሉ። ከሰዎች ሁሉ “እጅግ ትሑት” የነበረው ሙሴ የአምላክን ክብር የተመለከተ ከመሆኑም ሌላ ከእርሱ ጋር የቅርብ ወዳጅነት ነበረው። (ዘኍልቁ 12:3) ለ40 ዓመታት፣ አብዛኛውን በአረቢያ ባሕር ሰርጥ በእረኝነት ላሳለፈው ለዚህ ትሑት ሰው አምላክ በብዙ መንገዶች ከፍተኛ ሞገስ አሳይቶታል። (ዘፀአት 6:12, 30) ሙሴ፣ ይሖዋ በሚሰጠው ድጋፍ እየታገዘ የእስራኤል ብሔር ቃል አቀባይና ዋና አደራጅ ሆኖ አገልግሏል። ከአምላክ ጋር ፊት ለፊት የመነጋገር አጋጣሚ አግኝቷል። በራእይ “የእግዚአብሔርን መልክ” አይቷል። (ዘኍልቁ 12:7, 8፤ ዘፀአት 24:10, 11) ለዚህ የአምላክ ወኪልና ትሑት አገልጋይ እውቅና የሰጡ ሰዎችም ተባርከዋል። በተመሳሳይ እኛም ከሙሴ የሚበልጠውን ነቢይ፣ ኢየሱስን እንዲሁም እርሱ የሾመውን “ታማኝና ልባም ባሪያ” የምንቀበልና የምንታዘዝ ከሆነ እንባረካለን።—ማቴዎስ 24:45, 46 የ1954 ትርጉም፤ የሐዋርያት ሥራ 3:22

13. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ትሑት እረኞች የይሖዋን ክብር ያዩት እንዴት ነው?

13 የዓለም ‘መድኅን፣ እርሱም ጌታ ክርስቶስ’ መወለዱን መላእክት ያበሰሩትና ‘የጌታ ክብር ያበራው’ ለእነማን ነበር? ትዕቢተኛ ለነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ወይም ከፍተኛ ማዕረግ ለነበራቸው ታዋቂ ሰዎች ሳይሆን ‘በሌሊት መንጋቸውን ሲጠብቁ በሜዳ ላደሩ’ ትሑት እረኞች ነበር። (ሉቃስ 2:8-11) እነዚህ እረኞች በችሎታቸውና በሥራቸው ክብር የሚሰጣቸው ሰዎች አልነበሩም። ይሁንና ይሖዋ ትኩረት የሰጠውና የመሲሑን መወለድ በቅድሚያ ለማብሰር የመረጠው ለእነዚህ ሰዎች ነበር። አዎን፣ ይሖዋ ክብሩን የሚገልጠው ለትሑታንና ፈሪሃ አምላክ ላላቸው ሰዎች ነው።

14. አምላክ ትሑት ለሆኑ ሰዎች ምን በረከቶች ይሰጣቸዋል?

14 ከእነዚህ ምሳሌዎች ምን እንማራለን? ይሖዋ ወደ ራሱ የሚያቀርባቸውና ዓላማውን በተመለከተ እውቀትና ማስተዋል የሚገልጥላቸው ትሑት ለሆኑ ሰዎች እንደሆነ እንገነዘባለን። ይሖዋ የሚመርጠው በሰዎች ዓይን ሲታዩ ብቁ እንዳልሆኑ የሚቆጠሩትን ሲሆን እነዚህን ግለሰቦች ታላቅ ዓላማውን ለሌሎች እንዲያሳውቁ መሣሪያ አድርጎ ይጠቀምባቸዋል። ይህን ማወቃችን መመሪያ ለማግኘት ይሖዋን፣ ትንቢታዊ ቃሉንና ድርጅቱን መመልከታችንን እንድንቀጥል ሊያነሳሳን ይገባል። ይሖዋ የታላቅ ዓላማውን አፈጻጸም በተመለከተ ለትሑት አገልጋዮቹ አስፈላጊውን መረጃ መግለጡን እንደሚቀጥል እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ነቢዩ አሞጽ “በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምስጢሩን ለአገልጋዮቹ ለነቢያት ሳይገልጥ፣ ምንም ነገር አያደርግም” ሲል ተናግሯል።—አሞጽ 3:7

ትሕትና በማዳበር የአምላክን ሞገስ አግኙ

15. ትሕትናን ለማዳበር ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? የእስራኤል ንጉሥ የሳኦል ሁኔታ ይህን የሚያሳየውስ እንዴት ነው?

15 የአምላክ ሞገስ እንዳይለየን ከፈለግን ትሑት ሆነን መቀጠል አለብን። በአንድ ወቅት የነበረን ትሕትና ሁልጊዜ አብሮን ይኖራል ማለት አይቻልም። አንድ ሰው የትሕትና ባሕሪውን አጥቶ ኩሩና ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ ለትዕቢትና ለውድቀት ይዳርገዋል። ይሖዋ የቀባው የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ሳኦል እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ደርሶበታል። መጀመሪያ ለንግሥና እንደተመረጠ ‘በዐይኑ ፊት ታናሽ’ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። (1 ሳሙኤል 15:17) ይሁን እንጂ ንጉሥ ሆኖ ገና ሁለት ዓመት ከማለፉ የትዕቢት ባሕርይ ይታይበት ጀመር። ይሖዋ በነቢዩ ሳሙኤል አማካኝነት መሥዋዕት እንዲቀርብ ያደረገውን ዝግጅት ወደ ጎን ገሸሽ ያደረገ ከመሆኑም በላይ ለአድራጎቱ ሰበብ አስባብ ይደረድር ጀመር። (1 ሳሙኤል 13:1, 8-14) ይህ ሁኔታ ትሕትና እንደሚጎድለው በግልጽ የታየበት የመጀመሪያው አጋጣሚ ነበር። ከዚህም የተነሳ የአምላክን መንፈስና ሞገስ ያጣ ከመሆኑም በላይ በመጨረሻ በአሳፋሪ ሁኔታ ሞቷል። (1 ሳሙኤል 15:3-19, 26፤ 28:6፤ 31:4) መልእክቱ ግልጽ ነው በአንድ በኩል ትሕትናንና ታዛዥነትን ለማዳበር በሌላ በኩል ደግሞ ክብር የመፈለግን ስሜት ለማስወገድ ጥረት በማድረግ የይሖዋን ሞገስ የሚያሳጣ ማንኛውንም የትዕቢት እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ ይኖርብናል።

16. ከይሖዋና ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ላይ በትኩረት ማሰባችን ትሕትና እንድናዳብር የሚረዳን እንዴት ነው?

16 ትሕትና የመንፈስ ፍሬዎች ዝርዝር ውስጥ ባይገኝም እንኳ ልናዳብረው የሚገባ አምላካዊ ባሕርይ ነው። (ገላትያ 5:22, 23፤ ቆላስይስ 3:10, 12) ትሕትና ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ያለንን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ከአስተሳሰብ ጋር የተያያዘ ባሕርይ በመሆኑ ይህንን ባሕርይ ማዳበር የታሰበበት ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። ከይሖዋ አምላክና ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ላይ በቁም ነገር ማሰባችንና ማሰላሰላችን ትሑት ሆነን እንድንቀጥል ይረዳናል። ፍጽምና የሚጎድለን ሰዎች ሁሉ በአምላክ ዓይን ስንታይ ለጥቂት ጊዜ ከቆየ በኋላ ጠውልጎ እንደሚደርቅ ሣር ነን። ሰዎች እንደ ሜዳ አንበጣ ናቸው። (ኢሳይያስ 40:6, 7, 22) አንዲት ሣር ከሌሎች ሣሮች በቁመት በትንሹ ስለምትበልጥ የምትኩራራበት ምክንያት ይኖራል? አንድ አንበጣ ከሌሎች አንበጦች ይበልጥ መስፈንጠር ስለቻለ ብቻ ሊታበይ ይገባዋል? ሌላው ቀርቶ እንዲህ ብሎ ማሰቡ በራሱ ሞኝነት ነው። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን እንዲህ ሲል አሳስቧቸዋል “አንተን ከሌላው እንድትበልጥ ያደረገህ ማን ነው? ያልተቀበልኸው የራስህ የሆነ ነገር ምን አለ? ከተቀበልህ ታዲያ፣ እንዳልተቀበልህ ለምን ትመካለህ?” (1 ቆሮንቶስ 4:7) እንደዚህ ባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ማሰላሰላችን የትሕትና ባሕርይ እንድናዳብርና እንድናሳይ ይረዳናል።

17. ነቢዩ ዳንኤል ትሕትና እንዲያዳብር የረዳው ምንድን ነው? እኛንስ ምን ሊረዳን ይችላል?

17 ዕብራዊው ነቢይ ዳንኤል ‘ራሱን በማዋረዱ’ ማለትም ትሑት በመሆኑ በአምላክ ዘንድ “እጅግ የተወደድህ” ለመባል በቅቷል። (ዳንኤል 10:11, 12) ዳንኤል ትሕትና እንዲያዳብር የረዳው ምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ዳንኤል አዘውትሮ ወደ ይሖዋ በመጸለይ በእርሱ ላይ የተሟላ ትምክህት እንዳለው አሳይቷል። (ዳንኤል 6:10, 11) ከዚህ በተጨማሪ የአምላክን ቃል በትጋትና በትክክለኛ የልብ ዝንባሌ የሚያጠና ሰው ነበር፤ ይህም በአምላክ ታላቅ ዓላማ ላይ እንዲያተኩር ረድቶታል። የሕዝቡን ብቻ ሳይሆን የራሱንም ድክመቶች አምኖ ለመቀበል ፈቃደኛ ነበር። እንዲሁም የራሱን ሳይሆን የአምላክን ጽድቅ የማራመድ ልባዊ ፍላጎት ነበረው። (ዳንኤል 9:2, 5, 7) እኛስ ዳንኤል ካሳየው የላቀ ምሳሌ ትምህርት ማግኘትና በማንኛውም የሕይወታችን ዘርፍ ትሕትና ማዳበር እንዲሁም ማንጸባረቅ እንችላለን?

18. በዛሬው ጊዜ ትሕትና የሚያሳዩ ሰዎች ምን አስደሳች ጊዜ ይጠብቃቸዋል?

18 ምሳሌ 22:4 “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት፣ ሀብትን፣ ክብርንና ሕይወትን ያስገኛል” ይላል። አዎን፣ ይሖዋ ትሑት ለሆኑ ሰዎች ሞገስ ያሳያቸዋል፤ ከዚህም የተነሳ ክብርና ሕይወት ያገኛሉ። መዝሙራዊው አሳፍ ለአምላክ የሚያቀርበውን አገልግሎት ሊያቆም ተቃርቦ በነበረበት ጊዜ ይሖዋ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል ከረዳው በኋላ “በምክርህ መራኸኝ፤ ኋላም ወደ ክብር ታስገባኛለህ” ሲል በትሕትና ተናግሯል። (መዝሙር 73:24) ይህ ለእኛ ምን ትርጉም ይዟል? የትሕትና ባሕርይ የሚያሳዩ ሰዎች የሚያገኙት ክብር ምንድን ነው? ከይሖዋ ጋር የተቀራረበና አስደሳች ዝምድና ከመመሥረታቸውም በላይ ንጉሥ ዳዊት “ገሮች . . . ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” ሲል በመንፈስ ተነሳስቶ የጻፋቸው ቃላት ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ለማየት መጠባበቅ ይችላሉ። በእርግጥም ከፊታችን አስደሳች ጊዜ ይጠብቀናል!—መዝሙር 37:11

ታስታውሳለህ?

• ይሖዋ ክብሩን የገለጠለት እስጢፋኖስ በትሕትና ረገድ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?

• ይሖዋ አምላክ በየትኞቹ መንገዶች ትሕትና አሳይቷል?

• ይሖዋ ለትሑታን ክብሩን እንደሚገልጥላቸው ከየትኞቹ ምሳሌዎች ማየት ይቻላል?

• የዳንኤል ምሳሌ ትሕትና በማዳበር ረገድ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ቆራጥ ሆኖም ትሑት

በ1919 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ፣ ዩ ኤስ ኤ በተካሄደው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች ይባላሉ) የአውራጃ ስብሰባ ላይ በወቅቱ ዓለም አቀፉን ሥራ በበላይነት ይቆጣጠር የነበረው የ50 ዓመቱ ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ ለስብሰባ የመጡትን እንግዶችና የያዙትን ሻንጣ ወደ ክፍላቸው በማድረስ በደስታ ሠርቷል። በአውራጃ ስብሰባው የመጨረሻ ቀን ላይ “እናንተ የጌታችንን ክብራማ መንግሥት . . . ለሰዎች የምታውጁ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ የሆነው የክርስቶስ አምባሳደሮች ናችሁ” ብሎ ሲናገር 7,000 የሚያህሉት ተሰብሳቢዎች በከፍተኛ የደስታ ስሜት ተዋጡ። ወንድም ራዘርፎርድ እውነት እንደሆነ ያመነበትን ነገር በእርግጠኝነትና በግልጽ የሚናገር ጠንካራ የእምነት ሰው ነበር። ይሁንና በቤቴል የማለዳ አምልኮ ላይ የሚያቀርበው ጸሎት ልባዊ ትሕትና እንደነበረው በግልጽ የሚያሳይ ነበር።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከፍተኛ የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀት የነበረው እስጢፋኖስ ምግብ በማከፋፈል ሥራ በትሕትና አገልግሏል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምናሴ ትሕትና ማሳየቱ ይሖዋን አስደስቶታል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳንኤልን ‘እጅግ የተወደደ’ ሰው ያደረገው ምን ነበር?