ይሖዋ ‘በመከራ ጊዜ መጠጊያችን’ ነው
ይሖዋ ‘በመከራ ጊዜ መጠጊያችን’ ነው
“የጻድቃን ድነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ በመከራ ጊዜም መጠጊያቸው እርሱ ነው።”—መዝሙር 37:39
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ስለ ደቀ መዛሙርቱ ምን ብሎ ጸልዮአል? (ለ) አምላክ ስለ ሕዝቦቹ ያለው ፈቃድ ምንድን ነው?
ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው። ታማኝ አምላኪዎቹን እርሱ በፈለገው መንገድ ለመጠበቅ የሚያስችል ኃይል አለው። ሌላው ቀርቶ ሕዝቦቹን ቃል በቃል ከቀረው ዓለም ለይቶ ስጋት በሌለበትና ሰላማዊ በሆነ አካባቢ እንዲኖሩ ማድረግ ይችላል። ይሁን እንጂ፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በሚመለከት “የምለምንህም ከክፉው እንድትጠብቃቸው እንጂ፣ ከዓለም እንድታወጣቸው አይደለም” በማለት በሰማይ ወደሚኖረው አባቱ ጸልዮአል።—ዮሐንስ 17:15
2 ይሖዋ እኛን ‘ከዓለም ለማውጣት’ አልመረጠም። ከዚህ ይልቅ ተስፋና ማጽናኛ የያዘውን መልእክት ለሰዎች እንድንሰብክ በዓለም ውስጥ ከሕዝብ ጋር ተቀላቅለን እንድንኖር ይፈልጋል። (ሮሜ 10:13-15) ኢየሱስ በጸሎቱ ላይ እንደገለጸው በዚህ ዓለም ውስጥ መኖራችን ‘ለክፉው’ እንድንጋለጥ አድርጎናል። ታዛዥ ያልሆነው የሰው ዘርና ክፉ መንፈሳዊ ኃይላት በሰዎች ላይ ይህ ነው የማይባል መከራና ሥቃይ የሚያስከትሉ ሲሆን ክርስቲያኖችም ከመከራ ነጻ አይደሉም።—1 ጴጥሮስ 5:9
3. ታማኝ የይሖዋ አምላኪዎች እንኳ ምን አይቀርላቸውም? ይሁን እንጂ በአምላክ ቃል ውስጥ ምን ማጽናኛ እናገኛለን?
3 እንዲህ ያሉ መከራዎች ሲያጋጥሙን ለጊዜውም ቢሆን ተስፋ መቁረጣችን ያለ ነገር ነው። (ምሳሌ 24:10) መጽሐፍ ቅዱስ መከራ ስላጋጠማቸው ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች የሚዘግቡ በርካታ ታሪኮች ይዟል። መዝሙራዊው “የጻድቅ መከራው ብዙ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ከሁሉም ያድነዋል” ብሏል። (መዝሙር 34:19) አዎን፣ ‘ጻድቅ’ እንኳ ክፉ ነገር ይደርስበታል። እንደ መዝሙራዊው ዳዊት ሁሉ እኛም አንዳንድ ጊዜ ‘እጅግ ልንዝልና ፈጽሞ ልንደቅቅ’ እንችላለን። (መዝሙር 38:8) ይሁን እንጂ፣ ‘ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ መሆኑንና መንፈሳቸው የተሰበረውንም እንደሚያድናቸው’ ማወቃችን የሚያጽናና ነው።—መዝሙር 34:18፤ 94:19
4, 5. (ሀ) ይሖዋ መጠጊያ እንዲሆነን ከምሳሌ 18:10 ጋር በሚስማማ መንገድ ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ልንወስዳቸው የሚገቡ ሦስት አስፈላጊ እርምጃዎች ምንድን ናቸው?
4 ኢየሱስ በጸሎቱ ላይ እንደጠቀሰው በእርግጥም ይሖዋ ይጠብቀናል። እርሱ ‘በመከራችን ጊዜ መጠጊያችን’ ነው። (መዝሙር 37:39) የምሳሌ መጽሐፍ “የእግዚአብሔር ስም ጽኑ ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ በመሮጥ ተገን ያገኝበታል” በማለት ተመሳሳይ አገላለጽ ይጠቀማል። (ምሳሌ 18:10) ይህ ጥቅስ ይሖዋ ለፍጥረታቱ በእጅጉ ያስባል የሚለውን መሠረታዊ ሐቅ ያጎላል። አምላክ፣ ከለላ ለማግኘት ወደ አንድ ጽኑ ግንብ የሚሮጡ ያህል እርሱን ተግተው ለሚፈልጉት ጻድቅ አገልጋዮቹ መጠጊያ ይሆናቸዋል።
5 አሳዛኝ ችግሮች ሲያጋጥሙን ከለላ ለማግኘት ወደ ይሖዋ መሮጥ የምንችለው እንዴት ነው? የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት መውሰድ የሚኖርብንን ሦስት ወሳኝ እርምጃዎች እስቲ እንመልከት። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ወደ ሰማዩ አባታችን መጸለይ ይገባናል። በሁለተኛ ደረጃ፣ የቅዱስ መንፈሱን አመራር መከተል አለብን። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ከችግሮቻችን እፎይታ እንድናገኝ ሊረዱን ከሚችሉ ክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር በመሰብሰብ ለይሖዋ ዝግጅት መገዛት ይገባናል።
ጸሎት ያለው ኃይል
6. እውነተኛ ክርስቲያኖች ለጸሎት ምን አመለካከት አላቸው?
6 አንዳንድ የጤና ሊቃውንት ጸሎት ጭንቀትንና ውጥረትን ለማስወገድ እንደሚረዳ ይናገራሉ። ጸሎት ማቅረብና ረጋ ብሎ ማሰላሰል የሚያጋጥመንን ውጥረት ሊቀንስልን እንደሚችለው ሁሉ በአካባቢያችን ካሉ አንዳንድ የፍጥረት ሥራዎች የምንሰማቸው ድምፆች ሌላው ቀርቶ ጀርባን መታሸት እንኳ ተመሳሳይ ውጤት ሊያስገኙ ይችላሉ። እውነተኛ ክርስቲያኖች ጸሎትን እንደ ውጥረት ማስታገሻ ብቻ በማየት አቅልለው አይመለከቱትም። ጸሎትን ከፈጣሪያችን ጋር አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ የምንገናኝበት መስመር አድርገን እንመለከተዋለን። ጸሎት ለአምላክ ያለንን ፍቅርና በእርሱ ላይ ያለንን ትምክህት ያንጸባርቃል። አዎን፣ ጸሎት የአምልኮታችን ክፍል ነው።
7. በድፍረት መጸለይ ሲባል ምን ማለት ነው? እንዲህ ያለው ጸሎት ጭንቀትን ለመቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?
7 ጸሎታችን በይሖዋ እንደምንተማመን ወይም እንደምንመካ የሚያንጸባርቅ መሆን ይኖርበታል። ሐዋርያው ዮሐንስ “በእግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ ማንኛውንም ነገር እንደ ፈቃዱ ብንለምን እርሱ ይሰማናል” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:14) እርሱ ብቻ እውነተኛና ሁሉን ቻይ እንዲሁም ከሁሉም በላይ የሆነው ይሖዋ አምላኪዎቹ የሚያቀርቡለትን ከልብ የመነጨ ጸሎት ትኩረት ሰጥቶ ያዳምጣል። ጭንቀታችንንና ችግሮቻችንን አውጥተን በምንናገርበት ጊዜ አፍቃሪ የሆነው አምላካችን እንደሚያዳምጠን ማወቃችን ብቻ እንኳ የሚያጽናና ነው።—ፊልጵስዩስ 4:6
8. ታማኝ ክርስቲያኖች በጸሎት ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ሊፈሩ ወይም ብቃቱ እንደሌላቸው ሊሰማቸው የማይገባው ለምንድን ነው?
8 ታማኝ ክርስቲያኖች በጸሎት ወደ ይሖዋ በሚቀርቡበት ጊዜ ሊፈሩ፣ ብቃት እንደሚጎድላቸው ሊሰማቸው ወይም እምነት ሊያጡ አይገባም። እርግጥ ነው፣ በራሳችን ስናዝን ወይም ችግሮች ሲፈራረቁብን ወደ ይሖዋ በጸሎት ለመቅረብ አንገፋፋ ይሆናል። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ይሖዋ ‘ለተቸገሩት እንደሚራራ’ እንዲሁም ‘ሐዘንተኞችን እንደሚያጽናና’ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። (ኢሳይያስ 49:13፤ 2 ቆሮንቶስ 7:6) እንዲያውም መጠጊያ ወደሚሆነን የሰማዩ አምላካችን ያለ አንዳች ፍርሃት መጸለይ የሚገባን እንዲህ ባለው አስጨናቂና አሳዛኝ ወቅት ላይ ነው።
9. በጸሎት ወደ ይሖዋ በመቅረብ ረገድ እምነት ምን ሚና አለው?
9 አምላክ ከሰጠን የጸሎት መብት ሙሉ ተጠቃሚ ለመሆን እውነተኛ እምነት ሊኖረን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት” በማለት ይናገራል። (ዕብራውያን 11:6) እምነት አምላክ ‘መኖሩን’ ከማመን የበለጠ ነገርን ይጠይቃል። እውነተኛ እምነት አምላክ በሕይወታችን ውስጥ ለምንከተለው የታዛዥነት ጎዳና ወሮታውን ለመመለስ ችሎታም ሆነ ፍላጎት እንዳለው ከልብ የምናምን መሆናችንን ማሳየትን ይጨምራል። “የጌታ ዐይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉና፤ ጆሮቹም ጸሎታቸውን ለመስማት የተከፈቱ ናቸው።” (1 ጴጥሮስ 3:12) ይሖዋ ከፍቅር ተነሳስቶ እንደሚያስብልን ዘወትር ማስታወሳችን ጸሎታችን ልዩ ትርጉም እንዲኖረው ያደርጋል።
10. ከይሖዋ መንፈሳዊ ድጋፍ ማግኘት የምንፈልግ ከሆነ ጸሎታችን ምን ይዘት ሊኖረው ይገባል?
10 ይሖዋ በፍጹም ልብ የምናቀርባቸውን ጸሎቶች ያዳምጣል። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልቤ እጮኻለሁና መልስልኝ” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 119:145) በበርካታ ሃይማኖቶች ውስጥ እንደሚደረጉት የጸሎት ሥነ ሥርዓቶች የምናቀርባቸው ጸሎቶች በዘልማድ የሚደገሙ ወይም በተከፋፈለ ልብ የሚቀርቡ አይደሉም። ‘በፍጹም ልብ’ ወደ ይሖዋ የምንጸልይ ከሆነ የምንናገራቸው ቃላት ትርጉምና ግብ ይኖራቸዋል። እንዲህ ያለ ልባዊ ጸሎት ካቀረብን በኋላ ‘የከበደንን ነገር በይሖዋ ላይ’ መጣል የሚያስገኘው እፎይታ ይሰማናል። መጽሐፍ ቅዱስ በሰጠን ተስፋ መሠረት ‘እርሱ ደግፎ ይይዘናል።’—መዝሙር 55:22፤ 1 ጴጥሮስ 5:6, 7
የአምላክ መንፈስ ረዳታችን ነው
11. ይሖዋ እንዲረዳን አጥብቀን ‘ከለመንነው’ መልስ የሚሰጥበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው?
11 ይሖዋ ጸሎት ሰሚ ብቻ ሳይሆን ለጸሎት መልስ የሚሰጥም አምላክ ነው። (መዝሙር 65:2) ዳዊት “አንተ ስለምትመልስልኝ፣ በመከራዬ ቀን ወደ አንተ እጣራለሁ” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 86:7) ኢየሱስም የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ‘ሳይታክቱ እንዲለምኑ’ ደቀ መዛሙርቱን አበረታቷቸዋል፤ ምክንያቱም ‘የሰማዩ አባት ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸዋል።’ (ሉቃስ 11:9-13) አዎን፣ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ረዳት ወይም አጽናኝ በመሆን ሕዝቦቹን ይደግፋቸዋል።—ዮሐንስ 14:16
12. ከአቅም በላይ የሚመስል ችግር በሚያጋጥመን ጊዜ የአምላክ መንፈስ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
12 አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም እንኳ የአምላክ መንፈስ “እጅግ ታላቅ ኀይል” ሊሰጠን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) በርካታ አስቻጋሪ ሁኔታዎች የተፈራረቁበት ሐዋርያው ጳውሎስ “ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” በማለት በልበ ሙሉነት ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 4:13) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ብዙ ክርስቲያኖች ያቀረቡት ልመና ስለተሰማላቸው መንፈሳዊና ስሜታዊ ብርታት እንዳገኙ ተሰምቷቸዋል። ብዙውን ጊዜ የአምላክን መንፈስ እርዳታ ካገኘን በኋላ ሲያስጨንቁን የነበሩ ችግሮች ያን ያህል ከባድ እንዳልሆኑ ይሰማናል። አምላክ እንዲህ ያለ ብርታት ስለሚሰጠን እኛም እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ልንል እንችላለን፦ “ከየአቅጣጫው ብንገፋም አንንኰታኰትም፤ ግራ ብንጋባም ተስፋ አንቈርጥም፤ ብንሰደድም ተጥለን አንቀርም፤ መትተው ቢጥሉንም አንጠፋም።”—2 ቆሮንቶስ 4:8, 9
13, 14. (ሀ) ይሖዋ በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ አማካኝነት መጠጊያችን መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግህ ምን ጥቅም አስገኝቶልሃል?
13 በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ፣ የአምላክ ቃል ለእኛ ጥቅም ሲባል በጽሑፍ እንዲሰፍርና እስከ ዘመናችን እንዲቆይ አድርጓል። ችግር በሚያጋጥመን ጊዜ ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት መጠጊያ የሚሆንልን እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ ጥበብና የማመዛዘን ችሎታ በመስጠት ነው። (ምሳሌ 3:21-24) መጽሐፍ ቅዱስ አእምሯችንን የሚያሰለጥንልን ከመሆኑም ሌላ የማገናዘብ ችሎታችንን ያዳብርልናል። (ሮሜ 12:1) የአምላክን ቃል ዘወትር በማንበብና በማጥናት እንዲሁም ያገኘነውን እውቀት ተግባራዊ በማድረግ ‘መልካሙንና ክፉውን ለመለየት ራሳችንን ማስለመድ’ እንችላለን። (ዕብራውያን 5:14) ችግሮች ባጋጠሙህ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ እንድታደርግ እንዴት እንደረዱህ በግልህ የተመለከትክበት ጊዜ ይኖር ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ለሚያጋጥሙን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተግባራዊ መፍትሔ እንድናገኝ የሚያስችል ማስተዋል ይሰጠናል።—ምሳሌ 1:4
14 ከዚህም በላይ የአምላክ ቃል የመዳንን ተስፋ በመስጠት የብርታት ምንጭ ይሆንልናል። (ሮሜ 15:4) መጽሐፍ ቅዱስ መጥፎ ነገሮች የሚወገዱበት ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። የሚደርሱብን መከራዎች ሁሉ ጊዜያዊ ናቸው። (2 ቆሮንቶስ 4:16-18) ‘የማይዋሸው አምላክ ከዘመናት በፊት የገባው የዘላለም ሕይወት ተስፋ’ አለን። (ቲቶ 1:2) ይሖዋ ቃል የገባልንን አስደሳች የወደፊት ጊዜ ዘወትር እያስታወስን በተስፋው ደስ የምንሰኝ ከሆነ መከራ ሲያጋጥመን መጽናት እንችላለን።—ሮሜ 12:12፤ 1 ተሰሎንቄ 1:3
ጉባኤ—የአምላክ ፍቅር መግለጫ
15. ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው መረዳዳት የሚችሉት እንዴት ነው?
15 በመከራ ወቅት የሚረዳን ሌላው የይሖዋ ዝግጅት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የምናፈራው ወዳጅነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” ይላል። (ምሳሌ 17:17) የአምላክ ቃል የጉባኤው አባላት በሙሉ እርስ በርሳቸው እንዲከባበሩና እንዲዋደዱ ያበረታታል። (ሮሜ 12:10) ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ የራሱን ብቻ አይፈልግ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 10:24) እንዲህ ያለ አመለካከት ማዳበራችን በችግሮቻችን ላይ ብቻ ከማብሰልሰል ይልቅ ሌሎች በሚያስፈልጋቸው ነገር ላይ እንድናተኩር ይረዳናል። ሌሎችን ለመርዳት ራሳችንን በፈቃደኝነት ስናቀርብ እነርሱን ከመርዳታችን ባሻገር ሸክማችን ይበልጥ እንዲቀልልን የሚያደርግ ደስታና እርካታ እናገኛለን።—የሐዋርያት ሥራ 20:35
16. እያንዳንዱ ክርስቲያን የብርታት ምንጭ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
16 በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወንዶችና ሴቶች ሌሎችን በማበርታት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ። ይህን ለማድረግ በቀላሉ የሚቀረቡና የሚገኙ ለመሆን ይጥራሉ። (2 ቆሮንቶስ 6:11-13) ሁሉም ጊዜ መድበው ወጣቶችን ሲያመሰግኑ፣ አዳዲሶችን ሲያንጹና የተጨነቁትን ሲያበረታቱ በእርግጥም ጉባኤው ይባረካል። (ሮሜ 15:7) በመካከላችን ያለው የወንድማማች ፍቅር አንዳችን ሌላውን በጥርጣሬ ዓይን እንዳንመለከትም ይረዳናል። ከአንድ ክርስቲያን ጋር በባሕርይ መጣጣም ስላልቻልን ብቻ ያ ሰው መንፈሳዊ ድክመት አለበት ብለን ለመደምደም መቸኮል አይኖርብንም። ጳውሎስ ‘የተጨነቁ ነፍሳትን አጽናኑ’ በማለት ክርስቲያኖችን ማሳሰቡ የተገባ ነው። (1 ተሰሎንቄ 5:14 NW) መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ክርስቲያኖች እንኳ አስጨናቂ ሁኔታ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ይናገራል።—የሐዋርያት ሥራ 14:15
17. እርስ በርስ ያስተሳሰረንን የክርስቲያን ወንድማማች ሰንሰለት ለማጠናከር የሚያስችሉ ምን አጋጣሚዎች አሉን?
17 ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን እርስ በርስ እንድንጽናናና እንድንበረታታ የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ይከፍቱልናል። (ዕብራውያን 10:24, 25) እንዲህ ያለውን ፍቅራዊ ቅርርብ የምናደርገው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ብቻ መሆን አይኖርበትም። ከዚህ ይልቅ የአምላክ ሕዝቦች በሌሎች ጊዜያትም ተገናኝተው የሚጫወቱባቸውን አጋጣሚዎች ለማግኘት ይጥራሉ። በመካከላችን ጠንካራ ወዳጅነት ስለተመሠረተ የተለያዩ መከራዎች ሲያጋጥሙን እርስ በርሳችን በቀላሉ እንረዳዳለን። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአካል ብልቶች መካከል መለያየት ሳይኖር፣ እርስ በርሳቸው . . . እንዲተሳሰቡ ነው። አንድ ብልት ቢሠቃይ ብልቶች ሁሉ አብረው ይሠቃያሉ፤ አንድ ብልት ቢከብር ሌሎቹም ብልቶች አብረው ደስ ይላቸዋል።”—1 ቆሮንቶስ 12:25, 26
18. በሐዘን በምንደቆስበት ጊዜ የትኛውን ስሜት መዋጋት ይኖርብናል?
18 አንዳንድ ጊዜ በሐዘን በጣም ከመደቆሳችን የተነሳ ከክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ራሳችንን ልናገል እንችላለን። የእምነት ባልንጀሮቻችን ሊሰጡን ከሚችሉት ማጽናኛና ድጋፍ ተጠቃሚ ለመሆን እንዲህ ያለውን ስሜት መዋጋት ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ወዳጅነትን የማይፈልግ ሰው የራሱን ፍላጎት ብቻ ይከተላል፤ ቅን የሆነውን ፍርድ ሁሉ ይቃወማል” በማለት ያስጠነቅቀናል። (ምሳሌ 18:1) ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አምላክ ስለ እኛ እንደሚያስብ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው። ለዚህ ፍቅራዊ ዝግጅት ቦታ የምንሰጥ ከሆነ በመከራ ጊዜ እፎይታ እናገኛለን።
ገንቢ አመለካከት ይኑራችሁ
19, 20. መጽሐፍ ቅዱስ አፍራሽ አመለካከቶችን እንድናስወግድ የሚረዳን እንዴት ነው?
19 ተስፋ አስቆራጭና አሳዛኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ አፍራሽ ሐሳቦችን ማውጠንጠን ቀላል ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች መከራ ሲያጋጥማቸው እንዲህ ያለው አስቸጋሪ ሁኔታ የደረሰባቸው አምላክ ስለተዋቸው እንደሆነ በማሰብ ጥሩ መንፈሳዊነት ያላቸው ስለመሆኑ መጠራጠር ይጀምራሉ። ይሁን እንጂ፣ ይሖዋ ማንንም “በክፉ” እንደማይፈትን አስታውሱ። (ያዕቆብ 1:13) መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ሆን ብሎ ችግርን፣ ወይም መከራን በሰው ልጆች ላይ አያመጣም” በማለት ይናገራል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:33) እንዲያውም ይሖዋ አገልጋዮቹ መከራ ሲደርስባቸው ከልብ ያዝናል።—ኢሳይያስ 63:8, 9፤ ዘካርያስ 2:8
20 ይሖዋ “የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:3) ለእኛ የሚያስብልን ከመሆኑም ባሻገር እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ ያደርገናል። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር ምንጊዜም ማስታወሳችን ገንቢ አመለካከት እንዲኖረን እንዲያውም ደስተኞች እንድንሆን ይረዳናል። ያዕቆብ “ወንድሞቼ ሆይ፤ ልዩ ልዩ መከራ ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 1:2) ለምን? “ምክንያቱም ፈተናን ሲቋቋም እግዚአብሔር ለሚወዱት የሰጠውን ተስፋ፣ የሕይወትን አክሊል ያገኛል” በማለት መልሱን ይሰጠናል።—ያዕቆብ 1:12
21. ማንኛውም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥመን አምላክ ለታማኝ አገልጋዮቹ ምን ዋስትና ሰጥቷቸዋል?
21 ኢየሱስ እንዳስጠነቀቀን በዓለም እስካለን ድረስ መከራ ያጋጥመናል። (ዮሐንስ 16:33) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ችግር ወይም ሥቃይ ወይም ስደት ወይም ረሀብ ወይም ዕራቁትነት ወይም አደጋ’ ከይሖዋና ከልጁ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል ቃል ገብቶልናል። (ሮሜ 8:35, 39) የሚያጋጥመን ማንኛውም ዓይነት መከራ ጊዜያዊ መሆኑን ማወቃችን በጣም የሚያጽናና ነው! በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው ሥቃይ የሚያከትምበትን ጊዜ ስንጠባበቅ አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ ጥበቃ ያደርግልናል። መጠጊያ ለማግኘት ወደ ይሖዋ የምንሮጥ ከሆነ ፈጽሞ አያሳፍረንም፤ እርሱ “ለተጨቈኑት ዐምባ ነው፤ በመከራም ጊዜ መጠጊያ ይሆናቸዋል።”—መዝሙር 9:9
ምን ተምረናል?
• ክርስቲያኖች በዚህ ክፉ ዓለም እስካሉ ድረስ ምን እንደሚደርስባቸው መጠበቅ ይኖርባቸዋል?
• ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ የምናቀርበው ልባዊ ጸሎት የብርታት ምንጭ ሊሆንልን የሚችለው እንዴት ነው?
• የአምላክ መንፈስ ረዳታችን የሚሆነው እንዴት ነው?
• እርስ በርሳችን ለመረዳዳት ምን ማድረግ እንችላለን?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአደጋ ጊዜ ወደ ጠንካራ ግንብ እንደምንሮጠው ሁሉ ይሖዋን መፈለግ ይኖርብናል
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመንፈሳዊ የጎለመሱ ክርስቲያኖች እያንዳንዱን አጋጣሚ ተጠቅመው ሌሎችን ያመሰግናሉ እንዲሁም ያበረታታሉ